የዮሐንስ ራእይ መግቢያ

ክፍሌ ጠንካራ አማኝ ነበር። አንድ ቀን በሙስሊሞች አካባቢ እየመሰከረ ሳለ በውሸት ተከስሶ ለአምስት ዓመታት እንዲታሰር ተወሰነበት። ታሪኳ ክርስቶስን ትወድ ነበር። ነገር ግን አንድ ቀን የመኪና አደጋ ደርሶባት ከወገቧ በታች ሽባ ሆነች። ብዙ ብትጸልይም እንኳን ልትፈወስ አልቻለችም። ስንታየሁ በአንድ ጠንካራ የኦርቶዶክስ ቤተሰብ ውስጥ ያደገ ልጅ ነበር። ስንታየሁ በክርስቶስ ባመነ ጊዜ ቤተሰቡ አባረረው። ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገደደ፤ ሥራም አላገኘም። ወርቅነሽና ቤተሰቧ በመልካም ሁኔታ ሲኖሩ ሳለ በተከሰተው የመነንጃይትስ በሽታ ወረርሽኝ ሳቢያ ልጆቿና ባሏ ሞቱ።

የውይይት ጥያቄ፡– ለእነዚህ ግለሰቦች ለእያንዳንዳቸው ማጽናኛ ለመስጠት ከመጽሐፍ ቅዱስ የትኞቹን ዐበይት እውነቶች ትጠቀማለህ? 

ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው መጽሐፍ (የዮሐንስ ራእይ) በታላቅ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ተስፋ የሚዘራ መጽሐፈ ነው። መጽሐፉ በተጻፈበት ጊዜ ብዙ አማኞች ታስረው ነበር። አንዳንዶቹም በእምነታቸው ምክንያት ሞተው ነበር። ብዙ አማኞች የመግዛትና የመሸጥ ነጻነታቸውን ስለተነፈጉ በኢኮኖሚያዊ ችግሮች ውስጥ ተዘፍቀው ነበር። በተጨማሪም፦ የተለመዱ የሕይወት ችግሮች ነበረባቸው። አንዳንዶቹ ታመው ሊድኑ አልቻሉም። የሚወዷቸው ሰዎች በተፈጥሮ አደጋ ሞተውባቸዋል። እንደ ብዙዎቻችን፥ እነዚህ ነገሮች «ለምን» እንደሚከሰቱ ለማወቅ ይፈልጉ ነበር።

ማበረታቻም ያስፈልጋቸው ነበር። የዮሐንስ ራእይ የተጻፈው በመከራ ውስጥ ላሉት የእግዚአብሔር ሕዝብ ተስፋ ለመስጠት ነበር። የተስፋው መልእክት የመጣው ግን ባልተጠበቀ መንገድ ነው። ጸሐፊው፥ ከችግሮች ስለጠራ ወይም በክርስቶስ ማመን ነገሮችን መልካም ስለማያደርግበት ዓለም ሳይሆን ችግሮች እየጨመሩ ስለሚሄዱበት ዓለም ይገልጻል። እንደ ጦርነት፥ ረሃብ፥ በሽታ፥ ሞት፥ ክፉ መሪዎችና ለእምነት ሰማእት ሆኖ ማለፍ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ተጠቅሰዋል። ነገር ግን ወደ ክርስቶስ ምጽአት እየተቃረብን ስንሄድ ይበልጥ እየከፋ ከሚሄደው ከአሁኑ ዓለም የታሪክ ጽልመታም ምስል ባሻገር፥ ሁለት ተስፋ ሰጪ ብርሃናት አሉ። በመጀመሪያ፥ የእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ብርሃን አለ። የዮሐንስ ራእይ በሁሉም ሁኔታዎች ውስጥ እግዚአብሔር የሚሆነውን እንደሚወስን ይናገራል። ይህንንም የሚያደርገው ለራሱ መልካም ዓላማ ነገሮችን በመቆጣጠር ነው። ሁለተኛ፥ የመንግሥተ ሰማይ ብርሃን አለ። መንግሥተ ሰማይ ስደት፥ በሽታ፥ ሞት ወዶም መከራ የሌለባት ዘላለማዊ ከተማ ናት። ክፋት በሌለበት ደስታ እፎይ የምንልበት መልካም ዘመን ይመጣል። ዛሬ የሚያጋጥመን ሁሉ ጊዜያዊ ነው (1ኛ ቆሮ. 4፡16-18)። ስለሆነም ልንበረታታ ይገባል። የዚህ መከራ ፍጻሜ ተቃርቧል። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) እነዚህ ሁለት እውነቶች ጽልመታዊና ጎጂ ሁኔታዎች በሚገጥሙን ጊዜ የሚጠቅሙን እንዴት ነው?

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ስለ ዮሐንስ ራእይ ከመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት አንብብ። በመዝገበ ቃላት ውስጥ ስለ ጸሐፊው፥ ስለ መጽሐፉ፥ ስለ አንባቢዎቹ እና ስለ መጽሐፉ ዓላማ የተገለጸውን ጠቅለል አድርገህ ግለጽ። ለ) ራእይ 1፡4፥9 አንብብ። ጸሐፊው ማን ነው? እራሱንና ያለበትን ሁኔታ የገለጸው እንዴት ነው?

የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ በተለያዩ ስሞች ተጠርቷል። እንደ አማርኛ ስሙ ሁሉ ብዙ ጊዜ «የዮሐንስ ራእይ» ተብሎ ተጠርቷል። ይህ የመጽሐፉ ጸሐፊ ዮሐንስ መሆኑንና ከእግዚአብሔር ስለተቀበላቸው ራእዮች መጻፉን ያሳያል። ምናልባትም የሚሻለው ርእስ «የኢየሱስ ክርስቶስ ራእይ» የሚለው ይሆናል። ምክንያቱም ራእዩ የሚያተኩረው በጸሐፊው በዮሐንስ ላይ ሳይሆን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነው። «ራእይ» የሚለው ቃል በግሪኩ ቋንቋ ዮሐንስ የተመለከተውን ራእይ ብቻ የሚያሳይ አይደለም። ነገር ግን የኢየሱስ ክርስቶስን ማንነት፥ አሁንና ወደፊት ምን እንደሚሠራ የሚያሳየውን መገለጥ ጭምር ያመለክታል።

፩. የዮሐንስ ራእይ ጸሐፊ 

በመጽሐፉ ውስጥ አምስት ጊዜያት ጸሐፊው ራሱን ዮሐንስ ሲል ይጠራዋል (ራእይ 1፡4፥ 9፥ 22፡8)። እንደ ዮሐንስ ወንጌል፥ 1ኛ፥ 2ኛና 3ኛ ዮሐንስ ሁሉ በዚህ ስፍራ የተጠቀሰው ዮሐንስ የትኛው እንደሆነ ምሁራን ይከራከራሉ። የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ሽማግሌ ዮሐንስ የተባለ ሌላ የታወቀ የቤተ ክርስቲያን መሪ ነው የሚሉ ምሁራን አሉ። እነዚህም ምሁራን በራእይ ውስጥ ጸሐፊው በሕይወት ሳለ ክርስቶስን እንዳየው ወይም ሐዋርያ እንደሆነ የሚያሳይ ፍንጭ እንደሌለ ይገልጻሉ። ዮሐንስ ወንጌልን ከዮሐንስ ራእይ ጋር በማወዳደር፥ የቋንቋ አጠቃቀማቸው የተለያየ ስለሆነ ጸሐፊዎቹም የተለያዩ ናቸው ብለው ያስባሉ። በራእይ ውስጥ የሚታየው የግሪክ ቋንቋ ከዮሐንስ ወንጌልም ሆነ ከ1ኛ ዮሐንስ መልእክት ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ጥራት እንዳለው ይገልጻሉ።

የቤተ ክርስቲያንን ትውፊት ለሚከተሉ እና ለዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ፥ ሐዋርያው ዮሐንስ ነው ማለቱ የተሻለ ይመስላል። ከራእይ መጽሐፍ ውስጥ ስለ ጸሐፊው የሚከተሉትን ነገሮች እንረዳለን።

ሀ) ጸሐፊው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍትን የሚያውቅ አይሁዳዊ ነበር።

ለ) ጸሐፊው በትንሹ እስያ የሚገኙ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት የሚያውቁት የቤተ ክርስቲያን መሪ ነበር።

ሐ) በንጉሥ ዶሚቲያን ዘመን በምርኮኛነት ተወስዶ ፍጥሞ በምትባል ደሴት ውስጥ ታስሮ ነበር።

እነዚህ ነገሮች የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ስለ ሐዋርያው ዮሐንስ የሚናገረውን አሳብ ይደግፋሉ። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ዮሐንስ ወደ ትንሹ እስያ መሄዱንና በእስያ ውስጥ በጳጳስነት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ያመለክታል። አብዛኞቹ ቀደምት ጸሐፊዎች የዚህ መጽሐፍ ጸሐፊ ሐዋርያው ዮሐንስ መሆኑን ይመሰክራሉ። የዮሐንስ ወንጌልና 1ኛው ዮሐንስ የተጻፉት በሌላ ጸሐፊ እገዛ ከሆነ እና ዮሐንስ ራእይን ራሱ ዮሐንስ ከጻፈው፥ በመጽሐፎቹ ውስጥ የግሪክ ቋንቋ የጥራት ልዩነት የተከሰተው በዚህም ምክንያት ሊሆን ይችላል። ራእይ ከዮሐንስ ወንጌል ወይም ከ1ኛ ዮሐንስ የሚለይ የሥነ ጽሑፍ ዓይነት ስለሆነ፥ ይህም ልዩነቶች እንዲታዩ ሊያደርግ ይችላል። ዮሐንስ ራሱን «ሐዋርያ» ብሎ ያላስተዋወቀው ምናልባት አማኞቹ ስለሚያውቁት ይሆናል። በመሆኑም ዮሐንስ ራሱን «እኔ ወንድማችሁ የሆንሁ ከእናንተም ጋር አብሬ መከራውንና መንግሥቱን የኢየሱስ ክርስቶስንም ትዕግሥት የምካፈል ዮሐንስ» ሲል ያስተዋውቃል (ራእይ 1፡9)። ዮሐንስ በሕይወት ያለ የመጨረሻ ሐዋርያ ቢሆንም፥ ራሱን ከተራ ምእመናን አስበልጦ አላየም። ሁላችንም የእግዚአብሔር ልጆች እና የመንግሥቱ ተካፋዮች በመሆናችን፥ በእምነት ከሌሎች አማኞች ጋር ወንድማዊ ግንኙነት እንዳለው ተረድቷል። ዮሐንስ ሌሎች ከሚጋፈጡት ስደት ራሱን ለማግለል አልፈቀደም። ይልቁንም በመከራቸው ሊካፈል ወደደ። ይህም እንደ እነርሱ ሁሉ በትዕግሥት መጽናትን ጠይቆታል።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ዮሐንስ ስለ ሥልጣኑ እና ስደቱ ከገለጻው ስለ አመራር ምን ልንረዳ እንችላለን? ለ) ብዙ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከስደት ለማምለጥ ወይም ቤተሰቦቻቸው ስደትን እንዳይጋፈጡ ለመከላከል የሚጠቀሙት ለምንድን ነው? ይህ ተግባራቸው ለምእመናን ስለ አመራር የሚያስተላልፈው መልእክት ምንድን ነው?

፪. መልእክቱ የተጻፈው ለማን ነበር? 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ራእይ 1፡4፤ 11 አንብብ። ይህ መጽሐፍ የተጻፈው ለማን ነው? ለ) ለ«ሀ» ጥያቄ የሰጠኸውን መልስ በራእይ 2-3 አብያተ ክርስቲያናት ከተዘረዘሩበት ቅደም ተከተል ጋር አነጻጽር። 

ዮሐንስ መጽሐፉን የጻፈው «በእስያ ላሉት አብያተ ክርስቲያናት» ነበር። ወደ በኋላ እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት በኤፌሶን፥ ሰምርኔስ፥ ጴርጋሞን፥ ትያጥሮን፥ ሰርዴስ፥ ፊልድልፍያ እና ሎዶቅያ የሚባሉ መሆናቸውን ይገልጻል። ሌሎች እንደ ቆላስያስ ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በእስያ ግዛት ውስጥ የነበሩ ቢሆንም፥ ዮሐንስ ግን አልጠቀሳቸውም። ምናልባትም ዮሐንስ የጠቀሳቸው በእስያ ውስጥ የሚገኙ ታላላቅና ታዋቂ አብያተ ክርስቲያናት ሳይሆኑ አይቀርም። በእስያ ውስጥ እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን የሚጋፈጠው ችግር ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነበር። በመሆኑም የመጽሐፉ ግልባጭ በሚደርሳቸው ጊዜ መንፈስ ቅዱስ እንዲያውቁ የሚገልጸውን ለመረዳት ይችሉ ነበር።

የዮሐንስ ራእይ ከአንዱ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሌላው እየተላለፈ አማኞች ፊት የሚነበብ ረጅም ክፍት ደብዳቤ ነው። የአብያተ ክርስቲያናቱ ስም የተዘረዘረው መልእክተኛው በሚጓዝባቸው ስፍራዎች ቅደም ተከተል ነው። በፍጥሞ ደሴት የተጻፈው መጽሐፍ መጀመሪያ ወደ ኤፌሶን ይላካል። ኤፌሶን የእስያ የወደብ ከተማ እና እናት ቤተ ክርስቲያን ነበረች። ከዚያ መልእክተኛው ወደ ሰምርኔስና ጴርጋሞን ይጓዛል። ከዚያም ወደ ኋላ ተመልሶ በምሥራቅ አቅጣጫ ወደ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት መልእክቱን ያደርሳል።

ምንም እንኳን መጽሐፉ የተጻፈው ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ቢሆንም፥ ዮሐንስ ይህ መጽሐፍ መጀመሪያ በእስያ ላሉት ከዚያም በሮም ግዛት ለሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንደሚደርስ ያውቅ ነበር።

እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት አብዛኞቹ እንዴት እንደ ተመሠረቱ አልተገለጸም። ወንጌል መጀመሪያ ወደዚህ ክፍል የመጣው (በተለይም ወደ ኤፌሶን) በጳውሎስ ሁለተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ወቅት ነበር (የሐዋ. 18፡18-22)። ጳውሎስ በሦስተኛው የወንጌል መልእክተኝነት ጉዞ ወቅት በኤፌሶን ከተማ ከሁለት ዓመታት በላይ ተቀምጦ ወንጌልን ሲሰብክ ቆይቷል። ሉቃስ ከዚች የኤፌሶን ከተማ የእስያ ሕዝብ ሁሉ ወንጌልን እንደሰማ ይናገራል (የሐዋ. 19፡19)። በእስያ ውስጥ በሚገኙ ዐበይት ከተሞች ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት የተተከሉ ይመስላል። ጳውሎስ ወደ በኋላ በቆላስይስና በሎዶቅያ ስለነበሩት አብያተ ክርስቲያናት ይነግረናል (ቆላ. 4፡13-15)። ስለሆነም እነዚህ ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት (እንዲሁም ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት) ጳውሎስ በኤፌሶን ከተማ ውስጥ በነበረባቸው ሁለት ዓመታት ውስጥ የተመሠረቱ ይመስላል። ጳውሎስ ከታሠረ ከጥቂት ጊዜያት በኋላ (ምናልባትም ከሞተ በኋላ) ሐዋርያው ዮሐንስ ወደ ትንሹ እስያ ተጓዘ። በዚያም በምዕራባዊ የትንሿ እስያ ክፍል አብያተ ክርስቲያናትን እያስተባበረ የሽማግሌነት ወይም የጳጳስነት አገልግሎት ሲሰጥ ቆይቷል። በመሆኑም ዮሐንስ እነዚህን ሰባት አብያተ ክርስቲያናት የጎበኘና በቅርበት ያወቃቸው ይመስላል። ዮሐንስ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ (100 ዓ.ም አካባቢ) በዚህ አካባቢ ሲያገለግል ታይቷል። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚያመለክተው በፍጥሞ ደሴት ጥቂት ጊዜ ካሳለፈ በኋላ በ95 ዓ.ም አካባቢ ወደ ኤፌሶን ተመለሰ። በዚያም አርጅቶ ሞቷል።   

፫. ራእይ የተጻፈበት ዘመንና ስፍራ 

ክርስቲያኖች በስደት ውስጥ እንደነበሩ ከራእይ መጽሐፍ ውስጥ በግልጽ ይታያል። በመጀመሪያው ምእተ ዓመት ውስጥ ሮማውያን በክርስቲያኖች ላይ ሁለት ጊዜ ስደቶችን አስነሥተው ነበር። የመጀመሪያው ስደት የተከሰተው በኔሮ ዘመነ መንግሥት ነበር (54-68 ዓ.ም)። ጴጥሮስና ጳውሎስ በሰማእትነት የተገደሉት በዚህ የስደት ጊዜ ነበር። አንዳንድ ምሁራን የዮሐንስ ራእይ የተጻፈው በዚህ ጊዜ እንደነበር ይናገራሉ። ምናልባትም በ70 ዓ.ም ኔሮ ከሞተ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ይህ መጽሐፍ እንደተጻፈ ይናገራሉ። ሁለተኛው የስደት ጊዜ በዶሚቲያን ዘመነ መንግሥት ነበር (81-96 ዓ.ም)። የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚያሳየው፥ ሐዋርያው ዮሐንስ ታሥሮ የተወሰደውና በፍጥሞ ደሴት እንዲቀመጥ የተደረገው በዚህ ጊዜ ነበር። (የፍጥሞ ደሴት ከኤፌሶን 60 ኪሎ ሜትሮች ያህል ርቃ የምትገኝ ስፍራ ነበረች። ይህች አነስተኛ ደሴት 10 ኪሜ ስፋትና 15 ኪ.ሜ ርዝመት ነበራት።) ዮሐንስ ከታሰረ በኋላ እንደ ሌሎች አማኞች ለምን ሳይገደል እንደ ቀረ የተገለጸ ነገር የለም። ምናልባትም የአካባቢው የመንግሥት ባለሥልጣናት ዮሐንስ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቱን እንዳያቋርጥ በመፈለጋቸው ከትንሹ እስያ እንዲርቅ ይሆናል የፈለጉት። ያለ እርሱ አመራር ቤተ ክርስቲያን ልታድግ እንደማትችልና የክርስቲያኖች እንቅስቃሴ በቀላሉ እንደሚደክም ገምተው ነበር። ወይም ደግሞ ዮሐንስ ሽማግሌ በመሆኑ ሊገድሉት አልፈለጉ ይሆናል። ሽማግሌ በመሆኑ ምክንያት እዚያው በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚሞት ተስፋ አድርገው ነበር። ይሁንና ዮሐንስ በፍጥሞ ደሴት ታስሮ ሳለ ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ገለጠለት። ዮሐንስ ይህንን የአዲስ ኪዳን የመጨረሻ መጽሐፍ የጻፈው ምናልባትም በ95 ዓ.ም አካባቢ ሳይሆን አይቀርም። 

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

Discover more from

Subscribe now to keep reading and get access to the full archive.

Continue reading