የ2ኛ ቆሮንቶስ ዓላማ እና ልዩ ባሕሪያት

የ2ኛ ቆሮንቶስ ዓላማ

እንደዛሬው ሁሉ የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያንም ከሐሰተኛ አስተማሪዎች ጋር ታግላለች። ጳውሎስ አብያተ ክርስቲያናትን በተከለበት ስፍራ ሁሉ የሐሰት አስተማሪዎች ወንጌሉን ለመበረዝ ይጥሩ ነበር። ይህንን ያደርጉ የነበረው በሁለት ዐቢይ መንገዶች ነበር። አንደኛ፥ ሰዎች የእግዚአብሔርን መልእክተኛ እንዲጠራጠሩ ለማድረግ ይጥሩ ነበር። በዚህ መሠረት የሐሰት አስተማሪዎቹ የጳውሎስን እውነተኛነት በማጣጣል ሰዎች የጳውሎስን ትምህርት እንዲጠራጠሩ ያደርጉ ነበር።

ሁለተኛ፥ የወንጌሉን መልእክት ተቃወሙ። ክርስቶስ ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት መሞቱን በሚያስረዳው መልእክት ላይ የተለያዩ አሳቦችን ጨምሩ። በቆሮንቶስ የነበሩት የሐሰት አስተማሪዎች ክርስቲያኖች የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን መከተል እንዳለባቸው አስተማሩ። ሌሎች ደግሞ ክርስቲያኖች እውነተኛ አማኞች ለመሆን ተጨማሪ እውቀትን ማግኘት እንዳለባቸው ገለጹ። ሌሎች የሐሰት አስተማሪዎች ክርስቶስ አምላክ ነው ወይስ ፍጹም ሰው? ሲሉ ጠየቁ። አንዳንዶች ደግሞ ድነት (ደኅንነት) የሚገናኘው ከግለሰቡ ነፍስ ጋር ብቻ ስለሆነ፥ አማኞች በሥጋ የሚያደርጉት ነገር በደኅንነታቸው ላይ ተጽዕኖ እንደማያስከትል አመለከቱ። ስለሆነም፥ ጳውሎስና የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሰጡ መልእክቶችን ጻፉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በአሁኑ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንህን ከሚያውኩ የሐሰት ትምህርቶች አንዳንዶችን ዘርዝር። ለ) ብዙውን ጊዜ የሐሰት አስተማሪዎች የሚቃወሟቸውን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እውነተኛነት ለማሳጣት የሚጥሩበትን ሁኔታ ግለጽ። ሐ) እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች የወንጌሉን ንጽሕና የሚያጠቁት እንዴት ነው? መ) የቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች ምእመኖቻቸውን ከእነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች ለመጠበቅ ምን እያደረጉ ናቸው?

1ኛ ቆሮንቶስ ከተጻፈ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጠንካራ የሐሰት አስተማሪዎች በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሥራት ጀመሩ። በአመዛኙ እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች ራሳቸውን ክርስቲያኖች ነን ብለው የሚጠሩ አይሁዶች ሳይሆኑ አይቀሩም። እነዚህ ሰዎች ከኢየሩሳሌም የ12ቱን ሐዋርያት ሥልጣን ይዘው መምጣታቸውን ይናገሩ ነበር። ቀደም ሲል የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በተዘፈቀችበት ግራ መጋባት ላይ ተጨማሪ ውዝግብ ለመፍጠር ሲሉ በጳውሎስ ላይ የተቃውሞ አሳቦችን ይሰነዝሩ ጀመር። የ2ኛ ቆሮንቶስን መልእክት በምንመረምርበት ጊዜ፥ እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች ጳውሎስ የድጋፍ ደብዳቤ ስለሌለውና ከ12ቱ ይፋዊ ሐዋርያት አንዱ ስላልሆነ፥ እውነተኛ ሐዋርያ አይደለም ማለታቸውን እንገነዘባለን (2ኛ ቆሮ. 3፡1፤ 11፡5፤12፡11-12)። በተጨማሪም፥ ጳውሎስ አንደበተ ርቱዕ ያልሆነ ደካማ ሰው እንደሚመስል ገለጹ (2ኛ ቆሮ. 11፡6)። እንዲሁም ጳውሎስ በአካል ቀርቦ ለመነጋገር ሳይችል ጠንካራ ደብዳቤዎችን የሚጽፍ መሆኑን አስረዱ (2ኛ ቆሮ. 10፡10)። ከዚህም ሌላ በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ስም ለራሱ ገንዘብ እንደሚሰበስብም በመግለጹ ሳይከሱት አልቀሩም (2ኛ ቆሮ. 8፡20-23)። ጳውሎስ እንደሚጎበኛቸው ከተናገረ በኋላ በመቅረቱ ሊታመን እንደማይችል ጭምር ተናገሩ (2ኛ ቆሮ. 1፡15-2፡1)። እነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች የጳውሎስን አስተምህሮና ከብሉይ ኪዳን ጋር ያለውን ግንኙነት፥ እንዲሁም የድነትን (ደኅንነትን) መንገድ ተቃወሙ።

ጳውሎስ ለዚህ ተቃውሞ ምላሽ በመስጠት ልቡንና ሕይወቱን ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ከፈተ። ጳውሎስ ከደብዳቤ ይልቅ የግል ምስክርነት በሚመስለው መልእክቱ ስለ አገልግሎቱ፥ ሐዋርያነቱን ስለሚያረጋግጡት ነገሮችና መልእክቱ ተቀባይነት ሊያገኝ ስለሚገባቸው ምክንያቶች አብራርቷል።

ጳውሎስ በመልእክቱ ውስጥ ካካተታቸው ነገሮች አንዳንዶቹ የሚከተሉት ናቸው።

  1. በዕቅዱ መሠረት ለምን ቆሮንቶስን እንዳልጎበኘ ለማብራራት (2ኛ ቆሮ. 1፡15-24)።
  2. ቀደም ሲል የጻፈላቸውን መልእክት ስለተቀበሉ ለመልእክቱና ለእርሱ የነበራቸውን አመለካከት ስለቀየሩ አማኞችን ለማመስገን (2ኛ ቆሮ. 7፡14-15)
  3. በቤተ ክርስቲያን የተቀጣውን ወንድም ወደ ኅብረቱ እንዲመልሱት ለማሳሰብ (2ኛ ቆሮ. 2፡6-9)።
  4. የሐሰት አስተማሪዎችን የሚከተሉትን ወገኖች ለማስጠንቀቅ (2ኛ ቆሮ 11፡3፥ 4፥ 13)።
  5. የክርስቶስ እውነተኛ ሐዋርያ እንደሆነና በእርሱ ሥልጣን የሚናገር እገልጋይ መሆኑን ለማረጋገጥ (2ኛ ቆሮ. 11፡1-12፡21)።
  6. የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለኢየሩሳሌም ድሆች በሚዋጣው ገንዘብ ላይ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ለማሳሰብ (2ኛ ቆሮ. 8፡10-12)፡፡

ይህ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን የተጻፈው መልእክት ንስሐን በማስከተሉና አማኞች ጳውሎስን እንዲቀበሉ በማድረጉ ረገድ ውጤታማ የነበረ ይመስላል። ይህንንም ጳውሎስ መልእክቱን ከጻፈ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ቆሮንቶስ ተጉዞ ለሦስት ወራት ካገለገለበት ሁኔታ መረዳት ይቻላል ( የሐዋ. 20፡2-3)። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥም ሉቃስ በጳውሎስና በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን መካከል አለመግባባት ስለመኖሩ አልጠቀሰም። ጳውሎስ የሮሜን መልእክት የጻፈው በዚህ ጊዜ ሲሆን፥ በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ችግር ስለመኖሩ አልገለጸም። በተጨማሪም፥ «ጠንካራው መልእክት» ጠፍቶ ሳለ ይኸኛው መልእክት ተጠብቆ መቆየቱም የቆሮንቶስን አማኞች የልብ ለውጥ ያሳያል።

የ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ልዩ ባሕርያት

  1. የእግዚአብሔርን ሰው ታላቅ የሚያደርገው ምንድን ነው? የልቡ ፍላጎት ምን ሊሆን ይገባል? መረዳቱ ምን ሊሆን ይገባል? ከቤተ ክርስቲያን ጋር የሚኖረው ግንኙነት ምን ዓይነት መሆን አለበት? ስደቶችንና አሳዛኝ ሁኔታዎችን እንዴት ማስተናገድ አለበት? የ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክት ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል። ይህንን የሚያደርገው ግን ምን ልናደርግ እንደሚገባን የሚያስረዳ ስብከት በመጻፍ አይደለም። ነገር ግን ጳውሎስ እግዚአብሔር በሕይወቱ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ በሚሠራበት ጊዜ ስለነበረው አኗኗሩ የግል ምስክርነቱን ይሰጣል። ጳውሎስ ሌሎች ሰዎች የእርሱን «ምሳሌነት» እንዲከተሉ ይፈልጋል። «እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ» ሲል ተናግሯል (1ኛ ቆሮ. 11፡1)። ጳውሎስ ከየትኞቹም መልእክቶቹ በላይ በ2ኛ ቆሮንቶስ ስለ ግል ሕይወቱ ይነግረናል። እንደ ጳውሎስ እግዚአብሔር እንዲጠቀምባቸው የሚፈልጉ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና ወንጌላውያን ይህን መልእክት ሊያጠኑና ከሕይወታቸው ጋር ሊያዛምዱ ይችላሉ።
  2. ጳውሎስ ሰዎችን ወደ ታላቅነት የሚወስደው የመስቀሉ መንገድ ወይም የመከራ ጎዳና እንደሆነ አሳይቷል። እንደ ዛሬው ዘመን ሁሉ፥ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ክርስቲያን በመሆናቸው ምክንያት በሚያገኙት ጥቅም ላይ ያተኮሩ ይመስላል። የተሟላ ጤንነት፥ በተአምራት መመካት፥ በሌሎች ዘንድ ተቀባይነትን ማግኘት፥ ሰብአዊ ኃይል፥ ወዘተ. ይፈልጉ ነበር። በትምህርትና ሌሎችን በሚያስደስቱ ነገሮች ላይ ያተኩሩ ነበር። ክርስቶስን የሚከተሉት በራስ ወዳድነት ነበር። ጳውሎስ ግን ክርስቶስን መከተል የመስቀሉ ጎዳና እንደሆነና እግዚአብሔርም መከራን ለሚቀበሉት የመጽናናት አምላክ እንደሆነ ያስረዳል (2ኛ ቆሮ. 1፡3-7)። እንደ ሐዋርያና እንደ ክርስቲያኖች ሁልጊዜም ለክርስቶስ ሲሉ ሞትን መጋፈጥ ነበረባቸው (2ኛ ቆሮ. 4፡11)። ጳውሎስ ከድካም፥ ስድብ፥ መከራ፥ ስደትና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ከመሸሽ ይልቅ ይመካባቸው ነበር። ምክንያቱም በሚደክምበት ጊዜ የእግዚአብሔር ኃይል እንደሚያልፍበት ያውቅ ነበር (2ኛ ቆሮ. 11፡30፤ 12፡10)።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዛሬ ምን ያህል ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ይልቅ ራሳቸውን ለማክበር በመፈለጋቸው ምክንያት ከክርስቶስ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለራስ ወዳድነት ዓላማ እንዴት እንደሚጠቀሙ ግለጽ። ለ) ዛሬ ወጣት ክርስቲያኖች የመስቀሉን የመከራ መንገድ የሚፈሩት ለምንድን ነው? ሐ) ስንደክምና መከራን ስንቀበል እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ እንደሚያይል የሚያስረዳውን መንፈሳዊ መርሆ መረዳቱ ለምን ይጠቅማል? መ) ይህ በአንተ ወይም በሌላ ሰው ሕይወት ውስጥ እንዴት እንደተፈጸመ የሚያስረዱ ምሳሌዎችን ዘርዝር።

  1. ጳውሎስ ዓለም ከማይቀበለው የጎሳ ድንበር ባሻገር ዓለም አቀፋዊቷ ቤተ ክርስቲያን እርስ በርሷ መረዳዳት እንዳለባት ያሳያል። በጳውሎስ ዘመን በአይሁዶችና አሕዛብ መካከል ጠንካራ ጠላትነት ነበር። በአሕዛብ አገሮች አይሁዶች ለትንሽ ጉዳይ መከራ ይቀበሉና ይገደሉ ነበር። አይሁዶችም አሕዛብን አጥብቀው ከመጥላታቸው የተነሣ ድነትን (ደኅንነትን) ሊያገኙ እንደማይችሉና እግዚአብሔር ለፍርድ እንደፈጠራቸው ያምኑ ነበር። በጳውሎስ አገልግሎት አማካኝነት በቀዳሚነት አይሁዶች የሚበዙበት ቤተ ክርስቲያን በአሕዛብ እየተሞላች መጣች። ይህም በአይሁዶች መካከል ቁጣንና ጥላቻን አስከተለ። ጳውሎስ አይሁድና አሕዛብ ክርስቲያኖች አንድ ቤተሰብ መሆናቸውን ያውቅ ነበር። በተጨማሪም፥ ሰይጣን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ቅንአትንና ጠላትነትን በቀላሉ ለማራባት እንደሚፈልግ ያውቅ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የአሕዛብ ክርስቲያኖች የአይሁድ ክርስቲያኖችን እንዲቀበሉና እንዲረዱ፥ አይሁዶቹም ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ዕርዳታውን እንዲቀበሉ ለማግባባት ከፍተኛ ጥረት አደረገ። ጳውሎስ የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያናት ለማያውቋቸው የኢየሩሳሌም ድሆች በልግስና እንዲሰጡ አበረታታቸው። በጎሳዊ ቡድኖች መካከል ጠላትነት በሚኖርበት ጊዜ ክርስቲያኖች ቤተ ክርስቲያናቸው ያንኑ ጠላትነት እንዳታንጸባረቅ ማድረግ አለባቸው። ነገር ግን አንደኛው የጎሳ ቡድን ለሌላኛው ፍቅርንና አቀባበልን ማሳየት አለበት። በዚህ ዓይነት ሁላችንም የአንድ መንፈሳዊ ቤተሰብ አባላት መሆናችንንና ይህም ቤተሰብ ከምድራዊ ቤተሰብ ወይም የጎሳ ቡድን እንደሚበልጥ ልናሳይ እንችላለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በኢትዮጵያ ውስጥ ታሪካዊ የጠላትነትና የጥርጣሬ ግንኙነት ያላቸውን ሁለት ጎሳዎች ጥቅስ። ለ) ይኸው ተመሳሳይ ጥላቻና ጥርጣሬ እንዴት ወደ ቤተ ክርስቲያን ሊመጣ እንደሚችል ግለጽ። ሐ) የአንደኛው ጎሳ አባላት የሆኑ ክርስቲያኖች ሌላኛው የጎሳ አባላት የተወደዱ፥ ተቀባይነት ያገኙና የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን ለማሳየት ሊያደርጓቸው የሚችሏቸውን ነገሮች ዘርዝር።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: