ጴጥሮስ መልእክቱን የጻፈው ለማን ነው፣ መቼ እና የት ተጻፈ?

ጴጥሮስ መልእክቱን የጻፈው ለማን ነው?

ጴጥሮስ በመግቢያው ላይ፥ «ለጳንጦስና፥ ለገላትያ፥ በቀጰዶቂያም፥ በእስያም፥ በቢታንያም ለተበተኑት መጻተኞች» ይላል። እነዚህ አውራጃዎች የሚገኙት ከትንሹ እስያ (የአሁኗ ቱርክ) በስተ ሰሜን ነበር። መንፈስ ቅዱስ ጳውሎስ ወደ እነዚህ አካባቢዎች እንዳይገባ ነግሮት ነበር (የሐዋ. 16፡6-8)። ምሁራን መንፈስ ቅዱስ ጳውሎስ ወደዚህ አካባቢ እንዳያገለግል የከለከለው ጴጥሮስ ቀደም ሲል ወይም ወደ በኋላ በዚህ አካባቢ የወንጌል አገልግሎት ይሰጥ እንደነበረ ስለሚያውቅ ነው ይላሉ። ጴጥሮስ በእነዚህ አውራጃ ዎች ውስጥ መቼ እንዳገለገለ ባናውቅም፥ ብዙ ጊዜ እያገለገለ በመቆየቱ ምክንያት በአማኞች ዘንድ ሊታወቅ የቻለ ይመስላል።

ጴጥሮስ በእነዚህ አካባቢዎች ስለነበሩት አማኞች አስገራሚ ገለጻ ያደርጋል። በመጀመሪያ፥ በእግዚአብሔር የተመረጡ ይላቸዋል። ጴጥሮስ ልክ እንደ ጳውሎስ እግዚአብሔር በምሕረቱ እያንዳንዱን አማኝ እንደ መረጠው ያውቅ ነበር። ድነትን (ደኅንነትን) አስመልክቶ የጴጥሮስ ትኩረት እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ያደረገው ተግባር እንጂ የእኛ ክርስቶስን መምረጥ አይደለም። ጴጥሮስ ይህንን የጻፈው በመከራ ውስጥ የሚያልፉትን ክርስቲያኖች ለማበረታታት ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ከመረጣቸው፥ እያንዳንዳቸውን እንደ ውድ ልጆቹ ስለሚመለከት እንደሚጠብቃቸው ግልጽ ነው። ሁለተኛ መጻተኞች ይላቸዋል። ጴጥሮስ እነዚህ ስደት የበዛባቸው አማኞች ገና ከቤታቸው እንዳልደረሱ ያሳስባቸዋል። እንደ አብርሃም፥ በምድር ላይ በጉዞ ይኖሩ ነበር። እማኞች ወደ እውነተኛይቱ ቤታቸው የሚደርሱት መንግሥተ ሰማይ ሲደርሱ ብቻ ነው። በመሆኑም፥ ከእምነታቸው የተነሣ ቤቶቻቸውንና ሥራቸውን በሚያጡበት ጊዜ ተስፋ ሊቆርጡ አይገባም። ምክንያቱም ማንም ከእነርሱ የማይወስደው ዘላለማዊ ቤት በሰማይ አላቸውና።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር እኛን ለይቶ መምረጡ መከራን በምንቀበልበት ጊዜ እንዴት ያበረታታናል ለ) በዓለም ውስጥ የምንኖር መጻተኝነታችንን መገንዘብ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?

አንዳንድ ምሁራን ጴጥሮስ የአይሁዶች ሐዋርያ እንደ መሆኑ መጠን «የተበተኑ» የሚለውን ሐረግ እንደ ተጠቀመ ይናገራሉ። ይህም በሮም ግዛቶች ሁሉ ውስጥ የተበተኑትን አይሁዶች የሚያመለክት ቃል ነው። ጴጥሮስ መልእክቱን በቀዳሚነት የጻፈው በሰሜን ቱርክ የሚገኙ ጥቂት አይሁዳውያን አማኞች ለመሠረቷቸው አብያተ ክርስቲያናት ነበር። ነገር ግን የአንደኛ ጴጥሮስ መልእክት የተጻፈው በሰሜኑ የትንሹ እስያ ክፍል በተለያዩ ከተሞች ይሰበሰቡ ለነበሩ አይሁዳውያንና አሕዛብ አማኞች ይመስላል። በመሆኑም ይህ በስብሰባ ጊዜ በአንዱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከተነበበ በኋላ ወደ ሌላው ቤተ ክርስቲያን እየተላከ አብያተ ክርስቲያኑን በሞላ እንዲያዳርስ የታሰበ ተዘዋዋሪ ደብዳቤ ሳይሆን አይቀርም። እንዲያውም ጴጥሮስ የሮምን አውራጃ ዎች የጠቀሰበት ቅደም ተከተል መልእክቱን ለየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚያዳርሰው መልእክተኛ የሚሄድባቸውን ከተሞች ቅደም ተከተል የሚያመለክት ሳይሆን አይቀርም። እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ደብዳቤውን ገልብጠው ለራሳቸው ያስቀሩና ቀስ በቀስ እነዚሁ ቅጂዎች በክርስትናው ዓለም ውስጥ የተሰራጩ ይመስላል።

አንደኛ ጴጥሮስ የተጻፈበት ጊዜና ስፍራ

የውይይት ጥያቄ፡– 1ኛ ጴጥሮስ 5፡13 አንብብ። ይህ ጥቅስ 1ኛ ጴጥሮስ የት እንደ ተጻፈ ያሳያል? ጴጥሮስ ይህን መልእክት በጻፈ ጊዜ ከእርሱ ጋር ማን ነበር?

ይህ መልእክት በትክክል መቼ እንደ ተጻፈ አናውቅም። በ95 ዓ.ም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በጽሑፋቸው ውስጥ መልእክቱን ስለጠቀሱ፥ ከዚሁ ጊዜ ቀደም ብሎ እንደ ተጻፈ ለመረዳት ይቻላል። ጴጥሮስ በ68 ዓመተ ምሕረት በተጠናቀቀው የኔሮ ክርስቲያኖችን የማሳደድ ዘመቻ ውስጥ እንደ ሞተ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስለሚያመለክት፥ ይህ መልእክት ከዚሁ ጊዜ ቀደም ብሎ የተጻፈ ይመስላል። ይህ መልእክት ኔሮ ክርስቲያኖችን ማሳደድ ከጀመረ በኋላ ከ64-65 ዓመተ ምሕረት ባለው ጊዜ ውስጥ የተጻፈ ይመስላል።

ጴጥሮስ በመልእክቱ በመጨረሻ ላይ ከባቢሎን ለሆኑት አማኞች ሰላምታ ይልካል። በአዲስ ኪዳን ዘመን፥ የብሉይ ኪዳን ዘመኗ ባቢሎን ፈራርሳ ነበር። በዚህ ጊዜ ባቢሎን ተብላ ትታወቅ የነበረችው አነስተኛ መንደር ነበረች። ምንም እንኳን ጳውሎስ በዚህች አነስተኛ መንደር ውስጥ ሊኖር ቢችልም፥ የባቢሎንን ከተማ ማመልከቱ አልነበረም። በመጀመሪያው ምእተ ዓመት መጨረሻ ላይ አይሁዳውያንም ሆኑ ክርስቲያን ጸሐፊዎች የሮምን ከተማ ባቢሎን በሚባል ተምሳሌታዊ ስም ይጠሩ ነበር። ይህንንም ያደረጉት ቀደም ሲል ባቢሎን አይሁዶችን በምርኮኛነት ማጋዟን በማስታወስ አሁንም ሮም አይሁዶችንና ክርስቲያኖችን እያሳደደች መሆኗን በመገንዘባቸው ነበር። ስለሆነም፥ ጴጥሮስ ይህን መልእክት የጻፈው ከሮም ከተማ ይመስላል። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በኔሮ የስደት ጊዜ ጴጥሮስና ጳውሎስ በሮም ከተማ እንደ ነበሩና ጴጥሮስ መልእክቶቹን ከሮም ከተማ ሆኖ እንደ ጻፈው ያረጋግጣል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: