ጳውሎስ አማኞች መሪዎቻቸውን እንዲያከብሩ ይመክራቸዋል (1ኛ ተሰ.5፡12-28)

ጳውሎስ በዚህ የማጠቃለያ ክፍል እያንዳንዱን የቤተ ክርስቲያን አባል የሚመለከቱትን ትእዛዛት ይዘረዝራል፡

ሀ) የቤተ ክርስቲያን አባላት መሪዎቻቸውን ማክበር ይኖርባቸዋል። እነዚህ መሪዎች ምእመናንን ለመምራት ጊዜያቸውን የሚሰዉና የክርስቲያኖችን መንፈሳዊ ፍላጎቶች የሚያሟሉ ናቸው።

ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እርስ በርሳቸው በሰላም መኖር አለባቸው። በእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ላይ ባላቸው የአመራር ኃላፊነት ክርስቲያኖች ተግተው እንዲሠሩ ሊያበረታቱና ራሳቸው ስደትን ለመጋፈጥና ለክርስቶስ ለመመስከር ቆራጦች ሊሆኑ ይገባል። በመጎዳት ላይ ያሉትን አማኞች ሊንከባከቡና ክርስቲያኖች ለእግዚአብሔር ክብር ለመኖር በሚጥሩበት ወቅት ሊረዷቸው ይገባል። ክርስቲያኖች በሚያሳድዳቸው ዓለማውያንና በሌሎችም ሰዎች ላይ ቂም ሊይዙ ይችሉ ነበር። መሪዎች አማኞች እንዲህ ዓይነቱን የመራርነትና የበቀል ስሜት እንዲያስወግዱ በማስተማር ይረዷቸዋል። ክርስቲያን መሪዎች ሰዎች የሚዋደዱበትንና እርስ በርስ የሚተጋገዙበትን ድባብ የመፍጠር ኃላፊነት ተጥሎባቸው ነበር።

ሐ) ከእግዚአብሔር ጋር የሚመላለሱ አማኞች ሁሉ የሚከተሉት ባሕርያት ይኖራቸዋል፡-

  1. በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ደስ መሰኘት። እግዚአብሔር ምንጊዜም ባስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንደማንገባ ቃል አልገባልንም። ነገር ግን ስደትና አስቸጋሪ ሁኔታዎች በሚገጥሙን ጊዜ ከእኛ ጋር አብሮ እንደሚሆን ቃል ገብቶልናል። የትኛውም ችግር ከምንቋቋመው በላይ እንዳልሆነ እያሳየን በችግሩ ውስጥ ያሳልፈናል (1ኛ ቆሮ. 10፡13 አንብብ)። እግዚአብሔር ወደ ሕይወታችን የሚመጣው ነገር ሁሉ በእርሱ ፈቃድ እንደሚፈጸምና ይህም በመንፈሳዊ ሕይወታችን ስዕሎች እንድንሆን የሚያግዘን መሆኑን ያስረዳል።
  2. አማኞች ለማንኛውም ሁኔታ ጸሎትን ቀዳሚ ምላሻችን ልናደርገው ይገባል።
  3. አማኞች የትንቢትን ስጦታ ቸል ማለት የለባቸውም። የሐሰት ትንቢትን በሚናገሩ ሰዎች ላይ ቤተ ክርስቲያናቸውን ከእውነት በሚያርቁ ሰዎች ሳቢያ የተሰሎንቄ ቤተ ክርስቲያን ትንቢት እንዳይነገር የከለከለች ይመስላል። ወይም ደግሞ ነቢያትን የማክበርና ትምህርታቸውን የመስማት ፍላጎት አልነበራቸውም። ጳውሎስ ግን ይህን የእግዚአብሔር ስጦታ የምናስተናግደው በዚህ መንገድ እንዳልሆነ ያስረዳል። እግዚአብሔር የሰጠንን አንድ ነገር ለመቀበል ፈቃደኞች በማንሆንበት ጊዜ የመንፈስን እሳት ማጥፋታችን ነው። ስለሆነም የተሰሎንቄ አማኞች የትንቢትን ስጦታ መፍቀድ ያስፈልጋቸው ነበር። ጳውሎስ የተሰሎንቄ አማኞች ሁሉንም እንዲመረምሩና መልካሙን እንዲይዙ ያበረታታቸዋል። ለመሆኑ አንድ ትንቢት ከእግዚአብሔር መሆን አለመሆኑን የምንፈትነው እንዴት ነው። በዚህ ረገድ ልንጠቀም የምንችላቸው አምስት መሣሪያዎች አሉ።

በመጀመሪያ፥ ይህ ትንቢት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሰው አሳብ ጋር ይስማማል ወይ? ብለን መጠየቅ ይኖርብናል። የተስሎንቄ አማኞች አንዳንድ የሐሰት ነቢያት ክርስቶስ በዚህ ቀን ይመጣል ባሏቸው ጊዜ ይህንን ጥያቄ ለማንሣት ባለመቻላቸው ሥራቸውን አቁመዋል። ክርስቶስ እኔ የምመጣበትን ቀን ማንም አያውቅም ሲል የተናገረውን ዘንግተው ነበር (ማቴ. 24፡36)።

ሁለተኛ፥ ይህ ለቤተ ክርስቲያን ዕድገትና እውቀት ጠቃሚ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ማንሣት። መንፈሳዊ ጠቀሜታ የሌላቸው ትንቢቶች አሉ። አንድ የቤተ ክርስቲያን መሪ የትንቢት ቃል አለ ወይ ብሎ በጠየቀ ጊዜ አንድ ሰው ብድግ ብሎ ሃሌሉያ እያለ ደጋግሞ ይጮህ ጀመር። በዚህ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩት ሰዎች በሙሉ እልል አሉ። በመሠረቱ ይህ የትንቢት ቃል አይደለም። ይህ ለትምህርትም ሆነ ሕዝቡን ለማነጽ የማይጠቅም የቃላት ድግግሞሽ ነው። የዚህ ዓይነቱ ትንቢት ማንንም ወደ እግዚአብሔር አያስጠጋም።

ሦስተኛ፥ ትንቢቱን የሚናገረው ግለሰብ ባሕርይ ነው። እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ ቃሉን ለማስተላለፍ በመንፈሳዊ ሕይወቱ የበሰለና ለቃሉ የሚታዘዝ ሰው ይጠቀማል። ነገር ግን ትንቢቱን የሚናገረው ግለሰብ በኃጢአት የሚመላለስ ከሆነ ወይም ደግሞ ትንቢቱ የተነገረው ትንቢቱን ለሚናገረው ነቢይ አንድን ጥቅም ወይም ክብር ለማስገኘት ታስቦ ከሆነ፥ እንዲህ ዓይነቱን መልእክት ስንቀበል ልንጠነቀቅ ይገባል።

አራተኛ፥ ትንቢቱን የሚናገረውን ግለሰብ ምን ያህል እናውቀዋለን? የሚለው ጥያቄ ነው። የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም ሆኑ ምእመናን የማያውቁት ሰው ብድግ ብሎ ትንቢትን በሚናገርበት ጊዜ ይህንኑ ትንቢት በአጥጋቢ ሁኔታ መመርመሩ አስቸጋሪ ነው። አንድ አዲስ ሰው ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥቶ ትንቢት ለመናገር በሚፈልግበት ጊዜ መሪዎቿ መጀመሪያ ሊሰሙትና መልእክቱን ሊገመግሙት ይገባል። እግዚአብሔር መሪዎች ቤተ ክርስቲያናቸውን ከስሕተት እንዲጠብቁ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል። ብዙውን ጊዜ የሐሰት ትምህርቶች ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡት ትንቢትን ወይም ትምህርትን በሚሰጡ ያልታወቁ ሰዎች አማካኝነት ነው። ግለሰቡ ትንቢቱን ወይም ትምህርቱን ለሕዝቡ ሁሉ ማስተላለፍ ያለበት መሪዎቹ መልእክቱን ከገመገሙት በኋላ መሆን አለበት። ልብ አድርግ የሐሰት ትምህርት አንድ ጊዜ ወደ ሕዝቡ ዘልቆ ከገባ በኋላ በስፋት እንዳይሰራጭ መከላከሉ ከባድ መሆኑን አትዘንጋ። ነገር ግን እግዚአብሔር ብዙውን ጊዜ ከቃሉ ጋር የሚስማማ መልእክት ለማስተላለፍ የሚጠቀምበትን አገልጋይ ካወቀ፥ አኗኗራቸው የእግዚአብሔርን ቃል እንደሚከተል እንገነዘባለን። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ለምእመናን የእግዚአብሔርን ቃል በይፋ እንዲናገር ልንፈቅድለት እንችላለን።

አምስተኛ፥ የተነገረው ትንቢት መፈጸሙን በመከታተል፡፡፡ ትንቢቱ በተነገረበት መንገድ በትክክል ካልተፈጸመ፥ ይህ ትንቢት ከእግዚአብሔር እንዳልመጣ ልናረጋግጥ እንችላለን። ከዚህ በኋላ ይህን ትንቢት የተናገረውን ግለሰብ ልንጠራጠር እንችላለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ቤተ ክርስቲያን፥ በተለይም ወጣቶች መሪዎቻቸውን ለማክበር የሚፈልጉት በምን መንገድ ነው። ይህንን በበለጠ እንዲያከናውኑት ምን ትመከራቸዋለህ? ለ) ጳውሎስ በዚህ ስፍራ እንደገለጸው የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ኃላፊነታቸውን በአጥጋቢ ሁኔታ ለመወጣት ምን ሊያደርጉ ይገባል? ሐ) አንድ ትንቢት በትክክል ካለመፈተኑ የተነሣ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተለያዩ ችግሮችን ስላስከተለበት ሁኔታ ምሳሌዎችን ስጥ። መ) ትንቢት ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እድገትን ስላመጣበት ሁኔታ ግለጽ። ሠ) መልካም የሆነው አሳብ ለሕዝብ እንዲቀርብና ሐሰተኛ የሆነው መልእክት እንዳይሰራጭ ለመከላከል ቤተ ክርስቲያን ልትጠቀም የምትችላቸው ዘዴዎች ምን ምንድን ናቸው?

  1. ጳውሎስ የተሰሎንቄ አማኞች በሁለንተናቸው፥ ማለትም በሥጋቸው፥ በነፍሳቸውና በመንፈሳቸው በቅድስና እንዲያድጉ ይጸልያል። ይህም ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ እንከን የሌላቸው እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። ጳውሎስ እግዚአብሔር በእነዚህ አዳዲስ አማኞች ሕይወት ውስጥ በመሥራት እንደሚያሳድጋቸው እርግጠኛ ነበር።

ጳውሎስ እነዚህ አዳዲስ ክርስቲያኖች በጸሎት እንዲተጉ በመጠየቅ መልእክቱን ይደመድማል። እርስ በርሳቸውም ያላቸውን ፍቅር በተቀደሰ አሳሳም እንዲገልጹ ያሳስባቸዋል። በመሳሳም ሰላምታ መለዋወጡ በመደበኛነት የሚገለጽ ሥርዓታዊ ተግባር ሳይሆን፥ አማኞች እርስ በርሳቸዉ ያላቸውን ፍቅርና መሰጠት የሚገልጹበት ሊሆን ይገባል። ጳውሎስ ይህ መልእክት ለክርስቲያኖች ሁሉ እንዲነበብ ካሳሰበ በኋላ ቡራኬ በመስጠት መልእክቱን ይደመድማል።

የውይይት ጥያቄ፡- ከ1ኛ ተሰሎንቄ ውስጥ ሕይወትህን የባረኩ አንዳንድ ነጥቦች ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “ጳውሎስ አማኞች መሪዎቻቸውን እንዲያከብሩ ይመክራቸዋል (1ኛ ተሰ.5፡12-28)”

  1. በእዉነት እንድህ አይነት አስተማሪና ወደ ህይወት የሚመራ ትምህርት ተምሬ አላወኩትም. ከተወለድኩት ጀምሬ 19አመት ሙሉ በእስልምና ሀይማኖት ነበር ዕድሜን ስባክን የከረምኩት.ዛሬ ደግሞ ያ ታሪክ ገልብጦ ወደ ህይወት ያመጣኝ ይባረክ.ጌታ በምያዉቀዉ አዳንዬ የአንቴን ትምህርት በመከታተለ በጣም እድለኛ ነኝ. ጌታ ኢየሱስስ ዘመንህን ይባርክ አመሠግናለሁ

Leave a Reply

%d bloggers like this: