ክርስቶስ ከመላእክት ይበልጣል (ዕብ. 1፡4-2፡18)

በአይሁዶች ባሕሪና እምነት ውስጥ መላእክት በከፍተኛ ደረጃ ይከበራሉ። አይሁዶች ታላቅ የእግዚአብሔር መገለጥ እንደሆነ የሚያምኑት የሙሴ ሕግ የተሰጠው በመላእክት በኩል ነበር (ዕብ. 2፡2)። ስለሆነም፥ አይሁዳውያን አማኞች ክርስቶስ ከመላእክት እንደሚበልጥ መረዳት ያስፈልጋቸው ነበር። የዕብራውያን ጸሐፊ ክርስቶስ ከየትኛውም መልአክ የሚበልጥባቸውን መንገዶች እንደሚከተለው ዘርዝሯል፡-

ሀ) ክርስቶስ ለየትኞቹም መላእክት ከተሰጠ ስም ወይም ማዕረግ የሚበልጥ ስም አለው። እርሱ የእግዚአብሔር «ልጅ» ተብሏል።

ለ) እግዚአብሔር መላእክት ክርስቶስን እንዲያመልኩ አዝዟቸዋል።

ሐ) መላእክት የእግዚአብሔር አገልጋዮች እንጂ የሚመለኩ አይደሉም። ነፋስና እሳት ሰውን የሚያገለግሉ ነገሮች እንደሆኑ ሁሉ በነፋስ የሚሠራ ወፍጮ ለማስነሣት፥ ምግብ ለማብሰል፥ ወዘተ)፥ መላእክትም የተፈጠሩት እግዚአብሔርን እንዲያገለግሉ እና ዕቅዱን እንዲፈጽሙ ነው።

መ) የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ክርስቶስ አምላክ ነው። አምላክ እንደ መሆኑ መጣን፥ ዙፋኑ ዘላለማዊ ነው። በዚሁ የዘላለም መንግሥት ውስጥ በሰዎች ሁሉ ላይ የመግዛት ሥልጣን አለው። እርሱ ከእግዚአብሔር ፍጥረታት ሁሉ በላይ ነው። ይህም መላእክትንና ሰዎችን ይጨምራል።

ሠ) ክርስቶስ ዘላለማዊ ነው። አርጅቶ ከሚሞትና በአንድ ቀን ከሚጠፋ ፍጥረት በተቃራኒ፥ ክርስቶስ ለዘላለም አይለወጥም። ከዚህ በተቃራኒ መላእክት ፍጡራን በመሆናቸው ጅማሬ አላቸው።

ረ) ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ የሥልጣን ሥራ ተሰጥቶታል፡፡ ይህ የክብር ስፍራ ከክርስቶስ በቀር ለመላእክት አልተሰጠም።

ጸሐፊው ለአይሁዳውያን አማኞች ክርስቶስ እንዴት ታላቅ እንደሆነ እያሳያቸው ነው፡፡ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ያሉትን እንደ መላእክት ያሉትን ታላላቅ የተፈጠሩ ነገሮች በመውሰድ ከክርስቶስ ጋር ያነጻጽራቸዋል። መላእክት ታላቅ ሥልጣን ቢኖራቸውም፥ ክርስቶስ አምላክ በመሆኑ ይበልጣቸዋል። ስለሆነም፥ አይሁዶችና እንደ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ያሉ ሰዎች መላእክትን ማክበር ቢኖርባቸውም፥ ከክርስቶስ ጋር ሲነጻጸሩ ግን እጅግ ዝቅተኛ ስፍራ እንዳላቸው መገንዘብ ይኖርባቸዋል። መመለክ የሚገባው ኢየሱስ ነው፤ መልአክን በፍጹም ማምለክ የለብንም።

ከዚያም ጸሐፊው ሌላ አስደናቂ እውነት ይገልጻል። በመላእክትና በክርስቲያኖች መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? ክርስቲያኖች ለመላእክት ልዩ ክብር መስጠት ይገባቸዋል? ወደ መላእክት መጸለይ አለብን? ልናመልካቸው ይገባል? ጸሐፊው በአይሁዳውያን አስተሳሰብ እነዚህን ጥያቄዎች በማንሣት፥ መላእክት ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚያገለግሉ መናፍስት አይደሉምን?» ሲል ይጠይቃል። ምንም እንኳን መላእክት ታላቅና ኃያል ቢሆኑም፥ በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የእግዚአብሔር መንፈሳዊ አካል የሆኑ ክርስቲያኖች ከመላእክት ይበልጣሉ። መላእክት እግዚአብሔር ፈቃዱን ለማስፈጸም የሚጠቀምባቸው አገልጋዮች ናቸው። እግዚአብሔር ልጆቹን (አማኞችን) እንዲያገለግሉ መላእክትን ይጠቀማል።

የውይይት ጥያቄ፡– ይህ ምንባብ መላእክት ላይ ከፍተኛ ትኩረት ማድረግንና እነርሱን ለማምለክ መሻትን በተመለከተ ጠንካራ ማስጠንቀቂያ የሚሰጠው እንዴት ነው?

(የመጀመሪያው የማስጠንቀቂያ ምንባብ – ዕብ. 2፡1-4)

ጸሐፊው ክርስቶስ ከመላእክት እንደሚበልጥ ማስተማሩን አቋርጦ የመጀመሪያውን ዐቢይ የማስጠንቀቂያ ምንባብ ያቀርባል። ይህ የጎንዮሽ ጉዳይ በማቅረብ የመጽሐፉን አሳብ የሚያቋርጥ በመሆኑ፥ ምሁራን ቅንፋዊ ሲሉ ይገልጹታል። ከዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ዐበይት ዓላማዎች አንዱ የአይሁድ አማኞችንና ክርስቲያኖችን በሙሉ ከእምነት ተሰናክለው እንዳይወድቁ ማስጠንቀቅ ነው። እያንዳንዱ የማስጠንቀቂያ ምንባብ ካለፈው ይበልጥ እየጠጠረ ይሄዳል።

የውይይት ጥያቄ፡- ዘጸ. 19፡1-25፤ 20፡18-21 አንብብ። ሀ) እግዚአብሔር ለአይሁዶች ሕግ ለመስጠት በሲና ተራራ ላይ በተገለጸበት ወቅት ሁኔታው ምን ይመስል እንደነበር ግለጽ። ለ) አይሁዶች ይህን ያህል የፈሩት ለምን ነበር? ሐ) ከፍርሃታቸው የተነሣ ሙሴ ምን እንዲያደርግ ለመኑት?

ስለ መላእክት ማስተማሩ ጸሐፊው ሕግ በመላእክት አማካኝነት በእስራኤላውያን ስለተሰጠበት ሁኔታ እንዲያስብና የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ልጅ ለሰው ልጆች ከገለጸበት ሁኔታ ጋር እንዲያነጻጽር አደረገው። የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ክርስቶስ ከመላእክትና ከሙሴ እንደሚበልጥ ሁሉ፥ ክርስቶስ ያመጣው በጻጋ የሚገኝ የመዳን መንገድን እንዲሁ መላእክት ለአይሁዶች ካመጡት የሕግ መንገድ ይበልጥ ነበር (ዘዳግ. 33፡2)። አይሁዶች ሁሉ የሕጉን መሰጠት በታላቅ እድናቆት ነበር የሚያስታውሱት። ቅዱሱ እግዚአብሔር ከመላእክት ጋር ፍጹም ሕጉን ምርጥ ሕዝብ ለሆኑት አይሁዶች ሰጥቷል። ይህ ጊዜ ምን ያህል ልዩ እንደ ነበር መመልከት ይቻላል። አይሁዶች ሁሉ ለዚሁ የሕግ መሰጠት ራሳቸውን ማንጻት ያስፈልጋቸው ነበር። እነርሱም ሆኑ እንስሶቻቸው ወደ ተራራው ቢጠጉ ሞት እንደሚጠብቃቸው ተነግሯቸው ነበር። የእግዚአብሔር የሕልውናው ክብር እጅግ ታላቅ በመሆኑ እስራኤላውያን በፍርሃት ተዋጡ። ከዚህም የተነሣ ሙሴ ከእግዚአብሔር ጋር እንዲገናኝ ጠየቁት። ሕጉ እራሱ የጠነከረ በመሆኑ፥ ከዚሁ የሕግ ክፍሎች አብዛኞቹን መተላለፍ የሞት ቅጣት ያስከትል ነበር (ለምሳሌ፥ ዘጸ. 31፡14፤ 21፡12-17፥ ዘሌዋ. 20፡10-11)። በመሆኑም የብሉይ ኪዳን የሕግ መንገድ አለመቀበሉ ታላቅ ቅጣት ያስከትል ነበር።

ስለሆነም፥ በተፈጠሩ መላእክት አማካኝነት የተሰጠው ዝቅተኛው የብሉይ ኪዳን ሕግ ተላላፊዎችን በሞት የሚያስቀጣ ከሆነ፥ የእግዚአብሔር ልጅ በሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የመጣው የእግዚአብሔር የጸጋ መንገድ በማይቀበሉት ሰዎች ላይ የበለጠ ቅጣት ያስከትል ነበር። ይህም በእግዚአብሔር ልጅ በኩል መምጣቱ ብቻ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር ለአይሁዶች በተለያዩ ተአምራቶች ያረጋገጠው መንገድ ነው። (እግዚአብሔር ተአምራትን ስለሚልክባቸው ምክንያቶች አንዱ ይህ ነው። ተአምራቶች የሚመጡት የሰዎችን ፍላጎት ብቻ ለማሟላት ሳይሆን ወንጌሉ ከእግዚአብሔር እንደሆነ ለማረጋገጥ ጭምር ነው።) በኢየሱስ ክርስቶስ ለሚያምኑ ሰዎች መንፈሳዊ ስጦታዎች መሰጠታቸው ወንጌሉ ከእግዚአብሔር ዘንድ መምጣቱን ያመለክታል። ይህ በብሉይ ኪዳን ዘመን ያልነበረ ልምምድ ነው። ይህንን ሁሉ ችላ ብሎ ዝቅ ወዳለው የሕግ መንገድ መመለሱ የበለጠ ቅጣት ያስከትል ነበር። ይህም ሥጋዊ ሞት ብቻ ሳይሆን፥ መንፈሳዊና ዘላለማዊ ሞት ጭምር ነው።

ስለሆነም፥ ጸሐፊው ራሱን ጨምሮ አማኞች ሕይወታቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው ያስጠነቅቃል። ክርስቲያኖች ከወንጌሉ እውነት እንዳይወድቁ ያስጠነቅቃቸዋል። ብዙ ጊዜ አለማመን በድንገት የሚከሰት ነገር ሳይሆን በሂደት የሚመጣ ነው። ይህ መልሕቋ ተሰብሮባት ወደ ውኃ እንደምትሰምጥ እና ከዚያም ከድንጋይ ጋር እንደምትጋጭ ጀልባ ማለት ነው። ወይም ደግሞ የታሰረበትን ገመድ በጥሶ ወደ ጫካው ውስጥ በመሮጥ ጉድጓድ ውስጥ እስኪገባ ድረስ በሚንከራተት በኋላም የአውሬ ራት እንደሚሆን በግ ማለት ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ ጸሐፊው ወደ ሐሰት ትምህርት የምንገባውና ባለማመን ልባችን የሚደነድነው ቀስ በቀስ እንደሆነ ይናገራል። መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብና ሳናቋርጥ መጸለይ እናቆማለን። ከዓለማውያን ጋር ወዳጅነት እንመሠርታለን። ገንዘብ ወይም ትምህርት ዋነኛው ነገር እንደሆነ በማሰብ በእነዚሁ ነገሮች ላይ እናተኩራለን። ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ እናቆማለን። ዓይኖቻችን ሴቶችን በምኞት ይመለከታሉ። ከሥራ ባልደረቦቻችን ጋር ቢራ መጠጣት እንጀምራለን። እነዚህ ሁሉ ነገሮች መንፈሳዊ ሕይወታችን እንዲጎዳ ያደርጋሉ። በመጨረሻም፥ የእምነታችን መሠረት ይናጋና እምነታችን ይደረመሳል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እምነቱን ስለካደ እና በግል ስለምታውቀው አንድ ሰው አስብ። ክህደታቸው እምነታቸውን ባለመጠበቃቸው ምክንያት ቀስ በቀስ የጀመረው እንዴት ነበር? ለ) ባለማመን እንዳትወድቅ በሕይወትህ ምን እያደረግክ ነው?

ጸሐፊው ክርስቲያኖች ባለማመን እንዳይወድቁ በጽኑ ካስጠነቀቃቸው በኋላ፥ ክርስቶስ ከመላእክት እንደሚበልጥ የሚያስረዳውን ትምህርት ይቀጥላል።

ሠ) ክርስቶስ ሰው በመሆኑ ከመላእክት ይበልጣል (ዕብ 2፡5-9)። ጸሐፊው ስለ ሁለት ዓይነት ሰዎች የሚያስብ ይመስላል። በመጀመሪያ፤ ፍጹም ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ፡፡ ምንም እንኳን ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ቢሆንም፥ ሰው ሆኗል። ይህ ማለት ግን በሥልጣንና ኃይል ከመላእክት በታች ሆኗል ማለት አይደለም። ክርስቶስ ሰው መሆኑ፥ የመግዛት መብቱን ከመቀነስ ይልቅ በምድር ላይ በመሢሕነቱ እንዲገዛ አስችሎታል። ይህ ሰው ከመሆኑ በፊት የሚቻል አልነበረም። ይህ ደግሞ ለየትኛውም መልአክ ያልተሰጠ መብት ነው።

ሁለተኛ፥ ዛሬ ክርስቶስን በታማኝነት ከተከተልነው አማኞች ሁላችንም በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ እንደምንገዛ ቃል ተገብቶልናል (2ኛ ጢሞ. 2፡12፤ ራእይ 5፡10)። ብዙውን ጊዜ መላእክት ከሰዎች እንደሚበልጡና አስፈላጊነታውም ከሰዎች በላይ እንደሆነ እናስባለን። ወደ እግዚአብሔር የቀረቡና ቅዱሳን ናቸው ብለን እንገምታለን። ኃጢአት አይሠሩም። የበለጠም ኃይል አላቸው። ስለሆነም ይበልጣሉ ብለን እናስባለን። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከዚህ የተለየ አቋም አለው። የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ መዝሙር 8፡4-6ን በመጥቀስ፥ በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ሰዎች ከመላእክት እንደሚበልጡ ያስተምራል። በሚመጣው ዓለም ውስጥ ማለትም ወደፊት በሚመሠረት የክርስቶስ መንግሥት ውስጥ፥ እግዚአብሔር ለመላእክት የመግዛትን ሥልጣን አልሰጠም። ነገር ግን በምድር ላይ እና ወደፊት በሚመጣው መንግሥት ላይ የመግዛት ሥልጣን የተሰጠው ለሰዎች ነው። ምንም እንኳን የሰው ልጅ ከኃያላን መላእክት ጋር ሲነጻጸር ደካማ ቢሆንም፥ በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ የመግዛት ሥልጣን የተሰጠው ለሰው እንጂ ለመላእክት አይደለም። እግዚአብሔር ሰዎችን በፈጠረ ጊዜ ምድርን እንዲገዙ ሥልጣን ሰጥቶአቸዋል (ዘፍጥ. 1፡26)። ነገር ግን ከኃጢአት የተነሣ የሰዎች አገዛዝ እግዚአብሔር እንዳሰበው ተግባራዊ አልሆነም። አንድ ቀን ግን ይህ ይለወጣል። የእግዚአብሔር ልጆች ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር አብረው ምድርን ይገዛሉ። ይህ አገዛዝ እግዚአብሔር መጀመሪያ ዓለምን ሲፈጥር ያቀደውን ውጥን ተግባራዊ ያደርገዋል።

ፍጹም ሰው የሆነው ክርስቶስ ቀድሞውኑ መግዛት ጀምሮአል። ምንም እንኳን ክርስቶስ በምድር ላይ የሚኖር ፍጹም ሰው፥ ለእግዚአብሔር የተገዛና በመስቀል ላይ የሞተ በመሆኑ ምክንያት ለጊዜው ከመላእክት አንሶ የነበረ ቢሆንም፥ ክርስቶስ ከመላእክት እንደሚበልጥ የሚያመለክቱ አያሌ ነገሮች ተፈጽመዋል፡

ሀ) ክርስቶስ የክብር ስፍራ በሆነው በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ተቀምጧል። ጳውሎስ እንደተናገረው፥ ክርስቶስ ከስሞች ሁሉ የሚበልጥ ስም ተሰጥቶታል (ፊልጵ. 2፡9-10)።

ለ) ክርስቶስ ለሰዎች ሁሉ ሞትን ቀምሷል። ክርስቶስ እምነታችንን በእርሱ ላይ በጣልን ሰዎች ምትክ በመሆን ለሥጋዊ እና መንፈሳዊ ሞት ራሱን አሳልፎ ሰጥቷል። መንፈሳዊ ሞቱን ከእግዚአብሔር አብ መለየቱ ነበር። እኛ በሥጋ ልንሞት ብንችልም፥ መንፈሳዊ ሞት ግን አይገጥመንም። የዘላለም ሕይወት ይኖረናል።

ሐ) ክርስቶስ የድነት (ደኅንነት) ምንጭ ነው። በእግዚአብሔር ዕቅድ መሠረት፥ የነገሮች ሁሉ ጀማሪ የሆነው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጆች የሆኑት ሰዎች ሁሉ መሠረት መሪ ነው። በግሪኩ «ጸሐፊ» (በአማርኛ መጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ጀማሪ ዕብ. 4፡10) የሚለው ቃል ከሰዎች ፊት እየቀደመ ጫካውን በመመንጠር መንገድ የሚያበጅንም ሰው ያመለክታል። በመሆኑም ክርስቶስ ከዚህ በፊት ያልነበረውን የድነት (ደኅንነት) መንገድ ለመክፈት የእግዚአብሔር መሣሪያ ሆኖ አገለገለ። ሰዎች ሁሉ (አይሁዶችን ጨምሮ) ድነትን ከፈለጉ ክርስቶስ የከፈተውን መንገድ መከተል ይኖርባቸዋል።

ክርስቶስ ይሄንን የድነት (ደኅንነት) መንገድ ለመክፈት ብቁ የሆነው እንዴት ነው? ይሄንን በአምላክነቱ ሊያደርግ አይችልም ነበር። ክርስቶስ ይህን ተግባር ለማከናወን ሥጋና ደም የለበሰ ሰው መሆን ያስፈልገው ነበር። ሙሉ አዳኝና አማላጅ ሊሆን የሚችለው ሰው ሲሆን ብቻ ነበር። ስለ ላሞች ብዙ ልናውቅና ነገር ግን ሰዎች እንጂ ላሞች ባለመሆናችን ምክንያት ላሞችን በትክክል ልንረዳቸውና በገጠማቸው ችግር ብዙ ልንረዳቸው እንደማንችል ሁሉ፥ ክርስቶስ ሰው ከመሆኑ በፊት እግዚአብሔር በሰይጣን ቁጥጥር እና በራሳችን የኃጢአት ተፈጥሮ ሥር ታስረን የምንኖርበት የሰብአዊነት ሕይወት ምን እንደሚመስል በትክክል ሊረዳ አይችልም ነበር። መሞት ማለት ምን ማለት እንደሆነም ከራሱ ገጠመኝ ተነሥቶ ሊያውቅ አይችልም ነበር። ፍጹም አምላክ የነበረው ክርስቶስ ሰው በሆነ ጊዜ ግን ይህ ሁሉ ተለወጠ። እርሱ ሙሉ በሙሉ ከሰዎች ጋር ራሱን አስተባበረ ስለሆነም ክርስቶስ ሰው ሆኖ መኖር ምን እንደሚመስል ከራሱ ገጠመኝ ሊያውቅ ይችል ነበር። ድካም ተሰምቶታል፤ ተፈትኗል፥ ድህነትና ሞት ሁሉ ተፈራርቀውበታል። እነዚህ ነገሮች እግዚአብሔር ቀደም ሲል ሙሉ በሙሉ በሕይወት ገጠመኝነት የማያውቃቸው ነበሩ። በመሆኑም፥ ክርስቶስ ከአምላክነቱ ሊያደርግ የማይችለውን ተግባር ለመፈጸምና የበለጠ ብቁ አማላጅና አዳኝ ለመሆን ችሏል። ለሰው ልጆች ኃጢአት የሞተ ሰብአዊመለኮታዊ አካል በመሆኑ፥ ዲያቢሎስ በሰዎች ዘላለማዊ ዕድል ፈንታና ነፍሳት ላይ የነበረውን ቁጥጥር አስወግዷል። ክርስቶስ የኃጢአታችንን ዋጋ ስለከፈለ፥ የእርሱን ይቅርታ መንገድ ተቀብላለች፥ ለድነታችን (ለደኅንነታችን) በክርስቶስ በምናምንበት ጊዜ ሰይጣን ሞት የሚገባን ኃጢአተኞች መሆናችንን በመግለጽ ሊከስሰንና ወደ መንፈሳዊ ሞት ሊመራን አይችልም።

ለ) ክርስቶስ ሰዎች ከአዳምና ሔዋን ዘመን ጀምሮ ሲፈሩ የነበሩትን የሞት ፍርሃት ባርነት አስወግዷል። ሞት ክርስቶስ ከሙታን እስከተነሣበት ጊዜ ድረስ ገዝቷል። ሃብታም፥ ዝነኛ፥ ኃያላን ወይም መንፈሳዊ የነበሩ ሰዎች በሙሉ ሞተዋል። የሰው ልጅ ይህን የሞት አደጋ ሊያስወግድ የሚችልበት ምንም መንገድ የለም። ክርስቶስ በሞተና በተነሣ ጊዜ ግን የእግዚአብሔር ልጆች ከሞት በኋላ ምን እንደሚሆኑ የሚያመለክት ተግባር አከናውኗል። የሞትን ፍርሃት በማስወገድ ከእግዚአብሔር ልጆች ላይ የሞትን መውጊያ አንሥቷል። እርሱ የትንሣኤ ሙታን ማረጋገጫችን ነው።

ሐ) እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ኃጢአተኛ ለሆኑት ለሰው ልጆች የበለጠ ርኅራኄ እና እገዛ ሊያደርግላቸው ይችላል። ቀደም ሲል ይህንን ለማድረግ አልቻለም ነበር። ጸሐፊው እንዳለው «እርሱ እራሱ ተፈትኖ መከራን ስለተቀበለ የሚፈተኑትን ሊረዳቸው ይችላልና።» እግዚአብሔር በሥጋው መከራ ተቀብሎ አያውቅም። በመሆኑም፥ እኛ መከራ በምንቀበልበት ጊዜ ከራሱ ገጠመኝ ተነሥቶ ሊራራልን አይችልም ነበር። ክርስቶስ ሰው ከሆነባቸው ምክንያቶች አንዱ ለኃጢአት የምንፈተንበትን ሁኔታ ወይም ሞትን እንዴት እንደምንፈራ ለመረዳት ነበር። ክርስቶስ ሰው ከሆነ በኋላ ታላቅና ኃያል አምላክ ብቻ ሳይሆን፥ ችግሮቻችን የሚረዳ ሰው ለመሆን ችሏል። እርሱ ልክ እንደኛ ሆነ፡፡ የዕብራውያን ጸሐፊ እንደሚለው፥ ምንም እንኳን ክርስቶስ ፍጹም ቅዱስ እና ኃጢአት የሌለው ቢሆንም፥ ክርስቶስ አሁን ፍጹም ሆኗል። በዚህ ስፍራ «ፍጹም» የሚለው ቃል ክርስቶስ ቀደም ሲል ኃጢአተኛ እንደነበረና አሁን ግን ኃጢአት እንደሌለው የሚያመለክት አይደለም። ነገር ግን ክርስቶስ አሁን ሙሉ ለሙሉ የሰው ልጆች የድነት (ደኅንነት) ምንጭና ሊማልድላቸው የሚችል ሊቀ ካህን ለመሆን እንደቻለ የሚያመለክት ነው።

ሰዎች እንደ ሙሴ ወይም ማርያም ያሉ አማላጆች ያስፈልጉናል ከሚሉባቸው ምክንያቶች አንዱ እግዚአብሔር ሩቅ እንደሆነና ያሉበትን ሁኔታ እንደማይገነዘብ ወይም ለመገንዘብ እንደማይፈልግ በማሰባቸው ነው። የዕብራውያን መልእክት ግን ይህ እውነት እንዳልሆነና አማላጆች እንደማያስፈልጉን ይናገራል። አምላክ ብቻ ሳይሆን ፍጹም ሰው የሆነ አዳኝ አለን። አሁን እንኳን በሰማይ እያለ ክርስቶስ ፍጹም ሰው ነው። ሰው እንደ መሆኑም ከፈተና ጋር መታገል ምን እንደሆነ ያውቃል። ክርስቶስ ስደትንና ሞትን መፍራት፥ እምነትን ለመካድ መፈተን ምን እንደሆነ ያውቃል፡፡ ድህነት፥ ከጓደኞችና ቤተሰቦች ዘንድ ተቀባይነትን ማጣት፥ ወዘተ… ምን እንደሆነ ያውቃል። ክርስቶስ የምንጋፈጣቸውን ነገሮች ሁሉ ስለሚያውቅ፥ እነዚህ ሁኔታዎች በሚከሰቱበት ጊዜ እንደሚረዳንና እንደሚያግዘን በማወቅ በልበ ሙሉነት ወደ እርሱ ልንነሣ እንችላለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አማኞች እንዲፈሩና እምነታቸውን እንዲክዱ የሚያደርጉ ነገሮች ምን ምን ናቸው? ለ) ክርስቶስ እንዴት በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ እንዳለፈ ግለጽ። ሐ) በመጋፈጥ ላይ ያለነውን ችግር ቀደም ሲል ተጋፍጦ ያለፈና ሊረዳን የሚፈቅድ ክርስቶስ ከሰማይ እንዳለ ማወቁ ለምን እንደሚያበረታታንና እንደሚያስፈልገን ግለጽ።

መ) ክርስቶስ «ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት» ሆነ። ይህ ከዕብራውያን መልእክት ዐበይት ትምህርቶች አንዱ በመሆኑ ወደ በኋላ ሠፋ አድርገን እንመለከተዋለን። የዕብራውያን ጸሐፊ ኃጢአተኛ፥ ጊዜያዊና ሊረዳን ከማይችል የአይሁድ ሊቀ ካህናት በተቃራኒ፥ የሚያውቀን፥ ስለ እኛ የሚገደውና ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት የሚረዳን ሊቀ ካህናት በሰማይ እንዳለን ያስረዳል። ክርስቶስ ሊቀ ካህናታችን ለመሆን ይችል ዘንድ ከኃጢአት በቀር ሰብአዊ ልምምዶችን ሁሉ አደረገ። ካልሆነማ፥ በእግዚአብሔር አብ ፊት እንዴት በብቁ ሁኔታ ሊማልድልን ይችል ነበር?

ሠ) ክርስቶስ ራሱን በመስቀል ላይ በመሠዋት፥ «ለሕዝብ ኃጢአት ለማስተሰረይ» ቻለ። ስርየት የሚለው ቃል ከብሉይ ኪዳን የመሥዋዕት ሥርዓት የመጣ ነው (ዘሌዋ. 17፡11፤ 16፡20-22 አንብብ።) የቃሉ ትርጉም ኃጢአትን በመሸፈን የእግዚአብሔር ቁጣና ቅጣት ከሰው ላይ እንዳይደርስ መካላከልን ያመለክታል። እግዚአብሔር ለሰው ኃጢአት የሚሰጠው ፍርድ በምትክነት መርሕ ተግባራዊ ይሆን ነበር። በግለሰቡ ፋንታ አንድ እንስሳ እንዲሞት ይደረጋል። የእንስሳው ደም በሚረጭበት ጊዜ የግለሰቡን ኃጢአት ስለሚሸፍን ሰውየው ከእግዚአብሔር ፍርድ ይተርፋል። (ጸሐፊው ወደ በኋላ ኢየሱስ በመስቀል ላይ በሞተበት ወቅት ከእንስሳት ደም የበለጠ የኃጢአት መሸፈኛ እንደተገኘ ያብራራል።) ኢየሱስ በእኛ ምትክ ስለሞተ እና ደሙ ኃጢአታችንን ስለሚሸፍን፥ እግዚአብሔር ይቅር ሊለንና ፍርዱን ከእኛ ላይ ሊያነሣ ይችላል። ጳውሎስ እንዳለው፥ «በክርስቶስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም» (ሮሜ 8፡1)።

ረ. ክርስቶስ ብዙ ልጆችን ወደ ክብር ያመጣል። ጸሐፊው ይህን የሚለው የድነትን (ደኅንነትን) የመጨረሻ ጫፍ በመመልከት ነው። ይህ ክርስቶስ ለልጆቹ በሚመለስበት ጊዜ የሚከናወን ተግባር ይሆናል። በእርሱ የምናምን ሁላችን ከሞት እንነሣና አዲስ አካል እንለብሳለን። ከዚያም በክብር በእግዚአብሔር ፊት እንቆማለን።

የውይይት ጥያቄ፡– የሚማልድልህ ሰውና አምላክ የሆነ አዳኝ በሰማይ መኖሩ የሚያበረታታህ ለምንድን ነው? አሁን አምላክና ሰው የሆነው ስላደረገልህና እያደረገልህ ስላለው ነገር ለማመስገን ጊዜ ውሰድ፡፡

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading