፩. የእግዚአብሔር ሕዝብ ቤተሰባዊ ግንኙነት (1ኛ ጴጥ. 3፡1-7)
እግዚአብሔር እንደሚፈልገን ለመኖር እና የሚደርስብንን ስደትና መከራ ለማሸነፍ የምንችለው ጤናማ ቤተሰባዊ ግንኙነት ካለን ብቻ ነው። ይህም ግንኙነት ከእግዚአብሔር አካል፥ ከወላጆች፥ ከልጆች፥ ከወንድሞችና ከእኅቶች ጋር የሚደረገውን ቤተሰባዊ ግንኙነት ይመለከታል።
- ሚስቶች ለባሎቻቸው መገዛት አለባቸው (1ኛ ጴጥ. 3፡1-6)። ጴጥሮስ ሚስቶች ለባሎቻቸው መገዛት እንዳለባቸው ያስተምራቸዋል። ባሎቻቸው ክርስቲያኖች ባይሆኑም እንኳን መታዘዝ አለባቸው፡፡ ሴቶች መንፈሳዊ ባሕርያትን እንዲያጎለብቱ ይመክራቸዋል። እግዚአብሔር ይህን መልካም ባህሪያቸውን በመጠቀም ባሎቻቸውን ወደ ክርስትና እምነት እንደሚያመጣ ያስተምራል። ክርስቲያን ሴቶች በውጫዊ ውበት ላይ ሳይሆን፥ በውስጣዊ ባህሪያቸው ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።
- ክርስቲያን ባሎች ደጎችና ከሚስቶቻቸው ጋር በማስተዋል አብረው የሚኖሩ መሆን አለባቸው (1ኛ ጴጥ. 3፡7)። ጴጥሮስ በዚህ ክፍል ውስጥ ሚስቶችን እንዴት እንደሚገልጽ ልብ ብለህ ተመልከት።
ሀ) ተካፋዮች ናቸው፡፡ ሚስቶች ባሪያዎች አይደሉም። ወንድ እንደፈለገ የሚጫወትባቸው ንብረቶች አይደሉም። ይልቁንም ትዳሩን የመሠረተውን እግዚአብሔርን ደስ ለማሰኘት አብረው በእኩልነት የሚሠሩ ተካፋዮች ናቸው።
ለ) ሚስቶች ከባሎቻቸው ጋር አብረው የሕይወትን ጸጋ የሚወርሱ ናቸው። ጴጥሮስ የሚናገረው ስለ ድነት (ደኅንነት) እና ዘላለማዊ በረከት ነው። በአገራችን ለወንዶች ልጆች ከሴቶች ልጆች የበለጠ ትኩረት ስለሚሰጣቸው፥ በአብዛኛው ንብረትን የሚወርሱት ወንዶች ናቸው። ሴቶች ግን ምንም አይደርሳቸውም ማለት ይቻላል። እግዚአብሔር ግን ወንዶችንና ሴቶች ልጆቹን የሚመለከተው በዚህ ዓይነት መንገድ አይደለም። እርሱ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ድነትን (ደኅንነትን) እና የዘላለም በረከቶችን እኩል እንዲወርሱ ያደርጋል።
ሐ) “ሴቶች ደካማ ፍጥረቶች ናቸው፡፡” ጴጥሮስ ይህንን ሲል ምን ማለቱ ነው? በሥነ ምግባርና በመንፈሳዊነት ከወንዶች ያነሱ ናቸው ማለቱ ይሆን? ብዙውን ጊዜ ሴቶች ከወንዶች በላይ ለመንፈሳዊ ነገሮች ንቁ ስለሆኑና በቤተ ክርስቲያንም ውስጥ በትጋት ስለሚሳተፉ፥ ጴጥሮስ ይህንን ማለቱ አይመስልም። በአእምሮአቸው ይሆን የደከሙት? አይደለም። ሴቶችም የወንዶችን ያህል የማሰብ ችሎታ ያላቸው ናቸው፡፡ ምናልባትም ጴጥሮስ ሴቶች ደካማ ፍጥረቶች ናቸው ያለው ሁለት ነገሮችን ለማመልከት ይሆናል። በመጀመሪያ፥ ሴቶች በአካላዊ ጥንካሬ ከወንዶች ያነሱ ናቸው። የወንዶችን ያህል ብዙ ጭነት ሊሸከሙ አይችሉም። ሁለተኛ፥ ከሁሉም በላይ በስሜታዊ ጥንካሬ ከወንዶች ያንሳሉ፤ ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ሴቶች ከወንዶች ያነሰ ስሜታዊ ጥንካሬ ይታይባቸዋል።
ይህንን ቤተሰባዊ ግንኙነት ጤናማ አድርጎ መጠበቅ የሚያስፈልገውና በተለይም ባሎች ሚስቶቻቸውን መውደድ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው? ጴጥሮስ በቤት ውስጥ ግንኙነታችን ትክክል ካልሆነ፥ ጸሎታችንን እግዚአብሔር እንደማይመልስ ይናገራል። እግዚአብሔር ጸሎታችንን የማይሰማ ከሆነ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ኃይልን እናጣለን። ይህም ስደትን እንዳንቋቋምና ለኃጢአት ፈተና በቀላሉ እጅ እንድንሰጥ ያደርገናል።
የውይይት ጥያቄ፡– ባለትዳር ከሆንክ፥ ከትዳር ጓደኛ ጋር ያለህን ግንኙነት መርምር፡፡ ትዳር ጴጥሮስ እንዳለው እግዚአብሔርን የሚያስከብር ነውን? ካልሆነ፥ ኩራትህንና ኃጢአትህን ለእግዚአብሔር ተናዘዝ፡፡ ከዚያም ትዕቢትህን ለትዳር ጓደኛህ ተናዘዝ። እግዚአብሔር ጸሎትህን እንዲሰማ የትዳር ችግርህን በፍጥነት አስተካክል።
፪. መልካም በማድረግ መከራን መቀበል (1ኛ ጴጥ. 3፡8-22)።
ስደት ወደ እግዚአብሔር ሕዝብ በሚመጣበት ጊዜ የተለያዩ ነገሮች ይፈትኗቸዋል። እነዚህን ፈተናዎች መቋቋሙ አስፈላጊ ነው። የሚጎዱንን ሰዎች የመጥላትና መበቀል ፈተና ይኖራል። ወይም ደግሞ የሚያሠቃዩንን ሰዎች ለመበቀል ፈተና ይሆንብናል። ከአለማውያን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ላለማድረግ መፈተንም ይኖራል። ጴጥሮስ ክርስቲያኖች ለእነዚህ ፈተናዎች እጃቸውን እንዳይሰጡ ያስጠነቅቃል። ስደትን ከሚያመጡብን ዓለማውያን ጋር በሚኖረን ግንኙነት የሚከተሉትን ነገሮች ልናደርግ እንደሚገባ ይመክረናል፡
- አማኞች ከጎረቤቶቻቸው ጋር በሰላም ለመኖር የሚችሉትን ጥረት ሁሉ ማድረግ ይኖርባቸዋል።
- ክርስቲያኖች ለጎረቤቶቻቸው ትሕትናን፥ ርኅራኄንና ፍቅርን ማሳየት ይኖርባቸዋል።
- የእግዚአብሔር ልጆች ጎረቤቶቻቸው በሚያሳድዱአቸው ጊዜ ሊበቀሏቸው፥ ወይም ሊሰድቧቸው አይገባም። ይልቁንም ክርስቲያኖች እርዳታ መጠየቅ የሚኖርባቸው ከእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው።
- ክርስቲያኖች በልባቸው ክርስቶስን ሊቀድሱት ይገባል። ዓለም ከምትጠብቀው የተለየ ሕይወት ለመምራት መቁረጥ ይኖርብናል። ይህንን ልናደርግ የምንችለው ክርስቶስን የሕይወታችን ጌታና ንጉሥ ስናደርገው ነው። እንዲሁም በባህላችን ወይም በደመ ነፍሳችን ተመርተን ለበቀል ከመነሣሣት ይልቅ በሁሉም ነገር ክርስቶስን ስንታዘዘው ነው።
- ክርስቲያኖች በእነርሱ ስላለ ተስፋ ምክንያትን ለሚጠይቋቸው ሁሉ መልስ ለመስጠት ዘወትር የተዘጋጁ ሊሆኑ ይገባል። ጴጥሮስ ይህን ሲል ዓለም ከሚጠብቀው በተለየ መንገድ ለሁኔታዎች ምላሽ በምንሰጥበት ጊዜ ሰዎች እንደሚደነቁ መግለጹ ነው። በዚህም ጊዜ ወደ አማኞች መጥተው ለምን ልንለይ እንደቻልን ይጠይቁናል። በዚህም ጊዜ ክርስቲያኖች ክርስቶስ ስለሰጣቸው ተስፋ ለመመስከር መዘጋጀት አለባቸው። ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ዓለማውያንን በቃላቸው ዝብዘባ ለማሳመን ይሞክራሉ። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ የክርስቲያንም የዓለማዊውም ተግባር ተመሳሳይ ነው። እኛ ክርስቲያኖቹ እንደ ዓለማውያኑ የተከፋፈልን፥ የምናጭበረብር፥ ጉቦ የምንሰጥ፥ እንዲሁም የሚጎዱንን ሰዎች የምንበቀል ሆነናል። በመሆኑም፥ ብዙ ዓለማውያን ሊሰሙን አይፈልጉም፥ ምክንያቱም የእነርሱም የእኛም ሕይወት ተመሳሳይ ነውና። ጴጥሮስ በፍቅር፥ በገርነትና በከበሬታ እየተመላለስን መንፈሳዊ ሕይወት የምንኖር ከሆነ፥ ብዙውን ጊዜ የሚያሳድዱን ዓለማውያን በሥራቸው እንደሚያፍሩ ይናገራል። ከዚያም በክርስቶስ አምነው የእኛን ደስታ፥ ሰላምና መንፈሳዊ ሕይወት ይጋራሉ።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በአሁኑ ጊዜ ክርስቲያኖች ለስደት ምላሽ የሚሰጡት ጴጥሮስ ባስተማረው መንገድ ነውን? ለ) አንድ አማኝ በስደትና በመከራ በሰጠው መልካም ምላሽ ምክንያት እግዚአብሔር ብዙ ሰዎችን ወደ ክርስቶስ ያመጣበትን ሁኔታ ጥቀስ። ሐ) የአማኞች ትክከለኛ ያልሆነ ተግባርና አመለካከት ሰዎችን ከወንጌል ስላገለለበት ሁኔታ ምሳሌዎችን ስጥ።
ጴጥሮስ ክርስቶስ ስደትን ስለምንቀበልበት ሁኔታ መልካም ምሳሌአችን መሆኑን ይናገራል። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡17-22 በአዲስ ኪዳን ውስጥ ለመረዳት ከሚያዳግቱን ምንባቦች አንዱ ነው። በዚህ ስፍራ ጴጥሮስ ለማስተላለፍ የሚፈልገውን መልእክት ለመረዳት ከመሞከራችን በፊት የዚህን ክፍል ዋነኛ ትምህርት መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል። በ1ኛ ጴጥሮስ 2፡18-25 ክርስቶስ ምንም ኃጢአት ሳይሠራ መከራ እንደ ተቀበለና እንደ ሞተ እኛም ኃጢአት ሳንሠራም እንኳን በክርስቶስ ላይ ላለን እምነት መከራን መቀበልና መሞት እንዳለብን አስረድቷል። 1ኛ ጴጥሮስ 3፡17-22 በድጋሚ ወደ ክርስቶስ ምሳሌነት ይመለከታል። በዚህ ጊዜ ግን ጴጥሮስ ከክርስቶስ ሞት በኋላ ስለተፈጸመው ነገር ይናገራል። ክርስቶስ መከራ ተቀብሎ ቢሞትም፥ እንደ ሞተ አልቀረም። እግዚአብሔር ከሞት አስነሥቶ በክብርና በሥልጣን መቀመጫ በቀኙ አስቀምጦታል። እግዚአብሔር ለክርስቶስ ፍትሕ በመስጠቱ የማይታዘዙ መናፍስትን ጨምሮ ከሁሉም በላይ አክብሮታል።
በተመሳሳይ ሁኔታ አማኞች መከራ ተቀብለው ቢሞቱም፥ ይህ ግን ፍጻሜአቸው አይሆንም። ከሞት ተነሥተው ወደ ሰማይ ይገባሉ፡፡ በዚህም ጊዜ እግዚአብሔር ፍትሕን ይሰጣቸዋል። ምክንያቱም እግዚአብሔር በኖኅ ዘመን በዓለም ላይ ያመጣውን ፍርድ የሚመስል የፍርድ ቀን እየመጣ ነው፡፡ እግዚአብሔር በኖኅ ዘመን ሰዎችን በኃጢአታቸው አለመቅጣቱ ፍትሐዊ መስሎ እንዳልታየ ሁሉ፥ ዛሬም እግዚአብሔር ሰዎች ለእምነታቸው መከራ እንዲቀበሉ ማድረጉ ፍትሐዊ ላይመስል ይችላል። ነገር ግን እግዚአብሔር በኖኅ ዘመን ሰዎች ከኃጢአታቸው ንስሐ እንዲገቡና ከጥፋትም እንዲድኑ ለ120 ዓመታት በትዕግሥት ሲጠብቃቸው ቆይቷል። በመጨረሻም በምድር ላይ ከነበሩት በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ሰዎች 8 የኖኅ ቤተሰቦች ብቻ ሊድኑ በቅተዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ እግዚአብሔር ለልጆቹ ፍትሕን በመስጠት በዓለም ውስጥ ያሉትን ክፉ ሰዎች የማያጠፋው ንስሐ ገብተው በክርስቶስ እንዲያምኑ ዕድል ለመስጠት ነው። አንድ ቀን ግን የእግዚአብሔር ትዕግሥት ያልቅና ለልጆቹ ፍትሕን ይሰጣል። የሚያሳዝነው እንደ ኖኅ ዘመን በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ዓላማውያን መካከል ድነት (ደኅንነት)ን የሚያገኙ ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። እግዚአብሔር በስደት ውስጥ እያሉ ምላሽ ባለመስጠቱና ፍትሕን ባለማምጣቱ ተስፋ ቆርጠው በራሳቸው እጅ ለመበቀል ከሚነሣሱ፥ እንደ ኖኅ እግዚአብሔርን በመተማመን በትዕግሥት ሊጠብቁት ይገባል። እግዚአብሔር በጊዜው ፍትሕን ይሰጣቸዋል። ምክንያቱም ምሳሌአቸው የሆነው ክርስቶስ በሰዎችም ሆነ በመናፍስትም ላይ ሥልጣን አለው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እግዚአብሔር አንድ ቀን የሚያሳድዱን ሰዎች ንስሐ ገብተው የማያምኑ ከሆነ ወደ ፍርድ የሚያቀርባቸው የመሆኑ ሁኔታ ዛሬ ስደትን በትዕግሥት እንድንቀበል የሚያስችለን እንዴት ነው? ለ) ከዚህ ክፍል ስለ እግዚአብሔር ባህሪ እና ፍላጎት፥ እንዲሁም ስለ ክርስቶስ ኃይል ምን እንማራለን?
ጴጥሮስ ክርስቶስ ከሞተ በኋላ የተከሰቱትን አንዳንድ ነገሮች ጠቅለል አድርጎ ያቀርባል።
- ክርስቶስ ቢሞትም ተነሥቷል።
- ክርስቶስ ከረጅም ጊዜ በፊት ላልታዘዙት መናፍስት በወኅኒ ሰብኮላቸዋል። ይህ ለመረዳት የሚያስቸግር ምንባብ ነው። ከዚህ ክፍል፥ ሀ) ክርስቶስ መቼ እንደ ሰበከ መረዳቱ አስቸጋሪ ነው። ይህ የሆነው ክርስቶስ ከሞተ በኋላና ከመነሣቱ በፊት ነው? ከተነሣ በኋላ ነው? ወይስ ቀደም ሲል በኖኅ ዘመን ነበር? ለ) መናፍስት የተባሉት እነማን ናቸው? የወደቁ መላእክት ወይስ የሞቱ ሰዎች? ሐ) የቀረበው ስብከት ምን ነበር? ድነት (ደኅንነት)፥ ፍርድ ወይስ የድል አዋጅ?
ሰዎች ይህንን ክፍል በተለያዩ መንገዶች ተረድተዋል። ከእነዚህም መካከል ሦስቱ ዐበይት አተረጓጎሞች የሚከተሉት ናቸው።
- አንዳንድ ምሁራን ይህ ክፍል ክርስቶስ ከመሞቱ በፊት የነበረውን ሁኔታ ያመለክታል ይላሉ። ክርስቶስ በኖኅ ምስክርነት ውስጥ በኖኅ ዘመን የነበሩት ኃጢአተኞች ንስሐ ገብተው እንዲመለሱ ሰብኳል ሲሉ ያስተምራሉ። ይህ ለክፍሉ አሳብ የሚቀርብ አተረጓጎም አይመስልም።
- ሌሎች ምሁራን ደግሞ ክርስቶስ ከሞተ በኋላ እና ከመነሣቱ በፊት የሞቱ መናፍስት ወይም የሞቱ ሰዎች ወደሚኖሩበት ስፍራ እንደ ወረደ ይናገራሉ። በዚያም በጥፋት ውኃ ወቅት ለሞቱት ሰዎች ሰበከላቸው። ለእነዚህም ሰዎች ወንጌልን ወይም ደግሞ በአዳኝነት ያገኘውን ድል፥ እንዲሁም ባለማመናቸውና በአመፃቸው ምክንያት የጠፉ መሆናቸውን ገልጾአል።
- ሌሎች ምሁራን ደግሞ ጴጥሮስ በኖኅ ዘመን የእግዚአብሔር ልጆች የተባሉ መላእክት የሰዎች ሴቶች ልጆች ከተባሉት ሰብአዊ ፍጡራን ጋር የወሲብ ኃጢአት መፈጸማቸውን እንደሚያመለክት ይናገራሉ (ዘፍጥ. 6፡1-4)፥ መሳ. 6፤ 2ኛ ጴጥ. 2፡4)። እግዚአብሔር እነዚህን መላእክት በፍርድ ወደ ጥልቁ ጉድጓድ (ወኅኒ) ላካቸው፥ በዚያም በመጨረሻው ዘመን የሚመጣውን የፍጻሜ ፍርድ ይጠባበቃሉ። ይህን አሳብ የሚያቀርቡ ምሁራን ክርስቶስ ከሞተ በኋላና ከመነሣቱ በፊት ወደዚህ ጉድጓድ ወርዶ በሰይጣንና በክፉ መላእክት ሁሉ ላይ ድል መቀዳጀቱን እንዳወጀ ያስረዳሉ። (አንዳንድ ምሁራን እነዚህ የወደቁ መላእክት ሁሉንም ክፉ መናፍስት ወይም አጋንንት በተምሳሌትነት እንደሚያሳዩ ይናገራሉ)። በመሆኑም ክርስቶስ በትንሣኤው ወቅት በእነርሱ ላይ ድል መቀዳጀቱንና የተሸነፉ ጠላቶች መሆናቸውን ገልጾላቸዋል። (ቆላ. 2፡15 አንብብ።]
ጴጥሮስ እነዚህን በወኅኒ ያሉትን መናፍስት የጠቀሰው በእግዚአብሔር በቀል ከሞት የተነሣው ክርስቶስ ምን ያህል ታላቅ ኃይል እንዳለው ለማሳየት ሳይሆን አይቀርም። ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ በሰዎችና በመንፈሳውያን ፍጥረታት ሁሉ ላይ ሥልጣንና ኃይል አለው (ቆላ. 2፡15)። የክርስቶስ ኃይል እና ሥልጣን እጅግ ታላቅ በመሆኑ በኖኅ ዘመን በእግዚአብሔር ላይ ባመፁት በእነዚህ ክፉ መናፍስት እና መንፈሳዊ ፍጥረታት ላይ የተቀዳጀውን ሥልጣን ገልጾአል።
ጴጥሮስ የኖኅን ዘመን ክፋት በጠቀሰ ጊዜ፥ በዘመኑ የነበሩት አማኞች ሁኔታ ኖኅ ከነበረበት ጊዜ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን አጢኗል። እንዲሁም በጥፋት ውኃና በጥምቀት ውኃ መካከል ያለውን አንድነት ተረድቷል። ጴጥሮስ በዚህ ስፍራ ለማስተላለፍ የሚፈልገውን መልእክት መረዳቱ አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም ይህን ክፍል በተሳሳተ መንገድ የተረዱ ክርስቲያኖች ሰውን የሚያድነው የውኃ ጥምቀት ነው የሚለውን አሳብ ስለሚጠቀሙበት ነው፡፡ (ማስታወሻ፡— በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጥምቀት ሰውን ሊያድን እንደሚችል የሚያሳይ ብቸኛው ጥቅስ ይሄ ብቻ ነው። ጥምቀት ሰውን የሚያድን ቢሆን ኖሮ እግዚአብሔር በሌሎች የአዲስ ኪዳን ምንባቦች ውስጥ በግልጽ ባሠፈረው ነበር።) የሚታየው የውኃ ጥምቀት ማንንም እንደማያድን አዲስ ኪዳን በግልጽ ይናገራል። አለዚያማ፥ ድነት (ደኅንነት) እኛ የምናደርገው ተግባር ይሆን ነበር። ጳውሎስ ግን በሮሜ፥ ገላትያ፥ እንዲሁም ኤፌሶን መልእክቶች ውስጥ ድነት (ደኅንነት) በክርስቶስ በማመን የሚገኘው የእግዚአብሔር ነፃ ስጦታ መሆኑን አመልክቷል። (ለምሳሌ፥ ኤፌ. 2፡8-9 አንብብ)። በሌሎች የአዲስ ኪዳን ክፍሎች ጥምቀት የሚጠቀሰው ከንስሐ ወይም ከእምነት ቀደም ብሎ ነው። (ለምሳሌ፥ የሐዋ. 2፡38)። ጴጥሮስ የውኃ ጥምቀት ድነትን ያስገኛል ማለቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ምክንያቱም ጥምቀት ከሰውነት ላይ እድፍን ማስወገድ ሳይሆን፥ ሕሊናን ማንጻት እንደሆነ ያስረዳል። ውኃ ኃጢአትን ሊያጥብ አይችልም። ይህን ሊያደርግ የሚችለው በክርስቶስ ኢየሱስ ላይ ያለን እምነት ብቻ ነው።
ጴጥሮስ ጥምቀት ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ ለመረዳት የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ይህን ቃል እንዴት እንደ ተረዳች ማወቁ ጠቃሚ ነው። ለእኛ ጥምቀት ማለት አንድ እማኝ የሚያደርገው ተግባር ነው። ብዙውን ጊዜ አማኞች በክርስቶስ ካመኑ ከ3-6 ወራት መንፈሳዊ ትምህርት ከተከታተሉ በኋላ፥ ከክርስቶስ ላለመለየት እና የቤተ ክርስቲያን አባል ለመሆን የሚፈልጉ መሆናቸውን ለማሳየት የውኃ ጥምቀት ይወስዳሉ። አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ሕጻናትን ያጠምቃሉ። ይህም የእግዚአብሔር ቤተሰብ አባላት መሆናቸውን ለማሳየት የሚወስዱት እርምጃ ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ግን ጥምቀት የተገለጸው ለየት ባለ ሁኔታ ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ሰዎች የሚጠመቁት በክርስቶስ እንዳመኑ ወዲያውኑ ነው (የሐዋ. 8፡36-39፤ 16፡30-33 አንብብ)። ጆሲፈስ የተባለው አይሁዳዊ ጸሐፊ ከጴጥሮስ ዘመን ትንሽ ዘግየት ብሎ ሲጽፍ ሰዎች ወደ መጥምቁ ዮሐንስ ለመጠመቅ የሚመጡት የጽድቅ ኑሮ ለመምራት ሰዎችን በፍትሕ ለማስተናገድና በእግዚአብሔር ፊት የተቀደሰ ኑሮ ለመምራት፥ በዚሁም የጥምቀቱ ተካፋይ ለመሆን በመወሰን ነው ብሏል። የክርስትና ጥምቀት የመጥምቁ ዮሐንስን ጥምቀት ምሳሌነት የተከተለ ነው። በመሆኑም የቀድሞዎቹ አማኞች በሚጠመቁበት ጊዜ ውኃው እንደሚያድናቸው አያስቡም ነበር። ነገር ግን ይህ በልባቸው ውስጥ የተፈጸመውን ነገር በይፋ የሚገልጹበት መንገድ ነበር። ክርስቲያኖች ሲጠመቁ በክርስቶስ ማመናቸውን ያሳያሉ። ከዚህም በኋላ ክርስቶስን በጽድቅ፥ በተቀደሰ ሕይወትና ከሌሎች ጋር እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ግንኙነት በማድረግ ለመከተል ይወስናሉ።
የውይይት ጥያቄ፡- የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖችና የዛሬዎቹ ክርስቲያኖች ስለ ጥምቀት ያሉዋቸውን አመለካከቶች እነጻጽር። ልዩነቶቻቸውና አንድነቶቻቸው ምን ምንድን ናቸው?
ጴጥሮስ በዚህ ስፍራ ለማስተላለፍ የፈለገው መልእክት ምንድን ነው? ጴጥሮስ በኖኅ ዘመን የተፈጠረውን ሁኔታ ክርስቲያኖች ከሚያልፉበት ሁኔታ ጋር ያነጻጽረው ነበር። ሁለቱም የኖሩት በክፉ ዘመን ውስጥ ነበር። በሁለቱም ጊዜያት፥ እግዚአብሔር ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ እየተጠባበቀ ቅጣትን አዘግይቷል። በሁለቱም ጊዜያት፥ እግዚአብሔር የኋላ ኋላ ኃጢአተኞችን ቀጥቷል። በሁለቱም ጊዜያት፥ በአንጻራዊነት ጥቂት ሰዎች ብቻ ድነዋል። በሁለቱም ጊዜያት፥ እግዚአብሔር ሰዎችን ለማዳን ውኃን ተጠቅሟል።
በኖኅ ዘመን የጥፋት ውኃ በክፉ ሰዎች ላይ የእግዚአብሔርን ፍርድ ከማምጣቱም በላይ፥ ድነትንም (ደኅንነትም) እንዳስገኘ ጴጥሮስ ገልጾአል። እግዚአብሔር ውኃውን ተጠቅሞ መርከቢቱ ወደ ላይ ከፍ እያለች ያለ ስጋት እንድትሄድ አድርጓታል። ስለ ጥፋት ውኃው ማሰብ ጴጥሮስ የጥምቀት ውኃንም ጉዳይ እንዲያነሣ አድርጎታል። ጥምቀት በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ የተፈጸመውን ነገር ሁሉ በተምሳሌትነት ያሳያል። አማኞች በክርስቶስ በማመናቸው፥ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ ለመኖር በመቁረጣቸውና በጥምቀት እምነታቸውን በይፋ በመግለጻቸው፥ እግዚአብሔር ከዚህ ክፉ ዓለም አድኗቸዋል።
መንፈስ ቅዱስ በልባችን ላይ ስላለው ኃጢአት በሚወቅሰን ጊዜ እንደ ኖኅ የእምነት ምላሽ መስጠት አለብን፡፡ እራሳችንን ለእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች ማስገዛት ይኖርብናል። ለኖኅ፥ ይህ መርከብ መሥራትንና ዝናብ ከመውረዱ በፊት ወደ መርከቢቱ መግባቱን ያጠቃልል ነበር። ለእኛ ደግሞ፥ ክርስቶስ በእኛ ፈንታ መሞቱ እንደሚያድነን ማመንንና በክርስቶስ የተስፋ ቃሎች መመላለስን ይጠይቃል። ጥምቀት ለድነታችን (ለደኅንነታችን) በክርስቶስ እንደምናምን የሚያሳይ ውጫዊ ተምሳሌት ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንዳንድ ክርስቲያኖች ድነት (ደኅንነት) ከመጠመቅ እንደሚገኝ ሲያስተምሩ ሰምተህ ታውቃለህ? ለ) እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ወንጌል ከእግዚአብሔር የምንቀበለው ስጦታ ሳይሆን ራሳችን የምናከናውነው ተግባር መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው? ሐ) እላይ የቀረበውን ማብራሪያ በመጠቀም፥ ጴጥሮስ ስለ ጥምቀትና ድነት (ደኅንነት) ያቀረበውን አሳብ እንዴት ትገልጻለህ?
ጴጥሮስ ውኃ ለኖኅና ለአማኞች ያስገኘውን ድነት (ደኅንነት) ካነጻጸረ በኋላ፥ አማኞች የክርስቶስን ምሳሌነት በመከተል ለሚደርስባቸው መከራ እንዴት መልስ ሊሰጡ እንደሚገባ ያስረዳል። የክርስቶስ ትንሣኤ አማኞች የኋላ ኋላ ከሞት እንደሚነሡና ድነት እንደሚቀዳጁ ዋስትና ይሰጣል። ክርስቶስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ ከእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦአል። በዚያም ሰዎችም ሆኑ መላእክት ከሥልጣኑ ሥር ይሆናሉ። ክርስቶስ በሰይጣን ላይ ሥልጣን ስላለው በአማኞች ሕይወት ውስጥ ስደትንና መከራን በማምጣት ሊያከናውን የሚፈልጋቸውን ተግባራት ይገድባል። ክርስቶስ ብዙውን ጊዜ የእግዚአብሔርን ልጆች በሚያሳድዱበት የመንግሥታት መሪዎችና የማያምኑ ሰዎች ላይ ሥልጣን አለው። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ እግዚአብሔር ስደትን ለተቀበሉት ክርስቲያኖች ፍትሕን የሚሰጥበት ቀን ይመጣል። በጠላቶቻቸው ላይ ሥልጣን ተቀዳጅተው ከክርስቶስ ጋር ይነግሣሉ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)