ሰባት የማኅተም ፍርዶች (ራእይ 6፡1-8፡1)

የውይይት ጥያቄ፡– ራእይ 6-9 አንብብ። ሀ) ስድስቱን የማኅተም ፍርዶች ዘርዝር። ለ) በአንድ መቶ አርባ አራት ሺህዎቹ ላይ ምን እንደሚደርስ ግለጽ። ሐ) በሰማይ የታዩትን እጅግ ብዙ ሕዝብ ግለጽ። መ) ስድስት የመለክት ፍርዶችን ዘርዝር። ሀ) እግዚአብሔር አሁንም ሆነ ወደፊት በምድር ላይ የሚከናወኑትን ነገሮች ስለ መቆጣጠሩ እነዚህ ምዕራፎች ምን ያስተምሩናል? ረ) እነዚህ ምዕራፎች ስለ መጨረሻው ዘመን ባሕርይ ምን ያስተምሩናል?

እግዚአብሔር ለልጆቹ በሰማይና በምድር የሚከናወኑ ተግባራት በእርሱ የተወሰኑ መሆናቸውን ለማሳየት ይፈልጋል። በራእይ 4-5፥ እግዚአብሔር ለዮሐንስ በሰጠው ራእይ አማካኝነት የሰማይን የዙፋን ክፍል ያሳየናል። በዚያ ዙፋን አካባቢ ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ በመሆናቸው ምክንያት የፍርሃት ምልክት ሲከሰት አንመለከትም። ሰይጣን ሊያደርግ የማይገባውን በማድረጉ ወይም በማሸነፉ ምክንያት የታየ ጭንቀት አልተጠቀሰም። በቤተ ክርስቲያን ድክመት ምክንያት ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ መሆናቸውም አላሳሰበም። ነገር ግን ዙፋኑ በኃይል፥ በሥልጣን፥ በቁጥጥርና በልበ ሙሉነት የተሞላ ነው። እግዚአብሔር ነገሮችን ሁሉ ሙሉ በሙሉ የሚቆጣጠር ፍጹማዊ ገዢ በመሆኑ ፍጥረታት ሁሉ ያመሰግኑታል። ለመሆኑ ታላቁ አምላክ አገዛዙን የሚያከናውነው እንዴት ነው? ዮሐንስ እግዚአብሔር አብ ለወልድ የታሪክን ጥቅልል በመስጠት በምድር ላይ የሚከናወኑትን ነገሮች ሁሉ እንዲቆጣጠር ማድረጉን ያሳየናል። በራእይ 6-19፥ እግዚአብሔር በምድር ላይ ነገሮችን የሚቆጣጠር ማን እንደሆነ ብቻ ሳይሆን፥ በመጨረሻው ዘመን የሰውን ልጅ ታሪክ ከፍጻሜው ለማድረስና የኢየሱስ ክርስቶስን ዘላለማዊ መንግሥት ለመመሥረት እንዴት ተግባሩን እንደሚያከናውንም ያሳየናል።

ምሁራን እነዚህ ፍርዶች መቼ እንደሚፈጸሙ በሚያቀርቧቸው አሳቦች ይለያያሉ። አንዳንዶች ራእይ 6–19 ታላቁ መከራ የተባለውንና ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ምድር ሊመለስ ሲል የሚፈጸመውን የሰባት ዓመታት የመከራ ክፍለ ጊዜ ያመለክታል ይላሉ። እነዚህ ምሁራን በዚህ ክፍለ ጊዜ ውስጥ የእግዚአብሔር ጽኑ ፍርድ በምድር ላይ እንደሚወርድ አማኞች ታይቶ የማይታወቅ ስደት እንደሚደርስባቸውና በእነዚህ ራእዮች እንደተገለጸው ሐሳዊ መሢሕ በምድር ላይ እንደሚገዛ ይናገራሉ። ሌሎች ምሁራን ደግሞ እነዚህ ክርስቶስ ወደ ምድር ሊመለስ ሲል በምድር ላይ የሚከሰቱ ፍርዶች መሆናቸውን ቢገልጹም፥ የጊዜ ገደቡን አይወስኑም። እነዚህ እውነቶች አሁን በምድር ላይ ረሃብና ስደት በእኛ ላይ ሐዘንን በሚያስከትሉበት ወቅት በሰማይ ላይ ስለሚከሰቱት ነገሮች የሚያሳዩ ናቸው ብሎ መቀበሉ የሚሻል ይመስላል። ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ኢየሱስ ክርስቶስ ሊመለስ ሲል ሙሉ በሙሉ ይፈጸማሉ።

፩. ስድስት የማኅተም ፍርዶች (ራዕይ 6)

በጥንት ዘመን ደብዳቤ ወይም ጠቃሚ ሰነድ በማኅተም ይታተም ነበር። ይህም የሚሆነው በመጽሐፉ ጥቅልል ጫፍ ላይ ሰም በመጨመርና ከሰሙ ላይ ደብዳቤውን የጻፈው ግለሰብ ቀለበት እንዲያርፍ በማድረግ ነበር። በዚህም ጊዜ አንድ ሰው ያለ ፈቃድ ደብዳቤውን መክፈቱ በቀላሉ ይታወቅ ነበር። ክርስቶስ የተቀበለው የመጽሐፍ ጥቅልል እጅግ ጠቃሚ በመሆኑ በሰባት ማኅተሞች ታትሟል። አንዳንድ ምሁራን ይህ እያንዳንዳቸው መጻሕፍት በአንዳንድ ማኅተሞች የታተመበትን ሁኔታ ያሳያል ይላሉ። እያንዳንዱ የማኅተም ፍርድ በአንዳንድ ጥቅልል ላይ እንደ ተጻፈና ክርስቶስም እያንዳንዱን ፍርድ በሚያመጣበት ጊዜ ይህንኑ ጥቅልል እንደሚያነብ ይናገራሉ። ዮሐንስ የሚናገረው ይህንኑ ይሁን ወይም ሰባት ማኅተሞች ያረፉባት አንድ ትልቅ የመጽሐፍ ጥቅልል በትክክል ለማወቅ ያስቸግራል። የማኅተም ፍርዶች የመጨረሻውን ዘመን ባሕሪ በሰፊው ይገልጻሉ። ዮሐንስ ክርስቶስ በጥቅልሉ ላይ ያለውን ማኅተም በከፈተና የተጻፈውን መልእክት ባነበበ ቁጥር ምን እንደሚከሰት ይገልጻል፡-

ሀ) የመጀመሪያው ማኅተም፡ በነጭ ፈረስ የሚጋልበው ሰው ድል እንዲነሣ ሥልጣን ተሰጠው። ምሁራን ይህ ፈረሰኛ ማን እንደሆነ ይከራከራሉ። ጋላቢው ጠላቶቹን ድል የሚነሣው ክርስቶስ ይሆን? ወይስ ዓለምን እንዲያሸንፍ መብት የተሰጠው ሐሳዊ መሢሕ? በአመዛኙ ግን አንዱ አገር ሌላውን ለማሸነፍ በሚፍጨረጨርበት ጊዜ የሚታየው የጦርነትና የማሸነፍ መንፈስ ነው። ይህ ሌላውን የማሽነፍ መንፈስ በመጨረሻው ዘመን እያየለ ይሄዳል።

ለ) ሁለተኛው ማኅተም፡ በቀይ ፈረስ ላይ የተቀመጠው ጋላቢ ትልቅ ሰይፍ ተሰጠው። ይህ ሰዎች እርስ በርስ መገዳደላቸውን ያሳያል፡፡ የመጀመሪያው ማኅተም አገሮች እርስ በርሳቸው እንደሚዋጉ የሚያመለክት ሲመስል፥ ይሄኛው ግን በእያንዳንዱ አገር ውስጥ የሚከሰተውን የእርስ በርስ ውጊያ የሚያሳይ ይመስላል። በዚህም ጊዜ ከጥቂት ዓመታት በፊት በሩዋንዳ እንደተከሰተው በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ጎሳዎች እርስ በርሳቸው ይጨፋጨፋሉ። ምንም እንኳ ይህ ታሪክ ሁሉ የተለመደ ችግር ቢሆንም፥ ወደ መጨረሻው ዘመን አካባቢ የአገር ውስጥ ዐመፆችና የጎሳዎች መዋጋት እየጨመረ ይሄዳል። በዚህም ብዙ ሰዎች ይገደላሉ።

ሐ) ሦስተኛው ማኅተም፡ በጥቁር ፈረስ ላይ የተቀመጠው ሰው ምግብን ለመመዘን ሚዛን ይዟል፡፡ ይህ ፈረስ ረሀብን ያመለክታል። ከጦርነትና ከእርስ በርስ ግጭት፥ እንዲሁም ከአየር መዛባት የተነሣ በዓለም ላይ ረሃብ ይከሰታል። ይህ ራእይ አነስተኛ ስንዴ (ብዙ ሰዎች የሚመገቡት የምግብ ዓይነት) ለማግኘት ብዙ ገንዘብ እንደሚጠይቅ ያስረዳል። አንድ ሰው ብቻ ሊመገብ የሚችለውን ስንዴ ለማግኘት ሙሉ ቀን መሥራት ያስፈልጋል። ብዙዎች የማይወዱትን ማሽላ ለማግኘት ደግሞ የአንድ ቀን ትጋትን ይጠይቃል። ይህም ጥቂት ሰዎች ላሉበት ቤተሰብ የአንድ ቀን ምግብ ይሆናል።

መ) አራተኛ ማኅተም፡ ሞት የተባለ ጋላቢ ከገረጣ ፈረስ ላይ ይቀመጥና ሲዖል ይከተለዋል። ከጦርነት፥ ከእርስ በርስ ግጭቶች፥ ከረሃብ፥ ከበሽታና ከሌሎችም መቅሰፍቶች የተነሣ፥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ይሞታሉ። በዚህ ስፍራ ሲዖል የሚያመለክተው የዘላለምን ፍርድ ሳይሆን፥ እስከ ፍርድ ጊዜ ድረስ ኃጢአተኞች የሚቆዩበትን ጊዜያዊ ስፍራ ነው።

ሠ) አምስተኛው ማኅተም፡ በሰማዕትነት ያለፉ የታማኝ አማኞች ነፍሳት፡፡ ይህ ማኅተም በዚህ ጊዜ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ የሚደርሰውን ሁኔታ እንጂ እግዚአብሔር በዓለም ላይ የሚያመጣውን ፍርድ አይገልጽም። ይህ ታላቅ ስደት የሚከሰትበት ወቅት በመሆኑ በእግዚአብሔር ቃልና ለምስክርነታቸው (ስለ ክርስቶስ በመመስከራቸውና የተቀደሰ ሕይወት በመኖራቸው) ይገደላሉ። እግዚአብሔር አማኞች በምድር ላይ ቀላል ሕይወት እንደሚያሳልፉ ቃል አልገባላቸውም። ነገር ግን ለእምነታችን እንድንሞት ጠርቶናል። ስለሆነም በታማኝነት ለመጽናት መቁረጥ አለብን። ከኃጢአተኞች ጋር በሲዖል ከመኖር ይልቅ እነዚህ ነፍሶች ወደ እግዚአብሔር ቀርበው እንመለከታለን። እነርሱ የነበሩበት የሰማይ መሠዊያ ከእግዚአብሔር ዙፋን ፊት የሚገኝ ነው። ሞት አማኞችን ወደ እግዚአብሔር አምጥቷቸዋል። እነዚህ በሰማዕትነት ያለፉ አማኞች እግዚአብሔርን «እስከ መቼ?» እያሉ ይጠይቁታል። ይህም የአሳደዷቸው ሰዎች ላይ እግዚአብሔር መቼ ፍርዱን እንደሚሰጥ መጠየቃቸውን ያመለክታል። እግዚአብሔር ግን እንዲጠብቁ ይነግራቸዋል። የእግዚአብሔር የታሪክ ዕቅድ ከፍጻሜው ከመድረሱ በፊት ገና ብዙ አማኞች ይሞታሉ።

ይህ ዛሬ ተወዳጅነት ያለው መልእክት አይደለም። ነገር ግን በብዙ የአዲስ ኪዳን መልእክቶችና በተለይም በዚሁ በዮሐንስ ራእይ ውስጥ እንደተመለከትነው እግዚአብሔር ልጆቹ ለእምነታቸው እንዲሞቱ ይጠይቃቸዋል። ለእርሱ ታማኞች ሆነን በመቆም ታማኝነታችንንና ፍቅራችንን እንድንገልጽለት ይፈልጋል። እግዚአብሔር የልጆቹን ሞት በፍጥነት አይበቀልም። ነገር ግን በራእይ 17-19 እንደምንመለከተው እግዚአብሔር የኋላ ኋላ ጠላቶቹን (ጠላቶቻችንን) በሙሉ ይቀጣቸዋል።

ረ) ስድስተኛው ማኅተም፡ ምድርን ብቻ ሳይሆን ሰማይን ጭምር ያናወጠ ታላቅ የምድር መንቀጥቀጥ። ክርስቶስ ሊመለስ ሲል ምድር በደም መፍሰስና በሞት ከመሞላቷ ባሻገር ፍጥረት ሁሉ ይናወጣል።

ይህን ሁሉ ሲመለከቱ ነገሮችን ሁሉ ልንቆጣጠር እንችላለን የሚሉት ታላላቅ መሪዎች ሳይቀሩ የምድር ነዋሪዎች ሁሉ በፍርሃት ይወጣሉ። የእግዚአብሔርን ኃይለኛ ፍርድ ከመቀበል ይልቅ የተፈጥሮ አደጋ ቢደርስባቸው ይመርጣሉ።

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ክርስቶስ ሊመለስ ሲል የሚከሰተው የመጨረሻ ዘመን ሁኔታ ምን እንደሚመስል ጠቅለል ባለ መልኩ ግለጽ፡፡ ለ) ዛሬ በሚኖሩት አማኞች ውስጥ እነዚህ እውነቶች ምን ለውጥ ሊያመጡ ይገባል? ሐ) አንድ ያልተጠበቀ አደጋ በሚደርስበት ጊዜ የአማኞች እምነት ሲናጋ የተመለከትከው እንዴት ነው? 

ያልተጠበቁ ችግሮች በሚደርሱብን ጊዜ በአብዛኛው ግራ መጋባትና ጥርጣሬ ይወርሩናል፡፡ እግዚአብሔር በምድር ላይ ከማንኛውም ዓይነት ስደትና መከራ እንደሚጠብቀን የሚያስተምሩ ሰዎች አሉ። ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ከመከራ ቢጠብቀንም፥ ብዙውን ጊዜ በመከራና ስደት ውስጥ እንድናልፍ ይፈቅዳል። እግዚአብሔር በዮሐንስ አማካኝነት ልጆቹ በአብዛኛው መከራ የሚቀበሉ መሆናቸውን ያስገነዝበናል። ይህም ያለምንም ግራ መጋባት፥ ፍርሃትና ጥርጣሬ ስደትንና መከራን ለመቀበል እንድንዘጋጅ ያደርገናል። ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ይህንን እውነት ባለመረዳታቸው ችግር በሚደርስባቸው ጊዜ ግራ ይጋባሉ። የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እግዚአብሔር ሕዝቡን ከስደትና መከራ እንደሚታደግ ብቻ ሳይሆን፥ በዚሁ መከራ ውስጥ እንዲያልፉ የሚፈቅድ መሆኑን ጭምር ማስተማር ያስፈልጋቸዋል። 

፪. የእረፍት ጊዜ (ማቋረጫ) (ራእይ 7፡1-8፡1)

ዮሐንስ ሰባተኛውን ማኅተምና ቀጣዮቹን የመለከት ፍርዶች ከመግለጹ በፊት፥ የመጨረሻውን ዘመን ሁለት ሌሎች ባሕርያት ለማሳየት ሲል የእግዚአብሔርን ሕዝብ ሁለት ቡድኖች ያቀርባል። ምሁራን ይህንን ቅንፍ ወይም ማቋረጫ ብለው ይጠራሉ። ምክንያቱም ይህ ሌሎች እውነቶችን ለመግለጽ ሲባል የፍርዶችን ገለጻ ማቋረጥን ያስከተለ በመሆኑ ነው። ዮሐንስ ወደ ሰባተኛው ማኅተም በመመለስ በራእይ 8፡1 ስለ እግዚአብሔር ፍርዶች ተጨማሪ ገለጻዎችን ያቀርባል።

ሀ) የአንድ መቶ አርባ አራት ሺህ ሰዎች መታተም (ራእይ 7፡1-8)፡፡ ዮሐንስ በዚህ ራእይ ውስጥ እግዚአብሔር ከእስራኤል በተመረጡት አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ ሰዎች ላይ ማኅተሙን ከማሳረፉ በፊት በምድር ላይ ፍርድ እንዳይፈጸም አራቱ መላእክት ነፋሳትን ይዘው ሲቆሙ እንመለከታለን። የዚህ ራእይ ዋንኛ ትምህርት እግዚአብሔር በልጆቹ ሁሉ ላይ ማኅተምን እንዳደረገ ማሳየት ነው። እርሱ ማን መሆናችንን ያውቃል። በእኛ ላይ የሚደርሰውን ሁሉ ይቆጣጠራል። እንዲሁም በምድር ላይ ከሚመጣው ፍርድ ሁሉ ይጠብቀናል። (ወደ በኋላ እንደምንመለከተው ሰይጣንም አውሬውን በሚያመልኩት ተከታዮች ላይ ማኅተሙን ያኖራል።) ነገር ግን ዮሐንስ ይህ ጥበቃ የግድ እማኞችን ከስደትና ከመከራ እንደማይታደግ ያሳያል። ነገር ግን በመከራና በስደት ጊዜ በእምነታችን ጸንተን እንድንቆም ያግዘናል። በራእይ 14፡1-5፥ እነዚሁ አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ ሰዎች በሰማዕትነት ካለፉ በኋላ በሰማይ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት መገኘታቸው ተገልጧል። በምድር ላይ ራሳቸውን በንጽሕና ጠብቀዋል። በእምነታቸው ሲሞቱም በሰማይ የከበረ ስፍራ አላቸው። ከእነርሱ አንዱም እንኳን አልጠፋም።

ለመሆኑ አንድ መቶ አርባ አራት ሺህዎቹ እነማን ናቸው? ለዚህ ጥያቄ የሚሰጡ ሁለት መሠረታዊ መልሶች አሉ። በመጀመሪያ፥ አንዳንድ ምሁራን እነዚህ ሰዎች በመጨረሻው ዘመን ለክርስቶስ ታማኞች ሆነው የሚጸኑትን ክርስቲያኖች በተምሳሌትነት የሚያሳዩ ናቸው ይላሉ። እነዚህ ምሁራን ዮሐንስ እግዚአብሔር ሕዝቡን ሁሉ እንደሚጠብቅና አንድም እንኳ እንደማይጠፉ ለማሳየት ሁለት ተምሳሌታዊ ቁጥሮችን፥ 10 (ሙላትን የሚያመለክት) እና 12 የእግዚአብሔርን ልጆች ሁሉ የሚያመለክት) ይጠቀማል ይላሉ። ይህን አመለካከት የሚይዙ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ያተማቸው አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ ሰዎችን ዮሐንስ በሰማይ የተመለከታቸው እጅግ ብዙ ሕዝብ አንድ ቡድን ሰዎችን የሚያመለክቱ መሆናቸውን ይናገራሉ። እነዚህም የቤተ ክርስቲያን አካል ናቸው። ሁለተኛ፥ ሌሎች ደግሞ እነዚህ አይሁዳውያን አማኞች ናቸው ይላሉ። በዚህ የታላቁ መከራ ወቅት እግዚአብሔር በአይሁዶች መካከል ስለሚሠራ ብዙ ሰዎች በክርስቶስ ያምናሉ ብለው ያስተምራሉ። (ጳውሎስ አንድ ቀን እስራኤላውያን ሁሉ እንደሚያምኑ ትንቢት ተናግሯል – ሮሜ 11፡25-26)፡፡ አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ ሰዎች (ከእያንዳንዱ ነገድ 12 ሺህ ሰዎች) እግዚአብሔር የአይሁድን ቅሬታ ለማስቀረት ሲል ከክህደት የሚጠብቃቸው አይሁዳውያን አማኞች ሊሆኑ ይችላሉ። የብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የነበሩት አይሁዶች ሙሉ ለሙሉ አይጠፉም፡፡ ሌሎች ደግሞ እነዚህን አንድ መቶ አርባ አራት ሺህ ሰዎች ወንጌልን በዓለም ሁሉ የሚያሰራጩ የተለዩ አይሁዳውያን ወንጌላውያን ናቸው ይላሉ። እጅግ ብዙዎች ሕዝብ በእነዚህ ወንጌላውያን አገልግሎት የዳኑ ናቸው። (ማስታወሻ፡ ዳን በዚህ የነገዶች ዝርዝር ውስጥ አልተጠቀሰም፡፡ ይህ የሆነው ምናልባት ከእስራኤላውያን ነገዶች በመጀመሪያ በቡድን ወደ ጣዖት አምልኮ የተመለሰው የዳን ነገድ በመሆኑ ሳይሆን አይቀርም፡፡ መሳፍንት 18)። 

የውይይት ጥያቄ፡- እግዚአብሔር ልጆቹን ማተሙ ክርስቲያኖችን በመከራ ጊዜ የሚያጽናናቸው እንዴት ነው?

ለ) በሰማይ የታየ እጅግ ብዙ ሕዝብ (ራእይ ፡9-17)። ዮሐንስ በዚህ ሁለተኛው ራእይ የእግዚአብሔር ሕዝብ በመጨረሻው ዘመን ያሉበትን ሁኔታ ይገልጻል። አሁንም ዮሐንስ በሰማይ ዙሪያ እየተመለከተ መሆኑን እናያለን። በዚህን ጊዜ ቀደም ሲል ያልተመለከታቸው ሌሎች የሕዝብ ቡድኖች በእግዚአብሔር ዙፋን ዙሪያ ቆመው ይመለከታል። ዮሐንስ ስለ እነዚህ ሰዎች ሲገልጽ፥ «እንደ ሰው እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ» ይላል። እነዚህ አማኞች በሰማያዊው አምልኮ ላይ ይተባበራሉ። ዮሐንስ እንደሚነግረን እነዚህ ሰዎች ከታላቁ መከራ የመጡ ናቸው። እነዚህ ሰዎች አይሁዶች ብቻ ሳይሆኑ በምድር ላይ ካሉ ነገዶች ሁሉ የተወጣጡ ነበሩ። አንዳንድ ምሁራን ይህ በመጨረሻው ዘመን ወንጌል በስፋት እንደሚሰራጭ ያሳያል ይላሉ። ክርስቶስ ከመመለሱ በፊት እግዚአብሔር ከሚያወርዳቸው አስከፊ ፍርዶችና የሐሳዊ መሢሕ ተቃውሞ ባሻገር፥ ሰዎች በምድር ላይ ካሉት ነገዶችና አገሮች ሁሉ ወንጌልን ሰምተው በክርስቶስ ያምናሉ። ክርስቶስ ሊመለስ ሲል፥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በክርስቶስ አምነው ለእምነታቸው ይሠዋሉ። ሌሎች ደግሞ በታሪክ ሁሉ በዓለም ውስጥ የሚካሄደውን የወንጌል ስርጭት ያሳያል ይላሉ። እነዚህ ምሁራን ታላቁ መከራ የሚጀምረው ከዮሐንስ ዘመን ጀምሮ ሲሆን፥ ክርስቶስ እስከሚመለስበት ጊዜ ይቀጥላል ሲሉ ያስተምራሉ።

ዮሐንስ በሰማይ ስለታዩት ስለ እነዚህ እጅግ ብዙ ሕዝብ በተመለከተው ራእይ ሁለት ነገሮችን አጉልቶ ያሳየናል። የመጀመሪያው፥ ክርስቶስ ከመመለሱ በፊት ወንጌሉ ምን ያህል እንደሚሰራጭ ይነግረናል፡፡ በሰማይ የሁሉም ጎሳ አባላት ተወክለው ይገኛሉ። ወንጌሉ በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ ነጮች ሃይማኖት ብቻ አይደለም። በአፍሪካ ሙስሊም ያልሆኑ የአንዳንድ ሰዎች ሃይማኖትም ብቻ አይደለም። በእስያ የሚገኙ የተመረጡ ወገኖች የሚከተሉትም አይደለም። ወንጌሉ ለሁሉም ስለሆነ በመልእክተኞቹ የታማኝነት ምስክርነትና ንጹሕ ሕይወት አማካኝነት ይህ ወንጌል ለሁሉም አገርና ጎሳ ይዳረሳል። ያኔ ክርስቶስ ይመለሳል (ማቴ. 24፡14)። ሁለተኛ ዮሐንስ እነዚህን ታማኝ የክርስቶስ ተከታዮች ስለሚጠብቃቸው ዘላለማዊ ደስታ ይናገራል። በክርስቶስ በማመናችን ምክንያት የሞትን ቅጣት መቀበሉ ሽንፈት አይደለም። ይልቁንም ይህ ከምድር ላይ ሥቃይ ወደ ሰማያዊ ክብር የምናልፍበት መንገድ ነው። በሰማይ የእግዚአብሔር ታማኝ ተከታዮች የሚወዱትን ክርስቶስን ፊት ለፊት እያዩ ያገለግሉታል። እግዚአብሔር ጠባቂያችን ይሆናል። ከእንግዲህ የምድር ላይ ሥቃይ ስደት፥ በሽታ፥ ሞት፥ ረሀብ፥ ጦርነት፥ ወዘተ መቅመስ አያስፈልገንም። ሥቃዩ ያከትምና ኢየሱስ ክርስቶስ እረኛችን ሆኖ የሚያስፈልገንን ሁሉ ያሟላልናል። 

የውይይት ጥያቄ፡- ሀ) ወንጌሉ ለሁሉም ብሔሮች እንዲዳረስ አንተና ቤተ ክርስቲያንህ ምን እያደረጋችሁ ነው? ለ) ለአማኞች ሞት ሽንፈት ሳይሆን ሥቃይ ወደሌለበትና ከእግዚአብሔር ጋር የተሟላ ግንኙነት ወደምናደርግበት ስፍራ የሚያሸጋግረን በር መሆኑን መረዳቱ ለአማኞች ለምን እንደሚያስፈልግ ግለጽ። 

፫. ሰባተኛው ማኅተም (ራእይ 8፡1) ስለ መጨረሻውና ሰባተኛው ማኅተም የምናውቀው አንድ ነገር ብቻ ነው። ክርስቶስ ይህን ማኅተም ሲከፍተው በሰማይ ለግማሽ ሰዓት ያህል ጸጥታ ይሰፍናል። ለምን? ይህ ምናልባትም በዓለም ላይ ስለሚመጡት ታላላቅ ፍርዶች ፍጥረት ሁሉ ጸጥ ብሎ በጉጉት ማሰብ የጀመረበት ሰዓት ሳይሆን አይቀርም። ብዙ ምሁራን ቀጣዮቹ ሰባት የመለከት ፍርዶች በሰባተኛው ማኅተም ውስጥ የተካተቱ መሆናቸውን ይናገራሉ። ምናልባት ደግሞ ክርስቶስ ወደ ምድር የሚመለስበት ጊዜ መድረሱን የሚያሳይ ጸጥታ ሊሆን ይችላል።

(ማብራሪያው የተወሰደው በ ኤስ.አይ.ኤም ከታተመውና የአዲስ ኪዳን የጥናት መምሪያና ማብራሪያ፣ ከተሰኘው መጽሐፍ ነው፡፡ እግዚአብሔር አገልግሎታቸውን ይባርክ፡፡)

Leave a Reply

%d bloggers like this: