- ጳውሎስ ለአይሁዶች ንግግር አደረገ (ሐዋ. 21፡40-22፡29)።
ጳውሎስ ለሕዝቡ ለመናገር ጠይቆ ከተፈቀደለት በኋላ፥ የአይሁድ ቋንቋ በሆነው በአረማይስጥ ቋንቋ መናገሩን ቀጠለ። ለአይሁዶች ሲናገር፥ ከክርስቶስ በፊት ምን ዓይነት ሰው እንደነበረ ገለጸላቸው። በዘመኑ እጅግ ታላቅ ሰው በሆነው በገማልያል እግር ሥር የተማረና ለሃይማኖቱ ቀናዒ የሆነ አይሁዳዊ እንደነበረ ገለጸ። ልክ እንደ እነርሱ የመንገዱን ተከታዮች ጠልቶ እያሳደደ ይገድላቸው ነበር። ከዚያ በኋላ እንዴት ተለወጠ? ከናዝሬቱ ኢየሱስ ጋር በመገናኘቱ ነበር የተለወጠው፡፡ ለዚህ ምስክሩ ማን ነበር? ሐናንያ የተባለና ምናልባትም በቤተ መቅደሱ ውስጥ ከነበሩት አይሁዶች አንዳንዶቹ የሚያውቁት ፈሪሃ እግዚአብሔር ያደረበት አይሁዳዊ ነበር። ጳውሎስ እግዚአብሔር ከድነቱ (ከደኅንነቱ) በኋላ ስለነገረው ሌላ ራእይ በመግለጽ ንገሩን ቋጨ።
ጳውሎስ ስለ አሕዛብ መናገር ሲጀምር አይሁዶች በቁጣ ገነፈሉ፡፡ «እንዴት እግዚአብሔር እኛን ትቶ አንድን አገልጋይ ወደ አሕዛብ ይልከዋል? አሕዛብ እንዴት እንደ ምርጥ የእስራኤል ሕዝብ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ሊያገኙ ይችላሉ?» ሲሉ አሰቡ፡፡ አይሁዶች በጣም ስለተበሳጩ የሮም ወታደረች ባሉበት ጳውሎስን ለመግደል ሞክሩ።
የርም ሻለቃ የአረማይስጥ ቋንቋ ስለማያውቅ አይሁዶች ለምን እንደ ተቆጡ አልገባውም ነበር። በተለመደው የሮማውያን ስልት ጳውሎስን ለመግረፍና እውነቱን ለማውጣት ወሰነ። ጳውሎስ ግን የሮም ዜግነቱን በመጠቀም ከመገረፍ ዳነ። ያን ጊዜ የሮም ዜግነት እንደ ዛሬው የአሜሪካ ዜነት ይፈለግ ነበር፡፡ (ብዙ ሰዎች ለዲቪ ሉተሪ ይወዳደራሉ) ሻለቃው የሮምን ዜግነት ያገኘው በገንዘብ ገዝቶ ነበር፡፡ ጳውሎስ ግን የሮም ዜጋ ሆኖ ነበር የተወለደው። ይህም የጳውሎስ ወላጆች አያት ቅድማያቶች የሮምን መንግሥት የሚያስደስት ተግባር አከናውነው ይህን ዜግነት እንዳገኙ ያሳያል። የሮም ዜጎች በዚህ መንገድ አይቀጡም ነበር። አንዳንድ ጊዜ ጳውሎስ ከስደት ለመዳን የሮም ዜግነቱን ሲጠቀም፥ ሌላ ጊዜ (ለምሳሌ በፊልጵስዩስ) ከቅጣቱ በፊት ስለ ሮማዊ ዜግነቱ ለመግለጽ አለመፈለጉ አስገራሚ ነበር (የሐዋ. 16፡16–40)። የሮም ዜግነቱን ሳይገልጽ ስደቱን የተቀበለባቸው ጊዜዎች ነበሩ።
- ጳውሎስ በአይሁድ ሸንጎ ፊት ማስረጃውን አቀረበ (የሐዋ.22፡30-23፡11)።
በማግሥቱ የሮሙ ሻለቃ የአይሁድ ሸንጎ ጳውሎስን በተመለከተ ስብሰባ ተቀምጦ እንዲወያይ አዘዘ። ጳውሎስ በእግዚአብሔር ፊት ሕሊናው ንጹሕ እንደሆነ በመግለጽ መከላከያውን አቀረበ። በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህን የነበረውና ከ47-59 ዓም. ያገለገለው ሐናንያ ነበር። (ማስታወሻ፡- ይሄ ክርስቶስ በተሰቀለ ጊዜ ከነበረው ሐናንያ የተለየ ነው)። እርሱም ጳውሎስ እንዲገረፍ ከሰጠው ትእዛዝ እንደምንረዳው በጨካኝነቱ የታወቀ ሰው ነበር፡፡ ሐናንያ በሰዎች ዘንድ የተጠላ ስለነበር፣ አይሁዶች በሮም ላይ ባመጹ ጊዜ እርሱንም ገድለውታል።
ምንም እንኳ ሐናንያ በጳውሎስ ላይ የድብደባ ተግባር እንዲፈጸም በማድረግ የእግዚአብሔርን ሕግ ቢተላለፍም፥ ጳውሎስ ሊቀ ካህኑን ተቃውሞ መናገሩ ስሕተት እንደሆነ አምኗል። ጳውሎስ ሊቀ ካህናቱን ተቃውሞ መናገሩ ስሕተት የሆነው ለምንድን ነው? ጻዊት ሳዖልን ለመግደል እንዳልፈለገ ሁሉ፥ ጳውሎስ እግዚአብሔር የመሪዎችን ሹመት እንደሚቆጣጠር ያውቅ ነበር፡፡ እግዚአብሔርን ቢወዱም ባይወዱም፣ ክርስቲያን እግዚአብሔር የሾማቸውን ሰዎች እስኪሽር ድረስ ማክበርና መታዘዝ አለበት። (ሮሜ 13፡1-7 አንብብ።)
የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ክርስቲያኖች ብዙውን ጊዜ በፖለቲካ መሪዎቻቸው ላይ የትችት ቃላት የሚሰነዝሩት እንዴት ነው? ለ) ጳውሎስና መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምሩት መሠረት፥ ይህ ትክክል ይመስልሃል? ሐ) 1ኛ ጢሞ. 2፡1-2 አንብብ። አንተና ቤተ ክርስቲያንህ ይህን ትእዛዝ እየፈጸማችሁ ያላችሁት እንዴት ነው? ለመሪዎቻችን ብንጸልይላቸው፣ ይህ በእነርሱ ላይ ከማማረር የሚጠብቀን እንዴት ነው?
ጳውሎስ የወንጌሉ ማዕክል የሆነውን ነገረ መለኮታዊ መሠረት በማንሣት በአይሁድ ሸንጎ ፊት መናገር ጀመረ። በሸንጎው ውስጥ ከሁለት የተለያዩ ቡድኖች የተውጣጡ ሰዎች ነበሩ። ከሊቀ ካህናቱና ከሀብታም ነጋዴዎች ወገን የሆኑት ሰዱቃውያን በትንሣኤ ሙታን አያምኑም ነበር። ሕግ በመጠበቅ ላይ ያተኩሩ የነበሩት አክራሪ ፈሪሳውያን ግን በትንሣኤ ሙታን ያምኑ ነበር። የወንጌሉ እምብርት የክርስቶስ ሞት ብቻ ሳይሆን ትንሣኤውም ጭምር ነው። ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮ. 15፡12-19 እንደ ገለጸው፥ የሙታን ትንሣኤ ባይኖርና ክርስቶስ ከሞት ባይነሣ ኖሮ፥ የክርስትና እምነት ዋጋ አይኖረውም ነበር። አይሁዶች ሊከራከሩበት የሚገባው ቁልፍ ጉዳይ የሙታን ትንሣኤ መኖር ወይም አለመኖርና የክርስቶስ ከሞት መነሣት ወይም አለመነሣት በመሆኑ፥ ጳውሎስ የሙታን ትንሣኤ የእስራቱ ምክንያቱ እንደሆነ ገለጸ። የጳውሎስን ንግግር ተከትለው አይሁዳውያኑ እርስ በርሳቸው ስለ ሙታን ትንሣኤ መኖር አለመኖር ይሟገቱ ጀመር። አንዳንዶች ጳውሎስን ደግፈው መናገር ጀመሩ። ጠቡ እየተካረረ ሲመጣ ሻለቃው በጳውሎስ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት በማሰብ ወደ እስር ቤት መልሶ ወሰደው። ከዚያም እግዚአብሔር ወደ ጳውሎስ ዘንድ በመምጣት ወደ ሮም ሄዶ እስኪመሰክርለት ድረስ ምንም ክፉ ነገር እንደማይደርስበት በመግለጽ አበረታታው፡፡ ጳውሎስ ይህ ሁሉ ሲሆን ከሁለት ዓመት በላይ እንደሚፈጅ አላወቀም ነበር።
- አይሁዶች ጳውሎስ በቂሣርያ ታስሮ ሳለ ሊገድሉት አሤሩ (የሐዋ. 23፡12-35)።
እግዚአብሔር ፈቃዱን ለመፈጸም ሁኔታዎችን የሚቆጣጠርበት መንገድ አስገራሚ ነው። የአይሁድ መሪዎች ጳውሎስን ለመግደል ቆርጠው ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር የጳውሎስ እኅት ልጅ ዕቅዳቸውን እንዲሰማ አደረገ። ጳውሎስና ሻለቃው የአይሁዶችን ዕቅድ ከሰሙ በኋላ፥ አይሁድ በብዛት በሚኖሩበት የኢየሩሳሌም ከተማ ጳውሎስን ማሰሩ ለሕይወቱ አስጊ እንደሆነ ተገነዘቡ። ከዚህ ይልቅ በፍልስጥኤም የሮም ግዛት ማዕከል በነበረችው ቂሣርያ ለማሰር ወሰኑ። ሻለቃው በይሁዳና በኢየሩሳሌም የሮም ገዥ ለነበረው ፊሊክስ በጻፈው ደብዳቤ፥ ጳውሎስ የፖለቲካ ወንጀል እንዳልፈጸመና ከአይሁድ ባለሥልጣናት ጋር ሃይማኖታዊ ሙግት እንዳለበት በግልጽ አመልክቷል። ሉቃስ ሮማውያን እንዲያውቁ የሚፈልገውም ዋነኛ መልእክት ይህ ነበር። ይኽውም ጳውሎስ ሞት ወይም እስራት የሚገባው ዓማጺ አለመሆኑ ነበር። ጳውሎስ በሕጋዊ መንገድ እንዳይመረመር በአቋራጭ ሊገድሉት የሚፈልጉ የአይሁድ መሪዎች ነበሩ። ይህ የሃይማኖት ጉዳይ ደግሞ ሮማውያን ጣልቃ ለመግባት የሚፈልጉት ነገር አልነበረም።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር ሁኔታዎችን በመቆጣጠር (የማያምኑ ሰዎች “እጋጣሚ” እንደሚሉት) ሕዝቡን ሲጠብቅ ወይም ሲጠቅም የተመለከትህበትን መንገድ ግለጽ፡፡ ለ) ይህ እግዚአብሔር በክርስቲያን ሕይወት ውስጥ የሚፈጸመውን ነገር ሁሉ ለለ መቀጣጠሩ ምን ያስተምርሃል?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)