ለሽማግሌዎችና ለጎልማሶች የተሰጠ ምክር (1ኛ ጴጥ. 5፡1-14)

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መልካም ግንኙነት ሊኖር ይገባል። ጴጥሮስ ከሚያሳድዱን ዓለማውያን፥ ከቤተሰብ አባላትና ከሌሎች አማኞች ጋር ስለሚኖረን ግንኙነት አስተምሯል። አሁን ደግሞ የእግዚአብሔር ሕዝብ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖረው እንደሚገባ ያስተምራል።

 1. ጴጥሮስ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሆኑት ሽማግሌዎች ይጀምራል። በተለይ በስደት ጊዜ የሽማግሌዎች ቀዳማይ ኃላፊነት ምንድን ነው? ሽማግሌዎች የእግዚአብሔር መንጋ እረኞች እንደ መሆናቸው መጠን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉትን አማኞች ሁሉ በጥንቃቄ መጠበቅ ያስፈልጋቸዋል። ምንም እንኳን ይህ ተጨማሪ ሸክም ቢሆንም፥ እግዚአብሔር ይህንን የአመራር ኃላፊነት ከሰጣቸው በደስታ ሊቀበሉት ይገባል። ነገር ግን መሪዎች ከዚሁ አገልግሎታቸው የተነሣ የሚጋፈጧቸውን የተለመዱ አደጋዎች መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። እንደ ገንዘብ ወይም የግል ሥልጣን (በኃይል መግዛት) ላሉት ጥቅሞች ሲሉ የመሪነትን አገልግሎት መቀበል የለባቸውም። መሪዎች የመጨረሻው ሽልማታቸው የእረኞቹ አለቃ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ ከጥሩ ደመወዝ ወይም ከሰዎች ከሚያገኙት ክብር እንደማይመጣ መረዳት ይኖርባቸዋል። በመንግሥተ ሰማይ፥ የክብርን አክሊል ይቀበላሉ። ይህም ከምድራዊው የገንዘብ ወይም የሥልጣን ሽልማት በተቃራኒ ከእነርሱ ሊወሰድ የማይችል ነው።

(ማስታወሻ፡ ጴጥሮስ ስለ መሪዎች ዐቢይ ኃላፊነት ጠቃሚ እውነትን ገልጾአል። ሽማግሌ የቤተ ክርስቲያን አባላት እረኛ ነው። ጴጥሮስ ይሄንን የጻፈው በጎቻቸውን በሚገባ የሚጠብቁትን አይሁዳውያን እረኞች በማስታወስ ነው (ለምሳሌ፥ መዝ. 23)። ሽማግሌዎች የቤተ ክርስቲያናቸውን አባላት ሁሉ በግል ማወቅ ይኖርባቸዋል። ይህም አማኞች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዲያድጉና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ፍሬያማ አገልግሎት እንዲያበረክቱ ለማበረታታትና ለማገዝ ያስችላቸዋል። በጴጥሮስ ዘመን አብያተ ክርስቲያናት በግለሰብ ቤቶች ውስጥ ይሰበሰቡ ነበር። በመሆኑም ሽማግሌዎች እያንዳንዱን አማኝ በግል ያውቁ ነበር። በዛሬዎቹ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ግን በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች ስለሚገኙ፥ ሽማግሌዎች አባሎቻቸውን በግል ለማወቅ ይቸገራሉ። ይህ ግን እያንዳንዱን ክርስቲያን በአግባቡ በእረኝነት ለማገልገል እንዳይሞክሩ ያደርጋቸዋል ማለት አይደለም። አንድ ሽማግሌ ከ50 የሚበዙትን ክርስቲያኖች በበቂ ሁኔታ በእረኝነት ሊያገለግል አይችልም። በመሆኑም እያንዳንዱ ሽማግሌ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት የተወሰኑትን ሰዎች በእረኝነት እንዲያገለግል ሊመደብ ይገባል። እንዲሁም ሽማግሌዎች ከሥራቸው የሚያገለግሉትን ሰዎች መሾም ያስፈልጋቸዋል። ምናልባትም ብዙ ክርስቲያኖች በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የማያድጉት፥ በሐሰት ትምህርት የሚወሰዱት ወይም ወደ ዓለም የሚመለሱት፥ ሽማግሌዎች ተገቢውን የእረኝነት አገልግሎት ስለማይሰጡ ይሆናል። እግዚአብሔር ሽማግሌዎች የእረኝነት አገልግሎት እንዲሰጡ ይጠብቃል። በእግዚአብሔር እርዳታ የእያንዳንዱ ክርስቲያን መንፈሳዊ ፍላጎቶች መሟላታቸውን ስለምናረጋግጥባቸው መንገዶች ማሰብ ይኖርብናል።)

የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) አብዛኞቹ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች አባሎቻቸውን የሚያውቁና ፍላጎቶቻቸውን በበቂ ሁኔታ የሚያሟሉ ይመስልሃል? ካልሆነ፥ ለምን? ለ) በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እያንዳንዱ ክርስቲያን በበቂ ሁኔታ ከሽማግሌዎች የእረኝነት አገልግሎት በሚያገኙበት መልኩ አመራርን ለማዋቀር ምን ማድረግ ያስፈልጋል?

 1. በመቀጠልም ጴጥሮስ ብዙውን ጊዜ ከሽማግሌዎች ጋር ለሚጋጩ ወጣቶች ምክርን ይሰጣል። ብዙውን ጊዜ ወጣቶች አሁኑኑ ለውጥ እንዲመጣ ይፈልጋሉ። በሥልጣን ላይ መቀመጥ ይሻሉ። ወጣቶች ብዙውን ጊዜ ከእነርሱ ያነሰ ትምህርት ያላቸውን ሽማግሌዎች ይንቃሉ። በእድሜ ገፋ ያሉ መሪዎች የእነርሱን ያህል መንፈሳዊ እንዳልሆኑ ያስባሉ። ጴጥሮስ ለውጥ በማምጣቱ አስፈላጊነት ላይ ሲያተኩር፥ እነዚህ ወጣቶች ለሽማግሌዎች እንዲገዙ ይመክራል። ሽማግሌዎች መንፈሳውያን ባይሆኑም እንኳን ወጣቶች በትሕትና ራሳቸውን ማስገዛት ይኖርባቸዋል። ወጣቶች እግዚአብሔር ሰውን ወደ ታላቅነት የሚያደርስበትን መንገድ ማስተዋል ይኖርባቸዋል። በመጀመሪያ አንድ ሰው ከሁኔታዎች ሁሉ ባሻገር ለእግዚአብሔርና ለሌሎችም መገዛት ይኖርበታል። ከዚያም እግዚአብሔር በራሱ ጊዜ እና መንገድ የሥልጣንን ስፍራ ይሰጠዋል። የትሕትናን ትምህርት ሳይማሩ ወደ ሥልጣን ለመውጣት መቸኮሉ ለወጣቱ ብቻ ሳይሆን ለቤተ ክርስቲያኒቱም አደገኛ ነው። የሕይወትን ጠቃሚ ነገሮች ለመማርና ለመብሰል ጊዜን ይጠይቃል፡፡ እነዚህ ትምህርቶች ደግሞ ከመጽሐፍ የሚገኙ አይደሉም።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ጴጥሮስ ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከሚሰጣቸው ምክሮች መካከል የዛሬዎቹ መሪዎች ለመፈጸም የሚሞክሩዋቸው የትኞቹ ናቸው? እግዚአብሔር የሚፈልገውን ዓይነት መሪ እንዳይሆኑ የሚከለክሏቸው ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? ለ) ወጣቶች የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን እርምጃዎች በትዕግሥት ለመቀበል ባለመቻላቸው ወደ መሪነት ሥልጣን ለመውጣትና ቅጽበታዊ ለውጥ ለማምጣት ሲጥሩ የተመለከትክበትን ሁኔታ ግለጽ፡፡ ጴጥሮስ ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ስለሚሞክሩበት ሁኔታ ምን ምክር ሰጠ?

 1. በመጨረሻም፥ ጴጥሮስ አማኞች ሁሉ ሊያስታውሱ የሚገባቸውን አንዳንድ ጠቃሚ እውነቶች በፍጥነት ይዘረዝራል።

ሀ. «እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃቸውን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት»። አማኞችን የሚያስጨንቁ ብዙ ነገሮች አሉ። ከእነዚህም መካከል ስደት፥ የገንዘብ እጥረት፥ ሥራ አጥነት፥ በሽታና የመሳሰሉት ሊጠቀሱ ይችላሉ። አማኞች ለእነዚህ ችግሮች ምን ዓይነት ምላሽ ሊሰጡ ይገባል? እግዚአብሔር እንደሚያስብልንና በእርሱ አመለካከት ለእርሱ ጥሩ የሆነውን ብቻ ወደ ሕይወታችን እንደሚያመጣ በማመን፥ በጸሎትና በትሕትና ችግራችንን ለእርሱ ማሳወቅ ይኖርብናል።

ለ. በመጠን ኑሩ ንቁም። ጴጥሮስ ስለምን መንቃት እንዳለብን አልገለጸም። እየተናገረ ያለው ግን በመከራና ሥቃይ ዐውድ ውስጥ ሆኖ ነው። ሁልጊዜም፥ በተለይም በመከራና በሥቃይ ጊዜ አማኞች ልባቸውንና ሕይወታቸውን በጥንቃቄ መጠበቅ ይኖርባቸዋል። መራርነትና ቁጣ እንዳይሞላን መጠንቀቅ አለብን። አማኞች ሰዎችን ለመበቀል ማሰብ የለብንም። ከፍርሃት፥ እምነታችን ከመካድ ወይም ከመደበቅ መጠንቀቅ አለብን። ክርስቲያኖች ሁሉ የዓለም ወይም የኃጢአት ፍቅር ወደ ውስጣችን ዘልቆ እንዳይገባና ምስክርነታችን እንዳይጠፋ መጠንቀቅ አለብን። ሰይጣን እነዚህን ነገሮች ሁሉ እኛን ለማሸነፍ ቢጠቀምም ማወቅና መንቃት አለብን።

ሐ. ከምንጋፈጠው ትግል በስተጀርባ ያለውን መንፈሳዊ ጦርነት ማስታወስ አለብን። ጴጥሮስ፥ «ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት» ይላል። ጴጥሮስ ሰይጣንን እንዴት እንደምንቃወም አልገለጸም። በክርስቶስ ስም ከዚህ ሂድ ብለን በመገሠጽ ነው? ጴጥሮስ በዚህ ክፍል እንዲህ ዓይነት እርምጃ እንድንወስድ አልመከረንም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰይጣንን ስለመቃወም የሚያሳየን ምሳሌ ክርስቶስ በምድረ በዳ ውስጥ የሰይጣንን ፈተና የተቃወመበት ነው (ማቴ. 4፡1-11)። ክርስቶስ በቀዳሚነት የሰይጣንን ፈተና የተቃወመው የእግዚአብሔርን ቃል በመጥቀስ ነው። እንዲሁም ሰይጣን ከእርሱ ፈቀቅ እንዲል በማዘዝ ነው። የዚህ ትእዛዝ ዐውድ እንደሚያሳየው፥ በስደትና መከራ ጊዜ ሰይጣን በተለይ ተግቶ ይዋጋናል። ሰይጣን እምነታችንን ለማጥፋት፥ ሕይወታችንን በመራርነት ለመሙላት፥ እምነታችንን እንድንክድ ወይም እንድንደብቅ ለማድረግ የሚታገል መሆኑን በመገንዘብ፥ በእምነት ጸንተን ልንቃወመው ይገባል። ሰይጣንን የምንቃወመው ችግሮች ወደ ሕይወታችን የገቡት ኃጢአት በመሥራታችን፥ እግዚአብሔር እየቀጣን በመሆኑ ስለማይወደን ወደ ጥንቷ መንገዳችን በመመለስ ከስደት እንድናመልጥ በመግለጽ የሚያመጣቸውን ውሸቶች ባለመስማት ነው። ለክርስቶስ ያለንን መሰጠት በማደስና ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕይወት በመኖር ሰይጣንን እንቃወማለን። ይህንን የስደትና የመከራ ችግር የምንጋፈጠው ብቻችንን እንዳልሆነ በመገንዘብ ልንበረታታ ይገባል። ብዙ አማኞች እነዚህን ችግሮች እየተቀበሉ በእምነታቸው ጸንተው ቆመዋል።

ሰይጣን መከራ በምንቀበልበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር የማይስማማ እርምጃ በመውሰድ በምንፈተንበት ጊዜም በሕይወታችን ውስጥ ተሳትፎ ለማድረግ መጣሩ የማይቀር ነው። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ ይኖርብናል? ድልንም የምንቀዳጀው እንዴት ነው?

 1. መጸለይ አለብን፡- በክርስቶስ ኃይል ሰይጣን ከአካባቢያችን እንዲርቅ የማዘዝ ሥልጣን አለን? (መጽሐፍ ቅዱስ በክርስቶስ ስም መጸለይ ሲል ይህን ማለቱ ነው።) (ነገር ግን አንዳንድ ክርስቲያኖች በተሳሳተ መንገድ እንደሚጸልዩት ሰይጣንን ወደ ጥልቁ የመላክ ሥልጣን የለንም።) በሰይጣን ላይ ድልን ለመቀዳጀት መጽሐፍ ቅዱስ ጸሎታችን ቢያንስ አራት ነገሮችን ሊያካትት እንደሚገባ ያስተምራል።
 2. በሕይወታችን ውስጥ ያለውን ማንኛውንም ኃጢአት ማስወገድ አለብን። ንስሐ ያልተገባበት ኃጢአት የሰይጣን ምሽግ ነው። ይህን ምሽግ ለማስለቀቅ ክርስቲያኖች ኃጢአታቸውን ለእግዚአብሔር መናዘዝ ያስፈልጋቸዋል። ኃጢአቱ የተፈጸመው በሌሎች ሰዎች ላይ ከሆነ ደግሞ፥ ለሰዎቹም መናዘዝ ያስፈልጋል። ሰይጣን ከአካባቢያችን እንዲርቅ መጸለዩ ብቻ በቂ አይደለም። ኃጢአታችንን ከተናዘዝን በኋላ፥ እግዚአብሔር ሰይጣን በእኛ ላይ ያለውን ምሽግ እንዲያፈርስ ልንጠይቅ እንችላለን። እግዚአብሔር ጸሎታችንን እንደ መለሰ በማመንና በክርስቶስ ስምና ሥልጣን የሚቀርበውን የጸሎት ሥልጣን በመጠቀም፥ ሰይጣን ምሽጉን እንዲለቅ ልናዘው እንችላለን።
 3. እግዚአብሔር ከሰይጣን እንዲጠብቀን የእግዚአብሔርን የጦር መሣሪያ መታጠቅ አለብን። (ኤፌ. 6፡10-18 አንብብ።) የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ ሳንለብስ ሰይጣን ከአካባቢያችን እንዲርቅ በመጠየቃችን ብቻ ለቅቆ እንደሚሄድ ወይም እንደሚሸነፍ ማሰብ የለብንም።
 4. ክርስቶስ የእግዚአብሔርንም ቃል እንድንጠቀም ያስተምረናል። ሰይጣን በፈተነው ጊዜ ሁሉ ክርስቶስ የእግዚአብሔርን ቃል በመጥቀስ ነበር ምላሽ የሰጠው። ለምሳሌ ያህል፥ ስለ አንድ ሰው እንድንዋሽ በሚጠይቀን ጊዜ «በባልንጀራህ ላይ በሐሰት አትመስክር» (ዘጸ. 20፡16) የሚለውን ዓይነት ጥቅስ መጠቀም ይኖርብናል።
 5. ጴጥሮስ የሰይጣንን ውሸቶች ላለማመን ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ እንዳለብን ይነግረናል። የሰይጣንን ፈተና ሳንቀበል እግዚአብሔር እርሱን ለመታዘዝ እንዲያስችለን በእምነት ብንጠይቀው፥ እውነተኞች እና ንጹሖች ሆነን እግዚአብሔር የሚፈልገንን ዓይነት ሕይወት ልንኖር እንችላለን። ሰዎች በሚሳለቁብን ጊዜ ከመቆጣት ወይም ለመበቀል ከማሰብ ይልቅ፥ ሰይጣን እንድናደርግ የሚፈልገውን ከማድረግ ይልቅ እነዚህን ሰዎች ለመርዳት፡ ይቅር ለማለትና ስለ እነርሱ ለመጸለይ እንመርጣለን። ሰይጣንም በሚፈትነን ጊዜ ሁሉ የሚለንን ላለመስማት ቁርጥ ውሳኔ መወሰን አለብን።

በዚህ ዓይነት፥ ሀ) በጸሎት፥ ለ) ኃጢአትን በመናዘዝ፥ ሐ) የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ በመጠቀም፥ መ) በቃሉ አማካኝነት፥ እንዲሁም ሠ) ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ፥ ሰይጣንን እናሸንፋለን። እነዚህ አምስቱ ነጥቦች አስፈላጊዎች ናቸው። ንጹሕ ሕይወት ለመምራት ሳንቆርጥ መጸለይ ሰይጣንን አያሸንፈውም። ሳንጸልይ እና እግዚአብሔርን ለመታዘዝ ሳንወስን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ብንጠቅስ ሰይጣን አይሸነፍልንም? ጸሎት፥ የእግዚአብሔር ቃልና የእኛ ቅዱሳን ለመሆን መምረጥ አስፈላጊዎች ናቸው።

ጴጥሮስ ሰይጣንን በመቃወሙ እና በእምነታችን በመጽናቱ ረገድ ልንበረታ እንደሚገባ በማሳሰብ ይህንን ክፍል ይደመድማል። ጴጥሮስ እግዚአብሔር በስደት ውስጥ ጸጋን እንደሚሰጠን ይነግረናል። እርሱ በእምነታችን ጠንክረን እንድንጸና ያስችለናል። አንድ ቀን ደግሞ መከራው ያበቃና በክርስቶስ የምናገኘውን ዘላለማዊ ክብር እንቀዳጃ ለን።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አብዛኛዎቹ አማኞች ጴጥሮስ ዲያብሎስን ተቃወሙት ሲል ምን ማለቱ ነው ብለው ያስባሉ? ለ) ብዙ ክርስቲያኖች ሰይጣን ከአካባቢያቸው እንዲርቅ በተሟሟቀ ሁኔታ እየጸለዩ፥ ዳሩ ግን በግል ሕይወታቸው በቤተ ክርስቲያናቸው ውስጥ በኃጢአት ላይ ድል የማይቀዳጁበትን ሁኔታ ግለጽ። ይህ የሚሆነው ለምን ይመስልሃል? ሐ) እነዚህ ሰይጣንን የመቃወሚያ አምስት ነጥቦች አስፈላጊ ናቸው? ከሆነ በሕይወትህ ሰይጣንን ለመቃወም እንዴት እንደተጠቀምክባቸውና ሰይጣንን ከአካባቢህ እንዲርቅ እንዳደረገ ግለጽ?

ማጠቃለያ (1ኛ ጴጥ. 5፡12-14)፡፡ ጴጥሮስ ስልዋኖስ (ሲላስ) በዚህ ደብዳቤ ውስጥ አስተዋጽኦ እንዳደረገለት በመግለጽ መልእክቱን ይፈጽማል። ሲላስ እንዴት እንደረዳው አልተገለጸም። ምናልባት ደብዳቤውን ከጴጥሮስ ተቀብሎ ወደ ተከታዮቹ አድርሶ ይሆናል። ምናልባትም ደግሞ ሲላስ ጴጥሮስ የሚናገረውን ቃል እየሰማ በጽሑፍ አስፍሮት ይሆናል።

ጴጥሮስ በባቢሎን ካሉት ወገኖች ሰላምታ ያቀርባል። ምናልባትም ይህ ሮምን የሚያመለክት ተምሳሌት ሊሆን ይችላል። ጴጥሮስ ማርቆስን በስሙ ጠርቶታል። በመጀመሪያው የወንጌል መልእክተኝነት ወቅት ከጳውሎስና በርናባስ ጋር አብሮ የነበረው ዮሐንስ ማርቆስ ነው። ቀደምት የቤተ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ማርቆስ በኋላ የጴጥሮስ ረዳት ሊሆን እንደቻለና ከጴጥሮስ ጋር ካለው ቅርበት የተነሣ የማርቆስን ወንጌል ሊጽፍ እንደበቃ ይናገራል።

የውይይት ጥያቄ፡– ከአንደኛ ጴጥሮስ ጥናት የተረዳሃቸው ቁልፍ ትምህርቶች ምን ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

3 thoughts on “ለሽማግሌዎችና ለጎልማሶች የተሰጠ ምክር (1ኛ ጴጥ. 5፡1-14)”

 1. 1 መሪዎች የመጨረሻው ሽልማታቸው የእረኞቹ አለቃ ከሆነው ከኢየሱስ ክርስቶስ እንጂ ከጥሩ ደመወዝ ወይም ከሰዎች
  ከሚያገኙት ክብር እንደማይመጣ መረዳት ይኖርባቸዋል። *
  ···/1
  እውነት

  ውሸት
  No correct answers
  ለምን ትክክል እንዳልሆንኩ አልገባኝም ልትስረዱኝ ትችላላችሁ

  On Fri, Jun 7, 2019 at 6:36 PM ወንጌል በድረ-ገፅ አገልግሎት wrote:

  > tsegaewnet posted: “በቤተ ክርስቲያን ውስጥ መልካም ግንኙነት ሊኖር ይገባል። ጴጥሮስ ከሚያሳድዱን
  > ዓለማውያን፥ ከቤተሰብ አባላትና ከሌሎች አማኞች ጋር ስለሚኖረን ግንኙነት አስተምሯል። አሁን ደግሞ የእግዚአብሔር ሕዝብ
  > በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖረው እንደሚገባ ያስተምራል። ጴጥሮስ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሆኑት
  > ሽማግሌዎች ይጀምራል። በተለይ በስደት ጊዜ የሽማግሌዎች ቀዳማይ ኃላፊነት ምንድን”
  >

 2. Hi There,  Thank You so much for what you doing for the sake of the kingdome of God. I really don’t have enough word to thank you.if you have any teaching about serving God please send me.  With big respect and love. Be blessed

  1. እሕቴ ሃና፣

   አስቀድሜ ስለአበረታች አስተያየትሽ ምስጋናዬን ላቅርብ፡፡ ወደ ጥያቄሽ ስመለስ፣ የወንጌል በድረ ገጽ አገልግሎት ዌብ ሳይት (https://ethiopiansite.com/) በርካታ መንፈሳዊ ጽሑፎችን የያዘ ሳይት ነው፡፡ በዌብ ሳይቱ የድነት (የደኅንነት) ትምሕርቶች (https://goo.gl/fDtBXd)፣ የደቀ መዝሙር ማሰልጠኛ ማኑዋሎች (https://goo.gl/26UzGK)፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መሳሪያዎች (https://goo.gl/Eou24Y)፣ ለተለያዩ ጥያቄዎች መልስ የሚሰጡ አጫጭር የጥናት ጽሑፎች (https://goo.gl/UWbZjw)፣ ወዘተ ተካተዋል፡፡ እንግዲህ እንደ ምርጫሽ ሊንኮቹን በመጫን ጥናትሽን ማካሄድ ትችያለሽ፡፡

   የወንጌል በድረገጽ ዌብ ሳይት ተከታታይ (follower) ለመሆን የምትሺ ከሆነ የወንጌል በድረ-ገጽ አገልግሎት ዌብ ሣይት (https://ethiopiansite.com/) የፊት ገጽ ግርጌ ላይ በመሄድ፣ በስተቀኝ ባልው ክፍት ሣጥን ውስጥ የኢ-ሜይል አድራሻሽን በመጻፍና “ድረ-ገጹን ይከታተሉ” የሚለውን ቁልፍ በመጫን የዌብ ሣይቱ ተከታይ (follower) መሆን ትችያለሽ፡፡ ይህን ስታደርጊ በዌብ ሣይቱ ላይ አዳዲስ ጽሑፎች ሲጫኑ፣ በኢ-ሜይል አድራሻሽ የማንቂያ መልእክት (notification) የምታገኚ ይሆናል፡፡

   ከዚህ በተጨማሪ የግል ጥያቄዎች ቢኖሩሽ በሚከተለው ኢሜይል ልትልኪልኝ ትችያለሽ፣ በደስታ ለመርዳት ዝግጁ ነኝ (tsegaewnet@gmail.com)፡፡

   የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከአንቺና ቤተሰብሽ ጋር ይሁን። አሜን።

Leave a Reply

%d bloggers like this: