በጳውሎስና በበርናባስ መካከል የተከሰተ አለመግባባት (የሐዋ.15፡36-41)

ካሳና አስፋው የአንዲት ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ናቸው። ካሳ ጭምትና አርቆ አስተዋይ ሲሆን፥ አስፋው ግን ተጫዋች ነበር። ሁልጊዜ የአንዱ ባሕርይ ለሌላው ይከብደዋል። ሁለቱም ቤተ ክርስቲያናቸው እንድታድግ ይፈልጋሉ። ነገር ግን ካሳ ለቤተ ክርስቲያን እጅግ አስፈላጊው ነገር ትምህርት በመሆኑ ገንዘቡ በሙሉ በዚህ ላይ እንዲውል ይፈልጋል። አስፋው ግን ብዙው የቤተ ክርስቲያኒቱ በጀት ወንጌላውያንን ለመቅጠር እንዲውል ይሻል። የሁለቱም አሳብ ስለማይስማማ በሽማግሌዎች ስብስባ ላይ ሁልጊዜ ይጋጫል። የአሳብ ግጭቱ እየከረረ በመሄዱ ሁለቱም አገልጋዮች መነጋገር አቆሙ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰዎች በግንኙነታቸውና በአገልግሎታቸው እንደነካላ ሲጣሉ ያየኸው እንዴት ነው? ለ) የተለያዩ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት በምን ምክንያቶች ሊጣሉ እንደ ተመለከትህ ግለጽ። ሐ) የሐዋ. 5፡36-41 አንብብ። ጳውሎስና በርናባስ ግንኙነታቸው እንዲደፈርስ ያደረገው ምን ነበር? መ) ከዚህ መለያየታቸው የተገኘ መልካም ነገር ነበር?

ግንኙነት ምን ጊዜም እክል አያጣውም። የተለያዩ ግለሰቦችና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሳይግባቡ ሲቀሩ ሁልጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ችግሮች ይኖራሉ። እንደ ጳውሎስና በርናባስ ያሉ ታላላቅ መንፈሳዊ መሪዎች መጣላት/መጋጨት ከቻሉ፥ ብዙዎቻችን በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ብናልፍ አያስደንቅም፡፡ በግንኙነት ጊዜ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት፥ የችግሮቹን ምንጮች ማወቅ ወሳኝ ነው። ለግንኙነት መደፍረስ ብዙ የተለያዩ ምክንያቶች ሲኖሩ፥ እያንዳንዱ ምክንያት የተለየ አመለካከትና መፍትሔ ይሻል፡፡

ሀ. ከባሕርይ ልዩነት የሚመጡ አለመግባባቶች፡- ሁልጊዜ ከሌሎች ጋር ለመግባባት የሚያስቸግር ባሕርይ ያላቸው ሰዎች አሉ። ካሳና አስፋው ከተጋጩባቸው ምክንያቶች አንዱ የተለያዩ ባሕርያት ያሏቸው መሆናቸው ነበር፡ ለዚህ ዓይነቱ ግጭት መፍትሔው እግዚአብሔር ለሁለቱም የተለያዩ ባሕርያትን እንደ ሰጠ መገንዘብ ነው። ሁለቱም በእግዚአብሔር ፊት የከበሩ ሲሆኑ ለቤተ ክርስቲያንም ያስፈልጓታል። ምንም እንኳ ካሳና አስፋው ጥሩ ጓደኛሞች ለመሆን እድላቸው የመነመነ ቢሆንም፥ አንዱ የሌላውን ጥንካሬ ካከበረና እርስ በርሳቸው ለመዋደድና ለመግባባት ከቆረጡ የተሻላ ግንኙነት ሊኖራቸው ይችላል።

ለ. ከተለያየ አመለካከት የሚመነጩ ልዩነቶች፡- ካሳና አስፋው ከተጋጩባቸው ምክንያቶች ሁለተኛው ይሄ ነው። ለቤተ ክርስቲያን የሚበጃት የትኛው ነው? በሚለው ጥያቄ ላይ ሁለቱም የተለያዩ አመለካከቶችን ይዘዋል። ትክክለኛው ማን ነው? የተሳሳተውስ? የእግዚአብሔርን ሥራ የማከናወኛ መንገዳቸው ከመለያየቱ በስተቀር፥ እገሌ ትክክል ነው ወይም ስሕተት ነው ልንል አንችልም። ጳውሎስና በርናባስ ያጋጠማቸው መሠረታዊ ችግር ይሄ ነበር። ዮሐንስ ማርቆስ ለወንጌል አገልግሎት ስኬትም ሆነ ውጤት አደገኛ በመሆኑ፥ ጳውሎስ አብሯቸው እንዲሄድ አልፈለጉም። በርናባስ ግን ዮሐንስ ማርቆስ በእምነቱ እንዲያድግ ለማበረታታት ስለፈለገ አብሯቸው እንዲሆን ፈለገ። ሁለቱም አመለካከቶች የየራሳቸው ብርቱ ጎን አላቸው። ምናልባትም ለዛሬም ዘመን ምሳሌ የሚሆነን ሸምገል ያሉ ክርስቲያኖች ጸጥታ የሰፈነበትን አምልኮ ሲፈልጉ፥ ወጣቶቹ ግን በጭብጨባ በእልልታና በሽብሸባ የደመቀ አምልኮ መሻታቸው የሚያስከትለው የአሳብ ልዩነት ሊሆን ይችላል። ለዚህ ዓይነቱ ልዩነት መፍትሔው አንዱ የሌላውን ምክንያቶች ተገንዝቦ አሳቡን ለመቀየር በትሕትናና በፍቅር መነሣሣቱ ነው።

ሐ. ኃጢአት በሆነ ጉዳይ ላይ የሚከሰቱ ልዩነቶች፡- አብዛኛውን ጊዜ ክርስቲያኖች ኃጢአት የሚሠራን ሰው ለመጋፈጥ አይፈልጉም፡፡ በባሕርይ ወይም በአመለካከት ልዩነቶች ላይ እየተጣላን ግጭቱ እንዲቀጥል እናደርጋለን። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ጉዳይ ላይ እንዳንስማማ ያሳስበናል። ጳውሎስ ከአባቱ ሚስት ጋር እያመነዘረ ስለሚኖር ክርስቲያን በሰማ ጊዜ፥ ግለሰቡ ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት እንዲወጣ አስጠንቅቆታል (1ኛ ቆሮ. 5፡1-5)። ክርስቶስ፥ ኃጢአት የሚሠራ ክርስቲያን ካጋጠመን፡ በኃጢአቱ ወቅሰን ወደ ንስሐ ለማምጣት ኃላፊነት እንዳለብን ገልጾአል (ማር. 18፡15-18)። ያዕቆብም ኃጢአት እየሠራ ያለውን ሰው ወቅሶ ወደ ንስሐ መመለስ ነፍሱን ማዳን እንደሆነ ተናግሯል (ያዕ. 5፡19-20)።

መ. በአስተምህሮ ጉዳዮች አለመስማማት፡- ሁለት ዓይነት አስተምህሮአዊ መለያየቶች አሉ። አንደኛው፥ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ባልተናገረባቸው ነገሮች ላይ የሚከሰት አለመስማማት ነው። ከዚህ አንጻር፥ ክርስቲያኖች የመጨረሻው ዘመን ስለሚፈጸምበት ሁኔታ፥ በልሳን መናገር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስለመሆኑ ወይም አለመሆኑ፥ ጥምቀት እንዴት መካሄድ እንዳለበት እና ሌሎችም የተለያዩ አሳቦች አሏቸው። በአሳብ መለያየት እንዳለ ሁሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ ባልተነገሩ አስተምህሮአዊ ልዩነቶች ፍቅርና መቻቻልን ማሳየት ይኖርብናል። ይህም የአመለካከት ልዩነቱ እንዳለ ሆኖ ክርስቲያናዊ አንድነትን እንድንጠብቅ ያስችለናል።

ነገር ግን ለእግዚአብሔር ቃል እውነት መሠረታዊ የሆኑ አስተምህሮአዊ ልዩነቶች አሉ። የሐሰት መምህራንና መናፍቃን እነዚህን መሠረታዊ እውነቶች በሚቃወሙበት ጊዜ ልንታገሣቸው አይገባም። ጴጥሮስ አሕዛብም ከአይሁድ እኩል በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የሚችሉት፥ በአይሁድ ሥርዓት ውስጥ ሲያልፉ ነው ባለ ጊዜ፥ ጳውሎስ በግልጽ ተቃውሞታል (ገላ. 2፡1-18)። የይሖዋ ምስክሮች፥ የብልጽግና ወንጌል ሰባኪዎች፥ የአዲሱ ዘመን እንቅስቃሴ አራማጆች ወይም “የኢየሱስ ብቻ” አስተማሪዎች የሐሰት ትምህርታቸውን ወደ ቤተ ክርስቲያን በሚያመጡበት ጊዜ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በመመሥረት ሊቋቋሟቸው ይገባል። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለሰዎቹ ጥላቻን ወይም ቁጣን ሳያሳዩ፥ በፍቅር አሳባቸውን ሊቋቋሙ ይገባል።

ስለሆነም፥ መለያየት በተለይም የአመለካከት ልዩነቶች በሚከሰቱበት ጊዜ፥ የሚከተሉትን ነገሮች ልናደርግ ይገባል።

  1. የአሳብ ልዩነቱ ከላይ ከተጠቀሱት አራት ነጥቦች የትኛው እንደሆነ ለይ። ልዩነቱን የምናስተናግድበት መንገድ በልዩነቱ ዓይነት ይወሰናል።
  2. ልባችንን እንመርምር፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ከሌሎች ሰዎች ጋር የምንጣላው በልባችን ውስጥ ራስ ወዳድነትና ለምን ተነካሁ ባይነት ስላለ ነው። የተጣላናቸው ስላላዳመጡን ወይም አሳባችንን ስላልተቀበሉን ሊሆን ይችላል። እነዚህ ሁለት ኃጢአቶች ለብዙ ግጭቶች መሠረት ናቸው። እነዚህን ኃጢአቶች ለይተን በማወቅ ለእግዚአብሔርና ለተቀያየምነው ሰው መናዘዝ አለብን፡
  3. በምታደርገው በማንኛውም ተግባር የክርስቶስ ስም እንዳይሰደብ ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የክርስቶስን ስም የሚያሰድብ አሳፋሪ ነገር ከመፈጸም ይልቅ ብንበደል ይሻላል (1ኛ ቆሮ. 6፡7)።
  4. ለእግዚአብሔር መንግሥት ቀዳሚ ትኩረት ስጥ (ማቴ. 6፡33)። ለራስህ፥ ለቤተሰብህ፥ ለቤተ ክርስቲያንህ ወይም ለቤተ እምነትህ የሚጠቅመውን ብቻ ሳይሆን፥ የእግዚአብሔርን መንግሥት ከሁሉም በተሻለ ሁኔታ የሚያስፋፋውን መንገድ ምረጥ።
  5. ሌሎችን ውደድ፡፡ የክርስቲያን ፍቅር፥ «ሌላውን ሰው ለማክበርና ለመደገፍ ምን ላድርግ?» ሲል ይጠይቃል። ፍቅር ግለሰቡ የሚናገረውን ብቻ ሳይሆን፥ የልቡን ስሜት ጭምር እንድንታዘብ ያስችለናል። ፍቅር ራሳችንን ዝቅ አድርገን አመለካከታችንን በመተው ለሌሎች እንድንገዛ ያደርገናል። ፍቅር ከምጠላው ግለሰብ ጋር ያለኝ ግንኙነት አካል ሲሆንና ግለሰቡም እያዳመጥሁትና እየተቀበልሁት እንደሆነ ሲረዳ፥ እርሱም እኔን ለመውደድና ለማዳመጥ አይቸገርም። ይህም በጋራ የተሻለ ውሳኔ እንድንወስን ያስችለናል። ከሁሉም በላይ ደግሞ የዚህ ዓይነቱ ስምምነት ለክርስቶስ ስም ታላቅ ምስክር ይሆናል።
  6. የእግዚአብሔርን ቃል ግልጽ አስተምህሮ አትጣስ። የእግዚአብሔር ቃል የሕይወታችን መመዘኛ ስለሆነ፥ ግልጽ ሆኖ በቀረበ ጊዜ ልንከተለው ይገባል። የእግዚአብሔር ቃል ስለ ጉዳዩ የሚናገረው አሳብ አሻሚ ትርጉም የሚሰጥ ሲሆን ግን፥ የአሳብ ልዩነቶችን በትዕግሥት ማስተናገድ አለብን።

ከጳውሎስና በርናባስ ግጭት ታሪክ ሌሎች ሁለት ጠቃሚ እውነቶችን ልንማር እንችላለን። አንደኛው፥ በሰዎች አለመግባባትም ውስጥ እንኳ እግዚአብሔር ልዑል እንደ ሆነ እንረዳለን። በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር አንዱን የወንጌል ተልእኮ ቡድን ሁለት ለማድረግ ስምምነት አለመኖሩን ተጠቅሞበታል። ታላቅ ስጦታ በነበራቸው ክርስቲያኖች የሚመሩ ሁለት የወንጌል ልዑካን ቡድኖች ከአንድ ቡድን ይልቅ ወንጌሉን በፍጥነት ለማዳረስ ችለዋል። ሁለተኛ ወዲያውኑ ግጭቱ ተወግዶ የኋላ ኋላ ዮሐንስ ማርቆስ ከጳውሎስ የቅርብ ጓደኞች መካከል አንዱ ለመሆን በቅቷል። ጳውሎስ ለሞት በተቃረበበት ሰዓት አብረውት እንዲሆኑ ፈልጎ ነበር። ከእዚህም አንዱ ጢሞቴዎስ ሲሆን፥ ሁለተኛው ደግሞ ለጳውሎስ ጠቃሚ ሆኖ የተገኘው ዮሐንስ ማርቆስ ነበር (ቆላ. 4፡10፤ 2ኛ ጢሞ. 4፡11)።

የውይይት ጥያቄ፡- የሐዋ. 15፡36-18፡22 አንብብ፡ ሀ) ይህ ክፍል ስለ መንፈስ ቅዱስ ምን ይነግረናል? ለ) ለለ ጤናማ ቤተ ክርስቲያን ምን ልንማር እንችላለን?

የሐዋ. 15፡36-18፡22 ስለ ጳውሎስ ሁለተኛ የወንጌል ጉዞ ይናገራል፤ ጊዜውም ከ 49-52 ዓም. ነበር። በአውሮፓ ታሪክ ይህ እጅግ ታላቅ የወንጌል ጉዞ ነበር። ይህ በእግዚአብሔር ዕቅድ ወንጌል ከእስያ ወደ አውሮፓ የተሻገረበት ወቅት ነበር። ለተከታዮቹ 1900 ዓመታት አውሮፓ፣ ወንጌልን ከእስልምና በመከላከልና ወደ ዓለም ሁሉ በማሰራጨት፥ የወንጌሉን አደራ ለመጠበቅ ችላለች።

በጳውሎስና በበርናባስ መካከል የተከሰተ አለመግባባት (የሐዋ.5፡36-41)

ጳውሎስና በርናባስ በአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምን ያህል ጊዜ ሲያገለግሉ እንደ ቆዩ አልተገለጸም። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ለወንጌል አገልግሎት እንዲወጡ ልባቸውን እነሣሣ። ይሁንና፥ ስለ ጉዛቸው እያቀዱ ሳለ ችግርች ተከሰቱ። በርናባስ የአክስቱ ልጅ እንደገና አብሯቸው እንዲሄድ ሲሻ፥ ጳውሎስ ግን ዮሐንስ በመጀመሪያው የወንጌል ተልእኮ ጉዞ ወቅት ተለይቷቸው ወደ ኢየሩሳሌም በመሄዱ ከልቡ አዝኖ ስለነበር የበርናባስን አሳብ ተቃወመ። ስለሆነም፥ ሁለቱ መሪዎች ሁለት ቡድኖችን መሥርተው ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች ተጓዙ። በርናባስ ዮሐንስ ማርቆስን ይዞ ወደ ቆጵሮስ ደሴት ተመለሰ። የሐዋርያት ሥራ ታሪክ ያተኮረው በጳውሎስ ላይ በመሆኑ፥ በርናባስ ከዚያ በኋላ ወዴት እንደሄደ አልተጠቀሰም። የቤተ ክርስቲያን ታሪክም ስለዚህ ጉዳይ ምንም የሚለው የለውም።

ጳውሎስ ለወንጌል አገልግሎቱ አጋር ያስፈልገዋል። ብሉይ ኪዳን እንደሚያስተምረው፥ ሁለት ሰዎች ከአንድ ሰው ይልቅ ብርቱ እንደሆኑ ይናገራል (መክ 4፡9-12)። ክርስቶስም ደቀ መዛሙርቱን ሁለት ሁለት አድርጎ እንደ ላካቸው ሁሉ (ሉቃስ 10፡1)፣ ጳውሎስ የሚያበረታታውና የሚረዳው አንድ ሰው እንደሚያስፈልገው ያውቅ ነበር። ስለሆነም ሲላስን መረጠ። ሲላስ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ስለ አሕዛብ ክርስቲያኖች ያስተላለፉአቸውን ውሳኔዎች ለአንኪያ ቤተ ክርስቲያን እንዲያብራሩ ከላከቻቸው ሰዎች አንዱ ነበር (የሐዋ. 15፡32)። ሲላስ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሰ ቢሆንም፥ ወደ እንጾኪያ ለአገልግሎት ተመልሶ መጥቶ ይሆናል ወይም ጳውሎስ ልኮ አስመጥቶት ይሆናል። ጳውሎስ ምናልባትም በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን በነቢይነት አገልግሎቱ ይከበር የነበረው ሲላስ፥ አንዳንድ የአይሁድ ክርስቲያኖች አሕዛብ በእግዚአብሔር ቤተሰብ ውስጥ ተቀባይነት ለማግኘት መጀመሪያ ወደ አይሁድነት መለወጥ እንዳለባቸው በመግለጽ ለሚያቀርቡት ትምህርት እልባት ለመስጠት እንደሚረዳው አስቦ ይሆናል። ጳውሎስና ሲላስ በመጀመሪያ የወንጌል ጉዞ የተመሠረቱትን አብያተ ክርስቲያናት በመጎብኘት የወንጌላዊ ጉዟቸውን ጀመሩ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: