የጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ፣ ለአይሁድ ባሕል ያለውን አክብሮት ማሳየት እና መታሰር (የሐዋ. 21፡1-39)

  1. ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ (የሐዋ. 21፡1-16)።

ጳውሎስ ቀስ ብሎ ወደ ኢየሩሳሌም መጓዙን ቀጠለ። እግዚአብሔርም በኢየሩሳሌም ስለሚጠብቀው ነገር ማስጠንቀቁን ቀጠለ።

ሀ. በጢሮስ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ፡- ጳውሎስና ባልደረቦቹ የሚጓዙበት ጀልባ በጢሮስ ለአያሌ ቀናት ቆማ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስና ሌሎችም ደቀ መዛሙርቱን ለማግኘት ሄደው በዚያ ሰባት ቀናት ተቀመጡ። መንፈስ ቅዱስ በኢየሩሳሉም በጳውሎስ ላይ ስለሚደርስበት ነገር አስቀድሞ መልእክት ለደቀ መዛሙርቱ ተናገረ፡፡ ምንም እንኳ መንፈስ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ የመራው ቢሆንም፣ (የሐዋ 20፡22)፥ እነዚህ ክርስቲያኖች የመንፈስ ቅዱስን ማስጠንቀቂያ በትክክል ስላልተረዱ፥ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ጎተጎቱት። ይህ እኛም ሁልጊዜ የመንፈስ ቅዱስን አመራር እንለያለን ብለን ግትሮች እንዳንሆን ሊያስጠነቅቀን ይገባል። ጳውሎስ፣ መንፈስ ቅዱስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲሄድ የሚፈልግ መሆኑን ሲያምን ሌሎች ክርስቲያኖች ግን ወደዚያ እንዳይሄድ የሚያስጠነቅቀው መሰላቸው፡፡

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) መንፈስ ቅዱስ፥ ሰዎች ወይም ቤተ ክርስቲያን ምን እንዲያደርጉ እንደሚፈልግ የአሳብ ልዩነት በሚከሰትበት ጊዜ ምን ሲፈጸም እንደ ተመለከትህ ግለጽ ለ) ስለ አመራር ምን እንማራለን? ሙሉ በሙሉ እርግጠኞች ልንሆን የምንችለውና የእግዚአብሔር አመራር አሻሚ ፍች እንዳለው በትሕትና ተቀብለን በእግዚአብሔር ሉዓላዊነት የምንተማመነው መቼ ነው?

ለ. በቂሣርያ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ:- ጳውሎስና ባልደረቦቹ በመርከብ ወደ ቂሣርያ ሄዱ፡፡ ወንጌላዊው ፊልጶስና ትንቢት የመናገር ስጦታ የነበራቸው ሴት ልጆቹ በዚያ ስለነበሩ፥ ጳውሎስ እነርሱ ዘንድ አረፈ። ይህም የትንቢት ስጦታ በወንዶች ብቻ አለመወሰኑን ያሳያል። እዚያ ሳሉ አጋቦስ የተባለ ነቢይ ከይሁዳ መጣ። አጋቦስ ለብዙ ዓመት እውቅ ነቢይ ሆኖ ያገለገለ ይመስላል። ቀደም ሲል ድርቅ እንደሚመጣ ተንብዮ ነበር (የሐዋ. 11፡27-30)። ይህ ነቢይ በትዕይንት መልክ ጳውሎስ በኢየሩሳሌም እንደሚታሰር አመለከተ። ከዚያም ሌሎች ክርስቲያኖች ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይሄድ ለመከላከል መሞከራቸው አስገራሚ ነው።

ሐ. ጳውሎስ ኢየሩሳሌም ደረሰ በዚያም ምናሶን በሚባል ከቆጵሮስ ከመጣው አይሁዳዊ ቤት ተቀመጠ፡፡

  1. ጳውሎስ ለአይሁዶችና ለባሕላቸው የነበረውን አክብሮት አሳየ ሐዋ. 21፡17-26)

የውይይት ጥያቄ:- 1ኛ ቆር. 9፡19-23 አንብብ። ሀ) ጳውሎስ በሐዋ. 21፡17-26 ይህንን መርሕ ያሳየው እንዴት ነው? ለ) ይህ መርሕ ዛሬ ተግባራዊ የሚሆንባቸውን መንገዶች ዘርዝር። በሕይወትህ ይህን መርሕ ያሳየህበትን መንገድ በምሳሌ ግለጽ።

ለብዙ ወራት ጳውሎስ በአይሁዶች የበዓለ ኀምሳ በዓል ላይ ለመገኘት ሲጥር ታይቷል (የሐዋ. 20፡16)። በመጨረሻም፥ ከጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በስፍራው ደረሰ። የክርስቶስ ወንድምና የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ የቤተ ክርስቲያን መሪ ከነበረው ከያዕቆብና ከሌሎችም የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች ጋር በመገናኘት፥ እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ስላከናወነው ተግባር ሪፖርት አደረገ።

እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል በሚያከናውነው ተግባር ደስ ቢሰኙም እንኳ፥ እነዚህ ሽማግሌዎች አንድ ስጋት ነበራቸው። ይኽውም ጳውሎስ በኢየሩሳሌም ሰዎች ዘንድ የአይሁድና የሙሴ ሕግ ጠላት ተደርጎ ይቆጠር ነበር። በሐዋርያት ሥራ 15 ላይ አሕዛብ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ምን ማድረግ አለባቸው? በሚለው ጉዳይ ላይ ቀደም ሲል ቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ተቀምጣ የመከረች ሲሆን፥ አሁን ደግሞ ጳውሎስ ከዚያ ርቆ በመሄድ ለአይሁድ የሙሴን ሕግ መጠበቅ አስፈላጊ አይደለም በማለት እያስተማረ ነው የሚል ግምት ነበራቸው። ስለሆነም፥ ክርስቲያኖችም ክርስቲያኖችም ያልሆኑ በሺህ የሚቆጠሩና በዓሉን በኢየሩሳሌም ለማክበር የተሰበሰቡ የአይሁድ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች፥ ክርስቲያኖች የአይሁድ ባሕሎቻቸውንና የብሉይ ኪዳን ሕግ መጠበቃቸውን የግድ መተው እንደሌለባቸው ለማሳየት ፈለጉ፡፡

የናዝራዊ ስለት የተሳሉ አራት አይሁድ ክርስቲያኖች አሉ (ዘኁል. 6፡2-12)። ይሁንና በሥርዓቱ መሠረት አልነጹም። የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን መሪዎች፥ ጳውሎስ ለአይሁድ የብሉይ ኪዳን ደንቦች ያለውን ድጋፍ እንዲያሳይ ከእነዚህ አራት ሰዎች ጋር የመንጻት ሥርዓት እንዲፈጽም ጠየቁት። ይህ ውጫዊ የብሉይ ኪዳን ልማዶችን ማክበር ጳውሎስ የአይሁዶችን የብሉይ ኪዳን ልማዶች መቀጠል እንደማይቃወም በግልጽ ያሳይ ነበር፡፡ ጳውሎስ ከተለያዩ ቡድኖች ጋር ራሱን ለማስማማት የሚሞክር አገልጋይ ከመሆኑም በላይ፥ ይህ የአሕዛብ ደኅንነት ጉዳይ ባለመሆኑ ፈቃደኛነቱን ገለጸ። ከአማኞች ጋር መስማማቱንና ወንጌልን ማስፋፋቱ ለጳውሎስ ከሕይወቱና በፈለገበት መንገድ ለማምለክ ከመቻሉ በላይ ነበር (1ኛ ቆሮ. 9፡19-23)።

  1. ጳውሎስ ታሰረ የሐዋ. 21፡27-39)

በሰባተኛው ቀን መጨረሻ ላይ ጳውሎስና አራቱ ሰዎች የመንጻት ሥርዓቱን ለማሟላት ወደ ቤተ መቅደስ ሄዱ። በቤተ መቅደስ ውስጥ የተለያዩ ክፍሎች ነበሩ። የውስጠኛው ክፍል የካህናት፥ ቀጣዩ የወንዶች፣ ከዚያም የሴቴቶሽ የመጫረሻው ደሞ የአሕዛብ አደባባይ ነበር። አሕዛብ ለእነርሱ ከተወሰነው ክልል ለማለፍ መብት አልነበራቸውም። ከአሕዛብ ወደ ሴቶች አደባባይ በሚያስገባው በር ላይ አሕዛብ ወደዚያ ቢገቡ የሞት ፍርድ እንደሚጠብቃቸው የሚያስጠነቅቅ ጽሑፍ ነበር። የእስያ አይሁዶች ጳውሎስን በወንዶች አደባባይ ውስጥ ሊመለክቱ፥ አሕዛብን ወደዚያው ይዟቸው የገባ መሰላቸው። እነዚህ ሰዎች ጳውሎስን የሙሴን ሕግ እንዲተዉ ሰዎችን እንደሚያስተምርና አሕዛብን ወደ ቤተ መቅደሱ እንዳስገባ በሚናገሩበት ወቅት ብጥብጥ ተፈጠረ። ጳውሎስን ከቤተ መቅደሱ አስወጥተው ሊወግሩት በሚወስዱበት ጊዜ የሮም ወታደሮች ደርሰው አስጣሉት። ቀደም ሲል ብዙ አይሁዶች በሮም መንግሥት ላይ እንዲያምጹ ያደረገ ግብጻዊ አይሁድ ነው ብለው ስላሰቡ ወደ እስር ቤት ወሰዱት።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: