የያዕቆብ መግቢያ

ጳውሎስ በሮሜና ገላትያ መልእክቶች ውስጥ፥ «እድን ዘንድ ምን ማድረግ ይገባኛል» ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሰጣል። አይሁዳውያን አማኞች ድነትን (ደኅንነትን) እና በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን ለማግኘት ውጫዊ ተግባራት መከናወን እንዳለባቸው ስለሚያስቡ፥ ጳውሎስ ድነት (ደኅንነት) ሁልጊዜም ክርስቶስ ለእርሱ ኃጢአት እንደ ሞተ ለሚያምን ሰው እግዚአብሔር በነፃ የሚሰጠው ስጦታ እንደሆነ ያስተምራል። የያዕቆብ መጽሐፍ ግን፥ «አሁን ድነትን እንዳገኝ ምን ማድረግ ይገባኛል?» የሚለውን ጥያቄ ይመልሳል። ይህ መጽሐፍ እግዚአብሔርን የሚያሳስበው ሰው በክርስቶስ አምኖ መዳኑ እስከሆነ ድረስ አንድ ክርስቲያን ስለ አኗኗሩ መጨነቅ የለበትም ብለው ያስቡ ለነበሩ ሰዎች ምላሽ ይሰጣል። እንዲህ ዓይነት አመለካከት ያላቸው ሰዎች አንድ ሰው ድነትን የሚያገኘው ስለ ክርስቶስ የተገለጠውን እውነት በዕውቀት ደረጃ በማመን እንደሆነ ያስቡ ነበር። በእነርሱ አስተሳሰብ ድነት በተለወጠ ሕይወት መገለጡ አስፈላጊ አልነበረም። የያዕቆብ መልእክት የአንድ ሰው እምነት ከእውነት ጋር ከሚደረግ አእምሮአዊ ስምምነት ያለፈ እንደሆነ፥ የግለሰቡ የሕይወት ክፍሎች ሁሉ ለክርስቶስ መገዛት እንዳለባቸው ያስረዳል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንድ ሰው ይድን ዘንድ ምን ማድረግ እንደሚገባው ቢጠይቅህ፥ ምን ብለህ ትመልስለታለህ? ለ) አዳዲስ አማኞች ድነትን (ደኅንነትን) ካገኙ በኋላ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሲጠይቁህ ምን ታስተምራቸዋለህ?

የውይይት ጥያቄ፡- ስለ ያዕቆብ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። በመዝገበ ቃላት ውስጥ ስለ ጸሐፊው፥ መጽሐፉ ስለ ተጻፈበት ጊዜ፥ ስለ አንባቢዎቹ እና ስለ ዓላማው የተገለጹትን አሰቦች ጠቅለል አድርገህ ጻፍ። ለ) ያዕ. 1፡1 አንብብ። የዚህ መልእክት ጸሐፊ ነኝ ያለው ማን ነው? ራሱን እንዴት ይገልጻል?

፩. የያዕቆብ ጸሐፊ

ጥንታዊ የደብዳቤ አጻጻፍ ስልት በመከተል ጸሐፊው ከደብዳቤው መጀመሪያ ላይ ስሙን ይጠቅሳል። እራሱን «ያዕቆብ» ሲል ያስተዋውቃል። ለመሆኑ ጸሐፊው የትኛው ያዕቆብ ነበር? በአዲስ ኪዳን ውስጥ በዚህ ስም የሚጠሩ አራት ሰዎች አሉ።

 1. የዘብዴዎስ ልጅና የዮሐንስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ። በኢየሱስ ዘመን፥ ያዕቆብ ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ ነበር። ክርስቶስ ካረገ በኋላ ያዕቆብ የኢየሩሳሌምን ቤተ ክርስቲያን ከሚያስተዳድሩ ቁልፍ መሪዎች አንዱ ነበር። ነገር ግን በ44 ዓ.ም ንጉሥ ሄሮድስ ያዕቆብ እንዲገደል አዘዘ። ምንም እንኳን የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ የጌታ ደቀ መዝሙር የነበረው ያዕቆብ ሊሆን ቢችልም ክርስቶስ ካረገ ብዙም ሳይቆይ፥ ቤተ ክርስቲያን ከመስፋፋቷ በፊትና በመጽሐፉ ውስጥ የተገለጠው ርእሰ ጉዳይ ከመታየቱ በፊት ስለተገደለ ይህን መልእክት የጻፈው የጌታ ደቀ መዝሙር የነበረው ያዕቆብ አይመስልም።
 2. የእልፍዮስ ልጅና ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ የነበረው ያዕቆብ (ማቴ. 10፡3 አንብብ)። ይህ ደቀ መዝሙር አንዳንድ ጊዜ ትንሹ ያዕቆብ በመባል ይታወቃል። ከክርስቶስ እርገት በኋላ በዚህ ደቀ መዝሙር ላይ ስለደረሰው ሁኔታ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ብዙም መረጃ ስለማይሰጠን፥ ምሁራን ይህን መልእክት የጻፈው የእልፍዮስ ልጅ የነበረው ያዕቆብ ነው የሚል ግምት የላቸውም።
 3. የይሁዳ አባት (ይህ አስቆሮቱ ይሁዳ አይደለም)፥ እንዲሁም ታዲዮስ በመባል የሚጠራውና ከ12ቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ የሆነው ያዕቆብ (ሉቃስ 6፡16፥ ማር. 3፡18)።
 4. የክርስቶስ ግማሽ ወንድምና የዮሴፍና ማርያም ልጅ የነበረው ያዕቆብ። አብዛኞቹ ምሁራን የያዕቆብን መልእክት የጻፈው ይሄኛው ያዕቆብ እንደሆነ ያስባሉ። ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት ሐዋርያው ዮሐንስ ምናልባትም መልእክቱ ከመጻፉ በፊት እንደ ሞተ፥ ሌሎች ሁለቱ ያዕቆቦች ይህን ያህል በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የታወቁ ባለመሆናቸው መልእክቱን ሊጽፉ እንደማይችሉ በመገመት ነው። ያዕቆብ ከሚለው ስም በስተቀር ሌላ መግለጫ አለመጠቀሱ የመልእክቱ ጸሐፊ በአይሁዳውያን ማኅበረሰብ ውስጥ በሚገባ የታወቀ አገልጋይ መሆኑን ያመለክታል። ያዕቆብ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን መሪ ስለነበር፥ ይህን መልእክት ለመጻፍ የሚያስችል ደረጃና አይሁዳዊ ዳራ አለው። እንዲያውም ምሁራን ያዕቆብ በያዕቆብ መልእክትና ያዕቆብ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15 ውስጥ ባቀረበው ንግግር ውስጥ ተመሳሳይነቶች መኖራቸውን ይናገራሉ።

የክርስቶስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ምናልባትም ማርያምና ዮሴፍ ከወለዷቸው ከሦስቱ ልጆች ታላቁ ሳይሆን አይቀርም። ሌሎች ሁለቱ ልጆች ስምኦንና ይሁዳ በመባል ይታወቃሉ። (ማቴ. 13፡15 አንብብ።) እነዚህ ልጆች የተወለዱት ክርስቶስ ከተወለደ በኋላ ነበር። ምንም እንኳ ያዕቆብ በአንድ ቤት ውስጥ ከክርስቶስ ጋር አብሮ ቢያድግም፥ ክርስቶስ በሕይወት በነበረበት ወቅት ያዕቆብ ሊያምንበት አልፈለገም ነበር። እንዲያውም፥ እርሱና ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ክርስቶስ እንዳበደ በማሰብ ወደ ቤት ሊወስዱት መጥተው ነበር (ማር. 3፡21፤ ዮሐ 7፡3-5)። ያዕቆብ በክርስቶስ ባያምንም ትምህርቱን ሲሰማ የኖረ ይመስላል። ምክንያቱም በመጽሐፉ ውስጥ ሁሉ የክርስቶስን ትምህርቶች ይጠቅሳል። ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ የያዕቆብን ሕይወት የለወጠ አንድ ነገር ተከሰተ። ያዕቆብ ክርስቶስ በቀጥታ ራሱን ለወንድሞች እንደገለጸ ይነግረናል (1ኛ ቆሮ. 15፡7)። ክርስቶስ ከተነሣ ከ50 ቀን በኋላ በበዓለ ኀምሳ (በ30 ዓ.ም)፥ ያዕቆብ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በሰገነቱ ላይ እንደነበረ ተገልጾአል (የሐዋ. 1፡14)። ያዕቆብ ድነትን ካገኘ በኋላ በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረው ሥልጣን በፍጥነት እያደገ ሄደ። የዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብ በተገደለበት ወቅት የክርስቶስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ታላቅ መሪ እስከ መሆን ደርሶ ነበር። በመሆኑም ጴጥሮስ መልአክ ከእስር ቤት እንዴት እንዳወጣው ለያዕቆብ እንዲናገሩ ጠይቋቸዋል (የሐዋ 12፡17)። ጳውሎስ፥ ያዕቆብ ከኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን «አዕማዶች» እንዱ እንደነበር ይናገራል (ገላ. 2፡9)። በሐዋርያት ሥራ 15 በተገለጸው የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ወቅት ያዕቆብ በኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን መሪ ነበር። አሕዛብ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት ለማግኘት ግርዛትን ተቀብለው አይሁዳውያን መሆን እንደማያስፈልጋቸው በመግለጽ ጉባኤውን ከፍጻሜ ያደረሰው እርሱ ነበር (የሐዋ. 15፡13)። ጳውሎስ በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞው መጨረሻ ላይ ራሱን ለያዕቆብ አቅርቧል። በአሕዛብና አይሁዳውያን አማኞች መካከል የነበረውን ክፍፍልና ጳውሎስ ጸረ አይሁዳዊ ነው የሚለውን አሉባልታ ለማክተም፥ ያዕቆብ ጳውሎስ በቤተ መቅደስ ውስጥ መሥዋዕት ለማቅረብ ለአይሁዶች ያለውን ድጋፍ እንዲገልጽ ተጠየቀ። ጳውሎስ ይህንን በታዘዘ ጊዜ ታስሮ ወደ ሮም የሚሄድበት ሁኔታ ተፈጥሮአል (የሐዋ. 21፡18-26)። የሚያምኑ ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆኑ በኢየሩሳሌም የነበሩ የሚያምኑ አይሁዶች ጭምር ያዕቆብን ያከብሩ ነበር። ያዕቆብ በመንፈሳዊ ጉጉቱና ለአይሁድ ልማዶች በነበረው ታማኝነት የታወቀ ነበር። አይሁዶች የጽድቅ ባህሪውን ለማመልከት «ጻድቁ ያዕቆብ» ብለው ይጠሩት ነበር። ጳውሎስ ከታሰረ ብዙም ሳይቆይ ፊስጦ በድንገት ሲሞት፥ ሀናንያ የተባለ የአይሁድ ሊቀ ካህናትና የቤተ ክርስቲያን ጠላት ያዕቆብ ክርስቶስን እንዲክድ ጠየቀው። ያዕቆብ ይህንን ለማድረግ ባልፈቀደ ጊዜ ተገድሏል።

፪. ያዕቆብ መልእክቱን የጻፈው ለማን ነው?

የውይይት ጥያቄ፡- ያዕ. 1፡2 አንብብ። መልእክቱ የተጻፈው ለማን ነበር?

ያዕቆብ «ለተበተኑ ለ12 ወገኖች» እንደጻፈው ይናገራል። ምሁራን ይህንን አሳብ በሁለት መንገዶች ይረዳሉ። በመጀመሪያ፥ አንዳንድ ምሁራን «12 ነገዶች» የሚለው ቃል ክርስቲያኖችን ሁሉ የሚያመለክት ተምሳሌታዊ አገላለጽ ነው ይላሉ። አዲስ ኪዳን የአብርሃም እምነት ስላለን እውነተኛ አይሁዶች መሆናችንን ስለሚያመለክት (ገላ. 3፡26-29)፥ ያዕቆብ የሚጽፈው ለመንፈሳውያን አይሁዶች እንደሆነ ይናገራል።

ሁለተኛ፥ በአመዛኙ ግን መልእክቱ የተጻፈው በሮም ግዛት ውስጥ ለሚኖሩ ክርስቲያን አይሁዶች ይመስላል። በግሪክ ቋንቋ «የተበተኑ» የሚለው ቃል ከፓለስታይን ውጪ በሮም ግዛቶች ውስጥ ተበታትነው የሚኖሩትን አይሁዶች የሚያመለክት ሙያዊ ቃል ነበር። የያዕቆብ መልእክት የአይሁድ አገላለጾችን ይጠቀማል። የአጻጻፍ ስልቱም የብሉይ ኪዳንን የትንቢት ወይም የጥበብ ሥነ ጽሑፎች ይመስላል። ይህ መልእክት ቤተ ክርስቲያንን ምኩራብ ሲል ይጠራታል። ይህም ከቤተ መቅደስ ውጪ አይሁዶች ለአምልኮ የሚሰበሰቡበት ስፍራ ነው።

ምናልባትም ያዕቆብ መልእክቱን የጻፈው ከእስጢፋኖስ ጀምሮ ሲሰደዱ ለነበሩትና በመካከለኛው ምሥራቅ ሁሉ ለተበተኑት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ሳይሆን አይቀርም። (የሐዋ. 8፡1-4፤ 9፡1-2፤ 11፡9 አንብብ።) እነዚህ ሰዎች የያዕቆብ ቤተ ክርስቲያን አባላት በመሆናቸው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ለማበረታታትና በክርስትና እምነት ላይ ስለነበሯቸው የተዛቡ አመለካከቶች ለማስጠንቀቅ ይህን መልእክት ጽፎ ይሆናል።

ከያዕቆብ መልእክት ለመረዳት እንደሚቻለው፥ አብዛኛዎቹ አይሁዳውያን አማኞች ድሆች በመሆናቸው ሀብታም የመሬት ባለቤቶች እና ነጋዴዎች የተጠቀሙባቸው ይመስላል። ምናልባትም ክርስቶስን በመከተላቸው የተሰደዱም ይመስላል። የይሁዲነት አማኞች ክርስትናን አይወዱም ነበር። አንዳንድ ምሁራን ሁለተኛው የአማኞች ትውልድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይመጣ እንደነበር ያስባሉ። እነዚህ አማኞች ስለ ክርስቶስ የአእምሮ እውቀት ያላቸው እና እምነታቸውን ተግባራዊ የሚማያደርጉ ነበሩ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ብዙውን ጊዜ ሁለተኛ ትውልድ አማኞች እንደ መጀመሪያው ትውልድ በእምነታቸው የተሟሟቁና እምነታቸውን ተግባራዊ የማያደርጉ የሚሆኑት እንዴት ነው? ይህ እውነት የሆነው ለምን ይመስልሃል? ለ) የሁለተኛ ትውልዶችን አማኞች እምነት እውን ለማድረግና ከሕይወታቸው ጋር በማዛመድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?

፫. የያዕቆብ መልእክት የተጻፈበት ዘመንና ስፍራ

የጌታ ወንድም የሆነው ያዕቆብ በ62 ዓ.ም ስለ ሞተ ይህ መጽሐፍ ከዚያ በፊት መጻፍ ይኖርበታል። በመጽሐፉ ውስጥ አይሁዳውያን አማኞች በሮም ግዛት ሁሉ መበታተናቸው ስለተገለጸ ይህ መጽሐፍ ከክርስቶስ እርገት በኋላ የተጻፈ ይመስላል። ስለ አሕዛብ አማኞች የተጠቀሰ ነገር አለመኖሩ መጽሐፉ የተጻፈው ወንጌል ወደ አሕዛብ ከመሰራጨቱ በፊት እንደነበር ያመለክታል። እንዲያውም አንዳንድ ምሁራን ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በፎኔሽያ፥ ቆጵሮስ፥ እንዲሁም የሶሪያ አንጾኪያ ለተበተኑ አይሁዳውያን እማኞች እንደሆነ ይናገራሉ። እነዚህ አማኞች የተበተኑት ከእስጢፋኖስ ሞት በኋላ በተከሰተው – ስደት ምክንያት ነበር (የሐዋ. 8፡1፤ 11፡19)። ሌሎች ምሁራን ደግሞ ይህ መልእክት የተጻፈው ከጳውሎስ የመጀመሪያው ወይም ሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ በኋላ እንደነበር ይናገራሉ፡፡ ይህ መልእክት በክርስቶስ ማመን የሚጠይቀው ከተለወጠ ሕይወት ይልቅ በክርስቶስ የማመን አእምሯዊ ስምምነት ብዙ እንደሆነ ብቻ የሚናገሩ አንዳንድ አማኛችን ለማረም ነበር። ይህ መጽሐፍ በ44 ና 50 ዓ.ም መካከል የተጻፈ ይመስላል። ይህም የያዕቆብ መልእክት ከመጀመሪያዎቹ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት (ምናልባትም የመጀመሪያው) ሊሆን እንደሚችል ያሳያል። (ማስታወሻ፡ ምናልባት ከዚህ መልእክት ሊቀድም የሚችለው የገላትያ መልእክት ይሆናል።)

የያዕቆብ መልእክት የት እንደ ተጻፈ የሚያሳዩ ብዙ መረጃዎች ባይኖሩም፥ ያዕቆብ ይህንን መእልክት የጻፈው በኢየሩሳሌም በነበረበት ወቅት ሳይሆን አይቀርም። ያዕቆብ የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን መሪ ነበር።

፬. የያዕቆብ መልእክት ዓላማ

የመጀመሪያው ዓላማ፡ በተለያዩ መከራዎች ውስጥ የነበሩትን አማኞች ማበረታታት። ከእነዚህ አማኞች አንዳንዶቹ በአይሁዳውያን ወገኖቻቸው ይሰደዱ ነበር። ሌሎቹ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ነበሩባቸው። ያዕቆብ እነዚህ ድሀ አይሁዳውያን ከስደት እንዳይሸሹና ዳሩ ግን በደስታ እንዲቀበሉት ያበረታታቸዋል። ለዚህም ምክንያቱ እግዚአብሔር ስደትን እና መከራን በመጠቀም የክርስቲያኖችን ባሕሪ የሚቀርጽ መሆኑ ነው።

ሁለተኛ ዓላማ፡ እውነትን በተግባራዊ መንገዶች ሳያሳዩ ለአእምሮ ማወቅ አስፈላጊ እንደሆነ የሚያስቡትን አማኞች ለመገሠጽ። እውነተኛ እምነት አነጋገራችንን፥ በእምነት የሚዛመዱንን ሰዎች የምናስተናግድበትን ሁኔታ፥ ድሆችን እና ሀብታሞችን የምናቀርብበትን መንገድ፥ የጸሎት ሕይወታችንን፥ ወዘተ… ይለውጣል። የእምነታችንን እውነተኛነት የምናሳየው በአኗኗራችን ነው።

፭. የያዕቆብ መልእክት ልዩ ባሕርያት

 1. ምሁራን የያዕቆብ መልእክት የትንቢትና የጥበብ መጻሕፍትን በሚመስል ስልት እንደተጻፈ ያስባሉ (ከኢዮብ-መኃልየ መኃልይ ያሉትን መጻሕፍት ይመስላል)። ያዕቆብ እንደ ነቢይ በማኅበረሰብ ውስጥ የተመለከታቸውን አንዳንድ ኃጢአቶች፥ በተለይም የድሆችን በደል (በአማኞች መካከል ሳይቀር) በግልጽ ነቅሶ ያወጣል። የያዕቆብ ትእዛዛትና ማስጠንቀቂያዎች የሰሉ ናቸው። አማኞችን ሳይቀር «የተከፈለ ልብ ያላችሁ» ሲል ይጠራቸዋል። እንደ የብሉይ ኪዳን የጥበብ መጻሕፍት በተለይም እንደ መጽሐፈ ምሳሌ፥ ያዕቆብ መንፈሳዊ ጥበብ ምን እንደሆነና ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት በአኗኗራችን በተግባር እንድንገልጽ እንደሚጠይቀን ያስረዳል። እንደ መጽሐፈ ምሳሌ ያዕቆብ በፍጥነት ከአንዱ ጭብጥ ወደ አንዱ ጭብጥ ይጓዛል።
 2. የያዕቆብ መልእክት በትእዛዛት የተሞላ ነው። በ108 ጥቅሶች ውስጥ ከ50 የሚበልጡ ልዩ ትእዛዛት አሉ።
 3. ያዕቆብ ከሚናገረው ነገሮች አብዛኛዎቹ የክርስቶስን ትምህርቶች፥ በተለይም፥ የተራራውን ስብከት (ማቴ. 5-7) ይዳስሳሉ። ያዕቆብ እንደ ክርስቶስ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቃል ተግባራዊ እንዲያደርጉ ያደፋፍራል (ያዕ. 1፡22-25 ከማቴ. 7፡26 ጋር አነጻጽር። ያዕቆብ በተጨማሪም የክርስቶስን ዓይነት ምሳሌዎች ይጠቀማል (ያዕ. 2፡5 እና ማቴ. 5፡3፤ ያዕ. 3፡10-12 እና ማቴ. 7፡15-20፥ ያዕ. 3፡18 እና ማቴ. 5፡9፥ ያዕ. 5፡2-3 እና ማቴ. 6፡19-20፥ ያዕ. 5፡12 እና ማቴ. 5፡33-37 አነጻጽር)።
 4. የያዕቆብ መልእክት በአዲስ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙት ዐበይት መጻሕፍት መካከል ጥቂት አስተምህሮ እና ብዙ ተግባራዊ ትምህርት የሚገኝበት መጽሐፍ ነው። ያዕቆብ የሚያተኩረው መንፈሳዊ እውነትን በማብራራቱ ላይ ሳይሆን፥ እምነታችን በአኗኗራችን ላይ ሊያስከትል የሚገባቸውን ለውጦች ይዘረዝራል።
 5. ያዕቆብ በአማኞች አነጋገር ላይ ያተኩራል። ሁሉም ምዕራፎች ማለት ይቻላል እንደበታችንን እንዴት እንደምንገዛ እግዚአብሔርን ለማክበርና ለንስሐ እንጂ እርስ በርሳችን ለመቦጫጨቅ ልንጠቀም እንደማይገባም ይናገራል። ያዕቆብ አንደበት የአንድ አማኝ የመንፈሳዊነቱ መልካም አመልካች መሆኑን ያስረዳል።
 6. ያዕቆብ በዚህ መልእክት ውስጥ ብዙ ዘይቤያዊ አነጋገሮችንና ምሳሌዎችን ይጠቀማል። ከዓሣ አጥማጅነት፥ ከባህር፥ ከአበቦች፥ ከሚነድድ ቁጥቋጥ፥ ወዘተ… ምሳሌዎችን ይጠቀማል።
 7. ብዙ ምሁራን የያዕቆብ መልእክትን በተለይም ያዕቆብ 2፡14-16 ጳውሎስ በእምነት ስለ መጽደቅ ካስተማረው ጋር አነጻጽረው ለማብራራት ሞክረዋል (ሮሜ 3፡28-30)። እነዚህ ምሁራን እንደሚሉት፥ ያዕቆብ አንድ ሰው የሚድነው በሥራና በእምነት መሆኑን ያስተምራል። ጳውሎስ ግን ጽድቅ የሚገኘው በእምነት ብቻ መሆኑን ያስረዳል። አንዳንድ ምሁራን በእነዚህ ሁለት አመለካከቶች ላይ የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን የተከፋፋለችበት ወቅት እንደነበረ ጭምር ይናገራሉ። ነገር ግን ዐውደ ንባቡን በጥንቃቄ በምንመረምርበት ጊዜ ሁለቱም ጸሐፊያን ስለ ጽድቅ ከሁለት የተለያዩ ገጽታዎች አንጻር የሚናገሩ መሆናቸውን እንረዳለን። ጳውሎስ ጽድቅን የተመለከተው ከሕጋዊ ገጽታው ሲሆን፥ በእግዚአብሔር ዘንድ ጻድቅ መባልን አጉልቶ ያሳያል። ያዕቆብ ጽድቅን የተመለከተው በሰዎች ፊት ጻድቅ ወይም እውነተኛ ሆኖ ለመታየት ከሚል ገጽታ ነበር። ስለሆነም ጳውሎስ እግዚአብሔር ድነትን ስለሚሰጥበት ሁኔታ ሲናገር፥ ያዕቆብ ግን ሰዎች በራሳቸው መዳናቸውን ለሌሎች ሰዎች በሚያሳዩበት ሁኔታ ላይ ያተኩራል። የዚህ ቡድን ሌላው ግንዛቤ ጳውሎስ በእግዚአብሔር ፊት አሁን ትክክል ስለሆነበት ሁኔታ ሲናገር (ክርስቶስ በማመን)፥ ያዕቆብ ግን በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ በምንቀርብበት ጊዜ እንዴት ከፍርዱ እንደምናመልጥ (ሽልማትን እንዳናጣ) ያስረዳል የሚለው ነው። አዲስ ኪዳን ሁለት የድነት (ደኅንነት) ገጽታዎችን ያሳያል። እግዚአብሔር አንድ ነገር በማድረጋችን ወይም ጥሩዎች በመሆናችን ሳይሆን፥ በክርስቶስ በማመናችን፥ የድነትን (ደኅንነትን) ስጦታ ይሰጠናል። ይህ ጳውሎስ ያተኮረበት ርእሰ ጉዳይ ነው። ያዕቆብ ያተኮረበት ደግሞ በእርግጥ ድነትን ካገኘን፥ አዳዲስ ፍጥረታት ከሆንን፥ መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን ካለ፥ ሕይወታችን ይለወጥና በአኗኗራችን ይህንኑ እናሳያለን የሚለው ነው።

፮. የያዕቆብ መዋቅር

የያዕቆብ መልእክት ግልጽ የሆነ መዋቅር የለውም። ልክ እንደ መጽሐፈ ምሳሌ እርሱ ሊያስተላልፈው የፈለገው መልእክት በአጫጭር አባባሎች ወይም አጫጭር ርእሰ ጉዳዮች ወይም ችግሮች የተሞላ ሆኖ እንመለከተዋለን።

፯. የያዕቆብ አስተዋጽኦ

 1. በመከራና ፈተና ወቅት የአማኝ ኃላፊነት (ያዕ. 1፡1-18)

ሀ) ለመከራዎች ሊሰጥ የሚገባው ምላሽ (ያዕ. 1፡1-13)

ለ) ለፈተናዎች ሊሰጥ የሚገባው ምላሽ (ያዕ. 1፡13-18)

 1. አማኝ እምነቱን ተግባራዊ የሚያደርግባቸው መንገዶች (ያዕ. 1፡19-2፡26)

ሀ) እውነተኛ እማኞች ቁጣቸውንና አንደበታቸውን ይገዛሉ (ያዕ. 1፡19-20)።

ለ) እውነተኛ አማኞች የቃሉን እውነት ተግባራዊ በማድረግ አኗኗራቸውን ይለውጣሉ (ያዕ. 1፡21-27)።

ሐ) እውነተኛ አማኞች በድሃና በሀብታም አማኞች መካከል መድልዎ አይፈጽሙም (ያዕ. 2፡1-13)።

መ) እውነተኛ አማኞች በተግባራቸው የእምነታቸውን እውነተኛነት ያሳያሉ (ያዕ. 2፡ 14-26)።

 1. አማኝ አንደበቱን ይቆጣጠራል (ያዕ. 3፡1-12)።
 2. አማኝ ከሌሎች ሰዎች ጋር ባለው ግንኙነት ውስጥ እውነተኛ ጥበብን ያሳያል (ያዕ. 3፡13-4፡12)።
 3. አማኝ ከሥራው ጋር ያለው ግንኙነት (ያዕ. 4፡13-5፡6)
 4. አማኝ ከመከራ፥ ከበሽታና ከኃጢአት ጋር ያለው ግንኙነት (ያዕ. 5፡7-20)

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ አስደናቂ አገልግሎታቸው እግዚአብሔር ይባርካቸው፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: