የተቀደሰ አኗኗር (ቆላ. 3፡1-17)

አንድ ጊዜ አንድ መምህር ለስኬታማ ክርስቲያናዊ ሕይወት ምሥጢሩ በሕይወታችን እውነቶችን ሚዛናዊ ማድረግ ነው ብሎ ነበር። ብዙውን ጊዜ የተሳሳተ ልምምድና ትምህርት የሚከሠተው አንድን እውነት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች እውነቶች ጋር ሚዛናዊ ከማድረግ ይልቅ እንደ ዋነኛ እውነት አድርገን ስንወስደው ነው። ይህንን በብዙ መንገዶች መመልከት ይቻላል። በልሣን መናገር መንፈሳዊ ስጦታ መሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመልክቷል። ነገር ግን በልሳን መናገር የችግሮች ሁሉ መፍትሔ ወይም የመንፈሳዊነት ምልክት ነው ብሎ ማሰቡ ሚዛናዊነት የጎደለው አስተሳሰብ ነው። የእግዚአብሔር ቃል ሌሎች ብዙ መንፈሳዊ ስጦታዎችና ተግባራት ለመንፈሳዊነት እኩል ጠቀሜታ እንዳላቸው ያስተምራል። መዘመርና ማምለክ አስፈላጊዎች ናቸው። ነገር ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጋር መመጣጠን አለባቸው። የሰው ወይም የቤተ ክርስቲያን ደንቦች ሕጋዊ ቢሆኑም ቀዳማዊ አጽንኦት ሊሰጣቸው አይገባም። ይልቁንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ያለንን ግንኙነት እናንጸባርቅ ዘንድ በልባችን፥ በአመለካከታችንና በተግባራችን ላይ ልናተኩር ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰዎች የሚያተኩሩባቸውንና የእምነት ወይም የተግባር አለመመጣጠን የሚያስከትሉትን ነገሮች ግለጽ። ለ) አዲስ ኪዳን ለመንፈሳዊ ሕይወታችን በጣም ጠቃሚዎች መሆናቸውን እየገለጸ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብዙውን ጊዜ የማይነገሩትን አንዳንድ እውነቶች ዘርዝር። አገልጋዮች እነዚህን እውነቶች የሚያስተምሩት ለምንድን ነው?

በቆላስይስ የነበሩ አስተማሪዎች በብዙ ሰው ሠራሽ ደንቦች ላይ ትኩረት ያደርጉ ነበር። አይሁዶችም የራሳቸው ደንቦች ነበሩዋቸው። ግሪኮችም እንዲሁ። ነገር ግን እነዚህ ሁሉ አንድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር በሚያደርገው ግንኙነት ላይ የሚያስከትሉት አዎንታዊ ተጽዕኖ አልነበራቸውም። ጳውሎስ የቆላስይስ ክርስቲያኖች እነዚህን ከመከተል እንዲቆጠቡ አስጠንቅቋቸዋል። ይህ ማለት ክርስቲያኖች የሚከተሉት ሕግ ወይም ትእዛዝ የለም ማለት አይደለም። የምንፈልገውን የማድረግ «ነጻነት» የለንም።

ነገር ግን እግዚአብሔር እንድንሆን የሚፈልገውን የመሆን፥ እርሱ በፈጠረን ዓላማ የመኖርና ክርስቶስ ባዳነን መንገድ የመመላለስ ነጻነት አለን። ይህ የቆላስይስ መልእክት የመጨረሻው ክፍል (ቆላ. 3-4) እንዴት ላመንንበት ወንጌል እንደሚገባ መኖር እንዳለብን ያሳያል።

ሁላችንም ከምንጋፈጣቸው ችግሮች አንዱ የምናምነውን ከአኗኗራችን ጋር ማስማማት ነው። ባኗኗራችን ክርስቶስን እንደምናስከብር መናገር ወይም ኢየሱስ ጌታ ነው ማለቱ ቀላል ነው። ነገር ግን በሥራ ቦታ፥ በቤት፥ በማኅበረሰቡ መካከል ወይም በትምህርት ቤት የምናከናውነው ተግባር ክርስቶስን እንደሚያስከብር የምንገመግመው ጥቂቶች ነን። በቀዳማዊነት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በምናከናውነው ተግባር በአምልኮአችን ወይም እንደ ዝሙት ያሉትን ታላላቅ ኃጢአቶች ባለመፈጸም ክርስቶስን እንደምናስከብር እናስባለን። ለወንጌሉ እንደሚገባ መመላለስ ማለት ግን የሕይወታችንን ክፍሎች በሙሉ ለክርስቶስ አሳልፎ መስጠት ማለት ነው። ተግባራችን ክርስቶስን እንደሚያስከብር ወይም እንደማያስከብር ከምንገመግምባቸው መንገዶች አንዱ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለራሳችን ማቅረብ ነው። ክርስቶስ ቢሆን ምን ያደርግ ነበር? ክርስቶስ ነጋዴ ቢሆን ኖሮ ምን ያደርግ ነበር? ጉቦ ይሰጥ ነበር? ተገቢ ያልሆነ ዋጋ ያስከፍል ነበር? የውጪ አገር ዜጎችን ያጭበረብር ነበር? ክርስቶስ ተማሪ ቢሆን ምን ያደርግ ነበር? ከተማሪዎች መልስ ይኮርጅ ነበር? ፈተናውን ለመስረቅ ይሞክር ነበር? በቤትስ ምን ያደርግ ነበር? ልጆቹና ሚስቱ እንደ ባሮች ያገለግሉት ዘንድ ስማቸውን እየጠራ ያዋክባቸው ነበር? ክርስቶስ በቤተ ክርስቲያን አመራር ውስጥ ቢኖር ምን ያደርግ ነበር? ከሕዝቡ ጋር ሳይቀላቀል እርሱ የሚፈልገውን ብቻ እንዲያደርጉ በሥልጣን ያዛቸው ነበር? ክርስቶስ ራሱን ለማስከበር፥ ኃይሉን ለማሳየት፥ ከመሪነት እንዲወርድ በሚጠየቅበት ጊዜ ፈቃደኛ ባለመሆን፥ የአመራር ጥቅማ ጥቅሞችን ከሕዝቡ ይልቅ ወደ ራሱና ወደ ቤተሰቦቹ እንዲግበሰበሱ በማድረግ ሰዎችን ይበድል ነበር? ክርስቶስ ለመንግሥት ቢሮ ቢሠራ ኖሮ ምን ያደርግ ነበር? ሰዓቱን እክብሮ ይሠራ ነበር? ወይስ አርፍዶ መጥቶ ሰዓቱ ሳይደርስ ይሄድ ነበር? ጉቦ በመቀበል አድልዎ ይፈጽም ነበር? ወይስ ሰዎችን በእኩልነት ያስተናግድ ነበር? በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስብከት እንዲያቀርብ ቢጠየቅ ምን ያደርግ ነበር? ብዙም ሳያጠና የሰበከው ጥሩ እንደሚሆን ተስፋ ያደርግ ነበር? ወይስ በሚገባ በማጥናት፥ መልእክቱን በግልጽ ለማቅረብ በመዘጋጀትና እግዚአብሔር መልእክቱን እንዲባርክ በጸሎት በመጠየቅ የድርሻውን ይወጣ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ከላይ የቀረቡትን ጥያቄዎች ተመልከት። ሀ) ከላይ በቀረቡት ሁኔታዎች ሁሉ ውስጥ ክርስቶስ ምን የሚያደርግ ይመስልሃል? ይህንን ብዙዎች ክርስቲያኖች ክሚያደርጉት ጋር በማነጻጸር መልስ። ለ) ይህ ክርስቶስን እያስከበሩ ስለ መኖርና ዛሬ በተቃራኒው ብዙ ክርስቲያኖች ስለሚኖሩበት ሁኔታ ምን ያሳያል?

ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ ለወንጌሉ እንደሚገባ መኖር አለመኖርህን ያሳያል። ዓለምን የምንኮርጅ ከሆነ በተገቢው መንገድ እየኖርን አለመሆናችንን እናውቃለን። እግዚአብሔር በሚፈልገው መንገድ የማንኖር ከሆነ ደግሞ እግዚአብሔር ኃጢአትን ምን ያህል እንደሚጠላ አልተገነዘብንም ማለት ነው። እንዲሁም አማኞች እንደ መሆናችን ለኃጢአት የሞትንና ለእግዚአብሔር ሕያዋን የሆንን አዳዲስ ፍጥረታት መሆናችንን አልተገነዘብንም ማለት ነው። ዛሬ ከምንጋፈጣቸው ዐበይት ችግሮች አንዱ አብዛኞቹ ምእመናን ክርስቶስን በሚያስከብር መንገድ የማይኖሩ መሆናቸው ነው። ክርስቶስን የማናስከብር ከሆነ ደግሞ የሚገባንን ያህል አንወደውም ማለት ነው።

ትክክለኛ ነገሮችን ማመኑ ብቻ በቂ አይደለም። እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ መኖር አለብን። በዚህ የቆላስይስ መልእክት የመጨረሻ ክፍል ጳውሎስ አንዳንድ ነጥቦችን ጠቅለል ባለ መልኩ ያቀርባል። እነዚህም ነጥቦች እምነታችንን ለማንጸባረቅና በወንጌሉ እንደሚገባ ለመመላለስ በሕይወታችን ውስጥ ሊለወጡ የሚገባቸውን ነገሮች ያሳያሉ።

ሀ. እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ለመኖር የሚያግዙ ሁለት መሠረታዊ መርሆዎች፥ በቆላስይስ 3፡1፥ ጳውሎስ የቆላስይስ ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ጋር መተባበራቸውን ያስገነዝባቸዋል። ከዚህም የተነሣ ለኃጢአት ባሕርያቸው ሞተው እግዚአብሔርን ለማገልገል ከክርስቶስ ጋር ሕያዋን ሆነዋል። አንድ ቀን ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ከእርሱ ጋር አብረው ይከብራሉ። ጳውሎስ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መልኩ ለመኖር ልናደርጋቸው የሚገቡ ሁለት መሠረታዊ መርሆዎች እንዳሉ ያስረዳል።

በመጀመሪያ፥ «በላይ ያለውን እሹ»። ጳውሎስ ያስፈልጉናል ስለምንላቸው ነገሮች ነው የሚናገረው። ዓይኖቻችንን በሰማይ ላይ እንድናሳርፍ ይናገራል። ዋናው ነገር የዘላለም ሕይወት፥ ከክርስቶስ ጋር መንገሥ፥ በእርሱ መሸለምና እርሱ እንደሚፈልገው መኖር ነው። ዘላለማዊ እሴት ላላቸው ነገሮች ቅድሚያ መስጠት አለብን። ይህም የምንወደውንና ለኃጢአታችን የሞተውን ክርስቶስን ለማስደሰት መሻታችንን ያሳያል። የዓለምን ነገሮች (ክብር፥ ሀብት፥ ትምህርት፥ ጥሩ አኗኗር፥ ወዘተ…) በመሻት ቀዳማይ ትኩረት ልንሰጣቸው አይገባም።

ሁለተኛ፥ «በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም።» ቀኑን ሁሉ የምናስበው ነገር ለሕይወታችን ወሳኝ ጉዳይ ነው። ዓለም ስፍራ ስለሚሰጣቸው ነገሮች የምናስብ ከሆነ፥ ኢየሱስ ጌታ እንደሆነ የሚያመለክት ሕይወት ልንኖር አንችልም። ነገር ግን እግዚአብሔር አስፈላጊ ናቸው ስለሚላቸው ነገሮች የምናስብ ከሆነ፥ ሕይወታችን ይለወጥና እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንኖራለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከሰማይ ያልሆኑትንና ክርስቲያኖች ልባችንን ልናሳርፍ የምንችልባቸውን ነገሮች ዘርዝር። ለ) ክርስቲያኖች አእምሮአችንን ልናሳርፍባቸውና እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ከመኖር የሚመልሱንን ነገሮች ዘርዝር። ሐ) እግዚአብሔርን በሚያስከብሩና በሚያስደስቱ ነገሮች ላይ እናተኩር ዘንድ ልባችንንና አእምሯችንን ልናሠለጥን የምንችልባቸው መንገዶች ምን ምንድን ናቸው?

ለ. ጳውሎስ ክርስቲያኖች ሊያደርጓቸው የማይገቧቸውን «አሉታዊ» ነገሮች ይዘረዝራል። እነዚህ ነገሮች በእግዚአብሔር ዓይኖች ፊት ጥሩዎች ባለመሆናቸው ልንገድላቸው ወይም ልናስወግዳቸው የሚገቡ ናቸው።

  1. ልንቆጠብባቸው የሚገቡን የተለያዩ ኃጢአቶች። ከእነዚህ ኃጢአቶች አንዳንዶቹ ታላላቅ ኃጢአቶች ናቸው የምንላቸው ናቸው። እነዚህም እንደ አመንዝራነትና ዝሙት ያሉ ናቸው። እጅግም መጥፎዎች አይደሉም የምንላቸው ሌሎች ኃጢአቶች ደግሞ ምኞት፥ ክፉ አሳብና ስግብግብነት ናቸው። አንድ የቤተ ክርስቲያን አባል ዝሙት ከፈጸመ ቤተ ክርስቲያን ልትቀጣው ትችላለች። የስግብግብነትን ኃጢአት ግን እምብዛም ከቁም ነገር አንቆጥረውም። እግዚአብሔር ግን ኃጢአትን ትንሽና ትልቅ ብሎ አይከፋፍልም። ሁሉም ኃጢአት በእግዚአብሔር ላይ የሚፈጸም ዓመፅ በመሆኑ ትክክል ሊሆን አይችልም። እንዲያውም ጳውሎስ ስግብግብነት ጣዖትን እንደ ማምለክ ነው ብሏል። ይህ በየጠዋቱ የምንሰግድለት ቁሳዊ ጣዖት ላይሆን ይችላል። በእግዚአብሔር ፊት ግን ጣዖት ከእግዚአብሔር አስበልጠን የምንወደው ማንኛውም ነገር ነው። ስግብግብነት ገንዘብን ከእግዚአብሔር በላይ መውደድ ነው። ንግዳችንን ለማስፋፋት ብለን ጉቦ ስንሰጥ በልባችን ውስጥ ስግብግብነትና አምልኮተ ጣዖት አቆጥቁጠዋል ማለት ነው።
  2. የቆላስይስ አማኞች ግንኙነቶችን የሚያወድሙትንና እግዚአብሔርን የማያስከብሩትን ባሕርያትና ተግባራት ማስወገድ ያስፈልጋቸው ነበር። ጳውሎስ እንደ ቁጣ፥ ንዴት፥ ክፋት፥ ስድብ፥ ጸያፍ ንግግር፥ ውሸት ያሉትን ዘርዝሯል። ጳውሎስ እነዚህ ከወሲባዊ ኃጢአቶች እንደሚያንሱ አልገለጸም። ሁሉም ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነው። ይህም ሆኖ፥ ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ሌሎችን በመጥላትና በማማት እግዚአብሔርን ይበድላሉ። በዚህም ሁሉ ኃጢአት መፈጸማቸው ትዝ አይላቸውም። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚከሠቱት ክፍፍሎች የአብዛኞቹ መንሥኤዎች ክፋት፥ ስድብና ውሸት ናቸው። እግዚአብሔር እነዚህን ኃጢአቶች ምን ያህል እንደሚጠላቸው የምንገነዘበው መቼ ይሆን?
  3. አማኞች የክርስቶስ አካል በሆነችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን አንድነት ማስታወስ ነበረባቸው። ጳውሎስ በዘመኑ የነበሩትን አንዳንድ ክፍፍሎች ዘርዝሯል። በአይሁድ (በተገረዙ) እና በግሪኮች (አሕዛብና ያልተገረዙ)፥ ባልተማሩ (አረማዊ) እና በተማሩ፥ እስኩቴስ (በአገራችን ቆላማ አካባቢዎች የሚገኙትን ዘላኖች የሚመስሉ)፥ በባሪያና በጨዋ (ነፃ) ሰዎች መካከል ልዩነቶች ነበሩ። የጎላ ልዩነቶች አስፈላጊ ነገሮች አይደሉም። ትምህርት፥ የአኗኗር ዘይቤ (ዘላኖችና ገበሬዎች)፥ እንዲሁም የኢኮኖሚ ደረጃዎች (ነፃ ወይም ባሪያ) አስፈላጊዎች አይደሉም። በክርስቶስ ካመንን እርሱ በሁላችንም ውስጥ በእኩል ደረጃ ይኖራል።

ሐ. የቆላስይስ አማኞች እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኙትን ተግባራትና ባሕርያት እንዲለብሱ ተጠይቀዋል። እግዚአብሔር የሚፈልገው ኃጢአት መሥራታችንን እንድናቆም ብቻ ሳይሆን፥ አዎንታዊ ለውጦችንም እንድናሳይ ጭምር ነው። ጳውሎስ በክርስቶስ አካል ውስጥ አንድነትንና ኅብረትን በሚያመጡት ነገሮች ላይ ያተኩራል። አንድነትን የሚያመጡት እነዚህ ባሕርያት ምን ምንድን ናቸው? እነዚህም «ምሕረት፥ ርኅራኄ፥ ቸርነት፥ ትሕትና፥ የዋህነት፥ ትዕግሥት» ናቸው። በአሳብ የመለያየት ሁኔታ መከሠቱ የማይቀር ነው። ነገር ግን ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው ይቅር እንዲባባሉ ጳውሎስ ጥሪ አቅርቧል። እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ ሌሎችን ይቅር እንድንል በሚጠይቅበት ጊዜ እርሱ እኛን ይቅር እንዳለ ይናገራል። ቅዱስ የሆነው አምላክ በእርሱ ላይ አስከፊ ኃጢአት የሠራነውን ሰዎች ይቅር ብሎናል። እኛም እኛ እግዚአብሔርን ከበደልነው ኃጢአት ጋር ሲነጻጸሩ በጥቂቱ የበደሉንን ሰዎች ይቅር ልንል ይገባል። ብዙውን ጊዜ ሌሎችን ይቅር ለማለት በማንፈልግበት ጊዜ ምን ያህል ኃጢአተኞች እንደነበርን ወይም እግዚአብሔር ምን ያህል ይቅር እንዳለን አልተገነዘብንም ማለት ነው። ጳውሎስ እነዚህን ሁሉ ባሕርያትና ተግባራት የሚያቅፈውን ፍቅርን በአጽንኦት ገልጾአል።

መ. አማኞች በእግዚአብሔር ቃል ሥር መስደድ ያስፈልጋቸው ነበር። ብዙ ሰዎች ሀብታም ለመሆን እንደሚፈልጉ ሁሉ፥ የእግዚአብሔርም ሕዝብ ቃሉን በመረዳት መበልጸግ አለባቸው። የእግዚአብሔርን ቃል በግል ደረጃ ማወቁ ለሁለት ዐበይት አገልግሎቶች ጠቃሚ ነው።

  1. ሌሎችን ማስተማር። በኮሚኒዝም ዘመን «የተማረ ሁሉ ያስተምር» የሚል መፈክር ይነገር ነበር። ይህ ከእኛ ከሚጠበቀው ነገር ጋር ይመሳሰላል። ሁላችንም በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ አስተማሪዎች ነን። ወላጆች ከሆንን ልጆቻችንን፥ በሳል ክርስቲያኖች ከሆንን አዳዲስ አማኞችን እናስተምራለን። የእግዚአብሔርን ቃል አውቀን ለሌሎች ማስተላለፍ አለብን።
  2. አምልኮ። ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል ማወቅ ከአምልኮ ጋር ማያያዙ አስገራሚ ነው። ከዚህም እግዚአብሔርን ልናከብር የምንችለው መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረው መንገድ ያመለክን እንደሆነ መሆኑን እንረዳለን። ክርስቶስ እንዳለው፥ እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኘው መንገድ ለማምለክ በእውነትና በመንፈስ ልናመልከው ይገባል (ዮሐ. 4፡23-24)። ወጣቶች ብዙውን ጊዜ «መንፈስን»  ወይም ጮክ ብሎ መዘመር፥ እጅን ማጨብጨብ፥ ማሸብሸብና መደነስ የሚታይበትን ስሜታዊ የአምልኮ ክፍል ይወዳሉ። አንዳንድ አማኞች አምልኮን የሚገልጹት በስሜታዊነት ደረጃው ነው። ጳውሎስ ግን ሁሉም አምልኮ በእግዚአብሔር ቃል ግልጽ እውቀት ሊካሄድ፥ በእውነት ላይ ሊመሠረትና ከአመስጋኝ ልብ ሊመነጭ እንደሚገባ ያስተምራል። ጳውሎስ ይህንን አሳብ ያመጣው ቀደም ሲል አማኞች ሊያደርጓቸው የሚገባቸውንና የማይገቧቸውን ነገሮች ካብራራ በኋላ መሆኑን አጢን። ይህም እግዚአብሔርን ለማስከበር እርሱ በሚፈልገው መንገድ መመላለስ እንዳለብን ያሳያል።

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) የቤተ ክርስቲያን አባላት እግዚአብሔርን በእውነት ከማምለካቸው በፊት ሊያደርጓቸው ስለሚገቧቸውና ስለማይገቧቸው ነገሮች ምን ሊያውቁ ይገባል? ለ) ብዙ አማኞች በእግዚአብሔር ቃል ከማደግ ይልቅ በመዝሙር ላይ የሚያተኩሩት ለምንድን ነው? ሐ) አምልኮ እውነትንና መንፈስን እንዲይዝና በእግዚአብሔር ቃል ላይ እንዲመሠረት በቤተ ክርስቲያንህ ምን ሊለወጥ ይገባል?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: