ተስፋን በከርስቶስ ዳግም ምጽአት ላይ መጣል እና እርስ በእርስ መዋደድ (1ኛ ዮሐ. 2፡28-3፡24)

፩. የእግዚአብሔር ልጆች ተስፋችንን በከርስቶስ ዳግም ምጽእት ላይ መጣል አለብን። ይህም ወደ ጽድቅ ኑሮ ይመራናል (1ኛ ዮሐ. 2፡28-3፡10)።

ዓለም ሰዎች መሆናችንን ብቻ ትገነዘባለች። ነገር ግን እኛ ማን ነን? ዮሐንስ የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ይናገራል። ለመቼውም ቢሆን ይህንን ታላቅ እውነት መዘንጋት የለብንም። ምንም እንኳን ዛሬ ብዙም የተለየን መስለን ባንታይም፥ ወደፊት እጅግ የተለየን ሰዎች እንሆናለን። ዮሐንስ አማኞች ስለ ወደፊቱ እንዲያስቡና የክርስቶስን ዳግም ምጽአት በናፍቆት እንዲጠባበቁ ያበረታታል። ወደፊትን አሻግረን የምንመለከትና ዳግም ለሚመለሰው ክርስቶስ ክብርን በሚያመጣ መልኩ ሕይወታችንን የምንመራ ከሆነ ሁለት ነገሮች ይፈጸማሉ። በመጀመሪያ፥ የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ፍርሀትን ወይም ኀፍረትን ሳይሆን፥ ልበ ሙሉነትን ያጎናጽፈናል። ሁለተኛ፥ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆነና እኛም የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን (ከእግዚአብሔር ስለተወለድን)፥ እርስ በርሳችን እንመሳሰላለን። ክርስቶስ ዳግም ሲመለስ፥ እኛም እንደ እርሱ እንሆናለን። ዮሐንስ ይህን ሲል ውጫዊ መልካችንን ማለቱ ሳይሆን፥ ልባችንንና ባህሪያችንን ማመልከቱ ነው። በጽድቅ ለመኖር ስንሻ እዚሁ በምድር ላይ የለውጥን ሂደት እንጀምራለን። ይህም ለውጥ ክርስቶስ ዳግም ሲመለስና ሙሉ በሙሉ እርሱን ስንመስል የተሟላ ይሆናል።

ነገር ግን በዚያን ጊዜ ክርስቶስን እንመስል ዘንድ አሁን መለወጥ ይኖርብናል። የልማድ ኃጢአት መፈጸማችንን ማቆም አለብን። ባለማቋረጥ ኃጢአት እየፈጸመ የሚኖር ሰው የእግዚአብሔር ልጅ አለመሆኑን ያረጋግጣል። እንዲህ ዓይነቱ ሰው የሰይጣን ተከታይ ነው። ይህም ከሰይጣን ጎን በመሰለፍ የክርስቶስን ቅጣት እንዲቀበሉ ያደርጋቸዋል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የክርስቶስን ዳግም ምጽአት መጠባበቅ ዛሬ በቅድስና እንድንመላለስ የሚያግዘን እንዴት ነው? ለ) አንድ ቀን ክርስቶስን እንደምንመስልና ከኃጢአት ባህሪ ነፃ እንደምንወጣ ማወቃችን እንዴት እንደሚያበረታታን ግለጽ።

፪. የእግዚአብሔር ልጆች እርስ በርሳቸው በመዋደድ አንድነትን ይጠብቃሉ (1ኛ ዮሐ 3፡11-24)።

በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በመሪዎችም ሆነ በታዋቂ አባላት መካከል ተቃራኒ አሳቦች በሚሰነዘሩበት ጊዜ በአብዛኛው የስሜት መጎዳቶችና ክፍፍሎች ይከሰታሉ። ሰዎች በአንድ ጉዳይ ላይ መስማማት በማይችሉበት ጊዜ ክፍፍል ይፈጠራል። ከዚያም አንዱ ሌላውን መተቸት ይጀምራል። ትክክል ያልሆኑ መነሻ አሳቦችንም መገመት ይጀምራል። በዚህም ጊዜ ቤተሰቦችና ጓደኞች ከሚደግፉት ወገን ጎን በመሰለፍ ክፍፍልን ያስከትላሉ። ብዙም ሳይቆይ ጠቅላላይቱ ቤተ ክርስቲያን በተከፋፈሉት ሰዎች ትሞላለች። ብዙውን ጊዜ እንደዚህ ዓይነቱ ሁኔታ በሚከሰትበት ጊዜ ክፍፍሉ ከመንሥኤ ጉዳዩ እልፍ ብሎ የክፍፍሉን ተሳታፊዎች የሚመለከት ይሆናል። ይህ በትንሹ እስያ ውስጥ በነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ዘንድ የተከሰተ ይመስላል። መሪዎች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አለመስማማት ሲጀምሩ፥ የቃላት ጦርነት ገጠሙ። ብዙም ሳይቆይ ከፍተኛ የሆኑ ክፍፍሎች ተከሰቱ።

ተቃራኒ አሳቦች በሚኖሩበት ጊዜ (በተለይም ሐሰተኛ ትምህርት ወይም አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ወደ ቤተ ክርስቲያን በሚመጣበት ጊዜ)። ሰይጣን ክፍፍልን ለማምጣት ይሞክራል። ይህን በሚያደርግበት ጊዜ የተባበረች ቤተ ክርስቲያን ጠንካራ በመሆንዋ ሊያሸንፋት አይችልም። የተከፋፈለች ቤተ ክርስቲያን ደካማ ስለሆነች፥ ሰይጣን ብዙ ሰዎችን በግጭቱ አማካይነት ሊያጠፋ ይችላል። ስለሆነም፥ ስለ ሐሰተኛ ትምህርት በሚጽፍበት ጊዜ፥ ዮሐንስ የፍቅርን ጉዳይ ያነሣል። ዮሐንስ ፍቅርን ከጥላቻ ጋር ሲያነጻጽር እንመለከታለን። ጥላቻ የቃየልን መንገድ ይከተላል። ቃየል በወንድሙ ላይ ስለቀናና እግዚአብሔርን በልቡ ለማዳመጥ ስላልፈለገ፥ ወንድሙን አቤልን ገድሎታል። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ እግዚአብሔርን ለመስማት የማይፈልጉ ዓለማውያን እማኞችን በመጥላት ያሳድዷቸዋል። ይህም አንዳንድ ጊዜ እማኞችን እንዲገድሉ ያደርጋቸዋል። ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትዕቢትና ቅንአት አማኞች የሌሎች አማኞችን ዝና፥ አገልግሎት፥ ግንኙነት፥ ወዘተ… እንዲገድሉ ማድረጉ የበለጠ አሳዛኝ ነው።

የእግዚአብሔር ልጆች እግዚአብሔርን መምሰል ይኖርባቸዋል። በማንስማማበት ጊዜ እንኳን እርስ በርሳችን መዋደድ ይኖርብናል። ፍቅር እሳትን እንደሚያጠፋ ውኃ ነው። ፍቅር የትዕቢትና የራስ ወዳድነት ተቃራኒ በመሆኑ፥ የጥላቻን ሥር ያጠፋዋል። ዮሐንስ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በምሳሌነት ይጠቅሳል። አምላክ የነበረው ክርስቶስ ከፍቅሩ የተነሣ ሁሉንም በረከት ትቶ ስለ እኛ ሞቷል። በትሕትናና ሌሎችን በማገልገሉ ረገድ ክርስቶስን መምሰል ይኖርብናል። ይህ ፍቅር እራሱን በተለያዩ መንገዶች ይገልጻል። በመጀመሪያ፥ አንድ ግለሰብ በእምነት ወንድሙ ለሆነው ሰው ሕይወቱን አሳልፎ በሚሰጥበት ጊዜ ፍቅር ይገለጣል። ምንም እንኳን ይህ ለሌላ ሰው ብሎ መሞትን የሚያመለክት ቢሆንም፥ ዮሐንስ በተምሳሌትነት የሚናገረው ለሌላው ሰው ስንል ለዝናችን፥ ለአሳባችን ወይም ለምንመርጠው ነገር ስለመሞታችን ነው። ዋነኛው እውነት ግልጽ በማይሆንበት ሁኔታ ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ፥ ከእነርሱ ጋር ባልስማማም እንኳን እነ እገሌን ለመርዳት ምን ማድረግ አለብኝ? የሚለው ጥያቄ ቀዳሚውን ስፍራ ሊይዝ ይገባዋል። ሁለተኛ፥ ፍቅር ለመኖር የሚያስፈልጓቸው ነገሮች የሌላቸውን ሰዎች ለመርዳት የሚችልበትን መንገድ በመፈለግ ራሱን ይገልጻል። የእነዚህ ሰዎች ችግር እንደ ገንዘብ፥ ምግብ ወይም ሥራ ዓይነት ቁሳዊ ነገር ሊሆን ይችላል። ወይም እንደ ጓደኝነትና ተቀባይነት ያለ ስሜታዊ ጉዳይ ሊሆን ይችላል። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉት ሰዎች የተለያዩ ፍላጎቶች አሏቸው። ፍቅር በሚኖርበት ጊዜ የቤተ ክርስቲያን አባላት እርስ በርሳቸው ይረዳዳሉ።

የክርስቲያኖች እርስ በርስ መዋደድ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ፥ ዮሐንስ በሐሰተኛ አስተማሪዎችና በራሳችን እምነት እውነተኛነት መካከል ለመለየት ከሚያስችሉ መንገዶች ይህ ዋነኛው እንደሆነ ይናገራል። ሰዎችን የማንወድ ከሆነ፥ የፍቅር አምላክ የሆነው እግዚአብሔር ከልባችን ውስጥ መኖሩ አጠራጣሪ ይሆናል። የፍቅር ሕይወት ሁለት ነገሮችን ያደርጋል። በመጀመሪያ፥ እውነተኛ ፍቅር የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ለልባችን ያረጋግጥልናል። እንደሚገባን ሰዎችን ልንወድ የምንችለው በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ብቻ ነውና። ሁለተኛ፥ በሕይወታችን ውስጥ ያለ ፍቅር ከእግዚአብሔር ጋር ትክክለኛ ግንኙነት እንዳለንና ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ጸሎታችን እንደሚመልስ ያሳያል። (ማስታወሻ፡ በፍቅር ቁጥጥር ሥር የዋለ ሕይወት ብዙውን ጊዜ የሚጸልየው ከራስ ይልቅ ለሌሎች ነው፡፡ ከዚህም የተነሣ፥ እግዚአብሔር እነዚህን ጸሎቶች ለመመለስ ደስ ይሰኛል። ነገር ግን ብዙውን ጊዜ ለግል ፍላጎቶቻችን የምንጸልይ ከሆነ፥ ጸሎቶቻችን ራስ ወዳድነት ያጠቃቸዋል። እግዚአብሔርም በአብዛኛው እነዚህን ጸሎቶች አይመልስም።)

ዮሐንስ እግዚአብሔር የአማኞችን ጸሎት የሚመልሰው አራት ነገሮች ከተሟሉ እንደሆነ ይናገራል፡- ሀ) በክርስቶስ በማመን ግላዊ ግንኙነትን መመሥረት፥ ለ) ክርስቶስ ለሰጠን ትእዛዛት መታዘዝ፥ ሐ) ሌሎችን የምናገለግልበት የፍቅር ሕይወት እና መ) ከክርስቶስ ጋር የሚደረግ ሕያውና የጥገኝነት ግንኙነት። የተሟሟቀ የጥገኝነት ግንኙነት እንዳለ የምናውቀው መንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን ውስጥ ስላለና ለመንፈሳችን ስለሚመሰክር ነው።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) በራስህ ቤተ ክርስቲያን ወይም አንተ በምታውቀው ሌላ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተከሰተን አንድ አለመግባባት አስብ። አለመስማማቱን የፈጠረው መሠረታዊ ችግር ምን ነበር? ለ) ሰዎች ስለ እርስ በርሳቸው በሚነጋገሩበት ወቅት ጥላቻና ግድያ የተከሰተው እንዴት ነበር? ይህ ሁኔታ አለመግባባቱን እንዴት እንዳባባሰው ግለጽ። ሐ) በዚህ ሁኔታ ውስጥ እውነተኛ ፍቅር ቢኖር ኖሮ የተለያዩ ሰዎች የሰጡት ምላሽ እንዴት የተለየ ሊሆን ይችል ነበር? መ) እነዚህ ጥቅሶች እምብዛም ፍቅር ስለማይታይባቸው አብያተ ክርስቲያኖቻችን የሚያስተላልፉአቸው ጠንካራ ማስጠንቀቂያዎች ምንድን ናቸው?

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d