እግዚአብሔር ልጆቹን ከሰይጣን ጥቃቶች ለማዳንና ድል-ነሺዎች እንዲሆኑ ለማገዝ መንፈሳዊ የጦር ዕቃዎችን ሰጥቷቸዋል (ኤፌ. 6፡10-24)

ጳውሎስ አማኞች የሰይጣንን ጥቃቶች እንዴት ሊያሸንፉ እንደሚችሉ መመሪያዎችን በመስጠት የትምህርቱን ክፍል ያጠቃልላል። ሰይጣን የክርስቲያኖች ኃይለኛ ስውር ጠላት ነው። ሰይጣን እግዚአብሔርን ይጠላል። ብዙውን ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር የሚዋጋው ልጆቹን በማጥቃት ነው። ጳውሎስ ከኃጢአት ባሕሪያችን ጋር፥ ከሌሎች አማኞች ወይም ከማያምኑ ሰዎች ጋር፥ በአጠቃላይም በዚህ ምድር ላይ እስካለን ድረስ በሚገጥሙን ትግሎች ሁሉ ውስጥ የሰይጣን እጅ እንዳለበት ገልጾአል። ጳውሎስ ከሰይጣንና ከብዙ ረዳቶቹ (አጋንንት ወይም ከፉ መናፍስት) ጋር የምናደርገውን ውጊያ አስመልክቶ፥ «መጋደላችን. . . ከእለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር ነው እንጂ » ብሏል። ይህም የሰይጣን ሠራዊት ሰዎች እንደሚያደራጁት የጦር ኃይል የተደራጀ መሆኑን ያሳያል።

ሰይጣን ማንነት ያለው ጠላት ቢሆንም በዓይን አይታይም። እንግዲህ ክርስቲያኖች ከዚህ ጠላት ጋር የሚዋጉት እንዴት ነው? ዛሬ ድምፅን ከፍ አድርጎ በመጸለይና በመገሠጽ ሰይጣንን መዋጋት እንደሚቻል ይታመናል። አንዳንዶች ወደ ጥልቁ ውረድ! እያሉ የተሳሳተ ጸሎት ይጸልያሉ። እግዚአብሔር ሰይጣንን ወደ ጥልቁ የማውረድ ሥልጣን አልሰጠንም። አንድ ቀን እግዚአብሔር ሰይጣንን ወደ ጥልቁ ከዚያም ወደ ሲኦል እንደሚያወርደው ቢታወቅም (ራእይ 20፡1-10)፥ ይህ የሚሆነው ግን በእኛ ወይም በጸሎታችን አማካኝነት አይደለም። ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ ውጊያ ሲያስተምር፥ ሰይጣንን ለመቋቋምና ለማጥቃት መዘጋጀት እንዳለብን አጽንኦት ሰጥቶ ገልጾአል። ጳውሎስ ጸንተን እንድንቆም ያሳስበናል። ጳውሎስ ሰይጣንን እንድናጠቃ ሳይሆን፥ በሕይወታችንም ሆነ በቤተ ክርስቲያን ወደ ፈተና እንድንገባና እንድንታለል የሚጠቀምባቸውን በሮች መዝጋት እንዳለብን አስረድቷል። [ማስታወሻ:- (ሰይጣን ኃጢአት እንድንፈጽም የመፈተን እንጂ በግድ ኃጢአት የማሠራት አቅም የለውም። ኃጢአትን የምንፈጽመው በእውነት ከመጽናት ይልቅ ሰይጣን የሚናገረውን ውሸት በማመን ነው። ይህ የእኛ ውሳኔ ስለሆነ፥ ለኃጢአታችን ኃላፊነት የምንወስደው ራሳችን ነን። (ያዕ. 1፡13-15 አንብብ።)]

ጳውሎስ ይህን መልእክት የጻፈው ሮም ታስሮ በነበረበት ወቅት ነበር። በዚህ ጊዜ ምናልባትም ከእርሱ ጋር በሰንሰለት የታሰሩ ወይም እንዳያመልጥ ወኅኒ ቤቱን የሚጠብቁ የሮም ወታደሮች ነበሩ። ጳውሎስ ከእነዚህ ወታደሮች የተመለከተውን የጦር መሣሪያ በመጠቀም ከሰይጣን ጥቃት ራሳችንን እንዴት እንደምንከላከል የሚያስረዳ መልእክት ጽፎአል።

ሀ. የእውነት መቀነት (ቀበቶ)፡፡ ቀበቶ የጦር መሣሪያ ጠቃሚ አካል ባይመስልም፥ ለሮማውያን ከፍተኛ ጠቀሜታ ነበረው። መቀነቱ በሚዋጉበት ጊዜ ልብሳቸው እንዳይወልቅ ከመካከሉም በላይ፥ አብዛኛዎቹ የጦር መሣሪያዎች ከመቀነታቸው ጋር የተያያዙ ነበሩ። ያለ መቀነቱ መከላከያዎቻቸው ሰውነታቸውን ሊሸፍኑ አይችሉም ነበር። ስለሆነም፥ ጳውሎስ ከሰይጣን ጥቃቶች ራሳችንን ለመከላከል ከምናደርጋቸው ነገሮች አንዱ እውነትን በማወቅ እንደሆነ ያስረዳል። ሰይጣን የውሸት አባት ስለሆነ ( ዮሐ 8፡44)፥ ክርስቲያኖች ውሸትን እንዲያምኑ በማድረግ በከፍተኛ ደረጃ ያጠቃቸዋል። የምንፈጽመው ኃጢአት ሁሉ ምንም ጉዳት እንደማያገኘን በማረጋገጥ ውሸት ላይ የተመሠረተ ነው። የምንከተለው የተሳሳተ ትምህርት ሁሉ የሰይጣን ውሸት ነው። የመከላከያ መሣሪያዎቻችን ሁሉ ከእውነት ጋር ካልተያያዙ፥ ሰይጣንንና የውሸት ፍላጻዎቹን ለመመከት የሚያስችል ኃይል ሊኖረን አይችልም። ይሁንና አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ለእውነት ግድ የላቸውም። ብዙ ክርስቲያኖች ወደ አምልኮ ወይም የፈውስ ፕሮግራም እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ወደሚረዱበት የሰንበት ትምህርት ቤት ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመሄድ አይፈልጉም። በእውነት ካልተሸፈንን ሰይጣን በቀላሉ ሊያሸንፈን ይችላል።

ለ. የጽድቅ ጥሩር። ጳውሎስ የገለጸው ሁለተኛው የጦር መሣሪያ ከከብት ቆዳ፥ ከነሐስ ወይም ከብረት ተሠርቶ የወታደሮችን ደረት የሚሸፍነው ጥሩር ነው። ይህ መሣሪያ እንደ ልብ ያሉትን ወሳኝ የሰውነት ክፍሎች ከአደጋ ይጠብቃል። ጳውሎስ ጽድቅ ሰይጣን ከሚወረውራቸው ውሸቶችና ጥርጣሬዎች እንደሚጠብቀን አስረድቷል። ይህ ጽድቅ በሁለት አቅጣጫዎች ይታያል። በመጀመሪያ፥ በክርስቶስ የተገኘውን የስፍራ ጽድቅ መገንዘብ ያሻል። ሰይጣን ከሳሽ ስለሆነ ብዙውን ጊዜ ለድነት (ደኅንነት) ብቁዎች እንዳልሆንን በመግለጽ ይከሰናል። ነገር ግን በክርስቶስ ባመንን ጊዜ እግዚአብሔር «ጥፋተኞች እንዳልሆንን» ወይም የእርሱን ጽድቅ እንደተቀበልን ተናግሯል። ስለሆነም በክርስቶስ ደም የተሸፈንንና የእርሱ ጽድቅ ስላለን፥ ሰይጣን እኛን ለመክሰስ ሥልጣን የለውም። ሁለተኛ፥ ይህ አዎንታዊ፥ ተግባራዊ ጽድቅንም ያመለክታል። እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ ስንኖር፥ ኃጢአትን ከሕይወታችን ስናስወግድ፥ እግዚአብሔርን የሚያስከብሩትን መልካም ነገሮች ስናደርግና ስናስብ፥ ሰይጣን እኛን ለማጥቃትና ለማሽነፍ ይቸገራል። የሰይጣን ፍላጻዎች ወደ ሕይወታችን ሊገቡና ሊያሸንፉን የሚችሉት በኃጢአታችን ምክንያት ክፍተቶች በሚፈጠሩበት ጊዜ ብቻ ነው።

ሐ. የሰላም ወንጌል፡፡ አንድ ወታደር ትክክለኛውን ጫማ ሳያደርግ በድንጋይ እግሩ እየተጎዳ ለመዋጋት መቸገሩ የማይቀር ነው። ትክክለኛውን ዓይነት ጫማ ካደረገ ግን ደኅንነቱ ተጠብቆለት በብቃት ሊዋጋ ይችላል። የሮም ወታደሮች በጭቃና በአቧራ ውስጥ አዳልጧቸው እንዳይወድቁ ብዙውን ጊዜ በጫማቸው ሶል ላይ እንደ ሚስማር ያሉ ጉጠታማ ነገሮች ይሠሩ ነበር። ለእኛ ግን መጫሚያችን ወንጌሉ ነው። ወንጌሉን አውቀን ለሌሎች በምናካፍልበት ጊዜ ከሰይጣን ጥቃቶች ልናመልጥ እንችላለን። ነገር ግን እምነቱን በንቃት የማያካፍል ዝምተኛ ክርስቲያን ብዙውን ጊዜ ለሰይጣን ጥቃቶች ይጋለጣል።

መ. የእምነት ጋሻ፡፡ ጥንታውያን ወታደሮች ሁለት ዓይነት ጋሻዎችን ይጠቀሙ ነበር። እግረኛ ጦር በተጋጋለ ጦርነት ውስጥ በሚሆንበት ጊዜ የሚጠቀምበት አነስተኛ ጋሻ ነበር። በተጨማሪም፥ ከተሞችን በሚወሩበት ጊዜ የከተማይቱ ዜጎች ከሚወረውሩባቸው ፍላጻዎች ራሳቸውን ለመከላከል መላ አካላቸውን የሚሸፍኑበት ትልቅ ጋሻም ነበር። ጳውሎስ የእምነት ጋሻ የሚለውን ቃል የተጠቀመው ትልቁን ጋሻ ለማመልከት ነው። ብዙውን ጊዜ ሰይጣን የሚወረውራቸው ፍላጻዎች ስለ እግዚአብሔር፥ ስለ ደኅንነታችን፥ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር፥ ወዘተ… እንድንጠራጠር የሚያደርጉ ናቸው። እነዚህን ጥርጣሬዎች የምናሸንፈው በእምነት ነው። የዕብራውያን መልእክት፥ እምነት ያልታዩትን ነገሮች በእርግጠኝነት መረዳት እንደሆነ ያስረዳል (ዕብ. 11፡1)። ስለሆነም፥ ሰይጣን የጥርጣሬን ፍላጻ ወይም የኃጢአትን ፈተና ወደ ሕይወታችን በሚልክበት ጊዜ ጥርጣሬን አስወግደን በእርግጠኝነት በመሞላት በእግዚአብሔር፥ በመልካምነቱ፥ በፍጹም መንገዱና በማዳኑ ማመን አለብን። ይህ ትልቅ ጋሻ ጎን ለጎን የሚቆሙ ወታደሮች፥ ፍላጻዎችን የሚከላከል ግድግዳ ለመፍጠር እንዲችሉ የሚያያይዟቸው መንጠቆዎች ያሉት መሆኑ አስገራሚ ነው። ይህም እምነታችንን ለመጠበቅ ከሁሉም የሚሻለው መንገድ ከሚያውቁን፥ ከሚጸልዩልንና ሰይጣን በሚያጠቃን ጊዜ በእምነታችን እንድንጸና ከሚያግዙን የክርስቶስ አካላት ጋር መተሳሰር መሆኑን ያስረዳል። የሰይጣንን ጥቃት ልናሸንፍ የምንችለው በጠንካራ እምነት በመጽናት ነው። ጠንካራ እምነት እንዲኖረን ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር የቅርብ ግንኙነት ሊኖረንና ልንተማመንበት ይገባል። በተጨማሪም፥ በእምነታችን እንድንጸና ከሚረዱን አማኞች ጋር የቅርብ ኅብረት ልንመሠርት ይገባል።

ሠ. የመዳን ቁር። ውጊያው የሚካሄደው በሰይፍ ስለነበርና ጠላትን ለመግደል ከሁሉም የሚሻለው ጭንቅላቱን በሰይፍ መውጋት ስላነበር፥ የሮም ወታደሮች በራሳቸው ላይ ቁር ይደፉ ነበር። ይህ የወታደሩን ጭንቅላት ለመጠበቅ ይረዳ ነበር። እኛም ክርስቲያኖች አእምሯችንን መጠበቅ አለብን። የሚጠብቀን ደግሞ ድነት (ደኅንነት) ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ «ድነት (ደኅንነት)» የሚለው ቃል በሁለት መንገዶች ይታያል። በመጀመሪያ፥ በክርስቶስ የሚያምን ክርስቲያን ሁሉ ድነትን ተቀብሏል። ሰይጣን ይህንን ድነት (ደኅንነት) ማግኘታችንን እንድንጠራጠር ይሞክራል። ነገር ግን እግዚአብሔር በቃሉ ውስጥ በሰጠው የተስፋ ቃል ምክንያት ክርስቲያኖች መዳናቸውን ያውቃሉ። ሁለተኛው ዓይነት ድነት (ደኅንነት) በየዕለቱ በድል ነሺነትና ክርስቶስን በመምሰል መመላለሳችንን ያመለክታል። ለእግዚአብሔር እየታዘዝን ስንመላለስ፥ በባሕሪያችንና በድነት (ደኅንነት) ዋስትናችን በማደግ ክርስቶስን እንመስላለን። ይህም ሰይጣን የአስተሳሰባችንና የተግባራችን ምንጭ በሆነው አእምሯችን ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት ይወስነዋል።

ረ. የመንፈስ ሰይፍ፡ የጥንት ወታደሮች ሁለት ዓይነት ሰይፎችን ይጠቀሙ ነበር። አንደኛው ጠላትን ለማጥቃት በሁለት እጆቻቸው የሚሰነዝሩት ነበር። በዚህ ስፍራ ጳውሎስ በሁለቱም በኩል ስለታም ስለሆነው አጠር ያለ ሰይፍ ይናገራል። ጳውሎስ የማጥቂያ መሣሪያችን መንፈስ ቅዱስ ሰይጣንን ለማሸነፍ የሚጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስ መሆኑን አስረድቷል። ሰይጣን ክርስቶስን በፈተነውና በተዋጋው ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን በመጥቀስ ምላሽ ሰጥቷል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ጠላትን ለማሸነፍ እግዚአብሔር የሚሰጠንና መንፈስ ቅዱስ ድልን ለመንሣት የሚጠቀምበት መሣሪያ የእግዚአብሔር ቃል ነው። አሁንም ሰይጣንን ለማሸነፍ መጽሐፍ ቅዱስን ማወቅ ጠቃሚ መሆኑን እንመለከታለን።

ነገር ግን ውጊያውን በአጥጋቢ ሁኔታ ለማካሄድ ሌላም አንድ አስፈላጊ ነገር አለ። ወታደሩ ከጦር አዛዥ ጋር የቀረበ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል። ግንኙነት ከሌለ ወታደሩ ወደ ግራ፥ ወደ ቀኝ መዞር ወይም ባለበት መጠበቅ እንዳለበት አያውቅም። ልንዋጋ የሚገባንና ሰይጣን በእኛ ላይ የሚሰነዝረውን ጥቃት በማሸነፍ የመንግሥቱን ግዛት ልንወስድ የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ አዛዣችን ከሆነው ከክርስቶስ ጋር የቅርብ ግንኙነት ሊኖረን እንደሚገባ አስረድቷል። ይህንን የምናደርገው በጸሎት ነው። ስለሆነም፥ ጳውሎስ የኤፌሶን ክርስቲያኖች በማያቋርጥ ጸሎት መንፈሳዊ ሕይወታቸውን እንዲያረሰርሱ ያሳስባቸዋል። እንደ ግለሰቦችና የቤተ ክርስቲያን አካል ለራሳቸውና ለእርስ በርሳቸው በሚጸልዩበት ጊዜ ድል ነሺዎች ይሆናሉ። ለጳውሎስ በሚጸልዩበት ጊዜ ደግሞ እግዚአብሔር ጸሎታቸውን በመጠቀም ጳውሎስ ሰዎችን ከሰይጣን መንግሥት እየነጠቀ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት እንዲያመጣ ያደርጋል። እጅግ ውጤታማዎች ጸሎቶች ብዙውን ጊዜ ለእርስ በርሳችን የምናቀርባቸው የራስ ወዳድነት ጸሎቶች (ለምሳሌ፥ የፈውስ፥ የሥራ፥ ወዘተ) ሳይሆኑ፥ ቀደም ሲል ጳውሎስ በኤፌሶን ውስጥ የጸለያቸው ዓይነት ናቸው። እነዚህ ስለ እግዚአብሔር ፍቅርና ጥልቅ የእውነት ግንዛቤ ያላቸው ጸሎቶች ናቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰይጣን አንተን ያጠቃበትን የግል ሁኔታ ግለጽ። ጥቃቱ (ፍላጻው) ምን ነበር? እነዚህ የጦር መሣሪያዎች ሰይጣንን ለማሸነፍ እንዴት ይረዱሃል? ከእነዚህ መሣሪያዎች የአንዱ መጉደል ሽንፈትን የሚያስከትለው እንዴት ነው? ለ) ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንህን የሚያጠቃበትንና የሚያሸንፍበትን ሁኔታ ግለጽ። ከእነዚህ የጥበቃ መሣሪያዎች የጎደሉት የትኞቹ ናቸው? በውጊያው የበኩልህን እገዛ ለማድረግ ምን ልትሠራ ትችላለህ? ሐ) ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊ ውጊያ ያቀረበው ገለጻ ብዙውን ጊዜ ከምንረዳውና ተግባራዊ ከምናደርገው እንዴት ይለያል?

የማጠቃለያ ሰላምታ (ኤፌ. 6፡21-24)

ጳውሎስ ቲኪቆስን ከኤፌሶን ሰዎች ጋር ያስተዋውቀዋል። ምናልባትም ይህን መልእክት ከሮም ወደ ኤፌሶን ያመጣውና ወደ ሌሎችም አብያተ ክርስቲያናት ያደረሰው ቲኪቆስ ሳይሆን አይቀርም። ቲኪቆስ ለቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን (ቆላ. 4፡7) እና ምናልባትም ለፊልሞናም የጳውሎስን መልእክቶች አድርሷል። ጳውሎስ የኤፌሶን አማኞች የእግዚአብሔር ጸጋ፥ ሰላምና ፍቅር እንዲበዛላቸው በመጸለይ መልእክቱን ደምድሟል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: