ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በሕጎች ላይ ባለማተኮር የወንጌሉን እውነት እንዲጠብቅ ያስጠነቅቀዋል (1ኛ ጢሞ. 1፡1-11)

ለ20 ዓመታት የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ሆኖ አገልግሏል። ሚስቱ መልካም መንፈሳዊት ሴት ስትሆን፥ ልጆቹም በእግዚአብሔር እውነት ይጓዙ ነበር። በተለይም ኮሚኒዝም በሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት እግዚአብሔር ስንታየሁን በብዙ መንገዶች ተጠቅሞበታል። የኋላ የኋላ ግን በመንፈሳዊ ዕድገትና ባሕርያት ላይ ከማተኮር ይልቅ ሕይወቱ እያዘቀዘቀ እንዲሄድ አድርጓል። አንድ ቀን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እየሠራ እያለ አንዲት ቆንጆ ወጣት ስለ ግል ጉዳይዋ ልታማክረው መጣች። ስንታየሁ ከተለያዩ ውይይቶች በኋላ ከዚህች ልጅ ጋር ወሲባዊ ኃጢአት ፈጸመ። ከዚህም የተነሣ ሚስቱን ፈታ። ከቤተ ክርስቲያን መሪነቱም ወረደ። ከዚያ በኋላ እንደ ማንኛውም ዓለማዊ ሰው ይኖር ጀመር።

በላይነሽ በቤተ ክርስቲያኗ ውስጥ የታወቀች ሴት ነበረች። የቤተ ክርስቲያኒቱ የጸሎት ቡድን መሪ ከመሆኗም በላይ፥ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያንና የቀጠና የሴቶች ማኅበር መሪም ነበረች። አንድ ቀን ባሏ ከፍተኛ ደመወዝ በሚከፍል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት (መያድ) ውስጥ ሥራ አገኘ። ብዙም ሳይቆይ እርሷም በዚሁ ድርጅት ውስጥ ተቀጠረች። ነገር ግን ከሥራው ጋር በተያያዘ እርሷና ባለቤቷ ሊወስኑዋቸው የሚገቡ ነገሮች ተከትለው መጡ። ድርጅቱ እርሱን በሰሜን ኢትዮጵያ እርሷን ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያ ውስጥ መደባቸው። ለእነዚህ ሰዎች ቤተሰባቸው ሥራው ከሚያስገኘው ገንዘብ የበለጠ አስፈላጊ ነበር? እርሱ ሁለት ትልልቅ ልጆችን እርሷ ደግሞ ሁለት ትንንሽ ልጆችን ይዘው በተለያዩ ቦታዎች መኖር ጀመሩ። እርስ በርሳቸው ብዙም ሳይገናኙ በሚያገኙዋቸው ገንዘብና ጥቅማ ጥቅሞች መደሰታቸውን ቀጠሉ። መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ብዙ ገንዘብ ቢከፍሉም ከሠራተኞቻቸው ብዙ ሥራ ይጠብቃሉ። በመሆኑም በላይነሽ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወይም የጸሎት ስብሰባዎች ለመሄድ የምትችልበትን ጊዜ ልታገኝ አልቻለችም። ብዙውን ጊዜ እሑድ እሑድ ቀን ስብሰባዎች ይካሄዳሉ። ይህም ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳትሄድ ከለከላት። ከሁለት ልጆቹ ጋር በሰሜን የሚኖረው ባለቤቷ ምግብ የምታዘጋጅላቸው ሠራተኛ ቀጠረ። የኋላ ኋላ ግን ከዚህችው ሠራተኛ ጋር አብሮ ይተኛ ጀመር። ምንም እንኳ ሥራው፥ ገንዘቡና ተራርቆ መኖሩ ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን ግንኙነት የሚቀንስና እነርሱንም የሚያራርቃቸው መሆኑን ቢገነዘቡም፥ ገንዘብ የሚያስገኘውን ጥቅም ለማጣት አልፈለጉም። ከዚህም የተነሣ ብዙም ሳይቆይ መንፈሳዊ ሕይወታቸው በጽኑ ተጎዳ።

ሙሉጌታ ለረጅም ጊዜያት የቤተ ክርስቲያን መሪ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። ምንም እንኳን ሙሉጌታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን አባል ቢሆንም፥ የእግዚአብሔርን ቃል ለማጥናት ወይም እውነትን በማወቅ ለማደግ ጊዜ አልወሰደም። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚያስተምርበት ጊዜ ሁሉ ስለ ደኅንነት ወይም አንድ ሰው ጥሩ ክርስቲያን ለመሆን ሊያደርጋቸው ስለሚገቡ ነገሮች ከመናገር የበለጠ አሳብ አያቀርብም። አንድ ቀን አንድ ሐሰተኛ አስተማሪ ወደ እነ ሙሉጌታ ቤተ ክርስቲያን መጥቶ መጽሐፍ ቅዱስ የሥላሴን አስተምህሮ እንደማያስተምር ገለጸ። ይህ ሰው በብሉይ ኪዳን ዘመን አብ፥ በምድር ላይ በነበረ ጊዜ ደግሞ ወልድና አሁን ደግሞ በሰዎች ልብ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ሆኖ የሚኖር አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ አስተማረ። ይህ ግለሰብ የተወሰኑ ጥቅሶችን ያለ አውዳቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ ፈልቅቆ በማውጣት ሙሉጌታ እውነተኛ ክርስቲያን አለመሆኑን አሳየው። በመሆኑም ሙሉጌታ የቀድሞ አሳቡን ለውጦ ወደ ሌላ ቤተ ክርስቲያን ተዛወረ። ይህም ከእውነት ወደ ሐሰተኛ ትምህርት እንዲቅበዘበዝ አደረገው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ሁሉ መሪዎች እግዚአብሔር ለሕይወታቸው ካቀደው ዓላማ እንዲኮበልሉ ያደረጋቸው ችግር ምን ነበር? በቤተ ክርስቲያንህ እነዚህን ሦስት ችግሮች እንዴት እንደተመለከትህ ግለጽ። ለ) ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከእነዚህ ሦስት ችግሮች መራቅ እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው?

የጢሞቴዎስ መጽሐፍ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለክርስቶስ ውጤታማ አገልግሎት ይሰጡ ዘንድ ሕይወታቸውን በጥንቃቄ እንዲጠብቁ ያስጠነቅቃቸዋል። የወሲብ ሕይወታችንን በመጠበቅ ንጹሐን ሆነን መመላለስ ይኖርብናል። ለእግዚአብሔር ከምናገለግለው አገልግሎት ወይም ከቤተሰባችን እንዳይበልጥብን የገንዘብ ፍቅር ራሳችንን መጠበቅ አለብን። ከሐሰት ትምህርቶችም ራሳችንንና የቤተ ክርስቲያናችንን ምእመናን መጠበቅ ይኖርብናል። እነዚህ ሦስት ችግሮች ዛሬ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ባለማቋረጥ የሚጋፈጧቸው ችግሮች ናቸው። ጳውሎስ በዚህ የጢሞቴዎስ መልእክት ውስጥ ጢሞቴዎስና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሙሉ ልባቸውን እንዲጠብቁ፥ ሕይወታቸውን እንዲጠብቁና እምነታቸውን በንጽሕና እንዲይዙ ያስጠነቅቃል።

ጳውሎስ ከሮም እስር ቤት ከተፈታ በኋላ በአውሮፓና በእስያ ውስጥ የሚገኙትን አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት የጎበኘ ይመስላል። በዚህም ጊዜ ጢሞቴዎስና ቲቶ አብረውት ይጓዙ ነበር። ጳውሎስ የቆጵሮስን ቤተ ክርስቲያን እንዲመሠርትና አንዳንድ ችግሮቻቸውን በማስወገድ ረገድ ይረዳቸው ዘንድ ቲቶን እዚያው ተወው። የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን የምትጋፈጣቸውን ችግሮች ለማስተካከልም ጢሞቴዎስን በኤፌሶን አቆየው። ጳውሎስ ቶሎ ወደ ኤፌሶን ለመመለስ እያሰበ ሳይሆን አይቀርም ወደ መቄዶኒያ የሄደው። ጳውሎስ እንዳሰበው በፍጥነት ባለመመለሱና ጢሞቴዎስም ወደ መቄዶኒያ ለመሄድ እያቀደ በመሆኑ፥ ጳውሎስ ይህንኑ የ1ኛ ጢሞቴዎስ መልእክት በመጻፍ ጢሞቴዎስ በኤፌሶን መሥራቱን እንዲቀጥል ይነግረዋል። በተጨማሪም ጳውሎስ በዚህ መልእክቱ ውስጥ የጢሞቴዎስ አገልግሎት በኤፌሶን ምን መሆን እንዳለበት ያብራራል። በዚህ መልእክት ውስጥ አንዳንድ ጠቃሚ ትምህርቶች ቀርበዋል። እነዚህም ሁሉም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በጥንቃቄ ሊያጤኗቸውና ሊከተሏቸው የሚገቡ ናቸው።

ሰይጣን የቤተ ክርስቲያን ጠንካራው ጠላት ሲሆን፥ ቤተ ክርስቲያን ውጤታማነቷን እንድታጣና እንድትጠፋ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ከሚዋጋባቸው ቀዳማይ መንገዶች አንዱ መሪዎቿን ማጥቃት ነው። ቤተ ክርስቲያን ከመሪዋ መንፈሳዊ ሕይወት አልፋ ልታድግ አትችልም። መሪዎች መንፈሳዊ ምስክርነታቸውን ካጡ፥ ሕይወታቸው ከቆሸሸ፥ እምነታቸውን ካመቻመቹ፡ ሰይጣን መሪውን ብቻ ሳይሆን ቤተ ክርስቲያኒቱንም አሸንፎአል ማለት ነው። በተጨማሪም አምልኮ፥ መሪዎቹን በሚመርጡበት ሁኔታ፥ እርስ በርሳቸው በሚዛመዱባቸው መንገዶች ቤተ ክርስቲያንን ለማጥቃት ይሞክራል። ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ እንድትንቀሳቀስ ከተፈለገ፥ በአግባቡ የተመረጡ መሪዎች፥ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለድሆች እንክብካቤ የተወጠነ ዕቅድና በማኅበረሰብ ውስጥ መልካም ምስክርነት ያለው የአባላት አኗኗር ወሳኝ ነው። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ የሰጠው ምክር እነዚህን ነጥቦች ይዳስሳል።

በአብዛኛቹ መልእክቶቹ እንደተለመደው፥ ጳውሎስ ይህንን መልእክት በእግዚአብሔር ፈቃድ የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ የሆነ ጳውሎስ በማለት ይጀምራል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት የሚጠቀምበትን ደብዳቤ ሲጽፍ በሐዋርያዊ ሥልጣኑ ላይ አጽንኦት ሰጥቷል። ዛሬ ይህንን እውነት የማንቀበል ከሆነ ይህ የጳውሎስን የሐዋርያነት ሥልጣን ብቻ ሳይሆን እነዚህን ቃላት የጻፈውን የመንፈስ ቅዱስ ሥልጣንም ቸል እያልን ነው ማለት ነው።

ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ለሁለት ዓይነት ትምህርቶች ጥንቃቄ እንዲያደርግ በመምከር ይጀምራል። በመጀመሪያ፥ ተረቶችና ፍፃሜ የሌላቸው የትውልድ ታሪኮች ነበሩ እነዚህ ነገሮች ምን እንደሚያካትቱና የሚያስተምሯቸው ደግሞ አይሁዶች ወይም አሕዛብ መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ አይጠቅስም። ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ምንም ዓይነት መንፈሳዊ ለውጥ የማያስከትሉ ሥነ መለኮታዊ ወይም ምሁራዊ ክርክሮች ሳይሆኑ አይቀሩም። ይህ ቤተ ክርስቲያንን ከማነጽና መንፈሳዊ ዕድገትን ከማምጣት ይልቅ የሚከፋፍሉ ሥነ መለኮታዊ ጉዳዮችን ለምንከታተል ሰዎች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ነው። ስለ እነዚህ ደቃቅ አስተምህሮዎች መከራከሩ ብዙውን ጊዜ ከንቱ ድካም ነው። ውጤቱም ክርስቶስን የማያስከብር ክፍፍል በክርስቲያኖች መካከል ማስከተል ነው። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ የንጹሕ ልብ፥ የፍቅር፥ የመልካም ሕሊናና የእውነተኛ እምነት ምንጭ በሆኑት የእግዚአብሔር ቃል እውነቶች ላይ እንዲያተኩር ያሳስሰዋል።

ሁለተኛ፥ በግልጽ ከእውነት ያፈነገጡና ሰዎችን ከቤተ ክርስቲያን የሚያስኮበልሉ ትምህርቶች ነበሩ። ጳውሎስ በሁሉም መልእክቶቹ ውስጥ ማለት ይቻላል ሰይጣን ሰዎችን ከቤተ ክርስቲያን ለማስኮብለል የሚጠቀምባቸውን የተለያዩ የሐሰት ትምህርቶች የሚመለከት ትምህርት ያቀርባል። ጳውሎስ ባለማቋረጥ ከእነዚህ የሐሰት ትምህርቶች ጋር መዋጋትና ለእውነት መጋደል ከነበረበት፥ ዛሬም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በአብያተ ክርስቲያኖቻችን ተመሳሳይ ሁኔታዎች እንደሚኖሩ መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በኤፌሶን እንዲቆይ የፈለገበት ዋነኛው ምክንያት በዚያች ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አንዳንድ ሰዎች ሐሰተኛ አስተምህሮዎችን ያስፋፉ የነበሩ መሆናቸው ነበር። ከእነዚህም የሐሰት ትምህርቶች አንዱ ስለ ሕግ የተሳሳተ ግንዛቤ መያዝ ነበር። ጳውሎስ በአግባቡ ከተጠቀሙበት የብሉይ ኪዳን ሕግ መልካም መሆኑን ያምናል። ሕግ የተሰጠው ደኅንነትን ለማስገኘት ወይም የመንፈሳዊነት ማረጋገጫ እንዲሆን አልነበረም። ይልቁንም ሕግ የተሰጠው የሰዎችን የልብ ክፋት ለመቆጣጠርና ፈሪሀ እግዚአብሔር የሌላቸውን ተግባራት ለመገደብ ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሰይጣን በእነዚህ ሁለት ዓይነት የተሳሳቱ ትምህርቶች እማካኝነት ቤተ ክርስቲያንን ሲያጠቃ የተመለከትከው እንዴት ነው? ለ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሚዛናዊነቱን የጠበቀ ትምህርት እንዲሰጥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በሕጎች ላይ ባለማተኮር የወንጌሉን እውነት እንዲጠብቅ ያስጠነቅቀዋል (1ኛ ጢሞ. 1፡1-11)”

  1. Amanuel Mathewos

    እግዚአብሄር ሲሰራ የስራው አካል መሆን ደግሞም ከእርሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍን እንደ እድል ሲሰጥ እድሉን መጠቀም የክርስትና ሰውነት መለኪያ ነው። ለዚህ ስራችን ትልቅ ግበአት ሆናቹናል ጌታ በሁሉ ይባርካቹ… ከአርባምንጭ ክርስቲያን ተማሪዎች ህብረት በኳየር group daily Bible study አለን እናም በዚህ መልኩ እያጠናን ነው ጌታ ይባርካቹ።
    https://t.me/Choirs_BS ገብታቹ መመልከት ይቻላል ።

Leave a Reply

%d bloggers like this: