ጳውሎስ የተሰሎንቄን አማኞች አኗኗር ለማወቅ የወሰዳቸውን እርምጃዎች የፍቅሩ መግለጫ አድርጎ ይጠቅሳል። ከደረሰባቸው ስደት የተነሣ እምነታቸውን እንዳይተዉ ሰግቶ ነበር። ይህንንም ለማጣራት ጢሞቴዎስን ወደ ተሰሎንቄ ላከው። ጢሞቴዎስ ጳውሎስ ወደሚያገለግልባት የተሰሎንቄ ከተማ በተመለሰ ጊዜ፥ ከስደቱ ባሻገር የተሰሎንቄ አማኞች በክርስቶስ ማመናቸውን እንደቀጠሉና ታላቅ ፍቅርም እንደነበራቸው ለጳውሎስ አብራራ። ይህ ጳውሎስን እጅግ በማስደሰቱ እነርሱን ለማየት የነበረውን ጉጉት አናረው። ጳውሎስ ስደትን ተቋቁሞ መዝለቅ በዋናነት የሰዎች ጥረትና ችሎታ ሳይሆን የእግዚአብሔር የማስቻል ውጤት እንደሆነ ይገነዘብ ነበር። ስለሆነም እግዚአብሔር የተሰሎንቄን አማኞች ልብ እንዲያበረታ፥ እንዲያጸናቸውና እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ምጽአት ድረስ ቅዱሳን አድርጎ እንዲጠብቃቸው ይጸልያል።
ብዙውን ጊዜ ስደት በሚደርስብን ጊዜ ምን እንደምናደርግ እናስባለን። ለክርስቶስ የተሰጠ ሕይወት መኖራችንን ለማመልከት ሕይወታችንን መመርመሩ ጠቃሚ ነው። ነገር ግን ስደት በሚመጣበት ጊዜ እግዚአብሔር እንደማይተወን መረዳት አለብን። እርሱ ከእኛ ጋር በመሆን ፈተናውን እንድንቋቋምና ጸንተን እንድንቆም ይረዳናል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ከእምነትህ የተነሣ የተሰደድክበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) በዚህ ጊዜ ለክርስቶስ ታማኝ ሆኖ ስለ መጽናት ምን ተማርክ? ሐ) ለአማኞች እግዚአብሔር በስደት ጊዜ በእምነታቸው የሚጸኑበትን ኃይል እግዚአብሔር እንደሚሰጣቸው መረዳቱ ምን ይጠቅማል?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)
ጥናቶቹ የተብራሩ ቢሆኑ የበለጠ ለመረዳት ያስችላል በጥቅል ባይቀርብ ተባረኩ