በክርስቶስ የሚገኝ መንፈሳዊ በረከት (ኤፌ. 1፡1-14)

ሁሴን በሙስሊም ቤተሰብ ውስጥ ነበር ያደገው። ነገር ግን ትምህርቱን በመከታተል ላይ ሳለ ከሌላ ተማሪ ስለ ክርስቶስ ወንጌል ሰማ። ወንጌሉን አምኖ ስለተቀበለ ቤተሰቦቹ ወዲያውኑ ከቤት አባረሩት። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ በነበረባቸው ጊዜያት ከአንድ ክርስቲያን ቤት ወደ ሌላው እየተዘዋወረ ሲቸገር ኖረ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ካጠናቀቀ በኋላ ሥራ ይዞ ራሱን እንደሚያስተዳድር ተስፋ ያደርግ ነበር። ነገር ግን ሥራ ባለማግኘቱ ኑሮው ትግል የበዛበት ሆነ። ቡቱቶ ልብሱን ለብሶ ወዲያ ወዲህ ማለት አሳፈረው። በዚህ ጊዜ ክርስቶስን ለመከተል መወሰኑ ትክክል ስለመሆኑ ያመነታ ጀመር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለክርስቲያኖች በድህነት ውስጥ በደስታ መኖር አስቸጋሪ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ኤፌ. 1፡3-14 አንብብ። ክርስቲያኖች በሰማያዊ ስፍራ የተባረኩባቸውን ነገሮች ዘርዝር። ሐ) የበለጠ ጠቀሜታ ያላቸው ምድራዊ በረከቶች ናቸው ወይስ መንፈሳዊ የሰማይ በረከቶች? ለምን? መ) ክርስቲያኖች ድህነት ወይም ስደት በሚደርስባቸው ጊዜ መንፈሳዊ በረከቶቻቸውን ማስታወስ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

ብዙዎቻችን እግዚአብሔር በብዙ ምድራዊ በረከቶች ይባርከናል ብለን እናስባለን። አንዳንድ ጊዜ እንደዚያ ያደርጋል። ብዙውን ጊዜ ግን አማኞች ከገንዘብ፥ ከበሽታና ከሌሎችም ሁኔታዎች ጋር የተያያዙ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክት እግዚአብሔር ድነትን (ደኅንነትን) ባገኘን ጊዜ ምን ዓይነት በረከቶችንና ዋስትና እንደሰጠን ግልጽ አድርጓል። ጳውሎስ በቁሳዊ በረከቶች ላይ ከማተኮር ይልቅ እግዚአብሔር ለልጆቹ ሁሉ የሚሰጣቸውን መንፈሳዊ በረከቶች እንድናስታውስ አበረታቶናል። ማንም ሰው ሊወስድብን በማይችላቸው በእነዚህ ዘላለማዊ መንፈሳዊ በረከቶች ልንበረታታ ይገባል።

፩) መግቢያ (ኤፌ. 1፡1-2)

ጳውሎስ በመልእክቶቹ ሁሉ በእግዚአብሔር ፈቃድ የክርስቶስ «ሐዋርያ» ሊሆን መብቃቱን ይናገራል። የኤፌሶን ክርስቲያኖች የጳውሎስን ሐዋርያነትና ሥልጣን ስላልተጠራጠሩ፥ ጳውሎስ በዚህ ጉዳይ ላይ ለገላትያ ቤተ ክርስቲያን የጻፈውን ያህል አጽንኦት አላደረገም (ገላ. 1፡1)።

ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው «በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምእመናን» ነበር። «ኤፌሶን» የሚለው ቃል በመጀመሪያው የጳውሎስ መልእክት ውስጥ ስለመኖሩ ምሁራን የሚከራከሩ መሆኑን በአንደኛው ቀን ትምህርት ተመልክተናል። ይህ ለኤፌሶን ብቻ ሳይሆን በእስያ ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት የተላከ ተዘዋዋሪ ደብዳቤ ሊሆን ይችላል። ኤፌሶን እጅግ አስፈላጊና በቀዳሚነት መልእክቱን የተቀበለች ቤተ ክርስቲያን በመሆኗ፥ ቀደምት ምሁራን «ኤፌሶን» የሚለውን ቃል ጨምረው ይሆናል።

እነዚህ ክርስቲያኖች ከዓለም የተለዩና ለክርስቶስ በታማኝነት የኖሩ ስለነበሩ፥ የወቀሳ አሳቦች አልተሰነዘሩም። ጳውሎስ እንዲለውጡ የጠየቃቸው አስተምህሮዎች ወይም ልምምዶች የሉም። ነገር ግን ጳውሎስ የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን የተለማመዳቸውን የጸጋና የሰላም ቡራኬ ሰጥቷል።

፪) የእግዚአብሔር ልጆች መንፈሳዊ በረከቶች (ኤፌ. 1፡3-14)

ዛሬ በምንኖርበት ዘመን ክርስቲያኖች በምድራዊ በረከቶች ላይ ያተኩራሉ። አንዳንድ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ካመንን ሀብታሞች እንሆናለን ብለው ያስባሉ። በክርስቶስ ካመንን፥ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች ከተከተልንና እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ከኖርን፥ እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ በቁሳዊ በረከቶች ይባርከናል ይላሉ። አንዳንድ ጊዜ ግን ይህንን አያደርግም። እግዚአብሔር ቢባርከንም እንኳን እነዚህ ምድራዊ በረከቶች ዋነኛ ነገሮች አለመሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል። ዋነኞቹ መንፈሳዊ በረከቶች ናቸው።

ጳውሎስ ለቅዱሳን ወይም በክርስቶስ ላሉት ከሁሉም የላቀ በረከት እንደ ተሰጠ አስረድቷል። እነዚህም ምድራዊ በረከቶች ሳይሆኑ፥ ጳውሎስ እንደሚለው በሰማያዊ ስፍራ የሚገኙ ናቸው። ጳውሎስ ብዙውን ጊዜ በምሥጢራዊ መንገድ ከክርስቶስ ሞት፥ ትንሣኤና ዕርገት ጋር መተባበራችንን ሲገልጽ መቆየቱን አንስተናል። በዚህ ስፍራ ጳውሎስ በክርስቶስ ዕርገት ላይ ያተኩራል። ክርስቶስ ወደ ሰማይ ስላረገና እኛም ከእርሱ ጋር ስለተባበርን፥ እግዚአብሔር የሚሰጠን በረከቶችም ያሉት በሰማይ ነው። ከክርስቶስ የተነሣ እነዚህ ሁሉ በረከቶች የእኛ ናቸው። እነዚህ በረከቶች ምን ምንድን ናቸው?

ሀ. እግዚአብሔር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን እንሆን ዘንድ መርጦናል። ስለ ድነት (ደኅንነት) ስናስብ ብዙውን ጊዜ በሰዎች ሚና ላይ እናተኩራለን፥ በክርስቶስ ስለማመናችንም እንናገራለን። ጳውሎስ ግን ድነት የሚመለከተው ከእግዚአብሔር እይታ አንጻር ነው። እግዚአብሔር በማንረዳው መንገድ በዓለም ውስጥ ከሚገኙ እጅግ ብዙ ዓለማውያን መካከል መርጦናል። ድነት (ደኅንነት) እግዚአብሔር አንተንና እኔን ልጆቹ አድርጎ ከመምረጡ ተግባር ነው የሚጀምረው። የበለጠ የሚገርመው ደግሞ ጳውሎስ ይህ ምርጫ የተካሄደው ከዓለም ፍጥረት በፊት እንደሆነ መናገሩ ነው። አዳምና ሔዋን ከመፈጠራቸው በፊት እግዚአብሔር አንተና እኔ የቤተሰቡ አካላት እንድንሆን መፈለጉን ያውቅ ነበር። ስለሆነም፥ መረጠን።

እግዚአብሔር የመረጠን ድነት እንድናገኝ ብቻ አልነበረም። እኛን የመረጠበት ዓላማ ኃጢአተኞች ብንሆንም እንኳ ተለውጠን እንድንቀደስና በፊቱ ነውር የሌለን እንሆን ዘንድ ነበር። ይህ በሁለት የተለያዩ መንገዶች ይከናወናል። በመጀመሪያ፥ ድነት ስናገኝ እግዚአብሔር ያጸድቀናል ወይም የኃጢአት በደለኞች አለመሆናችንን ያውጃል። የክርስቶስ ደም ኃጢአታችንን ስለሚሸፍን፣ እግዚአብሔር በፊቱ ንጹሐን እንደሆንን አድርጎ ያየናል። እንዲሁም የኢየሱስ ክርስቶስን ጽድቅ ይሰጠናል። የክርስቶስ ጽድቅና ፍጹማዊ ቅድስና የእኛ ጽድቅና ቅድስና ይሆናሉ። በዚህም መንገድ በእግዚአብሔር ፊት ቅዱሳንና እንከን እንደሌለን ሆነን እንታያለን። ነገር ግን ጳውሎስ የሚለው ከዚህም ያለፈ ነው። ሁለተኛ፥ እግዚአብሔር ኃጢአትን በማሸነፍና ክርስቶስን በመምሰል በቅድስና እንድናድግ ይፈልጋል።

ለ. እግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን ወስኗል። ሁለተኛው የድነት (ደኅንነት) እርምጃ እግዚአብሔር ከመረጠን በኋላ ልጆቹ ሊያደርገን መወሰኑ ነው። ይህ የእግዚአብሔር አሠራር እኛ ክርስቶስን ለመከተል ከመምረጣችን ወይም ካለመምረጣችን ጋር እንዴት እንደሚጣጣም ሙሉ ለሙሉ ለመገንዘብ አንችልም። ከእግዚአብሔር እይታ አንጻር ግን ደኅንነታችን የሚጀምረው ከእግዚአብሔር ምርጫ ነው። ከዚያም እግዚአብሔር ሁኔታዎችን በመቆጣጠር የመረጣቸውን ሰዎች ልጆቹ እንዲሆኑ ያደርጋል።

እግዚአብሔር እኛን ሲመርጥ ምን ነበር የፈለገው? ጳውሎስ እንደ ልጆቹ ሊያደርገን መፈለጉን ያስረዳል። ምናልባትም ጳውሎስ ስለ ሮም የማደጎ ልጅነት ልማድ እያሰበ ይሆናል። በሮምና በአይሁዶችም ዘንድ፥ አንድ ሰው አንድን ሕፃን በሕጋዊ መንገድ በማደጎነት ለማሳደግ በሚፈልግበት ጊዜ የሚከተለው የማደጎነት ሥርዓት ነበር። ልጁ ከባሪያዎቹ መካከል የአንዱ፥ የድሃ ጎረቤቱ ወይም የወዳጁ ሊሆን ይችላል። ልጁ ከወለዳቸው ልጆች እኩል የሆነ ሕጋዊ የልጅነትና የቤተሰቡ አባልነት መብት ይኖረዋል። ልጁ የማደጎ ልጅነትን መብት ካገኘበት ጊዜ አንሥቶ ከተወላጅ ልጆች ጋር እኩል መብትና የመውረስ ሕጋዊ መብት ይኖረዋል። እኛም ከእግዚአብሔር ቤተሰብ የራቅን የሰይጣን ልጆች ነበርን። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጸጋና ዘላለማዊ ፍቅር የተነሣ እግዚአብሔር ልጆቹ አድርጎናል። ስለሆነም፥ እኛም ከልጁ ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን (ሮሜ 8፡17)። ከመወለዳችን በፊት እንኳን እግዚአብሔር ልጆቹ፥ የመንግሥቱ ሕጋዊ ወራሾችና የመንግሥተ ሰማይ አባላት እንደምንሆን ወስኗል። በምድር ላይ ምንም ያህል ድሆች ብንሆንም፥ በሰማይ የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ ልጆች ነን። ሰማያዊ ስፍራችን በምድር ላይ ካለው ከማንኛውም የንጉሥ ልጅ የላቀ ነው።

ጳውሎስ ለእግዚአብሔር ምርጫ ምን ያህል ትልቅ አጽንኦት እንደ ሰጠ ልብ በል። እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ይህን ዕድል የሰጠን በበጎ ፈቃዱ እንደ ወደደ ለጸጋው ክብር ምስጋና ነበር። እግዚአብሔር የመረጠን ልዩ ስለሆንን ወይም አንድን ታላቅ ተግባር ስላከናወንን አልነበረም። ይህ ምርጫ ከእግዚአብሔር ፈቃድ የመነጨ ነው። እግዚአብሔር የመረጠን ለእኛ ባለው ፍቅርና ለጸጋው ምስጋና ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የእግዚአብሔር ሕጋዊ ልጅ መሆን አስደናቂ የሚሆነው እንዴት ነው? ይህ ልጅነት የሚያስገኝልህን መልካም ዕድሎች ዘርዝር። ለ) እግዚአብሔር በቸርነቱ ልጁ እንድትሆን ስለመረጠህ አሁኑኑ አመስግነው።

ሐ. እግዚአብሔር በክርስቶስ ደም ዋጅቶናል፤ የኃጢአት ይቅርታም ሰጥቶናል። ቤዛ የሚለው ቃል ባሪያዎች ከሚሸጡበት ገበያ የተወሰደ ነው። በገበያ ላይ አንድ ሰው ለአንድ ባሪያ ካዘነለት ሊገዛውና ሰንሰለቱን ፈትቶ በነፃ ሊለቅቀው ይችል ነበር። ይህ ሰዎችን ነፃ ለማውጣት የሚካሄድ ግዥና ሽያጭ ቤዛነት ይባል ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ እኛም የኃጢአትና የሰይጣን ባሪያዎች እንደ ነበርን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ክርስቶስ ግን በሞቱ ለኃጢአታችን ዋጋ በመከፈል ሊገዛንና ነፃ ሊያወጣን ችሏል። በእግዚአብሔር ላይ የፈጸምነውን ኃጢአት ሁሉ ይቅር አለን። ይህ እግዚአብሔር በቸርነቱ በእኛ ላይ ያወረደው ጸጋ ምሳሌ ነው። ይህን ለምን አደረገ? ከፍቅሩ እንደ መነጨ ከመናገር በቀር ሌላ የምንረዳው ነገር የለም። ይህ የተደረገው የእግዚአብሔርን ታላቅ ጥበብና አሳቢነት በሚያሳይ መልኩ ነበር።

መ. እግዚአብሔር የፈቃዱን ምሥጢር አስታወቀን። በአዲስ ኪዳን «ምሥጢር» የሚለው ቃል የእግዚአብሔርን ስውር ምሥጢር ሳይሆን፥ ቀደም ሲል በከፊል ሳይገለጥ የቆየውንና አሁን ግን ለሰው ልጆች የተገለጠውን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ነው። ጳውሎስ እግዚአብሔር እስከ አዲስ ኪዳን ዘመን ሳይገልጥ ያቆያቸውን ነገሮች ለመግለጽ በኤፌሶን ውስጥ ምሥጢር (ስውር) የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ ተጠቅሟል። በብሉይ ኪዳን ከተሰወሩትና አሁን ግን በጳውሎስ በኩል ከተገለጡት ምሥጢሮች አንዱ፥ እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ በክርስቶስ የመጠቅለሉ ጉዳይ ነው። ሰማይና ምድር ለእግዚአብሔር ክብር በሚሰጡበት መልክ ይዋሃዳሉ። ይሄ ሁሉ ግራ መጋባት፥ ኃጢአት፥ ዓመፅ ሁሉ ተወግዶ ሰማይና ምድር በኢየሱስ በኩል ለተፈጠሩበት ተግባር ይውላሉ።

ሠ. እግዚአብሔር በሉዓላዊ ምርጫው ለክብሩ ምስጋና መርጦናል። ከጥንቱ ዘመን የአዳዲስ ክርስቲያኖች ማስተማሪያ መጻሕፍት አንዱ፥ «የሰው የኋላ ኋላ መጨረሻው ምንድን ነው?» ሲል ይጠይቃል። መልሱ፥ «እግዚአብሔርን ማክበርና ለዘላለም በእርሱ ደስ መሰኘት» የሚል ነው። ድነት (ደኅንነት) ከእግዚአብሔር አንጻር ሲታይ ቀዳሚ ዓላማው እኛን ማዳን ሳይሆን፥ እግዚአብሔር እንዲመሰገን ነው። የዓመፀኛ ኃጢአተኞች መዳን በሆነ ምሥጢራዊ መንገድ ለእግዚአብሔር ታላቅ ክብርን ያመጣል። ሞት የሚገባን ኃጢአተኞች ሆነን ሳለ እግዚአብሔር እንዳዳነን ስንገነዘብ፥ እግዚአብሔርን ለአስደናቂ ሥራው እናመሰግነዋለን።

ረ. እግዚአብሔር ተስፋ በተገባው መንፈስ ቅዱስ አትሞናል። «እርሱም የርስታችን መያዣ ነው፥ ለእግዚአብሔር ያለንን ሁሉ እስኪዋጅ ድረስ. . .»ጳውሎስ ስለ መጨረሻው መንፈሳዊ በረከት (ለእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ መንፈስ ቅዱስ ስለ መሰጠቱ) ከመናገሩ በፊት፥ ድነትን ከሰው እይታ አንጻር ይመለከታል። ስናምን ምን ይሆናል? ጳውሎስ በክርስቶስ ውስጥ እንደምንካተት ገልጾአል። በመንፈሳዊ ሁኔታ ከክርስቶስ ጋር እንዋሃዳለን። በክርስቶስ ውስጥ ሆነን እግዚአብሔር በሰማይ የሚሰጠንን በረከቶች ሁሉ እንቀበላለን። ጳውሎስ አስፈላጊው ነገር እምነት ብቻ ሳይሆን የምናምነው ነገር ጭምር መሆኑን አስረድቷል። እምነት ብቻውን አያድነንም። እምነታችን፥ በትክክለኛ ነገር ላይ ሊሆን ይገባል። ጳውሎስ «በእውነት ቃል» ማመን እንዳለብን ገልጾአል። የኤፌሶን ሰዎች አምነው የዳኑት በዚህ የወንጌል እውነት ነበር።

ጳውሎስ ማብራሪያውን እግዚአብሔር ከሚሰጠን እጅግ ጠቃሚ በረከቶች በአንዱ ይደመድማል። ይኸውም በእያንዳንዱ ክርስቲያን ልብ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ማደሩ ነው። ጳውሎስ ስለ መንፈስ ቅዱስ አገልግሎት ያተኮረባቸውን ነገሮች አስተውል።

 1. ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ እንደ «ምልክት» ወይም እንደ ፊርማ መሆኑን አስረድቷል። በገዛነው መጽሐፍ ላይ ፊርማ ስናስቀምጥ መጽሐፉ የእኛ ንብረት እንደሆነና ማንም ሰው ያለ እኛ ፈቃድ ሊወስደው እንደማይችል መግለጻችን ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ እግዚአብሔርም መንፈስ ቅዱስን ሲሰጠን የእርሱ መሆናችንን ለሰዎች ሁሉ መናገሩ ነው።
 2. መንፈስ ቅዱስ ለውርሳችን ዋስትና የሚሰጥ መያዣ ነው። አንድ ሰው አንድን ነገር ለመግዛት ፈልጎ በቂ ገንዘብ በሚያጣበት ጊዜ ቀብድ ይከፍላል። ቀብዱ የቀረውን ገንዘብ አምጥቶ ዕቃውን እንደሚገዛ የሚያረጋግጥ የተስፋ ቃል ወይም መያዣ ሆኖ ያገለግላል። በሰዎች ዓቅም የቀረውን ገንዘብ ከፍሎ ዕቃውን መውሰዱ አስቸጋሪ የሚሆንበት ሁኔታ ሊያጋጥም ይችላል። በእግዚአብሔር ዘንድ ግን እንደዚህ አይደለም። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን ሲሰጠን አንድ ቀን ወደ መንግሥተ ሰማይ እንደሚያስገባን ተስፋ መግባቱ ነው። መዋጀታችንን የምናጠናቅቅበት ጊዜ ይሆንና በእግዚአብሔር መንግሥት ለእኛ የሚሰጠንን ርስት የምንወርስ ተካፋዮች እንሆናለን።

እግዚአብሔር ይህን ልዩ በረከት የሰጠን ለምንድን ነው? ጳውሎስ ለክብሩ ምስጋና እንደሆነ ይገልጻል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጳውሎስ ስለ መንፈስ ቅዱስ አገልግሎት የሰጠው ማብራሪያ ብዙውን ጊዜ እኛ ስለ መንፈስ ቅዱስ ከምናስበው እንዴት ይለያል? ለ) እግዚአብሔር ወደ ሰማይ እንደሚወስደን የሚያስረዳው የተስፋ ቃል በምድር ላይ ካሉን በረከቶች ሁሉ የሚልቀው እንዴት ነው፥

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

2 thoughts on “በክርስቶስ የሚገኝ መንፈሳዊ በረከት (ኤፌ. 1፡1-14)”

 1. Asiretu samuel

  sile beretket betenesaw hasab lay yaleign tiyake
  1, metsihaf kidus bereketin menfesawina kusawi bilo yakefafilal woy??
  2, ye Abraham bereket menfesawi new woys kusawi??
  3, pawlos be semayawi sifira sil ye midir nuruachin ke bereket netsa new malet new woys?
  ye bereket timihrt sinesa ke pawlos melikt sayhon mejemer yalebet ke abraham bereket new. manignewm bereket akal kemelbesu befit menfesawi new. ye abraham bereket be kirstos eyesusu le ayzab yiders zend… gelatia3

  thank you for your feedback

  1. ወንድሜ፣ አስቀድሜ ስለጥያቄዎችህ አመሰኛለሁ፡፡ ከዚህ በታች ጥያቄዎቹን ለመመለስ ሞክሬአልሁ፡፡ ግልጽ ካልሆነለህ መልስህ ጥያቄህን እንድታነሳ አበረታታሃለው፡፡ ተባረክ፡፡

   1. metsihaf kidus bereketin menfesawina kusawi bilo yakefafilal woy??
   በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መንፈሳዊ (ኤፌ 1:3) እና ቁሳዉ/ስጋዊ (ዘፍ 45:18) በረከት በግልጽ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ መንፈሳዊና ስጋዊ የሚለው ክፍፍል፣ በረከቱ የሰውን የትኛውን ክፍል (ስጋ፣ ነፍስ/መንፈስ) በቀዳሚነት እነደሚያገለግል ከማሳየቱ አንጻር መታየት አለበት፡፡ ለምሳሌ መመረጣችን (ኤፌ 1:3)፣ ልጆቹ መሆናችን (ኤፌ 1:5)፣ በደሙ መቤዠታችን (ኤፌ 1:7)፣ የበደላችን መሰረይ (ኤፌ 1:7)፣ የፈቃዱን ምስጢር ማወቃችን (ኤፌ 1:9)፣ በመንፈስ ቅዱስ መታተማችን (ኤፌ 1:13)፣ ከእግዚአብሔር ጋር አብረን የምንሰራ መሆናችን (1ቆሮ 3:9)፣ የእርሱ ካህናት መሆናችን (2ቆሮ 11:2)፣ ከመታወቅ በላይ በሆነው ሰላሙ መሞላታችን (ፊሊ 4:7)፣ ወዘተ መንፈሳዊ በረከቶቻችን ናቸው፡፡ የእስራኤልን ሕዝብ ታሪክ ለአብነት በመውሰድ ስጋዊ በረከት ምን እንደሆነ እንመልከት፡፡ ከምድር አሕዛብ ሁሉ ላይ ከፍ ከፍ ማለት (ዘዳ 28:1)፣ በከተማ እና በእርሻ ቡሩክ መሆን (ዘዳ 28:3)፣ የሆድህ ፍሬ፥ የምድርህም ፍሬ፥ የከብትህም ፍሬ፥ የላምህም ርቢ፥ የበግህም ርቢ ቡሩክ መሆን (ዘዳ 28:4)፣ ከጠላቶችህ መጠበቅ (ዘዳ 28:7)፣ ጎተራህ በእህል መሙላቱና መትረፍረፍህ (ዘዳ 28:8)፣ ጤና ማግኘትህ ፣ ወዘተ ስጋዊ በረከቶች ናቸው፡፡

   2. ye Abraham bereket menfesawi new woys kusawi??
   የአብርሃም በረከት ሁለቱም ናቸው፡፡ መንፈሳዊው በረከት፣ በዘሩ ማለትም በክርስቶስ (ገላ 3:16) አህዛብ ሁሉ በባረካቸው ነው፡፡ “እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ (ገላ 3:29)።” ይህ በረከት በክርስቶስ አምኖ የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን በረከት ነው (ገላ 3:26)፡፡ ይህ ደግሞ መንፈሳዊ እንጂ ስጋዊ በረከት አይደለም፡፡ ስጋዊው በረከት ደግሞ የከንዓንን ምድር ከመውረስ ጋር በተያያዘ በሥጋ ዘሮቹ ለሚሆኑት እስራኤላውያን የተሰጠው ኪዳን ነው፡፡

   3. pawlos be semayawi sifira sil ye midir nuruachin ke bereket netsa new malet new woys?
   አይደለም:: ጳውሎስ በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ ማለቱ ምድራዊ በረከት የላችሁም የሚል ትርጉም ሊኖረው አይችልም፡፡ በዚህ ስፍራ ጳውሎስ ሊነግረን የፈለገው በክርስቶስ በመሆናችን ያገኘናቸውን መንፈሳዊ በረከቶች ነው፡፡ በማይጠፋው እና ዘላለም ተከትሎን በሚሄደው መንፈሳዊ በረከቶች ሁሉ መባረካችን በሚጠፋውና () ትተነው በምንሄደው በረከት አለመባረካችንን አያመለክትም፡፡ ይልቁንስ፣ “ ለገዛ ልጁ ያልራራለት ነገር ግን ስለ ሁላችን አሳልፎ የሰጠው ያው ከእርሱ ጋር ደግሞ ሁሉን ነገር እንዲያው እንዴት አይሰጠንም (ገላ 8:32)?”

   4. ye bereket timihrt sinesa ke pawlos melikt sayhon mejemer yalebet ke abraham bereket new.
   የበረከት ሃሳብ ከአብርሃም በፊትም ተጠቅሷል፡፡ በረከት የሚለው ቃለ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሶ የምናገኘው በስነ ፍጥረት ጊዜ ነው(ዘፍ 1:22፣ ዘፍ 1:28፣ ዘፍ 5:2፣ ዘፍ 9:1፣ ዘፍ 31:55፣ ዘፍ 48:20፣ ዘፍ 49:28)፡፡ ከላይ እንደተገለጸው የአብርሃም በረከት ስጋዊ እና መነፈሳዊ ነበር፡፡ ስጋዊው በስጋ ዘሮቹ ለሆኑት እስራኤላውያን ከናዓንን ከመውረስ ጋር የተያያዘው ሲሆን መነፈሳዊው ደግሞ አብርሃምን በመንፈስ የእኛ የአሕዛቦች አባት የሚያደርገው () እና በመንፈሳዊ ዘሩ ማለትም በክርስቶስ () ሁላችን በእምነት የእግዚአብሔር ልጆች የሚያደርገን በረከት ነው፡፡ የአብርሃምን መንፈሳዊ በረከት ከዚህ በታች ባሉት የገላቲያ መልእክት ጥቅሶች ሁስጥ ለማስተዋል ሞክር፡

   ገላ 3፥6-7 እንዲሁ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት። እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ።
   ገላ 3፥8 መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ፦ በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ።
   ገላ 3፥9 እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ።
   ገላ 3፥14 የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ።
   ገላ 3፥16 ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር፦ ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን፦ ለዘርህም ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ።
   ገላ 3፥29 እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።

   5. manignewm bereket akal kemelbesu befit menfesawi new.
   ይህ አባባል በረከት ወደመታየት እስኪመጣ ድረስ ስውር ነው ለማለት ከሆነ ያስኬዳል፡፡ ማንኛውም ነገር ከመገለጡ በፊት ስውር ነውና፡፡ ስውር መሆኑ ግን መንፈሳዊ አያደርገውም፡፡ መንፈሳዊ ወይም ስጋዊ የሚያደርገው አላማው እንጂ መገለጡ ወይም መሰወሩ አይደለም፡፡

   ye abraham bereket be kirstos eyesusu le ayzab yiders zend… gelatia3
   የዚህን ጥያቄ ምላሽ በዝርዝር ከላይ ይመልከቱ፡፡ ይህኛው በረከት መንፈሳዊ የሚባለው ነው፡፡ አብርሃም ሁለት አይነት በረከቶች ነው ቃል የተገባለት፡፡ አንደኛው ስጋዊ ነው (በሥጋ ዘሮቹ ለሚሆኑት የሚሰጥ)፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መንፈሳዊ ነው ይህም (በእምነት መንፈሳዊ ልጆቹ ለሆኑ ሁሉ፣ በመንፈሳዊ ዘሩ ማለትም በክርስቶስ በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ የሚሰጥ በእምነት የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን በረከት) ነው፡፡

Leave a Reply

%d bloggers like this: