የ1ኛና 2ኛ ተሰሎንቄ መግቢያ

አንዲት ነቢይ፥ «ክርስቶስ የዛሬ ዓመት ይመጣል። ስለሆነም ሁላችሁም በፍጥነት መጋባት ይኖርባችኋል። ሥራ ያላችሁ ደግሞ ሥራችሁን ለቅቃችሁ ባላችሁ ገንዘብ ራሳችሁን ማስደሰት አለባችሁ። እህል መዝራቱ አስፈላጊ አይሆንም። ባጨዳው ጊዜ እዚህ አትኖሩምና» ስትል ተነበየች። ብዙ ሰዎች አስተዋይ ሽማግሌዎች የሰነዘሩትን ማስጠንቀቂያ ችላ ብለው ምክሯን ተቀበሉ። ወጣቶቹ ስለ ነገ ሳያስቡ የትዳር ጓደኞችን መረጡ። ወዲያውም እነዚህ ልጃገረዶች አረገዙ። ሰዎች ሥራቸውን ለቅቀው ያጠራቀሙትን ገንዘብ ሁሉ መጠቀም ጀመሩ። ንብረቶቻቸውን ሁሉ ሸጡ። በዓመቱ መጨረሻ ላይ ሁሉም ነቢይቱ ክርስቶስ ይገለጣል ባለችው ስፍራ ላይ ተሰበሰቡ። የክርስቶስን መገለጥ እየተጠባበቁና እየዘመሩ ለረጅም ጊዜ ጠበቁት። እርሱ ግን ብቅ አላለም። በሁኔታው ተበሳጭተው ነብይቱን ከቤተ ክርስቲያን አባረሯት። ይሁንና ጥፋቱ ቀድሞውንም ተፈጽሞ ነበር።

አንዳንዶች ክርስቶስ ቃሉን አላከበረም በሚል እምነታቸውን ተዉ። ሥራቸውን የለቀቁት ወጣቶች ሕፃናት ልጆቻቸውን ለመንከባከብ ባለመቻላቸው ትዳራቸውን ጥለው ወደ ከተማ ኮበለሉ። ባሎቻቸው የተለዩአቸው ወጣት ሴቶችም የገቢ ምንጭ ለማግኘት ሲሉ ወደ ሴተኛ አዳሪነት ተሠማሩ። ብዙዎቹ ኑሮ ስለተናጋባቸው በድህነት ይማቅቁ ጀመር። በማኅበረሰቡ ውስጥ ይኸው የእብድ «ጴንጤዎች» ጉዳይ መሳለቂያ ሆነ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስ መቼ እንደሚመለስ የሚተነብይ መልእክት ሰምተህ ታውቃለህ? ትንቢቱ ተፈጽሟል? ለ) ይህ የሐሰት ትንቢት በክርስቶ ስም ላይ ምን ጉዳት አስከተለ?

በታሪክ ሁሉ እግዚአብሔር ክርስቶስ የሚመለስበትን ጊዜ ገልጦልናል የሚሉ ሐሰተኛ ወንድና ሴት ነቢያት ታይተዋል። የአውሮፓውያን 2000 ዓመተ ምሕረት ሲቃረብ ብዙ ሰዎች ክርስቶስ ይመለሳል በሚል እምነት ሥራቸውን ለቅቀውና ንብረታቸውን ሸጠው ወደ ኢየሩሳሌም ተጉዘዋል። ምስሉን ቀርጸው ለማስቀረት የፎቶግራፍ ማንሻ ካሜራም የያዙም ነበሩ። ይሄ ምንኛ ታላቅ ሞኝነት ነው! ምንኛ የእግዚአብሔርን ቃል አለማወቅ ነው። ምክንያቱም ክርስቶስ የሚመለስበትን ቀን ከአብ በስተቀር ማንም እንደማያውቅ ተናግሯል (ማቴ. 24፡36-44 አንብብ)። እንዲህ ዓይነቱ ሐሰተኛ ትንቢት በቤተ ክርስቲያን ላይ ከፍተኛ ጉዳት አስከትሏል።

የ1ኛና የ2ኛ ተሰሎንቄ መልእክቶች የተጻፉት አንዳንድ ሰዎች ክርስቶስ በተወሰነ ቀን እንደሚመጣ ወይም ቀደም ብሎ እንደ መጣና አማኞች ሳይነጠቁ እንደ ቀሩ በመግለጽ ስለረበሿቸው ነበር። ጳውሎስ የዚህች ለጋ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ሳይነጠቁ እንዳልቀሩ በመግለጽ ያበረታታቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ስለ 1ኛና 2ኛ ተሰሎንቄ አንብብ። ስለ መጽሐፉ፥ ስለ ጸሐፊው፥ ለማን እንደ ተጻፈ፥ ስለ ከተማይቱና ስለ ቤተ ክርስቲያኒቱ፥ እንዲሁም መልእክቱ ስለሚያተኩርባቸው ነጥቦች የቀረቡትን አሳቦች ጠቅለል አድርገህ ግለጽ።

ቀደም ሲል እንደተገለጸው ጥንታውያን ምሁራን የአዲስ ኪዳን አካላት የሆኑትን ደብዳቤዎች በሚያሰባስቡበት ወቅት የጳውሎስን መልእክቶች በሙሉ በአንድ ክፍል ውስጥ አኑረው ነበር። የጳውሎስን አሥራ ሦስት መልእክቶች ያስቀመጡት በጊዜ ቅደም ተከተል አልነበረም። ይልቁንም በጣም ረጅሙን የሮሜ መልእክት መጀመሪያ ላይ ከዚያም 1ኛና 2ኛ ቆሮንቶስን አስከትለዋል። በመቀጠል በጣም ጠቃሚውን የገላትያ መልእክት፥ ከዚያም ከአራቱ የእሥር ቤት መልእክቶቹ ሦስቱን ማለትም ኤፌሶን፥ ፊልጵስዩስና ቆላስይስን አስፍረዋል። ከቆላስይስ በኋላ አራተኛው የእሥር ቤት መልእክት የሆነውን ፊልሞናን ለማስከተል አልፈለጉም። ለዚህም ምክንያቱ የደብዳቤው አጭርነት ነው። የ1ኛና 2ኛ ተሰሎንቄ መልእክቶች ከገላትያ መልእክት በኋላ ቢጻፉም፥ ከእስር ቤት መልእክቶች በኋላ እንዲሰፍሩ ተደርገዋል። በመጨረሻም ለጢሞቴዎስና ለቲቶ የተጻፉ መልእክቶች ቀርበዋል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: