መንፈሳዊ መሪ እግዚአብሔርንና ሰውን ለማስታረቅ የሚሻ የክርስቶስ አምባሳደር ነው (2ኛ ቆሮ. 5፡11-6፡2)።

ጳውሎስ ሰዎችን ለማስደሰት ብሎ ያገለግላል የሚል ወቀሳ ተሰንዝሮበት ነበር። ነገር ግን አንድ ቀን በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ እንደሚቀርብ ከተናገረ በኋላ፥ ጳውሎስ እግዚአብሔርን ብቻ እንደሚፈራ ገልጾአል። ሰውን መፍራት ወይም ሰውን ለማስደሰት መጣር ዘላለማዊ ፍርድ ያስከትልበት ነበር። ተጨማሪ መከራ ቢያስከትልበትም እንኳ ጳውሎስ ለክርስቶስ የሚያበረክተውን አገልግሎት በቅንዓት የቀጠለው ክርስቶስን ለማስደሰት በመፈለጉ ነበር። አንዳንድ የቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ጳውሎስ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በማየት አእምሮውን ስቷል ብለው ሳያስቡ አልቀሩም። ጳውሎስ ዓለም ዕብደት ነው ብላ በምታስብበት መንገድ እንዲሠራ ያነሣሱትን አንዳንድ ነገሮች ጠቃቅሷል።

ሀ. የክርስቶስ ፍቅር ግድ አለው። ጳውሎስ ራሱን ጨምሮ ክርስቶስ ሰዎችን ሁሉ በመውደዱ ምክንያት በመስቀል ላይ እንደሞተላቸው ያውቅ ነበር። በመንፈሳቸው ሙታን የሆኑት ሰዎች ሕያዋን ሊሆኑ የሚችሉት በክርስቶስ ሞት በማመን ብቻ ነበር። ስለሆነም፥ ምንም እንኳ ይህ መልእክት ሞኝነት ቢመስልም (1ኛ ቆሮ. 1፡18)፥ ለሰዎች ብቸኛው ተስፋቸው ነበር። ጳውሎስም በድፍረት መስበኩን የቀጠለው በዚህ ምክንያት ነበር።

ለ. ጳውሎስ ሰዎችን የተመለከተው ከቤተሰባቸው፥ ከጎሳቸው፥ ከሀብታቸው ወይም ከትምህርታቸው አንጻር በሥጋ ዓይኑ አልነበረም። ነገር ግን ጳውሎስ ሰዎችን የተረዳቸው የዳኑ ወይም ያልዳኑ፥ አዲስ ፍጥረት ወይም አሮጌ ፍጥረት ከመሆናቸው አንጻር ነበር። አንድ ሰው በክርስቶስ ሲያምን ከውስጡ የተለወጠ አዲስ ፍጥረት ይሆናል። መንፈሳዊ ሕይወት ከማግኘቱ በተጨማሪ አስተሳሰቡና አተገባበሩ ሁሉ ይለወጣል። በክርስቶስ ያላመነ ሰው ዘላለማዊ ሞት ያጠላበት ስለሆነ ወንጌሉን መስማት አለበት። ይህም ወንጌል እግዚአብሔር በክርስቶስ ሞት አማካኝነት ዓመፀኛ ኃጢአተኞች ከእርሱ ጋር ሰላምን እንዲያደርጉና የቤተሰቡ አባላት እንዲሆኑ የፈቀደበት ዕርቅ ነው።

ሐ. ጳውሎስ የክርስቶስ አምባሳደር መሆኑን ያውቅ ነበር። አምባሳደር የአንድ ከእርሱ የሚበልጥ ባለሥልጣን ወኪል ነው። የኢትዮጵያ መንግሥት አገሪቱን ለመወከልና ይፋዊ መልእክቶችን ለማስተላለፍ አምባሳደሮችን ወደ ሌሎች አገሮች ይልካል። በተመሳሳይ መንገድ፥ እያንዳንዳችን የክርስቶስ አምባሳደሮች ነን። የነገሥታት ንጉሥ ከሆነው ከክርስቶስ ተቀብለን ለሰው ልጆች የምናስተላልፈው መልእክት ደግሞ «ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ» የሚል ነው። የእግዚአብሔር ጠላቶች ክርስቶስ የኃጢአታቸውን ቅጣት እንደከፈለ በማመን ይታረቃሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙ ክርስቲያኖች ስለ ክርስቶስ ለመመስከር የሚያፍሩት ለምንድን ነው? ለ) ጳውሎስ አንዳንዶች ዕብድ ነው ብለው እስኪጠራጠሩት ድረስ ወንጌሉን ለማካፈል ስላደረገው ጥረት ከሰጠው ማብራሪያ ምን እንማራለን?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “መንፈሳዊ መሪ እግዚአብሔርንና ሰውን ለማስታረቅ የሚሻ የክርስቶስ አምባሳደር ነው (2ኛ ቆሮ. 5፡11-6፡2)።”

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading