በእምነት ስላለመጽናት የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (ዕብ. 5፡11-6፡20)

ይህ ራስን ለእግዚአብሔር ለማስገዛትና ለመታዘዝ ትምህርት ጸሐፊው እንደገና ቆም ብሎ በክርስቶስ ላይ የነበራቸውን እምነት ለመተው እያሰቡ ላሉት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያ እንዲሰነዝር ገፋፋው። ይህ በዕብራውያን መልእክት ውስጥ ላሉት የማስጠንቀቂያ ምንባቦች ሁሉ ረጅሙ ሲሆን፥ በአራት ዐበይት ክፍሎች ሊከፈል ይችላል።

ሀ) ጸሐፊው በዕብራውያን 5፡11-14 አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በእምነታቸው ባለማደጋቸው ማዘኑን ይገልጻል። በክርስትና እምነታቸው የቆዩ በመሆናቸው የክርስትናን መሠረታዊ ትምህርቶች ከመከታተል ይልቅ፥ እነርሱ እራሳቸው አዳዲስ አማኞችን ማስተማር ይገባቸው ነበር። ጸሐፊው በአዲስ አማኝነታቸው ጊዜ ሊማሩአቸው የሚገባቸውን ትምህርቶች ደግሞ ለማስተማር መገደዱን ያስረዳል። አይሁዳውያን አማኞች የእግዚአብሔርን መርሆች ተግባራዊ ሊያደርጉ ከሚገዟቸው መንገዶች አንዱ ከቀድሞው ሃይማኖታዊ ልምምዳቸው ጋር የነበራቸውን ግንኙነትና ክርስቶስ እግዚአብሔርን የሚያመልኩበትን መንገድ እንዴት እንደ ለወጠ መረዳትን የሚጨምር ነበር። አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ወደ ይሁዲነት ለመመለስ ማሰባቸው የእግዚአብሔር ቃል አስተሳሰባቸውን በጥልቀት እንዲቀይር አለመፍቀዳቸውን ያሳያል።

ጸሐፊው የሚፈልገው የብስለት ምልክት ምንድን ነው? ብስለት የሚገለጠው አስቸጋሪ እውነትን በመረዳት ሳይሆን፥ የዕብራውያን ክርስቲያኖች እምነታቸውን በጽድቅ መንገድ በመግለጣቸው ነበር። በጽድቅ በመመላለስ በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት ጠበቅ አድርገው ሊይዙና ምንም ያህል ዋጋ ቢያስከፍሉአቸውም እግዚአብሔርን በመታዘዝ ሊኖሩ ይገባቸው ነበር። እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ መኖር ማለት ደግሞ የእግዚአብሔር እውነት በሁኔታዎች ሁሉ ውስጥ አኗኗራችንን እንደሚለውጥ ማሳየትን ይጠይቃል። ጸሐፊው ይህንን ሂደት ሲገልጽ «ክፉውንና መልካሙን ለመለየት ብስለታቸው የለመደ ልቦና ላላቸው» ብሏል። መንፈሳዊ ብስለት ያለው ሰው ሕይወቱን በሙሉ (ባህሪውን፥ ቤተሰባዊ ሕይወቱን፥ ሥራውን፥ በማኅበረሰብ ውስጥ ያለውን ግንኙነት፥ ወዘተ…) መጽሐፍ ቅዱስ በሚያስተምረው መሠረት ይገመግማል። ብስለት ያለው አማኝ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘው፥ እንዲሁም ለራሱ ግላዊ መንፈሳዊ እድገት የሚበጀውን ያውቃል። በእነዚህ የሕይወት ክፍሎቹ ሁሉ ሌሎችን የሚያንጽ የእግዚአብሔር አገልጋይ ሆኖ እንዴት ሊመላለስ እንደሚችልም ያውቃል። አለዚያም የእግዚአብሔር ቃል በሚሰጣቸው መርሆች መሠረት ሕይወቱን ይመራል። ጸሐፊው ይህ ቀላል ተግባር ነው አላለም። ነገር ግን ሥልጠናና ትምህርትን ይጠይቃል፡፡

የውይይት ጥይቄ፡- ሀ) በመልካሙና በክፉ መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት ትችል ዘንድ ራስህን በጽድቅ የምታሠለጥንባቸውን መንገዶች ዘርዝር። እንደ ባህሪ፥ ቤተሰብ፥ ቤተ ክርስቲያን፥ ሥራና ማኅበረሰብ ያሉትን የሕይወትህን ክፍሎች ገምግምና በመንፈሳዊ መረዳትና ተግባር ያደግህባቸውን መንገዶች ዘርዝር። ለ) በዚህ ረገድ አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያን አባሎች «በሳሎች» ተብለው ሊመደቡ የሚችሉ ይመስልሃል? ካልሆነ፥ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ያልበሰሉት ለምንድን ነው? ቤተ ክርስቲያንን እነዚህ ሰዎች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉ ለማገዝ ምን ልታደርግ ትችላለች?

ለ) በዕብራውያን 6፡1-3፥ ጸሐፊው የክርስቶስን የመጀመሪያ ትምህርት የእግዚአብሔርን ቃል መሠረታዊ እውነቶች ይዘረዝራል። እነዚህ የአይሁዳውያን ክርስቲያኖች የሃይማኖት መሠረቶች ሲሆኑ፥ በሕይወታቸው ከእነዚህ አልፈው ማደግ ያስፈልጋቸው ነበር። ምሁራን እነዚህ ስድስት ነገሮች ከይሁዲነት ወይም ከክርስትና ትምህርቶች በመምጣታቸው ላይ ይከራከራሉ። ምናልባት ሁለቱም ሃይማኖቶች እነዚህን ነገሮች መሠረታዊ ትምህርቶቻቸው አድርገው ሳይወስዱ አይቀሩም። እነዚህ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ምናልባትም ከአሕዛብ ክርስቲያኖች በላይ እነዚህ ነገሮች ከሁሉም በላይ አስፈላጊዎች እንደሆኑ ላያስቡ አልቀሩም። ይህም ስለ ክርስቶስ በሚናገሩ እውነቶች ሥር ሰድደው እንዳይመሠረቱ እና ለእርሱ እንዳይኖሩ አድርጓቸው ነበር።

  1. ከሞተ ሥራ ንስሐ፡- ብሉይ ኪዳን (2ኛ ዜና 6፡36-39። ኢሳ. 30፡15፥ 9፣ ኤር. 15፡9፤ ሕዝ. 18፡30) እና አዲስ ኪዳን የንስሐ አስፈላጊነትን ያስተምራሉ። መጥምቁ ዮሐንስ (ማቴ. 3፡1-2)፣ ኢየሱስ (ማቴ. 4፡17)፣ እንዲሁም ጴጥሮስ (የሐዋ. 2፡38) ሁሉም ንስሐ አስፈላጊ መሆኑን አስተምረዋል። አንድ ሰው ወደ ክርስቶስ በሚመጣበት ጊዜ በመጀመሪያ ከሚማራቸው ነገሮች አንዱ ንስሐ ነው። ሰዎች ወደ ክርስቶስ በሚመጡበት ጊዜ ኃጢአተኞችና በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ ላይ መሆናቸውን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። ከዐመፀኝነት መንገዳቸው ተመልሰው እግዚአብሔርን ለመታዘዝ መፍቀድ ይኖርባቸዋል። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንስሐ ሁልጊዜም የሚጀምረው ቅዱሱን አምላክ ደስ የሚያሰኝ ተግባር በመፈጸም ላይ ያለን ኃጢአኞች የመሆናችን ምክንያት በመገንዘብ ነው።

ይህም ወደ ኑዛዜ፥ ማለትም በእግዚአብሔር ላይ እያመጽን መሆናችንን ወደምንገነዘብበት ደረጃ ይመራናል። በዚህ ጊዜ ባህሪያችን ይለወጥና ተግባራችንም እንዲሁ ይለወጣል። ከዚያም እንደ ቀድሞው መመላለሳችን ያከትማል። ምናልባትም የሞተ ሥራ (ወደ ሞት የሚመራ) የሚያመለክተው አይሁዶች በሰናይ ምግባራት የእግዚአብሔርን ይቅርታ ማግኘት መሞከራቸውንና የኋላ ኋላ ግን መንፈሳዊ ሙታን መሆናቸውን ይሆናል። ነገር ግን ይህ አሳብ ከተገለጸው የእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ፊት ለፊት መላተምን ሊያመለክት ይችላል። እነዚህም ነገሮች መንፈሳዊ ሙታኖች መሆናችንን ያሳያሉ።

  1. በእግዚአብሔር ማመን፡- ጸሐፊው በክርስቶስ ማመን የሚለውን ሐረግ አለመጠቀሙ ብዙ ሰዎች እነዚህ ትምህርቶች የብሉይ ኪዳን እንጂ የአዲስ ኪዳን ይዘት የላቸውም ብለው እንዲደመድሙ አድርጓቸዋል። ነገር ግን የዕብራውያን መልእክት ጻሐፊ በእግዚአብሔር ስለማመንና በክርስቶስ ስለማመን ትኩረት ሰጥቶ እንደሚያብራራ መገንዘቡ ጠቃሚ ነው (ዕብ 11)። እምነት የእግዚአብሔርን መኖር ወይም የክርስቶስን በመስቀል ላይ መሞት የምንገነዘብበት አእምሮአዊ እውቀት ብቻ አይደለም። ነገር ግን እውነተኛ እምነት እውነትን ማወቅንና ይህንኑ እውነት በሚያንጸባርቅ መልኩ መኖርን ያመለክታል። የሰውን ሕይወት የሚለውጠው እውነት ነው። የማይቻል፥ የማይመችና ስደትን የሚጋብዝ በሚሆንበት ጊዜ ሳይቀር ሰው ለእውነት ይኖራል።
  2. የጥምቀት ትምህርት፡- ጥምቀት የአይሁዶችም ሆነ የክርስቲያኖች እምነት መሠረታዊ ክፍል ነው። አይሁዶች በየቀኑ ልዩ በዐላት ባሉባቸው ጊዜያት ሁሉ ሥርዐታዊ በውኃ የመታጠብ ተግባር ያከናውናሉ። (ጥምቀት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ በነጠላ ሳይሆን በብዙ ቁጥር እንደ ተገለጠ መመልከቱ ጠቃሚ ነው።)

መጥምቁ ዮሐንስ ጥምቀትን የሰው ሕይወት ከኃጢአት መንጻቱንና ንስሐ መግባቱን የሚያመለክት ውጫዊ ተግባር አድርጎ ተጠቅሞአል። ክርስቲያኖችም ስለ ጥምቀት የመጥምቁ ዮሐንስን የመሰለ አስተሳሰብ ነበራቸው። ይህም አንድ ሰው በኢየሱስ በሚያምንበት ጊዜ ኃጢአቶቹ ሁሉ መታጠብን የሚያመለክት በአንድ ጊዜ የሚፈጸም ተምሳሌታዊ ድርጊት መሆኑን ነው (ቲቶ 3፡5)።

  1. እጆችን መጫን፡ አይሁዶችና ክርስቲያኖች ይህንን ልምምድ ያካሂዱ ነበር። አንዳንድ ጊዜ ይህ ጥምቀትን ተከትሎ የሚከናወን ሲሆን፥ በመንፈስ ቅዱስ መሞላትና ወይም መንፈሳዊ ስጦታ መቀበልን ያስከትል ነበር (የሐዋ. 8፡14-17፤ 19፡4-7)። (ማስታወሻ፡ ምንም እንኳ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ሐዋርያት እጆቻቸውን በሰዎች ላይ በመጫን እንዴት መንፈስ ቅዱስን እንዲቀበሉና የጸጋ ስጦታዎችን እንዲያገኙ እንዳደረጉ በብዙ ስፍራዎች ላይ ቢጠቅስም፥ እግዚአብሔር ለሰዎች ስጦታዎችን የሚሰጥበት ተለምዶአዊው መንገድ ይኸው እንደሆነ አያብራራም። በሰዎች ላይ እጅ ሳይጫን መንፈስ ቅዱስ የወረደባቸው ብዙ ጊዜያት አሉ። ሰዎች መንፈስ ቅዱስን ወይም መንፈሳዊ ስጦታዎችን እንዲቀበሉ እጆቻችንን እንድንጭንባቸውም አልተነገረንም ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው በክርስቶስ በሚያምንበት ጊዜ እግዚአብሔር በቀጥታ ያለምንም የእጅ መጫን መንፈስ ቅዱስንና መንፈሳዊ ስጦታዎችን ያጎናጽፈዋል።)

በሌሎች ጊዜያት፥ ሰዎች ለመሪነት አገልግሎት ወይም ለሌሎች የቤተ ክርስቲያን ተግባራት በሚለዩበት ጊዜ እጅ ተጭኖ ይጸለይላቸዋል (የሐዋ. 6፡6፤ 1ኛ ጢሞ. 5፡22፤ 2ኛ ጢሞ. 1፡6)። ለታመሙት ሰዎችም አገልጋዮች እጃቸውን ጭነው ይጻልዩላቸው ነበር (ማር. 6፡5፤ የሐዋ. 28፡8)። በረከትን ለማውረድም እንዲሁ እጆችን የመጫን ተግባር ይከናወናል (ማቴ. 19፡13-15)። በይሁዲነትም ሆነ በክርስትና ይህ ተግባር የተለያዩ ዓላማዎች የነበሩት ቢሆንም፥ እጅን መጫን የመጀመሪያ እውነት በመሆኑ አማኞች ከዚያ እልፍ ብለው መሄድ ይኖርባቸው ነበር።

  1. የሙታን ትንሣኤ፡- አብዛኞቹ አይሁዶችና ሁሉም ክርስቲያኖች ከሞት እንደሚነሡ በመሠረታዊነት ያምኑ ነበር። ይህ በተለይም የትንሣኤ ሙታንን መኖርና አማኞችም በሚሞቱበት ጊዜ ከሞት እንደሚነሡ በማመልከት የክርስቶስን ከሞት መነሣት በመረጃነት በሚጠቅሰው ክርስትና ማዕከላዊ ትምህርት ነው። ጳውሎስ ትንሣኤ፥ በተለይም የኢየሱስ ትንሳኤ ከሌለ፥ እምነታችን ከንቱ ነው ብሏል (1ኛ ቆሮ. 15፡12-14)።
  2. ዘላለማዊ ፍርድ፡- አይሁዶችም ሆኑ ክስቲያኖች ከሞት በኋላ እግዚአብሔር በሙታንና በሕያዋን ላይ ፍርዱን በመስጠት በምድር ላይ ባከናወናቸው ተግባራት ሳቢያ ቅጣቶችንና ሽልማቶችን የሚሰጥበት ቀን እንደሚመጣ ያምናሉ።

ጸሐፊው እነዚህ እውነቶች አስፈላጊዎች አይደሉም አላለም። እነዚህ ስድስት ነገሮች አስፈላጊዎች ናቸው። ይሁንና አይሁዳውያን አማኞች ከእነዚህ መሠረታዊ እውነቶች (ወተት) ፈቀቅ ብለው ወደ ጠለቁ እውነቶች ሊያድጉና በሳል አማኞች ሊሆኑ ይገባ ነበር። ወደ አንደኛ ክፍል ገብቶ ፊደል መቁጠር ትምህርትን ለመጀመር አስፈላጊ ቢሆንም፥ እዚያው አንደኛ ክፍል ውስጥ «ሀ ሁ»ን ብቻ እየተማሩ መኖሩ ሞኝነትና አሰልቺም ነው። እንደዚሁም ደግሞ ወደ ጠለቁት እውቀቶች ሳይደርሱ ሁልጊዜም አንድ ዓይነት እውነቶችን መደጋገሙ ለክርስቲያኖች ሞኝነት ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ አብዛኛዎች አማኞች ዘመናቸውን የሚጨርሱት የክርስትናን ሀ፥ሁ፥ በመማር ነው። ይህም ወደ ጠለቁ ትምህርቶች ሳይደርሱ እንደ ድነት (ደኅንነት)፥ ክርስቲያን አኗኗር፥ ወዘተ… ባሉት ነገሮች ላይ ማተኮር ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉት አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚታየው ትልቁ ችግር እሑድ እሑድ ተከታታይነት ያለው ትምህርት ስለማይሰጥ እና ባመዛኙ ተጋባዥ ሰባኪዎች እንዲያገለግሉ ስለሚያደርጉ፥ ሁልጊዜም የሚሰጠው መሠረታዊ ትምህርት ይሆናል። ይህም አማኞች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ጠለቅ ብለው እንዲያድጉ አያደርጋቸውም። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እንደ ዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ በእነዚህ መሠረታዊ እውነቶች ላይ ሌሎች ጠንካራ ትምህርቶችን እየገነቡ ምእመኖቻቸውን ወደ ጠለቁ እውነቶች ሊወስዷቸው ይገባል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አማኞች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉና የጠለቁ እውነቶች ከሕይወታቸው ጋር እንዲያዛምዱ ከማገዝ ይልቅ ብዙውን ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመሠረታዊ ትምህርቶች ላይ የምናተኩርባቸውን ሁኔታዎች የሚያሳዩ ምሳሌዎች ስጥ። ለ) ላለፉት 6 ወራት የሰማሃቸውን ስብከቶች አስታውስ፤ ከእነዚህ ስብከቶች መካከል መሠረታዊ የሆኑትና ለበሳል ክርስቲያኖች የተዘጋጁ ጥልቅ እውነቶች የትኞቹ ናቸው? ሐ) የጠለቁ እውነቶች የማይሰበኩ ከሆነ፥ ቤተ ክርስቲያን በሳል አማኞች ወደ ጠለቀ እውነት እንዲዘልቁ ልታደርግ የምትችልበት ሌላ ምን አማራጭ ይኖራታል?

ሐ) ዕብራውያን 6፡4-6 ከእውነት ተመልሰው ወደ ይሁዲነትም ወይም ወደ ቀድሞው አኗኗራቸው የሚመለሱ አማኞች ጠንካራ ማስጠንቀቂያዎችን ይሰጣል። ይህ ክፍል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመተርጎም እጅግ አስቸጋሪ ከሆኑት ምንባቦች አንዱ ነው። ቃላቱ ራሳቸው ለመረዳት የሚያስቸግሩ አይደሉም። ነገር ግን ይህ ምንባብ ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር የሚቃረን አሳብ የሚያስተላልፍ ስለሚመስል፥ ከተቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ አሳብ ጋር ማስታረቁ አስቸጋሪ ይሆናል። በዚህ ምንባብ ላይ የተለያዩ ምሁራን የሚያቀርቡአቸውን አመለካከቶች ለመረዳት እንዲያግዘን በመጀመሪያ አንድ ሰው እምነቱን በመካድ ደኅንነቱን ሊያጣ ስለሚችልበት ሁኔታ ምሁራን የሚያቀርቡአቸውን ሦስት ዓይነት አመለካከቶች መረዳት ጠቃሚ ይሆናል።

  1. እውነተኛ ድነት (ደኅንነት) ያገኘ ሰው ደኅንነቱን ሊያጣ እንደማይችል የሚያስተምሩ ምሁራን። በዮሐንስ 10፡27-30 ኢየሱስ ከአብ የተቀበላቸውን አማኞች ሁሉ እንደሚጠብቅ የተስፋ ቃል ሰጥቷል። ከእነዚህም አንዱ እንኳን አይጠፋም። ማንም ከኢየሱስ እጆች ሊነጥቃቸውና ሊያጠፋቸው አይችልም፡፡ በዚህና በሌሎችም ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ በመመሥረት (ሮሜ 8፡28-39)፣ ብዙ ክርስቲያኖች አንድ ሰው ከዳነ በኋላ ምንጊዜም ደኅንነቱን ሊያጣ አይችልም ብለው ያስተምራሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር ቃላዊ እምነትን ሳይሆን የልብን እምነት እንደሚያይ እነዚህ አማኞች አጽንኦት ሰጥተው ያስተምራሉ። ስለሆነም የአንድን ሰው ልብ ማወቅ ስለማይቻል፥ የአንድን ሰው መዳን ወይም አለመዳን ማወቅ አይቻልም። አንድ ሰው መዳን አለመዳኑን ማወቅ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ በሕይወቱ ውስጥ ለውጦች (ፍሬዎች) መኖር አለመኖራቸውን መመልከትና በእምነቱ እስከ መጨረሻው ድረስ መጽናቱን ማረጋገጥ ነው። የዚህ አመለካከት አራማጆች አንድ ሰው እምነቱን ከካደ ቀድሞውንም አልዳነም ነበር ይላሉ። ይህን አቋም የሚይዙ ክርስቲያኖች አማኞች ወደ ኋላ እንዳይመለሱና እምነታቸውን እንዳይክዱ የሚያስጠነቅቁትን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ለመረዳት ይቸገራሉ። የዚህ አመለካከት አራማጆች በዕብራውያን 6፡4-6 ሦስት አተረጓጎሞችን ያቀርባሉ።

ሀ) ይህ ምንባብ ከእውነተኛ ክርስቲያኖች ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱትንና እውነተኞቹ አማኞች የሚያገኟቸውን ብዙ በረከቶች የሚካፈሉትን ሰዎች ያመለክታል። እነዚህ ሰዎች ግን በልባቸው በክርስቶስ ስላላመኑ ክርስቲያኖች አልነበሩም። ይህን አመለካከት የሚያራምዱት ሰዎች አይሁዳውያን ክርስቲያኖች አማኞች መሆናቸውን የሚያመለክቱትን ዕረፍተ ነገሮች ለማብራራት ይቸገራሉ።

ለ) ጸሐፊው ያቀረበው ሊሆን የማይችል መላምታዊ ሁኔታ ነው። ይህንን ያደረገው አይሁዳውያን አማኞች እምነታቸውን እንዳይክዱ ለማስፈራራት ነው። ነገር ግን በዕብራውያን 6፡9 እንደተመለከተው፥ ጸሐፊው እነዚህ አማኞች እውነተኛ አማኞችና ደኅንነታቸውንም ሊያጡ የማይችሉ መሆናቸውን ገልጾአል። ይህ የማስጠንቀቂያ ክፍል መሆኑና መላምታዊ አሳቦችን ለማቅረብ የማይመች ክፍል መሆኑ፥ ይህን አቋም ውድቅ ያደርገዋል።

ሐ) ሌሎች ደግሞ ድነት (ደኅንነት) ከተለያዩ የእይታ መነጽሮች አንጻር ሊታይ ይችላል ይላሉ። ከእግዚአብሔር የእይታ መነጽር ሲታይ፥ እርሱ የእያንዳንዱን ሰው ልብ ስለሚያይና የእምነቱን እውነተኛነት ስለሚያውቅ የዳነ ሰው ደኅንነቱን ሊያጣ አይችልም ይላሉ። ከሰው የእይታ መነጽር ሲታይ ግን የሰውን ልብ ማየት ስለማንችል እምነቱ እውነተኛ ወይም የውሸት መሆኑን ልናረጋግጥ አንችልም ብለው ያስተምራሉ። እምነቱ የአዕምሮ እውቀት ብቻ የሆነበት ሰው በቀላሉ ከእምነቱ ፈቀቅ ሊል ይችላል። የራሳችንንም ሆነ የሌሎችን ሰዎችን ልብ ለማየት ስለማንችል፥ የሰዎችን ድነት (ደኅንነት) በእርግጠኝነት ለመናገር አንችልም። በመሆኑም የዕብራውያን ጸሐፊ ሕይወታችንን አጥብቀን እንድንጠብቅ ያስጠነቅቀናል። እውነተኛ እምነት እንዳለን ወይም እንደሌለን ከምናውቅባቸው ነገሮች አንዱ እስክንሞት ድረስ በእምነት መጽናታችን ነው። እምነታችንን ከካድን፥ እውነተኛ እምነት እንዳልነበረን ይታወቃል። በዕብራውያን 6፡4-6 የተጠቀሱት አምስት በረከቶች በክርስቶስ ላይ እውነተኛ እምነት ወይም የአእምሮ እውቀት ብቻ ካላቸው ሰዎች ሕይወት ውስጥ ሊገለጽ ይችላሉ። ጸሐፊው አይሁዳውያኑ እማኞች በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት አጥብቀው እንዲይዙ፥ ካልሆነም ቀድሞውንም እውነተኛ አማኞች እንዳልሆኑና የእግዚአብሔር ፍርድ እንደሚደርስባቸው እያስጠነቀቁ ነው ሲሉ ያስተምራሉ።

  1. ሌሎች ክርስቲያኖች አንድ ሰው ትልቅ ኃጢአት ከሠራና በተለይም እምነቱን ከካደ ደኅንነቱን ሊያጣ እንደሚችል ይናገራሉ። እነዚህ ሰዎች ከእምነታቸው የወደቁትን ግለሰቦች እንደሚያውቁም ይጠቅሳሉ። እንደ ዕብራውያን 6፡4-6 ያሉትን ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች በመጥቀስ፥ እንድ አማኝ እምነቱን ሊያጣ (ሊተው) እንደሚችል ያስተምራሉ። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከፍርሃት የተነሣ እምነታቸውን የሚክዱ አማኞች እንዳሉ ለመግለጽ የሚያስተምሩ መሆናቸውን ይናገራሉ። አንድ ሰው ደኅንነቱን ሊያጣ እንደሚችል እና ንስሐ ገብቶ እንደገና ሊያምን እንደሚችል ያስተምራሉ። እነዚህ ሰዎች አንድ አማኝ እምነቱን ከካደ በኋላ በንስሐ ሊመለስ እንደማይችል የሚያመለክተውን የዕብራውያን 6፡6 አሳብ ለማብራራት ይቸገራሉ። እንዲሁም፥ በአዲስ ኪዳን ውስጥ አንድ ሰው በክርስቶስ አምኖ ከካደ በኋላ የዘላለም ሕይወት እንዳለውና ከዘላለማዊ ፍርድ እንደዳነ የሚያመለክቱትን ምንባቦች ለመረዳት ይቸገራሉ (ዮሐ. 6፡39-40፤ 10፡27-29፤ 1ኛ ጴጥ. 1፡5)።
  2. ሌሎች አማኞች ከመጀመሪያው ቡድን ጋር የሚመሳሰል አቋም ይይዛሉ። እነዚህ ሰዎች አንድ ሰው በክርስቶስ ላይ እውነተኛ እምነት ካለው ደኅንነቱን ሊያጣና ወደ ሲኦል ሊወርድ እንደማይችል ያስተምራሉ። የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆኑ እግዚአብሔር ልጆቹን ሊክድ አይችልም። ነገር ግን እነዚህ ክርስቲያኖች አንድ አማኝ በእግዚአብሔር ላይ ሊያምጽ እንደሚችል ያስተምራሉ። ይህንንም በሚያደርግበት ጊዜ ድነትን (ደኅንነትን) ሳይሆን፥ ዘላለማዊውን የክብርና የበረከት ሽልማት ያጣል። በትልቅ ኃጢአት ውስጥ ወድቆ ንስሐ ያልገባ አማኝ ወይም ደግሞ ክርስቶስን የሚክድ ክርስቲያን ወደ መንግሥተ ሰማይ ይገባል። ነገር ግን በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ የመግዛት ሥልጣን አይኖረውም። ከእሣት እንደሚድን ግን ይድናል (1ኛ ቆሮ. 3፡12-15)። ይህ አመለካከት ይህ ምንባብ ጸሐፊው እውነተኛ ክርስቲያኖችን እየገለጸ መሆኑን ይገልጻል። ነገር ግን ጸሐፊው አጥብቆ የሚያስጠነቅቃቸው ክርስቲያኖች ከክርስቶስ ከተመለሱ ሰማያዊውን በረከት (ሽልማት) እንደሚያጡ ነው። እነዚህ አማኞች ክርስቲያኖች የሚያጡት ሽልማትን ሳይሆን ድነትን (ደኅንነትን) እንደሆነ የሚያመለክቱትን ጥቅሶች ለማብራራት ይቸገራሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ዕብ. 6፡4-6 እንደገና አንብብ። እነዚህንና ሌሎችን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉትን ጥቅሶች ለማብራራት ከሁሉም የበለጠ ትክክለኛው አቋም የትኛው ይመስልሃል? ለምን?

ከእነዚህ አመለካከቶች እውነተኛው የቱ ነው? የዚህ የጥናት መምሪያ ጸሐፊ እንደሚያምነው ብዙውን ጊዜ የእግዚአብሔር መንገዶች ከእኛ ግንዛቤ በላይ ናቸው። መንግሥተ ሰማይ ደርሰን ከእግዚአብሔር የዕይታ መነጽር አንጻር እስክንረዳቸው ድረስ እርስ በርሳቸው የሚጋጩ የሚመስሉትን ምንባቦች (አንዳንዶቹ ሰው ደኅንነቱን ሊያጣ አይችልም ሲሉ፥ ሌሎቹ ያጣል ይላሉ) ወደ ሰማይ ሄደን እስክንረዳቸው ድረስ ሙሉ ለሙሉ ልናስታርቃቸው አንችልም። እነዚህ በዕብራውያን 6፡4-6 የተጠቀሱት ባሕርያት ክርስቲያኖች እንደሚያመለክቱ የሚያሳዩ ብዙ ደረጃዎች አሉ። ጸሐፊው እነዚህኑ በክርስቶስ ላይ የነበራቸውን አምነት ክደው ወደ ይሁዲነት ለመመለስ የሚያስቡትን አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በማስጠንቀቅ ላይ መሆኑ ግልጽ ነው። ጸሐፊው እርምጃቸው ከእግዚአብሔር ቤተሰብነት ውጭ ከማድረጉም በላይ፥ የዚህ ዓይነቱ ውሳኔ ወደ ክርስቶስ ተመልሰው ደግሞ ይቅርታ የሚያገኙበት መንገድ እንደሚዘጋባቸውም ያብራራል።

ክርስቶስን ለመካድ ለሚያስቡ ሰዎች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ፡- የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ለክርስቶስ ጀርባቸውን መስጠት ለሚፈልጉ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተሰጡት ጠንካራ ከሚባሉ ማስጠንቀቂያዎች አንዱን ሲሰነዘር እንመለከታለን። እነዚህን አምስት በረከቶች ተጠቃሚ የሆኑ (ዕብ. 6፡4-6) ከዚያ በኋላ ጀርባቸውን ለክርስቶስ የሰጡ ሰዎች፥ ደግሞ በንስሐ ሊታደሱ እንደማይችሉ ያስረዳል። መጽሐፍ ቅዱስን በምልአቱ በምንመለከትበት ጊዜ ይህንን ጠንካራ ማስጠንቀቂያ እንድናውቅ የሚያግዙንን እውነቶች እናገኛለን። ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል።

አንደኛ፥ አንድ ሰው በሕይወት እስካለ ድረስ ምንም ዓይነት በደል ቢፈጽምም እንኳን እግዚአብሔር ሁልጊዜም ወደ ድነት (ደኅንነት) ሲጋብዘው ይኖራል። ቀደም ሲል የዕብራውያን ጸሐፊ እንደገለጸው፥ «ዛሬ» ሁልጊዜም ሰዎች በክርስቶስ አምነው ወደ እግዚአብሔር የድነት (ደኅንነት) እረፍት ይገቡ ዘንድ ክፍት ነው (ዕብ. 4፡7)።

ሁለተኛ፥ አንድ ሰው ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ፈልጎ፥ እግዚአብሔር ግን፥ «አዝናለሁ፥ ይቅር ልልህ አልችልም፥ የሠራኸው ኃጢአት በጣም ትልቅ ነው። ቀደም ሲል ክደኸኛል፥ ስለሆነም ሁለተኛ ዕድል ልሰጥህ አልችልም» ያለበትን ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንመለከትም። ማንም ሰው ንስሐ ገብቶ ወደ እግዚአብሔር ከተመለሰ፥ እግዚአብሔር ይቀበለዋል። ክርስቶስን የካደው ጴጥሮስ እንኳን እንደገና በንስሐ ተመልሷል።

ሦስተኛ፣ በእግዚአብሔር ሥራ ላይ ልባቸውን ያጠነከሩ እንደ ፈርኦን ያሉ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰዋል። እነዚህ ሰዎች ልባቸውን ስላደነደኑ እግዚአብሔር ልባቸው ሁልጊዜም ይደነድን ዘንድ ፍርዱን ሰጥቷቸዋል። ከዚህም የተነሣ፥ በእግዚአብሔር ለማመን አልቻሉም። እነዚህ ሰዎች በእግዚአብሔር ለማመን ፈልገው እግዚአብሔር አልቀበላችሁም አላለም። ነገር ግን እግዚአብሔር እርሱን ለመከተል አለመፈለጋቸውን በማክበር ልባቸውን ወደ እርሱ ለመመለስ እስከማያስቡበት ድረስ አደንድኖታል።

ከእነዚህ እውነቶች ስንነሣ ይህ ምንባብ የሚያስጠነቅቀው። ሀ) እግዚአብሔር በሕይወታቸው ውስጥ የፈጸማቸውን በረከቶች ሁሉ በመተው ክርስቶስን ለመከተል ያልፈለጉትን፥ ወይም ለ) እውነትን እያወቁ ለክርስቶስ ሕይወታቸውን ለማስገዛት የማይፈልጉትን ሰዎች ይመስላል። እነዚህ ሰዎች ምናልባትም እንደገና ንስሐ ገብተው በክርስቶስ ሊያምኑ በማይችሉበት አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ሳይሆኑ አይቀርም።

ንስሐ ሊገቡ የማይችሉበት ምክንያት፥ የዕብራውያን ጸሐፊ ንስሐ የላቸውም ያለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እነዚህ ሰዎች እውነትን እያወቁ ለክርስቶስ ለመታዘዝ አልፈለጉም። ጀርባቸውን ለክርስቶስ ሰጥተው ነበር። እነዚህ ሰዎች ልክ ከፈሪሳውያንና ከሌሎችም ክርስቶስን ከሰቀሉ ሰዎች ጎን ቆመው «ስቀለው ስቀለው!» እያሉ ይጮኹ እንደነበረ ያህል ነበር። በአንድ ወቅት ክርስቲያን ተብለው ይጠሩ ስለነበረ የክርስቶስን ስም አሰድባዋል። ክርስቶስ ከሙታን የተነሣ አምላክ እንደሆነ እያወቁ በሥራቸው ግድ የለኝም የሚል አኗኗር ተከትለዋል። ክርስቶስ ዳግም ላይነሣ እንደገና ቢሞትም ግድ የለኝም የሚል ዓይነት አመለካከት ነበራቸው።

የውይይት ጥያቄ፡- ዕብ 6፡4-6 አንብብ። የዕብራውያን ጸሐፊ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ከተቀበሏቸውና እሁን ባለማመናቸው ምክንያት የሚያጧቸው በረከቶች ምን ምንድን ናቸው ይላል? እነዚህ አምስት በረከቶች ዛሬም በእኛ ሕይወት ውስጥም የሚሠሩት እንዴት ነው?

ማስጠንቀቂያው የተሰጠው ለማን ነበር? ይህ ክፍል ስለ ክርስቶስ ሰምተው ለማያውቁ ወይም እርሱን ለመከተል ቃል ገብተው ለማያውቁ ሰዎች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ አይደለም። ይህ ማስጠንቀቂያ የተሰጠው ለአማኞች ማኅበረሰብ አባል ብቻ ሳይሆን፥ በክርስቶስ አምነናል ብለው የእግዚአብሔር ልጆች ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ደስ የሚሰኙባቸውን በረከቶች ለተቀበሉት ሰዎች ነው፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ አምስት በረከቶች ክርስቲያኖች ነን የሚሉትን (እንደ የክርስቲያኖች ልጆች) ሊያመለክቱ ቢችሉም፥ እነዚህ በረከቶች ክርስቲያኖች የሚያገኟቸውን ነገሮች በትክክል የሚያሳዩ ይመስላል።

ሀ) አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ብርሃን በርቶላቸው ነበር። የመረዳት ዓይናቸው ተከፍቶ ስለ ክርስቶስና የእግዚአብሔር የማዳን መንገድ ለመረዳት ችለው ነበር።

ለ) ሰማያዊውን ስጦታ ቀምሰዋል። ጸሐፊው ይህን ሲል ምን ለማለት እንደ ፈለገ በግል ለመረዳት ያስቸግራል። ምናልባትም ድነትን (የዘላለም ሕይወትን) ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ከእግዚአብሔር እንደሚመጡ የሚናገራቸውን ሌሎች በረከቶች ማመልከቱ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ምሁራን የዕብራውያን ጸሐፊ የቀመሱ ሲል እነዚህ ሰዎች የመንፈስ ቅዱስን ስጦታና እግዚአብሔር ሊሰጣቸው ቃል የገባውን መንፈስ ቅዱስ ሙሉ በሙሉ እንዳልበሉ ወይም እንዳላገኙ መናገሩ ነው ይላሉ። ይህም ስጦታ ከወላጆቻቸው ወይም ከሌሎች የቤተ ክርስቲያን አባላት ሕይወት ውስጥ በመመልከት ብቻ ሊለማመዱ እንደቻሉ ያስረዳሉ። ነገር ግን ለሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች መቅመስ የሚያመለክተው የእግዚአብሔርን በረከት ሙሉ በሙሉ ማግኘት ነው (ለምሳሌ፥ መዝሙር 34፡8)።

ሐ) አይሁዳውያን አማኞች የመንፈስ ቅዱስ ተካፋዮች ነበሩ። እነዚህ አማኞች እንደ ሌሎች አማኞች ሁሉ ባመኑ ጊዜ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ተቀብለው ነበር።

መ) መልካሙን የእግዚአብሔር ቃል ቀምሰው ነበር። የእግዚአብሔርን ቃል በማጥናትና ስብከቶችን በማዳመጥ መልካምነቱን ተረድተው ነበር። ዳዊት እንዳለው የእግዚአብሔር ቃል ከወርቅ ወይም ከማር የበለጠ ነው (መዝ. 19፡10)።

ሠ) ሊመጣ ያለውን የዓለም ኃይል ቀምሰው ነበር። ይህ መጪው ዘመን ክርስቶስ የሚመለስበትንና በመንግሥተ ሰማይ የሚመሠረተውን ዘላለማዊ መንግሥት ያመለክታል። ጸሐፊው ይህን ሲል መንፈስ ቅዱስ በመካከላቸው ከፈጸመው ተአምር የተነሣ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የእግዚአብሔርን ኃይል እንደ ተመለከቱ መግለጹ ነበር። ይህም የእግዚአብሔር ኃይል በሰማይ በበለጠ ይገለጣል።

ሰዎች እማኞች ነን እያሉ ይህንኑ በእምነታቸው ጸንተው በተግባር በሚያሳዩበት ጊዜ ምን እንደሚከሰት ለማሳየት፥ ጸሐፊው ስለ እርሻ ቦታ ይናገራል። ገበሬው መልካም ፍሬ በመሻት ጥሩ ዘር ሲዘራ ቆየ። ነገር ግን በመልካም እርሻ ፈንታ ሁልጊዜም እሾህ የሚበቅል ከሆነ፥ እሾሁን ለማቃጠል ሲባል በመሬቷ ላይ እሳት ይለቀቃል፡፡ ይህም እሳት በመሬቱ ላይ ያለውን አነስተኛ እህል ያጠፋዋል። በሚቀጥለው ዓመት እሾህ የሌለበት መልካም ሰብል ማግኘት የሚቻለው በዚሁ መንገድ ነውና። እንደዚሁም እግዚአብሔር እማኞች ነን እያሉ በጽናት ወይም በመልካም ሥራ እምነታቸውን በተግባር በማያሳዩት ሰዎች ላይ ፍርዱን ይገልጣል።

ምንም እንኳን የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች እምነታቸውን ይክዳሉ ብሎ ቢሰጋም፥ ሙሉ በሙሉ ተስፋ አልቆረጠም። እነዚህ ሰዎች በታሪካቸው እግዚአብሔርን በማገልገልና ከፍቅር የተነሣ ሌሎችን ሰዎች በመርዳት የእምነታቸውን እውነተኛነት ገልጸዋል። ይህም አማኞቹ እውነተኛ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናቸውንና እግዚአብሔርም በእምነታቸው እንዲጸኑ እንደሚረዳቸው የሚያሳይ ማረጋገጫ ነበር። ይሁንና እግዚአብሔር መንፈሳዊ ሕይወታችንን ጠንካራና የተሟሟቀ በማድረግ (በጸሎት፥ በጾም፥ የእግዚአብሔርን ቃል በማንበብና ለሌሎች በመመስከር) ከእርሱ ጋር እንድንተባበር ይፈልጋል። ይህም ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት ግድየለሾች ከመሆን የተሻለ አማራጭ ነው።

ረ. አብርሃም የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ስለ ማመንና ለእርሱ በታማኝነት ስለ መጽናት መልካም ምሳሌአችን ነው (ዕብ. 6፡13-20)። እግዚአብሔር በታማኝነት ለሚጸና አማኝ ሁሉ የዘላለም ሕይወትና የዘላለማዊ በረከትን የተስፋ ቃል ሰጥቶአል። ለዚህ የተስፋ ቃል የእኛ ምላሽ ምን መሆን አለበት? የተስፋው ቃል እስኪፈጸም ድረስ ምንም ያህል ቢቆይ ተስፋውን በማመን በታማኝነት መጽናት ይኖርብናል። ምናልባትም አይሁዳውያን ክርስቲያኖች «ክርስቶስ ዳግም እንደሚመለስና መንግሥቱን እንደሚመሠርት ተናግሮ ነበር። ይሄ እስካሁን አልሆነም፡፡ ምናልባት ተሳስቶ ይሆናል፡፡ አልያም እርሱ መሢህ አልነበረም ማለት ነው» ብለው ሳያስቡ እልቀሩም። ጸሐፊው ከብሉይ ኪዳን የአብርሃምን ምሳሌነት በመጠቀም የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች የሚፈጸሙ መሆናቸውን ያረጋግጣል። ይህም የተስፋ ቃሎቹ እኛ እንደፈለግነው በፍጥነት ባይመጡም እንኳን መፈጸማቸው የማይቀር መሆኑን ያመለክታል።

እግዚአብሔር አብርሃምን በጠራው ጊዜ (ዘፍጥ. 12፡1-3፤ 22፡15-18)፥ አብርሃምን እንደሚባርከውና ብዙ ልጆች እንደሚሰጠው የተስፋ ቃል ገባለት። አብርሃም እግዚአብሔርን አመነ። ነገር ግን እግዚአብሔር የተስፋ ቃሉን በመፈጸም ይስሐቅን የሰጠው ከ25 ዓመታት በኋላ ነበር። እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሮቹ የሰጣቸው ሌሎች የተስፋ ቃሎች (ለምሳሌ የከነዓን ምድር) ከመፈጸማቸው በፊት 400 ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህም አብርሃም ከሞተ ከብዙ ዓመታት በኋላ የተፈጸመ መሆኑን እንረዳለን።

እግዚአብሔር የዘላለምን ሕይወት ተስፋ ሰጥቶናል። ሊዋሽ የማይችለው አምላክ ተስፋ የገባልንን ነገር ሁሉ ይፈጽምልናል። ነገር ግን እግዚአብሔር የገባልንን የተስፋ ቃል እስኪፈጽምልን ድረስ ተግተን ልንጠብቀው ይገባል። የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ በረከት ያመጣልናል። በክርስቶስ ላይ ያለንን እምነት መተው ማለት እግዚአብሔር ተስፋ የገባልንን ነገር ሁሉ ማጣት ማለት ነው። ስደት በሚበዛበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር ለእኛ ግድ የሌለውና የተስፋ ቃሎቹም የማይፈጸሙ ሊመስል ይችላል። ይሁንና የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል በትዕግሥት መጠባበቅ ይኖርብናል። ማዕበል በሚነሣበት ጊዜ መልሕቅ መርከብን ከመስመጥ እንደሚታደግ እንዲሁም ጥልቀት ያላቸው ሥሮች ዛፋቹን በኃይለኛ ነፋስ ተገፍተው እንዳይወድቁ እንደሚይዙ ሁሉ፥ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ሁሉ ያለን ጽኑ ተስፋ ወይም ልበ ሙሉነት በስደትና መከራ ጊዜ ለመንፈሳዊ ሕይወታችን ዋስትና ይሰጠናል፡፡ የእምነታችን መልሕቅ ክርስቶስ ነው። ክርስቶስ ሊቀ ካህናችንን እንደ መሆኑ መጠን፥ ወደ ሰማይ ገብቶ ለእኛ በመማለድ ላይ ይገኛል።

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ስለ መንግሥተ ሰማይ የሰጣቸውን የተስፋ ቃሎች ዘርዝር። ተስፍ ሳይቆርጡ እነዚህን የተስፋ ቃሉች መጠባበቅ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው? ለእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች በግልጽ መረዳቱ በችግር ጊዜ ጸንተን እንድንቆም የሚያግዘን እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d