እግዚአብሔርን እያስደሰትን እንድንኖር ከሚያነሣሡን እጅግ ጠንካራ ምክንያቶች አንዱ ቀደም ሲል የነበርንበትን ሁኔታ ከአሁኑ የእግዚአብሔር ልጅነት ሕይወታችን ጋር ማነጻጸር ነው። ከማመናችን በፊት ፈጽሞ ምስኪኖች እንደ ነበርንና የእግዚአብሔር ጸጋ ድነትን እንደ ሰጠን፥ እንዲሁም ስለ ዘላለማዊ በረከቶቻችን በተሻለ ሁኔታ ስንረዳ፥ በዚህ መንገድ የሚወደንን አምላክ ደስ ለማሰኘት እንሻለን።
የውይይት ጥያቄ፡– ኤፌ. 2፡1-3 አንብብ። ጳውሎስ ስላልዳኑት ሰዎች የገለጻቸው አምስት ነገሮች ከመዳንህ በፊት በሕይወትህ ውስጥ እንዴት እንደ ተንጸባረቁ አብራራ።
ሀ. ከመዳናችን በፊት የነበርንበት የምስኪንነት ሕይወት (ኤፌ. 2፡1-3)።
- በበደላችንና በኃጢአታችን ሙታን ነበርን። የሞተ ሰው ሕይወት ስለሌለው ለራሱ የሚጠቅሙትን ነገሮች ሊመርጥ አይችልም። ጳውሎስ በክርስቶስ ከማመናችን በፊት፥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ፍጹም ሙታን እንደ ነበርን ያስረዳል። ወንጌሉን ሰምተን ልንረዳ አንችልም ነበር። በክርስቶስ ለማመን ልንመርጥ አንችልም ነበር።
- ሙሉ በሙሉ በኃጢአት ቁጥጥር ሥር እንኖር ነበር። የኃጢአት ባሕርይ እስረኞች ነበርን።
- «በማይታዘዙትም ልጆች ላይ አሁን ለሚሠራው መንፈስ አለቃ እንደሆነው በአየር ላይ ሥልጣን እንዳለው አለቃ ፈቃድ»፥ ማለትም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር እንኖር ነበር።
- የኃጢአት ተፈጥሯችን የሚፈልገውን እየሠራን ለራሳችን ብቻ ደስ በመሰኘት እንኖር ነበር።
- የቁጣ ልጆች ነበርን። የእግዚአብሔር መለኮታዊ ቁጣና ፍርዱ በእኛ ላይ ነበር። የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነው። ምንም ዓይነት ተስፋ ስላልነበረን የምንጠባበቀው ነገር ቢኖር እግዚአብሔር በዘላለማዊ ፍርዱ ወደ ሲኦል እንዲልክን ነበር።
ለ. ካመንን በኋላ ያገኘናቸው በረከቶች (ኤፌ. 2፡4-10)።
ጳውሎስ «ነገር ግን» በሚል ቃል ይህንን ክፍል ይጀምራል። መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት «ነገር ግን» እና «እንግዲህ» (ስለሆነም) የሚሉ ቃላት በጣም ጠቃሚዎች ናቸው። «እንግዲህ» የሚለው ቃል የአንድን አሳብ መደምደሚያ ያሳያል። ይህ አንድ ነገር እውነት በመሆኑ፥ እግዚአብሔር የተለየ ውጤት እንደሚመጣ ይናገራል። (ሮሜ 8፡1 አንብብ። ከ«እንግዲህ» በፊትና በኋላ የተከሰተው ልዩነት ምንድን ነው?) እዚህ በኤፌሶን 2፡4 ጳውሎስ «ነገር ግን» የሚለውን ቃል ተጠቅሟል። ይህም ከ «ነገር ግን» በፊትና በኋላ ያሉት ጉዳዮች ያላቸውን ከፍተኛ ልዩነት ያስረዳል። ጳውሎስ ሁላችንም ተስፋ በሌለው ሁኔታ ውስጥ እንደ ነበርን ካሳየ በኋላ፥ የእግዚአብሔር ጸጋና ፍቅር ያመጣውን ልዩነት ለማመልከት «ነገር ግን» የሚለውን ቃል ተጠቅሟል።
የልዩነቱ ምንጭ የእግዚአብሔር «ታላቅ ፍቅር» እና «የምሕረቱ ባለጸግነት» ነበር። ልዩነቱ የተገኘው ከእኛ መልካምነት ወይም እግዚአብሔር የሚወደውን ምርጫ ለመምረጥ በመቻላችን አይደለም። እኛ ሙታን በመሆናችን ይህን ልናደርግ እንችልም ነበር። ነገር ግን ያገኘናቸው በረከቶች ሁሉ ከእግዚአብሔር ምሕረትና ፍቅር የመነጩ ናቸው። ምሕረት ለማይገባው ሰው መልካምን ነገር ማድረግ ነው። ስሜት ብቻ ሳይሆን እርዳታ ለማይገባቸው ወገኖች እጅን መዘርጋት ነው።
ለመሆኑ ከእግዚአብሔር ፍቅርና ምሕረት የተነሣ ያገኘናቸው በረከቶች ምን ምንድን ናቸው?
- እግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር አስነሣን። ክርስቶስ ከሞት እንደ ተነሣ ሁሉ እኛም ከመንፈሳዊ ሙትነታችን ተነሥተናል። ይህም ወንጌሉን እንድንሰማ፥ እንድንገነዘብና እንድናምን አስችሎናል።
- እግዚአብሔር በጸጋው አድኖናል። ይህ በመልካምነታችን፥ ከትክክለኛው ጎሳ በመወለዳችን ወይም በአኗኗራችን ለውጥ የምናገኘው አይደለም። ድነት (ደኅንነት) የእግዚአብሔር ነፃ ስጦታ ስለሆነ፥ ማንም በክርስትናው ሊመካ አይችልም። እንደ አልጄሪያ ክርስቲያኖች ከሌሉበት አገር ይልቅ ወንጌሉን ልንሰማ በምንችልበት አገር እንድንኖር ያደረገው የእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ነው። እግዚአብሔር እያመፅንበት ሳለ የመረጠንና ልጆቹ ያደረገን በማይገባን ምሕረቱ ብቻ ነው። እግዚአብሔር እኛን ፈለገን እንጂ እኛ እግዚአብሔርን አልፈለግነውም።
- በሰማያት ከክርስቶስ ጋር የተቀመጥን ስለሆነ፡ የታላቅ ቸርነቱን (የጸጋውን የማይነገር ባለጠግነት) ለዘላለም እናያለን። ጳውሎስ ይህን የሚለው ከክርስቶስ ጋር በሞቱ፥ በቀብሩ፥ በትንሣኤውና በዕርገቱ መተባበራችንን በምሳሌነት በመጠቀም ነው። አንድ ቀን ወደ ሰማይ እንደምንሄድና የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ ጸጋና በረከቶች እንደምናገኝ ቢታወቅም፥ ጳውሎስ በእግዚአብሔር ዓይኖች ቀድሞውኑ ወደ ሰማይ ሄደን በረከቶቹን እየተቀበልን መሆናችንን ያስረዳል።
- እግዚአብሔር ቀደም ሲል ያዘጋጀውን «መልካሙን ሥራ» እናደርግ ዘንድ በጥንቃቄ ቀርጾናል። የጳውሎስ ገለጻ የሚያሳየው እንድን እንጨት በጥንቃቄ ቀርጾ ውብና ጠቃሚ ዕቃ የሚሠራውን ዋነኛ አናጺ ነው። እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ በጣም ግላዊ ተሳትፎ ያደርጋል። ለእያንዳንዳችን የተለየ ስብዕና፥ ስጦታ፥ ሥልጠና፥ ልምድ፥ ወዘተ… በመስጠት ይቀርጸናል። እነዚህ ሁሉ ዓላማ አላቸው። እግዚአብሔርን እንድናገለግል (መልካሙን ሥራ እንድንሠራ) ይረዱናል። የሚያስደንቀው ግን እግዚአብሔር ከፈጠረን ሁኔታ ጋር በሚጣጣም መልኩ እናገለግለው ዘንድ ነገሮችን ይመርጣል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር አንተን ስለፈጠረበት ሁኔታ አንዳንድ ልዩ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? ለ) እግዚአብሔርን ለማገልገል ይህንን እየተጠቀምህ ያለኸው እንዴት ነው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)