ጳውሎስ ወንጌልን በቆሮንቶስ ሰበከ (የሐዋ. 18፡1-22)

ጳውሎስ የግሪክ ግዛትና ታላቅ የትምህርት መዲና ከነበረችው ከአቴና የግሪክ የንግድ ማዕከል ወደ ነበረችው ወደ ቆሮንቶስ ተጓዘ፡፡ ቆሮንቶስ ከአቴና 80 ኪሎ ሜትር ያህል ትርቅ ነበር። ቆሮንቶስ የወደብ ከተማና ዐቢይ የንግድ ማዕከል በመሆኗ የብዙ ሕዝብ መገናኛም ስፍራ ነበረች። የከተማይቱ ታዋቂ ጣዖት «የፍቅር ጣዖት» ትባል ነበር። ለዚህች ጣዖት የሚቀርብ አምልኮ፥ ከቤተ ጣዖቱ ካህናት ጋር የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸምን ይጨምር ነበር። ከተማይቱ በዘማዊነቷ ትታወቅ ስለነበር፥ አንድ ሰው የዘማዊነት ባሕርይ ካሳየ ሰዎች «የቆሮንቶስን ሰው» ይመስላል ይሉ ነበር።

ቆሮንቶስ በጳውሎስ የወንጌል ተልእኮ ጉዞው ወቅት የአገልግሎቱ ማዕከል ሆና አገልግላለች። ጳውሎስ ከአቴና ወደ ቆሮንቶስ ሲደርስ እግዚአብሔር ጵርስቅላና አቂላ ወደሚባሉ ባልና ሚስት መራው። እነዚህ ባልና ሚስት በሮም ያደጉ አይሁዶች ሲሆኑ፥ በዚያም የንግድ ሥራ ነበራቸው። ነገር ግን በሆነ ምክንያት ገላውዲዎስ የተባለ ንጉሥ አይሁዶችን ከሮም አስውጥቷቸው ነበር። አንድ የሮም የታሪክ ጸሐፊ እንደ ዘገበው፥ በገላውዲዎስ ዘመን አይሁዶች «ክሬስተስ» በተባለ ሰው ጉዳይ ይጋጩ ነበር። ብዙ ምሑራን ይህ «ክርስቶስ» ለማለት የታሰበ ስም ነው ይላሉ። ወንጌል ወደ ሮም በደረሰ ጊዜ አይሁዶች ክርስቶስ መሢሕ ነው በሚለው ጉዳይ ላይ በአሳብ ተለያይተው ይጣሉ ጀመር። ጉዳዩ ያስቆጣው ንጉሥ፥ አይሁድ የተባሉ ሁሉ ከከተማይቱ እንዲወጡ አዘዘ። በዚህ ጊዜ ጵርስቅላና አቂላ ወደ ቆሮንቶስ ተጉዘው የድንኳን መስፋት ሥራ ጀመሩ። ጵርስቅላና አቂላ በሁለተኛና ሦስተኛው የጳውሎስ የወንጌል አገልግሎት ወቅት ጳውሎስንና ወንጌልን በከፍተኛ ደረጃ ከደገፉ ክርስቲያኖች መካከል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው። በክርስቶስ የሆኑበት ጊዜ ስላልተጠቀሰ ቀድሞውኑ ክርስቲያኖች የነበሩ ይመስላል። በኋላ ጵርስቅላና አቂላ የጳውሎስ የሦስተኛው የወንጌል ጉዞ መናገሻ ወደ ሆነችው ኤፌሶን ሄደዋል። ቤተ ክርስቲያን በቤታቸው ውስጥ ትሰባሰብ ነበር። በዚህ ውስጥ የእግዚአብሔርን አስደናቂ አሠራር ልንመለከት እንችላለን። እንደ ጳውሎስ ያሉትን የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ብቻ ሳይሆን፥ እንደ ጵርስቅላና አቂላ ያሉትን መልካም ሰዎች ለወንጌሉ መስፋፋት ተጠቅሞባቸዋል።

በአይሁድ ባሕል፥ የሃይማኖት ምሑራንን ጨምሮ አይሁዶች ሁሉ በንግድ ሥራ ተሰማርተዋል። የጳውሎስ ንግድ ድንኳን ሰፍቶ መሸጥ ስለነበር፥ ከጵርስቅላና አቂላ ጋር አብሮ በመኖር ድንኳን በመስፋቱ ሥራ ረድቷቸዋል። በትርፍ ጊዜው ጳውሎስ በተራው በምኩራብ ውስጥ ይሰርና ያስተምር ነበር። (ማስታወሻ፡ በዚህ ዘመን ሚሲዮናውያን ወይም ወንጌላውያን ወደ አገራቸው እንዳይመጡ (እንዳይገቡ) የሚከለክሉ ብዙ አገሮች አሉ። ነገር ግን ክርስቲያን ነጋዴዎች ወደ አገራቸው ገብተው እንዲሠሩ ይፈልጋሉ። እግዚአብሔር ክርስቲያኖች በእነዚህ አስቸጋሪ አገሮች ውስጥ እየሠሩ እንዲመሰክሩ መርቷቸዋል። በትርፍ ጊዜአቸው ወንጌል ይመሰክራሉ፡፡ በወንጌል መልእክተኝነት ሥራ ውስጥ እኒህ ሰዎች «ድንኳን ሰፊዎች» ይባላሉ። ይህም ጳውሎስ ራሱን እየረዳ ወንጌልን የመሰከረበትን ምሳሌ የሚያመለክት ነው። እግዚአብሔር በደርግ ዘመን እንደዚህ ዓይነት ብዙ ሰዎች በኢትዮጵያ ውስጥ አብያተ ክርስቲያናትን እንዲመሠርቱ ተጠቅሞባቸዋል። አስተማሪዎች፥ የጤና ባለሙያዎችና ነጋዴዎች በእግዚአብሔር መሪነት ወንጌል ባልደረሰባቸው አካባቢዎች በመመስከር፥ አሁን እያበቡ ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት መሥርተዋል፡፡ ወንጌልን ማስፋፋት ደመወዝ የሚከፈላቸው ወንጌላውያን ሥራ ብቻ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ከወንጌላውያኑ በተጨማሪ ሌሎች ባለሙያዎችንም ይጠቀማል። በሥራቸው ምክንያት ተንቀሳቅለው ባስቀመጣቸው ስፍራ በታማኝነት ወንጌልን እንዲመሰክሩ ያደርጋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በሙያ ዘርፋቸው ተሰማርተው እያሉ በኢትዮጵያ ወንጌል ባልደረሰበት ስፍራ ቤተ ክርስቲያን ለመትከል እግዚአብሔር የተጠቀመባቸውን ሰዎች ስም ዝርዝር፡፡ ለ) ይህ ቤተ ክርስቲያን እነዚህ የሙያ ሰዎች ወንጌሉን ስለሚመሰክሩበት ቤተ ክርስቲያን ስለሚተክሉበትና ስለሚያሳድጉበት መንገድ ሥልጠና መስጠትና ማበረታታት እንደሚያስፈልጋት ምን ያስተምረናል?

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ሲላስና ጢሞቴዎስ የፊልጵስዩስን፣ የተሰሎንቄንና የቤሪያን አብያተ ክርስቲያናትን ሲያስተምሩና ሲያንጹ ቆይተው ወደ መቄዶኒያ መጡ። (ጳውሎስ በቆሮንቶስ ሳለ በሆነ ወቅት ላይ 1ኛና 2ኛ ተሰሎንቄን በመጻፍ ስለ ጌታ ምጽአት ለነበራቸው ስጋት ምላሽ ሰጥቷል) ሲላስና ጳውሎለ ምናልባትም ከፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ይዘው ሲመጡ፥ ጳውሎስ ጊዜውን በሙሉ ለማስተማርና ለምስክርነት የሚያውልበትን ዕድል አግኝቷል። እንደ ልማዱ በመጀመሪያ የሚሰብክው ለአይሁዶች ነበር፥ ምንም እንኳ ከጣዖት አምልኮ የተመለሱ አሕዛብ ቢሰሙትም፣ አይሁዶች እንደ ቡድን ወንጌልን ላለመቀበል በመወሰናቸው ምክንያት እንደ ቀርስጶስ (የአይሁድ የምኩራብ እለቃ) ዓይነት ብዙ አይሁዶች ባያምኑም ጳውሎስ አገልግሎቱን ልባቸውን ከፍተው የሚቀበሉ ብዙ ሰዎች ወደሚገኙበት የአሕዛብ አገልግሎት ለውጧል።

አሁንም ጳውሎስ ሳይሆን አይሁዶች ሁከት ማስነሣታቸውን ሉቃስ ገልጾአል፡፡ እነዚህ አይሁዶች በመጀመሪያ ጳውሎስን ይዘው እንዲፈረድበት በጋልዮስ ፊት አቀረቡት። ጋልዮስ አሳባቸውን ካለመቀበሉም በላይ፣ አይሁዶች ለሚያስነሱት ውዝግብ እንደሚጠየቁ አስጠነቀቃቸው። ከክፍሉ እንደሚታየው፥ አሕዛብ ከአይሁድ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት የነበራቸው ይላላል። አይሁዶች ከፍርድ ቤቱ መጥተው እንደሄዱ ከአሕዛብ ሶስቱንላ የተባለውን አዲስ የምኩራብ አለቃ ይዘው ደበደቡ፡ (ሶስቴንስ በኋላ ክርስቲያን የሆነ ይመስላል [1ኛ ቆሮ. 1፡1]

ጳውሎስ በቆሮንቶስ ለአንድ ዓመት ተኩል ካገለገለ በኋላ፥ ወደ አንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን በመመለስ እግዚአብሔር የሠራውን ለመመስከር ፈለገ፡፡ ጳውሎስ ከጵርስቅላና አቂላ ጋር በመርከብ ተጉዞ ከኤፈሶን ወደብ ደረሰ እዚያም ወደ ምኩራብ ገብቶ ስለ ክርስቶስ መሰከረ። እዚያ እንዲቆዩ ቢፈልጉም፥ እርሱ ግን ወደ ኢየሩሳሌምና አንጾኪያ ለመድረስ ቸኩሎ ነበር፡፡ ስለሆነም፥ ተመልሶ እንደሚመጣ ነገራቸው። ጵርስቅላና አቂላ በኤፌሶን ሲቀሩ፥ ጳውሎስ ወደ ቂሣርያ ተጓዘ፡፡ ከዚያም ወደ ኢየሩሳሌም ከደረሰ በኋላ በስተ ሰሜን አቅጣጫ ወደምትገኘው ወደ አንጾኪያ ሄደ።

የውይይት ጥያቄ፡- ከዚህ የጳውሎስ የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ስለ ወንጌላዊ ሥራው ጥሪው፥ የአገልግሎት ዘዴው፥ ወንጌልን ለማካፈል ስለሚከፈል ዋጋ ምን እንማራለን?

ጳውሎስ ሌሎች ወንጌላውያን ሊከተሉት የሚገባ፥ ምሳሌ ወንጌላዊ (ሚሲዮናዊ) ነው። ከእርሱ አገልግሎት ብዙ ትምህርቶችን ልናገኝ እንችላለን።

ሀ. ለመንፈስ ቅዱስ አመራር መንቃት፡- የወንጌል መስኮች ሁሉ በአንድ ጊዜ ዝግጁ አይሆኑም። በሁለተኛው የወንጌል አገልሎቱ ወቅት እግዚአብሔር ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን እንዲሄድ አልፈለገም። በሶስተኛው የወንጌል ጉዞው ወቅት ግን ኤፌሶን ዋና የአገልግሎት ቦታ ትሆን ነበር። ወዴት መሄድ፥ ከማን ጋር መነጋገርና መሥራት እንዳለብን ሊያሳየን የሚገባው መንፈስ ቅዱስ ነው።

ለ. የስደትን ዋጋ ለመክፈል መዘጋጀት፡- የሰይጣንን መንግሥት በማፈራረስ ላይ የሚገኝ ወንጌላዊ፥ ነገሮች አልጋ በአልጋ ይሆኑልኛል ብሎ መጠበቅ የለበትም። ሰይጣን በመቶዎችና በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የነገሠበትን ስፍራ ያለ ተቃውሞ ለመልቀቅ አይፈልግም። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ወንጌሉን በሰበከባቸው ስፍራዎች ሁሉ ስደትን እንደ ተቋቋመ ሁሉ፥ ሌሎች ወንጌላውያንም በዚህ መስመር ያልፋሉ፡፡ እግዚአብሔር ከፈቀደ መከራ ለመቀበልና ለመሞት መዘጋጀት አለባቸው። ይህ ግን ግልጽ የመንፈስ ቅዱስ ምሪትን ይጠይቃል። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር አገልጋዮቹ ከስደት እንዲተርፉ ሲያደርግ፥ በሌሎች ጊዜያት አገልጋዮቹ በስደት ውስጥ እንዲያልፉ ይፈቅዳል። ምን፥ የት ስፍራ መደረግ እንዳለበት የሚወስነው የመከሩ ጌታ የሆነው እግዚአብሔር ነው፣ ሁልጊዜ የሚሠራ አንድ ዓይነት ቀመር የለም።

ሐ. አመቺ ማዕከሎችን መምረጥ፡- የጥንቷን ዓለም ካርታ ብናጠና፥ ጳውሎስ ሁልጊዜ ከተሞችን እያለፈ ሲሄድ እንመለከታለን። ከተሞችን የሚመርጠው ለምንድን ነው? በእርግጠኝነት ለመናገር ባንችልም። ጳውሎስ ለወንጌል ስብከት አመቺ ማዕከሎችን የሚመርጥ ይመስላል። ጳውሎስ እንደ ኤፈሶን፥ ፊልጵስዩስ፥ አንጾኪያ፥ ጵስዲያ፥ አቴናና ቆርንቶስ የመሳሰሉትን የጥንቱ ዓለም ቁልፍ ከተሞች መርጧል። ወንጌሉ በእንደዚህ ዓይነት ከተሞች ሥር ከሰደደ በቀላሉ ወደ ሌሎች የአካባቢው አገሮችና ባላገሮች ሊሰራጭ ይችላል በሚል እምነት ይሆናል።

መ. ጳውሎስ በአንድ አካባቢ ብዙ ጊዜ አልቆየም፡- የእርሱ ዓላማ ቤተ ክርስቲያን መመሥረት፥ ማስተማርና ማጽናት፥ ከዚያም መሪዎችን መምረጥ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ቤተ ክርስቲያኒቱን በተመረጡት መሪዎች አማካይነት ለሚሠራው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል ያስረክባል። ይህን ካደረገ በኋላ አልፎ አልፎ በመጎብኘት፥ ደብዳቤዎችን በመጻፍና እንደ ጢሞቴዎስ ያሉትን ሰዎች በመላክ ችግሮቻቸውን እንዲያቃልሉ ያደርጋል። እርሱ ግን እዚያ አይቆይም፡፡ አዳዲስ ክርስቲያኖች በእርሱ ላይ እንዲደገፉ፥ ለሁሉም ችግሮች ምላሽ እንዳለውና ኃይልን ሁሉ እንደ ያዘ አምላክ አድርገው እንዲመለከቱት ላይሆን፣ መንፈስ ቅዱስ ላይ መደገፍን እንዲማሩ ይፈልግ ነበር። ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ ሃያል እንደሆነና ለአዲሶቹ ክርስቲያን መሪዎች አመራሩን እንደሚሰጣቸው በማመን ወደ ቀጣዩ አገር ይሄድ ነበር። ወንጌላውያን መማር ከሚገባቸው ነገሮች ውስጥ አንዱ መቼ ወደፊት መቀጠል እንዳለባቸው ነው፡፡ በአንድ አካባቢ ለረዥም ጊዜ ከቆዩ ሕዝቡ በወንጌላውያኑ ላይ ስለሚደገፍ (ጥገኛ ስለሚሆን) አያድግም። ወንጌላውያን እንደ ጳውሎስ ለክርስቶስ ለመመስከር ግልጽ ግንዛቤ ከመያዛቸው ባሻገር፥ የአጥቢያ አማኞች በአጭር ጊዜ ውስጥ የአመራር፥ የምስክርነት፥ የማስተማርና ቤተ ክርስቲያኒቱን የማንቀሳቀስ ኃላፊነት እንዲረከቡ ማሠልጠን አለባቸው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: