እግዚአብሔር የመጽናናት አምላክ (2ኛ ቆሮ. 1፡1-11)

ጌታሁን ከቦታ ቦታ እየተጓጓዘ ስለ ክርስቶስ የሚመሰክር ፍሬያማ ወንጌላዊ ነበር። በአገልግሎቱ ውጤታማ ነበር። አንድ ቀን ተሳፍሮ የሚጓዝበት አውቶቡስ ተገልብጦ ገደል በመግባቱ ጌታሁን ለሽባነት ተዳረገ። እየተጓዘ የሚያገለግለው አገልግሎቱ ተቋረጠ። ብዙ ክርስቲያኖች ወደ እርሱ መጥተው እንዲፈወስ ጸለዩለት። ምንም እንኳን በእግዚአብሔር ላይ ጠንካራ እምነት ቢኖረውም ሊፈወስ አልቻለም። ስለሆነም፥ «እግዚአብሔር ይህ በእኔ ላይ እንዲደርስ ለምን ፈቀደ? አንዳንድ ክርስቲያኖች በከፍተኛ ደረጃ የሚሠቃዩት ለምንድን ነው?» እያለ ይጠይቅ ጀመር።

የጌታሁን ጥያቄ ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ የሚያነሡት ነው። መከራን ስንቀበል፥ ስንታመም፥ መጥፎ ነገር በቤተሰባችን ላይ ሲደርስ ሁላችንም ጥያቄዎችን እናነሣለን። እግዚአብሔር ልጆቹ እንዲሠቃዩ የሚፈልግባቸውን ምክንያቶች ሙሉ በሙሉ ባናውቅም፥ የ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክት አንዳንድ ምክንያቶችን ይገልጽልናል። ሐዋርያው ጳውሎስ መከራ በሕይወቱ ውስጥ ስላበረከተው አስተዋጽኦ አብራርቷል። መከራ እግዚአብሔር ጳውሎስን ፍሬያማ የአሕዛብ ሐዋርያ አድርጎ የተጠቀመበት ዐብይ መሣሪያ ነበር። መከራ ርግማን ሳይሆን የእግዚአብሔር የሥልጠና መሣሪያ ነው። መከራ እግዚአብሔር መሪዎቹን የሚያሠለጥንበት ትምህርት ቤት ነው። አንድ አስተማሪ እንደተናገሩት፥ «እግዚአብሔር አንድን ሰው በከፍተኛ ደረጃ ከመጠቀሙ በፊት መጀመሪያ ክፉኛ ይሰብረዋል።»

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሮሜ 5፡3-5፤ ያዕ. 1፡2-4፤ 2ኛ ቆሮ. 1፡3-7 አንብብ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ መከራ የተለያዩ ዓላማዎች ምን ያስተምሩናል? እግዚአብሔር በመከራ አማካኝነት ሊፈጽም የሚፈልገው ተግባር ምንድን ነው? ለ) እግዚአብሔር አንተን ወይም ሌላ ክርስቲያንን ላዘጋጀው ተግባር ብቁ ለማድረግ ሲል በመከራ ውስጥ ሲያሳልፍ ያየኸው እንዴት ነው? ሐ) መከራ በሰው ባሕርይ ወይም አመለካከት ላይ የሚያስከትለው ለውጥ ምንድን ነው? መ) መከራ እግዚአብሔር በመንፈሳዊ ሕይወታችን እናድግ ዘንድ ለማገዝ የሚጠቀምበት መሣሪያ መሆኑ በቤተ ክርስቲያን ሲሰበክ የማንሰማው ለምንድን ነው? ክርስቶስን ከመከተል በምናገኛቸው መልካም ነገሮች፥ ማለትም የጸጋ ስጦታዎች፥ ፈውስ፥ ደስታ፥ ወዘተ. ላይ ብቻ የምናተኩረው ለምንድን ነው?

ከእግዚአብሔር ዘንድ በምናገኛቸው መልካም ነገሮች ላይ በምናተኩርበት በአሁኑ ዘመን፥ አስተምህሯችንን እግዚአብሔር ልጆቹን በመከራ መንገድ ወደ ብስለት ከሚመራበት ሁኔታ ጋር ሚዛናዊ ማድረግ አለብን። በአዲስ ኪዳን ውስጥ መከራ የምንሸሸው ሳይሆን የምንደሰትበትና የምንማርበት መንገድ ሆኖ ተጠቅሷል። መንፈሳዊ ባሕርይና ፍሬያማ አገልግሎት የሚገኙት በደስታና በምቾት ጊዜ ሳይሆን በመከራ ጊዜ ነው።

ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ የተጠቀመው መግቢያ ከሌሎች መልእክቶቹ የተለየ ነው። ጳውሎስ በእግዚአብሔር መለኮታዊ ምርጫ ስላገኘው የሐዋርያነት ሥልጣን አጽንኦት ሰጥቶ ከገለጸ በኋላ፥ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሰላምታ አቀረበላቸው። ከእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ ከጳውሎስ ጋር ኅብረት ያልነበራቸውና አገልግሎቱን የሚንቁ ነበሩ። ከጳውሎስ ጋር በአንዳንድ ጉዳዮች ባይሰማሙም እንኳን፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ መሆናቸውን ገልጾአል። ይሁንና፥ በሌሎች መልእክቶቹ እንደሚያደርገው ስለ ምንም ነገር አላመሰገናቸውም። (1ኛ ቆሮ. 1፡1-9ን ከ2ኛ ቆሮ. 1፡1-2 ጋር አነጻጽር።) ይህ ምናልባትም ለእነርሱ ግድ መሰኘቱንና ከአንዳንድ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጋር ሸካራ ግንኙነት እንደነበረው የሚያመለክት ይሆናል።

ጳውሎስ 2ኛ ቆሮንቶስን የጻፈው ከእስያ አውራጃ ተነሥቶ ወደ መቄዶንያ እንደገባ ነበር። ምናልባትም ጳውሎስ ከእስያ የወጣው በተቀበለው ከባድ መከራ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም፡፡ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ይህ መከራ ምንን እንዳካተተ አያብራራም። ነገር ግን ድሜጥሮስ በጳውሎስ ላይ ሁከትን እንዳስነሣ ይገልጻል። ጳውሎስም በዚያ ከአራዊት ጋር እንደታገለ አመልክቷል (1ኛ ቆሮ. 15፡32)። እነዚህ አራዊት እንደ አንበሳ ያሉ የዱር እንስሳት ወይም ከእግዚአብሔር እውነትና ከጳውሎስ ጋር የታገሉት ሰዎች ተምሳሌቶች ሊሆኑ ይችላሉ።

ጳውሎስ ስለ መከራ መናገሩ በ2ኛ ቆሮንቶስ ውስጥ በግልጽ ይታያል። የ2ኛ ቆሮንቶስ መልእክቱም በአብዛኛው በመከራ ላይ የተመሠረተ ነው። ከዚህ ክፍል ውስጥ የሚከተሉትን አጢን።

ሀ. ጳውሎስ በመከራ ጊዜ እግዚአብሔር አብ እንዳጽናናውና ርኅራኄን እንዳሳየው ገልጾአል (2ኛ ቆሮ. 1፡3)። ርኅራኄ በሌሎች መከራ የመካፈል ስሜታዊ ተግባር ነው። ምንም እንኳ እግዚአብሔር ከመከራዎች ሁሉ የላቀ ቢሆንም፥ ይህ ግን ስለ እኛ ደንታ የለውም ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን በመከራ ውስጥ ስናልፍ ኀዘናችንን ይካፈላል። እግዚአብሔር መከራን በግል ሊረዳ የሚችለው እንዴት ነው? በቀዳሚነት በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል እግዚአብሔር በምድር ላይ የምንጋፈጣቸውን የመከራ ዓይነቶች ሁሉ ተቀብሏል (ዕብ. 5፡7-9 አንብብ።) እግዚአብሔር በመከራችን ስለሚካፈል፥ መከራን በምንቀበልበት ጊዜ ወደ እኛ ተጠግቶ ያጽናናናል። በመከራ ውስጥ በምናልፍበት ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር እንደማይተወንና ዳሩ ግን ከእኛ ጋር እንደሚሠቃይ፥ ብሎም እንደሚያጽናናን መገንዘብ አለብን።

ለ. እግዚአብሔር በመከራ ውስጥ እንድናልፍ የሚፈቅደው በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል እንድንችል ነው። መከራ እየተቀበልን ለክርስቶስ ታማኞች ሆነን በምንጸናበት ጊዜ በመከራ ውስጥ የሚገኙትን ሌሎች ክርስቲያኖች ልናበረታታ እንችላለን። እንደኛ ዓይነት መከራ ካልተቀበለ ክርስቲያን መጽናናትን ማግኘቱ ከባድ ነው። እንዲህ ዓይነት ሰዎች የአእምሮ እውቀት ሊኖራቸውና ትክክለኛ አሳቦችን ሊያካፍሉን ቢችሉም፥ ንግግራቸው ብዙም ትርጉም የሚሰጠን አይሆንም። ነገር ግን አንድ ሰው እንደኛው ዓይነት መካራ እንደተቀበለ ስናውቅ፥ በሚነግረን ቃል እንጽናናለን። በመከራ ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ እግዚአብሔር እኛን የሚያጽናናበት ዐቢይ መንገድ መከራ የተቀበሉትን ሌሎች ክርስቲያኖች በመጠቀም ነው። ስለሆነም፥ መከራ የተቀበልን ሰዎች ሌሎችን በመርዳት መከራችንን የበረከት መሣሪያ ልናደርግ ይገባል።

መከራ አንድን ሰው መራር ወይም ርኅሩኅ ሊያደርግ ይችላል። መከራን ለመቀበል የማንፈልግ ከሆነ፥ እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ለመሥራት የሚጠቀምበትን መሣሪያ ተቃውመናል ማለት ነው። ነገር ግን የእግዚአብሔርን የመከራ መሣሪያ ብንቀበል፥ ብንጸናና ብንማርበት ርኅሩኆችና ሌሎችን ለማጽናናት የምናገለግል የእግዚአብሔር መሣሪያዎች እንሆናለን።

ሐ. መከራ ለሰዎች ሁሉ የማይቀር ግዴታ ነው። ክርስቶስ በሞተ ጊዜ እግዚአብሔር ተሠቃይቷል። ክርስቶስም ሰዎች በተሣለቁበት፥ በገፉትና በሰቀሉት ጊዜ ተሠቃይቷል። ምንም እንኳ ሐዋርያ ቢሆንም ጳውሎስ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆኖ በሚሠራበት ጊዜ መከራ ተቀብሏል። ጳውሎስ ከመከራ ጽናት የተነሣ በሕይወቱ ተስፋ ሊቆርጥ የደረሰበት ጊዜ እንደነበረ ገልጾአል። ጳውሎስ የቆሮንቶስም አማኞች በተመሳሳይ ሁኔታ መከራን እንደሚቀበሉ ተናግሯል። ስለሆነም፥ እያንዳንዱ ሰው የእኛን ማጽናናት ይፈልጋል። የምናጽናናቸው ወገኖች ደግሞ ሌሎችን ማጽናናት ይኖርባቸዋል። መከራ በክርስቶስ አካል ውስጥ የአገልግሎት በሮችን ይከፍታል።

መ. በመከራ ጊዜ በትዕግሥት የመጽናት ባሕርይ ሊኖረን ይገባል። በትዕግሥት የመጽናትን ባሕርይ ለማግኘት ደግሞ እግዚአብሔር ሁኔታዎችን በመቆጣጠር ላይ መሆኑን ተረድተን ልንገዛለትና ልንታመንበት ይገባል።

ሠ. እግዚአብሔር መከራ ውስጥ የሚከተን በራሳችን ሳይሆን ሙታንን በሚያስነሣ አምላክ እንድንደገፍ ለማስተማር ነው። በምቾት ጊዜ በችሎታችን፥ በብርታታችንና በጥበባችን ላይ ወደ መደገፍ እናዘነብላለን። ነገር ግን ሁኔታዎችና ችግሮች ከዓቅማችን በላይ በሚሆኑበት ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ ለመደገፍ እንገደዳለን።

ረ. መከራን በምንቀበልበት ጊዜ የመጨረሻው ድፍረታችን ትንሣኤ ነው። ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ለክርስቲያን ዐቢይ ጠላት ስላልሆነ መፍራቱ አስፈላጊ አይደለም። በበሽታ ወይም በስደት ምክንያት ብንሞት እንኳ ከትንሣኤ የተነሣ ሁሉንም አሸንፈን ለዘላለም ከእግዚአብሔር ጋር እንኖራለን።

ሰ. በስደት ጊዜ እርስ በርሳችን የምንረዳዳበት ትልቁ መሣሪያ ጸሎት ነው። እግዚአብሔር እኛ በማንረዳባቸው መንገዶች ጸሎታችንን ይጠቀማል። አንዳንድ ጊዜ በጸሎታችን አማካኝነት የክርስቲያኖችን መከራ ሲያቆም፥ በሌሎች ጊዜያት ደግሞ እግዚአብሔር ጸሎታችንን ተጠቅሞ ክርስቲያኖች በመከራ ውስጥ እርሱን የሚያስከብር ተግባር እንዲፈጽሙ ያደርጋቸዋል። አንዳንድ ጊዜም በሐዋርያት ሥራ 12፥19 በጴጥሮስ ሕይወት እንደተፈጸመው ጸሎት ክርስቲያኖችን ከመከራ ይታደጋቸዋል። በሌሎች ጊዜያት ግን (በሐዋርያት ሥራ 12፡1-2 በያዕቆብ ላይ እንደተፈጸመው) ተግተን እየጸለይን ሳለ እግዚአብሔር ክርስቲያኖች እንዲሞቱ ሊፈቅድ ይችላል።

የውይይት ጥያቄ፡- በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ መከራ የሚቀበሉትን ሰዎች ስም ዘርዝር። እነዚህ እውነቶች በዚህ የመከራ ጊዜ ጸንተው እንዲቆሙ የሚያበረታቷቸው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: