- ጳውሎስ፥ ፊሊክስ በተባለ የሮም ባለሥልጣን ፊት ተመረመረ (የሐዋ. 24)።
የአይሁድ መሪዎች ጉዳያቸውን በፊሊክስ ፊት ያቀርብ ዘንድ ጠርጠሉስ የተባለ ጠበቃ ቀጠሩ፡፡ ስሙ እንደሚያመለክተው፥ ይህ ጠበቃ ሮማዊ ነበር። ወይም ደግሞ በሮም አድርጎ በሮማውያን ስም የሚጠራ አይሁዳዊ ሊሆን ይችላል። ጠርጠሉስ ጳውሎስ የናዝራውያን (የክርስቲያኖች) ወገን መሪ ሆኖ በሮም ግዛት ሁሉ ሁከትን እንደ ፈጠረና ቤተ መቅደሱን እንዳረከሰ በመግለጽ ይክስሰው ጀመር፡፡ (ምናልባትም በሮም ለቄሣር የቀረበው ክስ ይሄ ሳይሆን አይቀርም፡፡) ጳውሎስ ሁከትን እንዳላስነሣና የአይሁድን ሕግና ቤተ መቅደስ እንዳላረከሰ በመግለጽ ከክሱ ነፃ መሆኑን አስረዳ። ይህም ሆኖ፥ የ «መንገዱ» እምነት ተከታይ መሆኑን አልካደም። ክርስትና የአይሁድ ዓማፂ ወገን ሳይሆን፥ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን የሰጠው የተስፋ ቃል ፍጻሜ እንደሆነ አብራራ። ሁከትን በተመለከተ፣ በቅርቡ በኢየሩሳሌም የተከሰተው ሁኔታ እንደሚያመላክተው፥ ሁከት የሚፈጥሩት ክርስቲያኖች ወይም ጳውሎስ ሳይሆን አይሁዶች ነበሩ።
ምንም እንኳ ፊሊክስ ክርስቲያኖች ለሮም መንግሥት አስጊ እንዳልሆኑ ቢያውቅም፥ አይሁድ መሪዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ አልደፈረም። ስለሆነም፥ ምንም ነገር አላደረገም። ጳውሎስ ወደ እስር ቤት እንዲመለስ ካደረገ በኋላ በድብቅ ለእርሱና አይሁዳዊ ለነበረች ሚስቱ ስለ ክርስቶስ እንዲመሰክርላቸው ጠየቀው። ጳውሎስ ወንጌልን በመስበክ ስለ መጭው የእግዚአብሔር ፍርድ ሲናገር፥ ፊሊክስ ሊሰማው አልወደደም፡፡
ለሁለት ዓመት ፊሊክስ ጳውሎስን እስር ቤት አኖረው። ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ችሎት ፊት የቀረበ አይመስልም፡፡ ዛሬ እንደምታዩዋቸው ብዙ የመንግሥት መሪዎች፥ ፊሊክስ ለፍትሕ ጉቦ ፈለገ። በእነዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ጳውሎስ ለመስበክ ባለመቻሉ አንዳንድ ሰዎች ጊዜ ባክኖበታል ብለው ያስባሉ። እግዚአብሔር ጳውሎስ ያንን ሁሉ ጊዜ ከእስር ቤት እንዲያሳልፍ የፈቀደው ለምንድን ነው? መልሱን አናውቅም፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ጊዜ አያባክንም። እግዚአብሔር ልዑል በመሆኑ ምናልባትም እስከ ዘላለሙ ለማስተዋል የማንችላቸው ስውር ዓላማዎች አሉት። እግዚአብሔር አንዳንድ ጠቃሚ ነገሮችን በማስተማር በጳውሎስ ሕይወት እየሠራ ነበር። ሉቃስ ወንጌሉን የጻፈው በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። አንዳንድ ምሑራን ጳውሎስ የኤፈሶንን፥ የፊልጵስዩስንና የቆላስይስን መልእክቶቹን የጻፈው በዚህ ጊዜ እንደነበር ያስባሉ። (አብዛኞቹ ምሑራን ግን እነዚህ መልእክቶች በሮም እንደ ተጻፉ ያስባሉ።)
የውይይት ጥያቄ:-እግዚአብሔር ሰዎች እንደ ባከነ ጊዜ ወይም እንደ ጉዳት የቆጠሩትን ነገር እንዴት ለክብሩ ሊጠቀም እንደ ተመለከትህ ግለጽ።
- ጳውሎስ በፊስጦስ ፊት ቀረበ (የሐዋ. 25፡1-12)።
ተከታዩ የሮም ባለሥልጣን ፊስጦስ ነበር። ገና ሥልጣን ከመጨበጡ የአይሁድ መሪዎች የጳውሎስን ክስ ይዘው ቀረቡ። ጳውሎስ ሁከትን እንዳላስነሣና የአይሁድን ሕግና ቤተ መቅደስ እንዳላረከሰ በመግለጽ ከክሱ ነፃ መሆኑን አስረዳ። በተጨማሪም፥ ጳውሎስ ለፊስጦስና ለሮም መንግሥት አስጊ ሰው አለመሆኑን አብራራ። ጳውሎስ በመንገድ ላይ እንደሚገድሉት ወይም ፍትሕ እንዳያገኝ ያደርጋሉ ብሎ ስላሰበ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ አልፈለገም። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ የሮም ባለሥልጣን የአይሁድ መሪዎችን ስለሚፈራ ፍትሐዊ ምርመራ እንደማይደረግለት ተገንዝቦ ነበር። ስለሆነም፥ የሮም ዜግነቱን ለመጠቀም ወሰነ። ማንም የሮም ዜግነት ያለው ሰው ጉዳዩ በሮም ከፍተኛ ችሎት የመዳኘት መብት ስለነበረው ጳውሎስ ለቄሣር ይግባኝ ጠየቀ። ጉዳዩ ፊስጦስን እፎይ ሲያሰኝ፥ አይሁዶችን እንዳስቆጣ ጥርጥር የለውም። በዚህ ጊዜ ክሱ አይሁዶችን ከሚፈሩትና በጣም አስቸጋሪ በሆነው አውራጃ ሰላምን ለማስፈን ከሚፍጨረጨሩት የአካባቢው ባለሥልጣናት እጅ ወጥቶ ነበር። ፊስጦስ ጳውሎስን ወደ ሮም ለመስደድ ተገደደ። ሉቃስ ለሮም ባለሥልጣናት ጳውሎስ ወደ ሮም የሄደው በይሁዳ ከነበሩት ወኪሎቻቸው ፍትሕን ስላላገኘ መሆኑን እያመለከተ ነበር።
- ጳውሎስ በንጉሥ አግሪጳ ፊት ቀረበ የሐዋ. 25፡13-26፡32)
ንጉሥ አግሪጳ ዳግማዊ፣ ፊስጦስ የይሁዳ ገዥ ሆኖ በመሾሙ እንኳን ደስ አለህ ሊለው መጥቶ ነበር። በዚህ ጊዜ እርሱ የገሊላና የቤሪያ አካባቢ ገዥ ነበር፡፡ በተጨማሪም በኢየሩሳሌም ሊቀ ካህናትን የመሾም ሥልጣን ተሰጥቶት ነበር፡፡ በ 66 ዓም አይሁዶች በሮም መንግሥት ላይ እንዳያምጹ ለማድረግ ቢሞክርም አልተሳካለትም። በዐመጹ ጊዜ ከአይሁዶች ይልቅ ለሮማውያን ነበር የወገነው።
ንጉሥ አግሪጳ ዳግማዊ የፍልስጥኤም ጉዳይ ሊቅ በመሆኑ፥ ፊስጦስ የጳውሎስን ክስ ሊያዋየው ፈለገ፡፡ ፊስጦስ አይሁዶች ጳውሎስን የጠሉት በፖለቲካዊ ጉዳይ ሳይሆን ስለ ክርስቶስ በተነሣው ክርክር እንደሆነ ለመገንዘብ ችሎ ነበር፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ጥላቻ ለምን ከነገረ መለኮታዊ ክርክር ሊመነጭ እንደ ቻለ ለመረዳት ባለመቻሉ፥ ፊስጦስ ንጉሥ አግሪጳ ችግሮቹን እንዲያብራራለትና ስለ ጳውሎስ ለሮም ባለሥልጣናት ምን እንደሚጽፍ እንዲመክረው ጠየቀው።
ለንጉሥ አግሪጳ ባቀረበው መከላከያ ጳውሎስ የሕይወት ታሪኩን ብቻ ነበር የተረከለት። በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ትኩረት ያደረገው ከክርስቶስ ጋር ከመገናኘቱ በፊት በነበረው ሕይወቱና እግዚአብሔር እንዴት እንደ ለወጠው ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ፈሪሳዊና የብሉይ ኪዳንን ሕግ ለመከተል የሚፈልግ ሰው እንደነበር ገለጸ። በክርስቲያኖች ላይ ስለወሰዳቸው ጠንካራ እርምጃ ዎችም ገልጿል፡፡ ነገር ግን ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር በደማስቆ መንገድ ሲገናኝ ነገሮች ከመቅጽበት ተለመጡ። ጳውሎስ እግዚአብሔር መንፈሳዊ ዓይኖቻቸውን ለመክፈት ወደ አይሁዶችና አሕዛብ እንዴት እንደ ላከው አብራራ። መልእክቱም ዐመፅ ሳይሆን፥ የኃጢአት ኑዛዜ፥ ይቅርታና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት ነበር። “አንድ ሰው እግዚአብሔር በዚህ ዓይነት ሲጠራው ምን ሊያደርግ ይችላል?” ሲል ጠየቀ፡፡ ሊያደርግ የሚችለው ነገር ቢኖር እግዚአብሔርን በመታዘዝ በዓለም ሁሉ ወንጌልን መመስከር ነበር። የአይሁድ መሪዎች ሊገድሉት የፈለጉት እግዚአብሔርን ስለ ታዘዘ ነበር።
ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ከብሉይ ኪዳን ስለ ክርስቶስ ያብራራ ጀመር። ይህም አግሪጳ የሚያውቀው ነገር ነበር። ነገር ግን ይህ ለፊስጦስ ከባድ አሳብ ስለነበር ጳውልስ ያበደ መሰለው። ጳውሎስ የመከላከያ አሳቡን ያቀረበው ግን ብሉይ ኪዳንን ለሚያውቀው አግሪጳ ነበር። የሚያሳዝነው አግሪጳ በክርስቶስ ለማመን ፈቃደኛ አልነበረም።
ለሉቃስ አለፈላጊው ነገር አግሪጳ ስለ ጳውሎስ የነበረው አስተያየት ነበርና አይሁዶች በጳውሎስ ላይ የመሠረቱት ክስ ባዶ ነበር። ለጳውሎስ መገደል ቀርቶ ለመታሰርም እንኳ በቂ መሠረት ያለው ክስ ሊያቀርቡበት አልቻሉ፡፡ የሮም ወዳጅና የአይሁድን ሁኔታ ከሁሉም በተሻለ መልኩ የሚያውቀው አግሪጳ፥ የጳውሎስን ንጽሕና መስክሮ፥ ሮማውያን እንደ ስጋት ላይቆጥሩ በነፃ ሊያሰናብቱት ይገባ ነበር።
የውይይት ጥያቄ:- ሀ) እግዚአብሔር፥ ጳውሎስ ወደ ሮም እንደሚሄድ ተናገር ነበር (የሐዋ. 23፡11)። እግዚአብሔር ጳውሎስን ወደ ሮም ለመውሰድ ለምን ይህንን መንገድ የተጠቀመ ይመስልሃል? ለ) ጳውሎስ እስረኛ በመሆኑ ብቻ ወንጌልን ሊሰሙ የቻሉትን ሰዎች ዘርዝር፡፡ ሐ) ይህ እግዚአብሔር ጳውሎስ በእስር ቤት ረዥም ዓመታት እንዲያሳልፍ ስላደረገባቸው ምክንያቶች ምን ፍንጭ ይሰጣል?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)