ንጋቱ ከአንድ ከታወቀ የመጽሐፍ ቅዱስ ኮሌጅ ተመርቆ የአንዲት ታላቅ ቤተ ክርስቲያን መጋቢ ሆነ። ንጋቱ በትምህርቱ ስለሚኩራራ ኮሌጅ ውስጥ የተማረውን የግሪክና የዕብራይስጥ ቋንቋ ለጉባኤው በማቅረብ ልታይ ባይነትን ያበዛ ነበር። ንጋቱ ይበልጥ እውቅና እያገኘ ሲሄድ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሽማግሌዎች የሚያቀርቡትን አሳብ መቀበሉን አቆመ። ብዙ ገንዘብና ሥልጣን ለማግኘት ሲል የተለያዩ ተግባራትን አከናወነ። አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ስሜታዊና ሞቅ ያሉ ስብከቶችን እንደሚወዱ በመገንዘቡ፥ በእግዚአብሔር ቃል እውቀታቸው እንዲያድጉ ከመጣር ይልቅ የሚያስደስታቸውን ትምህርት ብቻ ያቀርብላቸው ጀመር።
የውይይት ጥያቄ፡- ንጋቱ በተግባራቱ የገለጻቸው አንዳንድ የአገልግሎት መነሣሻ ምክንያቶች ምን ምንድን ናቸው?
ንጋቱ ሰይጣን ብዙውን ጊዜ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን ለማጥመድ ከሚጠቀምባቸው ፈተናዎች በአንዱ ተጠመደ። እግዚአብሔር የሰጠውን አገልግሎት ሰዎችን ለማስደነቅ፥ ምሁርነቱን ለማሳየት፥ ሀብትና ሥልጣን ለማግኘትና ሰዎችን ለማስደሰት ተጠቀመበት። ወደ ቆሮንቶስ የመጡት የሐሰት አስተማሪዎች በጳውሎስ ላይ ያቀረቡት ክስ እንዲህ ዓይነት ነበር። ስለሆነም ጳውሎስ የእውነተኛ አገልጋይ አመለካከትና ተግባራት ምን ዓይነት መሆን እንዳለባቸው ይዘረዝራል።
በቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኙ የሐሰት አስተማሪዎች ጳውሎስ ሐዋርያነቱን ለግል ጥቅም ማካባቻ እየተገለገለበት መሆኑን በመግለጽ የከሰሱት ይመስላል። ጳውሎስ የሚያገለግለው ሥልጣን፥ ክብርንና ገንዘብን ለማግኘት ነው እያሉ ሲያወሩ አልቀሩም። ጳውሎስ ለዚህ ምላሽ በመስጠት ስለ አገልግሎት የተማራቸውን አንዳንድ እውነቶችና በመሪነቱ ተጨማሪ ችግሮች እየደረሱበት እንኳን ለምን ወደኋላ እንዳላፈገፈገ ያብራራል።
ሀ. አገልግሎት የሚመነጨው ከሰው ምርጫ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጥሪ ነው (2ኛ ቆሮ. 4፡1)። ጥሪው የሚመጣው በእግዚአብሔር ምሕረት እንጂ ግለሰቡ የተማረ፥ በመሪዎች የተመረጠ፥ የወንጌላዊ ልጅ ወይም ለሥራው የተቀጠረ በመሆኑ አይደለም። አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ በእግዚአብሔር መጠራቱንና መሪነቱ የተሰጠውም በብቃቱ ሳይሆን በእግዚአብሔር ምሕረት መሆኑን ማወቅ አለበት። መሪው እግዚአብሔር ለአገልግሎቱ በኃላፊነት እንደሚጠይቀው ካላወቀ አገልግሎቱን ለራሱና ለቤተሰቡ ጥቅም ሊያውለው ይችላል። አንድ አገልጋይ አገልግሎቱን ከእግዚአብሔር እንደተቀበለና የሚያግዘውም እርሱ እንደሆነ በሚያስታውስበት ጊዜ ከፍተኛ መከራ ቢደርስበት እንኳን ተስፋ አይቆርጥም።
ለ. አንድ አገልግሎት እግዚአብሔርን ሊያስከብር እንዲችል በትክክለኛ ልብና አስተሳሰብ መካሄድ ይኖርበታል (2ኛ ቆሮ. 4፡2-6)።
- የእግዚአብሔር መሪዎች በፍጹም ታማኝነትና እውነተኛነት መሥራት ይኖርባቸዋል። መሪው ሌሎች ሰዎች ቢያውቁት የሚያፍርበት ምሥጢር ወይም ድርጊት ሊኖረው አይገባም። መሪው ሰዎችን በማታለልና በማስገደድ የራሱን ፈቃድ እንዲፈጽሙ ለማድረግ አገልግሎቱን መጠቀሚያ ማድረግ የለበትም። ጳውሎስ ሕይወቱ ማንንም በማያሳፍር መንገድ ግልጽ እንዲሆን ይፈልጋል። ሌሎች ክርስቲያኖችም ሆኑ ከሁሉም በላይ ክርስቶስ እንዲያፍርበት አልፈለገም።
- አገልግሎት የእግዚአብሔርን ቃል በግልጽ በማቅረብ ሊካሄድ ይገባል። ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል በተሳሳተ መንገድ ለመተርጎም አልፈለገም። የእግዚአብሔርን ቃል በአግባቡ ለማስተላለፍ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ ሊያውቃቸው የሚገቡ አያሌ ነገሮች አሉ።
በመጀመሪያ፥ የሚናገረው ትክክል ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔርን ቃል ማወቅ አለበት። ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሚገባ ባለመዘጋጀታቸውና ባለመረዳታቸው ምክንያት የእግዚአብሔርን ቃል ለመስበክ በሚሞክሩበት ጊዜ ያበላሹታል።
ሁለተኛ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪው ቃሉ የራሱ ሳይሆን የእግዚአብሔር እንደሆነ ማስታወስ አለበት። የቤተ ክርስቲያን መሪው ሰዎችን በእውቀቱ ለማስደነቅ ከመሞከር ይልቅ የእግዚአብሔርን ቃል ሁሉም ሰው በሚረዳው መንገድ ለማቅረብ መጣር አለበት። የተማሩት ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ምእመናኑም ቃሉን መረዳት ይኖርባቸዋል።
ሦስተኛ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪው ሰዎችን ለማስደሰት ሳይሆን ሕይወታቸውን ለመለወጥ ብሎ መስበክ አለበት። የሰዎችን ሕይወት የሚለውጠው ግልጽ የሆነ የእግዚአብሔር ቃል ትምህርት ነው። አንድ ሰው የዚህ ዘመን አለቃ በሆነው ሰይጣን ተቆጣጣሪነት ምክንያት ለማመን ባለመፈለጉ እንጂ በትምህርቱ አስቸጋሪነት ምክንያት ወንጌሉን ሳይረዳ መቅረት የለበትም።
አራተኛ፥ ሰባኪው ስለ ራሱ ወይም ስላከናወናቸው ተግባራት ታላቅነት ሳይሆን ስለ ክርስቶስ ማሰብ አለበት። ብዙውን ጊዜ ሰባኪያን በራሳቸው ላይ በማተኮር ስላከናወኑት ተግባራትና ስለ ሌሎች ነገሮች ይናገራሉ። ጳውሎስ ግን በክርስቶስ ላይ ብቻ በማተኮር ለሌሎች ስለ ጌትነቱ ለማስተማር ቆረጠ። ጨለማ በዋጠው ዓለም ውስጥ ብርሃንን የሚፈነጥቀው ስለ ክርስቶስ የሚሰጥ ትምህርት ብቻ ነው።
አምስተኛ፥ ጳውሎስ ራሱን የሚመለከተው ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው በእምነታቸው ያድጉ ዘንድ ለቤተ ክርስቲያን እንደተሰጠ የክርስቶስ ባሪያ ነበር። ራሱን ሥልጣንና ክብር እንዳለው ታላቅ መሪ አድርጎ አይመለከትም ነበር።
የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ሁላችንም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተለያዩ መንገዶች እንድናገለግል ጠርቶናል። ሀ) ስለ አገልግሎት እነዚህን እውነቶች ማስታወስ ያለብን ለምን እንደሆነ አስረዳ? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እነዚህን እውነቶች በመዘንጋት ችግሮችን የሚፈጥሩባቸውን ሁኔታዎች በምሳሌዎች አስረዳ።
ሐ. በእግዚአብሔር መንገድ የተካሄደ አገልግሎት ሥቃይ ቢኖርበትም እንኳ ድልን ያስገኛል (2ኛ ቆሮ. 4፡7-12)። ብዙውን ጊዜ ጳውሎስ ፈተና ያልገጠመው ታላቅ መንፈሳዊ ጀግና እንደሆነ እናስባለን። ጳውሎስ የእርሱም ሆነ የሌሎች አገልግሎት መገፋትን፥ መጨነቅን፥ መሰደድን፥ መውደቅንና መገለልን እንደሚያካትት ገልጾአል። ጳውሎስ የከፍተኛ ስደት ቁስሎች ደርሰውበታል። እነዚህም የሞት ምልክቶች ነበሩ። ጳውሎስ ብዙ ጊዜ በአገልግሎቱ ወደ ሞት እየቀረበ ሕይወቱን ለአደጋ አጋልጧል። ይህንንም ያደረገው ለግል ጥቅሙ ሳይሆን ሌሎች ወንጌሉን ሰምተው እንዲድኑ ነበር።
ጳውሎስ እግዚአብሔር ከእነዚህ ችግሮች ሁሉ ሊያድነው እየቻለ በመከራ ውስጥ እንዲያልፍ እንደፈቀደ ያውቅ ነበር። ስለ አገልግሎት አስደናቂው እውነት ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔር መከራን እንድንቀበል መፍቀዱ ነው። ጳውሎስ ሕይወቱን ከውኃ መቅጃ እንስራ ጋር ያነጻጽራል። ትንሽ ነገር ቢነካው እንስራው ይሰበርና ውኃው ይፈሳል። እግዚአብሔር የወንጌሉን «መዝገብ» በደካማ የሰው ሰውነት ውስጥ አስቀምጧል። ለምን? ለምን በማይሰበር የብረት ዕቃ ውስጥ አላስቀመጠም? እግዚአብሔር አንድ ውጤታማ ተግባር የሚከናወነው በእርሱ ኃይል እንጂ በእኛ ልዩ ብቃት እንዳልሆነ እንድናስተውል ይፈልጋል። ስለሆነም፥ ብዙ መከራ ብንቀበል እንኳ ይህ በሕይወታችን ውስጥ የሚከሰተው አስደናቂ ኃይልና ሁሉንም የሚያልፈው ብርታት ከእግዚአብሔር እንጂ ከእኛ እንዳልመጣ ለሰዎች ሁሉ ይታወቃል። ይህ ኃይል በሚኖርበት ጊዜ እንደማንወድቅ፥ እንደማንጨነቅ፥ እንደማንተውና እንደማንጠፋ እናውቃለን።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔርን በማገልገል ምክንያት መከራ የተቀበልህባቸውን መንገዶች ግለጽ። ለ) ለክርስቲያን አገልጋይ ሁላችንም እግዚአብሔር የወንጌሉን መዝገብ ያስቀመጠብን የሸክላ ዕቃ መሆናችንን ማስታወስ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)