የዕብራውያን መልእክት ልዩ ባሕርያት፣ መዋቅር እና አስተዋጽኦ

የዕብራውያን መልእክት ልዩ ባሕርያት

 1. የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ እንደ ጳውሎስ ኢየሱስ ክርስቶስ፥ ክርስቶስ ኢየሱስ ወይም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ እያለ አይጽፍም። ነገር ግን አንዱን ስም ብቻ (ኢየሱስ ወይም ክርስቶስ) ሲል ይጽፋል።
 2. ከመጨረሻዎቹ ጥቂት ቁጥሮች በስተቀር፥ የዕብራውያን መልእክት ደብዳቤ አይመስልም። ጸሐፊው ስሙን በማስተዋወቅ ሰላምታ የሚሰጥበት መግቢያ በመጽሐፉ ውስጥ አይገኝም። ይህ እምነታቸውን ለመካድ ለሚያስቡ የተወሰኑ የአይሁድ ክርስቲያኖች የተላከ ሰነድ ወይም ስብከት ነው።
 3. በመጽሐፉ ውስጥ አምስት «የማስጠንቀቂያ» ምንባቦች አሉ (ዕብ. 2፡1-4፤ 3፡7-4፡13፤ 5፡11-6፡8፤ 10፡19-39፤ 12፡14-29)። (ማስታወሻ፡ አንዳንድ ምሁራን ሰባት የማስጠንቀቂያ ምንባቦች እንዳሉ ይናገራሉ። እነዚህም፥ ዕብ. 2፡1-4፣ 3፡7-19፣ 4፡11-13፤ 5፡11-6፡20፣ 10፡26-31፤ 12፡25-29፥ 13፡15-19)። እነዚህ ምንባቦች እማኞች ክርስቶስን ክደው ወደ ቀድሞው አኗኗራቸው እንዳይመለሱ ጽኑ ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጣሉ። ድነት (ደኅንነት) እና ዘላለማዊ በረከቶች የሚገኙት በክርስቶስ ብቻ ነው።
 4. የዕብራውያን መልእክት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በሚገባ የሚያውቁትን ብሉይ ኪዳን በብዙ ስፍራዎች ላይ ይጠቅሳል። ነገር ግን ጸሐፊው የተጠቀመባቸው የብሉይ ኪዳን ክፍሎች የተወሰዱት ከአረማይክ ወይም ዕብራውያን የብሉይ ኪዳን ሳይሆን፥ ሴብቱዋጄንት ከሚባለው የግሪክ የብሉይ ኪዳን ትርጉም ነው። ይህም እነዚህ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የዕብራውያን የብሉይ ኪዳን በብዛት ከግልጋሎት ላይ ከሚውልበት ኢየሩሳሌም ከተማ ሳይሆን፥ የግሪክ የብሉይ ኪዳን አገልግሎት በሚሰጥባት በሌላ የሮም ግዛት ውስጥ እንደነበሩ ያመለክታል። ጸሐፊው ከብሉይ ኪዳን ሲጠቅስ፥ በአብዛኛው ከሙሴ መጻሕፍት ወይም ከመዝሙራት ይጠቅሳል። እንደ ብዙዎች የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ሙሴ ወይም ዳዊት ምንባቡን እንደ ጻፈው ከመናገር ይልቅ እግዚአብሔር (ዕብ. 2፡6)፥ ኢየሱስ (ዕብ. 2፡11-12) ወይም መንፈስ ቅዱስ (ዕብ. 3፡7) ምንባቡን እንደተናገረ ይገልጻል። በዚህም የብሉይ ኪዳንን መለኮታዊ ሥልጣን ከፍ አድርጎ ያሳያል።
 5. ጸሐፊው እንደ ሀ) «የሚሻል» (ዕብ. 1፡4፤ 6፡9፣ 7፡7፥ 22፤ 8፡6፤ ወዘተ…)፤ ለ) «ዘላለማዊ» (ዕብ 1፡8፤ 5፡6፥ 9፤ 6፡1-2፥ 20፣ 7፡11፥ 17፥ 21፥ 24፥ 28፤ ወዘተ…)፤ ሐ) «ፍጹም» (ዕብ. 2፡10፤ 5፡9፣ 7፡11፥ 19፣ 9፡9፤ 10፡1፥ 14፤ ወዘተ..) መ) «ሰማያዊ» (ዕብ. 1፡10፤ 3፡1፤ 4፡14፤ 6፡4፤ ወዘተ) ባሉት ቃላት ላይ ትኩረት ይሰጣል።
 6. ጸሐፊው ትምህርቱ ራሱንም እንደሚያጠቃልል የሚያመለክቱትን አገላለጾች ይጠቀማል (ዕብ. 4፡1፥ 11፥ 14፥ 16፤ 6፡1፤ 10፡22-25፤ 12፡1-3፥ 28፤ 13፡1፥5፥ 13፥15።)

የዕብራውያን መልእክት ስለ ክርስቶስ ማንነትና ሥራ ሰፊ ማብራሪያ ያቀርባል። ክርስቶስ ካህናችን መሆኑን፥ ለኃጢአታችን መሠዋቱን፥ እንዲሁም ፍጹም አምላክና ፍጹም ሰው መሆኑን ያብራራል።

የዕብራውያን መዋቅር

 1. ዕብራውያን በጥንቃቄ የተዋቀረ መጽሐፍ ነው። ጸሐፊው ክርስቶስ ከሌሎች የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ማዕከላት እንደሚበልጥና የእነዚሁ የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዓቶች ፍጻሜ የሆነላቸውን ምክንያቶች በመዘርዘር መልእክቱን ግሩም አድርጎ አዋቅሮአል። በመሠረታዊነት ይህ መልእክት ሁለት ዐበይት ክፍሎች አሉት።

ሀ. ዕብ. 1፡1–10፡18 የመጽሐፉን መሠረታዊ ትምህርት ያቀርባል። ይኸውም አይሁዶች ጥንታዊ ሃይማኖታቸውን ታላቅ እንዳደረጉ ከሚያስቧቸው ነገሮች ሁሉ ክርስቶስ እንደሚበልጥ የሚያሳይ ነው። ክርስቶስ ከብሉይ ኪዳን ቅዱሳን መጻሕፍት፥ መላእክት፥ ሙሴ፥ ኢያሱ፥ አሮን፥ የእንስሳት መሥዋዕቶች፥ ወዘተ እንደሚበልጥ ተገልጾአል።

ለ) ዕብ. 10፡19-13፡25 በእምነት መኖር ምን ማለት እንደሆነና አማኞች እምነታቸውን በእግዚአብሔር ላይ በመጣል እንዴት በታማኝነት እንደሚጻኑ ያብራራል። ወደ መንግሥተ ሰማይ እስክንደርስ ድረስ ለእርስ በርሳችን ታማኞች ሆነን መጽናት ይኖርብናል። መንግሥተ ሰማይ አማኞችን ሁሉ በመጠባበቅ ላይ ያለች እውነተኛይቱ ኢየሩሳሌም ናት።

 1. ጸሐፊው ትምህርቱን በሚያቀርብበት ጊዜ በአመዛኙ ቆም ይልና የሚያስተምራቸው እውነቶች ምን ዓይነት አስከትሎት እንዳላቸው ለአንባብያኑ ያስገነዝባል። በተለይም እንዲህ ዓይነቱን ማስጠንቀቂያ የሚሰጠው ክርስቶስን ክዶ ወደ ይሁዲነት መመለስ አደገኛ መሆኑን ለማመልከት ነው። እነዚህ አምስት (አንዳንድ ምሁራን እስከ ሰባት ያደርጓቸዋል) የማስጠንቀቂያ ምዕራፎች (ዕብ. 2፡1-4፤ 3፡7-4፡13፤ 5፡11-6፡8፤ 10፡19-39፤ 12፡14-29) ቅንፋዊ ምንባቦች በመባል ይታወቃሉ፥ ለዚህም ምክንያቱ እነዚህ ምንባቦች ወደኋላ ለመመለስ የሚያስቡትን ሰዎች ለማስጠንቀቅ ሲሉ የክርክሩን ይዘት የሚያቋርጡ መሆናቸው ነው። ጸሐፊው ማስጠንቀቂያውን ከሰጠ በኋላ፥ ወደ አሳቡ በመመለስ ክርስቶስ ከብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዓት እንደሚበልጥ የሚያምንባቸውን ማረጋገጫዎች ያቀርባሉ።

የዕብራውያን አስተዋጽኦ

 1. ክርስቶስ በብሉይ ኪዳን ከተከበሩት ነገሮች ሁሉ በላይ ነው (ዕብ. 1፡1-10፡18)።

ሀ. ክርስቶስ የእግዚአብሔር ከፍተኛው መገለጥ ነው (ዕብ 1፡1-3)።

ለ) ክርስቶስ ከመላእክት ይበልጣል (ዕብ. 1፡4-2፡18)።

የመጀመሪያው የማስጠንቀቂያ ምንባብ – (ዕብ 2፡1-4)

ሐ) ክርስቶስ ከሙሴ ይበልጣል (ዕብ. 3፡1-19)።

መ) ሁለተኛው የማስጠንቀቂያ ምንባብ- ዕብ 3፡7-4፡13። [ክርስቶስ ከኢያሱ እንደሚበልጥ የሚናገረውን ክፍል ያጠቃልላል።(ዕብ. 4፡1-13)]

ሠ. ክርስቶስ ከአሮን ወገን ከሆኑት ሊቀ ካህናት ይበልጣል (ዕብ. 4፡14-7፡28)።

 1. ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ለመሆን ብቁ ነው (ዕብ. 4፡14–5፡10)።
 2. ሦስተኛ የማስጠንቀቂያ መልእክት (ዕብ. 5፡11-6፡20)።
 3. የክርስቶስ ሊቀ ካህንነት ከአሮን ይበልጣል (ዕብ 7)።

ረ) የክርስቶስ አገልግሎትና መሥዋዕት በብሉይ ኪዳን ዘመን ከነበሩት ይበልጣል (ዕብ. 8-10)።

 1. የክርስቶስ አገልግሎት ከብሉይ ኪዳን በሚበልጠው አዲስ ኪዳን ላይ የተመሠረተ ነው (ዕብ 8)።
 2. የክርስቶስ አገልግሎት ከመገናኛ ድንኳን በሚበልጠው ሰማያዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ ይካሄዳል (ዕብ. 9፡1-12)።
 3. የክርስቶስ መሥዋዕት ከእንስሳት መሥዋዕቶች ይበልጣል (ዕብ 9፡13–10፡18)።
 4. ክርስቶስ ከብሉይ ኪዳን ውስጥ ካሉት ነገሮች ሁሉ ስለሚበልጥ፥ እርሱን እንዴት መከተል እንዳለብን (ዕብ. 10፡19–13፡25)

ሀ. አራተኛው የማስጠንቀቂያ ምንባብ (ዕብ. 10፡19-39)።

ለ. ክርስቶስን መከተል እምነትን ይጠይቃል (ዕብ. 11)።

ሐ. ክርስቶስን መከተል ማለት በመንፈሳዊ ሩጫችን መጽናት ማለት ነው (ዕብ. 12፡1-13)።

መ. አምስተኛው የማስጠንቀቂያ ምዕራፍ (ዕብ. 12፡14–29)።

ሠ. እንደ የክርስቶስ ተከታዮች እንዴት መመላለስ እንዳለብን (ዕብ. 13፡1-17)።

ረ. መደምደሚያ (ዕብ. 13፡18-25)

Leave a Reply

%d bloggers like this: