ታረቀች ባል ካገባች ከብዙ ዓመታት በኋላ ወንጌልን ሰምታ በክርስቶስ አመነች። ለክርስቶስ ጥልቅ ፍቅር ስለነበራት በሚቻላት ጊዜ ሁሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን አምልኮና በአቅራቢያቸው በሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ትሄዳለች። ቀደም ሲል ትሄድበት ወደነበረው የመጠጥ ማኅበር መሄዱን አቆመች። ቀስ በቀስ በክርስቶስ ስላገኘችው አዲስ ሕይወት ለባለቤቷ መመስከር ጀመረች። ባለቤቷ፥ ግን አዲስ ሃይማኖት ስለተከተለች እንደ ቀድሞው ከእርሱ ጋር አብራ ለመጠጣትና ለመጨፈር ስላልፈለገች በጣም ተቆጣት፡፡ በየቀኑ ይደበድባትና ወደ ቡና ቤቶች እየሄደ ይጠጣ ጀመር። ከሌሎች ሴቶችም ጋር ማሳለፍ ጀመረ። በዚህም ጊዜ ታረቀች ተስፋ ቆረጠች። «በክርስቶስ ማመን ከዚህ በፊት አጋጥሞኝ የማያውቀውን የትዳር ችግርና ሥቃይ እያስከተለ በዚህ እምነት መግፋቱ ትክክል ይሆን?» ስትል አሰበች።
ሀብታሙ ከዩኒቨርስቲ በከፍተኛ ውጤት ከተመረቀ በኋላ በጣም ታዋቂ በሆነ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት (መያድ) ውስጥ ተቀጠረ። ብዙ ደመወዝ፥ መኪናና ሌሎችም ጥቅማ ጥቅሞች ተሰጡት። ሀብታሙ በመንፈሳዊ ሕይወቱ የበረታ ሰው በመሆኑ፥ እግዚአብሔር ይህን ልዩ ሥራ እንደሰጠው ያምን ነበር። ሀብታሙ በድርጅቱ ውስጥ ደፍሮ ይመሰክርና ሠራተኞቹ በምሳ ሰዓት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲያካሂዱ ያደራጅ ጀመር። የዚህ ድርጅት ኃላፊ ወንጌል አማኝ ክርስቲያኖችን አይወድም ነበር። አንድ ቀን ሃብታሙ ወደ ሥራ ሲመጣ አላስፈላጊ ባህሪ በማሳየቱ ምክንያት ከሥራው እንደ ተባረረ የሚያመለክት ደብዳቤ ከጠረጴዛው ላይ ተቀምጦ አየ። ኃላፊው አለአግባብ ሃብታሙን አባርረሃል ተብሎ እንዳይወቀስ ገንዘብ ሲሰርቅ እንደቆየ የሚያሳይ የውሸት መረጃ አሰባስቦ ነበር። በመሆኑም ሃብታሙ ከሥራ መባረር ብቻ ሳይሆን ወደ ሌሎች ስፍራዎች ሥራ ፍለጋ በሚሄድበት ጊዜ ስሙ ስለጎደፈበት የሚቀጥረው አጣ። እግዚአብሔር ለእርሱ ለመመስከር ስፍጨረጨር ለምን ይህን ችግር አመጣብኝ? በሥራ ቦታ ለጽድቅ መርሆችና ለእግዚአብሔር መቆሙ ትክክል ይሆን? እምነቴን ብደብቅ ይሻል ይሆን? እያለ ያስብ ጀመር።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ወንጌል በታረቀችና ሀብታሙ ሕይወት ውስጥ ያስከተለው መከራ ምን ዓይነት ነው? ለ) አንድ ሰው በክርስቶስ በሚያምንበት ጊዜ ለመከራ የሚጋለጥባቸውን ሌሎች መንገዶች ዘርዝር። ክርስቶስን መከተሉ ሥቃይ በሚያስከትልበት ጊዜ ለአማኞች እምነታቸውን መጠራጠር የሚቀልለው እንዴት ነው?
የአንደኛ ጴጥሮስ መጽሐፍ የተጻፈው መከራ ለሚቀበሉ ክርስቲያኖች ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ክርስቶስ በማመናቸው ምክንያት ሥራቸውን የማጣት፥ ከማኅበረሰቡ የመገለል፥ መሳለቂያ የመሆን፥ የመታሰርና የመደብደብ አደጋዎች ደርሰውባቸው ነበር። በመሆኑም፥ «ለሥቃይ የሚያጋልጠኝ ሆኖ ሳለ ክርስቶስን መከተሉ ተገቢ ነውን?» እያሉ ራሳቸውን ይጠይቁ ነበር። የአንደኛ ጴጥሮስ መልእክት ጸሐፊ ለእነዚህ አማኞች ለክርስቶስ መሠቃየት ክብር እንደሆነና የእግዚአብሔር ጥሪ አካል እንደሆነ ይገልጽላቸዋል። መከራን በምንቀበልበት ጊዜ፥ ለጽድቅ መከራ የተቀበለውን የክርስቶስን ሕይወት እንደግማለን። ምንም እንኳን ዲሞክራሲ ከስደት የምንላቀቅበትን ሁኔት ባመቻቸበት በዛሬው ዓለም ውስጥ ስለዚሁ ርእሰ ጉዳይ መነጋገሩ የሚያስደስተን ቢሆንም፥ የአዲሱ ትውልድ አማኞች ለእምነታቸው መሰደድ የእግዚአብሔር ፈቃድ አካል መሆኑን መገንዘብ ይኖርባቸዋል። አንድ ቀን ስደት ይመጣል፥ በመሆኑም እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ምላሽ እንሰጠው ዘንድ መዘጋጀት ይኖርብናል።
የውይይት ጥያቄ፡– ስለ አንደኛ ጴጥሮስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። በመዝገበ ቃላት ውስጥ ጸሐፊው፥ መልእክቱን ስለ ጻፈላቸው ሰዎች፥ ስለ መጽሐፉና ስለ ተጻፈበት ዓላማ የቀረበውን አሳብ ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)