ስለ አለማመን የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (ዕብ. 3፡7-4፡13)

ብዙውን ጊዜ ስላለፈው ዘመን ታላቅነት ለማውራት እንወዳለን። ቤተ ክርስቲያናችን እንዴት እንደ ተመሠረተችና እንዳደገች፥ እግዚአብሔር በመካከላችን የሠራቸው ተአምራት፥ ወዘተ. ተናግረን አንዘልቅም። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ አይሁዶች የሙሴን ዘመን ታሪኮች ቀይ ባህርን ስላቋረጡባቸው ተአምራታዊ ሁኔታዎች ያስታውሱ ነበር። መናውን፥ ከዓለት ውስጥ የፈለቀውን ውኃ፥ ድርጭቱን እግዚአብሔር ለሕዝቡ አስደናቂ ነገር እንደሠራበት ዘመን አድርገው ይቆጥሩ ነበር። የአይሁዶችን ታላቅ ሕዝብነት ለመግለጽ ኃላፊ ታሪኮች ይጠቅሱ ነበር። ይሁንና የታሪኩን ሌላኛ ጎን ዘንግተው ነበር። ይኸውም የአይሁድን ሕዝብ ዐመፅና እግዚአብሔርም በእርሱ ላይ የነበራቸውን እምነት በማጣታቸው ምክንያት ያመጣባቸው ፍርድ እንዳልተፈጸመ ታሪክ ማለፋቸው ነበር። የዕብራውያን ጸሐፊ የተቀረውን የሙሴን ታሪክና በአባቶቻቸው ላይ የደረሰውን ሁኔታ ሊያስታውሳቸው ፈለገ። እግዚአብሔር በሠራላቸው ተአምራት ላይ ከማተኮር ይልቅ፣ ጸሐፊው በእግዚአብሔር ላይ እምነታቸውን ጥለው ቢሆን ኖሮ ምን ሊከሰት እንደሚችል ይገልጽላቸዋል።

በዚህ በሁለተኛው የማስጠንቀቂያ ምንባብ ጸሐፊው ወደ ከነዓን በመግባቱ «እረፍት» ላይ አጽንኦት ይሰጣል። ጸሐፊው ወደ ከነዓን የመግባቱን እረፍት ድነት (ደኅንነትን) ከማግኘትና ወደ መንግሥተ ሰማይ ከመግባቱ እረፍት ጋር ያነጻጽራል። ምሁራን ይህ እረፍት የሚያመለክተው አማኞች በምድር ላይ ያገኙትን በረከት ስለመሆኑ ይከራከራሉ። ምናልባትም ይህ እረፍት በክርስቶስ የሚገኘውን የድነት (ደኅንነት) እረፍት (ከነዓንን ሳይሆን) በመንግሥተ ሰማይ የምናገኘውን ክብር አጣምሮ የያዘ ሳይሆን አይቀርም።

በብሉይ ኪዳን፥ አይሁዶች ከሙሴ መሪነት ከግብጽ እስከ ከነዓን የተጓዙበት መንገድ ጥቂት ሳምንታትን ብቻ የሚፈጅ ነበር። ነገር ግን ለአይሁዳውያኑ አርባ ዓመታት ፈጀባቸው። ካለማመናቸው የተነሣ፥ በምድረ በዳ ውስጥ የእግዚአብሔርን አስደናቂ ተአምራት የተመለከቱት ከሃያ ዓመት እድሜ በላይ የሆኑ አይሁዶች (ከኢያሱና ካሌብ በስተቀር) ወደ ከነዓን ምድር እረፍት ሳይገቡ ሞተዋል። በኢያሱ መሪነት ጊዜም አይሁዶች ወደ ከነዓን ሊገቡና ከአገሪቱ የተወሰነውን ክፍል ሊይዙ ቢችሉም፥ እግዚአብሔር ሊሰጣቸው የፈለገውን እረፍት አላገኙም ነበር። ባለማቋረጥ ከጠላቶቻቸው ጋር ጦርነት ይገጥሙ ነበር። በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ከእግዚአብሔር ጋር አይጓዙም ነበር። ከዚህም የተነሣ በኋላ ከዚህች አገር በምርኮኛነት ተወስደዋል። አይሁዶች ከቶውንም እግዚአብሔር ሊሰጣቸው የፈለገውን መንፈሳዊና ሥጋዊ እረፍት አላገኙም። ለዚህም ምክንያቱ በእምነታቸው ሊጸኑና ለእግዚአብሔር ታማኞች ሆነው ሊኖሩ አለመቻላቸው ነው። ይህ እግዚአብሔር ለአይሁዶች ተስፋ የገባው እረፍት ገና ያልተፈጸመና ወደፊት የሚመጣ መሆኑን በመዝሙር 95፡7-11 ውስጥ ተገልጾአል። የኢያሱ ዘመን ካለፈ ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ የተጻፈው ይኸው መዝሙር፥ የእግዚአብሔር ሕዝብ እረፍቱን ለማግኘት በእግዚአብሔር ታማኝነት ሊጸና እንደሚገባ ያሳስባል።

የአይሁድ ክርስቲያኖች፥ እንዲሁም ዛሬ በሕይወት ያለን ሁላችንም እግዚአብሔር ለእኛ ወዳዘጋጀው ወደዚሁ መንፈሳዊ የድነት (ደኅንነት) እረፍትና መንግሥተ ሰማይ እንድንገባ ተጠይቀናል። ነገር ግን ወደዚሁ እረፍት ለመግባት እንደ ቀድሞዎቹ አይሁዶች መሆን የለብንም። ልክ እንደ እነርሱ እግዚአብሔር እረፍቱን እንዳዘጋጀልን የተስፋ ቃል ሰጥቶናል። እንደ እነርሱ ወንጌሉን ሰምተናል፤ ልክ እንደ እነርሱ፥ የእግዚአብሔርን ተአምራት አይተናል። እረፍቱን ማግኘታችን ወይም አለማግኘታችን የሚወሰነው በእግዚአብሔር ላይ ባለን እምነትና ለእርሱ ታማኞች በመሆናችን ነው። ካላመንን ግን ዛሬ ምንም ያህል በረከቶች ብናገኝም፥ የኋላ ኋላ በአለማመናችን የተነሣ የእግዚአብሔርን ፍርድ እንቀበላለን። ስለሆነም፥ «እንደዚያ አለመታዘዝ ምሳሌ ማንም እንዳይወድቅ ወደዚያ እረፍት ለመግባት እንትጋ»። በመጀመሪያ፥ መንፈሳዊ እረፍታችንን ልንጀምር የምንችለው እንደ ይሁዲነት ባለ ታሪካዊ ሃይማኖት ወይም የወላጆቻችንን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ እምነት በመከተል ሳይሆን፥ በክርስቶስ በማመን መሆኑን ሊታወስ ይገባል። ከክርስቶስ ፊታችንን በምንመልስበት ጊዜ ወደ እረፍቱ ለመግባት አልፈለግንም ማለት ነው። ሁለተኛ፥ እግዚአብሔርን ሆን ብለን ሳንታዘዝ ስንቀርና በክርስቶስ ላይ የነበረንን እምነት ስንክድ፥ ይህ የዘላለማዊውን የመንግሥተ ሰማይ እረፍታችንን ከአደጋ ላይ ይጥላል። እግዚአብሔር ለአሁንና ለወደፊት የገባልንን መንፈሳዊና ዘላለማዊ እረፍት እናገኝ ዘንድ ለእግዚአብሔር ታማኝነት ጸንተን ስደትን ልንጋፈጥ ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቲያኖች ነን የሚሉ ሰዎች ወደ ዓለም ወይም ወደ ቀድሞው ሃይማኖታቸው በሚመለሱበት ጊዜ፥ እግዚእብሔር ለእነርሱ ያዘጋጀውን እረፍት የሚገፉት እንዴት ነው? ለ) የመንግሥተ ሰማያትን ዘላለማዊ እረፍት በተመለከተ፥ እንዲህ ዓይነቱ ውሳኔ የሚያስከትለው ዘለቄታዊ ውጤት ምንድን ነው?

ጸሐፊው ሁለተኛ ማስጠንቀቂያውን ወደ እግዚአብሔር ቃል በማመልከት ይፈጽማል። ሁላችንም ከምንጋፈጣቸው እጅግ አደገኛ ነገሮች መካከል ከእምነታችንና ከታዛዥነታችን መውደቅ ይገኙባቸዋል። መውደቅ በምንጀምርበት ጊዜ፥ ብዙውን ጊዜ በልባችን ውስጥ ምን እየተፈጸመ እንዳለ መመልከቱ አዳጋች ነው። አእምሮአችን ወደ ተሳሳተ ትምህርት ወይም አስተሳሰብ እንዴት እየገሰገሰ እንዳለ አንገነዘብም። ፍላጎታችን እግዚአብሔር ወደማይከብርባቸው ነገሮች እየተሯሯጠ መሆኑን አንመለከትም። በኃጢአት በምንወድቅበት ጊዜ እንኳን ብዙውን ጊዜ አእምሮአችን ለፈጸምነው ጥፋት ማመኻኛ ለማግኘት ይሞክራል። ለመሆኑ ለዚህ ዓይነቱ ችግሮች መፍትሔው ምንድን ነው? የራሳችንን ልብ እንድንመለከት የሚረዳን ምን ይሆን? የዚህ መልእክት ጸሐፊ መፍትሔው የእግዚአብሔር ቃል ብቻ መሆኑን ይጠቁማል። በሆስፒታል ውስጥ የበሽተኛውን ሰውነት ቀዶ ከውስጡ የተበላሸውን ነገር እንደሚያይና እንደሚያስወግድ ሐኪም የእግዚአብሔር ቃልም ከስለታም ሰይፍ በበለጠ ሁኔታ ወደ ሰው ልብ ይዘልቃል። የእግዚአብሔር ቃል እጅግ ጠልቆ ወደ ነፍሳችን ውስጥ ይዘልቃል። ይህም ብዙውን ጊዜ ሌሎችና ከራሳችንም የተደበቀ ስፍራ ነው፡፡ በዚያም የእግዚአብሔር ቃል የልብን አሳብና ፍላጎት ይመረምራል። ይህ አዎንታዊም አሉታዊም ውጤት አለው። በአዎንታዊ መልኩ፥ የእግዚአብሔር ቃል የተሳሳተ አሳብ መጠንሰስ የጀመርንበትን ስፍራ ያሳየናል። የተሳሳተ ተግባር የሚከተለው ከዚሁ አሳብ ነውና። ይህ ደግሞ የምንለወጥበትን፥ ንስሐ የምንገባባትን፥ ወደ እግዚአብሔር የምንመለስበትንና ወደ እረፍት ካለመግባቱ ፍርድ የምናመልጥበትን መንገድ ያመቻቻል። በአሉታዊ ጎኑ፥ ከእግዚአብሔር ምንም ነገር ልንደብቅ እንደማንችል ያሳያል። መንፈሳዊ ነን ብለን ሰዎችን ልናሞኝ ብንችልም፥ እግዚአብሔርን ግን ልናታልለው እንችልም። እርሱ በተደበቀው ማንነታችን፥ በነፍሳችንና በአእምሮአችን ያለውን ሁሉ ያያል። በሚያየውም መሠረት፥ ተጠያቂዎች አድርጎ ይፈርድብናል። ይህም በአመዛኙ በውጫዊ ማንነታችን ውስጥ ከሚታየው የበለጠ ነው። ከዛ ትንሿን አለመታዘዝ ወይም ሰዎችን የምትጎዳ የማትመስለውን አነስተኛ ኃጢአት ያያል።

ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል የማይጠሙ በሚመስሉበት ዘመን ውስጥ እንኖራለን፤ አስደናቂ ነገሮችን ለማየት እንናፍቃለን፤ እንደ በልሣን መናገር፥ ፈውስ እና እነዚህን በመሳሰሉ ነገሮች የሚናገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ብቻ እናነባለን፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ቁጣ ለማምለጥ፥ እንደ ግለሰቦች እና ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር እንድንገባ ወደሚፈልገው እረፍት ለመግባት ከፈለግን፥ ሰይፉን ከሕይወታችንና ከአብያተ ክርስቲያኖቻችን ማዛመድ ይኖርብናል። እግዚአብሔር በልባችን ውስጥ የተደበቀውን እንዲገልጥና እያጠፋን ያለውን በሽታ እንዲያስወግድ መፍቀድ አለብን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በብዙ ክርስቲያኖች እና አብያተ ክርስቲያናት ልቦች ውስጥ የተሰወሩትን አንዳንድ በሽታዎች ዘርዝር። ለ) እነዚህን ነገሮች ቆፍሮ ለማውጣትና ሰዎችን ለመለወጥ ብቃት ያለው የእግዚአብሔር ቃል ብቻ የሆነበትን ሁኔታ ግለጽ። ሐ) ቤተ ክርስቲያንህ ይህ የእግዚአብሔር ሰይፍ ከሰዎች ሕይወት ኃጢአትን እንዲያስወግድ በተሻለ ሁኔታ የምትጠቀምበት እንዴት ነው ነው? መ) መንፈስ ቅዱስ ሰይፍ ውስጣዊ ሁኔታን ለራስህ እንዲያሳይህ በግል ሕይወትህ ምን እያደረግክ ነው? ሠ) እግዚአብሔር የሚፈልገውን ዓይነት ሰው ትሆን ዘንድ በታላቅ ሰይፉ እንዲያስተካክልህ በጸሎት ጠይቀው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: