ይሁዳ «ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ» (ይሁዳ 3)
የውይይት ጥያቄ፡- ከትልቅ ከተማ ውስጥ የምትገኝ ሰፊ ቤተ ክርስቲያን መጋቢ ነህ እንበል። ቤተ ክርስቲያንህ ከተለያዩ ሐሰተኛ ትምህርቶች ተጽዕኖ እየደረሰባት መሆኑን ትገነዘባለህ። አንድ ሰው ይነሣና ሥላሴ የሚባል ነገር የለም፥ ኢየሱስና እግዚአብሔር አብ ሁለት የተለያዩ ስሞች ያሉትን አንድ አካል ያመለክታሉ ሲል ይናገራል። ሌላው ደግሞ ሁላችንም አማልእክት ነን ሲል ያስተምራል። ሦስተኛው አስተማሪ በበኩሉ እውነተኛ አማኞች በልሳን የሚናገሩት ናቸው ይላል። ሌላው ደግሞ የሚያድነን ጥምቀት ነው ሲል ያስረዳል። ሀ) ከእነዚህ ከእያንዳንዳቸው ሐሰተኛ ትምህርቶች የጎደለው ወይም የተሳሳተው ነገር ምንድን ነው? ለ) መጋቢ እንደ መሆንህ፥ እግዚአብሔር ለእምነት እንድትጋደል ምን ምን የሚጠብቅብህ ይመስልሃል? ሐ) ለእምነትህ መጋደል የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው? መ) በራስህ ወይም በሌሎች አብያተ ክርስቲያናት እነዚህ ሐሰተኛ አስተማሪዎች ተጽዕኖ ማሳደራቸውን ያየህበትን ሁኔታ ግለጽ። ሠ) የሰዎቹን እምነት በንጽሕና ለመጠበቅ አሁን ያሉት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን በማድረግ ላይ ናቸው? ከዚህ የተሻለ ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
የቤተ ክርስቲያን መሪ ሊያከናውናቸው ከሚገቡ ዐበይት ተግባራት አንዱ የእግዚአብሔርን ቃል እውነት መጠበቅ መሆኑን በአዲስ ኪዳን ጥናታችን ውስጥ ተመልክተናል። ማናችንም ብንሆን ከሰው ጋር መከራከር አንፈልግም። ማናችንም ብንሆን ሰዎች የተሳሳቱ መሆናቸውን ለመናገር አንደፍርም፤ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነት እርምጃዎች ሰዎችን የማንወድ ወይም ተቺዎች የሆንን ያስመስልብናል። ነገር ግን እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እውነትን እንዲጠብቁ ያዝዛቸዋል። በቃሉ ውስጥ ያለውን እውነት መጠበቅ ይኖርባቸዋል። የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገች ስትመጣ፥ ይሁዳ ሐሰተኛ ትምህርቶች እየጎረፉ በመምጣታቸው ይበልጥ አሳሰበው። ስለሆነም አማኞችና በተለይም የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለእውነት እንዲጋደሉ ለማበረታታት ይህችን አጭር መልእክት ጻፈ። ይሁዳ እውነቱ ከተቀየረ፥ ከእግዚአብሔር ቃል ላይ አንድ ነገር ከተቀነሰ ወይም ከተጨመረ፥ ሰዎች ምንም ያህል የተሟሟቀ መንፈሳዊነት ቢኖራቸውም ከሰይጣን ውሸቶች አንዱን እያመኑ በመሆናቸው ለፍርድ እንደሚዳረጉ ያውቅ ነበር። ብቸኛው የመዳን ተስፋችን የእግዚአብሔር ቃል እንደሚገልጸው እውነት ነው። ስለሆነም፥ እውነቱን ልናውቅና እውነትን የሚጠመዝዙ ሰዎች የተሳሳቱበትን ምክንያት ገልጠን ልናሳይ ይገባል። ፍላጎታችን የተሳሳተ ትምህርት የሚያስተምሩ ሰዎችን ማዋረድ ሳይሆን፥ ሰዎች ትክክለኛውን ነገር አውቀው እንዲታዘዙ ማገዝ ሊሆን ይገባል።
የውይይት ጥያቄ፡– ስለ ይሁዳ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። በመዝገበ ቃላት ውስጥ ስለ ጸሐፊው፥ መልእክቱ ስለተላከላቸው ሰዎችና ስለ መልእክቱ ዓላማ የተገለጠውን ጠቅለል አድርገህ ጻፍ።
፩. የይሁዳ መልእክት ጸሐፊ
የውይይት ጥያቄ፡- ይሁዳ ምዕራፍ አንድን አንብብ። ሀ) የመጽሐፉ ጸሐፊ ማን ነኝ ይላል? ከገለጻው ስለዚህ ሰው ምን እንረዳለን? ለ) መልእክቱ የተጻፈው ለማን ነው? ከገለጻው ስለ መልእክቱ ተቀባዮች ምን እንረዳለን?
በጥንት ዘመን እንደተለመደው፥ ጸሐፊው ስሙ ይሁዳ መሆኑን በመግለጽ ደብዳቤውን ይጀምራል። ለመሆኑ ይህን መልእክት የጻፈው የትኛው ይሁዳ ነበር? በአዲስ ኪዳን ውስጥ የተጠቀሱ ስምንት ይሁዳ የሚባሉ ሰዎች ቢኖሩም፥ የዚህ መልእክት ጸሐፊ ሊሆኑ የሚችሉት ሦስት ብቻ ናቸው።
በመጀመሪያ፥ ከክርስቶስ አሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት አንዱ የነበረው የያዕቆብ ልጅ (ሉቃስ 6፡16)።
ሁለተኛ፥ ይሁዳ ወይም ጁዳስ፥ እንዲሁም፥ በርስያን ተብሎ የሚታወቀውና ስለ ኢየሩሳሌም ጉባኤ ውሳኔ ለአንጾኪያ ቤተ ክርስቲያን ለመናገር ከጳውሎስ፥ በርናባስና ሲላስ ጋር የተላከ አገልጋይ (የሐዋ. 15፡22)
ሦስተኛ፥ የክርስቶስ ከፊል ወንድም የነበረው ይሁዳ (ማቴ. 13፡55)። ይህችን አጭር መልእክት የጻፈው ይኸኛው ይሁዳ ሳይሆን አይቀርም። ምሁራን የሚከተሉትን ምክንያቶች በመግለጽ የይሁዳን መልእክት የጻፈው የክርስቶስ ከፊል ወንድም የሆነው ይሁዳ እንደነበር ይናገራሉ፡-
ሀ) ጸሐፊው የያዕቆብ ወንድም መሆኑን ይናገራል። በአይሁድ ባህል ብዙውን ጊዜ አንድ ሰው የእገሌ ልጅ ነኝ እንጂ የእገሌ ወንድም ነኝ ስለማይል ይኼ ያልተለመደ ነገር ነው። ነገር ግን የክርስቶስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ የኢየሩሳሌሟ እናት ቤተ ክርስቲያን ታዋቂ መሪ ነበር። ስለሆነም ይሁዳ ከአባቱ ዮሴፍ ይልቅ ሁሉም የሚያውቁትን ያዕቆብን ሲጠቅስ እንመለከታለን። ባለፈው ሳምንት እንደተመለከትነው፥ ሐዋርያው ያዕቆብ ከሞተ በኋላ ቀጣዩ ታዋቂ መሪ የነበረው ያዕቆብ የክርስቶስ ከፊል ወንድም ነበር። እርሱም የኢየሩሳሌም ቤተ ክርስቲያን መሪ ለመሆን በቅቷል።
ለ) ጸሐፊው ከሐዋርያት አንዱ ነኝ አላለም (ዮሐ 9፡17)
ሐ) የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን መሪዎች ይህን መልእክት ለመጥቀስ ጸሐፊው የክርስቶስ ወንድም የሆነው ይሁዳ እንደነበር ገልጸዋል።
ይሁዳ የክርስቶስ ወንድም መሆኑን ያልገለጸው ለምንድን ነው? የቀድሞይቱን ቤተ ክርስቲያን ታሪክ በምናጠናበት ጊዜ ከክርስቶስ ወንድሞች አንዳቸውም ወይም የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ጋር ሥጋዊ የቤተሰብ ግንኙነት ላላቸው ሰዎች ትኩረት ሲሰጡ አንመለከትም። ለምሳሌ ያህል፥ ወንጌላትም ይሁኑ የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ የክርስቶስ እናት በሆነችው ማርያም ላይ እምብዛም ትኩረት አያደርጉም። ምንም እንኳን አልፎ አልፎ በታሪኮች ውስጥ ብትታይም (ማቴ. 13፡55፤ ዮሐ 19፡25፤ የሐዋ. 1፡14)፥ የቀድሞይቱ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ እናት በመሆኗ ልዩ ክብር እንደሰጠቻት የሚያሳይ መረጃ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም። ይልቁንም መጽሐፍ ቅዱስ አጽንኦት የሚሰጣቸው ለክርስቶስ እና ለደቀ መዛሙርቱ ነው። እንደ ያዕቆብ ሁሉ ይሁዳም የክርስቶስ ወንድም ስለመሆኑ አልተናገረም። ይልቁንም ራሱንም «የኢየሱስ ባሪያ» ሲል ይጠራዋል (ያዕ. 1፡1ን ከይሁዳ 1 ጋር አነጻጽር)። ዋናው ነገር ከአንዲት እናት መወለዳቸው ሳይሆን አዳኛቸውና አምላካቸው ከሆነው ከክርስቶስ ጋር ቀጣይ ግንኙነት ማድረጋቸው ነበር። እነርሱም ቢሆኑ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ትልቅ ክብርና ሥልጣን ያገኙት የክርስቶስ ወንድሞች በመሆናቸው ምክንያት ሳይሆን፥ በመንፈሳዊ ብቃታቸው ነበር።
ይሁዳ፥ ማርያምና ዮሴፍ እንደወለዷቸው ሌሎች ወንድሞቹ ሁሉ ከክርስቶስ ጋር በገሊላ ነበር ያደገው። ማርያም ክርስቶስ በተለየ መልኩ መወለዱን ሳትገልጽላቸው አልቀረችም። ነገር ግን እነርሱ አላመኗትም። እንዲያውም፥ ክርስቶስ በቤተሰቡ ውስጥ የተለየ መሆኑ ሳያስቀናቸው አይቀርም። ክርስቶስ ይፋዊ ግንኙነቱን በጀመረ ጊዜ ወንድሞቹ መሢሕነቱን ለመቀበል ፈቃደኞች አልነበሩም። ሌሎች ሲያምኑበት የክርስቶስ ወንድሞች አእምሮው የተነካ መስሏቸው ነበር (ማር. 3፡21፤ ዮሐ 7፡1-5)። እንደ ያዕቆብ ሁሉ ከክርስቶስ ትንሣኤ በኋላ ይሁዳም አንድ አዲስ ነገር ተፈጥሮበታል። ክርስቶስ ራሱን ለያዕቆብ (ጳውሎስ የሚናገረው ስለ ሐዋርያው ያዕቆብ ሳይሆን፥ የክርስቶስ ወንድም ስለነበረው ያዕቆብ ነው) እና ለሌሎችም ወንድሞች (1ኛ ቆሮ. 15፡7) ታይቷል። ከዚህም የተነሣ በክርስቶስ አምነው ከእርገቱ በኋላ ከሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ጋር በሰገነቱ ላይ ይሰባሰቡ ነበር (የሐዋ. 1፡12-14)። ይሁዳ እንደ ያዕቆብ ዝነኛ የቤተ ክርስቲያን መሪ ሆነ። ከዚህ በኋላ ይሁዳ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ እና በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ እምብዛም ስላልተገለጸ ምን እንደ ደረሰሰት አናውቅም። አንድ የቤተ ክርስቲያን የታሪክ ጸሐፊ እንደሚለው፥ የይሁዳ የልጅ ልጆች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ለመሆን ችለዋል። ንጉሥ ዶሚቲያን (81-96 ዓ.ም) እነዚህ ልጆች ከዳዊት ዘር መሆናቸውን ሲሰማ ማርኮ ወስዷቸዋል። በዶሚቲያን ፊት ቀርበው የክርስቶስ መንግሥት ሰማያዊ እንደሆነ እና በሮም ላይ በሚፈጸም ዐመፅ ሳይሆን በዘመን መጨረሻ የሚከሰት መሆኑን ሲነግሩት ለቀቃቸው። ንጉሡ ሲያያቸው አገዛዙን የማይቀናቀኑ ተራ ድሆች ሆነው አገኛቸው።
ብዙውን ጊዜ ከዝነኛ ሰዎች ጋር ያለንን ግንኙነት በመናገር ትልቅነታችንን ለመግለጽ እንሞክራለን። «የታላቁ ወንጌላዊ ልጅ ነኝ፥ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌ ሴት ልጅ ነኝ» እያለን ራሳችንን እናስተዋውቃለን። ይህን በማድረጋችን ሁልጊዜ ልዩ ሰዎች መሆናችንን ለማሳየት እንጥራለን። ይሁዳ ግን እንዲህ ዓይነት አመለካከት ለማሳየት አልፈለገም። የክርስቶስ ወንድም ነኝ ቢል ኖሮ ሰዎች በጣም ያከብሩት ነበር። እርሱ ግን የሰውን ክብር አልፈለገም። ነገር ግን ራሱን የክርስቶስ ባሪያና የያዕቆብ ወንድም ነኝ ሲል፡-
ሀ. የክርስቶስ ባሪያ፡ ይሁዳ ከሞት የተነሣ ወንድሙን ካገኘው በኋላ ክርስቶስ አምላክ እንደሆነ ተረድቶ ነበር። ከእርሱ ጋር ያለውን ወንድማዊ ግንኙነት እየገለጸ ራሱን ከማክበር ይልቅ ክርስቶስን እንደ ባሪያ ለማገልገል ወስኖ ነበር።
ለ. የያዕቆብ ወንድም፡ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይሁዳ ተብለው የሚታወቁ ብዙ ሰዎች ስለነበሩ፥ ይሁዳ ራሱን ለማስተዋወቅ የተጠቀመበት መንገድ ብዙዎች የሚያውቁት የወንድሙን ስም መጥቀስ ነበር።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) አንዳንድ ጊዜ አማኞች ስለ ቤተሰባችን ወይም የቤተ ክርስቲያን ማንነታችንን በመግለጽ ክብር ለማግኘት የምንፈልግበትን ሁኔታ ግለጽ? ለ) ከዚህ ሁሉ ይልቅ የኢየሱስ ክርስቶስ ባሪያ ተብሎ መታወቁ የበለጠ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድን ነው። ሐ) እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ባሪያ የምትመላለስበትን ሁኔታ ግለጽ።
፪. ጸሐፊው መልእክቱን ለማን ጻፈው?
የይሁዳ መልእክት ከአጠቃላይ መልእክቶች የመጨረሻው ነው። ይህም ለአንድ ግለሰብ ወይም ለአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን ለአማኞች በአጠቃላይ የተጻፈ መልእክት ነው። ይህም ከአብዛኛዎቹ የጳውሎስ መልእክቶች የተለየ ያደርገዋል። ይሁዳ ለቤተ ክርስቲያን ግልጽ ደብዳቤ ጽፎአል። ይህ ደብዳቤ በመጀመሪያ የተጻፈው ለአይሁዳውያን ክርስቲያኖች ወይም ለአሕዛብ ክርስቲያኖች ወይም ለሁለቱም ስለመሆኑ የምናውቀው የለም። መልእክቱ ከ2ኛ ጴጥሮስ ጋር በጣም ስለሚመሳሰል ብዙ ምሁራን ይህ ደብዳቤ የተጻፈው ጴጥሮስ ለጻፈላቸውና በትንሹ እስያ ውስጥ ለሚገኙ ተመሳሳይ ግለሰቦች ነው ይላሉ። ነገር ግን በይሁዳና በ2ኛ ጴጥሮስ መልእክቶች የተገለጹት ሐሰተኛ አስተማሪዎች በሮም ግዛቶች ውስጥ ሁሉ የታወቁ በመሆናቸው ይሁዳ በሌሎች የሮም ክፍሎች ውስጥ ለነበሩ አማኞችም ጽፎ ሊሆን ይችላል። ይሁዳ አንባቢዎቹን «የተወደዳችሁ ወንድሞቼ» ብሎ መጥራቱ በግል እንደሚያውቃቸው ሊያመለክት ይችላል።
ይሁዳ ለአማኞች የሰጠውን ገለጻ ልብ ብሎ መመልከት ጠቃሚ ነው። በዚህ መልእክት ውስጥ አማኞችን በሦስት መንገድ ይገልጻቸዋል። በመጀመሪያ፥ ክርስቲያኖች «የተጠሩ» ተብለዋል። በሌላ አገላለጽ፥ እግዚአብሔር ለድነት (ደኅንነት) ጠርቶናል። ድነትን ያገኘነው በአጋጣሚ ወይም በማመን ብቻ አይደለም። ሁለተኛ፥ ክርስቲያኖች «የተወደዱ» ተብለዋል። እግዚአብሔር አብ ፍቅሩን በእኛ ላይ ገልጧል። ለዚህም እንደ ልጆቹ ወዶናል። ሦስተኛ፣ ክርስቲያኖች በኢየሱስ ክርስቶስ «ተጠብቀዋል»።
እርግጥ ነው አንባቢዎቹ ስደትና ሕይወትን የማጣት አደጋ ተጋርጦባቸው ሊሆን ይችላል። ሐሰተኛ አስተማሪዎችም ጥቃት እየሰነዘሩባቸው ይገኛሉ። ነገር ግን የክርስቲያኖች ዋስትና በራሳቸው ኃይል እምነታቸውን ለመጠበቅ በመቻላቸው ላይ ሊደገፍ አይችልም። ነገር ግን ኢየሱስ ክርስቶስ እያንዳንዱ አማኝ በሰላም ወደ መንግሥተ ሰማይ እስኪገባ ድረስ ይጠብቀዋል።
የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ይሁዳ አማኞችን በዚህ መንገድ የገለጸው ለምን ይመስልሃል? ለ) ለአማኞች ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት በዚህ መልክ መረዳቱ ለምን ይጠቅማል?
፫. የይሁዳ መልእክት የተጻፈበት ጊዜና ቦታ
ይሁዳ ይህን መልእክት መቼ እንደ ጻፈና መልእክቱን በሚጽፍበት ስፍራ የት እንደነበር ማወቅ አይቻልም። ይህን በተመለከተ ከሐዋርያት ሥራ መጽሐፍም ቢሆን፥ ከቤተ ክርስቲያን ታሪክ የምናገኘው ፍንጭ የለም። 2ኛ ጴጥሮስን ባጠናንበት ወቅት እንደተመለከትነው 2ኛ ጴጥሮስና ይሁዳ በተወሰነ ደረጃ የሚዛመዱ ይመስላል። ምክንያቱም በ2ኛ ጴጥሮስ ውስጥ የሚገኘው አብዛኛው አሳብ በይሁዳ መልእክት ውስጥም ይገኛል። ስለሆነም፥ ብዙ ምሁራን፥ አንድም ጴጥሮስ የይሁዳን መልእክት አንብቦታል፥ ወይም ይሁዳ የጴጥሮስን መልእክት አንብቦታል ይላሉ። ብዙ ምሁራን 2ኛ ጴጥሮስ መጀመሪያ የተጻፈ በመሆኑ ይሁዳ አንብቦት ይሆናል ሲሉ ይገምታሉ። ኢየሩሳሌም በ70 ዓ.ም መደምሰሷ መልእክቱ ውስጥ ስላልተገለጠ አንዳንድ ምሁራን ይሁዳ መልእክቱን የጻፈው ከዚህ ክስተት በፊት እንደ ነበር ይናገራሉ»። አንዳንዶች መልእክቱ በ68 ዓ.ም አካባቢ እንደ ተጻፈ ይገምታሉ።
ይሁንና ከ65-80 ዓ.ም መካከል ያለው ጊዜ መልእክቱ የተጻፈበትን ዘመን ሊያመለክት ይችላል። ይሁዳ ይህን መልእክት የጻፈው የት ስፍራ ሳለ እንደነበር አናውቅም። ምናልባትም አብዛኞቹ ደቀ መዛሙርትና አይሁዳውያን ክርስቲያኖች በነበሩባት ፓለስታይን ምድር ወይም ከትንሹ እስያ ተቀምጦ የጴጥሮስን ደብዳቤ አንብቦ ይሆናል።
፬. የይሁዳ መልእክት ዓላማ
ቤተ ክርስቲያን ሐሰተኛ ትምህርት ከመስማት እንድትቆጠብ በማስጠንቀቅ ይሁዳ አማኞች እምነታቸውን እንዲጠብቁ ይነግራቸዋል። «መጠበቅ» (ወይም መከላከል) የሚለው ወታደራዊ ቃል ነው። ይህም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተቀምጦ ሐሰተኛ እውነቶች ወይም የጠላት ጥቃቶች ሲሰነዘሩ ዝም ማለትን አያመለክትም። ነገር ግን ይህ ቃል የእግዚአብሔርን ቃል በማወጅ እና ሰዎች እውነትን እንዲከተሉ በማሳመን ሁሉንም ዓይነት ሐሰተኛ ትምህርቶች ማጥቃት እንዳለብን ያመለክታል። ይሁዳ የሚመለከታቸው አያሌ ስሕተቶች አሳስበውት ነበር። የእግዚአብሔር ጸጋና ድነት (ደኅንነት) ምን እንደሆኑ እና ከአማኝ አኗኗር ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ሰዎች በትክክል አልተረዱም ነበር። አንዳንድ ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን በቀዳሚነት የሚያሳስበው አኗኗራችን ሳይሆን እምነታችን ነው ይሉ ነበር። ስለሆነም ብዙዎች እግዚአብሔርን የሚያስከብር ሕይወት አይኖሩም ነበር። ይሁዳ ክርስቶስን እንከተለዋለን እያሉ በኃጢአት የሚመላለሱትን ክርስቲያኖች ያስጠነቅቃል። ሌሎች ደግሞ ስለ ክርስቶስ ማንነት የተሳሳቱ ትምህርቶችን ያስተምሩ ነበር። አንዳንዶች ክርስቶስ ፍጹም አምላክ መሆኑን አያምኑም ነበር። ሌሎች ደግሞ ፍጹም አምላክ መሆኑን ለመቀበል አልፈለጉም። ይሁዳ አማኞችም ሆኑ ሐሰተኛ አስተማሪዎች እግዚአብሔር ልክ በብሉይ ኪዳን ዘመን እንዳደረገው ከእውነት ፈቀቅ የሚሉትን በጽኑ እንደሚቀጣ ተገንዝበው ሕይወታቸውን እንዲያስተካክሉ ያስጠነቅቃቸዋል።
የይይት ጥያቄ፡- ሀ) በቤተ ክርስቲያንህ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሐሰተኛ ትምህርቶች ምን ምን ናቸው? ለ) የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እነዚህን ሐሰተኛ ትምህርቶች ለመከላከል ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?
፭. የይሁዳ መልእክት ልዩ ባሕርያት
- የይሁዳ መልእክት ከ2ኛ ጴጥሮስ ጋር ተመሳሳይ ነው (ይሁዳ 4፡6–16)ን ከ2ኛ ጴጥ. 2፡1-18፤ ይሁዳ 17–18ን፥ ከ2ኛ ጴጥሮስ 3፡2-3 ጋር አነጻጽር)። ይሁዳ 2ኛ ጴጥሮስን ካነበበ በኋላ የራሱን መልእክት ለመጻፍ በምንጭነት ይጠቀም ወይም ጴጥሮስ የይሁዳን መልእክት ይጠቀም የታወቀ ነገር የለም፤ ወይም ሁለቱም አንድ ሌላ ሰነድ በማጣቀሻነት ተጠቅመው ይሆናል። ነገር ግን ይህ ሐሰተኛ ትምህርት (ክህደት) እጅግ የከፋ በመሆኑ የሁለቱ መልእክቶች ዋነኛ ጸሐፊ የሆነው መንፈስ ቅዱስ ማስጠንቀቂያው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁለት ጊዜ እንዲጠቀስ አድርጓል።
- ይሁዳ በብሉይ ኪዳን ዘመን የተከሰተውና የእግዚአብሔርን ፍርድ በመጥቀስ ክህደት አደገኛ ውጤቶችን እንደሚያስከትል ይናገራል። እግዚአብሔር በይሁዳ ዘመንና በእኛም ዘመን የተነሡትን ሐሰተኛ አስተማሪዎች እንዴት እንደሚቀጣ ለማሳየት ጸሐፊው በመላእክት፥ ቃየን፥ ሰዶምና ገሞራ፥ እስራኤላውያን፥ በለዓምና ቆሬ ላይ የደረሰውን ፍርድ በምሳሌነት ያቀርባል። ሰዎችን ከእግዚአብሔር እውነት የሚያርቁ ሐሰተኞች በታሪክ ምዕራፍ ውስጥም ሆነ በተለይም በእግዚአብሔር ፊት ለፍርድ በሚቀርቡበት ጊዜ አስከፊ ቅጣት ያገኛቸዋል።
- አንዳንድ ምሁራን የይሁዳንና የወንድሙን የያዕቆብን አጻጻፍ ተመሳሳይነቶች ያነጻጽራሉ። ሁለቱም መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያዘው ውጭ የሚመላለሱትን ሰዎች እንደ ነቢያት አጥብቀው ይገሥጻሉ።
- ይሁዳ በብሉይ ኪዳን ውስጥ የማይገኙትን ታሪካዊ ክስተቶች ይጠቅሳል። ለምሳሌ ያህል፥ ሚካኤልና ዲያቢሎስ በሙሴ ሥጋ ላይ ያካሄዱትን ጦርነት፥ እንዲሁም ሄኖክ የሰጠውን ትንቢት ይጠቅሳል። እነዚህ ሁለቱም አሳቦች የተወሰዱት አይሁዶች በብሉይ ኪዳን መጨረሻና በአዲስ ኪዳን መጀመሪያ ላይ በነበሩት አራት መቶ ዓመታት ውስጥ ከጻፉአቸው ሌሎች ሁለት መጻሕፍት ነው። ምንም እንኳን ብዙ አይሁዶች እነዚህ መጻሕፍት የብሉይ ኪዳን አካል ናቸው ብለው ባያምኑም፥ ብዙዎች አይሁዳውያን ይጠብቋቸው ነበር። ይሁዳ እነዚህን ሁለት ታሪኮች የጠቀሰው ለመልእክቱ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት እንጂ ታሪኮቹ የተወሰዱባቸው መጻሕፍት የመጽሐፍ ቅዱስ አካል መሆናቸውን ለማሳየት አይደለም።
፮. የይሁዳ አስተዋጽኦ
- መግቢያ (ይሁዳ 1-4)
- ለሐሰተኛ አስተማሪዎች የተሰጠ ማስጠንቀቂያ (5-6)
ሀ) እውነትን ያጣጣሉ ሰዎች ስለደረሰባቸው ቅጣት የተሰጡ ታሪካዊ ምሳሌዎች (5-7)
ለ) በይሁዳ ዘመን እውነትን የማይቀበሉት ሰዎች አኗኗር (ይሁዳ 8-16)
- የእግዚአብሔር ሕዝብ እንዴት ሊኖሩ እንደሚገባ የተሰጠ ትምህርት (ይሁዳ 17-23)
- አማኞችን ከውድቀት ለሚጠብቃቸው ታላቁ አምላክ የቀረበ ምሥጋና (ይሁዳ 24-25)
የውይይት ጥያቄ፡– ይሁዳን አንብብ። ሀ) ስለ ሐሰተኛ ትምህርትና ይህንኑ ትምህርት ስለ መቋቋም የተሰጡት ማስጠንቀቂያዎች ምን ምንድን ናቸው? ለ) ክርስቲያኖች ሊመላለሱበት ስለሚገባው አኗኗር የተሰጠው ትእዛዝ ምንድን ነው?
(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)
Thank you.
God bless you.
የይሁዳ መልዕክትን በቆንጆ ሁኔታ ነው የተረዳሁት እግዚአብሔር አምላክ ብዙ ይባርካቸው