ክርስቶስ አገልግሎቱን የሚሰጠው ከመገናኛው ድንኳን በምትበልጠው ከሰማይቱ ቤተ መቅደስ ውስጥ ነው (ዕብ. 9፡1-12)

የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዓት በሚከተሉት ነገሮች ላይ የተመሠረተ ነበር። ሀ) በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የተደረገ ብሉይ ኪዳን (ስምምነት)፥ ለ) አምልኮን የሚመራ ሊቀ ካህናት፥ ሐ) ኃጢአትን የሚሸፍኑ የእንስሳት መሥዋዕቶች፥ እና መ) አምልኮ የሚካሄድበት የመገናኛ ድንኳንና በኋላም ቤተ መቅደስ ናቸው። የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ክርስቶስ ከእነዚህ ሁሉ የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ነገሮች እንደሚበልጥና እነርሱንም እንደሚተካቸው ያስረዳል። ክርስቶስ ከአሮን የዘር ሐረግ ከፈለቁት ሰብአውያን ሊቃነ ካህናት የሚበልጥ ሊቀ ካህናት መሆኑን ያብራራል (ዕብ. 7)። ቀደም ብሎ አዲሱ ኪዳን አሮጌውን ኪዳን እንደሚተካና እንደሚበልጥ አብራርቷል (ዕብ. 8)። አሁን ደግሞ ክርስቶስ በምትሻል ቤተ መቅደስ ውስጥ እንደሚያገለግልና ከብሉይ ኪዳን ዘመናት የበለጠ መሥዋዕት እንደሚሠዋ ያስረዳል።

ጸሐፊው መጀመሪያ በሰሎሞን፥ በዘሩባቤል በታደሰውና በንጉሥ ሄሮድስ በድጋሚ ታድሶ በጥንቱ ዓለም ውስጥ ከነበሩት ታላላቅ ሕንጻዎች አንዱ ሊሆን የቻለው ቤተ መቅደስ ላይ ከማተኮር ይልቅ፥ የመጀመሪያውን የአምልኮ ስፍራ (የመገናኘው ድንኳን) የትምህርቱ መሠረት እንዲሆን አድርጓል። ጸሐፊው የመገናኛውን ድንኳን ለምን እንደመረጠ አናውቅም። ምናልባት የመገናኛው ድንኳን የመጀመሪያ የአምልኮ ስፍራ ስለነበረና ንድፉም በቀጥታ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስለመጣ ይሆን ይሆናል።

የውይይት ጥያቄ፡– ስለ መገናኛ ድንኳን ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እና ከዘጸአት 37፡1-38፡8 አንብብ። የመገናኛውን ድንኳን ሁለት ክፍሎች እንዲሁም በመገናኛው ድንኳን ውስጥና ውጪ የሚገኙትን የተለያዩ ዕቃዎች የሚያሳይ ሥዕል ሣል። በንድፉና የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚገኙትን ዕቃዎች በሚደረድርበት ሁኔታ መካከል ምን ዓይነት ልዩነቶችን ትመለከታለህ።

ሀ) ሊቀ ካህናቱ የሚያገለግሉበት የመገናኛው ድንኳን

በዕብራውያን 9፡1-10 ጸሐፊው እግዚአብሔር በሲና ተራራ ላይ ለሙሴ የሰጠውን የመጀመሪያውን የአምልኮ ስፍራ ይገልጣል። አይሁዶች በምድረ በዳ ውስጥ በሚቅበዘበዙበት ጊዜ እና በኋላም በመሳፍንት ዘመን ይጠቀሙበት የነበረው የመገናኛው ድንኳን የተሠራው ሙሴ የብሉይ ኪዳን ሕጎችን ከተቀበለ በኋላ ነበር።

የመገናኛው ድንኳን ተንቀሳቃሽ የአምልኮ ስፍራ ነበር። በዚሁ ሰፊ ትልቅ ድንኳን ውስጥ ሁለት ሰፋፊ ክፍሎች ነበሩ። ከሁለቱም የበለጠ ሰፋ የሚለው ውጫዊው ክፍል ቅዱስ ስፍራ በመባል ይታወቃል። አነስ የሚለው ውስጠኛ ክፍል ቅድስተ ቅዱሳን በመባል ይጠራል። በእነዚህ በሁለት ክፍሎች መካከል ከጣሪያው እስከ ወለሉ የወረደ መጋረጃ ይዘረጋል። በውጭ ሦስት የአምልኮ ዕቃዎች ነበሩ። እነዚህም የኅብስቱ መቀመጫ የሆነው ጠረጴዛ፥ ብርሃን የሚሰጥ መቅረዝና ዕጣን የሚሠዋበት የወርቅ መሠዊያ ነበሩ። የወርቅ መሠዊያው ሁለቱን ክፍሎች ከሚለየው መጋረጃ ፊት ይቀመጥ ነበር። በድንኳኑ ውስጠኛ ክፍል አንድ ዕቃ ብቻ ነበር። እርሱም የቃል ኪዳኑ ታቦት ነበር። ሽፋኑ «የስርየት መክደኛ» በመባል ይጠራ ነበር። ከዚህ መክደኛ በላይ የእግዚአብሔር ህልውና አንጸባራቂ ክብር ነበር። ከታቦቱ ውስጥ መና የአሮን በትርና አሥርቱ ትእዛዛት የተጻፈባቸው ጽላቶች ነበሩ (ዘዳግም 10፡1-15)።

የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ የወርቅ መሠዊያው በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ እንደሚገኝ መግለጹ አስገራሚ ነው። ምናልባትም ይህንን ያደረገው በስርየት ዕለት ላይ ለማተኮር ይሆናል። በዚያን ቅዱስ ዕለት የወርቅ መሠዊያው በቅድስተ ቅዱሳን ውስጥ ከሚካሄደው አምልኮ ጋር በቅርብ የተሣሠረ ነበር። በዓመት አንድ ጊዜ በሚከበረው የስርየት በዐል ቀን ሊቀ ካህናቱ መጀመሪያ ወደ ቅዱስ ስፍራ ይገባና የዕጣን መሠዊያውን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ይወስዳል። ከዚያም ከልዩ የእንስሳት መሥዋዕት ደም የተወሰደውን ይዞ ወደ ውስጠኛው ክፍል ይገባና በቃል ኪዳኑ ታቦት ላይ ደሙን ይረጫል። ይህም ደም እርሱም ሆነ ሕዝቡ ዓመቱን ሙሉ በእግዚአብሔር ላይ የፈጸሙትን ኃጢአት ያነጻላቸዋል።

የዕብራውያን መልእክት ጸሐፊ ይህ መንፈስ ቅዱስ ለአይሁዶች ለማሳየት የሚፈልገው ምሳሌያዊ ትምህርት መሆኑን ያመለክታል። በመጀመሪያ ቅዱስ ስፍራን ከቅድስተ ቅዱሳን የሚለየው መጋረጃ ፥ ለአይሁዶች ሁልጊዜም ከእግዚአብሔር ህልውና የተለዩ መሆናቸውን የሚያስረዳ መሆኑን ይገልጻል። የእንስሳት መሥዋዕቶች ኃጢአተኛ ሰዎች እግዚአብሔር ወዳለበት ስፍራ ይገቡ ዘንድ ከኃጢአታቸው ሊያነጹ አይችሉም ነበር። ሁለተኛ፥ ይህ በየዓመቱ የሚደጋገም ሥርዐት ነበር። ድግግሞሹ የሰዎች ኃጢአት ሙሉ በሙሉ እንዳልተሽፈነ እና የእንስሳትን መሥዋዕቶች ወይም ደግሞ ሌሎች የአምልኮ ልምዶች የአምላኪዎችን ሕሊና ሊያነጹ እንደማይችሉ ያስገነዝባል። ስለሆነም ይህ የብሉይ ኪዳን የአምልኮ ሥርዐት ደካማና ክርስቶስ ካከናወነው ተግባር ጋር ሲነጻጸር ያልተሟላ መሆኑን ያሳያል።

ለ) ኢየሱስ በታላቁ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚሰጠው አገልግሎት

በዕብራውያን 9፡11-12 ጸሐፊው ክርስቶስ በሰማያዊቱ እና በምትበልጠው ቤተ መቅደስ ውስጥ ወደሚያከናውነው አገልግሎት ይመለሳል። ጸሐፊው የመገናኛው ድንኳን በሰማይ ያላቸው የታላቋ ቤተ መቅደስ ግልባጭ እንደሆነች አመልክቷል። ሰማያዊው ቤተ መቅደስ ከመገናኛው ድንኳንም ሆነ በምድር ላይ ከተሠሩት ቤተ መቅደሶች የላቀች ነበረች (ዕብ 8፡5-6)። እግዚአብሔር በውበቱ የሚኖረው በሰማይ ነው። አሁን ደግሞ ጸሐፊው በሰማይ የሚካሄደው የክርስቶስ አገልግሎት በማደሪያው የመገናኛ ድንኳን ውስጥ ከሚካሄደው የሰብአዊ ሊቃነ ካህናት አገልግሎቶች እንደሚበልጥ ያስረዳል። ለዚህም ምክንያቱ ክርስቶስ የሚያገለግልበት ሰማያዊቱ ቤተ መቅደስ እንደ የመገናኛው ድንኳን እና ቤተ መቅደስ በሰዎች ሳይሆን በእግዚአብሔር የተሠራች መሆኗ ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይህ ከሰማያዊው እውነተኛ የአምልኮ ስፍራችን በላይ በሰው እጅ በተሠሩት የቤተ ክርስቲያን ሕንጻዎች ላይ ከመጠን በላይ ትኩረት ስለ መስጠት ምን ያስተምረናል? ለ) ጸሎት በሰማይ ወዳለው የእግዚአብሔር የጸጋ ዙፋን የሚያቀርበን ከሆነ (ዕብ 4፡16)፥ አምልኮን በምናካሂድበት ጊዜ በመንፈሳዊ ሁኔታችን የት ስፍራ እንደምንገኝ ግለጽ።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: