በክርስቶስ አካል ያለ አንድነት (ኤፌ. 4፡1-16)

ጳውሎስ የኤፌሶን ክርስቲያኖች ለወንጌሉ እንደሚገባ ይመላለሱ ዘንድ ጠየቀ (ኤፌ. 4-6)።

ጳውሎስ የእግዚአብሔርን አስደናቂ ጸጋ፥ ለእኛ ያለውን ፍቅር፥ የማይገባን ሆነን ሳለ የሰጠንን የድነት (ደኅንነት) እና ያጎናጸፈንን ሰማያዊ ስጦታዎች በትክክል ከተረዳን፥ አኗኗራችንን ለመለወጥ እንደምንሻ ገልጾአል። ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር እንድንለወጥ ያደርገናል።

የኤፌሶን መልእክት የመጨረሻው ክፍል (ምዕ. 4-6) በክርስቶስ ላይ ያለን እምነት የሚያስከትላቸውን ነገሮች ያስረዳል። ጳውሎስ እንደሚለው፥ እነዚህ እግዚአብሔር ለሰጠን ታላቅ ድነት (ደኅንነት) እንደሚገባ እንድንመላለስ የሚረዱን ነገሮች ናቸው። በክርስቶስ ላይ ያለን እምነት አኗኗራችንን እንዴት ሊለውጥ እንደሚገባ ለማሳየት የሚያግዙ ብዙ የሕይወት ክፍሎች ቀርበዋል። ጳውሎስ ብዙዎቻችን ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ውስጥ ወሳኞች ናቸው ብለን በምናስባቸው አምልኮና ተአምራት ላይ ብዙም ትኩረት አለማድረጉ አስገራሚ ነው። ነገር ግን ጳውሎስ በሚያስቸግሩን ተግባራዊ የሕይወት ክፍሎች ላይ ያተኩራል። እምነታችን አኗኗራችንን እስካልለወጠ ድረስ ለወንጌሉ እንደሚገባ አልተመላለስንም ማለት ነው። እምነታችን ከሌሎች ክርስቲያኖች፥ ከዓለማውያን፥ ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎታችንና ከቤተሰቦቻችን ጋር በምናደርገው ግንኙነት ላይ ለውጥ ማምጣት አለበት። እምነታችንም የሰይጣንን ውጊያ ለማሸነፍ ኃይል ይሆነናል።

ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ሁሉ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በተከፋፈለችበት ዘመን ውስጥ እንኖራለን። በሁሉም የኢትዮጵያ ቤተ እምነቶች ማለት ይቻላል፥ ዐበይት ውስጣዊ አለመስማማቶች አሉ። እነዚህ አለመግባባቶች ከተለያዩ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አለመግባባት የመነጩ ናቸው። በተጨማሪም፥ ብዙ ቤተ እምነቶች ከሌሎች ቤተ እምነቶች ጋር በመጣላት ላይ ናቸው። በዚሁ መሠረት የተጋጋለ አምልኮ ስለምናካሂድና ብዙ ተአምራቶች ስለሚታዩ ከበፊቱ የበለጠ መንፈሳውያን ነን ብለን እናስባለን። ጳውሎስ እውነተኛው የመንፈሳዊነትና የመነቃቃት መፈተኛ አኗኗራችን እንደሆነ አስረድቷል። እምነታችንን እንዲያንጸባርቅ ለማድረግ ከሚያዳግቱን ነገሮች አንዱ ከሌሎች ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ነው። ጳውሎስ እርስ በርሳችን የምናደርገው ግንኙነት እግዚአብሔርን ወደሚያስከብሩ ግንኙነቶች የሚመራ ትክክለኛ አመለካከትና ግልጽ ግንዛቤ ሊኖረው እንደሚገባ አስረድቷል።

ሀ. ግንኙነቶች የሚጀምሩት በጋራ እምነታችን ውስጥ እውነት የሆነውን ነገር በመገንዘብ ነው። አማኞች ሁሉ በጋራ እምነታቸው በአንድነት መተሳሰር አለባቸው። ጳውሎስ እምነታችን እንደ «ሙጫ» ሊያያይዘን እንደሚገባ ለማሳየት «አንድ» የምትለውን ቃል ደጋግሟል። አማኞች ሁሉ በአንድ «አካል» ማለትም የክርስቶስ አካል የሆነች ቤተ ክርስቲያን እንዳለች ያምናሉ። በምድር ላይ ብዙ የተለያዩ ቤተ እምነቶች ሊኖሩን ቢችሉም፥ በሰማይና በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት በእውነተኛ አማኞች የተገነባች አንዲት አካል ብቻ አለች። በእያንዳንዱ ክርስቲያን ልብ ውስጥ የሚያድር አንድ መንፈስ ቅዱስ ብቻ አለ። በሙሉ ወንጌል የሚሠራውና በመካነ ኢየሱስ የሚሠራው መንፈስ ቅዱስ አንድ ነው። አንዳንዶች መንፈስ ቅዱስ እንዳላቸውና ሌሎች እንደሌላቸው ወደሚያስረዳው ትምህርት የሚመራው ሐሰተኛ እምነት ነው።

አንድ «ተስፋ» አለ። ይኸውም አንድ ቀን ሁላችንም በመንግሥተ ሰማይ እንደምንሰባሰብ የሚያሳይ ነው። አንድ «ጌታ» አለ። እርሱም ለኃጢአታችን የሞተውና የቤተ ክርስቲያን ራስ የሆነው ክርስቶስ ነው። በክርስቶስ አምነን የምንድንበት አንድ «እምነት»፥ አማኞች ሁሉ ሊከተሉት የሚገባ አንድ «ጥምቀት»፥ ብሎም ነገሮችን ሁሉ የሚቆጣጠር አንድ መንፈሳዊ የጋራ «አባት» አለን። ጳውሎስ በክርስቶስ የምናምን ሁላችን እነዚህን እውነቶች ሁሉ ከያዝን፥ ላለመጣላትና እርስ በርሳችን ለመተባበር በቂ ምክንያት እንዳለን አመልክቷል።

ነገር ግን ይህ ትምህርት አሉታዊ ገጽታም አለው። ጳውሎስ ይህ የአንድነት መሠረት የሌላቸው ሰዎች መቼም ከእኛ ጋር ሙሉ በሙሉ አንድ ሊሆኑ እንደማይችሉ አመልክቷል። በሥላሴ ካላመኑ፥ ወይም በኢየሱስ ክርስቶስ ካላመኑ፥ ወይም ድነትን (ደኅንነትን) ለማግኘት እምነታቸውን በኢየሱስ ላይ ካላኖሩ፤ የአንድነት መሠረት የላቸውም ማለት ነው። በዘመናችን ሁሉም መንገዶች ወደ እግዚአብሔር እንደሚመሩና ሁሉም ሃይማኖቶች ተቀባይነት እንዳላቸው አንዳንድ አስተማሪዎች ያስተምራሉ። ጳውሎስ ግን አንድነታችን በመሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እምነቶች ላይ የተመሠረተ መሆኑን በመግለጽ ይህንኑ አመላካከት ይቃወማል። በእነዚህ ነገሮች የማያምኑ ሰዎች ከእኛ ጋር አንድነት ሊኖራቸው አይችልም።

ለ. አንድ መሠረታዊ እምነት ያለን የአንድ ቤተሰብ አካል ስለሆንን፥ አመለካከታችን ይህንኑ ማንጸባረቅ አለበት። ከሌሎች ምእመናን የተሻልን ነን ብለን ከምናስብ ይልቅ «ትሑታን» ልንሆን ይገባል። ዋነኛ ባልሆኑ ጉዳዮች ከእኛ የተለየ ቀኖናዊ አቋም ያላቸውን ሰዎች «መታገሥ» አለብን። ፍቅርን ማሳየት አለብን።

ሐ. ሁላችንም አንድ እምነት ያለን የክርስቶስ አካል ክፍሎች ስለሆንን፥ በአንድነትና በሰላም በመመላለስ አንድነታችንንና ፍቅራችንን መግለጽ አለብን። በጸጋው እንደሚገባ እንደምንመላለስና በክርስቶስ ባገኘነው ይቅርታ ደስ መሰኘታችንን የምናሳየው በዚህ መንገድ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- በክርስቲያኖች መካከል መከፋፈል በሚኖርበት ጊዜ ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት ነገሮች አንዱ ይጓደላል። ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ የሚከሰቱትን ክፍፍሎች ዘርዝር። ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት ነገሮች የጎደለውና ክፍፍልን የሚያስከትለው ምንድን ነው? ለ) በክርስቲያኖች መካከል መልካም ግንኙነቶች ባልኖረበት ሁኔታ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መነቃቃት ሊኖር ይችላል ብለህ ታስባለህ? መልስህን አብራራ።

ክርስቶስ የአካሉ ክፍሎች ለእርስ በርሳቸው አገልግሎት እንዲሰጣጡና በብስለት እንዲያድጉ የተለያዩ ስጦታዎችን ሰጥቷቸዋል (ኤፌ. 4፡7-16)።

ጳውሎስ ሁሉም አማኞች የአንድ አካል ክፍሎች እንደ መሆናቸው ተስማምተው ሊኖሩ እንደሚገባ ካሳየ በኋላ፥ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ያስተምራል። መንፈሳዊ ስጦታ አንድ አማኝ በክርስቶስ አካል ውስጥ እንዲያገለግል መንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው የአገልግሎት ችሎታ ነው። ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች ዝርዝር ጉዳዮችን አላቀረበም። በ1ኛ ቆሮንቶስ 12-14 ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች በስፋት አስተምሯል። በኤፌሶን 4፡7 ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ ስጦታዎች አንዳንድ ጠቃሚ አሳቦችን ጠቃቅሷል።

በመጀመሪያ፥ መንፈሳዊ ስጦታን «ጸጋ» ይለዋል። ይህም እግዚአብሔር የሚሰጠን ችሎታ ወይም አገልግሎት በጥረታችን ወይም ከሌሎች ተሽለን በመገኘታችን ሳይሆን፥ ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠን የማይገባ ጸጋ እንደሆነ ሊያስገነዘበን ይገባል።

ሁለተኛ፥ ጳውሎስ ለእያንዳንዳችን መንፈሳዊ ስጦታ እንደ ተሰጠን አብራርቷል። ይህም እያንዳንዱ ክርስቲያን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውል ቢያንስ አንድ ስጦታ እንዳለው ያሳያል። ስለሆነም፥ እያንዳንዱ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚጫወተው እግዚአብሔር የሰጠው ሚና ስላለው ተመልካች ብቻ ሊሆን አይገባም።

ሦስተኛ፥ ጳውሎስ እነዚህ የጸጋ ስጦታዎች እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን እንደ ተሰጡን ያስረዳል። መንፈሳዊ ስጦታዎች ከእግዚአብሔር የሚመነጩ እንጂ የተፈጥሮ ችሎታዎች ወይም የቅጥር ሥራዎች አይደሉም። ነገር ግን ምንጫቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። እግዚአብሔር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ልዩ ስጦታና ድርሻ በመስጠት ስጦታችንን አውቀን እንድናገለግለው ይፈልጋል።

ጳውሎስ ሁሉም ክርስቲያኖች መንፈሳዊ ስጦታዎችን እንደ ተቀበሉ ቢናገርም፥ በኤፌሶን መልእክቱ የመሪነት ስጦታዎችን በተመለከተ ብቻ በብዛት ጽፎአል። (ለምእመናን የተሰጡትን ሌሎች መንፈሳዊ ስጦታዎች ዝርዝር ከ1ኛ ቆሮንቶስ 12፡28-30 አንብብ።) ጳውሎስ ለቤተ ክርስቲያን የተሰጡትን አምስት ዐበይት የአመራር ስጦታዎች ገልጾአል። የአመራር ስጦታዎች ሰዎች በምርጫ ጊዜ የሚወስኗቸው አይደሉም። ነገር ግን እነዚህ ስጦታዎች እግዚአብሔር የሚሰጣቸውና እኛም ለይተን ለቤተ ክርስቲያን የምንጠቀምባቸው ናቸው። እግዚአብሔር የመሪነት ስጦታ የሰጣቸውን ሰዎች ለዚሁ አገልግሎት መምረጥ አለብን። ነገር ግን ስጦታ የሌለውን ሰው ልንመርጥና ከዚያ በኋላ እግዚአብሔር ስጦታውን ይሰጠዋል ብለን ልንጠብቅ አይገባም። በመጀመሪያ፥ ሐዋርያት ተጠቅሰዋል። እዚህ ላይ ጳውሎስ ክርስቶስ ስለ ሾማቸው በኢየሱስ ስለተመረጡት 12ቱና ስለ ራሱ እያሰበ መሆኑ አይጠረጠርም። ነገር ግን እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን ለመመሥረት ስለተጠቀመባቸው አገልጋዮችም እያሰበ ሊሆን ይችላል። ሁለተኛ፥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለክርስቶስ አካል የማስተላለፍ ኃላፊነት የተሰጣቸው ነቢያት አሉ። ይህ የመሪነት ተግባር አዲስ ኪዳን ከመጻፉ በፊት ለቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን የተለየ ጠቀሜታ ነበረው። ሦስተኛ፥ ወንጌሉን ለዓለማውያን የማካፈል ስጦታ የተሰጣቸው ወንጌላውያን ነበሩ። አራተኛ፥ የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን ምእመናን መንፈሳዊ ፍላጎቶች የማሟላት ኃላፊነት የተሰጣቸው መጋቢያን ነበሩ። አምስተኛ፥ ሰዎች እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ እንዲመላለሱ በሚያበረታታ መልኩ የእግዚአብሔርን ቃል የማስተላለፍ ስጦታ የተሰጣቸው መምህራን ነበሩ። (ከግሪኩ መጽሐፍ ቅዱስ የመጋቢነትና የአስተማሪነት ስጦታ አንድ ይሁን ወይም ሁለት የተለያዩ ስጦታዎች መሆናቸውን መረዳቱ አስቸጋሪ ነው።) ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን እነዚህን የመሪነት ስጦታዎች የሰጠው የክርስቶስ አካል መንፈሳዊ አመራር እንዲኖራት ነው። የአመራር ስጦታዎች ቤተ ክርስቲያንን ለመትከል፥ ለማሳደግና ለጠፉት ወንጌሉን እንድትሰብክ ለማገዝ ይረዳሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከላይ የተጠቀሱት አምስት መንፈሳዊ ስጦታዎች እንዳሏቸው የምታውቋቸውን ሰዎች በምሳሌነት ጥቀስ። ለ) ሰዎቹ መንፈሳዊ ስጦታዎቹ እንዳሏቸው እንዴት ታውቃለህ?

የአመራር ስጦታዎች ዓላማ ምንድን ነው? ብዙውን ጊዜ መሪዎች አገልግሎታቸውን በውል ስለማያውቁ ግራ ይጋባሉ። ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር የሚፈልገውን ከማድረግ ይልቅ የዓለምን የአመራር ስልት ይኮርጃሉ። ብዙ ሽማግሌዎች ወይም መጋቢዎች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሥራቸው የሚናገረውን አያውቁም። በኤፌሶን 4፡12-13 ጳውሎስ አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ እግዚአብሔር በሰጠው የመሪነት ስጦታ አማካኝነት ምን ማድረግ እንዳለበት አብራርቷል።

ሀ. መንፈሳዊ መሪዎች «ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራት ለክርስቶስ አካል ሕንፃ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ» ማዘጋጀት አለባቸው። ብዙውን ጊዜ መሪዎች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መሥራት እንዳለባቸው ያስባሉ። ጳውሎስ ግን ምእመናን የቤተ ክርስቲያኒቱን አገልግሎት ያካሂዱ ዘንድ መሪዎች ሊያሠለጥኗቸው እንደሚገባ አስረድቷል። መሪዎች ምእመናን ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን ስጦታ ለይተው እንዲያውቁ ሊረዷቸው ይገባል። ከዚያም በስጦታዎቻቸው አማካኝነት የክርስቶስን አካል ይገነቡ ዘንድ የአገልግሎትን ስፍራዎች ሊሰጧቸው ይገባል።

ለ. መንፈሳዊ መሪዎች ምእመኖቻቸውን በሚያሠለጥኑበት ጊዜ ሕዝቡ ወደ ክርስቶስ ፍጹም ሙላት ይደርሳሉ። በሌላ አገላለጽ፥ በእምነታቸው በመብሰል፥ ስለ ክርስቶስ የጠለቀ እውቀት በማግኘትና በአንድነት በመመላለስ ያድጋሉ። እግዚአብሔር እንደሚፈልግባቸው በመኖር ለወንጌሉ እንደሚገባ ይመላለሳሉ።

አንድ ክርስቲያን በብስለት ማደጉን እንዴት እናውቃለን? ያ ብስለት እንዴት ራሱን ይገልጻል? ጳውሎስ አያሌ ነገሮችን ዘርዝሯል።

  1. በሳል ሰው በእምነቱ ይረጋል። አዳዲስ የሐሰት ትምህርቶች ሲመጡ አይናወጥም።
  2. በሳል ሰው እውነትን በፍቅር ይናገራል። ይህ ከባድ ስለሆነ፥ ብዙውን ጊዜ ወደ አንደኛው አጽናፍ እናደላለን። አንዳንድ ክርስቲያኖች ብዙም ፍቅር ሳይኖራቸው እውነት ነው ብለው የሚያስቡትን በድፍረት ይናገራሉ። ይህ ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የስሜት መጎዳትንና ክፍፍልን ያስከትላል። ሌሎች ክርስቲያኖች በፍቅር ላይ ከማተኮራቸው የተነሣ የሰዎችን ስሜት እንዳይጎዱ በመፍራት እውነትን አይናገሩም። ይህም ሰዎች በተሳሳቱ መንገዶች እንዲመላለሱና የቤተ ክርስቲያን ምስክርነት እንዲጎድፍ ያደርጋል። እግዚአብሔር ስለ እውነት እንድንገደድና በክርስቶስ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን ለሆኑት ወገኖቻችን እንድንናገር ይፈልጋል። ነገር ግን ሌላውን ሰው በሚረዳና በሚያሳድግ መልኩ እውነትን በፍቅር እንድንናገርም ይፈልጋል።
  3. በሳል ሰው ከክርስቶስ ጋር የጠለቀ ግንኙነት አለው። ክርስቶስ በነገሮች ሁሉ ንጉሣችን እንደሆነ ተቀብለን በቅርብ ግንኙነት እንመላለሳለን። ክርስቲያኖች ሁሉ ከክርስቶስ ጋር እንዲህ ዓይነት ግንኙነት ሲኖራቸው ሁሉም ክርስቲያን በክርስቶስ አካል ውስጥ የራሱን ድርሻ ያሟላል። የዚህች ዓይነት ቤተ ክርስቲያን ታላቅ ኃይል አላት።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አብዛኛዎቹ የቤተ ክርስቲያንህ አባላት መንፈሳዊ ስጦታዎችን የሚያውቁ ይመስልሃል? ካልሆነ፥ ለምን? ለ) በቤተ ክርስቲያንህ የሚገኘው አብዛኛው ሕዝብ በመንፈሳዊ ሕይወቱ የበሰለ ይመስልሃል? ካልሆነ ለምን? ሐ) አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ የቤተ ክርስቲያኑ ምእመናን መንፈሳዊ ስጦታዎቻቸውን እንደሚያውቁ፥ እንደሚጠቀሙና ምእመናን ሁሉ በመንፈሳዊ ብስለት እንደሚያድጉ ለማረጋገጥ ምን ሊያደርግ ይችላል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d