የኤፌሶን መልእክት ጸሐፊ እና ተቀባይ

የኤፌሶን መልእክት ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡– ኤፌሶን 1፡1 አንብብ። ሀ) የኤፌሶን መልእክት ጸሐፊ ማን ነው? ለ) ራሱን እንዴት ገለጸ? ኤፌ. 1፡1ን ከገላ. 1፡1 ጋር አወዳድርና ጸሐፊው ራሱን እንዴት እንደሚገልጽ አብራራ።

እንደ ሌሎች ደብዳቤዎች ሁሉ፥ ጳውሎስ የኤፌሶንን መልእክት የጀመረው ጸሐፊነቱን በመግለጽ ነበር። እንደ ሌሎች ጊዜያት ሁሉ «ሐዋርያ» የሚለውን ማዕረጉንም ጨምሮ ጠቅሷል። ጳውሎስ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መመረጡንና የኢየሱስ ክርስቶስ ሹም ሆኖ መላኩን አመልክቷል። ጳውሎስ መልእክቱን በዚህ መንገድ የጀመረው በታላቅ ሥልጣኑ ለመመካት ሳይሆን፥ ደብዳቤው ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን የተላከ የክርስቶስ መልእክት መሆኑን ለማስረዳት ነው። ይህም አማኞቹ ሰምተው እንዲታዘዙት ነው።

ጳውሎስን መልእክቱን ለማን ጻፈ?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ ይህን መልእክት የጻፈው ለማን ነው? ለ) ጳውሎስ የመልእክቱን ተቀባዮች የገለጸው እንዴት ነው? ሐ) የሐዋ. 18፡18-20፡1 አንብብ። ወንጌሉ መጀመሪያ ወደ ኤፌሶን የደረሰው እንዴት ነው? ጳውሎስ በዚያ ለምን ያህል ጊዜ አገለገለ?

ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው «ለኤፌሶን ቅዱሳን» ነበር። «ቅዱስ» የተለየ የሚል ፍች ሲኖረው፥ እነዚህ ክርስቲያኖች ፍጹም ወይም ኃጢአት እልባ መሆናቸውን አያመለክትም። ነገር ግን ክርስቲያኖች በእግዚአብሔር እንደ ተመረጡና ለእግዚአብሔር ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ እንደ ተለዩ ያሳያል።

ብዙውን ጊዜ ይህ መልእክት ለኤፌሶን እማኞች እንደተጻፈ እናስባለን። ኤፌሶን፥ ጳውሎስ በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ውስጥ ለሦስት ዓመታት ያገለገለባት ቦታ ናት። ስለሆነም፥ ይህ መልእክት ጳውሎስ ወደ መሠረታት ቤተ ክርስቲያን የተጻፈ ይመስላል። ነገር ግን አንዳንድ ምሁራን ይህ መልእክት በቀጥታ ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን እንዳልተላከ በመግለጽ አያሌ ምክንያቶችን ይሰነዝራሉ። በመጀመሪያ፥ አንዳንድ ጥንታዊ የኤፌሶን መልእክት ቅጂዎች «ኤፌሶን» የሚል ቃል የለባቸውም። ነገር ግን «በኢየሱስ ክርስቶስ ለታመኑት ቅዱሳን» የሚል ሐረግ ተጽፎባቸዋል። ሁለተኛ፥ ጳውሎስ የሚጽፍላቸውን ሰዎች በአካል የሚያውቅ አይመስልም። በአካል ተገኝቶ እንደ ተመለከተ ሳይሆን፥ ስለ እምነታቸውና ፍቅራቸው እንደ ሰማ ይናገራል (ኤፌ. 1፡15)። በተጨማሪም፥ ጳውሎስ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት የሚናገሩትን እውነቶች (ኤፌ. 4፡21፥ ብሎም ስለ አገልግሎቱ መረዳታቸውን እንደሰማ ይናገራል (ኤፌ. 3፡2)። ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው ለሦስት ዓመታት ላገላገላት ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ቢሆን ኖሮ፥ ስለ ኤፌሶን ክርስቲያኖች እምነትና ፍቅር ራሱ ይመሰክር ነበር። ሦስተኛ፥ በተጨማሪም በመልእክቱ ውስጥ የግል ሰላምታም ሆነ ሁነኛ ችግሮች አልተጠቀሱም። ከእነዚህ ምክንያቶች የተነሣ ብዙ ምሁራን ይህ መልእክት ወደ ተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት የሚዟዟር እንደ ነበር ይናገራሉ። ጳውሎስ መልእክቱን መጀመሪያ ዐቢይ ቤተ ክርስቲያን ወደምትገኝባት ኤፌሶን ላከ። እዚያ ከተነበበ በኋላ ደብዳቤው በእስያ ውስጥ ወደሚገኙ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት (ምናልባትም በራእይ ውስጥ የተጠቀሱትን ሰባት አብያተ ክርስቲያናት ጨምሮ) ተላከ (ራእይ 1፡1)። በቆላስይስ 4፡16፣ ጳውሎስ ለሎዶቂያ ክርስቲያኖች ስለተጻፈ ሌላ መልእክት ጠቅሷል። አንዳንድ ምሁራን ይህ ኤፌሶን ብለን የምንጠራው ተዘዋዋሪ መልእክት እንደሆነ ያስባሉ።

ጳውሎስ እነዚህን ክርስቲያኖች «በክርስቶስ የታመኑ» ይላቸዋል። በክርስቶስ ማመን ብቻ ሳይሆን፥ ከእርሱ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማጥበቅ በታማኝነት ይከተሉት ነበር። የሚያሳዝነው የኤፌሶን ሰዎች ለኢየሱስ የነበራቸው ታማኝነት ዘለቄታ አልነበረውም። ከ40 ዓመታት ያህል በኋላ ክርስቶስ ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ልዩ መልእክት ልኳል። ለእርሱ የነበራቸውን የመጀመሪያ ፍቅር በማጣታቸው ወቅሷቸዋል። ንስሐ ገብተው ፍቅራቸውን ካላደሱ በፍርድ እንደሚመጣባቸው አስጠንቅቋቸዋል (ራእይ 2፡1-7 አንብብ)። ቤተ ክርስቲያን ዛሬ ታማኝ መሆኗ ብቻ በቂ አይደለም። ለክርስቶስ ያለን ፍቅር በቀጣይነት ሊያድግና ሊጠናከር ይገባል። ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በጠንካራ አቋም ጀምረው ከጥቂት ጊዜ በኋላ እየተዳከሙ ሄደዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ስለ ቤተ ክርስቲያንህ አስብ። ሀ) ክርስቶስ ከእርሱ ጋር ያለህን ግንኙነት እንዴት ይገልጻል? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ ከዚህ በፊትና አሁን ከእግዚአብሔር ጋር የምታደርገውን ግንኙነቷን አነጻጽር። እየተዳከመች ነው ወይስ እየበረታች? እየተዳከመች ከሆነ፥ የእግዚአብሔር ፍርድ እንዳይደርስባት ግንኙነት ለማደስ ስለ ምን ነገሮች ንስሐ ልትገባ ይገባል?

ጳውሎስ በወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ከየትኛውም ስፍራ በላይ በኤፌሶን ብዙ ጊዜ ቆይቷል። ጳውሎስ በአሁኗ ቱርክ ውስጥ የነበረችውን ኤፌሶንን እንደ ቁልፍ የአገልግሎት ስፍራ ነበረ የተመለከተው። ኤፌሶንን መናኸሪያ አድርጎ በመጠቀሙ ወንጌል በእስያ አውራጃ ውስጥ በፍጥነት ሊሰራጭ ችሏል (የሐዋ. 19፡10)።

የኤፌሶን ከተማ ዋነኛ የወደብ ከተማና የእስያ አውራጃ መዲና ነበረች። አብዛኛው የንግድ እንቅስቃሴ ከምዕራብ ቱርክ ወደ ኤፌሶን ከመጣ በኋላ ከዚያ ወደ ጥንቱ ዓለም ሁሉ ይሰራጭ ነበር። ጳውሎስ በዚያ በሚሠራበት ጊዜ ቢያንስ የ1100 ዓመታት ዕድሜ የነበራት ጥንታዊ የታሪክ ከተማ ነበረች። ብዙ አይሁዶችና ሌሎችም ከ500,000 የሚበልጡ ሰዎች በከተማይቱ ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ይገመታል። በዚያ ከነበሩት አይሁዶች አንዳንዶቹ ወደ ክርስትና እምነት ሲመጡ፥ አብዛኞቹ ግን የወንጌሉ ጠላቶች ሆነው ክርስቲያኖችን ያሳድዱ ነበር።

ኤፌሶን ዳያና በተባለች ጣዖት አምልኮም ትታወቅ ነበር። ዳያና የምትመለክበት ቤተ መቅደስና ሐውልቷ እጅግ አስደናቂ በመሆናቸው ከሰባቱ የጥንቱ ዓለም አስደናቂ ነገሮች እንደ አንዱ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠሩ ነበር። ዳያና የሚለው ሮማዊ ስምም ሆነ አርጤምስ የሚለው የግሪክ መጠሪያ የፍሬያማነትን አምላክ የሚያመለክት ነበር። ሴቶች ዳያናን በማምለካቸው ልጅ መውለድ እንደሚችሉ ይታመን ነበር። ከዳያናና ከሌሎች ጣዖታት በተጨማሪ ኤፌሶን ዋነኛ የጥንቆላና የምትሐት ማዕከል ነበረች። የኤፌሶን ሰዎች በክርስቶስ ካመኑ በኋላ ቢያንስ 50,000 ብር የሚገመቱ የምትሐት መጻሕፍት እንዳቃጠሉ ተነግሮናል። በኋላም የሮም ንጉሥ አምልኮ ከተጧጧፈባቸው ከተሞች አንዱ ኤፌሶን ነበረች። በዚህ ሃይማኖት ንጉሡን ለማምለክ ባለመፍቀዳቸው እንደ ዓመፀኞች በታዩት ክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ስደት ተከስቷል።

ጳውሎስ መጀመሪያ በኤፈሶን ወንጌልን የሰበከው በሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው መጨረሻ አካባቢ ነበር። ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ እግረ መንገዱን ከጵርስቅላና አቂላ ጋር ወደ ኤፌሶን ጎራ አለ (የሐዋ. 18፡18-19)። አንድ ጊዜ ለአይሁዶች ከሰበከ በኋላ ሰዎች እንዲቆይ ቢፈልጉም ወደ ኢየሩሳሌም አመራ። ጵርስቅላና አቂላ ግን እዚያው ቆዩ። በዚህ ጊዜ ከመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት አንዱ የነበረው አጵሎስ የሚባለው ወደ ኤፌሶን መጥቶ ማስተማር ጀመረ። ጵርስቅላና አቂላ ስለ ክርስቶስ የበለጠ ካስተማሩት በኋላ አጵሎስ በኤፌሶን ወንጌሉን እንዲያስፋፋ እግዚአብሔር በሚገባ ተጠቀመበት። ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ ወደ ቆሮንቶስ ለአገልግሎት ሄደ።

ጳውሎስ በኤፌሶን ዐቢይ የአገልግሎት መሠረት የጣለው በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው ነበር። በኤፌሶን ሲሰብክና ሲያስተምር ለሦስት ዓመታት ቆየ። ይህም በየትኛውም የአገልግሎት ጉዞው ካደረጋቸው ቆይታዎች ሁሉ የበለጠ ነበር። ብዙ ሰዎች የንግድ ማዕከል ወደነበረችው ኤፌሶን የንግድ ተግባራቸውን ለማከናወን ሲመጡ ወንጌሉን ይሰብክላቸው ነበር። እነርሱም ወንጌሉን ይዘው ወደመጡበት አገር ይመለሳሉ። ከዚህም የተነሣ ወንጌሉ በእስያ አገሮች ሁሉ ተስፋፋ (የሐዋ. 19፡10)። ምናልባትም በራእይ ውስጥ የተጠቀሱት ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናትና የቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን የተመሠረቱት በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። በኤፌሶን አገልግሎቱ መጨረሻ አካባቢ ተቃውሞ እየተጠናከረ በመሄዱ በከተማይቱ ውስጥ ብጥብጥ ተነሣ። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ጳውሎስ የግሪክን አብያተ ክርስቲያናት ጎብኝቶ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ።

ጳውሎስ የኤፌሶንን መልእክት የጻፈበት ዘመንና ስፍራ

የውይይት ጥያቄ፡– ኤፌ 3፡1 እና 4፡1 አንብብ። ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው የት ሆኖ ነበር?

ጳውሎስ ይህን መልእክት በጻፈ ጊዜ የሆነ ስፍራ ታስሮ ነበር። ግን የት እንደ ታሰረ? አያሌ ግምቶች አሉ። ቂሣሪያ ወይም ሮም ታስሮ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲደርስ መታሰሩን አስታውሰ። ለጥቂት ጊዜ በኢየሩሳሌም ታስሮ ከቆየ በኋላ ቂሣሪያ ወደተባለችው የሮም የአውራጃ ከተማ ተወስዶ ለሁለት ዓመታት ያህል ታስሯል (የሐዋ. 24፡27)። የእስር ቤት መልእክቶቹን የጻፈው በዚህ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም። ከሁለት ዓመታት በኋላ፥ ጳውሎስ በንጉሥ ችሎት ይዳኝ ዘንድ ወደ ሮም ተላከ። እዚያም ለሁለት ተጨማሪ ዓመታት ራሱ በተከራየው ቤት ታስሮ ቆየ (የሐዋ. 28፡30-31)። አብዛኞቹ ምሁራን ጳውሎስ አራቱን የወኅኒ ቤት መልእክቶች ሮም ሆኖ በ60 ወይም 61 ዓ.ም እንደ ጻፈ ያምናሉ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading