አብዛኛቹ ሐሰተኛ ትምህርቶች የሚመጡት አንድን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ነጥሎ ከማስተማር ነው። ብዙውን ጊዜ ሰይጣን በትንሽ እምነት ላይ በማተኮር መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን እንድንዘነጋ ለማድረግ ይሞክራል። በኤፌሶን ቤተ ክርስቲያንም የተከሰተው ይኸው ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ የራሱን ሕይወት በምሳሌነት በመጥቀስ፥ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ምን እንደሆነ ለጢሞቴዎስ ያስገነዝበዋል። እጅግ ጠቃሚውና አስፈላጊው እውነት የእግዚአብሔር አስደናቂ ጸጋ ነው። ይህ ጸጋ እንደ ጳውሎስ ያለውን በጣም ክፉ ሰው ወስዶ በክርስቶስ እንዲያምን ከማድረጉም በላይ፥ አገልጋዩ እንዲሆን ሾሞታል። (ጳውሎስ ደኅንነትን ከማግኘቱ በፊት አማኞችን ያስርና ይገድል የነበረ ነፍሰ ገዳይ መሆኑ ይታወቃል።) በጳውሎስ ላይ የነበረው ክፋት በሰዎችም ሁሉ ላይ የነበረ መሆኑ ግልጽ ነው። በምናደርጋቸው ነገሮች፥ በምንጠብቃቸው ሕግጋት ወይም እግዚአብሔርን ለማገልገል በምናከናውናቸው ተግባራት ላይ ትኩረት ማድረግ የለብንም። ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደዚህ ዓይነት ዝንባሌ አላቸው። ይልቁንም በሕይወታችን ውስጥ በተገለጸው የእግዚአብሔር አስደናቂ ጸጋና ምሕረት ላይ አጽንኦት ልንሰጥ ይገባል። ዋናው ነገር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በግልጽ የቀረበው መሠረታዊ ወንጌል እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ስለማያስተምራቸው እውነቶች የድምዳሜ አሳብ ማበጀት ወይም ደስ በሚያሰኙን የተወሰኑ እውነቶች ላይ ማተኮር አይደለም። ማተኮር ያለብን ግልጽና ጠቃሚ በሆነው መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት ላይ እንጂ፥ ግልጽ ባልሆነውና መንፈሳዊ ጠቀሜታ በሌለው አሳብ ላይ መሆን የለበትም። እንደ አለመታደል ሆኖ ግን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የዚህን ተቃራኒ እርምጃ ይወስዳሉ። በመሆኑም የወንጌልን እውነታዎች የሚያፋልሱትን የሐሰት አስተማሪዎች እየታገሱ እንደ መጠጣት፥ የሕፃናት ጥምቀት ወይም የጌታ ራት አወሳሰድ የመሳሰሉትን ልምምዶች ከእነርሱ በተለየ መንገድ የሚያከናውኑትን ክርስቲያኖች አጥብቀው ይቃወማሉ።
ጢሞቴዎስ ዓይናፋርና ሐሰተኛ ትምህርት የሚያቀርቡትን ሰዎች ለመጋፈጥ ያልደፈረ ይመስላል። ጳውሎስ ግን እንዲጋደል ይነግረዋል። የሐሰተኛ አስተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲያቀርቡ በመፍቀድ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ሰይጣን እንዲያጠፋ ከመፍቀድ ይልቅ፥ ጢሞቴዎስ የማጥቃት እርምጃ እንዲወስድ ተነግሮታል። የሚዋጋውም በሁለት መንገዶች ነው። በመጀመሪያ፥ ግላዊ ውጊያ ማካሄድ ነበረበት። ይኸውም እውነትን አምኖ በንጽሕና ይመላለስ ዘንድ ሕይወቱንና ምስክርነቱን መጠበቅ እንዳለበት የሚያስገነዝብ ነው። ሁለተኛ፥ ሐሰተኛ ትምህርትን የሚያስፋፉ ሰዎችን በመከላከልና ምእመናን እውነትን እንዲከተሉ በማድረግ የአደባባይ ውጊያ ማካሄድ ነበረበት። የትንቢት ስጦታው የእግዚአብሔርን ፈቃድና እውነትን እንዲያውቅ ያስችለው ነበር። ሰዎችን ፈርቶ ስጦታውን መደበቁ ወይም አለመጠቀሙ ትክክል አልነበረም። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ራሱንና ቤተ ክርስቲያኒቱን ለመከላከል አለመጣሩ እምነትን ሊያፈራርስ የሚችል አደገኛ ነገር መሆኑን አስገንዝቧል። ጳውሎስ ከእምነታቸው የወደቁትን ሁለት ሰዎች ይጠቅላል። እነዚህም ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ ናቸው። ምንም እንኳን በእምነት ላይ ያሉ ቢሆኑም፥ ስድብን ለማቆም ይማሩ ዘንድ ለሰይጣን አሳልፎ ሰጣቸው። እነዚህ ሰዎች ምን ዓይነት ኃጢአት እንደ ፈጸሙ አናውቅም። ምናልባትም የሐሰት ትምህርት እያስፋፉ ወይም በኃጢአት እየተመላለሱ ይሆናል።
ለሰይጣን አሳልፎ መስጠት ማለት ምን ማለት ነው? ይህ ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያንን የሥነ ሥርዓት እርምጃ ለመግለጽ የሚጠቀምበት ቃል ነው። አንድ ሰው በተለይም በመሪነት የሚያገለግል ግለሰብ በዐመፃ መንፈስ ተነሣሥቶ መንፈሳዊ ሕይወት ላለመኖር ወይም እውነትን ላለመከተል በሚመርጥበት ጊዜ ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን የቅጣት እርምጃ ይወስድበት ነበር። ይህንንም የሚያደርገው ከአማኞች ኅብረት ግለሰቡን በማግለል ነበር። ጳውሎስ የአማኞች ኅብረት አካል መሆኑ ከሰይጣን ቀጥተኛ ጥቃቶች እንደሚከላከል ያውቅ ነበር። ምክንያቱም በዚህ ኅብረት ውስጥ ክርስቶስ በተለየ ሁኔታ ይኖራልና። ከዚህ የአማኞች ኅብረትና ከመንፈስ ቅዱስ ጥበቃ ውጪ መሆኑ ሰውዬውን ለሰይጣን ጥቃት ያጋልጠዋል። ይህ ግን ሰይጣን ሰውዬውን ወደ ጠለቀ ኃጢአት እንዲመራው ለማድረግ የታሰበ አልነበረም። ይልቁንም ሰይጣን አካላዊ ጤናውን ወይም በዐመፀኛነቱ ከቀጠለ ሞትን በማስከተል ከኃጢአቱ ንስሐ እንዲገባ ያደርገዋል ከሚል አሳብ የመነጨ ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች ከቤተ ክርስቲያን ኅብረት ወጥተው እንዲቀጡ አዟል። ይህም በ1ኛ ቆሮንቶስ ምዕራፍ 5 ውስጥ ከተጠቀሰውና በኃጢአት ውስጥ ከሚኖር ግለሰብ ሕይወት ጋር የሚመሳሰል ነበር። ጳውሎስ ይህንን ያደረገው ኃጢአት የሠራውን ግለሰብ ለመቅጣት ብቻ አልነበረም። ሌሎች አማኞች በእግዚአብሔር ላይ ዐመፅ እንዳይፈጽሙና የቤተ ክርስቲያንን ንጽሕና እንዲጠብቁ ለማስጠንቀቅ ነበር።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለቤተ ክርስቲያን በዐመፀኝነት መንፈስ ተነሣሥተው ከኃጢአት ወይም ከሐሰተኛ ትምህርት ለመመለስ የማይፈልጉትን ሰዎች መቅጣት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለ) ቤተ ክርስቲያንህ አማኞችን የቀጣችበትን ሁኔታ ግለጽ። ሐ) ዓላማቸው ምን ነበር? መቅጣት ወይስ ማስተማር? መ) በቤተ ክርስቲያን ቅጣት ውስጥ ትክክለኛ ምክንያት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)