ማሞ ከልጅነቱ ጀምሮ የካቶሊክ እምነት ተከታይ ነበር። ከልጅነቱ ጀምሮ ኃጢአት በሚሠራበት ጊዜ ወደ ቄስ እንዲሄድ የሚያስረዳ ትምህርት ተከታትሎአል። ወላጆቹ፥ «ከቄሱ ዘንድ ሂድና የሠራኸውን ኃጢአት ተናዘዝ። እርሱም ይቅርታ ያደርግልሃል። ካልሆነ እግዚአብሔር በኃጢአትህ ይቀጣሃል» ሲሉ ያስረዱት ነበር። የሚሞቱበት ጊዜ በሚቃረብበት ወቅት ደግሞ ቄስ እንዲጠራና ጸበል እረጭቶ ኃጢአቶችን ሁሉ ይቅር እንዲያስብል ተነግሮት ነበር። ይህም ወደ መንግሥተ ሰማይ እንዲገባ ይረዳዋል ተብሎ የታሰበ ነበር።
ሚሚ የወንጌል አማኞች ቤተ ክርስቲያን አባል ነች። አንድ ሰው ክርስቲያን ለመሆን ከፈለገ፥ ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥቶ ማመን እንዳለበት ተምራለች። በዚህ ጊዜ ኅብረተሰቡን ወደ ክርስቶስ መምራት የሽማግሌዎች ኃላፊነት እንደሆነ ታውቃለች። ከቤተ ክርስቲያን ውጭ ደግሞ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ማምጣት የወንጌላዊው ሥራ እንደሆነ ታስባለች።
የውይይት ጥያቄ፡– እንደ ካህን ወይም የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ያሉ ሰዎች በእግዚአብሔርና በምእመናን መካከል የአማላጅነትን ተግባር ሲያከናውኑ ያየህበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) ይህ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው እውነት ይመስልሃል? ለምን?
በአብያተ ክርስቲያናት ውስጥ በእግዚአብሔርና በምእመናን መካከል የሚቆሙ የተወሰኑ መሪዎችን የማስነሣት ዝንባሌ ያለ ይመስላል። አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት እነዚህን ሰዎች ካህናት ወይም ቄሶች ይሏቸዋል። በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት፥ ሽማግሌዎች ወይም ወንጌላውያን የካህናትን ሚና ይጫወታሉ። ተራ የቤተ ክርስቲያን ምእመናን ግን ይህ በእነርሱና በእግዚአብሔር መካከል የተቀመጠ ግርዶሽ እንደሆነ ያስባሉ። ይቅርታ ለማግኘት ወይም ድነትን (ደኅንነትን) ለመቀበል እነዚሁኑ የሠለጠኑ ሰዎች ማማከር ያስፈልጋቸዋል። ነገር ግን በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከምንመለከታቸው ታላላቅ እውነቶች አንዱ መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ሁሉ ልብ ውስጥ እንደሚያድርና እያንዳንዱ አማኝ ካህን እንደሆነ ነው። እያንዳንዱ አማኝ በቀጥታ ወደ እግዚአብሔር ቀርቦ ችግሮቹን ሊያዋየው ይችላል፤ እንዲሁም እያንዳንዱ አማኝ ስለሌላው የማማለድ፥ በቃሉ መምከር እንዲሁ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ የመምራት መብት አለው (1ኛ ጴጥሮስ 2፡5፥ 9 አንብብ)። አማኞች ለይቅርታና ለእገዛ ሊመጡ የሚገባቸው ወደ አንድ ሊቀ ካህናት ብቻ ነው። እርሱም ታላቁ ሊቀ ካህናችን የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው።
አይሁዶች እግዚአብሔር ሊቀ ካህናት የተባለ አገልጋይ በእነርሱና በእግዚአብሔር መካከል እንደ ተሾመ በማመን ነበር የኖሩት። አምልኮ የሚካሄደው በሊቀ ካህናቱ በኩል ነበር። ይቅርታ የሚገኘውና መሥዋዕቶች የሚቀርቡት በካህናቱ በኩል ነበር። ሕዝቡ መሥዋዕቱን ይዞ ወደ ካህናት ወይም ሊቀ ካህናት ይመጣል። እነዚህም አገልጋዮች መሥዋዕቶቹን ለእግዚአብሔር ካቀረቡ በኋላ ሕዝቡ ይቅርታ እንዳገኙ ይናገራሉ። ምናልባትም የአይሁድ ክርስቲያኖች በቀድሞው አምልኮአቸው (ይሁዲነት) ሊቀ ካህናቱ የሚሰጣቸውን ይህንን ማረጋገጫ ከአዲሱ የክርስትና እምነታቸው አላገኙም ይሆናል። ወይም ደግሞ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ሊቀ ካህናቱ ቁልፍ ሚና የሚጫወትበት ጥንታዊ የአምልኮ ሥርዓት በክርስቶስ ስለነበራቸው እምነት አማራጭ ሊሆን እንደሚችል አስበው ይሆናል። ነገር ግን የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ክርስቶስ ከሊቀ ካህናቱ ሥልጣን እንደሚበልጥ ያሳያል። ክርስቶስ ከአሮን ወይም ካህናትና ሊቀ ካህናት ሆነው ካገለገሉት የአሮን ዘሮች ሁሉ በላይ ነው። ስለሆነም ከእንግዲህ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የሚቆም ሊቀ ካህናት አያስፈልግም። እንዲህ ዓይነቱን ሊቀ ካህናት መጠቀሙ እግዚአብሔር ክርስቶስ ብቻ ሊቀ ካህናችን እንዲሆን ካቀደበት ሁኔታ ጋር ይቃረናል። በክርስቶስ በኩል ሁላችንም ነፃና ቀጥተኛ የመግቢያ በር አለን።
ጥንታዊ የአይሁዳውያን አምልኮ በአራት ዐበይት ነገሮች ላይ የተመሠረተ ነበር። በመጀመሪያ፣ ካህናት የሚባሉ የአምልኮ መሪዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህም በዋናነት ጎልቶ የሚታየው ሊቀ ካህናቱ ነው። ሁለተኛ፥ የአምልኮ ቦታ፥ ማለትም የመገናኛ ድንኳንና በኋላም ቤተ መቅደሱ። ሦስተኛ፥ እንስሳት የሚሠዉበት የአምልኮ ሥርዓት፤ አራተኛ፥ በብሉይ ኪዳን የነበረ የአምልኮ አስተዋጽኦ ነበር። በሚቀጥሉት ስድስት ምዕራፎች ውስጥ ክርስቶስ እነዚህን ሁሉ ዓላማዎች ከብሉይ ኪዳን በላቀ መንገድ እንዴት ከፍጻሜ እንደሚያደርስ ጸሐፊው ያብራራል።
ጸሐፊው ክርስቶስ ከአሮን የዘር ሐረግ ከሚወለዱ አይሁዳውያን ሊቀ ካህናት እንዴት እንደሚበልጥ ከመግለጹ በፊት፥ በዕብራውያን 4፡14-16 ውስጥ የትምህርቱን ማጠቃለያ ይሰጠናል። ይህም ማጠቃለያ ክርስቶስ የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዓት ፍጻሜ እና በይሁዲነት ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ነገር የላቀ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ቀደም ሲል ጸሐፊው አምላክ የሆነው ኢየሱስ የሰውን ሥጋ ለብሶ በሰዎች መካከል ለመኖር በመቻሉ ሊቀ ካህናችን የመሆን ብቃት እንዳለው ገልጾአል። በዕብራውያን 4፡14-16፤ ጸሐፊው ሊቀ ካህናችን ስለሆነው ስለ ክርስቶስ ሦስት ቁልፍ ነገሮችን ይነግረናል፡
ሀ) ጸሐፊው ክርስቶስን «ትልቅ» ሊቀ ካህናት ይለዋል። ይህም ከአሮን ወይም ከማንኛውም ሊቀ ካህናት የሚበልጥ መሆኑን ያሳያል። ጸሐፊው ቀደም ሲል ክርስቶስ አምላክ መሆኑን ገልጾአል። በመሆኑም፥ ክርስቶስ እንደ አሮን ካለ ከማንኛውም ሊቀ ካህናት የበለጠ ነው።
ለ) ኢየሱስ በተሻለ ስፍራ (በሰማይ) ያገለግላል። ክርስቶስ በሰማይ ያለችው ቤተ መቅደስ ግልባጭ በሆነችው ምድራዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ አያገለግልም፡፡ ስለዚህ ጉዳይ በዕብራውያን ምዕራፍ 9 ውስጥ በስፋት እንመለከታለን።
ሐ) ኢየሱስ የሚራራ ሊቀ ካህናት ነው። ምንም እንኳን ኢየሱስ እምላክ ቢሆንም፥ እርሱ ፍጹም ሰውም ነው። ሰው እንደ መሆኑ መጠን፥ ዛሬ የሚያስቸግሩንን ነገሮች ሁሉ በሕይወት ዘመኑ ተጋፍጦ አይቷል። በየቀኑ ኃጢአት ለመሥራት እንደምንፈተን ሁሉ እርሱም ግላዊ ክብርን ለመሻት፥ የእግዚአብሔርን መንገድ ላለመታዘዝ፣ ከስደትና ከሞት ለመሸሽ የተፈተነባቸው ጊዜያት ነበሩ። ስለሆነም ሥጋ ለባሾች ለሆንን ለእኛ ሊራራልንና ሊረዳን ይችላል። በእኛና በክርስቶስ ሰብአዊነት መካከል ያለው ልዩነት አንድ ብቻ ነው። ይኸውም እኛ ኃጢአተኞች ስንሆን፥ እርሱ ኃጢአት ሠርቶ የማያውቅ መሆኑ ነው። ይህ እውነት ከእኛም ምላሽ ይጠብቃል። ጸሐፊው ከእኛ የሚጠበቁትን ሁለት ምላሾች ይገልጻል፡-
ሀ) «ጸንተን ሃይማኖታችንን እንጠብቅ!» ስደትን መፍራት ወይም የዓለም ነገሮች ከክርስቶስ ጋር ያለንን ጥብቅ እምነትና የቅርብ ግንኙነት እንዲሸረሽሩ መፍቀድ አይኖርብንም።
ለ) ሊቀ ካህናችን በችግሮቻችን እንዲረዳን መጠየቅ አለብን። እምነታችንን ለመካድ ወይም በኃጢአት ለመውደቅ በምንፈተንበት ጊዜ፥ ያለንበትን ሁኔታ ሊረዳ ወደሚችለው አምላክ በጸሎት መቅረብ ይኖርብናል። እርሱም ይረዳናል። በኃጢአት ለመውደቅ በምንፈተንበት ጊዜ፥ ክርስቶስ ችግራችንን በመረዳት ፈተናችንን እንድናሸንፍ ሊረዳን ቃል ገብቷል። ብቸኝነት ሲሰማን፥ በአገልግሎታችን ተስፋ ስንቆርጥ ወይም ምንም ዓይነት ችግር ሲደርስብን፥ እንደምንረዳ እናውቃለን። ምክንያቱም እንደ ሰው ያለንበትን ችግር የሚረዳና እንደ አምላክ ደግሞ ከችግሮቻችን ሁሉ የሚልቅ ሊቀ ካህናት አለንና።
እኛ ወደ እግዚአብሔር በምንቀርብበት አመለካከትና አይሁዶች ወደ እግዚአብሔር በሚቀርቡበት አመለካከት መካከል ትልቅ ልዩነት አለ። እግዚአብሔር ወደ ሲና ተራራ በቀረበ ጊዜ እጅግ ከመፍራታቸው የተነሣ እግዚአብሔር ከሙሴ ጋር ብቻ እንዲገናኝ ጠየቁት። አሁን ግን፥ ሙሉ ለሙሉ የኃጢአታችንን ይቅርታ ስላገኘን፥ በድፍረት ወደ እግዚአብሔር ልንቀርብ እንችላለን። ድፍረታችን የመነጨው ከራሳችን ላይሆን፥ ክርስቶስ በእኛ ምትክ ካቀረበው መሥዋዕት ነው። በልበ ሙሉነት ልንቀርብ የምንችልበት ምክንያት ደግሞ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠው አምላክ ምን ዓይነት እንደሆነና በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ምን እንዳደረገልን ስለምናውቅ ነው። ዙፋኑ በጸጋና በምሕረት የተሞላ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ይህንን ይመስላል። ልጆቹ ስለሆንን ይወደናል። ይህ ፍቅር ፍርሃታችንን አውጥቶ ይጥለዋል (1ኛ ዮሐ 4፡16-18)።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የእግዚአብሔርን እርዳታ በፈለግህ ጊዜ የተጋፈጥካቸውን ችግሮች ዘርዝር። ለ) ክርስቶስ አምላክም ሰውም፥ መለኮታዊ– ሰብአዊ ሊቀ ካህናችን መሆኑ እነዚህን ችግሮች በተጋፈጥክ ጊዜ ማበረታቻ የሆነህ እንዴት ነው? ሐ) ሊቀ ካህናትህ በችግር ጊዜህ እንዴት እንደረዳህ የሚያሳዩትን ምሳሌዎች ዘርዝር። አሁን ለእርዳታው እርሱን ለማመስገን ጊዜ ውሰድ።
አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ክርስቶስ ሊቀ ካህናት ነው በሚለው ትምህርት ግር እንደ ተሰኙ ጥርጥር የለውም። በሌሎች የአዲስ ኪዳን ክፍሎች እንዲህ ዓይነት ትምህርት አይገኝም። ክርስቶስ እንዴት ሊቀ ካህናት ሊሆን ይችላል? «እግዚአብሔር ሊቀ ካህናትን የሚመርጠው ከአሮን የዘር ሐረግ አልነበረምን?» ሲሉ መጠየቃቸው የማይቀር ነው። ክርስቶስ የይሁዳ ነገድ በመሆኑ፥ ሊቀ ካህናት የመሆን ብቃትን ከየት አገኘው? የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ የሊቀ ካህናትን አገልግሎት፥ ሊቀ ካህናት እንዴት እንደሚመረጡ፥ እንዲሁም የክርስቶስ የክህነት ሐረግ ከየት እንደሚመነጭ በመመርመር እነዚህን ጥያቄዎች ይመልሳል።
ሀ) የሊቀ ካህንነት መመዘኛዎች
- ሰው መሆን ያስፈልገዋል። «ከሰው ተመርጦ።» ከሊቀ ካህንነት ዐበይት መመዘኛዎች አንዱ የሚወክላቸውን ሰዎች መምሰሉ ነበር። ሰው እንደ መሆኑ መጠን፥ ሊቀ ካህናቱ የሰው ልጆች የሚጋፈጧቸውን ችግሮች ይረዳል። ኃጢአተኝነታቸውን፥ ነገሮችን በተሳሳተ መንገድ መገንዘባቸውን፥ ድካማቸውን ሁሉ ይረዳል። ሊቀ ካህናቱ እንዲህ ዓይነቱን ደካማ ግለሰቦች ወደ እግዚአብሔር ያቀርባቸዋል። በመሆኑም፥ ለሰዎች ሊቀ ካህናት ለመሆን ክርስቶስ ሰው መሆን ያስፈልገው ነበር። እግዚአብሔር ሰው መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ሰው ሆኖ ስላላየው፥ ሊቀ ካህናት ሊሆን አይችልም። እንዲሁም ደግሞ የሰውን ጥያቄዎችና ችግሮች ወደ ተቀደሰው አምላክ የሚያቀርብ አማላጅም ሊሆን አይችልም።
ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስ ክርስቶስ ከሌሎች ሊቀ ካህናት ሁሉ እንደሚበልጥ ከሚያሳዩት መረጃዎች አንዱ ሌሎች ሊቀ ካህናት እግዚአብሔርና ሰውን ከማገልገላቸው በፊት ከሚያከናውኑት ተግባር የመነጨ ነው። ሰዎችን ለመወከል በእግዚአብሔር ፊት ከመቆማቸው በፊት፥ ሊቀ ካህናት መጀመሪያ ስለ ራሳቸው ኃጢአት መሥዋዕት በማቅረብ ራሳቸውን ማንጻት ያስፈልጋቸው ነበር። ከአሮን የዘር ሐረግ የመጡ ሊቀ ካህናት ራሳቸው ኃጢአተኞች በመሆናቸው፥ በቅድስናቸው ሊመኩ ወይም ከሌሎች እንበልጣለን ብለው ሊያስቡ አይችሉም ነበር። ክርስቶስ ግን ኃጢአት ያልነካው በመሆኑ፥ ለራሱ ኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ ሳያስፈልገው የሌሎችን ኃጢአት በማስወገዱ ላይ አትኩሮአል።
- «ሊቀ ካህናት ሁሉ ስለ ኃጢአት መባንና መሥዋዕት ሊያቀርብ ከሰው ተመርጦ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ ስለ ሰው ይሾማልና» ማንም ሰው በድንገት ብድግ ብሎ፥ «እኔ ካህን መሆን እፈልጋለሁ» ሊል አይችልም። የተወሰኑ የሕዝብ ቡድኖችም፥ «ይህ ሰው ካህን እንዲሆን መርጠነዋል» ሊሉ አይችሉም። ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ሰዎችን ማን መወከል እንዳለበት የሚመርጠው እራሱ እግዚአብሔር ነው።
ለአይሁዶች፥ እሮን የክህነትን ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሟላ ግልጽ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን አሮንን እንደ መረጠና ለአይሁዶች ሊቀ ካህናት እንዳደረገው ግልጽ ነው (ዘጸ. 28፡1-5)። ነገር ግን ኢየሱስ እነዚህን ሁለት የብቃት መመዘኛዎች ያሟላ ሊቀ ካህናት የሆነው እንዴት ነበር? ጸሐፊው ለዚህ ጥያቄ ምላሽ የሰጠው ከብሉይ ኪዳንና ከኢየሱስ ሕይወት ማብራሪያ በማቅረብ ነበር።
ሀ) ኢየሱስ ሊቀ ካህናት ሊሆን የቻለው ከአሮን የዘር ሐረግ በመወለዱ ምክንያት ሳይሆን፥ እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዐት ነበር። በመዝሙር 110፡4 ላይ እግዚአብሔር ለመሢሑ እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዐተ ሊቀ ካህናት መሆኑን ተናግሯል። (ጸሐፊው ይህንን ጉዳይ በምዕራፍ 7 ውስጥ በስፋት ያብራራዋል።)
ለ) ክርስቶስ ሊቀ ካህናችን ሊሆን የቻለው ሰው እንደ መሆኑ መጠን፥ የሰው ልጆች በምድር ላይ የሚጋፈጧቸውን መከራዎችና ሥቃዮች ሁሉ ስለተቀበለ ነው። ጸሐፊው ኢየሱስ በጌቴሴማኒ በአትክልት ስፍራ ወደ እግዚአብሔር የጸለየበትን ሁኔታ የሚያመለክት በሚመስል መልክ ኢየሱስ ልክ እንደ እኛ በመከራ ዝሎ በታላቅ ጩኸትና በእንባ ወደ እግዚአብሔር እንደ ጸለየ ይናገራል። ጸሐፊው ይህንን የኢየሱስ የመከራና የሞት ጊዜ የተረዳበት መንገድ አስገራሚ ነው። የዕብራውያን መልእክት ጻሐፊ የኢየሱስ ጸሎት እንደ ተሰማ ይናገራል። ነገር ግን ጸሎቱ ቢሰማም እንኳን ኢየሱስ መጀመሪያ መሞት ያስፈልገው ነበር። ክርስቶስ እግዚአብሔር ከሞት እንዲያድነው ቢጸልይም፥ «የእኔ ፈቃድ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም» በማለት ለእግዚአብሔር ፈቃድ ራሱን አስገዝቷል (ሉቃስ 22፡41-44)። ይህም እግዚአብሔር ከመከራ እንዲያድነን መጸለይንና ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር በዚሁ መከራ ውስጥ እንድናልፍ የሚያደርግበትን ሁኔታ ያካትታል። በመከራ ውስጥ ማለፋችን ፈቃዱ በመሆኑ ስለሆነም የክርስቶስን አመለካከት በመያዝ በማንፈልገው ሁኔታ ውስጥ እንኳ ቢሆን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ራሳችንን ማስገዛት እና መታዘዝ ይኖርብናል።
ክርስቶስ ሁለት ጠቃሚ ነገሮችን ተምሯል። እነዚህም ኢየሱስ ሊቀ ካህናችን ይሆን ዘንድ የበለጠ ብቃት ያላበሱት ከመሆናቸውም በላይ፥ እኛም ችግሮችና ስደት በሚደርሱብን ጊዜ ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት እንዳለብን በምሳሌነት እንዲያሳየን አስችለውታል። በመጀመሪያ፥ እግዚአብሔርን በመፍራት ታዟል። በሌላ አገላለጽ፥ ክርስቶስ የራሱ ፈቃድ እንዲፈጸም የግድ አላለም። ወይም ደግሞ ጸሎቱ እርሱ በፈለገው መንገድ እንዲመለስ አልጠየቀም። ነገር ግን ኢየሱስ ጥያቄውን ለእግዚአብሔር ካቀረበ በኋላ፥ በእግዚአብሔር ፈቃድና መንገድ ራሱን አስገዝቷል። ለኢየሱስ የእግዚአብሔር ፈቃድ ከመከራ ማምለጡ ሳይሆን የመስቀልን ሞት መሞቱ ነበር። ለእኛም ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ፈቃድ ስደትን መጋፈጣችን ሊሆን ይችላል። ሁለተኛ፥ ክርስቶስ ከተቀበለው መከራ፥ «መታዘዝን ስለተማረ» ሊቀ ካህናችን ለመሆን ብቁ ሆኗል። ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልዩ ልጁ ቢሆንም፥ እግዚአብሔር መከራ እንዳይቀበል አላደረገም። በተመሳሳይ ሁኔታ እኛም ልጆቹ ብንሆንም፥ መከራ እንዳንቀበል አይሸሽገንም። ምክንያቱም በነገር ሁሉ እግዚአብሔርን መታዘዝን የምንማረው በመከራ ውስጥ ነውና። ምንም እንኳን ክርስቶስ ሁልጊዜም ኃጢአት እንደሌለው ፍጹም የእግዚአብሔር ልጅ አብን ሲታዘዝ ቢኖርም፥ ከመስቀል ሞቱ በፊት እግዚአብሔርን መታዘዝ ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍልና ሥቃይ የሞላበት እንደሆነ አጋጥሞት አያውቅም ነበር። ክርስቶስ ፍጹም የሆነው ወይም ሊቀ ካህናትና የሕይወት ራስ (የድነት ራስ) ሊሆን የበቃው በመከራው አማካኝነት ነበር። እኛም በእምነታችን እየበሰልን የምንሄደው በመከራ እማካኝነት ነው። ጸሐፊው የዘላለምን ድነት (ደኅንነት) የሚያገኙት እግዚአብሔርን የሚታዘዙ ብቻ መሆናቸውን እንደሚገልጽ አጢን።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የእግዚአብሔር ልጅ በመሆንህ ምክንያት የተጋፈጥካቸው አንዳንድ መከራዎች ምንድን ናቸው? ለ) እግዚአብሔር በዚህ ጊዜ እነዚህን ሁለት ባሕርያት ከአንተ የጠየቀው እንዴት ነበር? ሐ) ለእግዚአብሔር መታዘዝና መገዛት እጅግ አስፈላጊ የሆኑት ለምንድን ነው? መ) ስለ እነዚህ ሁለት ባሕርያት ቤተ ክርስቲያን አጥብቃ የማታስተምረው ለምንድን ነው? ሠ) የክርስቶስ ጸሎት እንዴት እንደ ተሰማና ዳሩ ግን እርሱ በፈለገበት መንገድ ምላሽ እንዳላገኝ አብራራ። የእኛ ጸሎቶች ብዙውን ጊዜ በእግዚአብሔር ዘንድ ተሰሚነት ያገኘው እኛ የምንፈልጋቸው ምላሾች የማናገኘው እንዴት ነው? ከዚህ ስለ ጸሎት ምን እንማራለን?
አሮንና ኢየሱስ ሁለቱም የሰው ልጆች ከመሆናቸውም በላይ በእግዚአብሔር የተመረጡ በመሆናቸው፥ እነዚህን ሁለት የሊቀ ካህንነት መመዘኛዎች ያሟላሉ። ነገር ግን ኢየሱስ ከአሮን የበለጠ ሊቀ ካህናት ከሚሆንባቸው ምክንያቶች አንዱ ኢየሱስ እንደ አሮን ሰው ብቻ ሳይሆን መለኮታዊና ኃጢአት የሌለው የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑ ነው።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)