የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡- ዕብራውያን 1፡1 አንብብ። ሀ) ስለ ጸሐፊው የተጠቀሰ ምን ነገር አለ? ለ) ሮሜ 1፡1 አንብብ። ይህ የሮሜ መጽሐፍ ስለ ጸሐፊው ከሚናገረው እንዴት ይለያል?

ምንም እንኳን የዚህ መጽሐፍ የአማርኛው ርእስ «የሐዋርያው የጳውሎስ መልዕክት ወደ ዕብራውያን» ቢልም፥ ጳውሎስ የመጽሐፉ ጸሐፊ እንደሆነ አይናገርም። ይህ ጳውሎስ በሮሜም ሆነ በሌሎች መልእክቶቹ መግቢያ ላይ ራሱን ከሚያስታውቅበት ሁኔታ የተለየ ነው። የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ በመልእክቱ ውስጥ ስሙን አልጻፈም። ይህ ከጥንታዊ የደብዳቤ አጻጻፍ ልማድ የተለየ ነው። መልእክቱ መጀመሪያ የተጻፈላቸው ሰዎች ጸሐፊውን ያውቁት እንደነበረ አይጠረጠርም። ምክንያቱም ጸሐፊው ሊጎበኛቸው እንዳልቻለ (ዕብ. 13፡19)፥ ዳሩ ግን አንድ ቀን ከጢሞቴዎስ ጋር ለመምጣት እንደሚፈልግ ይናገራል (ዕብ. 13፡23)። እንደ አለመታደል ሆኖ፥ መጽሐፉም ሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ማን እንደሆነ አይናገሩም። በአጠቃላይ፥ የጥንቶቹ ምሥራቃዊያን አብያተክርስቲያናት (ሶሪያ፥ ግብጽና ኢትዮጵያ) ጳውሎስ ይህን መልእክት እንደ ጻፈ ያምናሉ። ምዕራባዊያን አብያተ ክርስቲያናት (ሮም) ግን ጳውሎስ ይህን መልእክት እንደ ጻፈ አያምኑም።

የዕብራውያንን መልእክት ቀረብ ብለን ስንመረምር፥ ስለ ጸሐፊው የሚከተሉትን ነገሮች እናገኛለን።

ሀ) ጸሐፊው የብሉይ ኪዳንን የአምልኮ ሥርዓትና የአይሁዳዊያን ጽሑፎችን የሚያውቅ አይሁዳዊ ነበር።

ለ) ጸሐፊው የብሉይ ኪዳንን የግሪክ ትርጉም የሚያውቅ፥ ከፍልስጥኤም ውጭ የተወለደ ሔለናዊ አይሁድ ነበር። ጸሐፊው የተጠቀመበት የግሪክ ቋንቋ የፓለስታይን አይሁዶችን ዓይነት ሁለተኛ ቋንቋ አይመስልም። እንዲሁም ደግሞ የዕብራውያንን ብሉይ ኪዳን የተጠቀመው የፓለስታይን እይሁዶች በሚጠቀሙበት መንገድ አይደለም።

ሐ) ጸሐፊው የክርስቶስ ቀጥተኛ ደቀ መዝሙር አልነበረም። ክርስቶስን ባያየውም፥ ከክርስቶስ ጋር ከነበሩት ሰዎች ወንጌልን ሰምቷል (ዕብ. 2፡3)። (ማስታወሻ ፥ ይህም ጸሐፊው ጳውሎስ እንዳልሆነ የሚያሳይ ይመስላል። ምክንያቱም ጳውሎስ ወንጌሉን ከክርስቶስ እንጂ ከሌሎች ሐዋርያት እንዳልተቀበለ ይናገራል። ገላ. 1፡11-12 ተመልከት።)

መ) ጸሐፊው በ70 ዓ.ም ቤተ መቅደሱ በሮማውያን ሲደመሰስ በሕይወት ነበር። የዕብራውያን መልእክት በተጻፈበት ወቅት፥ ቤተ መቅደሱ አገልግሎት እየሰጠ ከመሆኑም በላይ የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዓትም እንደ ቀጠለ ነበር። ነገር ግን፥ በቅርብ ጊዜ ይህ ሁኔታ እንደሚያከትም የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ገልጾአል (ዕብ. 8፡13)።

ሠ) ጸሐፊው ይሁዲነትን የሚያውቅ ብቻ ሳይሆን፥ ሐዋርያነትና ቀደምት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የተቀበሉት ዝነኛ ሰው ነበር።

ረ) ጸሐፊው እስር ቤት ውስጥ የነበረውን ጢሞቴዎስን ያውቅ ነበር (ዕብ. 13፡23)። የዕብራውያንን መልእክት ተቀባዮች ከጢሞቴዎስ ጋር ለመጎብኘት ይፈልግ ነበር።

ሰ) ጸሐፊው በአንባቢዎቹ በሚገባ ስለሚታወቅ፥ ማንነቱን ለመግለጽና ተደማጭነት ለማግኘት ስሙን መጥቀስ አላስፈለገውም።

ሸ) ጸሐፊው አንባቢዎቹን ለመጎብኘትና ከእነርሱ ጋር ዳግም አብሮ ለመሆን ይፈልጋል። ነገር ግን በሆነ ምክንያት (ምናልባትም እስር ቤት ውስጥ በመሆኑ) ይህን ለማድረግ ሳይችል ቆይቷል። ለመሆኑ እነዚህን መመዘኛዎች የሚያሟላና የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ሊሆን የሚችል ሰው ማን ነው? የተለያዩ ምሁራን የሰጧቸው አስተያየቶች ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል።

  1. ጳውሎስ፡ ከ400 ዓ.ም እስከ 1600 ዓ.ም፥ ብዙውን ጊዜ ለዚህ መጽሐፍ የተሰጠው ርእስ «የጳውሎስ መልእክት ለዕብራውያን» የሚል ነበር። ይህም የመልእክቱ ጸሐፊ ጳውሎስ ነው የሚል አመለካከት በስፋት እንዲታይ አድርጓል። ጳውሎስ የፈሪሳዊነት ትምህርት የተከታተለ በመሆኑ፥ የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዓትንና የአይሁዶችን የአስተሳሰብ መንገዶች በጥልቀት ሊያውቅ ይችል ነበር። ሌሎች ከላይ የቀረቡትን መመዘኛዎችንም እንዲሁ ያሟላል። የዚህ መልእክት ጸሐፊ ጳውሎስ ነው የሚሉ ምሁራን ጳውሎስ ስሙን ያልጠቀሰበት ምክንያት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች መጽሐፉን ለማንበብና ትምህርቶቹን ለመቀበል ፈቃደኞች እንዲሆኑ በማሰብ ነው ይላሉ። በሐዋርያት ሥራ ውስጥ እንደተመለከተው፥ አይሁዶች ጳውሎስን ይጠራጠሩና ትምህርቱን ላለመቀበል ይሞክሩ ነበር። (ነገር ግን ከዕብራውያን መልእክት ውስጥ እንደምንመለከተው፥ የመልእክቱ አንባቢዎች ጸሐፊውን የሚያውቁት ይመስላል።) እነዚህ ምሁራን እንደሚሉት ምንም እንኳን ጳውሎስ በቀጥተኛ መገለጥ ከክርስቶስ ብዙ ነገር ቢቀበልም፥ ስለ ክርስቶስ አብዛኛዎቹን እውነታዎች የተማረው ከሐዋርያት ነበር ሲሉ ይከራከራሉ (1ኛ ቆሮ. 5፡1-3)። የጳውሎስ የቅርብ የሥራ ተባባሪ የሆነው ጢሞቴዎስ መጠቀሱ (ዕብ 13፡23)፥ የዚህ መልእክት ጸሐፊ ጳውሎስ ነው የሚለውን አስተሳሰብ ያጠነክራል።

ጳውሎስ ይህን መልእክት እንዳልጻፈው የሚናገሩ ምሁራን የሚከተሉትን ነጥቦች ይጠቅሳሉ።

ሀ) ጳውሎስ የመልእክቱ ጸሐፊ መሆኑን በመግቢያው ላይ አልጠቀሰም። ይህ የዕብራውያንን መልእክት ከሌሎች መልእክቶች ሁሉ ይለየዋል። አንባቢዎቹ ጸሐፊውን ስለሚያውቁ፥ መልእክቱን የጻፈው ጳውሎስ ቢሆን ኖሮ እንደ ሌሎች መልእክቶች ሁሉ ጸሐፊነቱን ይናገር ነበር።

ለ) የዕብራውያን መልእክት የተጻፈበት የግሪክ ቋንቋ ሌሎች የጳውሎስ መልእክቶች ከተጻፉበት የተለየ ነው።

ሐ) እንደ የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ያሉ ጳውሎስ በተደጋጋሚ የሚጠቀምባቸው አገላለጾች በዚህ መጽሐፍ ውስጥ አይገኙም።

መ) ቀደምት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የመጽሐፉ ጸሐፊ ማን እንደሆነ አያውቁም። መልእክቱ በግልጽ በጳውሎስ ቢጻፍ ኖሮ ያውቁት እንደነበር አይጠረጠርም።

  1. በርናባስ፡ በ200 ዓ.ም ተርቱሊያን የተባለ የቤተ ክርስቲያን የታሪክ ምሁር የዕብራውያን መጽሐፍ ጸሐፊ በርናባስ ነው ሲል ተናግሯል። በርናባስ ከላይ የተጠቀሱትን አብዛኞቹን መመዘኛዎች ያሟላል። በርናባስ ከሌዊ ወገን የተወለደ ሔለናዊ አይሁድ በመሆኑ፥ የብሉይ ኪዳንን የአምልኮ ሥርዓትና ይሁዲነትን በሚገባ ያውቃል (የሐዋ. 4፡36)። ያደገው በፍልስጥኤም ሳይሆን ቆጵሮስ ውስጥ ነበር። አይሁዶችና የቀድሞዋ ቤተ ክርስቲያን በርናባስን ያከብሩት ነበር። በርናባስ ከመጀመሪያዎቹ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት አንዱ አልነበረም። ነገር ግን ከሐዋርያት ጋር ጊዜ በማሳለፍ ስለ ክርስቶስ ሊያውቅ ችሏል። ምንም እንኳን በርናባስ በአሕዛብ መካከል የወንጌል ስርጭት ተግባራትን ቢያከናውንም፥ ትኩረት የሰጠው ለአይሁዶች ይመስላል።
  2. አጵሎስ፡ በ15ተኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ፥ ማርቲን ሉተር አጵሎስ ይህን መልእክት ሳይጽፍ እንዳልቀረ ተናግሯል። አጵሎስ በአሌክሳንደሪያ የተወለደ አይሁዳዊ ቢሆንም፥ አይሁዳዊ ክርስቲያን ነበር። አጵሎስ በጥንታዊቷ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በተለይም በአሕዛብ ዘንድ በስፋት ይታወቅ ነበር። ከአይሁዶች ጋር በመከራከር የክርስቶስን መሢህነት ለማሳየት የቻለ ብቃት ያለው አገልጋይ ነበር (የሐዋ. 18፡24-28)። ይህ ጸሐፊ ብሉይ ኪዳንን የተረዳባቸው አንዳንድ መንገዶች በዚህ ጊዜ በኤሌክሳንደሪያ (ግብጽ) የነበሩ አይሁዶች ከሚጽፉበት ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነበር።

4 ሉቃስ፡ አንዳንድ ምሁራን የዚህ መእልክት ጸሐፊ ሉቃስ እንደነበር ገልጸዋል። ይህንንም ያሉት ሉቃስ የጻፋቸውን የሐዋርያት ሥራና የሉቃስ ወንጌል የግሪክ ቋንቋና የአጻጻፍ ስልት ከዕብራውያን መልእክት ጋር በማነጻጸር ነው። ነገር ግን ሉቃስ አሕዛብ በመሆኑ እንዲህ ዓይነት መጽሐፍ ይጽፋል ተብሎ አይታሰብም።

  1. ጵርስቅላና አቂላ፡ አንዳንድ ምሁራን ጵርስቅላ በአቂላ እገዛ ይህን መጽሐፍ እንደ ጻፈች ያስባሉ። እነዚህ ሰዎች በሮም ከተማ ውስጥ የሚኖሩ አይሁዶች መሆናቸውን እናውቃለን። ጵርስቅላና አቂላ ክርስቲያናዊ እውነት የማስተማር ብቃት ነበራቸው። ምክንያቱም ከጳውሎስ የሁለተኛና ሦስተኛ የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞዎች ላይ በከፊል የተሳተፉ ከመሆናቸውም በላይ፥ አጵሎስን ለማስተማርና ለአገልግሎት ለማዘጋጀት ከፍተኛ ከአስተዋጽኦ አድርገዋል (የሐዋ. 18፡26)። ከጳውሎስ ጋር ረጅም ጊዜ በማሳለፋቸውና ሔለናዊ አይሁዶች በመሆናቸው የብሉይ ኪዳንን የአምልኮ ሥርዓትና የግሪኩን ብሉይ ኪዳን ሊያውቁ ይችሉ ነበር። በዕብራውያን ውስጥ እንደተገለጸው የክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ ጉዞ በእነዚህ ሰዎች በግልጽ የሚታወቅ ነበር። ምክንያቱም ራሳቸው ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱ ኖረዋልና። እንዲሁም በሮም ለተወሰነ ጊዜ የቆዩ በመሆናቸው በዚያ አካባቢ ይታወቁ ነበር። ስለሆነም፥ ሰላምታ የሚልኩላቸው ጣሊያናውያን ወዳጆች ሊኖሯቸው ይችሉ ነበር። ምናልባትም ጵርስቅላ በመልእክቱ ውስጥ ስሟን ያልጠቀሰችው የሴቶች ጸሐፊነት በወቅቱ ተቀባይነት ስለማያገኝ ይሆናል። ይሁንና፥ ይህንን ንድፈ አሳብ ለመቀበልም ሆነ ላለመቀበል የሚያስችል ብዙ መረጃ የለንም።

ሌሎች የተለያዩ ምሁራን የሰጡአቸው የአገልጋዮች ስሞች ቢኖሩም። በስፋት የሚታወቁት አምስቱ እነዚህ ናቸው። መልእክቱን የጻፉት ጳውሎስ ወይም በርናባስ የነበሩ ይመስላል። ነገር ግን የዕብራውያንን መልእክት ማን እንደ ጻፈው በትክክል ለማወቅ አልተቻለም። ይሁንና፥ መንፈስ ቅዱስ ቀደምት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የዕብራውያን መልእክት ትምህርቶች አስፈላጊዎች መሆናቸውን አምነው የአዲስ ኪዳን አካል አድርገው እንዲቀበሉት አስችሏቸዋል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: