የገላትያ መልእክት ዓላማ

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) «ወንጌል» ማለት ምን ማለት እንደሆነ አብራራ። ለ) አንድ ሰው ለመዳን ሰምቶ ስለሚያምነው ወንጌል በምናብራራበት ጊዜ ልናካትታቸው የሚገቡን እውነቶች ምን ምንድን ናቸው? ሐ) ስለ ወንጌሉ ምንነትና ሰዎች ሰምተው ይድኑ ዘንድ ስለሚቀርበው ምስክርነት አንድ ክርስቲያን ጥርት ያለ ግንዛቤ መጨበጥ የሚያስፈልገው ለምን ይመስልሃል?

የመጀመሪያው ዓላማ፡ ጳውሎስ ወንጌሉን በርዟል ለሚለው ክስ ምላሽ ለመስጠት። ጳውሎስ የእውነተኛ ወንጌልን ምንነት ለገላትያ ክርስቲያኖች አብራርቷል። እግዚአብሔር እንድን ሰው የሚቀበለው የተወሰኑ ውጫዊ ሕግጋትን ስለጠበቀ ሳይሆን፥ በክርስቶስ በማመኑ ነው። ጳውሎስ በመልእክቱ መልካሙ ዜና የሚያርፈው በክርስቶስ ሞትና ግለሰቡ ክርስቶስ ለኃጢአቱ እንደሞተ በሚያምንበት ጊዜ በሚሰጠው ጽድቅ (ከበደል መንጻት) ላይ እንዲሆነ ገልጾአል። በዚህ ቀላል እውነት ላይ በመጨመር፥ ሰዎች እንዲገረዙ ወይም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት እንዲጠብቁ መጠየቁ በወንጌል ላይ ሌላ ነገር መጨመር ይሆናል። ሰዎች በክርስቶስ እናምናለን ቢሉም እንኳ በእምነት መመዘኛ ላይ ሰብአዊ ተግባራት ከተጨመሩ መልካሙ የምሥራች ወንጌልነቱን ያጣል። ይህም እንደ ሌሎች የዓለም ሃይማኖቶች ሁሉ በሥራ ላይ የተመሠረተ ሃይማኖት ይሆናል። አንድ ሰው ለድነት (ደኅንነት) በራሱ ሥራ ላይ በሚታመንበት ጊዜ፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት የሌለው መንገድ በመምረጥ የክርስቶስ ሞት በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ ጠቀሜታ እንዳይኖረው ያደርጋል፡፡

የውይይት ጥያቄ፡- የሐዋርያት ሥራ 5፡1-35 አንብብ። ሀ) በኢየሩሳሌም የነበሩ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለምን በጉባኤ እንደ ተሰባሰቡ ግለጽ። ለ) በጊዜው የተነሣው መሠረታዊ የነገረ መለኮት ጥያቄ ምን ነበር? ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ስለዚሁ ጉዳይ ምን ወሰኑ? መ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አሕዛብ እንዲጠብቁ የጠየቁት ምን ምን ሕግጋትን ነበር? እነዚህን ሕግጋት ለምን ሰጧቸው?

የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን የታገለችው ከሁሉም የከበደ ጥያቄ፥ «አንድ ሰው ለመዳን ምን ማድረግ አለበት?» የሚለው ሳይሆን አይቀርም። አይሁዶች ከ1000 ለሚልቁ ዓመታት እንደ ግርዛት፥ የቤተ መቅደስ አምልኮ፥ አመጋገብ ላሉት ጉዳዮች ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቀበሏቸው ግልጽ መመሪያዎች ነበሯቸው። ከጳውሎስ በፊት በነበሩት 200 ዓመታት ውስጥ የአይሁድ መሪዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ለተጠቀሱት ሕግጋት ሌሎች በመቶዎች ሕግጋት ደንግገው ነበር። እነዚህ ተጨማሪ ሕግጋት እንድ መንፈሳዊ የሆነ አይሁዳዊ ሰው እንዴት ሊኖር፥ ምን ሊለብስና ምን ሊያደርግ እንደሚገባው ይዘረዝራሉ። የእነዚህ ተጨማሪ ሕግጋት ዓላማ የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን ማብራሪያ ማቅረብና በተወሰኑ ሁኔታዎች ውስጥ እንዴት እንደሚተገበሩ ለማሳየት ነበር። ለምሳሌ ያህል፥ ብሉይ ኪዳን ሰዎች በሰንበት ቀን እንዳይሠሩ አዟል። ምንም እንኳ በዚህ ትእዛዝ ውስጥ በዕልተ ሰንበት ውስጥ ስለተፈቀደውና ስለተከለከለው ሥራ አንዳንድ መመሪያዎች ቢሰጡም፥ ሌሎች ተጨማሪ ጉዳዮች ጥያቄዎችን ያስነሡ ነበር። ለምሳሌ፡ በሰንበት ቀን አንድ ሰው ስንት ኪሎ ሜትር እንዲሄድ ይፈቀድለታል? ስለሆነም የሃይማኖት መሪዎቹ በሰንበት አንድ ሰው ምን ያህል ርቀት መጓዝ እንደሚችል ወሰኑ። ከዚያ ርቆ ከሄደ ተግባሩ እንደ ሥራ ይቆጠርና ኃጢአትን እንደሠራ ይታወቃል። የብሉይ ኪዳን ሕግጋትና እነዚህ ተጨማሪ ሕጎች የአይሁዶች ባሕል ሆነው አሁን ይሁዲነት የምንለውን ነገር መሠረቱ። አይሁዶች ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት ለመፍጠር ሕግጋቱን በሙሉ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ያስተምራሉ። አንድ አሕዛብ ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ለመቀላቀል ሲፈልግ እንዲገረዝና እነዚህን ሁሉ ሕግጋት እንዲጠብቅ ይጠየቃል። ከዚያም ወደ እይሁድነት ይለወጣል። ብዙ አሕዛብ እግዚአብሔርን ስለሚወዱ እርሱን በሚያስከብር መንገድ ለመኖር ቢፈልጉም ሳይገረዙና ወደ አይሁድነትም ሳይለወጡ ቀርተዋል። «እግዚአብሔርን የሚፈሩ» ሰዎች ተብለው ቢታወቁም አይሁዶቹ ግን በፍጹም ከልብ አልተቀበሏቸውም ነበር።

እግዚአብሔር ሐዋርያ ጳውሎስን የአሕዛብ ሐዋርያ እንዲሆን እስከጠራው ጊዜ ድረስ፥ ሙሉ በሙሉ ማለት ይቻላል የቤተ ክርስቲያን ምእመናን አይሁዶች ብቻ ነበሩ። አይሁዶች ድነትን (ደኅንነትን) በሚቀበሉበት ጊዜ ጥቂት ለውጦች ማድረግ ያስፈልጋቸው ነበር። ወደ ቤተ መቅደስ ሊሄዱ፥ መሥዋዕቶችን ሊሠዉ፥ ሊገረዙ፥ ባሕላዊ የአይሁዶችን ሥርዓቶች ሊፈጽሙ፥ ለሥርዓታዊ ጉዳዮች ብለው ከአሕዛብ ሊለዩ፥ ወዘተ… ይችላሉ። የቀድሞ ልምምዳቸውን ሳይተዉ ክርስቶስ ለኃጢአታቸው የሞተላቸው መሢሕ እንደሆነ ተቀብለው አመኑ። ጥቂት አሕዛብ ድነትን (ደኅንነትን) በተቀበሉበት ወቅት ለአይሁዶች የተሰጡትን የብሉይ ኪዳን ሕግጋት እንዲከተሉ ተጠየቁ። ስለሆነም፥ መገረዝ፥ ንጹሕ ያልሆኑትን ምግቦች አለመመገብ፥ ወዘተ ይጠበቅባቸው ጀመር።

ነገር ግን ጳውሎስ ወንጌልን ወደ ገላትያ በወሰደ ጊዜ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአይሁዶች የሚበልጡ አሕዛብ የሚገኙባቸውን ምእመናን ያስተናግዱ ጀመረ። እነዚህ አሕዛብ የራሳቸውን ባሕል የመከተል እንጂ ወደ አይሁድነት የመለወጥ ፍላጎት አልነበራቸውም። በግሪክ ባሕል ግርዛት ተገቢ አልነበረም። አይሁዶች የማይበሏቸው እንደ አሳማ ሥጋ ያሉት ነገሮች ለግሪኮች ተወዳጅ ምግቦች ነበሩ። አሕዛብ በክርስቶስ ለማመንና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ወደ አይሁድነት መለወጥ ያስፈልጋቸው ነበር? ወይስ ድነት (ደኅንነት) እግዚአብሔር የተወሰኑ ሕግጋትን ለጠበቁት ሳይሆን በክርስቶስ ላመኑት ሁሉ የሚሰጣቸው ነፃ ስጦታ ነበር? ቤተ ክርስቲያን ክርስቲያኖችን በተለያዩ ደረጃዎች መመደብ ያስፈልጋት ነበር? ባሕላቸውን የለወጡ፥ የተገረዙና የአይሁዶችን ሕግጋት የሚታዘዙ «መንፈሳዊ» ክርስቲያኖችና በክርስቶስ እያመኑ የአይሁድን ባሕል ለመከተል የማይፈልጉ «ክርስቶስን የሚፈሩ» በማለት ክርስቲያኖችን በተለያዩ ደረጃዎች መመደብ ያስፈልጋቸው ነበር?

ጳውሎስ አሕዛብን ወደ አይሁድነት እንዲለወጡ ማስገደዱ በክርስቶስ እንዲያምኑ የሚከለክል የማሰናከያ ዓለት እንደሚሆን ተገንዝቦ ነበር። ጳውሎስ ድነት (ደኅንነት) የሰው ሥራ ሳይሆን የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነ ያውቅ ነበር። አንድ ሰው ባህላቸውን መለወጥ አያስፈልገውም ነበር። አይሁዶችም እንኳ እንደ መገረዝ ያሉትን ሕግጋት በመጠበቅ ድነት (ደኅንነትን) ሊያገኙ ስለማይችሉ፥ በክርስቶስ ለማመን አንድ ሰው ባሕሉን መቀየር አያስፈልገውም ነበር። እግዚአብሔር የኃጢአትን ይቅርታ፥ የክርስቶስን ጽድቅ፥ የእግዚአብሔርን ልጅነት መብትና የዘላለም ሕይወት በስጦታ ለመስጠት አንድ ሰው በትሕትናና በእምነት ወደ እርሱ እንዲመለስ ይጠይቃል።

በኢየሩሳሌም የሚገኙ አንዳንድ የአይሁድ ክርስቲያኖች፥ በተለይም ፈሪሳውያን ወይም ካህናት ሆነው በክርስቶስ ያመኑ አይሁዶች ይህን ትምህርት ለመቀበል ይቸገሩ ነበር (የሐዋ. 15፡5)። አንዳንዶቹ ጳውሎስን ተከትለው ወደ አሕዛብ አገሮች ሁሉ ይጓዙ ጀመሩ። ወደ ሶርያ፥ አንጾኪያና የገላትያ አብያተ ክርስቲያናት በመሄድ አሕዛብ ድነትን (ደኅንነትን) እና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት በግርዛትና የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን በመቀበል ወደ አይሁድነት መለወጥ እንዳለባቸው አስተማሩ።

ጳውሎስ ይህ አደገኛ ትምህርት አሕዛብ በክርስቶስ እንዳያምኑ ከማድረጉም በላይ የወንጌሉን ምንነት እንደሚለውጥ ተገነዘበ። ጳውሎስ ይህንን ከፋፋይ ጉዳይ ሐዋርያት ወደሚገኙባት የኢየሩሳሌም ከተማ ወሰደ። የሐዋርያት ሥራ 15 በዚህ ጉዳይ ላይ ስለተካሄደው ጉባኤ ያብራራል። ሐዋርያትና የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች፥ «አንድ ሰው ለመዳን ምን ማድረግ አለበት? የሚለውን ሥነ መለኮታዊ ጥያቄ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መረመሩ።

ይህ የኢየሩሳሌሙ ጉባኤ በሁሉም ዘመናት የሚኖሩ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የሃሳብ ልዩነት በሚከሰትበት ጊዜ ነገረ መለኮታዊ ጉዳዮችን እንዴት መፍታት እንዳለባቸው የሚያሳይ መልካም ምሳሌ ነው። ክፍፍሉ እንዲቀጥልና የኋላ ኋላ በራሱ ጊዜ እንዲጠፋ ዝም ብለው አልተዉትም። ሰዎቹ የሃሳብ ልዩነቶቻቸውን አጥብበው በሰላም እንዲኖሩ አላባበሏቸውም። ነገር ግን በፍጥነት ተሰብስበው የነገረ መለኮታዊ ጉዳዩን ሥር በመመርመር ውሳኔዎችንና ተግባራዊ እርምጃዎችን አድርገዋል። ከዚህ የመጀመሪያው ጉባኤ የምንማራቸው አንዳንድ ጠቃሚ መርሆዎች ከዚህ በታች ቀርበዋል።

ሀ. ሁሉም ወገኖች አመለካከታቸውን እንዲገልጹ ዕድል ተሰጥቷቸዋል። አሕዛብ ሊገረዙና የሙሴን ሕግጋት መከተል አለባቸው የሚሉ አይሁዶች በአንድ በኩል፥ ጳውሎስና ሌሎች ደግሞ በሌላ በኩል አመለካከቶቻቸውን አብራርተዋል።

ለ. ከዚያም የተከበሩ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እግዚአብሔር ቀደም ሊል ምን እንዳስተማራቸው ተናገሩ። ጴጥሮስ ወንጌሉን ወደ ቆርኔሌዎስ ስላመጣበት ሁኔታና (የሐዋ 10) እግዚአብሔር ቆርኔሌዎስንና ሌሎች አሕዛብን ተቀብሎ ወደ አይሁድነት እንዲለወጡ ወይም የሙሴን ሕግጋት እንዲጠብቁ ሳይጠይቅ መንፈስ ቅዱስን ስለሰጠበት ክስተት ገለጻ አደረገ። አስፈላጊው ነገር እምነት ብቻ ነው።

ሐ. ጉባኤው የእነዚህ ሰዎች አቋም ያስከተለውን ፍሬ መረመረ። ጴጥሮስ አይሁዶች እንኳ የብሉይ ኪዳንን፥ ብሎም የተጨመሩትን ሕግጋት በመጠበቅ እግዚአብሔርን ሊያስደስቱና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ሊያገኙ እንደማይችሉ ገለጸ። ይህም ሊሸከሙት የማይችሉት ቀንበር ነበር።

መ. መሪዎቹ የሰዎችን ምሥክርነት ይሰሙ ነበር። ጳውሎስ ወንጌል በገላትያ እንዴት እንዳስፋፋ ገለጸላቸው። ሳይገረዙ መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ላይ ይወርድ ነበር። እግዚአብሔር ተአምራትን በመካከላቸው ከመሥራቱ የተነሣ፤ አሕዛብ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመታዘዝና ለማፍቀር ከፍተኛ ጉጉት ነበራቸው።

ሠ. ጉባኤው መጽሐፍ ቅዱስን መረመረ። ያዕቆብ ስለ አሕዛብ መዳን የሚናገሩትን ቁልፍ የብሉይ ኪዳን ምንባቦች አብራራ።

ረ. መሪዎቹ ከጸሎትና ከውይይት በኋላ ውሳኔ ሰጡ። በውይይታቸው ወቅት ከነበረው አንድነታቸው በመነሣት መንፈስ ቅዱስ ውሳኔውን እንደሰጣቸው ተገነዘቡ። ቁልፍ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ድነት (ደኅንነት) የእግዚአብሔር ስጦታ እንደሆነና ለአሕዛብ የመዳንን መንገድ አስቸጋሪ ማድረግ እንደሌለባቸው ወሰኑ።

ሰ. የኢየሩሳሌሙ ጉባኤ ሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ወሳኔውን ተረድተው እንዲከተሉ በይፋ አስታወቀ። አይሁድና አሕዛብ ክርስቲያኖች ወደሚገኙባቸው አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ ውሳኔውን ገልጸው ደብዳቤ ጻፉ። ደብዳቤውን እውቀት፥ መንፈሳዊነትና የማብራራትና ጥያቄዎችን የመመለስ ብቃት የነበራቸው ሰዎች ይዘው ወደየአብያተ ክርስቲያናቱ ዞሩ። ከተላኩት መሪዎች መካከል አንዳንዶቹ (ጳውሎስና በርናባስ) ሥነ መለኮታዊውን ጥያቄ ያነሡ ሲሆን፥ ሌሎቹ (ይሁዳና ሲላስ)፥ የዚህ ጉዳይ ተካፋዮች አልነበሩም። ይህም እንደኛው ወገን ነገሮችን ባለመረዳቱ ወይም በተሳሳተ መንገድ በመረዳቱ ሳቢያ የሚከሰት ወቀሳ እንዳይኖር አድርጓል።

ሸ. ጉባኤው በአይሁድና በአሕዛብ ክርስቲያኖች መካከል ሊኖር ስለሚገባው አንድነት አንዳንድ ነገሮችን ለማመቻመች ተገደደ። እውነት ብቻ ሳይሆን ፍቅርና አንድነትም አስፈላጊዎች ናቸው። አብያተ ክርስቲያናቱ ሁለት የተለያዩ ባሕሎች ባሏቸው አይሁዶችና አሕዛብ የተገነቡ በመሆናቸው፥ አሕዛብ አይሁዶችን ሊያስቆጡ የሚችሉትን አንዳንድ ነገሮች ከመፈጸም እንዲታቀቡ ተጠየቁ። ያዕቆብ እንዳለው፥ እነዚህ አይሁዶች በብሉይ ኪዳን ላይ የተመሠረቱ ጥልቅ ግንዛቤዎች ነበሯቸው (ከጥንት ዘመን ጀምሮ የሙሴ ሕግ በሁሉም ከተማ የሚሰበክ ሲሆን በሰንበት ቀናት ደግሞ በምኩራቦች ይነበብ ነበር)።

የሚያሳዝነው ይህ በድነት (ደኅንነት)ና የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን በመጠበቅ መካከል ስላለው ግንኙነት የሚያስረዳው ጠቃሚ ሥነ መለኮታዊ ጉዳይ በፍጥነት እልባት አላገኘም። አንዳንድ አይሁዶች ወደየቤተ ክርስቲያናቱ እየዞሩ አሕዛብ ለመዳን ወይም መንፈሳዊ ለመሆን የተወሰኑ የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን መጠበቅ እንዳለባቸው ማስተማራቸውን ቀጠሉ። ጳውሎስ በጻፋቸው በሁሉም መልእክቶች ማለት ይቻላል፥ ስለዚሁ የሕግና የክርስቲያናዊ ነጻነት ጉዳይ ጠቅሷል።

ይህ ድነት (ደኅንነት) በሥራ ሳይሆን በእምነት እንደሚገኝና አሕዛብ ወደ አይሁዳዊነት መለወጥ ሳያስፈልጋቸው በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንደሚያገኙ የሚያስረዳው ትምህርት በጣም ከባድ በመሆኑ፥ እንደ ጴጥሮስና በርናባስ ያሉት መሪዎች እንኳን ሳይቀሩ ለጊዜው ግራ ተጋብተው ነበር። ጳውሎስ የአይሁድን ልማድ በመከተል በአንጾኪያ በአይሁዶችና በአሕዛብ መካከል ክፍፍልን በመፍጠሩና ድነት (ደኅንነት) በእምነት የመገኘቱን እውነት በማመቻመቹ ጴጥሮስን እንደ ገሠጸው አመልክቷል።

ያዕቆብና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለአብያተ ክርስቲያናት በጻፉት ደብዳቤ ለአማኞች ሁለት ዓይነት ትእዛዛትን ሰጡ። የመጀመሪያዎቹ፥ ሁልጊዜም ለሰዎች ሁሉ የሚያገለግሉ ግልጽ ትእዛዛት ነበሩ። ስለሆነም፥ አሕዛብ አማኞች ዝሙትን እንዳይፈጽሙ ጠየቋቸው። የሁለተኛዎቹ፥ ክርስቶስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በግልጽ ያልጠቀሳቸውና አይሁዶች ለመቀበል የሚቸገሩባቸው እንደ ለጣዖት የተሠዋ ሥጋ፥ የታነቀ እንስሳ ሥጋና ደም የመሳሰሉ ነገሮች ነበሩ። እነዚህ ነገሮች ለድነት (ደኅንነት) አስፈላጊ እንዳልሆኑና ነገር ግን በአይሁዶችና በአሕዛብ መካከል ሰላምንና አንድነትን ለመፍጠር የተሰጡ ትእዛዛት መሆናቸውን መረዳቱ ጠቃሚ ነው። ደብዳቤው አይሁዶቹ ጥንታዊ ባሕላቸውንና የብሉይ ኪዳን ሕግጋትን የመከተል መብት እንዳላቸው ያሳያል። አሕዛብ አይሁዶች እንዲለወጡ የማስገደድ መብት አልነበራቸውም። አይሁዶችም ቢሆኑ አሕዛብ ለመዳን ባሕላቸውን መለወጥ እንዳለባቸው የማስገደድ መብት አልነበራቸውም።

ይህ ነገረ መለኮታዊ ሃሳብ ቤተ ክርስቲያን ልትገነዘባቸው ከሚገቧት እጅግ መሠረታዊና ጠቃሚ እውነቶች አንዱ ነው። ሁሉም ሃይማኖቶችና የሰው ተፈጥሮ እግዚአብሔር በነፃ የሰጠውን ስጦታ በሥራ ወደሚገኝ ነገር የመለወጥ ዝንባሌ ይታይባቸዋል። ለዚህ ነው ወንጌሉን በምንመሰክርበትና ሰዎች ክርስቲያኖች በሚሆኑበት ጊዜ ስለሚለውጧቸው ነገሮች ማብራራት አደገኛ የሚሆነው። በዚህ ጊዜ አዲስ የሚያምነው ግለሰብ ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት በክርስቶስ ከማመኑ በተጨማሪ አንዳች ተግባር ማከናወን እንዳለበት ያስባል። ግለሰቡ ድነትን ካገኘና በእምነቱ ማደግ ከጀመረ በኋላ እግዚአብሔር እንዲለውጥ ስለሚፈልጋቸው ተግባራትና አመለካከቶች ልንነግረው እንችላለን። ነገር ግን በእነዚህ ነገሮች ላይ መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ማብራሪያ ካልሰጠና የቤተ ክርስቲያናችንን ልማድ ብቻ የምናስተምር ከሆነ፥ ክርስትናን እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ የምንመላለስበት ሕይወት ሳይሆን የሕግጋት መጠበቂያ ሃይማኖት እንዳናደርገው መጠንቀቅ ይኖርብናል።

ከእኛ የተለየ ባሕል ወዳለው ጎሳ ወንጌሉን ይዘን በምንሄድበት ጊዜ ሁሉ ይህንን ተግባራዊ ጉዳይ ማስታወስ አለብን። ሁላችንም የእኛ መንገድ ከሁሉም የተሻለ መስሎ ይሰማናል። ባሕላችን የተወሰነ አለባበስ፥ የፀጉር አቆራረጥ፥ በግብርና ወይም በንግድ ሥራ ላይ መሰማራት ለሰዎች የእግዚአብሔር ፍላጎት እንደሆነ ያስተምራል። እግዚአብሔር ሰዎች «እንዲሠለጥኑ» ይፈልጋል ብለን እናስባለን። በዘላኖች መካከል የሚሠሩ አንዳንድ ወንጌላውያን ሕዝቡ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት የወንጌላውያኑን ባሕል እንዲቀበሉ ይጠይቃሉ። ፀጉራቸውን የሚቀቡበትን ጭቃ እንዲያስወግዱ፥ ከንፈሮቻቸውን በጥተው ወጭት እንዳያስቀምጡ፥ የብር አምባሮቻቸውን እንዲጥሉ፥ ልብስ እንዲለብሱ፥ የከብቶቻቸውን ወተትና ደም እንዳይጠጡ፥ ወዘተ… ይከለክላሉ። እነዚህ ሁሉ ባሕላዊ ጉዳዮች ናቸው። ሰዎች ድነትን (ደኅንነትን) ወይም በቤተ ክርስቲያን ተቀባይነት ለማግኘት ባሕላቸውን እንዲቀይሩ የማስገደድ መብት የለንም። ብዙ ወንጌላውያንና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ዘላኖች ባሕላቸውን እንዲቀይሩ በመጠየቅ የማሰናከያ ዓለት እኑረውባቸዋል። የሁሉንም ባሕሎች አባላት የሚቀበል ወንጌል አይሰብኩም። ወንጌሉ ባሕሎች ሁሉ ከተገለጠው የእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር የሚቃረኑ ነገሮችን (ለምሳሌ፥ የጣዖት አምልኮ፥ የወሲብ ኃጢአት) እንዲተዉ ይጠይቃል። ነገር ግን ሌሎች የባሕላዊ ልምምዶችን የማስቀረት ምርጫ ለአማኙ መተው ይኖርበታል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የቤተ ክርስቲያንህ አማኞች በአሳብ የሚለያዩበትን አንድ ጉዳይ ምረጥ። ለ) ከላይ የተዘረዘሩትን ደረጃዎች በመጠቀም፥ መንፈስ ቅዱስ ይህንን ጉዳይ ቤተ ክርስቲያንህ እንዴት እንድታስተካክል እንደሚፈልግ አብራራ። ሐ) በአሁኑ ሰዓት ይህ ጉዳይ የሚስተናገደው እንዴት ነው? ጉዳዩ እየተስተናገደ ያለበት ሁኔታ መልካም ይመስልሃል ወይስ ወደፊት ወደ ተጨማሪ ችግሮች የሚያመራ ይመስልሃል? መልስህን አብራራ።

ሁሉም አሕዛብ የመጀመሪያው የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ባስተላለፈው ውሳኔ አመስጋኞች መሆን ይገባቸዋል። ይህ ጉባኤ አሕዛብ ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት ወደ አይሁድነት መለወጥ እንዳለባቸው የሚያመለክት ውሳኔ ቢያስተላልፍ ኖሮ፥ ወንጌሉ ኢትዮጵያን ጨምሮ ወደ አሕዛብ አገሮች ሁሉ መድረሱ አጠራጣሪ ነበር። ወንጌሉ በአይሁዶች ብቻ ይገደብ ነበር።

ዛሬ አብያተ ክርስቲያናትን የሚከፋፍሉ ብዙ ሥነ መለኮታዊ ጉዳዮች አሉ። እንደ ልሳን፥ ፈውስን የመሳሰሉ መንፈሳዊ ስጦታዎች፥ ኢየሱስ ብቻ የሚሉና የይሖዋ ምስክሮች ትምህርቶች በዘመናችን አብያተ ክርስቲያናትን ሲከፋፍሉ ይታያል። አብያተ ክርስቲያኖቻችን ለእነዚህ ጉዳዮች በመግባባት ላይ የተመሠረተ ሁነኛ አቋም ካልወሰዱ በምእመናን መካከል ተጨማሪ ክፍፍል መፈጠሩ የማይቀር ነው። ምንም እንኳ በክርስቲያናዊ ፍቅር መንፈስ ላለመስማማት ብንስማማም ልዩነቶች እንዳሉ ተቀብሎ ችግሮችን ለመፍታት መጣሩ አይሻልምን? እውነት ለእግዚአብሔር አስፈላጊው ነገር ነው። ነገር ግን እግዚአብሔር በልጆቹ መካከል ፍቅርና አንድነት እንዲኖርም ይፈልጋል። እውነት ወይም ፍቅር ከጎደለብን እግዚአብሔርን እንደሚፈልገው ልናመልከው አንችልም።

ሁለተኛ ዓላማ፡ ጳውሎስ ሐዋርያ ሳይሆን የሐሰት አስተማሪ ነው ለሚለው ክስ ምላሽ ለመስጠት። የአይሁድ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ጳውሎስን ስለ ሁለት ነገሮች ከስሰውት ነበር። በመጀመሪያ፥ የሐሰት አስተማሪዎቹ ጳውሎስ የክርስቶስ ሐዋርያ መሆኑን አላመኑም ነበር። እንደ እነርሱው በኢየሩሳሌም ካሉት እውነተኛ ሐዋርያት ሥልጣን ሥር እንደማይሠራ በመግለጽ ኮነኑት። ሁለተኛ፥ የጳውሎስ መልእክት የተሳሳተ ከመሆኑም በላይ የእውነተኛ ሐዋርያት ድጋፍ እንዳልተሰጠው ገለጹ። ጳውሎስ ወንጌሉ ሥራን ሳይጨምር በእምነት ብቻ ሰዎች የሚድኑበት እንደሆነ የመግለጽ ሥልጣኑ የመጣው በቀጥታ እግዚአብሔር ስለ ላከው እንደሆነ ማረጋገጥ ነበረበት። ጳውሎስ የሕይወት ምስክርነቱን በመስጠት ለእነዚህ ሁለት ክሶች ምላሽ ሰጥቷል። ከኢየሱስ ክርስቶስ መልእክት የተሰጠው እውነተኛ ሐዋርያ መሆኑን አመልክቷል። ጳውሎስ ወንጌሉን ከክርስቶስ ተቀበለው እንጂ ራሱ አልፈጠረውም። በኢየሩሳሌም ሐዋርያት ሳይላክ ወይም ባይመረጥም፥ ከእነርሱ አያንስም ነበር። መልእክቱም የመነጨው ከሐዋርያቱ ሳይሆን በቀጥታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የሚሰብከው ወንጌል ከሰው ወደ ሰው በመተላለፍ የተበረዘ ወንጌል አልነበረም። በሌላ በኩል፥ ጳውሎስ የሚሰብከው ወንጌል ሌሎች ሐዋርያት ከሚያስተምሩት ጋር የሚስማማ እንጂ የሚጋጭ አልነበረም። ጳውሎስ ከሐዋርያቱ ጋር በተገናኘ ጊዜ እርሱነቱንና አገልግሎቱን ተቀብለውታል።

ሦስተኛ ዓላማ፡ ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው በእምነት ብቻ ነው የሚለው የጳውሎስ ትምህርት ወደ ኃጢአተኝነት አኗኗር የሚመራ ነው ለሚለው ምላሽ ለመስጠት። ምንም እንኳ ድነት (ደኅንነት) የሚገኘው አንድ ሰው ክርስቶስ ስለ እርሱ እንደ ሞተ አምኖ በሚቀበልበት ጊዜ እንደሆነ ቢታወቅም፥ እግዚአብሔር ሰዎች የተለወጠ ሕይወት እንዲኖሩ ይፈልጋል። እምነት በፍቅር አማካኝነት ራሱን መግለጽ አለበት (ገላ. 5፡6)። እግዚአብሔር የኃጢአተኛ ሥጋችንን ተግባራት ለመቀነስና የመንፈስ ቅዱስን ፍሬ ለመስጠት ሲል መንፈስ ቅዱስን ልኮልናል (ገላ. 5፡22-23)።

የውይይት ጥያቄ፡- ለክርስቲያኖች በእነዚህ ሦስት የገላትያ መልእክት ዓላማዎች ውስጥ የሚገኙትን ትምህርቶች መረዳት ለምን ይጠቅማል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: