ሔለን ተወልዳ ያደገችው በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ነበር። በሕይወት ዘመኗ ሁልጊዜም ወንጌልን ዓላማ አድርጋ ኖራለች። በየጊዜው ወደ ቤተ ክርስቲያን ትሄድና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ታካሂድ ነበር። እንዲሁም በመዘምራን ቡድን (ኳየር) ውስጥ ትዘምር ነበር። አዝማቾችን መዘመር ትወዳለች። ማንም ሰው «ክርስቶስ ለኃጢአትሽ የሞተ ጌታ መሆኑን ታምኚያለሽ?» ብሎ ሲጠይቃት፥ በፍጥነት፥ አዎን» ስትል ትመልሳለች። እንዴት ክርስቲያን ልትሆን እንደቻለች ብትጠየቅም፥ «ሁልጊዜም ክርስቲያን ሆኜ ኖሬአለሁ፥ ወላጆቼ ክርስቲያኖች ናቸው» ትላለች። ነገር ግን ሔለን በቤተ ክርስቲያንና በትምህርት ቤት የምታሳየው ሁኔታ ጭራሽ የተለያየ ነበር። ሔለን ቆንጆ ልጅ ነበረች። ይህን ቁንጅናዋን በአጭር ቀሚሶች፥ ጌጣጌጦችና ሜካፖች አጉልታ ታሳይ ነበር። ሔለን ማጥናት ስለማትወድ ከክፍሉ ውስጥ አንደኛ ከሚወጣው ልጅ ጎን ተቀምጣ ትኮርጅ ነበር። ታዋቂነትን ለማትረፍ በመፈለጓ በትምህርት ቤት ውስጥ ታዋቂ የነበረውን ልጅ የወንድ ጓደኛዋ አድርጋ ያዘች።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ሔለን በቤተ ክርስቲያንና በትምህርት ቤት ውስጥ በምታከናውናቸው ተግባራት መካከል የሚታዩት ልዩነቶች ምን ምንድን ናቸው? ለ) ልዩነቱ የተከሰተው ለምን ይመስልሃል? ይህ ስለ ሔለን እምነት እውነተኛነት ወይም ጥልቀት ምን ያሳያል? ሐ) በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ የሚያድጉ ብዙ ልጆች ወደ ዩኒቨርስቲ በሚገቡበት ጊዜ እምነታቸውን ጠብቀው ለማቆየት የሚችገሩት ለምንድን ነው? መ) ቤተሰቦችና ቤተ ክርስቲያን ልጆቻቸው እምነታቸውን እንዲረዱና ይህም እኗኗራቸውን እንዲቆጣጠር ለማድረግ ምን ሊያከናውኑ ይችላሉ?
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሙሉ ኃይላችን ልንዘምር፥ ልንጸልይ፥ ብዙ የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ልናካሂድ፥ ወዘተ… በምንችልበት አስደሳች ዘመን ውስጥ እንኖራለን። በዚህ ደስታ ውስጥ ግን እናምናለን በምንለውና በዓለም ውስጥ በምንኖርበት ሁኔታ መካከል እያደገ የሚሄድ ክፍተት ይታያል። አማኞችም እንደማያምኑ ሰዎች ሁሉ ወሲባዊ ኃጢአቶችን ይፈጽማሉ። ክርስቲያኖች ጉቦ፥ ማጭበርበር ወይም መስረቅ የመሳሰሉትን ኃጢአቶች ይለማመዳሉ። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጸብ በመፍጠር በአብያተ ክርስቲያናት ክፍፍሎችን ያስከትላሉ። ለሴተኛ አዳሪዎች ወይም ለጎዳና ተዳዳሪዎች ብዙም ደንታ የለንም። ይህ እናምናለን በምንለውና በአኗኗራችን መካከል ያለው ክፍተት የግብዝነት ኃጢአት በመባል ይታወቃል። ይህም ኃጢአት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚታዩ አደገኛ ኃጢአቶች አንዱ ነው። አይሁዳውያን አማኞች ከዚህ ችግር ጋር ተጋፍጠው ነበር። ያዕቆብ ድፍረት በተሞላበት ነቢያዊ መንገድ በእርግጥም በክርስቶስ ካመንን፥ ይህም እምነታችን ከአእምሮ እውቀት ያለፈ እንደሆነ፥ አኗኗራችን መለውጥ አለበት ሲል አጽንኦት ሰጥቶ ያስተምራል። የምናምነው ነገር አኗኗራችንን መለወጥ አለበት። የያዕቆብ መልእክት እግዚአብሔርን የሚያስከብር ሕይወት በመምራቱ ምን ያህል እንደተዋጣለት ለመመርመር የሚያስችል መንገድ ይሰጠናል።
፩. ለመከራ ሊሰጥ የሚገባው ምላሽ (ያዕ. 1፡1-13)
ያዕቆብ ራሱን የሚገልጽበትን ሁኔታ መመልከቱ ጠቃሚ ነው። ምንም እንኳን ከማርያም የተወለዱና የኢየሱስ ወንድሞች ለመሆን የቻሉ ብዙ ሰዎች ባይኖሩም፥ ያዕቆብ በቤተሰባዊ ግንኙነቱ ሲመካ አንመለከትም። ወይም ደግሞ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ታላቅ መሪ በመሆኑ አይኩራራም። የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን በክርስቲያናዊ እንቅስቃሴ ወቅት እናት ቤተ ክርስቲያን ነበረች። ነገር ግን ያዕቆብ ራሱን «ባሪያ» ሲል ይጠራል። የሕይወቱ ዓላማ እግዚአብሔር አብን ማገልገል ነበር። በዚህ ጊዜ ያዕቆብ ኢየሱስ፥ ያ ታላቅና ኃይል ያለው ወንድሙ ብቻ ሳይሆን አምላክ መሆኑንም ተረድቷል። ኢየሱስ ከእግዚአብሔር አብ ጋር እኩል መሆኑን ይገልጻል። (ማስታወሻ፡ ይህ የ«ኢየሱስ ብቻ» ተከታዮች እግዚአብሔር አብና ኢየሱስ ክርስቶስ አንድ አካል መሆናቸውን በመግለጽ ስለ ሥላሴ የተሳሳተ እምነታቸውን የሚያሳየው ነጥብ ነው)።
ክርስቲያኖች ነን ብንልና እርሱን ለመከተል ብንፈልግ፥ ብዙውን ጊዜ የሚከሰቱ ነገሮች አሉ። ይኸውም ስደት ነው። ያዕቆብ መልእክቱን የሚጽፍላቸው አይሁዳውያን አማኞች ክርስቶስን መድኅናቸውና ጌታቸው አድርገው መከተላቸውን በመምረጥ ሳይሆን አይቀርም። ለአይሁዶች የኢየሱስን መሢሕነት መቀበሉ ከባድ ነበር። ከዚህ አልፎ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ነው ማለቱ ስድብ ነበር። አይሁዶች ክርስቶስን ለመከተል በሚወስኑባት ጊዜ ብዙውን ጊዜ አይሁዳውያን ወገኖቻቸው ያሳድዷቸው ነበር። ብዙውን ጊዜ ከምኩራብና ከአይሁዶች ኅብረት ይባረሩ ነበር። ከእነርሱ ጋር የንግድ ግንኙነት የሚያደርጉት ሀብታም ነጋዴዎች ያገልሏቸው ነበር። ድህነቱ እየጠና ሲሄድ ሕይወት ከባድ ትሆንባቸው ጀመር። ይህም አማኞችን ለተስፋ መቁረጥ ዳረጋቸው። ያዕቆብ እነዚህን የተበተኑና የተሰደዱ አይሁዶች ለማበረታታት ሲል ስለ መከራ ይጽፋል።
ከያዕቆብ 1፡2-18 ያለውን ትምህርት ለመረዳት «ፈተና» የሚለው የአማርኛ ቃል ሁለት የተለያዩ ትርጉሞች እንዳሉት መረዳት ይኖርብናል። በመጀመሪያ፥ ይህ ቃል ወደ ኃጢአት የሚመራንን የኃጢአት ባሕሪ ወይም የሰይጣን ፈተና ሊያመለክት ይችላል። ያዕቆብ በ1፡13-18 ስለዚህ ዓይነቱ ፈተና ይናገራል። ሁለተኛ፥ ይህ ቃል ግምገማን ወይም ምርመራን ሊያላይ ይችላል፤ ይህም እግዚአብሔር እምነታችንን ለመገምገምና ለማጠንከር፥ ችግሮች ወደ ሕይወታችን እንዲመጡ የሚፈቅድበት ነው። ያዕቆብ 1፡3-12 የሚያቀርበው ይህንኑ ዓይነት ፈተና ነው። ስደት ወይም እንደ በሽታና የወዳጅ ሞት ያለ ሌላ ፈተና ወደ ሕይወታችን በሚመጣበት ጊዜ እንደ አማኞች ምን ማድረግ ይኖርብናል? ያዕቆብ እምነታችን በሚፈተንበት ጊዜ ልናደርጋቸው የሚገቡንን አንዳንድ ነገሮች ይዘረዝራል።
ሀ. ችግሮችን በሩጫ ልንመልሳቸው እንደሚገቡ ጠላቶች ሳይሆን፥ እምነታችንን እንደሚያጠነክሩ መሣሪያዎች መመልከት ይኖርብናል። ያዕቆብ በዚህ ጊዜ ደስ መሰኘት እንዳለብን ይነግረናል። የምንደሰተው ስደቱ በሚያመጣብን ሥቃይ ላይሆን፥ እግዚአብሔር እኛን ለመለወጥ ይህንኑ ሥቃይ እየተጠቀመ መሆኑን በማወቃችን ነው። ያዕቆብ እነዚህን የመከራ ጊዜያት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ብናስተናግድ በሕይወታችን ውስጥ የሚመጡትን ለውጦች ያሳየናል። በፈተና ጊዜ ጠንክረን ብንቆም፥ እምነታችን ጽናትን ያፈራል። ይህም የኋላ ኋላ ወደ ብስለት ይመራናል። ነገር ግን ያዕቆብ ጽናት ሥራውን እንዲያጠናቅቅ መፍቀድ እንዳለብን፥ ይህ ካልሆነ ግን ወደ ብስለት እንደማይመራን ያስጠነቅቀናል። ከችግሩ ፊትን ማዞር፥ ማጉረምረም ወይም እጅን መስጠት መከራው በሕይወታችን እንድናድግ እንዳያግዘን ያደርጋል።
ይህ እውነት በአብያተ ክርስቲያኖቻችን የተወደደ ትምህርት አይደለም። ክርስቶስ መከራን ድል መንሣቱን ለመዘመር እንፈልጋለን። ስለ ቅጽበታዊ ፈውስና ከክርስቶስ ስለምናገኛቸው በረከቶች ለመደሰት እንፈልጋለን። እርሱም አንዳንድ ጊዜ ፈውስና ቀለል ያለ አኗኗርን ይሰጠናል። ነገር ግን በእርግጥ ልጆቹ ከሆንን፥ እግዚአብሔር እንዴት በመንፈሳዊ ሕይወታችን እያደግን እንዳለን ለመፈተንና የበለጠ እንድናድግ ለማገዝ ችግሮችን ወደ ሕይወታችን ማምጣቱ የማይቀር ነው። ሚዛናዊ የክርስትና አመለካከት እግዚአብሔር መከራን ወደ ሕይወታችን እንደሚያመጣ የሚያሳይ ነው። ድል የሚገኘው ደግሞ እግዚአብሔር መከራውን ከእኛ እንዲወስድ በማድረግ ሳይሆን፥ በችግር ጊዜ በእርሱ ብርታት ጸንቶ በመቆም ነው። በዚህ ሁሉ ደስታ የተሞላበት እምነት ይዞ መዝለቁ ወሳኝ ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ለመጨረሻ ጊዜ ስለ አማኞች መከራ መቀበል የሚያስረዳ ስብከት የሰማኸው መቼ ነው? ለ) ብዙውን ጊዜ የሚቀርበው ስብከት እግዚአብሔር ከመከራ እንደሚያድነን የሚያስረዳ ነው ወይስ እግዚአብሔር በሕይወታችን እንድናድግ መከራውን የሚጠቀምበት መሆኑ ነው? ሰዎች አንደኛውን ዓይነት ስብከት የሚወዱትና ሌላኛውን ዓይነት የማይወዱት ለምንድን ነው? ሐ) እግዚአብሔር ከመከራ እንድናመልጥ እንደረዳን ተነግሮን ሳለ ይህ ሳይሆን በሚቀርበት ጊዜ እምነታችን ምን ይሆናል?
ለ. መከራ በሚመጣበት ጊዜ እግዚአብሔር ዓላማውን ለመረዳትና በመንፈሳዊ ሁኔታ ለመኖር ጥበብን እንዲሰጠን መጠየቅ ይኖርብናል። የዚህ ተወዳጅ ጥቅስ (ያዕ. 1:5) ዐውደ ምንባብ መከራ ነው። ችግሮች የጠለቀ ሥቃይ በሚያስከትሉበት ጊዜ (ለምሳሌ፥ ስደት፥ በሽታ) ለዚህ ሁኔታ ምላሽ የምንሰጥበትን ጥበብ ማግኘቱ ጠቃሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥበብ ስለ አንድ ነገር እውነቶችን ማወቅ ብቻ ሳይሆን፥ በመንፈሳዊ ሁኔታ እንዴት መኖር እንዳለብን ማወቁ ጭምር ነው። ያዕቆብ፥ ግራ በተጋባንና ለአንድ ሁኔታ እንዴት ምላሽ መስጠት እንዳለብን በማናውቅበት ጊዜ እግዚአብሔር ሁልጊዜም ሊረዳን ዝግጁ መሆኑን ይነግረናል። እንዴት መመላለስና መጽናት እንዳለብን ስንጠይቀው እግዚአብሔር በቂ የሆነ ተግባራዊ ጥበብ ያፈስልናል። እግዚአብሔር እንደሚወደን መጠራጠር የለብንም። ጥያቄዎቻችን እኛ በምንፈልጋቸው መንገዶች በማይመለሱበት ጊዜ እግዚአብሔር ጸሎትን እንደሚመልስ መጠራጠር የለብንም። ነገር ግን አፍቃሪና ኃያሉ አምላካችን ሁልጊዜም እርሱ የሰጠንን ፈተና የምንቋቋምበትን ጥበብ እየሰጠን ጸሎታችንን በራሱ ጊዜና መንገድ እንደሚመልስ መረዳት ይኖርብናል።
አይሁዳውያን አማኞች ከተጋፈጧቸው ችግሮች አንዱ የኢኮኖሚ ችግር ነበር። ሕይወታቸውን ለመግፋት የሚያስችል ገቢ ለማግኘት የሚሯሯጡ ድሆች ነበሩ። አይሁዶች ልክ እንደኛዎቹ የጉራጌ ሕዝቦች ሠርቶ ገንዘብ የማግኘት ብቃት ነበራቸው። ለእነርሱ ድህነቱ ተስፋ የሚያስቆርጥ ብቻ ሳይሆን፥ እግዚአብሔር በቁሳዊ ሀብት ስላልባረካቸው የማይወዳቸው መሆኑን የሚያመለክት ጭምር ነበር። ከዚህም የተነሣ፥ አይሁዳውያን አማኞች ሀብታምና ዳሩ ግን በክርስቶስ የማያምኑ አይሁዶችን ለመለማመጥ ተገደዱ። ያዕቆብ የዛሬውን የድህነት ኑሮአቸውን ረስተው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ያገኙትን በረከት እንዲመለከቱ ያሳስባቸዋል። ክርስቲያኖች ከፍ ያለ ደረጃ አላቸው። እኛ የራሱ የእግዚአብሔር ልጆች፥ የሰማይና የዘላለም በረከቶች ሁሉ ወራሾች ነን። በመንፈሳዊ ብልጽግናችን ደስ ብንሰኝ፥ ጊዜያዊውን ድህነት ተቋቁመን ልንኖር እንችላለን። ያዕቆብ ሀብታም ዓለማውያን ስለ ገንዘብ ባላቸው አመለካከት ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይመክራቸዋል። ምክንያቱም ያላቸው ነገር ዝቅተኛ ግምት የሚሰጠው ወይም የተዋረደ ብቻ ነውና። ሰዎች በመሆናቸው ሀብታቸው እስኪሞቱ ድረስ ላላቸው አጭር ጊዜ ብቻ የሚያገለግል ይሆናል። እንደ አበቦች ለጊዜው ደስ ሊላቸው ቢችልም፥ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጠውልገው ይሞታሉ።
ሐ. መከራ የሚቀበሉ ክርስቲያኖች ዓይኖቻቸውን በሕይወት አክሊል (የዘላለም ሕይወት) ላይ ማሳረፍ ይኖርባቸዋል። ይህም እግዚአብሔር እርሱን ለሚወዱትና በመከራ ጊዜ በታማኝነት ጸንተው ይህንኑ ፍቅራቸውን ለሚያሳዩ አማኞች ተስፋ የገባላቸው ጉዳይ ነው።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) የፈተናን ጊዜ ከመጋፈጣችን በፊት አማኞች ሁሉ እነዚህን ሦስት ነጥቦች መረዳት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ለ) ከፍተኛ መከራ የገጠመህ መቼ ነው? እግዚአብሔር በሕይወትህ እንድታድግ ይሄንን መከራ የተጠቀመው እንዴት ነው?
፪. ለፈተና እንዴት ምላሽ መስጠት እንደሚገባ (ያዕ. 1፡13-18)
ያዕቆብ ከእምነት ግምገማ ወደ ሌላው ዓይነት ፈተና ይመለሳል። ይህም አንድን ሰው ወደ ኃጢአት የመምራት ፈተና ነው። አማኞች ኃጢአት በሚሠሩበት ጊዜ በአመዛኙ ጥፋቱ የሌላ ሰው ነው ወደ ማለቱ ያደላሉ።
ቤተሰብን፥ ሰይጣንን፥ ወይም ራሱ እግዚአብሔርን እንወቅሳለን። «እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ የሚቆጣጠር ከሆነ ከጋብቻ ውጭ የወሲብ ግንኙነት ወደማድረጉ ፈተና ያመጣኝ እግዚአብሔር አይደለምን?» ብለን እንጠይቃለን። «እግዚአብሔር ገንዘብ ቢሰጠኝ ኖሮ መስረቅ አያስፈልገኝም ነበር። እግዚአብሔር እንደነ እገሌ በትምህርት ቤት ጎበዝ ስላላደረገኝ ጥሩ ውጤት ለማምጣት ፈተና መኮረጅ አለብኝ። እግዚአብሔር ወሲባዊ ፍላጎቴን ስለፈጠረው፥ የዚህ ዓይነቱን ኃጢአት በመፈጸሜ የእርሱ ጥፋት ነው» የሚል ምክንያት እናቀርባለን። ያዕቆብ እንዲህ ዓይነቱን እግዚአብሔርን የመወንጀል ዝንባሌ በሁለት መንገዶች ያስተባብላል።
ሀ) እግዚአብሔር ሰዎች ክፉ ነገር እንዲያደርጉ አይፈትንም። እግዚአብሔር ቅዱስ ስለሆነ፥ ቅዱስ የሆነው አምላክ ሰዎች ኃጢአት የሆነውን ተግባር እንዲያከናውኑ አያደርግም። እርሱ የበጎ ነገር ሁሉ ምንጭ እንጂ የክፉ ነገር ምንጭ አይደለም። እግዚአብሔር ኃጢአትን እንድንሠራ አድርጎናል ማለቱ በእግዚአብሔር ባሕሪ ላይ የሚሰነዘር ስድብና የሚገባንን ያህል እርሱን እንደማናውቅ የሚያመለክት ነው።
ለ) ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ መወቀስ አለብን። እግዚአብሔርን ልንወቅስ አንችልም። ሌላውንም ሰው ልንወቅስ አንችልም። ሰይጣንን ጭምር መውቀስ አይኖርብንም። ሰይጣንን ጨምሮ ማንም ኃጢአትን እንድንሠራ ሊያስገድደን አይችልም። ሰይጣን ፈተናውን ከፊታችን ሊያስቀምጥ ይችላል። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ውጭ የሆነ ነገር ለማድረግ በምንመርጥበት ጊዜ ኃጢአትን እንሠራለን። ያዕቆብ ኃጢአት በምንሠራበት ጊዜ የሚከሰተውን ሁኔታ አይጦችን ከምንይዝበት ሁኔታ ጋር ያነጻጽራል። ይህ ሁሉ የሚጀምረው ስሕተት መሆኑን የምናውቀውን ነገር ከመመልከት ነው። አይጥ ለመያዝ አይጧ የምትወደውን ምግብ ከወጥመዱ ላይ እንደምንጨምር፣ ሰይጣንም እግዚአብሔር የማይፈልገውንና እኛ የምንወደውን ነገር ከፊታችን ያኖራል። ይህ ወደ ክፉ ምኞት ይመራናል። የተሳሳተ መሆኑን ብናውቅም ይህንኑ ነገር ለመቀበል እንፈልጋለን። በሌላ አገላለጽ፥ የኃጢአት ተፈጥሮአችን ማለትም ትክክል ያልሆኑትን ነገሮች የሚፈልገው ውስጣዊ ማንነታችን ሰይጣን ከፊታችን ይህንን ነገር እንዳስቀመጠ በመመልከት «አድርገው» ይለናል። እስከ አሁን ገና ኃጢአት አልሠራንም። ፈተና በራሱ ኃጢአት አይደለም። ክፉውን ምኞት ካልተቃወምን ፈተና በኃጢአት ለመውደቅ የመጀመሪያው ደረጃ ነው። አይጥ አንድ የምትወደውን ነገር ስትመለከት ወደ ወጥመዱ ትጓዛለች። ማጥመጃዋን ታሸታለች። ነገር ግን እስከ አሁን ገና በወጥመዱ አልተያዘችም። ይሁንና ፍላጎታችን ካልተገታ፥ «አይሆንም» ካላልን፥ ቀጣዩ እርምጃ ይከተላል። ይኸውም በወጥመዱ መያዝ ነው። እግዚአብሔርን ባለመታዘዝ ኃጢአት እንሠራለን፥ ወደ ወጥመዱ ዘላ እንደምትሄድ አይጥ እንያዛለን ማለት ነው። ያዕቆብ ወደ ኃጢአት የሚገፋፋ ስሜታችንን ካልተቆጣጠርን፥ የኋላ ኋላ ወደ ሞት እንደሚመራን ይናገራል። ይህም የግንኙነቶች፥ የሥጋዊና ምናልባትም መንፈሳዊ ሞት ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም የማያቋርጥ ልማዳዊ ኃጢአት በእምነታችን ውስጥ አንድ ነገር እንደ ጎደለ ያሳያል።
የውይይት ጥያቄ፡– ሀ) በተደጋጋሚ ስለፈጸምከው ኃጢአት ከክፉ ምኞት ኃጢአቱን እስከ መፈጸም ድረስ ያሉትን ደረጃ ዎች ዘርዝር። ለ) የኃጢአት ሕይወት መደጋገሙ ወደ አንድ ዓይነት ሞት ሲመራ ያየህበትን ሁኔታ ግለጽ።
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)