እግዚአብሔር የቤተሰብ አባላት እንዴት እንደሚዛመዱ ያብራራል (ኤፌ. 5፡21-6፡9)።

የውይይት ጥያቄ፡– ኤፌ. 5፡21-6፡9 አንብብ። ሀ) በዚህ ክፍል ስለ ቤተሰብና የሥራ ቦታ ግንኙነቶች የቀረቡት ጠቃሚ ትምህርቶች ምን ምንድን ናቸው? ለ) እግዚአብሔር ቤተሰቦች እርሱን በሚያስከብር መንገድ እንዲኖሩ የሚፈልገው እንዴት ነው? ሐ) በኢትዮጵያ በቅርበት የሚፋቀሩና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኙ ቤተሰቦች እንዳይኖሩ ችግር የሚፈጥሩት ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? መ) የቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች በቤተ ክርስቲያንህ ውስጥ ቤተሰባዊ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ምን እያደረጉ ናቸው?

ማኅበረሰብ የተለያዩ የሰው ቡድኖች የሚካተቱበት ተቋም ነው። ትንሹ ቡድን ግለሰቦችን የያዘ ሲሆን፥ የሚቀጥለው ደረጃ ደግሞ ቤተሰብ ነው። ከዚያም ጎሳና አገር ይከተላሉ። እግዚአብሔርን የምታስከብር ጠንካራ አገር ለመገንባት ከታች የሚገኙት ደረጃዎች መጠናከር አለባቸው። ይህም ግለሰቦች እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ መኖር እንዳለባቸው ያሳያል። ጳውሎስ ግለሰቦች ለወንጌሉ እንደሚገባ ስለሚኖሩበት ሁኔታ እያብራራ ነበር። አሁን ጳውሎስ ወደ ቀጣዩ ደረጃ በመሸጋገር ስለ ጠንካራ መንፈሳዊ ቤተሰቦች ይናገራል። ግለሰቦችና ቤተሰቦች እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ በሚኖሩበት ጊዜ በማኅበረሰቡና በአገሪቱ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ጳውሎስ በአያሌ የተለያዩ የቤተሰብ ግንኙነቶችና በሚዛመዱባቸው መርሆች ላይ አጽንኦት አድርጓል።

ሀ. የሁሉም መንፈሳዊ ግንኙነቶች መሠረታዊ መርሆ፡- «ለእያንዳንዳችሁ በክርስቶስ ፍርሃት የተገዛችሁ ሁኑ።» ወንዶች ሚስቶቻቸው እንዲገዙላቸው ሲያዙ መስማቱ የተለመደ ነገር ነው። ነገር ግን ጳውሎስ ባሎችና ሚስቶች እንዴት መዛመድ እንደሚገባቸው ከመናገሩ በፊት፥ ሁሉም ክርስቲያኖች ለእያንዳንዳቸው እንዲገዙ መክሯል። ጳውሎስ ይህን ሲል እርስ በርሳችን በምናደርገው ግንኙነት ከራሳችን መንገድ ይልቅ ሌሎችን እንድናከብርና የእነርሱን ጥቅም እንድንሻ ማሳሰቡ ነው። ሰዎች ለእኛ ጥሩዎች ባይሆኑስ? አንድ ሰው ቢነዳንስ፣ ለሰዎች የምንገዛላቸው መገዛት የሚገባቸው በመሆናቸው ሳይሆን ክርስቶስን ለመታዘዝ ስንል ነው። የሚወደንን ክርስቶስን ለማክበርና ለመታዘዝ ስንል የራሳችንን ፈቃድ ትተን ሌሎች የራሳቸውን መንገድ እንዲከተሉ እንፈቅድላቸዋለን። የሚገርመው ሌሎች ይህንን ወይም ያንን እንዲያደርጉ መፈለጋችንን ስንተው ብዙውን ጊዜ የምንመርጠውን እንድናደርግ ይፈቅዱልናል። ነገር ግን በፍላጎታችን ላይ በምናተኩርበት ጊዜ ከፍላጎታቸው ላለመመለስ ይጥራሉ።

ለ. ሚስቶች ለባሎቻቸው መገዛት አለባቸው። ብዙውን ጊዜ ወንዶች ይህን አሳብ አላግባብ ሲጠቀሙ፥ ሴቶች ደግሞ ይቃወሙታል። ብዙውን ጊዜ ሚስቶች፥ «ለባለቤቴ ለምን መገዛት ያስፈልገኛል?» ይላሉ። ባሎች ደግሞ፥ «ከአለቅነቴ ሥር ልትታዘዝ ይገባል» ይላሉ። ነገር ግን ጳውሎስ ስለ መገዛት የሚናገረው ብዙውን ጊዜ እኛ ከምናስበው በተለየ መንገድ ነው። ጳውሎስ መገዛት እግዚአብሔር በፍጥረት ውስጥ ባስቀመጠው ሥርዓት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያስረዳል። መጽሐፍ ቅዱስን በምናጠናበት ጊዜ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ክርስቶስ ወደ ምድር ለላከው ለእግዚአብሔር አብ እንደ ተገዛ እንመለከታለን። ይህ መገዛት ግን በፍቅር ላይ የተመሠረተ እንጂ ጭቆናን የሚያስከትል አይደለም። ክርስቶስ ከቤተ ክርስቲያን የሚጠብቀውም ይህንኑ ዓይነት መገዛት ነው።

ከእነዚህ አሳቦች ስለ መገዛት ሁለት ጠቃሚ እውነቶችን እንማራለን። በመጀመሪያ፥ መገዛት ለሚገዙለት ሰው የበታች መሆንን አያሳይም። አብና ወልድ እኩል አምላክ ናቸው። በሥልጣን ግን ወልድ ለአብ ይገዛል። ወንዶችና ሴቶች በእግዚአብሔር ዓይን ፊት እኩል ናቸው። ለዚህ ነው ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ወንድ የለም ሴት የለም ያለው (ገላ. 3፡28)። ነገር ግን እግዚአብሔር በመሠረተው ሥርዓት ወንዶች ከሴቶች በላይ ተሰይመዋል። ሁለተኛ፥ የተጠበቀው መገዛት አብ ከወልድ የጠየቀውና ወልድም ከቤተ ክርስቲያን የጠየቀው ዓይነት ነው። አብም ሆነ ወልድ ከሥራቸው ያሉትን ለመጨቆን ወይም ለመግደል ኃይላቸውን አይጠቀሙም። ነገር ግን ከሥራቸው ያሉትን ይወዳሉ ያከብራሉ። በመሠረቱ በዚህ ክፍል ውስጥ የቀረበው መገዛት የአሳብ ልዩነት በሚከሰትበት ጊዜ ሊኖረን የሚገባው አመለካከት ነው። ከክርስቶስ ጋር በነበረው ግንኙነት ውስጥ እንደታየው እግዚአብሔር የሚጠብቀው በጉዳዮች ላይ በጋራ መወያየት፥ ማን ምን እንደሚሠራ መወሰንን፥ የሁለቱንም ወገኖችን ፍላጎት መጣጣምን ነው። ነገር ግን እኛ ሰዎች ስለሆንን በአሳብ የምንለያይባቸው ጊዜያት አሉ። በእነዚያ ጊዜያት ሚስት ባትስማማ እንኳ ለባሏ ውሳኔ መገዛት ይጠበቅባት ነበር።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለአንድ ሰው ሥልጣን በሚሰጥበት ጊዜ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል ባሎች ማስታወስ ይኖርባቸዋል። ለምሳሌ፥ ንጉሥ ሥልጣን ቢኖረውም ከሥሩ ላሉት ሰዎች በጎነት የመሥራት ኃላፊነት አለበት። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ባል በቤተሰቡ ላይ ሥልጣን አለው። ይህ ግን በቀዳሚነት ፍላጎታቸውን የማሟላት ኃላፊነት እንዳለበት ያሳያል።

የውይይት ጥያቄ፡- መንፈሳዊ የቤተሰብ አገዛዝንና ሥልጣንን ብዙ ክርስቲያኖች ከሚይዙት ግንዛቤ ጋር አነጻጽር። ሚስት መንፈሳዊ መገዛትን፥ እንዴት ልታሳይ እንደሚገባ ምሳሌዎችን ስጥ። አምላካዊ ሥልጣን እንዴት በባል በኩል ሊታይ እንደሚችል በምሳሌ አስረዳ።

ሐ. ባል ሚስቱን እንዲያፈቅር ታዟል። ፍቅር የሚለው ቃል ራስን ለሌሎች ጥቅም አሳልፎ መስጠትን ያመለክታል። ስለሆነም፥ ባል ሊጠይቅ የሚገባው ዐቢይ ጥያቄ፡- «ሚስቴን ለመርዳት ምን ላደርግ እችላላሁ? ለቤት ሥራዋና ለልጆች እንክብካቤ ምን ባደርግላት ይበጃል? ሌሎች እንደ ትምህርት የመሳሰሉ የምትፈልጋቸው ነገሮች ምን ምንድን ናቸው?» የሚል መሆን አለበት። ጳውሎስ ይህን አሳብ ለማብራራት እንደገና የክርስቶስንና የቤተ ክርስቲያንን ግንኙነት በምሳሌነት ጠቅሷል። ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ወይም ጌታ ስለሆነ፥ ቤተ ክርስቲያን ልትገዛለት ይገባል። ክርስቶስ ግን ከፍቅሩ የተነሣ ለቤተ ክርስቲያን ለመሞት ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል። ባልም እንዲሁ ራሱን በፍቅር ለሚስቱ እሳልፎ ሊሰጥ ይገባል። ጳውሎስ እንዲህ ዓይነቱ አመለካከት ለባል ጠቃሚ መሆኑን ለማሳየት ሌላም ምሳሌ ሰጥቷል። ባልና ሚስት አንድ አካል ስለሆኑ፥ ባል ሚስቱን በሚበድልበት ጊዜ ሁሉ ራሱን ይጎዳል። በፍቅር በሚረዳት ጊዜ ደግሞ ራሱን ይረዳል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከሚስት መገዛትና ከባል የክርስቶስን የሚመስል የመሥዋዕትነት ፍቅር ከማሳየት የትኛው የሚከብድ ይመስልሃል? መልስህን አብራራ። ለ) ባል ለሚስቱ በተግባራዊ መንገድ ፍቅሩን ሊያሳይ የሚችልባቸውን አንዳንድ ምሳሌዎች ዘርዝር። ሐ) አብዛኞቹ ክርስቲያን ባሎች ከሚስቶቻቸው ጋር በዚህ መንገድ የሚዛመዱ ይመስልሃል? ይህ በቤተሰብ ውስጥ የሚረጋገጠው እንዴት ነው?

መ. ልጆች ለወላጆቻቸው መታዘዝ አለባቸው። በዚህ በምንኖርበት ዘመን ልጆች ለወላጆቻቸው በአጥጋቢ ሁኔታ አይታዘዙም። ወላጆቻቸው ብዙም የተማሩ ባለመሆናቸው ይንቋቸዋል። ይህ ግን መጽሐፍ ቅዱስ ከሚናገረው መንፈሳዊ ግንኙነት ይቃረናል። ጳውሎስ ከአሥርቱ ትእዛዛት አንዱን ለዚህ ትምህርት መሠረት አድርጎ ይጠቅሰዋል። እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን ወላጆቻቸውን ከታዘዙ መልካም ሕይወት እንደሚኖራቸው ገልጾላቸው ነበር። ዛሬም ይህ እውነት ነው። ልጆች ከወላጆቻቸው የበለጠ ሊማሩና ገቢ ሊያመጡ ቢችሉም፥ ወላጆቻቸውን ከማክበር ሊቆጠቡ አይገባም። ብዙውን ጊዜ በሰው ሕይወት ውስጥ ከፍተኛውን ጠቀሜታ የሚያስገኙት፥ ከወላጆች የተገኙ መርሆችና እውነቶች ናቸው። በወላጆች ላይ ማመፅ በሥልጣናት ሁሉ ላይ ወደ ማመፅ ስለሚመራ ልጆች መታዘዝንና መገዛትን ካልተማሩ የተሳካ ሕይወት ሊኖራቸው አይችልም።

ሠ. አባቶች ልጆቻቸውን ማሠልጠንና ማስተማር እንጂ ማስቆጣት የለባቸውም። አባት የቤቱ ራስ ስለሆነ ልጆች አባታቸውንና እናታቸውን ማክበር አለባቸው። ይህ ሥልጣን ግን ኃላፊነትን የሚያስከትል ነው። እግዚአብሔር ለቤተሰብ ልጆችን የሰጠው ለምንድን ነው? የቤተሰቡን ስም ከትውልድ ትውልድ ለማስተላለፍ ብቻ ነው? አይደለም። ነገር ግን ወላጆች ለልጆቻቸው ሥጋዊና መንፈሳዊ ዕድገት የግል ኃላፊነትን እንዲወስዱ ነው። ጳውሎስ ይህ በቀዳሚነት የአባት ኃላፊነት እንደሆነ አስረድቷል። ብዙውን ጊዜ ግን ወላጆች በተለይም አባቶች ለዚህ ኃላፊነት አጽንኦት አይሰጡም። ሥልጠናው በሰንበት ትምህርት ቤት ወይም በመንግሥት ትምህርት ቤት እንደሚካሄድ ያስባሉ። እግዚአብሔር ግን ለልጆቻቸው ሥልጠና ወላጆችን በተለይም አባቶችን ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። ሳንይቲስቶች ወላጆች በመጀመሪያዎቹ 5 ወይም 6 ዓመታት ውስጥ በልጆቻቸው ላይ ከሁሉም የላቀ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ ያስተምራሉ። ልጆች እሴቶቻቸውን የሚማሩት በእነዚህ የሕፃንነት ጊዜያት ነው። እግዚአብሔርን መውደድ ወይም መጥላት የሚማሩትም በዚሁ ጊዜ ነው። በዓለም ሁሉ ከ80% የሚበልጠ ክርስቲያኖች በክርስቶስ ላይ እምነታቸውን የጣሉት ከ15 ዓመታቸው በፊት ነው። ስለሆነም፥ ለልጆቻችን በጌታ መንገድ ስለመመላለስ የምናስተምረው እውነት በልጁ ማመንና ወደ መንግሥተ ሰማይ መሄድ ላይ ዐቢይ ሚና ይጫወታል። (ማስታወሻ፡- መጽሐፍ ቅዱስ ወላጆች ክርስቲያኖች መሆናቸው ልጆችን ክርስቲያን እንደሚያደርጋቸው አያስተምርም። እያንዳንዱ ግለሰብ ክርስቶስን ለመከተል የመምረጥ ኃላፊነት አለው። ወላጆች ልጆቻቸው በክርስቶስ እንዲያምኑ ሊጸልዩና ከሦስት ወይም አራት ዓመት ዕድሜያቸው ጀምሮ ሊያስተምሯቸው ይገባል።)

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች ወላጆች ያሏቸው አብዛኞቹ የክርስቲያን ወላጆች ልጆች ወላጆቻቸውን የሚታዘዙ ይመስልሃል? ለ) ልጆቻቸውን በጥንቃቄ ሲያስተምሩና ሲያሠለጥኑ ያየሃቸውን ወላጆች ምሳሌዎች ዘርዝር። ሐ) ጥቂት ወላጆች ብቻ ልጆቻቸውን በጥንቃቄ የሚያስተምሩት ለምን ይመስልሃል? መ) ወላጆቹን የሚታዘዝ ሰው ምን በረከት ሲያገኝ ተመልክተሃል? ሠ) ወላጆቹን የማይታዘዝ ሰው ምን ችግሮች ሲገጥሙት አይተሃል?

ረ. ባሮች ጌቶቻቸውን መታዘዝ፥ ማክበርና መፍራት ይኖርባቸዋል። በጥንቱ ዓለም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ባሮች ነበሩ። ከእነዚህ ባሪያዎች አብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች ሆነዋል። አማኝ ባሮች ለገዟቸው፥ እንደ ዕቃ ለሚቆጥሯቸውና ለሚበድሏቸው ሰዎች ምን ዓይነት ምላሽ ሊሰጡ ይገባል ? ማመፅ ነበረባቸው? በጌቶቻቸው ኑሮ ላይ ችግር መፍጠር ነበረባቸው? ምንም እንኳ ጳውሎስ ከተቻለ ባሮች ነጻነታቸውን ሊቀዳጁ እንደሚገባ ቢገልጽም (1ኛ ቆሮ. 7፡20-22)፥ ፊት ለፊት ባርነትን ሲቃወም አንመለከትም። ጳውሎስ ባሮች እግዚአብሔር የሰጣቸውን ደረጃ ላለመቀበል እንዳይፍጨረጨሩና ምድራዊ ጌቶቻቸውን በሚገባ እንዲያገለግሉ መክሯቸዋል። ይህን የሚያደርጉት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ለጌቶቻቸው ሲገዙ እግዚአብሔርን ማገልገላቸው ስለሆነ ነው። ስለሆነም፥ ለጌቶቻቸው የሚሰጡት አገልግሎት ለክርስቶስ እንደሆነው ሁሉ በትጋት የሚካሄድ ሊሆን ይገባል። እግዚአብሔር ለምድራዊ ጌቶቻቸው ለሚያሳዩት አመለካከትና ተግባር በኃላፊነት ይጠይቃቸዋል። በአሁኑ ዘመን የድሮ ትውልዶች ዓይነት ባርነት የለም። ነገር ግን የዘመናችን የሥራ ግንኙነት ቀጣሪና ተቀጣሪ  በመባል ይታወቃል፡፡ አብዛኞቻችን የመንግሥት፥ የንግድ ኅብረተሰብ፥ የቤተ ክርስቲያን፥ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት፥ ወዘተ… ተቀጣሪዎች ነን። ለአሠሪዎቻችን ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? እንዳያባርሩን ብቻ ነው መሥራት ያለብን? ጳውሎስ የምንችለውን ያህል ከፍተኛ ተግባር ማከናወን እንዳለብን ይመክራል። በጊዜ ከሥራ ገበታችን ላይ ልንገኝ፥ በትጋት ልንሠራ፥ ታማኝ ልንሆን፥ በሰዓቱ ከሥራ ገበታችን ልንወጣ፥ ወዘተ… ይገባል። ክርስቶስ አሠሪያችን ቢሆን ምን እናደርግ ነበር ብለን በማሰብ ተግባራችንን ማከናወን አለብን። ለወንጌሉ እንደሚገባ መመላለስ ማለት ለአንድ አሠሪ በምንሠራበት ጊዜ በተቻለ ትጋት መሥራት አለብን ማለት ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ለአሠሪዎቻቸው እንዲህ ዓይነት አመለካካት አላቸው? ካልሆነ፥ ለምን? ለ) ክርስቲያን ሠራተኞች በአመለካከታቸው፣ በጊዜ አጠቃቀማቸው፥ በትጋታቸው፥ ወዘተ. . አሠሪዎቻቸውን እንዴት እንደሚያታልሉ ግለጽ። ክርስቶስ በዚህ ዓይነቱ አመለካከት የሚደሰት ይመስልሃል? ሐ) አሠሪህ ማን ነው? ከእርሱ ጋር ያለህን ግንኙነትና ሥራህን መርምር። ክርስቶስ በዚህ መንገድ ስትሠራ ሲያይህ ይደሰታል ወይስ አንተው በዚህ ሥራህ የምታፍርበት ይመስልሃል? ለአሠሪህ በምታበረክተው አገልግሎት ታከብረው ዘንድ ክርስቶስ ምን ዓይነት ለውጦችን እንድታደርግ የሚፈልግ ይመስልሃል? መ) ወደ ቤተ ክርስቲያን አምልኮ ለመሄድ ስትል ሰዓቱ ሳይደርስ ከሥራ ቦታህ በመነሣትህ እግዚአብሔር ደስ የሚሰኝብህ ይመስልሃል? ለምን?

ይህ ትምህርት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሆነን ለምናገለግልም ይሁን ተቀጥረን ለምንሠራ ሰዎች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ የሚሰጠን ነው። ብዙውን ጊዜ ሌላ ሥራ ያላቸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን ስብሰባ ለመሄድ ሲሉ ከሥራ ገበታቸው ላይ ቀደም ብለው ይነሣሉ ወይም አርፍደው ይደርሳሉ። ይህ በእግዚአብሔር ፊት ስሕተት ነው። የአንድ ሰው ወይም ድርጅት ሠራተኛ ለመሆን በተስማማህ ጊዜ፥ ጊዜህንና ሥራህን የመጠቀም መብት ሰጥተኸዋል። አሁን በሥራ ሰዓት ጉልበትህንና ጊዜህን ለእነርሱ መስጠት አለብህ። ስለሆነም፥ አርፍደህ ስትመጣ፥ ቀደም ብለህ ስትሄድ፥ የስንፍና ተግባር ስታከናውን ወይም ለቤተ ክርስቲያን ስብሰባ ብለህ ከሰዓቱ በፊት ስትሄድ እየሰረቅሃቸው ነው። እግዚአብሔር ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ የአሠሪህን ጊዜ መስረቅህን እንደ ጥሩ ማመኻኛ አይቀበለውም። «መንፈሳዊ» ሥራ ለመሥራት ከሰዎች «መስረቅህን» አይደግፍም።

ሰ. ጌቶች ባሮቻቸውን በፍትሐዊ መንገድ ማስተዳደር ይኖርባቸዋል። አንዳንድ ሀብታም ባሪያ እስተዳዳሪዎችም በክርስቶስ አምነው ነበር። ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች ባሮቻቸውን ነፃ እንዲያወጡ ባይነግራቸውም፥ በአግባቡ እንዲያስተዳድሯቸው አስጠንቅቋቸዋል። ጳውሎስ ባሪያ ፈንጋይነትን በቀጥታ ባይቃወምም ለክርስቲያኖች ይህንን ተቋም አጣጥሎባቸዋል። ጳውሎስ በእግዚአብሔር ፊት ሰዎች ሁሉ እኩል መሆናቸውን አስተምሯል። እግዚአብሔር ባሮችንና ነፃ ሰዎችን እኩል አድርጎ ይመለከታቸዋል። ሁለቱም በእርሱ አምሳል የተፈጠሩ ፍጥረቶች ናቸው። በክርስቶስ ካመኑ በኋላም ሁለቱም የእርሱ ልጆች ናቸው። ባሪያዎችም ለሥራ አፈጻጸማቸው፥ ጌቶች ደግሞ ባሮቻቸውን ላስተዳደሩበት ሁኔታ በእግዚአብሔር ይጠየቃሉ።

ክርስቲያን አሠሪዎች፥ «ሠራተኞቼን ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እያስተዳደርሁ ነኝ? ሊያስተዳድራቸው የሚችል በቂ ደመወዝ እከፍላቸዋለሁ? ወይስ ትርፉን ሁሉ ለራሴ ለመሰብሰብ እየሞከርኩ ነኝ? አፍቃሪና ቸር ነኝ ወይስ ጨካኝ?» ብለው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው። እግዚአብሔር ከድርጅትህ ውስጥ የሚሠሩትን ሰዎች ስለምታስተዳድርበት ሁኔታ በኃላፊነት እንደሚጠይቅህ አስታውስ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: