የክርስቶስ ሊቀ ካህንነት ከአሮን ሊቀ ካህንነት ይበልጣል (ዕብ. 7፡1-28)

የዕብራውያን መልእክት የተጻፈው በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት ትተው ወደ ቀድሞው ኃይማኖታቸው (ይሁዲነት) ለመመለስ ለሚያስቡ ሰዎች ነው። ስደትን ከመፍራታቸው የተነሣ እምነታቸውን ለመካድ በማሰብ ላይ ነበሩ። ምንም እንኳን ቀደም ሲል ስደት የደረሰባቸው ቢሆንም፥ በዚህ ጊዜ በተለይም ከይሁዳውያን ወገኖቻቸው ተጨማሪ ስደት ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም። እንዲሁም እነዚህ አማኞች ክርስቶስ ብቸኛው የድነት (ደኅንነት) መንገድ መሆኑን መጠራጠር ጀምረው ነበር። በብሉይ ኪዳን ዘመን በክርስቶስ ማመን ሳያስፈልጋቸው አይሁዶች በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን አግኝተው ስለነበር፥ አሁንም በአይሁዳዊ አምልኮአቸው ብቻ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን የሚያገኙ መሰላቸው። በመሆኑም፥ «በሊቀ ካህናቱ አማካኝነት በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚካሄደውን የእንስሳት መሥዋዕት እያቀረብን በማምለክ ብቻ ድነትን (ደኅንነትን) ልናገኝ ከቻልን፥ ለምን አላስፈላጊ ስደት እንቀበላለን?» ሲሉ አሰቡ። የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ግን ክርስቶስ ከሁሉም የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዓቶች እንደሚበልጥና የእነዚህም ሥርዐቶች ፍጻሜ መሆኑን ይገልጽላቸዋል። ክርስቶስን መካድ ወደ ብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዐት እንዲመለሱ አያስችላቸውም ነበር። ምክንያቱም እግዚአብሔር የብሉይ ኪዳንን አምልኮ በመዝጋት በክርስቶስ በኩል አዲስ የአምልኮ መንገድ ከፍቶአልና ወደ ይሁዲነት መመለሱ አማራጭ የአምልኮ መንገድ ሊሆን አይችልም። ይልቁንም ይህ በእግዚአብሔር ላይ የሚፈጸም ክህደት ይሆናል። ከዚህም የተነሣ ምርጫቸው እንደ ዓለማውያን ሁሉ ለዘላለማዊ ፍርድ የሚያጋልጣቸው መሆኑን ያስገነዝባቸዋል።

(ማስታወሻ:- የዕብራውያን ምዕራፍ 7 ክርስቶስ ከአሮናዊ ሊቀ ካህንነት የሚበልጥ መሆኑን የሚያሳየው ዐቢይ ትምሕርት ቅጥያ ነው፡፡)

የዕብራውያን ጸሐፊ ክርስቶስ በመልከ ጼዴቅ ሥርዓት ለዘላለም የሚኖር ሊቀ ካህናት መሆኑን ለሁለተኛ ጊዜ ይጠቅሳል። ቀደም ሲል (ዕብ. 5፡1-10) ጸሐፊው ክርስቶስ ሰው እንደ መሆኑ መጠን የሚያስፈልገን ርኅሩኅ ሊቀ ካህናት ሊሆን እንደበቃ አስረድቷል። አሁን ደግሞ ክርስቶስ በምን ሥልጣን ሊቀ ካህናት ሊሆን እንደበቃ ያብራራል። አይሁዳውያን አማኞች ብሉይ ኪዳናቸውን በሚገባ ያውቁት ነበር። እነዚህ ሰዎች ሊቀ ካህንነት ለአሮን የዘር ሐረግ ብቻ እንደተሰጠ ያውቁ ነበር። ስለሆነም ከይሁዳ ነገድ የሆነ ኢየሱስ እንዴት ሊቀ ካህናት ሊሆን እንደሚችል ሳያስቡ አልቀሩም። ጸሐፊው ከአሮን ዘሮች የሚልቁ ሌላ ዓይነት ሊቀ ካህናት እንዳሉ ያስገነዝባቸዋል። ይህም የመልከ ጼዴቅ የዘር ሐረግ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዘፍጥረት 14፡17-20 አንብብ። ይህ ታሪክ ስለ መልከ ጼዴቅ ምን ይነግረናል። አብርሃም ከመልከ ጼዴቅ ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ነበረው። ለ) ስለ መልከ ጼዴቅ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንብብ። መልከ ጼዴቅ ከአሮን የበለጠው ለምንድን ነው?

ጸሐፊው የአይሁዶችን የክርክር ዘዴ በመጠቀም፥ ክርስቶስ ከአሮን እንደሚበልጥ ያረጋግጥላቸዋል። ይህንን ያደረገው መልከ ጼዴቅ ከአሮን እንደሚበልጥ በማሳየት ነው። ጸሐፊው ክርክሩን በማስደገፍ የተጠቀመባቸውን ነጥቦች ከዚህ በታች ተመልከት።

ሀ) መልከ ጼዴቅ ካህንና ንጉሥ በመሆኑ ከአሮን ይበልጣል። በሌላ በኩል፥ በአብርሃም ዘር የተወለደው አሮን ካህን ብቻ በመሆኑ ከመልከ ጼዴቅ ያንሳል። ክርስቶስም እንደ መልከ ጼዴቅ ካህንና ንጉሥ ነበር።

ለ) ስፍራውንና ሥልጣኑን የሚያመለክተው የመልከ ጼዴቅ ስም «የጽድቅ ንጉሥ» የሚል ፍች ይሰጣል። በመሆኑም መልከ ጼዴቅ የጽድቅ ንጉሥ የሆነው (ኤር. 23፡5-6) የክርስቶስ ተምሳሌት ነበር። የአሮን ትውልዶች ግን በአመዛኙ በክፋት የተሞሉና ከጽድቅ የራቁ ነበሩ።

ሐ) መልከ ጼዴቅ በኋላ ኢየሩሳሌም ተብላ የተጠራችው የሳሌም ከተማ ንጉሥ ነበር። ሳሌም የሚለው ቃል ሰላም የሚል ፍቺ አለው። ስለሆነም መልከ ጼዴቅ የሰላም ንጉሥ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። የመሢሑም ግዛት መለያ ሰላም እንደሚሆን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል (ኢሳ. 9፡6-7)። የአሮን ሊቀ ካህናት ግን በውጫዊም ሆነ በውስጣዊ ረገድ ለአይሁዶች ሰላምን አላሰፈነም።

መ) መልከ ጼዴቅ የትውልድ ሐረግም ሆነ የዘመን መጀመሪያና መጨረሻ አልነበረውም። እርሱ ለዘላለም ካህን ነበረ። የመልከ ጼዴቅ ታሪክ በዘፍጥረት መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ሆኖ እናገኘዋለን። በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ ሁሉም ዐበይት ገጸ ባሕርያት ከማን እንደ ተወለዱና መቼ እንደ ሞቱ የሚያሳይ የዘር ሐረግ አላቸው። ምንም እንኳን መልከ ጼዴቅ በአንድ ወቅት የሞተ ታሪካዊ ሰው ቢሆንም፥ ስለ ዘር ሐረጉም ሆነ ስለ ሞቱ የተገለጸ ነገር የለም። በመሆኑም፥ መጀመሪያና መጨረሻ እንደሌለው በሚያሳይ መልኩ ተተርኮ እናገኘዋለን። በዚህ ረገድ መልከ ጼዴቅ መጀመሪያና መጨረሻ እንደሌለው ኢየሱስ ክርስቶስ ሆኖ እናገኘዋለን። ስለሆነም በመሞታቸው ከሚታወቁ የአሮን የዘር ሐረግ ሊቀ ካህናት በተቃራኒ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘላለም ይኖራል።

ሠ) የአይሁዶች አባት የሆነው አብርሃም የጦርነት ምርኮውን ለመልከ ጼዴቅ በአስራት መልክ ስለሰጠውና ከመልከ ጼዴቅም በረከትን ስለተቀበለ፥ መልከ ጼዴቅ ከአይሁዶች አሮን ይበልጣል። የአስራት እና የበኩራት መርህ ትንሹ ለትልቁ አሥራትን እንደሚሰጥ፥ ትልቁ ደግሞ ትንሹን እንደሚባርክ ያሳያል። ስለሆነም በአይሁዶች አስተሳሰብ፥ አሮን ከአብርሃም ዘር ስለተወለደ አብርሃም ለመልከ ጼዴቅ አሥራትን በመክፈል እና በእርሱም በመባረክ ታላቅነቱን በገለጸ ጊዜ፥ አሮን በአብርሃም ዘር ውስጥ ነበረ። ስለሆነም እንደ መልከ ጼዴቅ ካህን የሆነው ክርስቶስ ከአብርሃም ከተወለደ ከአሮን ይበልጣል።

ረ) እግዚአብሔር ከመልከ ጼዴቅ የዘር ሐረግ ሌላ ካህን እንደሚመጣ በመተንበይ ከአሮን የዘር ሐረግ የሚመጡ ሊቀ ካህናት ብቁዎች አለመሆናቸውን ገልጾአል። (መዝሙር 110፡4 አንብብ)። እግዚአብሔር የአሮን የዘር ሐረግ ሥልጣን የያዘበትን የብሉይ ኪዳን በአዲሱ የጎልጎታ ኪዳን መተካቱ ለአዲሱ ሥርዓት አዲስ የካህናት የዘር ሐረግ እንዲመሠረት እድርጓል። ክርስቶስ ለማይጠፋ ሕይወት ከሞት ስለተነሣ እግዚአብሔር የአዲሱ ኪዳን ዘላለማዊ ሊቀ ካህናት አድርጎ ሾሞታል።

(ማስታወሻ፡ ጸሐፊው በሰብአውያን ሊቀ ካህናት የሚመራው የመጀመሪያው ቃል ኪዳን ደካማ መሆኑን ምን ያህል በተደጋጋሚ እንደሚገልጽ ልብ በል። አይሁዶች ወደዚሁ ቃል ኪዳን ነበር ለመመለስ የተፈተኑት። በዕብራውያን 7፡11፡ ጸሐፊው የብሉይ ኪዳን መሥዋዕቶችና ሊቀ ካህናት ፍጹምነትን ሊያስገኙ እንደማይችሉ ያስረዳል። ከዚያም በዕብራውያን 7፡18፥ «ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፥ ስለዚህ የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትዕዛዝ ተሽራለች» ይላል። ጸሐፊው ከዚህ ይልቅ ወደ እግዚአብሔር የምንቀርብበት «የሚሻል ተስፋ» እንደተገባልን ይናገራል።

ከዚያም ጸሐፊው የአሮንን ሰብአዊ ሊቀ ካህንነት ከክርስቶስ መለኮታዊ ሊቀ ካህንነት ጋር ያነጻጽራል።

ሀ) የአሮን ክህነት ጊዜያዊ ሲሆን፥ የክርስቶስ ሊቀ ካህንነት ግን ዘላለማዊ ነው። ከሞት የተነሣ፣ የአሮን ሊቀ ካህንነት ብዙ ሊቀ ካህናት ተከታትለው እንዲያገለግሉ አስገድዷቸዋል። ከእነዚህም መካከል አንዳንዶቹ ፈሪሀ እግዚአብሔር ያደረባቸው፥ ሌሎች ደግሞ እግዚአብሔርን የማያስከብሩ ነበሩ። ክርስቶስ ግን ከሞት ስለተነሣና ዘላለማዊ ስለሆነ፥ ለአዲስ ኪዳን ዘመን ብቸኛው ሊቀ ካህናት ነው።

ለ) የአሮን ክህነት ጊዜያዊ እገዛ ሲያመጣ፥ የክርስቶስ ክህነት ግን ለኃጢአተኞች ሁሉ የተሟላ ድነት (ደኅንነት) አስከትሏል። የአሮን ሊቀ ካህንነት አገልግሎት በሞት ምክንያት የሚቋረጥና ከዚህም የተነሣ ለሰዎች ሙሉ ድነት (ደኅንነት) ሊያስገኝ ያልቻለ ሲሆን፥ የኢየሱስ ዘላለማዊ ሊቀ ካህንነት ግን ሙሉ ድነት (ደኅንነት) ያመጣል። እርሱ ሁልጊዜም ለአማኞች ሊያማልድ ይችላል። ሞት የማማለድ አገልግሎቱን ሊያቋርጥበት አይችልም።

ሐ) የአሮን ካህናት ኃጢአተኞች ነበሩ ክርስቶስ ግን ቅዱስ ነው። የአሮን የዘር ሐረግ ካህናት ኃጢአተኞች መሆናቸው አገልግሎታቸውን አደናቅፎታል። ለሰዎች የኃጢአት ይቅርታ መሥዋዕት ከማቅረባቸው በፊት ለራሳቸው ኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ ያስፈልጋቸው ነበር። ክርስቶስ ግን፥ «ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውር የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ» ነው። ስለሆነም አገግልግሎቱ ሁልጊዜ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አለው። እርሱ ኃጢአት ስለሌለበት፥ የኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ አላስፈለገውም።

መ) አሮን ባለማቋረጥ የእንስሳትን መሥዋዕቶች በመሠዋት ጊዜያዊ የኃጢአት ይቅርታን ሲያስገኝ፥ ክርስቶስ ራሱን በመሠዋት ዘላለማዊ ይቅርታን አስገኝቷል። አሮንና ትውልዶቹ በተደጋጋሚ ኃጢአትን ስለ ሠሩ፥ በተደጋጋሚ ለራሳቸው ኃጢአቶች መሥዋዕቶች ማቅረብ ያስፈልጋቸው ነበር። የእንስሳት መሥዋዕቶች ለራሳቸውና ለሌሎች ሰዎች ኃጢአቶች ዘለቄታዊ መፍትሔዎችን የማይሰጡ፥ የእንስሳት መሥዋዕቶች ዕለት በዕለት፥ ዓመት በዓመት ያለማቋረጥ ይቀርቡ ነበር። ክርስቶስ ግን ራሱን በመሠዋት አንድ ጊዜ ብቻ መሞት ያስፈልገው ነበር። ሌላ የኃጢአት መሥዋዕት ማቅረብ አስፈላጊ ሆኖ አልተገኘም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንተ አይሁዳዊ ክርስቲያን ብትሆን ይህ ክርክር የክርስቶስን መሥዋዕት ትቶ ወደ ብሉይ ኪዳን የአምልኮ መንገድ መመለሱ ሞኝነት እንደሆነ ያሳምንህ ነበር? ለምን? ለ) ክርስቶስን ክዶ ወደ ቀድሞው ሃይማኖት ወይም ወደ ዓለም መመለስ ሞኝነት የሚሆንበትን ምክንያት አብራራ። ሐ) በእኛና በእግዚአብሔር መካከል ከሚቆም ሰብአዊ ሊቀ ካህናት ይልቅ የክርስቶስ ሊቀ ካህንነት የሚሻለው ለምንድን ነው? የክርስቶስን ሊቀ ካህንነት ትቶ መፍትሔ ፍለጋ ወደ ሰዎች ፊትን ማዞር ሞኝነት የሚሆነው እንዴት ነው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d