የጳውሎስ አገልግሎት በገላትያ፣ በእስያ እና በፊልጵስዩስ (የሐዋ. 16፡1-40)

  1. የጳውሎስ አገልግሎት በገላትያና በእስያ (የሐዋ. 16፡1-10)

የውይይት ጥያቄ፡- ስለ ጢሞቴዎስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብበህ ስለ እርሱ የምናውቀውን ሁሉ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ፡፡ ሉቃስ፥ ጳውሎስና ሲላስ በገላትያና በእስያ ስላደረጉት ጉዞ ብዙ አልነገረንም። በዚህ ክፍል አራት ዐበይት ነገሮች ተጠቅሰዋል። አንደኛው፥ ሉቃስ በልስጥራን ጢሞቴዎስ የተባለ ወጣት ከጳውሎስ ቡድን መቀላቀሉን ገልጾአል። ምናልባት ጢሞቴዎስ ገና ታዳጊ ወጣት ሳይሆን አይቀርም። ይህም ሆኖ፥ በገላትያ አብያተ ክርስቲያናት በብርቱ ክርስቲያንነቱ ይታወቅ ነበር፡፡ የጢሞቴዎስ አባት ግሪካዊ ሲሆን፥ እናቱ ግን አይሁዳዊት ነበረች። አባቱ በሞት ተለይቶት ይሆናል ወይም ልጁ የአይሁድን ባሕል እንዲከተል አልፈለገም ይሆናል፥ ያም ሆኖ ጢሞቴዎስ አልተገረዘም ነበር። ነገር ቀን እናቱና አያቱ እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሴቶች ስለነበሩ፥ ወንጌል ወደ ገላትያ ሲመጣ አመኑ። ጢሞቴዎስ ከፊል አይሁዳዊ በመሆኑ፥ ጳውሎስ ለአይሁዶች ወንጌልን ለመስበክ መሰናክል ላለመፍጠር ሲል ገረዘው። ጳውሎስ አሕዛብ (ቲቶ) እንዳይገረዙ ቢከራከርም፥ አይሁዶች ባሕላዊ ልማዶቻቸውን እንዲያደርጉ ያበረታታቸው ነበር። ለመጪዎቹ 15 ዓመታት ጢሞቴዎስ የጳውሎስ የቅርብ ባልደረባው ነበር፡፡ ጢሞቴዎስ ወንጌልን እንዲያካፍል እንዲያስተምር ጳውሎስ አሠለጠነው። ከዚያም እንደ ወኪሉ አድርጎ ወደ ተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ይልከው ጀመር።

ጳውሎስ ከአንድ መሪ ኃላፊነት ውስጥ አንዱ ተተኪ ትውልድን ማሠልጠን እንደሆነ ተገንዝቦ ነበር። ዛሬ መንፈሳዊ ስጦታ ያላቸው ወጣቶች ወደ አገልግሎት እንዳይገቡ ከሚከላከሉ መሪዎች በተቃራኒ፥ ጳውሎስ መንፈሳዊ ስጦታ ያላቸው ወጣቶች ውጤታማ አገልግሎት እንዲሰጡ ያሠለጥን ነበር። ይህንንም የሚያደርገው አብረውት በማገልገል ከሕይወቱና ከአገልግሎቱ ጠቃሚ እውነቶችን እንዲቀስሙ በመፍቀድ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ወንጌልን ለመመስከር ከፍተኛ ብቃት ያላቸውን ወጣቶች ከቤተ ክርስቲያንህ ዘርዝር፡፡ ለ) አንተና ሌሎች መሪዎች የእነዚህን ወጣቶች የመሪነት ብቃት ለማሳደግ እንዴት ልታሳድጓቸው ትችላላችሁ? ሐ) አሁን ካሉት መሪዎች ብዙዎቹ ወደፊት የሚነሡ መሪዎችን የሚፈሩት ለምን ይመስልሃል? በዚህ ጉዳይ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ምን የሚል ይመስልሃል?

ሁለተኛው፥ ሉቃስ ጳውሎስና ሲላስ ከኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን የተላከ ደብዳቤ መስጠታቸውን ገልጾአል። በገላትያ አብያተ ክርስቲያናት ውዝግብ የሚቀሰቅሉ አይሁዶች ስለነበሩ፥ (ጳውሎስ ቀደም ሲል ለገላትያ ሰዎች የጻፈው ለዚህ ነበር)፥ ይህ በአብያተ ክርስቲያናት መካከል ለነበረው መለያየት ተግባራዊ መፍትሔ ያመጣ ነበር። ችግሩ እነዚህ አሕዛብ መገረዝና የብሉይ ኪዳንን ሕግ መጠበቅ አለባቸው የሚሉ አይሁዶችን በጳውሎስ የአገልግሎት ዘመን ሁሉ እየተከታተሉ ሰው የብሉይ ኪዳንን ሕግ በመጠበቅ እንደሚድን ሲናገሩ ቆይተዋል። ጳውሎስ፥ ለሮሜና ለቆላስይስ ሰዎች የላካቸው መልእክቶች፥ በሕግና በድነት (በደኅንነት) መካከል ያለውን ግንኙነት ለመግለጽና ድነት (ደኅንነት) በክርስቶስ በማመን ብቻ የሚገኝ መሆኑን ለክርስቲያኖች ለማስተማር፥ መፈለጉን ያመለክታሉ።

ሦስተኛው፥ ሉቃስ ጳውሎስ በትንሹ እስያ ሳይሆን፥ በአውሮፓ እንዲያገለግል መንፈስ ቅዱስ በግልጽ እንደመራው ጠቅሷል። የጳውሎስ ዕቅድ ወንጌልን በትንሹ እስያ ማሠራጨት ነበር። ጳውሎስ ኤፌሶን በምትገኝበት እስያ በኩል ለማለፍ ሲሞክር፥ መንፈስ ቅዱስ ከለከላቸው። መንፈስ ቅዱስ ጳውሎስ ከሦስተኛው የወንጌል ጉዞው በፊት በእስያ እንዲያገለግል ሳይፈቅድለት ቆይቷል። በሰሜን አቅጣማ ወደምትገኘው ሚስያ ለመሄድ ሲሞክሩ አሁንም መንፈስ ቅዱስ ከለከላቸው። በመጫረሻም፥ የትንሹ እስያ ምዕራባዊ ክፍል ወደ ሆነችው ጢሮአዳ ተጓዙ። በዚያም እግዚአብሔር አንድ ግሪካዊ የመቀዶንያ ሰው ወንጌልን እንዲሰብክ ሲጠይቅ የሚያመለክት ራእይ ለጳውሎስ አሳየው፡፡ ጳውሎስ ይህን ምልክት ከእግዚአብሔር ዘንድ ተቀብሎ ከዚህ በፊት ወዳልሄደበት የአውሮፓ አህጉር ተሻገረ።

የውይይት ጥያቄ፡- ከዚህ ገጠመኝ ስለ መንፈስ ቅዱስ አመራር ምን እንማራለን?

አራተኛው፥ ሉቃስ ወደ ቡድኑ ተቀላቀለ። በሐዋ. 16፡11 ሉቃስ ታሪኩን በመለውጥ ራሱን ከቡድኑ ጋር ያደርጋል። ነገር ግን ከትንሽ ጊዜ በኋላ ቡድኑ ከፊልጵስዩስ ሲነሣ፥ ሉቃስ ከቡድኑ በመለየት “እነርሱ” እያለ መጻፍ ይጀምራል። ምናልባትም ሉቃስ በፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለማገልገል የፈለገ ይመስላል። ሉቃስ ከዚህ በኋላ ከጳውሎስ የወንጌል ተልእኮ ቡድን ጋር የተገናኘው በሦስተኛው ጉዞ ወቅት ነው።

  1. ጳውሎስ በፊልጵስዩስ አገለገለ (የሐዋ. 16፡11-40)

ጳውሎስ ለአገልግሎቱ አመቺ ስፍራዎችንና ከተሞችን የመምረጥ ልማድ ነበረው። በመሆኑም፥ በመቄዶንያ ከማገልገል ይልቅ ወደ ውስጠኛው የፊልጵስዩስ ክፍል ዘልቆ ሄደ። ፊልጵስዩስ ብዙ ሮማውያንና አሕዛብ (ጥቂት አይሁዶች) የሚገኙባት የሮም ቅኝ ግዛት ነበረች፡፡ ፊልጵስዩስ ከመቀዶንያ አውራጃዎች በአንዱ ውስጥ ዋነኛ ከተማ ነበረች።

ብዙ አይሁዶችና አገልግሎቱን ለመጀመር የሚያስችሉ በርካታ የአይሁድ ምኩራቦች ከነበሩባቸው ሌሎች ከተሞች በተቃራኒ፥ በፊልጵስዩስ ምኩራብ ለመገንባት የሚችሉ ብዙ አይሁዶች ስላልነበሩ፥ ከከተማይቱ ደጃፍ ላይ በአነስተኛ ስፍራ ይሰበሰቡ ነበር። ጳውሎስ በዚህ አነስተኛ የስብሰባ ስፍራ ወንጌልን ሲሰብክ ልድያ የተባለች ሀብታም ነጋዴ በክርስቶስ አመነች። ልድያ አንድ አምላክ ለማምለክ ስትል ከአሕዛብ ወደ አይሁድ እምነት የመጣች ሴት ነበረች፡፡ በጳውሎስ ምስክርነት እርሷና በቤት ውስጥ የነበሩ ሰዎች አምነው ተጠመቁ በፊልጵስዩስም ቤተ ክርስቲያን ተመሠረተች።

ሉቃስ የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንዳደገች ብዙ አልነገረንም። ጳውሎስ ይህች ቤተ ክርስቲያን ከቅርብ ረዳቶቹ አንዱ እንደሆነች ገልጾአል። ለአገልግሎቱ ገንዘብ በማምጣት የቤተ ክርስቲያኒቱ ምእመናን ከአጳውሎስ ጋር ለየት ያለ ግንኙነት ነበራቸው። (ፊልጵ. 4፡14-18 አንብብ።) ሉቃስ ይህቺን ቤተ ክርስቲያን ለመትከል የተከፈለውን ዋጋ ለማመልከት ሲል፥ ስለ ጳውሎስና ሲላለ መታሰር አጽንኦት ሰጥቶ ይናገራል።

ጳውሎስና የጥንቱ ክርስቲያኖች ከከተማይቱ ደጅ መሰብሰባቸውን ቀጠሉ። አንድ ቀን ተሰብስበው በማምለክ ላይ ሳሉ፥ ከአንዲት አገልጋይ ሴት ርኩስ መንፈስ አስወጣ፡፡ በአጋንንቱ አማካይነት ሴቲቱ ጳውሎስ የድነትን (የደኅንነትን) መንገድ የሚሰብክ የእግዚአብሔር ባሪያ እንደሆነ ትመሰክር ነበር፡፡ ጳውሎስ ግን ይህንን ምስክርነት አልፈለገም ነበር። አጋንንቱ ከወጣላት በኋላ ሴቲቱ ትንቢት እየተናገረች፥ ገንዘብ መሰብሰብ ስላልቻለች ጌቶቿ ተቆጡ። ጳውሎስንና ሲላስን እየጎተቱ ወደ ከተማይቱ ባለሥልጣናት ዘንድ በመውሰድ ሕገ ወጥ ሃይማኖት በማስተማር ላይ መሆናቸውን አስረዱ። ከዚያም ጳውሎስና ሲላስ ተደብድበው በወኅኒ ተጣሉ። ነገር ግን ተስፋ በመቁረጥና የእግዚአብሔርንም ፈቃድ በመጠራጠር ፈንታ (በመቄዶንያ እንዲያገለግሉ ከጠራቸው በኋላ፥ ለምን ለእስር እንደዳረጋቸው)፥ ለእግዚአብሔር የምስጋና መዝሙሮችን በመዘመር በእርሱ ላይ ያላቸውን መተማመን ገለጹ። ዝማሬአቸውና በመሬት መንቀጥቀጥ የተገለጸው የእግዚአብሔር ኃይል፥ ይጠብቃቸው የነበረውን ወታደር በማስደነቁ በክርስቶስ አመነ። በዚህ ጊዜ ጢሞቴዎስና ሉቃስ የት እንደነበሩና እንዴት ሳይታሰሩ እንደ ቀሩ አልተገለጸም። ምናልባት ጢሞቴዎስ ገና ልጅ ሲሆን፥ ሉቃስ በምስክርነቱ ውስጥ ከፍተኛ ተሳታፊ አልነበረም ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ስደትን የምንመለከትበት መንገድ ለወንጌሉ ብርቱ የምስክርነት ኃይል የሚሆነው እንዴት ነው?

ጳውሎስና ሲላስ በአንድ ከተማ ውስጥ ብዙ አይቆዩም ነበር። ጥቂት ክርስቲያኖች ሲገኙ ጳውሎስ እነርሱን ለእግዚአብሔር አደራ ሰጥቶ፥ ወደ ሌላ አካባቢ የመሄድ ልማድ ነበረው። ጳውሎስና ሲላስ የሮሜ ዜግነት ያላቸውን ሰዎች በማሰራቸው ባለሥልጣናቱን ከገሠጹአቸው በኋላ፥ ወደ ተሰሎንቄ ሄዱ። ጢሞቴዎስ አማኞችን ለማጽናት በዚያው የቀረ ይመስላል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: