ጳውሎስ ክርስቶስ በድንገት በሚመለስበት ጊዜ የሞቱት አማኞች ምን እንደሚሆኑ ያብራራል (1ኛ ተሰ. 4፡13-5፡12)

ጢሞቴዎስ የተሰሎንቄ አማኞች ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ የሞቱ አማኞች ምን እንደሚሆኑ ያነሷቸውን ጥያቄዎች ለጳውሎስ አቀረበ። ምንም እንኳ ጳውሎስ ተሰሎንቄን ከለቀቀ ከሦስት ወራት ባይበልጥም ቢያንስ አንድ ክርስቲያን በሞት የተለያቸው ይመስላል። ይህ ደግሞ የተሰሎንቄ አማኞች የሞቱ ክርስቲያኖች በተለይም ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ምን እንደሚሆኑ እንዲያስቡ አደረጋቸው። ለሁሉም ክርስቲያኖች ስለዚሁ ጉዳይ ጥርት ያለ አሳብ መያዙ በጣም አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ ካስተማራቸው ነጥቦች መካከል ዋና ዋናዎቹ ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል።

ሀ) ሞት ለክርስቲያን እንደ እንቅልፍ ነው። አንድ ሰው ማታ ወደ አልጋው እንደሚሄድና ከብዙ ሰዓታት በኋላ እንደሚነቃ ሁሉ፥ አንድ እማኝ በሚሞትበት ጊዜ ነገር ዓለሙ ጨለመ ማለት አይደለም። ምክንያቱም አንድ ቀን ሥጋዊ አካላችን ከሞት ይነሣልና። (መንፈሳችን አይሞትም፥ ነገር ግን ከክርስቶስ ጋር በሰማይ ይቆይና በትንሣኤ ከሰውነታችን ጋር እንደገና ይዋሃዳል።) ሞቶ የተነሣውን የክርስቶስ ኢየሱስን ምሳሌነት በመከተል እኛም ከሞት እንነሣለን። በመሆኑም ሞትን እንደ መጨረሻ ነጥብ አድርገን በመመልከት ልንፈራ አይገባም።

ለ) አማኞች ሁሉ ለዘላለም ሕይወት እንደሚነሡ ከሚያስረዳው የተስፋ ቃል የተነሣ ክርስቲያኖች ለሞት የተለየ አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል። ሞት እዚህ በምድር ላይ ከሚያመጣው መለየት የተነሣ ኀዘንና ሥቃይ ቢኖርም፥ የዓለማውያን ዓይነት ተስፋ ቢስነት ሊሰማን አይገባም። በመሆኑም አንድን አማኝ በምንቀርብበት ጊዜ ተስፋ ቢስነት ሊሰማን አይገባም። ይህ ማለት ግን ለሞተ ሰው ማልቀስ ትክክል አይደለም ማለት አይደለም። ምክንያቱም ክርስቶስ እንኳን አልዓዛር በሞተ ጊዜ አልቅሷልና (ዮሐ. 11፡35)። እዚህ ጋር ጳውሎስ የሚነቅፈው ተስፋ በመቁረጥ ሰዎች ከመጠን በላይ ማልቀሳቸውን ነው።

ሐ) የሞቱ አማኞች በክርስቶስ የወደፊት ግዛት ውስጥ የሚገለጡትን በረከቶች አያጡም። እንዲያውም ክርስቶስ ከሰማይ በሚመለስበት ጊዜ መጀመሪያ የሚያገኙት እነርሱ ናቸው። በትንሣኤ አካላቸው ከሞት ተነሥተው በእግዚአብሔር ዘላለማዊ መንግሥት ውስጥ ይኖራሉ። ከዚያ በኋላ በሕይወት ያሉት አማኞች ይለወጣሉ። ይህም የሚሆነው ሰውነታቸው በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ለመኖር በሚያስችል መልኩ እንዲቀየር ነው። ከሞት የተነሡት አማኞችና የተለወጡት አማኞች ክርስቶስን በአየር ተቀብለው ከእርሱ ጋር ለዘላለም ይኖራሉ።

የውይይት ጥያቄ፡– ክርስቲያኖች በሙታን ትንሣኤ ማመናቸውን ተግባራዊ ቢያደርጉ ለሞት፥ ለስደትና ለተቀደሰ አኗኗር የሚኖራቸው አመለካከት እንዴት ይቀየራል?

አማኞች ለረጅም ጊዜያት ስለዚሁ ንጥቀትና ከመጨረሻው ዘመን አንጻር መቼ እንደሚፈጸም ሲከራከሩ ቆይተዋል። በራእይ ምዕራፍ 20 ከተገለጸው የክርስቶስ የሺህ ዓመት መንግሥት ጋር እንዴት ይዛመዳል። ስለ መጨረሻው ዘመን ክስተቶች ቅደም ተከተል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከዚህ በግልጽ ተዘርዝሮ አንመለከተም። ከዚህም የተነሣ ክርስቲያኖች የተለያዩ አመለካከቶች አሏቸው። የአማኞችን መነጠቅ በተመለከተ ሁለት ዓበይት አተረጓጎሞች አሉ። ከእነዚህም አንዱ የተለያዩ አመለካከቶችን ያስተናግዳል።

1) ንጥቀትን ተከትሎ በራእይ 21-22 የተገለጸው የዘላለም መንግሥት ይቀጥላል። አንዳንድ ክርስቲያኖች በመጨረሻው ዘመን ክርስቶስ ልጆቹን ለመውሰድ ከሰማይ ይገለጣል። እርሱ የሞቱትን ያስነሣል። በሕይወት ያሉትን ደግሞ ይለውጣል። በዚህም ጊዜ በአዲስ ሰማይና ምድር ወዳለው ዘላለማዊ መንግሥቱ ይወስዳቸዋል። በዚህ ጊዜ የማያምኑ ሰዎች ከሞት ተነሥተው የክርስቶስን ፍርድ ይቀበላሉ። ከዚያም ወደ ዘላለማዊ ሲኦል ይወርዳሉ ብለው ያምናሉ።

2) የአማኞች መነጠቅ የክርስቶስን የሺህ ዓመታት መንገሥ አስቀድሞ የሚከሠት ይሆናል። አንዳንድ አማኞች በራእይ 20 ውስጥ የተገለጸው የክርስቶስ የሺህ ዓመት መንግሥት በራእይ 21–22 ከተገለጸው ዘላለማዊ መንግሥቱ እንደሚለይ ያስባሉ። እነዚህ አማኞች ክርስቶስ ምድራዊ አገዛዙን ሊጀምር ሲል ወደ ተከታዮቹ እንደሚመጣ ያስተምራሉ። በዚህን ጊዜ የሞቱ ክርስቲያኖች ይነሣሉ። በሕይወት ያሉትም ይለወጣሉ። ይህም በምድራዊ መንግሥት ላይ ከክርስቶስ ጋር እንዲገዙ ያስችላቸዋል። በእነዚህ አማኞች አመለካከት የዘላለም መንግሥት የሚጀምረው የሺህ ዓመቱ መንግሥትና የሰው ልጅ የመጨረሻ ዓመፅ ከተጠናቀቀ በኋላ ይሆናል። ነገር ግን የዚህ አመለካከት አራማጆች ይህ የክርስቲያኖች መነጠቅ መቼ እንደሚሆን ሦስት የተለያዩ አሳቦችን ያቀርባሉ።

በመጀመሪያ፡- ብዙ ክርስቲያኖች የአማኞች ንጥቀት ከክርስቶስ የምድር ላይ ንግሥና ጥቂት ቀደም ብሎ እንደሚፈጸም ያስባሉ። ክርስቲያኖች በታላቁ መከራ ውስጥ እንደሚያልፉና ብዙዎችም ለእምነታቸው እንደሚሞቱ ያምናሉ። ነገር ግን ክርስቶስ በሠራዊቱ ታጅቦ ከሰማይ ከመምጣቱ በፊት (ራእ. 19፡11-21 አንብብ)፥ በአየር ተገልጦ የሞቱትን አማኞች ያስነሣል፥ በሕይወት ያሉትንም ይለውጣል። እነዚህም አማኞች ከክርስቶስ ጋር ለመንገሥ ወደ ምድር ይመለሳሉ።

ሁለተኛ፡- ጥቂት አማኞች ይህ ንጥቀት ታላቁ መከራ በሚባለው ጊዜ አጋማሽ ላይ እንደሚፈጸም ያስባሉ። እነዚህ አማኞች የታላቁን መከራ ዘመን በሁለት የሦስት ተኩል ዓመታት ክፍለ ጊዜያት ይከፍላሉ። አማኞች በመጀመሪያው የሦስት ተኩል ዓመታት የመከራ ጊዜያት ውስጥ እንደሚያልፉና ከሁለተኛው የሦስት ተኩል ዓመታት የታላቁ መከራ ጊዜ እንደሚተርፉ ያምናሉ። ይህም የሚሆነው ክርስቲያኖች በመነጠቃቸው ነው። ስለሆነም ከሦስት ተኩል ዓመታት በኋላ እነዚህ ከሞት የተነሡት አማኞች በምድር ላይ ለመንገሥ ከክርስቶስ ጋር ከሰማይ ይመጣሉ።

ሦስተኛ፡- ሌሎች ብዙ አማኞች ክርስቲያኖች ከሰባት ዓመቱ ታላቅ መከራ በፊት ከዚህ ዓለም እንደሚወሰዱ ያምናሉ። ይህንንም የሚሉት በራእይ 3፡10 ለፊልድልፍያ ቤተ ክርስቲያን የተሰጠውን የተስፋ ቃል በመንተራስ ነው። ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑን ነጥቆ እንደሚወስድና ከዚያ በኋላ በመጨረሻዎቹ ሰባት ዓመታት የእግዚአብሔርን ፍርድ በምድር ላይ እንደሚያመጣ ያስተምራሉ። ከሰባት ዓመታት በኋላ ከክርስቶስ ጋር ወደ ምድር ተመልሰው ይገዛሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከእነዚህ አመለካከቶች የትኛውን ታምናለህ? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ ከእነዚህ አመለካከቶች የትኛውን ታምናለች? መልሱን ካላወቅህ ከቤተ ክርስቲያንህ መሪዎች አንዱን ጠይቅ። ሐ) ክርስቶስ ሊወስድህ እንደሚመጣ፥ ሙታንን እንደሚያስነሣ፥ በሕይወት ያሉትን እንደሚለውጥና ለዘላለም ከእርሱ ጋር እንደምንኖር መረዳቱ እነዚህ ክስተቶች መቼ እንደሚፈጸሙ ከመከራከር የበለጠ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

የተሰሎንቄ አማኞች ስለ መጨረሻው ዘመን ያነሡት ሌላም ጥያቄ ነበር። ክርስቶስ መቼ እንደሚመለስ ለማወቅ ፈልገው ነበር። አንዳንድ ሰዎች ክርስቶስ በቶሎ እንደሚመለስ ያስተምሩ ስለነበር አንዳንድ አማኞች ሥራቸውን ትተው ነበር። ጳውሎስ ይህንንም ጥያቄ በሁለት ዐበይት ነጥቦች አስደግፎ ይመልሳል፡-

ሀ) ክርስቶስ የሚመለስበት ጊዜ ድንገተኛና ያልተጠበቀ ስለሚሆን ጊዜው መቼ እንደሚሆን በትክክል ልናውቅ አንችልም። ይህ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ ሁሉ ድንገተኛና ያልተጠበቀ ይሆናል። ክርስቶስ ሰዎች ባልጠበቁት ሰዓት ይመጣል። ይህም ማለት ክርስቶስ በዚህን ጊዜ ይመጣል ማለቱ ትክክል አይሆንም ማለት ነው። ክርስቶስ በዚህ ቀን ወይም ዓመት ይመጣል ልንል አንችልም።

ለ) የክርስቶስን መምጣት እየተጠባበቁ መኖር ማለት ዛሬ እንደሚመጣ ሆነን መኖር ማለት ነው። እርሱን ለማስከበር በታማኝነት እንኖራለን። አማኞች የብርሃን ልጆች በመሆናቸው ወይም የእግዚአብሔር የጽድቅ መንግሥት ተካፋዮች በመሆናቸው፥ ከዓለም የተለየ ሕይወት መምራት ይኖርባቸዋል። ራሳችንን ልንቆጣጠር፥ በእምነት፥ በፍቅርና በተስፋ እየተመላለስን የክርስቶስን መምጣት መጠባበቅ ይኖርብናል። ከሁሉም በላይ በተስፋ ልንጸና ይገባል። ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ በሕይወት ብንኖር ወይም ብንሞት ለዘላለም ከእርሱ ጋር እንደምንኖር እናውቃለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዓለማውያንና ሥጋዊ ክርስቲያኖች የሚያደርጓቸውንና ክርስቶስ በሚመለስበት ጊዜ ፍርድን የሚያስከትሉባቸውን ነገሮች ዘርዝር። ለ) ክርስቶስ በየትኛውም ጊዜ ሊመጣ እንደሚችል በሚያንጸባርቅ መልኩ እንደምንኖር ለማሳየት ልናደርጋቸው የሚገቡ አንዳንድ ነገሮች ምን ምንድን ናቸው? ሐ) ብዙ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ የማይኖሩት ለምን ይመስልሃል? ስለ ክርስቶስ ምጽአት እነዚህ ክርስቲያኖች የዘነጉት ነገር ምንድን ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: