የ1ኛ ዮሐንስ መግቢያ

ተስፋዬ ዝነኛ ሰባኪና የኮንፍራንስ ተናጋሪ ነበር። እርሱ በሚሰብክበት ጊዜ ብዙ ሰዎች ያምኑ ነበር። ብዙ ሰዎችም በትምህርቱ ይባረካሉ። ተስፋዬ መንፈሳዊ ሰው መስሎ ይታይ ነበር። ነገር ግን ይህ አገልጋይ ሌላ ማንም ሰው የማያውቀው ምሥጢር ነበረው። ዝሙት እየፈጸመ ነበር የሚኖረው። ከጊዜ በኋላ የተስፋዬ ሕይወት እየተለወጠ ይሄድ ጀመር። በወንጌላዊነቱና ሰባኪነቱ ይኩራራ ጀመር። እርሱ የተናገራቸውን ነገሮች የማያከናውኑትን የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ይተችና መንፈሳዊ አለመሆናቸውን ይናገር ጀመር። በመጨረሻም በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ክፍፍል አመጣ። ወጣቶች በአድናቆት ይከተሉት ስለነበር፥ ብዙዎችን ከቤተ ክርስቲያናቸው አስወጥቶ የራሱን ቤተ ክርስቲያን መሠረተ። ታሞ ከሞተ በኋላ ነበር ሰዎች የኃጢአት ሕይወቱን ሊያውቁ የቻሉት። በዚህ ጊዜ ግን ብዙዎች ከእውነት መንገድ ፈቀቅ ብለው ሄደው ነበር።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አማኞች መንፈሳዊያን መስለው እየታዩ በሕይወታቸው ውስጥ ኃጢአትን ሲጠብቁ የተመለከትክበትን ሁኔታ ግለጽ። ለ) ብዙውን ጊዜ የተደበቀው ኃጢአታቸው ከጊዜ በኋላ ይፋ የሚወጣው እንዴት ነው? ሐ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አንድ ነገር እየሰበኩ ተቃራኒ ሕይወት በሚኖሩበት ጊዜ በቤተ ክርስቲያንና በወንጌል ስብከት ላይ የሚመጣው ጉዳት ምንድን ነው?

ሐዋርያው ዮሐንስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚፈጸም አንድ ችግር ሳቢያ አሳብ ገብቶት ነበር። ክርስቶስን እንከተላለን እያሉ የሚመላለሱ ሰዎች ነበሩ። በእነዚህ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ድብቅና የተገለጡ ኃጢአቶች ይታዩ ነበር። እነዚህ አማኞች፥ «እግዚአብሔርን የሚያሳስበው በክርስቶስ ማመናችን እንጂ አኗኗራችን አይደለም። የክርስቶስ ጸጋ ኃጢአታችንን ይሸፍነዋል። ማድረግ ያለብን ነገር ቢኖር የእግዚአብሔር ይቅርታ መጠየቅና እንደተለመደው ኑሮአችንን መግፋት ነው» ይሉ ነበር። ዮሐንስ ለእነዚህ ሰዎች ምላሽ ሲሰጥ፥ «ከእርሱ ጋር ኅብረት አለን ብለን በጨለማም ብንመላለስ እንዋሻለን። እውነትም አናደርግም» ብሏል።

ዛሬ በአብያተ ክርስቲያኖቻችን ውስጥ ከሚታዩት አደገኛ ነገሮች አንዱ በርካታ ሰዎች መንፈሳውያን መስለው መታየት መሞከራቸው ነው። እነዚህ ሰዎች ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችና የጸሎት ስብሰባዎች ይነጉዳሉ፥ በልሳን ይናገራሉ፥ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ይጸልያሉ፥ በግል ሕይወታቸው ግን የተደበቀ ኃጢአት ይለማመዳሉ። ወደ ሴተኛ አዳሪዎች የሚሄዱ ወይም ከጋብቻ ውጭ ዝሙት የሚፈጽሙ መጋቢያን አሉ። ወጣቶች፥ የመዘምራን ቡድን አባላት ላይቀር ጋብቻ ሳይመሠርቱ ወሲብ ይፈጽማሉ። ብዙዎች የመዋሸት፥ የመስረቅ፥ የቁጣ፥ የጥላቻ፥ ወዘተ… ኃጢአቶችን በሕይወታቸው ውስጥ ያስተናግዳሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ጣምራ ሕይወትን «ግብዝነት» ሲል ይጠራዋል። ግብዝነት ሁለት ዓይነት ሕይወቶችን የመኖር ኃጢአት ነው። በአማኞች ፊት አማኞች መንፈሳውያን መስለው ይታያሉ። በግል ኑሮአቸው ወይም ከማያምኑ ሰዎች ጋር እግዚአብሔርን በማያስከብር መንገድ የተለየ ሕይወት ይኖራሉ። ግብዝነት ሥውር ኃጢአት በመሆኑ ለመመልከትም ሆነ ለማስወገድ አስቸጋሪ ነው። ነገር ግን ዓለም በግልጽ ያየዋል። ከዚህም የተነሣ ሰዎች መጋቢዎችንና የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን እያከብሯቸውም። እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ያለውን ኃጢአት በማስወገድና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስንሆን ነን የምንለውን ዓይነት ሕይወት በመኖር በፍርሃት እንድንመላለስ ይጠራናል።

የውይይት ጥያቄ፡- ስለ 1ኛ ዮሐንስ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንብብ። በመዝገበ ቃላት ውስጥ ስለ ጸሐፊው ስለ አንባቢዎቹ እና ስለ መጽሐፉ ዓላማ የተገለጸውን ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።

የ1ኛ ዮሐንስ ጸሐፊ

የውይይት ጥያቄ፡- 1ኛ ዮሐንስ 1፡1 አንብብ። ሀ) ይህ ጥቅስ ስለ ጸሐፊው ምን ይላል? ለ) የመልእክቱ አንባቢዎች እነማን ናቸው? የተገለጹበት ሁኔታ ምን ይመስላል? ሐ) ይህ እስከ አሁን ካጠናናቸው መልእክቶች ለየት የሚለው እንዴት ነው?

ቀደም ሲል ካጠናናቸው መልእክቶች በተለየ ሁኔታ የ1ኛ ዮሐንስ መልእክት የጸሐፊውንና የመልእክቱን ተቀባዮች ማንነት አይጠቅስም። ጸሐፊው የተለመደውን የደብዳቤ አጻጻፍ ስልት አልተከተለም። በመሆኑም፥ ብዙ ምሁራን ይህ መልእክት ደብዳቤ ላይሆን ትራክት ወይም አነስተኛ የማስተማሪያ መጽሐፍ እንደሆነ ይናገራሉ። ምሁራን የጸሐፊውን ማንነት ለማወቅ ሌሎች ፍንጭ የሚሰጡ መረጃ ዎችን ይጠቀማሉ።

በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የ1ኛ ዮሐንስ መልእክት ጸሐፊ ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሆነ ይታመናል። ለዚህም ምክንያቱ፥

ሀ) ጸሐፊው ክርስቶስን እንዳየ ይናገራል (1ኛ ዮሐ 1፡1-4)

ለ) ከ150 ዓም በኋላ፥ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በሙሉ የ1ኛ ዮሐንስ መልእክት ጸሐፊ ሐዋርያው ዮሐንስ መሆኑን መስክረዋል።

ሐ) በ1ኛ ዮሐንስና በዮሐንስ ወንጌል መካከል ብዙ ተመሳሳይነቶች ይታያሉ። ሁለቱም ነገሮች በማነጻጸር ላይ ያተኩራሉ (ለምሳሌ፥ ብርሃንና ጨለማ፥ ሕይወትና ሞት፥ እውነትና ውሸት፥ ፍቅርና ጥላቻ)። ብዙ ተመሳሳይ አገላለጾችም በሁለቱ መጻሕፍት ውስጥ ይታያሉ (ለምሳሌ፥ የሚከተሉትን ጥቅሶች አነጻጽር። 1ኛ ዮሐ. 1፡1 እና ዮሐ 1፡1፥ 14፤ 1ኛ ዮሐ 1፡4 እና ዮሐ. 16፡24፤ 1ኛ ዮሐ 3፡14 እና ዮሐ 5፡24፤ 1ኛ ዮሐ 5፡14 እና ዮሐ 3፡36)፡፡ ስለሆነም ሁለቱም መጻሕፍት የጻፈው አንድ ጸሐፊ መሆኑ ግልጽ ነው። የዮሐንስን ወንጌል በምናጠናበት ጊዜ እንደተመለከትነው፥ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ሁሉም ፍንጮች ሐዋርያው ዮሐንስ የመጽሐፉ ጸሐፊ መሆኑን ያመለክታሉ። ይህም ሐዋርያው ዮሐንስ የ1ኛ ዮሐንስ መልእክት ጸሐፊ መሆኑን ያጠናክራል።

መ) ጸሐፊው እንደ ሐዋርያ ሁሉ መልእክቱን በሥልጣን ይጽፋል። አንዳንድ ምሁራን የ1ኛ ዮሐንስ መልእክት የጻፈው ሽማግሌው ዮሐንስ የተባለ ያልታወቀ የቤተ ክርስቲያን መሪ ነው ይላሉ። ነገር ግን የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ሐዋርያው ዮሐንስ እንደ ጻፈው በመግለጽ ያቆዩትን ትውፊት ላለመቀበል የሚያበቃ ምክንያት የለንም።

የውይይት ጥያቄ፡- በመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ውስጥ ለለ ሐዋርያው ዮሐንስ 1 የተጻፈውን አንብብ። ስለ ሕይወቱ የተሰጠውን መረጃ ጠቅለል አድርህ ጻፍ።

ሐዋርያው ዮሐንስ ከዘብዴዎስና ሰሎሜ ልጆች አንዱ ነበር። የያዕቆብም ታላቅ ወንድሙ ነበር። የዮሐንስ እናት የሆነችው ሰሎሜ እና የክርስቶስ እናት የሆነችው ማርያም እኅትማማቾች እንደነበሩ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። ይህም ያዕቆብና ዮሐንስ ከክርስቶስ ጋር የእኅትማማቾች ልጆች መሆናቸውን ያሳያል። ዮሐንስና ያዕቆብ በገሊላ ባህር ዳርቻ ባለው የገሊላ አውራጃ ክፍል ያደጉና ዓሣ በማጥመድ ሙያ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ነበሩ። ዘብዴዎስ ሀብታም ዓሣ አጥማጅ ይመስላል። ምክንያቱም ከአንድ የሚበዙ ጀልባዎችና ቅጥር ሠራተኞች ነበሩት። ታዳጊ ወጣት ሳለ ይመስላል፥ ዮሐንስ ስለ መጥምቁ ዮሐንስ ዝና ሰምቶ ወደ ይሁዳ ተጓዘ። በዚያም የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር ሆነ። ዮሐንስ ከመጥምቁ ዮሐንስ ተለይቶ ክርስቶስን መከተል የጀመረው መጥምቁ ዮሐንስ «የእግዚአብሔር በግ ይህ ነው» ሲል በመሰከረበት ወቅት ነበር። ዮሐንስ ለአጭር ጊዜ ከክርስቶስ ጋር ከቆየ በኋላ ወደ አባቱ ተመልሶ ዓሣ የማጥመዱን ተግባር ያከናውን ጀመር። ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቶቹ እንዲሆኑ የመረጣቸውን እርሱና ወንድሙ ያዕቆብ ከአባታቸው ጋር ዓሣ እያጠመዱ ሳለ ነበር በኋላም ዮሐንስ ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ሆኖ ተመረጠ። በተጨማሪም፥ ዮሐንስ ክርስቶስ ለየት ላለ ሥልጠና ከሚወስዳቸው ሦስት ደቀ መዛሙርት አንዱ ለመሆን በቃ (ለምሳሌ፥ የሞተችውን ልጅ ባስነሣ ጊዜ፥ ማር. 5፡37)። የዮሐንስ ወንጌል ዮሐንስ ከክርስቶስ ጋር የቀረበ ግንኙነት እንደነበረው ያመለክታል። ዮሐንስ «ጌታ ይወደው የነበረ ደቀ መዝሙር» ተብሎ ይጠራ ነበር። በመጨረሻው እራት ላይ ከክርስቶስ አጠገብ በክብር ስፍራ ላይ ተቀምጦ ነበር። ዮሐንስና ያዕቆብ የነጎድጓድ ልጆች ተብለው ይጠሩ ነበር። ይህም ጠንካራ ባህሪያቸውንና ብስጩነታቸውን የሚያሳይ ሳይሆን አይቀርም። አንድ ጊዜ ሳምራውያን መልካም መስተንግዶ ስላላደረጉላቸው ከሰማይ እሳት ወርዶ እንዲበላቸው ለመጠየቅ ፈልገው ነበር (ሉቃስ 9፡54)። እንዲሁም በክርስቶስ መንግሥት ውስጥ ቁልፍ መሪዎች ለመሆን ፈልገው ነበር (ማር. 10፡35-45)። ክርስቶስ ካረገ በኋላ፥ ዮሐንስ፥ በቀድሞይቱ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከነበሩት ዐበይት መሪዎች አንዱ፥ ምናልባትም ከጴጥሮስ ቀጥሎ ሁለተኛ መሪ ሳይሆን አይቀርም። ከመንፈስ ቅዱስ መምጣት በኋላ የመጀመሪያውን ተአምር ከጴጥሮስ ጋር አብሮ አከናውኗል (የሐዋ. 3)። የሰማርያን አማኞች ሁኔታ ለማጣራትም ከኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ከጴጥሮስ ጋር ተልኮ ሄዷል። ለቀጣይ 60 ዓመታት በዮሐንስ ላይ ስለደረሰው ሁኔታ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የሚነግረን ነገር የለውም። ምናልባትም በ68 ዓመተ ምሕረት እስራኤል ከሮማውያን ጋር ጦርነት በገጠመችበት ወቅት ስፍራውን ለቅቆ ለመሄድ እስከተገደደበት ጊዜ ድረስ ዮሐንስ በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሲያገለግል የቆየ ይመስላል። ከዚህ ጊዜ በኋላ በትንሹ እስያ ውስጥ ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት ለማገልገል ወደ ኤፌሶን እንደ ተጓዘ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይናገራል። ዮሐንስ ወደ ሕይወቱ መጨረሻ አካባቢ ታስሮ ወደ ፍጥሞ ደሴት ተጉዟል። በዚያም ዮሐንስ ራእይን መጽሐፍ ሊጽፍ በቅቷል። በመጨረሻም ከእስራቱ ተፈትቶ ወደ ኤፌሶን ከተመለሰ በኋላ፥ ከ95-100 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በጣም አርጅቶ አርፎአል።

ዮሐንስ መልእክቱን የጻፈው ለማን ነበር?

ቀደም ብለን እንደተመለከትነው፥ መልእክቱ ለማን እንደ ተጻፈ በግልጽ አይናገርም። ይህ መልእክት በአጠቃላይ ለአማኞች እንደ ተጻፈ ግልጽ ነው። ለዚህም ነው ምሁራን ከአጠቃላይ መልእክት ውስጥ የሚመድቡት። ምናልባትም የ1ኛ ዮሐንስ መልእክት ከቤተ ክርስቲያን ወደ ቤተ ክርስቲያን እየተላለፈ የሚነበብ ተዘዋዋሪ መልእክት ሳይሆን አይቀርም። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዮሐንስ በኤፌሶን ከተማ ይኖር እንደነበር ስለሚያመለክት፥ ምናልባትም መልእክቱን የጻፈው ከሥልጣኑ ሥር ለነበሩት የትንሹ እስያ አብያተ ክርስቲያናት ሳይሆን አይቀርም። ከዚያም መልእክቱ እየተገለጠ በሮም ግዛት ውስጥ ላሉት አብያተ ክርስቲያናት በሙሉ ተሰራጨ።

1ኛ ዮሐንስ የተጻፈበት ዘመንና ቦታ

ሐዋርያው ዮሐንስ ይህን መልእክት መቼ እንደ ጻፈው ማወቅ አስቸጋሪ ነው። ከጳውሎስ መልእክቶች በተቃራኒ ስለ ዮሐንስ ሕይወት የሚናገር በቂ መረጃ የለንም። በመሆኑም ይህ መልእክት በየትኛው የሕይወቱ ዘመን እንደ ተጻፈ ለማወቅ አስቸጋሪ ያደርገዋል። ምሁራን ዮሐንስ ይህን መልእክት በጻፈበት ጊዜ እድሜው እንደ ገፋና በኤፌሶን ከተማ ይኖር እንደነበር የሚገልጽባቸው ምክንያቶች እንዱ በመልእክቱ ውስጥ ስለ ሐሰት ትምህርቶች ያነሣው ርእሰ ጉዳይ ነው። ዮሐንስ የጠቀሰው የሐሰተኛ ትምህርት ገጽታ ከመጀመሪያው ምእተ ዓመት ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንን ያውክ የነበረውን የጥንታዊ ኖስቲሲዝም መልክ ይይዛል። ዮሐንስ የሞተው ከ95-100 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በመሆኑ፥ ምሁራን መልእክቱን የጻፈው 90-95 ዓ.ም ባለው ጊዜ ፣ ውስጥ ሊሆን እንደሚችል ይገምታሉ። ይህ መልእክት ከዮሐንስ ወንጌል በኋላ የተጻፈ ሳይሆን አይቀርም። ነገር ግን ይህ መልእክት የተጻፈው ዮሐንስ ወደ ፍጥሞ ደሴት ታስሮ ከመወሰዱና የዮሐንስ ራእይን ከመጻፉ በፊት ነው።

ዮሐንስ ይህን መልእክት በሚጽፍበት ጊዜ የት እንደነበረም በእርግጠኝነት ለመናገር አይቻለም። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዮሐንስ ከመሞቱ በፊት በኤፌሶን እንደነበረ ስለሚናገር፥ አብዛኞቹ ምሁራን የሚያስቡት የ1ኛ ዮሐንስ መልእክት ኤፌሶን ከተማ እንደ ተጻፈ ነው።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

1 thought on “የ1ኛ ዮሐንስ መግቢያ”

Leave a Reply

%d bloggers like this: