የ2ኛ ቆሮንቶስ መግቢያ

ስንታየሁ ከመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ በቅርቡ ተመርቆ አባል በነበረበት የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን መጋቢ በመሆን ያገለግል ጀመር። መጀመሪያ ነገሮች በጥሩ ሁኔታ ይከናወኑ ጀመረ። እምነቱን ለዓለማውያን ከማካፈሉም በላይ፥ በየእሑዱ የእግዚአብሔርን ቃል ማጥናትና መስበክ ያስደስተው ነበር። ብዙም ሳይቆይ ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ችግሮች መኖራቸውን ተገነዘበ። ሁለት ሽማግሌዎች ተጣልተው መነጋገር አቁመዋል። ሁለት የኳዬር መዘምራን ወሲባዊ ኃጢአት እየፈጸሙ ይመላለሱ ነበር። እነዚህ መዘምራን የታላላቅ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ልጆች ነበሩ። ጎሳዊ ውጥረቶች ቤተ ክርስቲያንን ይከፋፍሉ ነበር። እርሱ የአንድ ጎሳ አባል በመሆኑ ለዘሮቹ እንደሚያዳላ ይታማ ጀመር። ብዙውን ጊዜ ወዳጆቹና ቤተሰቦቹ ልዩ ችሮታ እንዲያደርግላቸው ይጠይቁታል። ሰዎች የትዳር፥ የሥራ ማጣት፥ የኤድስ በሽታና ሌሎችም ከባባድ ችግሮችን ይዘው በመምጣት የእርሱን እገዛ ይጠይቃሉ። እነዚህ የማያቋርጡ ችግሮች ስላዛሉት የቤተ ክርስቲያን አመራሩን ለመልቀቅ ተዘጋጀ። “ሁልጊዜም እነዚህን ችግሮች ከመስማት ይልቅ ነጋዴ መሆኑ በጣም ይቀላል” ሲል አሰበ። ነገር ግን የሙሉ ጊዜ አገልግሎቱን ለቅቆ ንግዱን ለመጀመር ባሰበ ቁጥር የጌታ መንፈስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ባለው አገልግሎቱ እንዲቀጥል ሲገፋፋው ይሰማዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንተ ወይም አንተ የምታውቀው ሰው በቤተ ክርስቲያን የአመራር ችግሮች ሲታወክ ያየኽው እንዴት ነው? ለ) 2ኛ ቆሮ. 11፡28-29 አንብብ። 1) ጳውሎስ ተጨማሪ ችግር አመጣብኝ ያለው ምንን ነው? 2) ይህ በቤተ ከርስቲያንህ ውስጥ ለሚያገለግሉ መሪዎች እውነት የሆነው እንዴት ነው? 3) እነዚህ ጥቅሶች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው እንደሚገባ የሚገልጹት እንዴት ነው? ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሰዎች ችግሮች ከመዛል የሚድኑት እንዴት ነው?

ጳውሎስም ከዚህ የቤተ ክርስቲያን አመራር ጋር ታግሏል። ሊያገለግላቸው የሚፈልጋቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ ብቃት እንደሌለው፥ አምባገነን እንደሆነ፥ እንደ ሌሎቹ ጥሩ መሪ እንዳልሆነ፥ የተሳሳቱ አነሣሽ ምክንያቶች እንዳሉት፥ ወዘተ… በመግለጽ በተሳሳተ መንገድ ይረዱት ነበር። ጳውሎስ ስለ ወንጌሉ ከፍተኛ አካላዊ መከራ እንደተቀበለ በ2ኛ ቆሮ. 11 ውስጥ ገልጾአል። ከሁሉም በላይ የሚከብደው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቱ እንደሆነም አስረድቷል። ለክርስቲያኖች ችግሮች መፍትሔ መፈለጉ አድክሞት ነበር።

የ2ኛ ቆሮንቶስ መጽሐፍ ስለ ቤተ ክርስቲያን መሪነት ከፍተኛ ትምህርት ይሰጣል። እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ለማገልገል ከፈለግን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ምን እንደሚመስል፥ ምን ዓይነት ኃዘንና ደስታን እንደሚያስከትል፥ ከሁሉም በላይ ችግሮች በሚኖሩበት ጊዜም እንኳ እግዚአብሔርን እንዴት በታማኝነት እንደምናገለግል ማወቅ አለብን።

የውይይት ጥያቄ፡– ስለ 2ኛ ቆሮንቶስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብና ስለ ጸሐፊው፥ ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱና ስለ መጽሐፉ የተጻፈውን ሁሉ ጠቅለል አድርገህ ግለጽ።

የ2ኛ ቆሮንቶስ ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) 2ኛ ቆሮንቶስ 1፡1 አንብብ። የ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ጸሐፊ ነኝ የሚለው ማን ነው? ለ) ከእርሱ ጋር ማን ነበር? ሐ) መልእክቱ የተጻፈው ለምንድን ነው?

ጳውሎስ ሁልጊዜም እንደሚያደርገው፥ የ2ኛ ቆሮንቶስን መልእክት የጀመረው ስሙንና የጻፈበትን ሥልጣን በመግለጽ ነበር። እርሱ «የክርስቶስ ሐዋርያ» ነበር። ሐዋርያው እንደ መሆኑ፥ ጳውሎስ ክርስቶስን እንዲወክልና በሥልጣኑ እንዲናገር ክርስቶስ ወክሎት ነበር። ጳውሎስ የተናገረው የግል አሳብ ሳይሆን ክርስቶስን የሚወክል ነበር። ስለሆነም፥ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ክርስቶስን የሚሰሙትን ያህል ጳውሎስን መስማት ነበረባቸው።

ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ጠቅሶታል። ጢሞቴዎስ የወንጌል ስርጭት አጋሩ፥ የበፊቱን የ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ያደረሰና (1ኛ ቆሮ. 4፡17) የቆሮንቶስን ክርስቲያኖች በሚገባ የሚያውቅ ነበር።

ጳውሎስ መልእክቱን ለማን ጻፈ?

ጳውሎስ ይህን መልእክት የጻፈው «በአካይያ አገር ሁሉ ከሚኖሩ ቅዱሳን ሁሉ ጋር በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን» ነበር። ቆሮንቶስ ከግሪክ ዐበይት ከተሞች አንዷ እንደነበረች በ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት መግቢያ ውስጥ ተጠቅሷል። ቆሮንቶስ ከግሪክ በስተደቡባዊ አካያን በሚባል አውራጃ ውስጥ ትገኝ ነበር። ጳውሎስ በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው በአብዛኛው በቆሮንቶስ ከተማ ኖሯል። በቆሮንቶስ ከተማ የተተከለችው ቤተ ክርስቲያን የኋላ ኋላ ወደ ሌሎች የአውራጃው ከተሞች ተሰራጨች። ቆሮንቶስ ሰፊ ከተማና የሌሎች አብያተ ክርስቲያናት «እናት ቤተ ክርስቲያን» ስለነበረች፥ የቆሮንቶስ አማኞች ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በጳውሎስና እርሱ ለመፍታት በሚፈልጋቸው ነገሮች ላይ የነበራቸውን አመለካከት ሊጫኑ ይችሉ ነበር።

ጳውሎስና በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መካከል የነበረው ግንኙነት በከፍተኛ ደረጃ ቢሻክርም፥ ጳውሎስ ሁለት ጠቃሚ ነገሮችን ተገንዝቧል። ይህ ግንዛቤም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ጋር በነበረው ግንኙነት ላይ ጠቃሚ አስተዋጽኦ አድርጓል። በመጀመሪያ፥ የክርስቲያኖች ማኅበረሰብ የእግዚአብሔር ንብረት ነበር። ምንም እንኳ ጳውሎስ ስጦታ ያለው ሐዋርያና የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መሥራች ቢሆንም፥ እያንዳንዱ ክርስቲያንና ጠቅላላው የክርስቲያኖች ማኅበረሰብ የእግዚአብሔር መሆናቸውን ተረድቷል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚታየው ነገር ሁሉ አምልኮተ እግዚአብሔርን ማንጸባረቅ ነበረበት። ሁለተኛ፥ ምንም እንኳ ሁልጊዜም በተግባራዊ ቅድስና የማይመላለሱ ደካሞችና ራስ ወዳዶች ቢሆኑም፥ ጳውሎስ እነዚህን ክርስቲያኖች «ቅዱሳን» ብሎ ይጠራቸዋል። ቅዱስ የሚባለው ሰው ኃጢአት-አልባና ለእግዚአብሔር አንድ ታላቅ ተግባር የፈጸመ ሰው አይደለም። ሥጋዊ ክርስቲያኖችን ጨምሮ፥ እያንዳንዱ ክርስቲያን ቅዱስ ነው። ቅዱሳን የሆንነው በእግዚአብሔር ስለተመረጥን፥ ከማያምኑ ሰዎች ስለተለየንና የእግዚአብሔር ቤተሰብ አካል ስለሆንን ነው።

ጳውሎስ 2ኛ ቆሮንቶስን የጻፈበት ዘመንና ስፍራ

ለአምስት ዓመታት ያህል ጳውሎስ ሦስተኛውን የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ሲያካሂድ ነበር (ከ52-57 ዓ.ም.)። በዚህ ወቅት አብዛኛውን ጊዜ የኖረው በኤፌሶን ከተማ ነበር። ጳውሎስ በኤፌሶን ሳለ ከቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የተለያዩ መሪዎች እንደጎበኙት በ1ኛ ቆሮንቶስ ጥናታችን ተመልክተናል። እነዚህ ጎብኚዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ስለነበሩት ክፍፍሎችና ኃጢአቶች ለጳውሎስ ገለጻ አደረጉለት። በተጨማሪም፥ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች፥ ለኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ስለሚሰጠው ስጦታ፥ ስለ ጋብቻ፥ ወዘተ. የሚጠይቁ አሳቦች የተካተቱበትን ደብዳቤ ከቆሮንቶስ ክርስቲያኖች አመጡለት። በ55 ዓ.ም የተጻፈውን የ1ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ለቤተ ክርስቲያኒቱ ያደረሰው ጢሞቴዎስ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡– 2ኛ ቆሮ. 2፡1-13፤ 7፡5-15፤ የሐዋ. 19፡21-41 አንብብ። እነዚህ ጥቅሶች በ1ኛና 2ኛ ቆሮንቶስ ጽሑፍ መካከል ስለተፈጸሙት አንዳንድ ነገሮች ምን የሚያመለክቱ ይመስላል?

በ1ኛና 2ኛ ቆሮንቶስ መጻፍ መካከል የተፈጸሙትን ነገሮች ማወቁ አስቸጋሪ ነው። በ1ኛና 2ኛ ቆሮንቶስ ጽሑፍ መካከል በነበሩት ከአንድ ዓመት በሚበልጡ ጊዜያት የሚከተሉት ነገሮች የተከናወኑ ይመስላል።

ሀ. ጢሞቴዎስ የአንደኛ ቆሮንቶስን መልእክት ይዞ ቆሮንቶስ ሊደርስ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች መልእክቱን የተቀበሉት በሁለት ቅይጥ ምላሾች ነበር። ስለ ጌታ እራትና ለጣዖት የተሠዋ ሥጋን ስለመብላት የሰጣቸው ምላሽ የጠቀማቸው ይመስላል። ነገር ግን የወሲብ ኃጢአት ስለፈጸመው ግለሰብ የሰጠው ፍርድ አንዳንድ ተቃውሞዎችን ያስከተለ ይመስላል (1ኛ ቆሮ. 5)። በተጨማሪም፥ አንዳንድ ሰዎች የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጳውሎስ ላይ እንዲያምጹና ሥልጣኑን እንዲጠራጠሩ የቀሰቀሱ ይመስላል። ይህም በጳውሎስና በቆሮንቶስ አማኞች መካከል የነበረውን ግንኙነት አቀዘቀዘው። ጢሞቴዎስ ወደ ጳውሎስ ተመልሶ ስለ አመለካከታቸው አብራራለት።

ለ. ጳውሎስ ለአጭር ጊዜ ጉብኝት ወደ ቆሮንቶስ ሄደ። ጳውሎስ ይህንን «የኃዘን ጉብኝት» ይለዋል (2ኛ ቆሮ. 2፡1)። በዚህ ጊዜ ስለተፈጸመው ነገር ጳውሎስ ምንም አልጠቀሰም። ነገር ግን ግንኙነታቸው በመሻከሩ ጳውሎስ ለማስተካከል የፈለጋቸውን ነገሮች ሳያስተካክል ወደ ኤፌሶን የተመለሰ ይመስላል።

ሐ. ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ከተመለሰ በኋላ ሐዋርያዊ ሥልጣኑን ተጠቅሞ ጠንካራ የተግሣጽ ደብዳቤ ጻፈላቸው። ይህንንም ደብዳቤ ሌላኛው ረዳቱ ቲቶ አደረሰላት (2ኛ ቆሮ. 2፡3-9፤7፡5-7)።

መ. የኤፌሶን አገልግሎቱ ሊፈጸም ሲል በጳውሎስ ላይ የነበረው ተቃውሞ ይበልጥ ተጠናከረ። ድሜጥሮስ በተባለ ግለሰብ መሪነት በኤፌሶን ጳውሎስን ለመግደል የሚፈልጉ ሰዎች ሁከት አስነሡ (የሐዋ. 19፡23-41)። ከአይሁዶች የተሰነዘረበት ተቃውሞም ቀላል አልነበረም። ከዚህ ሁከት በኋላ ብዙም ሳይቆይ ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዘ ሳለ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናትን ሊጎበኝ የወሰነ ይመስላል።

ሠ. ጳውሎስ ከኤፌሶን ወደ ጢሮአዳ ሲሄድ የተሳካ አገልግሎትና የጠነከረ ተቃውሞ ገጠመው። ከዚያም ወደ መቄዶንያ (ሰሜን ግሪክ) በመጓዝ የፊልጵስዩስን፥ የተሰሎንቄንና የቤሪያን አብያተ ክርስቲያናት ሳይጎበኝ አልቀረም። በመቄዶንያ ሆኖ የቆሮንቶስ አብያተ ክርስቲያናትን ምላሽ ይጠባበቅ ነበር (2ኛ ቆሮ. 7፡5-7)። በዚህ ጊዜ የተመለሰው ቲቶ የቆሮንቶስ አማኞች ንስሐ ገብተው አመለካከታቸውን እንደለወጡ በመግለጽ ጳውሎስን ደስ አሰኘው።

ረ. ጳውሎስ በ55 ዓ.ም. የመጨረሻዎቹ ወራት ወይም በ56 ዓ.ም የመጀመሪያዎቹ ወራት ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ሌላ መልእክት ጻፈ። ይህ ሁለተኛ ቆሮንቶስ ብለን የምንጠራው መልእክት በቆሮንቶስ ክርስቲያኖች የአመለካከት ለውጥ ጳውሎስ ደስ መሰኘቱን ያሳያል። ነገር ግን ይህን የደስታ መልእክት እየጻፈ ሳለ የሐሰት አስተማሪዎች በቆሮንቶስ እየተስፋፉ መሆናቸውን በመስማቱ ጳውሎስ ስለ እነዚሁ የሐሰት አስተማሪዎች በጥብቅ አስጠነቀቃቸው። እነዚህ ራሳቸውን ሐዋርያት ብለው የሚጠሩ የሐሰት አስተማሪዎች ጳውሎስ እውነተኛ ሐዋርያ አይደለም ብለው ያስተምሩ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ በእርሱ እውነተኛ ሐዋርያነትና በሌሎች ሐሰተኛ አስተማሪዎች መካከል ያለውን ልዩነት ያብራራል። ከዚያም ለቆሮንቶስ አማኞች በቅርቡ እንደሚጎበኛቸው ይነግራቸዋል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: