የእምነት ሕይወት የንጽሕናና ሌሎችን የማገልገል ነጻነት ያመጣል (ገላ. 5፡1-15)

ዘነበ የዩኒቨርስቲ ክርስቲያን ተማሪዎች ኅብረት አባል ነበር። ከሳምንታዊ አምልኳቸው በአንዱ አንድ ግለሰብ በክርስቶስ ስለሚገኝ ነጻነት ሰበከ። ሰባኪው፥ «ከሕግ ነፃ ስለሆናችሁ የፈለጋችሁትን ሁሉ ልታደርጉ ትችላላችሁ። ክርስቶስ ለኃጢአታችሁ እንደ ሞተ እስካመናችሁ ድረስ ምንም ዓይነት ሕግ መጠበቅ አያስፈልጋችሁም። ስለሆነም፥ ‹አትዋሽ፥ አትስረቅ፤ አታመንዝር የሚሉ የእግዚአብሔር ሕግጋት ከእንግዲህ በእኛ ላይ ተፈጻሚነት የላቸውም። እነዚህን ሕግጋት መጠበቅ አያስፈልገንም። በተጨማሪም፥ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኘው በነፍሳችሁ እንጂ በሥጋችሁ አይደለም። ስለሆነም፥ እስከ ጸለያችሁ፥ በልሳን እስከ ተናገራችሁ፥ በመዝሙር እስካመለካችሁና ልባችሁ ንጹሕ መሆኑን እስካረጋገጣችሁ ድረስ፥ በሥጋችሁ የምታደርጉት ነገር አሳሳቢ አይሆንም» ሲል አብራራ። ዘነበ እግዚአብሔር እንዳሻው እንዲኖር የፈቀደለት መሆኑን በማመን ከኅብረቱ ሴት አባላት ጋር ማመንዘር ጀመረ። እግዚአብሔርን የሚገድደው ስላልመሰለው የፈተና መልሶችንም መስረቅ ጀመረ።

የውይይት ጥያቄ ሀ) ሰባኪው ለዘነበ ያስተማረው ሃሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ይመስልሃል? ለ) በሕግጋት ካልዳንን አማኞች ከሆንን በኋላ ሕግጋት በሕይወታችን ውስጥ ምን ዓይነት ሚና እንዳላቸው ግለጽ።

በገላትያ የመጀመሪያው ክፍል (ገላ. 1-4)፥ ጳውሎስ «ሰው ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት ምን ማድረግ አለበት?» ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል። የጳውሎስ ምላሽ፥ «ክርስቶስ ለኃጢአትህ እንደ ሞተ ብታምን እግዚአብሔር ድነትን እንደ ነፃ ስጦታ ይሰጥሃል። «ጥፋተኛ አይደለህም› ሲል ያውጃል። ድነትን ለማግኘት መፈጸም የሚኖርብህ ተግባር ወይም መጠበቅ የሚኖርብህ ሕግ የለም» የሚል ነው። በዚህ በሁለተኛው የገላትያ መልእክት ክፍል (ገላ. 5-6)፥ ጳውሎስ፦ «ክርስቲያን ከሆንሁ በኋላ እንደ እግዚአብሔር ልጅ እንዴት መመላለስ ይኖርብኛል?» ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ይሰጣል።

አንድ ሰው በሥራ ሳይሆን በጸጋ ከዳነ በኋላ የሚያደርገው ነገር አሳሳቢ አይደለም የሚለው አመለካከት በጳውሎስ ዘመን የተለመደ ነበር።

በኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እንዲህ ዓይነት አመለካከት እየተስፋፋ መጥቷል። በክርስቶስ ነፃ ወጥተናል የሚለውን አሳብ ሰዎች እንደፈለግን ልንኖር እንችላለን ማለት ነው ብለው ይተረጉማሉ። ብዙውን ጊዜ የዚህ አመለካከት አራማጆች እግዚአብሔር ትኩረት የሚሰጠው ለመንፈሳችን፥ ከእርሱ ጋር ስላለን ግንኙነት ስለ አምልኳችንና ስለ ውዳሴያችን እንደሆነ ይናገራሉ። በሥጋችን ስለምናደርገው ነገር አያሳስበውም ይላሉ። ምንም እንኳ ብዙዎቻችን ይህን አሳብ በይፋ ባንናገርም፥ ራሳቸውን ክርስቲያኖች ብለው የሚጠሩና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተሟሟቀ አምልኮ የሚያካሂዱ ሰዎች የዓመፅ ኃጢአት (ለምሳሌ፥ ዝሙት፥ ውሸትና የመሳሰሉትን) የሚፈጽሙት፥ ባይታዘዙትም እንኳ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ባለው ግንኙነት እንደሚረካ ስለሚያስቡ ነው። ይህ የተሳሳተ ትምህርት ነው። በክርስቶስ በማመን ብንድንም፥ የዳንነው በነፍሳችን፥ በሥጋችንና በሁለንተናችን እግዚአብሔርን ለማክበር ነው። ክርስቲያናዊ ነጻነት ማለት እግዚአብሔር እንዳሻን እንድንኖር ይፈቅድልናል ማለት አይደለም። ነገር ግን ክርስቲያናዊ ነጻነት ማለት ከሰይጣን ባርነት ነፃ ወጥተን እግዚአብሔርን የሚያስከብርና ክርስቶስን እንመስል ዘንድ ለተፈጠርንለት ዓላማ ለመኖር ነፃ መሆን ማለት ነው። እግዚአብሔር ቅዱስ እንደሆነ እኛም እንደ እርሱ ለመሆን ነፃ እንሆናለን።

ክርስቲያኖች፥ «በክርስቶስ በማመኔና በእግዚአብሔር ነፃ ማዳን ምክንያት እንደ ዳንሁ አውቃለሁ። ከዚያ በኋላ ግን ቤተ ክርስቲያኔ የምትሰጠኝን ሕግና ትእዛዝ በመፈጸም እግዚአብሔርን ማስደሰት አለብኝ። መገረዝ፥ የተወሰነ የአለባበስ ስልት መከተል፥ ፀጉሬን በአግባቡ መያዝ፥ ወደ ቤተ ክርስቲያን ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መሄድ አለብኝ፥» ሊሉ ይችላሉ። አሕዝብ የነበሩት የገላትያ ክርስቲያኖች አይሁዳዊ ክርስቲያን አስተማሪዎቻቸውን ደስ ለማሰኘት በመፈለጋቸው ለመገረዝ እያሰቡ ነበር። የጳውሎስ ትምህርት አያሌ ዐበይት እውነቶችን ያካትታል።

ሀ. ጳውሎስ ውጫዊና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ሕግጋት በመጠበቅ ሌሎችን ለማስደሰት ለተፈተኑት ክርስቲያኖች፥ «በነጻነት ልንኖር ክርስቶስ ነጻነት አወጣን፤ እንግዲህ ጸንታችሁ ቁሙ እንደገናም በባርነት ቀንበር አትያዙ።» ብሏል (ገላ. 5፡1-12)። ጳውሎስ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር የማይጠብቅባቸውን ሕግጋት ለመከተል በመሞከር ለባርነት እንዳይዳረጉ ያስጠነቅቃቸዋል። ጳውሎስ አሕዛብ የነበሩት የገላትያ ክርስቲያኖች እንዳይገረዙና በወግ አጥባቂነት የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት እንዳይከተሉ ያዛቸዋል። ለመገረዝ ከፈቀዱ ሁለት ነገሮች እንደሚከሰቱ ያስረዳል።

  1. የብሉይ ኪዳንን ሕግጋት ሙሉ በሙሉ መጠበቅ ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ የሚወዷቸውን ሕግጋት ሊጠብቁና የማይወዷቸውን ሊተዉ አይችሉም ነበር። እነዚህን ሕግጋትና ደንቦች ለመጠበቅ በመሞከራቸው ለጠቅላላው ሕግ ባሪያዎች ይሆኑ ነበር።
  2. የክርስቶስ ሞት ጥቅም አይሰጣቸውም ነበር። መገረዝ ትንሽ ነገር ቢመስልም፥ የሚገረዙበትና ሕግን የሚጠብቁበት ምክንያት ጥልቅ አስከትሎቶችን ይመዝ ነበር። ይህም ለደኅንነታቸው በክርስቶስ ለማመን አለመፈለጋቸውንና እነዚህን ሕግጋት በመጠበቅ ከእግዚአብሔር ዘንድ ጽድቅን ሊያገኙ እንደ ፈለጉ ያመለክት ነበር። የተወሰኑ ተግባራት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን እንደሚያስገኝላቸው ያስቡ ነበር።

በብሉይ ኪዳን ሦስት ዓይነት ዐበይት ሕግጋት ነበሩ። በመጀመሪያ፥ የግብረገብ ሕግጋት ነበሩ። እነዚህ ሕግጋት ሰዎች ከእግዚአብሔርና እርስ በርሳቸው የሚዛመዱባቸውን መንገዶች የሚደነግጉ ነበሩ። በዘጸአት 20፡1-17 የተገለጹት አሥርቱ ትእዛዛት ለእነዚህ ሕግጋት ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው። በአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች ይታዘዟቸው ዘንድ ተደግመው የተገለጹት ሕጋጋት እነዚህ ብቻ ናቸው። ሁለተኛ፥ ማኅበራዊ ሕግጋት ነበሩ። እነዚህ ሕግጋት እስራኤላውያን እንዴት አብረው እንደሚኖሩ፥ ምን እንደሚመገቡ፥ የሀብት ክርክሮችን እንዴት እንደሚያስተናግዱ፥ በሚታመሙበት ጊዜ ምን ማድረግ እንደሚገባቸው፥ መሪዎች እንዴት እንደሚመረጡ፥ ወዘተ… የሚያሳዩ ነበሩ። ሦስተኛ፥ ሃይማኖታዊ ሕግጋትም ነበሩ። እነዚህ የአይሁዶችን አምልኮ፥ ለእግዚአብሔር መሥዋዕቶችን እንዴት እንደሚያቀርቡ፥ ምን ዓይነት ሃይማኖታዊ በዓላትን እንደሚጠብቁ፥ ወዘተ… የሚያሳዩ ነበሩ። ከግብረገባዊ ሕግጋት ውጭ ያሉትን ሕግጋት ክርስቲያኖች መጠበቅ አያስፈልጋቸውም። ነገር ግን ከእነዚህ ሕግጋት ውስጥ የምናወጣቸውና ለፍትሐዊ ማኅበራዊ ሕይወት የሚጠቅሙ መርሆች አሉ። በሌላ በኩል፥ ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት ብለን እስካልተጠቀምንባቸው ድረስ ብዙዎቹን ማኅበራዊ፥ ሃይማኖታዊና ቤተ ክርስቲያንህ የምትደነግጋቸውን ሕግጋት መጠበቁ ጉዳት የለውም። ይህ በታሪክ ሁሉ ብዙ ሰዎች የተሳሳተ አስተምህሮ እንዲከተሉ ያደረገ የተሳሳተ ግንዛቤ ነው።)

ለ. በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት መገረዝ ወይም አለመገረዝ ለውጥ የለውም። መገረዝን እንደ አስፈላጊ ባሕላዊ ተግባር ስለተመለከቱት በአይሁዶች ዘንድ ሥጋዊ ግርዛት ተቀባይነት ነበረው። አይሁዶቹ ይህን ልማድ ለማድረግ ነጻነት ነበራቸው። የአሕዛብ ክርስቲያኖች የራሳቸውን ባሕል ለመከተልና ልጆቻቸውን ላለማስገረዝ ሲፈልጉ፥ ይህም በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ነበረው፡፡ መገረዝ ወይም አለመገረዝ ፈጽሞ ከድነት (ደኅንነት) ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። ነገር ግን አንድን ነገር የምናደርግበት ምክንያት የተሳሳተ ከሆነ፥ ተግባሩም የተሳሳተ ይሆናል። ለምሳሌ፥ እግዚአብሔርን ለማስደሰት፥ ድነት (ደኅንነትን) ለማግኘት ወይም መንፈሳዊ ለመምሰል ብለን ለመገረዝ ብንፈልግ፥ የእግዚአብሔርን ቃል በተሳሳተ መንገድ ተረድተናል ማለት ነው። እግዚአብሔር ለሁለት ነገሮች ትኩረት ይሰጣል።

1) በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን እናገኝ ዘንድ ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ እንደ ሞተልን በፍጹም ልባችን ማመን። ጳውሎስ እምነት ድነት (ደኅንነት) ያገኘንበትን ሁኔታ የሚያመለክት ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም የተስፋችን መሠረት እንደሆነ ያስረዳል። ክርስቶስን የምንመስልበትን፥ የጽድቅ ተግባራት የምንፈጽምበትንና ከእርሱ ጋር ለዘላለም የምኖርበትን የድነት (ደኅንነት) ሂደት ፍጻሜ ልንመለከት የምንችለው በእምነት ነው። ስለሆነም፥ በመንፈሳዊ ጉዟችን ለእግዚአብሔር በምናከናውናቸው ተግባራት ወይም በምንጠብቃቸው ሕግጋት ላይ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር ለእኛ በፈጸመው ተግባር፥ በቅድስና እንድንመላለስና ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር ለመግለጽ የሚያስችሉንን ተግባራት እንድንፈጽም በረዳን እግዚአብሔር ላይ እናተኩራለን።

2) የእምነታችን እውነታ የሚገለጽበት ፍቅር። እግዚአብሔርን በሙሉ ልባችን፥ ነፍሳችን፥ ሥጋችንና አሳባችን እንድንወድ ታዘናል (ዘዳግ 6፡5፤ ማቴ. 22፡37)። ሌሎችንም እንድንወድ ታዘናል (ማቴ. 22፡37-40)።

በገላትያ ክርስቲያኖች መካከል ውዝግብን የሚፈጥር አንድ ቀንደኛ ሰው የነበረ ይመስላል። ጳውሎስ ለዚህ ሰው ጠንካራ ቃላትን ሰንዝሯል። እግዚአብሔር ለሚያስፋፋው የሐሰት ትምህርት ይቀጣዋል።

ሐ. ክርስቲያናዊ ነጻነት ራሳችንን ለማስደሰት ወይም የኃጢአት ባሕርያችንን ለማስተናገድ ማመኻኛ አይሆንም (ገላ. 5፡13-15)። እግዚአብሔር ምን ይፈልጋል? ለእርሱ የሚሰጠው ቅድሚያ ምንድን ነው? እምነታችንን የምንገልጽበት ዐቢይ መንገድ ምንድን ነው? ይህ መንገድ አምልኮ ነው? ጸሎት ነው? ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ ነው? ወይስ ትክክለኛ ልብሶችን መልበስ? እነዚህ ጠቃሚ ነገሮች ቢሆኑም እምነታችንን የምንገልጽባቸው ዐበይት መንገዶች አይደሉም። ጳውሎስ አንዳችን ሌላውን በፍቅር በማገልገል እምነታችንን ልንገልጽ እንደሚገባን አስረድቷል። እግዚአብሔር ከሌሎች ሰዎች ጋር ሊኖረን የሚገባውን ግንኙነት፥ «ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ» በሚል ቃል አጠቃልሎታል። በመጽሐፍ ቅዱስ፥ ፍቅር በቀዳሚነት ለሰዎች ያለን ስሜት ሳይሆን ተግባርና አመለካከት ነው። ሰዎችን ስንወድ እንቀበላቸዋለን፤ ሌሎችን ስንወድ በሰላም ለመኖር እንችል ዘንድ ለእነርሱ ትክክለኛ የሆነውን ነገር እናደርጋለን። ፍቅር ሁልጊዜም ዋጋ ያስከፍለናል። የተቸገሩትን ስንረዳ ወይም ለምስክርነት ስንወጣ ጊዜያችንን እንሠዋለን። ለድሆች ወይም ለወንጌል ስርጭት ገንዘባችንን ስንሰጥ ዋጋ እንከፍላለን። አንዳንድ ጊዜ ለሰዎች ስንል የምንፈልጋቸውን ነገሮች ለመተው እንገደዳለን። ጳውሎስ የገላትያ ክርስቲያኖች ፍቅርን አጥተው እርስ በርሳቸው እየተጣሉ በመሆናቸው እንዳይጠፉ አስጠንቅቋቸዋል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading