ክርስቶስ ጳውሎስ የሚያስተምረው የወንጌል መልእክት እምብርት ነው (ቆላ. 1፡24-2፡5)

ኖስቲኮች ሰው ከክፉ ዓለም ለማምለጥ ሊያከናውናቸው ይገባል ከሚሏቸው ምሥጢራዊ እውነቶች በተቃራኒ፥ ጳውሎስ ግልጽ የወንጌል እውነቶችን ሰብኳል። ለመሆኑ የዚህ ወንጌል መሠረቱ ምንድን ነው?

የወንጌል ትኩረቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ጳውሎስ በዚህ ክፍል ውስጥ በሚከተሉት ነገሮች ላይ አጽንኦት ይሰጣል።

ሀ. ጳውሎስ ወንጌሉን የመስበክ ቀዳማዊ ተልዕኮ ያለው የክርስቶስ አገልጋይ ነው። ይህ ተልዕኮ መከራ መቀበልን ይጨምር ነበር። ጳውሎስ በዚህ ጊዜ ለዚሁ ወንጌል ወኅኒ ቤት ታሥሮ ነበር። በማፈር ፈንታ ጳውሎስ፥ በዚህ መከራ ደስ ይለኛል ይላል። ጳውሎስ «በሥጋዬ በክርስቶስ መከራ የጎደለውን እፈጽማለሁ» ብሏል። ይህ ለመረዳት የሚያስቸግር አገላለጽ ነው። ይህ የክርስቶስ ሞት አማኞችን ለማዳን እንደማይበቃና ሞቱ ለኃጢአታችን በቂ ይሆን ዘንድ እኛም መከራ መቀበል አለብን ማለት እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ጳውሎስ ቀደም ሲል የክርስቶስ ሞት ነገሮችን ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት እንደሚያስታርቅ ገልጾአል። ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ አካል ስለመሆኗ የሚያስብ ይመስላል። ስለሆነም፥ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርስ ነገር ሁሉ በክርስቶስ ላይ ይደርሳል። ለዚህ ነው ክርስቶስ በሐዋርያት ሥራ 9፡4-5 ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ማሳደዱ እርሱን ማሳደድ መሆኑን የገለጸው። ይህም ማለት በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ፥ በምድር ላይ በክርስቶስ ላይ የደረሰው ዓይነት መከራ (ፈተና፥ ስደት፥ ሞት) በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ ይቀጥላል ማለት ነው። የምስራቹ ቃል ስብከት በመከራ ውስጥ ያድጋል። የክርስቶስ አካል ክፍል የሆኑ ክርስቲያኖች መከራን በሚቀበሉበት ጊዜ፥ ክርስቶስም ከእነርሱ ጋር ይሠቃያል። የጳውሎስ መታሠር በክርስቶስ ላይ ሥቃይን አስከትሏል። እኛም ለወንጌሉ በምንሠቃይበት ጊዜ ክርስቶስ አብሮን ይሠቃያል። ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ መከራችን በሙሉ ይጠናቀቃል። የእርሱም መከራ ፍጻሜን ያገኛል። በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር በልጆቹና ከዚህም የተነሣ በራሱ ላይ እንዲደርስ የፈቀደው መከራ ሁሉ ያከትማል። በዘላለሙ መንግሥት በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይም ሆነ በክርስቶስ ላይ የሚደርስ መከራ አይኖርም።

ለ. ወንጌሉ ምሥጢርን አካቷል። ሐሰተኛ አስተማሪዎች ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ከእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን የሚያስገኝ ምሥጢር እንዳላቸው ተናግረው ነበር። ጥልቅ መንፈሳዊነት የሚገኘው እነርሱ ዘንድ ብቻ እንደሆነና ልዩውን ቃል ወይም ሐረግ ሊያውቁ የሚችሉት ከእነርሱ ቡድን ጋር ግንኙነት ያላቸው ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ይናገሩ ነበር። ልዩው ቃል ወይም ሐረግ የእግዚአብሔርን ተጨማሪ ሞገስ ያስገኝላቸዋል ሲሉ አስተምረዋል። ጳውሎስ ግን አንድ ጠቃሚ ምሥጢር ብቻ እንዳለ ያስረዳል። ይኸውም የኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ነው። ይህ ወንጌል ለጥቂቶች ብቻ የተሰጠ ምሥጢር ሳይሆን ለሰዎች ሁሉ እየተሰበከ ያለው ነበር። ምሥጢሩ እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ዘመን ያልገለጠውና አሁን ግን ለሕዝቡ ሁሉ ያስታወቀው ነበር። ይህ ምሥጢር ምን ነበር? ምሥጢሩ አሕዛብ በክርስቶስ በማመን በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ሙሉ ተቀባይነት ማግኘታቸው ነበር። ይህ ወንጌል በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያተኩራል። እርሱም በሕዝቡ ልብ ውስጥ የሚያድር አምላክ ነው።

ሐ. ለሰዎች የሚያስፈልገው ብቸኛ ‹ጥበብ› ይኼ ወንጌል ብቻ ነው። የዓለም ጥበብ ወይም የኖስቲኮች ስውር ፍልስፍናዎች አያስፈልጉንም። ሁሉም ሰው ወንጌሉን ተረድቶ በሚቀበልበት ጊዜ ምሉዕ ይሆናል። («ፍጹም» የሚለው ቃል ምሉዕነትን እንጂ ኃጢአት አልባነትን አያመለክትም።)

መ. ይህ ወንጌል ጠቃሚ በመሆኑ ጳውሎስ በሙሉ ኃይሉ አሰራጭቶታል። ለዚሁ ወንጌል እስከ መታሠርም ደርሷል። ጳውሎስ መከራን የተቀበለው ለራሱ ወይም ለሚያውቃቸው አብያተ ክርስቲያናት ብቻ አልነበረም። ምንም እንኳ ለቆላስይስ የቅርብ ከተማ የነበረችውን ሎዶቅያን ጎብኝቶ ባያውቅም፥ መከራው ለእነርሱ ጥቅም ነበር። የጳውሎስ መከራን መቀበል ዛሬ ላለን ሰዎች ጥቅም አለው። ምክንያቱም በጳውሎስ መከራና በሰበከው ወንጌል አማካኝነት አሕዛብ የሆንን ሰዎች ድነት (ደኅንነትን) አግኝተናል። ጳውሎስ እሥር ቤት ውስጥ ሆኖ የጻፋቸው መልእክቶችም እጅግ ጠቅመውናል።

ምንም እንኳን ጳውሎስ ውጤታማ ወንጌላዊና ሐዋርያ ቢሆንም፥ ስለምንም ነገር መመካት እንደሌለበት ያውቅ ነበር። ያገኛቸው ውጤቶችና ክንውኖች ክርስቶስ በእርሱ በኩል የመሥራቱ ውጤቶች እንደነበሩ ያውቅ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ሁላችንም ለወንጌሉ መከራን እንድንቀበል እንዳቀደ ተገልጾአል። ሀ) ለወንጌሉ መከራ እየተቀበልህ ያለኸው እንዴት ነው? ለ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ከመከራ ለመሸሽና ለወንጌሉ መከራን ላለመቀበል የሚፈተኑት እንዴት ነው? ሐ) የክርስቶስ መከራ ተካፋይ መሆን ክብር የሚሆነው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d