ጳውሎስ በመቄዶንያና በግሪክ የነበሩትን አብያተ ክርስቲያናት መጎብኘቱ እና ከኤፌሶን መሪዎች ጋር ያደረገው ስንብት (የሐዋ. 20፡1-38)

  1. ጳውሎስ በመቄዶንያና በግሪክ የነበሩትን አብያተ ክርስቲያናት ጎበኘ (የሐዋ. 20፡1-12)።

ጳውሎስ ረዳቶቹ የሆኑትን ጢሞቴዎስንና ኤርስጦንን ወደ መቄዶንያ ልኳቸው ነበር (የሐዋ. 19፡21-22)። ብዙም ሳይቆይ ከብጥብጡ በኋላ፥ ጳውሎስ፥ ኤፌሶንን ትቶ በመቄዶንያ በኩል ወደ ቆሮንቶስ ሄደና እግረ መንገዱን የፊልጵስዩስን፥ የተሰሎንቄን፥ የቤርያንና የቆርንቶስን አብያተ ክርስቲያናት ጎበኘ። በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያስተማረና አንዳንድ የተሳሳቱ ነገሮችን እያስተካከለ ለሦስት ወራት ተቀመጠ። ጳውሎስ በመቄዶንያና በቆሮንቶስ በኩል ሲያልፍ ካደረጋቸው ነገሮች አንዱ፥ በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ድሆች የሚወስደውን ገንዘብ መሰብሰብ ነበር (2ኛ ቆሮ. 8፡1-15፤ 9፡1-15)።

በዚህ ጊዜ አይሁዶች ጳውሎስን ለመግደል ቆርጠው ነበር፡፡ ከጥቂት ቁልፍ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጋር ጳውሎስ በመቄዶንያ በኩል አለፈ። ከሉቃስ ጋር ከእስያ በስተ ምዕራብ ወደምትገኘው ጢሮአዳ (የዛሬዋ ቱርክ) ወደምትባል የወደብ ከተማ ተጓዘ። በዚያም ጳውሎስ ከታላላቅ ተአምራቱ አንዱን አደረገ፤ ጳውሎስ እየሰበከ ሳለ በመስኮት በኩል ወድቆ የሞተውን ወጣት እንዲያስነሣ እግዚአብሔር ኃይል ሰጠው።

  1. ጳውሎስ ለኤፌሶን መሪዎች መንጋውን አደራ ሰጥቶ ተሰናበተ (የሐዋ. 20፡13-38)።

እርሱም ለተወሰነ ጊዜ ወደ ሮም ለመሄድ ሲያስብ ቆይቷል (የሐዋ 19፡21)። የሮም ከተማ የሮም ግዛት መዲና በመሆኗ ክርስትና ወደ ዓለም ሁሉ እንዲደርስ ካስፈለገ፣ ወንጌሉ ወደ ሮም መግባት አለበት፡፡ መጀመሪያ ጳውሎስ ታስሮ ወደ ሮም እንደሚሄድ አላወቀም ነበር። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ችግር እንደሚገጥመው አስጠነቀቀው።

የውይይት ጥያቄ፡- የሐዋ. 20፡13-38 አንብብ፡፡ ከጳውሎስ ንግግር ውስጥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሊያስታውሱትና ሊጠቀሙበት የሚገባውን እውነት ዘርዝር።

ጳውሎስ በኤፈሶን ጠረፍ አካባቢ ወደነበረችው ወደ ሚሊጢን ሲደርስ፥ የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወደ እርሱ እንዲመጡ ላከባቸው። እንደገና የሚያገኛቸው ስላልመሰለው ቤተ ክርስቲያኒቱን ስለሚመሩበት መንገድ የመጨረሻ መመሪያዎችን ሊሰጣቸው ፈልጎ ነበር። ጳውሎስ ስለ መሪነትና አገልግሎት የተናገራቸውን የሚከተሉትን ነገሮች አስተውል።

ሀ. የጳውሎስ የመሪነት ምሳሌ

  1. የአገልግሎት መርሕ፡- ትሕትናና እንባ። ከአመራር አደጋዎች አንዱ ሕዝቡ ተቸግሮ እያለ የእኛ ልብ በሕዝቡ ችግር ፊት እንዲደነድን ማድረግ ነው። ክርስቶስን ላላገኙት ሰዎች መጥፋት እናለቅሳለን? ለቤተ ክርስቲያን ችግሮች እናለቅሳለን? ወይስ በኃይልና በሥልጣን ለመምራት እንሞክራለን? ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን መሪነት በኃይልና ሐዋርያዊ ሥልጣኑን በመጠቀም ሳይሆን፥ በትሕትና እንደሚካሄድ ገልጾአል። ለሕዝቡ ፍላጎት የተዘጋ ልብ እንዳይኖረውም ጥንቃቄ አድርጓል።
  2. ጳውሎስ ክርስቲያን ላልሆኑ ሰዎች ግልጽ መልእክት ነበረው። እያንዳንዱን አጋጣሚ ለአይሁድና ለአሕዛብ ወንጌሉን ለመመስከር ይጠቀም ነበር። ጳውሎስ በወንጌል አያፍርም ነበር፡፡ ትምህርቱ በክርስቲያኖች ላይ ብቻ ያተኮረ አልነበረም፡፡ በክርስቲያኖች መካከል ብዙ ችግርች ቢኖሩም የአሕዛብ ሐዋርያነቱን ሳይዘነጋ፥ ከፍተኛ ስደቶችን የሚያስከትል የክርስቶስን ወንጌል ይሰብክ ነበር። ሉቃስ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ባይጠቅስም ጳውሎስ በኤፌሶን ከአውሬ ጋር ለመታገል ተገድዶ ነበር (1ኛ ቆሮ. 15፡32)፡፡ ጳውሎስ ለኤፈሶን ሰዎች ከማንም ደም ነፃ እንደሆነ ለመግለጽ ችሏል። ይህን ሲል ሰዎች በክርስቶስ ካላመኑ የኋላ ኋላ የዘላለም ፍርድ እንደሚደርስባቸው እንዳስጠነቀቃቸው መናገሩ ነበር። ማስጠንቀቂያ ስለተሰጣቸው ሰዎቹ በክርስቶስ ባያምኑ ጥፋቱ የራሳቸው ይሆናል። ነገር ቀን ጳውሎስ እምነቱን ደብቆ ሳይመሰክርላቸው ቢቀር ኖር፥ ለዘላለም ጥፋታቸው ተወቃሽ በሆነ ነበር።
  3. ጳውሎስ አስፈላጊው ነገር ምን እንደሆነ በግልጽ ያውቅ ነበር። ለጳውሎስ ሕይወቱን ከአደጋ መጠበቅ፥ ምርጥ ደመወዝ ማግኘት፥ ማለፊያ ቤት ውስጥ መኖር አስፈላጊ ነገሮች አልነበሩም። መኖርም እንኳ ለጳውሎስ አስፈላጊው አልነበረም። እርሱን የሚያሳስበው እስከ መጨረሻው ድረስ ለክርስቶስ ታማኝ ሆኖ መጽናቱ ነበር። እርሱ የሚፈልገው ሩጫውንና ክርስቶስ የሰጠውን አገልግሎት መፈጸም ነበር። ከአሥር ዓመት በኋላ ጳውሎስ ለሞት በተቃረበበት ሰዓት እንዲህ ብሏል። «በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል። መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፤ ሩጫውን ጨርሼአለሁ፤ ሃይማኖትን ጠብቄአለሁ፤ ወደፊትም የጽድቅ አክሊል ተዘጋጅቶልኛል» (2ኛ ጢሞ. 4፡6-8)።

የውይይት ጥያቄ፡- ይህን እጅግ የላቀ ግብ የሆነውና፥ በዕለት ሕይወታችን ውስጥ ልናስታውሰውና ልንመኘው የሚገባን እንዴት ነው?

  1. ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ለማስተማር ግልጽ ተልእኮ ነበረው። ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ምክር ሁሉ እንዳስተማራቸው ገልጾአል። ጳውሎስ ሰዎችን ወደ ድነት (ደኅንነት) መምራት መቻሉ ብቻ በቂ አልነበረም። አዳዲስ አማኞችን በማስተማር፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲያውቁ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። ምክንያቱም ከፊል እውቀት አደገኛ ስለሆነ ነው። እውቀት የሌለው ቅንዓት አጥፊ ሊሆን ይችላል። ስለሆነም ከቤተ ክርስቲያን ዐበይት ኃላፊነቶች አንዱ፥ የእግዚአብሔርን እውነት ሁሉ በግልጽና ሥርዓታዊ በሆነ መንገድ ማስተማር ነው።
  2. ጳውሎስ በገንዘብ ጉዳይ ላይ ብርቱ ጥንቃቄ ያደርግ ነበር። ብዙ መሪዎች በአገልግሎታቸው የግል ጥቅም ለማግኘት ሲሉ፥ ወደ ተሳሳተ አቅጣግጫ ተጉዘዋል። ጳውሎስ የወንጌል አገልጋይ በመሆኑ ገንዘብ የመቀበል መብት ቢኖረውም፥ አገልግሎቱ እንዳይበላሽ ለማድረግ ሊል ይህንን መብቱን ላለመጠቀም ወስኗል። ጳውሎስ ከቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ከመቀበልና፥ «ጳውሎስ የሚያገለግለው ገንዘብ ለማግኘት ሲል ነው» የሚል ሐሜት ከማትረፍ ይልቅ፥ ሦስት ነገሮችን አድርጓል፡-

ሀ. ሰዎች የሚሰጡትን ገንዘብም ሆነ ከቤተ ክርስቲያን ደመወዝ አይቀበልም ነበር። (1ኛ ቆሮ. 9፡12-18 አንብብ።)

ለ. ለሚያስፈልገው ነገር የሚሆነውን ገንዘብ ለማግኘት በእጁ ይሠራ ነበር። ብዙ ወንጌላውያን ሰይጣን ለአገልሎት ያላቸውን አመለካከት እንዲያበላሽና ለስንፍናም እንዲዳርጋቸው ይፈቅዱለታል። በመዝናናት፥ በማውራትና በመጋበዝ ብዙ ጊዜ ያጠፋሉ። ተግተው ለመሥራት አይፈልጉም። ተቆጣጣሪ ለሌላቸው ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና ወንጌላውያን ስንፍና ትልቁ መርገም ነው። ጳውሎስ ከቤተ ክርስቲያን ብዙ ደመወዝ ሳይጠይቅ በእጁ እየሠራ ይተዳደር ነበር።

ሐ. ሠርቶ ካገኘው ለሌሎች መስጠትን ተምሯል። ከሚሠራባቸው ምክንያቶች አንዱም ለችግረኞች የሚያካፍለው ገንዘብ እንዲኖረው ነበር። ብዙ ወንጌላውያንና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች፥ ገንዘብ ለመቀበል እንጂ ለመስጠት አይፈልጉም፡፡ ብዙውን ጊዜ መጋቢያንና ወንጌላውያን አሥራት አይከፍሉም። “ለጌታ እየሠራሁ ስለሆነ፥ ገንዘቤን ለምን እሰጣለሁ? ይሄ ገንዘብ ለእኔ ያስፈልገኛል ድሀ ነኝ” ይላሉ። ይህን በማለታቸው የእግዚአብሔርን የአሥራት መርሕ ከመጣሳቸውም በላይ፣ በመስጠት የሚገኘውን ደስታ ያጣሉ። የማይሰጡ ከሆነ የገንዘብ ፍቅር ልባቸውን ያጠፋዋል። ልባችንን ከገንዘብ ፍቅር ከምንጠብቅባቸው መንገዶች አንዱ መስጠት ነው።

ለ. ጳውሎስ ለመሪዎች የሰጠው ምከር፡-

  1. ሕይወታቸውንና ልባቸውን እንዲጠብቁ። ሰይጣን ሕይወታችንን፥ ምስክርነታችንና የእግዚአብሔር ቃል እውቀታችንን ለማጥፋት ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ከማድረግ አይመለስም። ሰይጣን መንፈሳዊ ሕይወታችንን ለማጥፋት ከቻለ፥ እኛን በምሳሌነት የሚመለከቱትን ሰዎች ሁሉ ሕይወት ሊያጠፋ እንደሚችል ያውቃል። ማንኛውም መሪ በድንገት የወሲብ፥ ከምጽዋት ገንዘብ የመስረቅ ወይም የትዕቢት ኃጢአት ላይፈጽም ይችላል። ይህ የሂደት ውጤት ነው። የውስጥ ሕይወታችን በጥንቃቄ ጉድለት፥ በጸሎት ወይም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እጥረት ይቦረቦራል። አመራር የሚጀምረው ከግል ሕይወታችን በመሆኑ፥ እንደ መሪዎች ሕይወታችንን፥ መጥፎ ምኞቶቻችንንና ተግባሮቻችንን በጥንቃቄ መጠበቅ አለብን፡፡
  2. የእግዚአብሔርን መንጋ ጠብቁ። ጳውሎስ መንጋው የእግዚአብሔር እንጂ የሽማግሌዎቹ እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥቶ ተናግሯል። ክርስቲያኖችን በውድ ደሙ የገዛው ክርስቶስ በመሆኑ፥ መሪዎች በማንኛውም የቤተ ክርስቲያናቸው አባላት ላይ የባለቤትነት መብት የላቸውም። ብዙውን ጊዜ መሪዎች መንጋው የእግዚአብሔር እንደሆነ ይዘነጋሉ። መሪዎች የእግዚአብሔር መንጋ ተንከባካቢዎች በመሆናቸው የእግዚአብሔርን ልጆች ሊጠብቁ ይገባል።
  3. ሐሰተኛ መምህራን የመንጋው ቀንደኛ ጠላት ናቸው። እነዚህ የሐሰት ትምህርቶች በአብዛኛው የሚመጡት ከየት ነው? ትምህርቶቹ የሚመጡት ከማያምኑ ሰዎች ሳይሆን ከክርስቲያኖች ነው። ሰይጣን የአይሁድ ከርስቲያኖች የሐሰት ትምሕርቶችን እንዲያስፋፉ ለማድረግ እንደ ተጠቀመባቸው ሁሉ፥ እነዚህም ክርስቲያኖች እውነቱን አጣምመው ሕዝቡን ወደ ስሕተት እንዳይመሩ ጳውሎላ ለሽማግሌዎች ብርቱ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

የውይይት ጥያቄ፡- ጳውሎስ ለኤፌሶን ሽማግሌዎች ያስተማራቸውን እነዚህን ነገሮች በጸሎት መንፈስ ከልስ። በክርስቲያናዊ ጉዞህ የደከምኽው የቱ ላይ ነው? በአሉታዊ መልኩ ተጽዕኖ ያሳደረብህ ነገር ምንድን ነው? ንስሐ ገባ። ገንዘብብ በመስረቅ ጥፋት ፈጽመህ ከሆነ ኃጢአትህን ለሽማግሌዎች ተናዘዝ። በመጨረሻው ቀን የሚጸጽትህ ነገር እንዳይኖርህና ደም በእጅህ ላይ እንዳይገኝ፥ ለእግዚአብሔር ታማኝ ለመሆንና ሩጫህን በአግባቡ ለመሮጥ ከልብህ ቁረጥ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d