ጎራህን ለይ፤ ክርስቲያን እና የፖለቲካ ተሳትፎው

አገራችን ኢትዮጵያ በከፍተኛ የለውጥ ሮለር ኮስተር (ነውጥ) ላይ እንደምትገኝ የማይስማማ ቢኖር ለዜና አውታሮች ‘ጆሮ ዳባ’ ያለ ሰው ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡ ብዙ ፖለቲከኞች ያለንበትን ሁኔታ ምድራችን በምጥ ላይ እንዳለች ሴት አድርገው ይመስሉታል፡፡ ተስፋና ጽልመት፣ ብርሃንና ጨለማ፣ ሞትና ሕይወት፣ ደስታና ሐዘን፣ እውነትና ቅጥፈት፣ መሳ ለመሳ ተያይዘው የምጡን ህመም ማብቂያ የሌለው አስመስለውታል፡፡ አገራችን ብቻ ሳትሆን መላው አለም ከእነዚህ አይነቶቹ ውጥረቶች ልትጸዳ የማትችል እንደሆነና እንዳውም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት እየቀረበ በመጣ ቁጥር ምጡ እያየለ እንደሚሄድ መጽሐፍ ቅዱስን ለሚያነብ ሰው እንግዳ ጉዳይ አይሆንም (ማቴ 24)፡፡ አሁን ጥያቄው በዚህ ሁኔታ ውስጥ፣ እንደ ክርስቲያን የአንተ፣ የአንቺና የእኔ ድርሻ ምን መሆን አለበት የሚለው ነው? እንደ አማኝ ስለ ፖለቲካ ምን አይነት አመለካከት ልንይዝ ይገባል? ተሳትፏችንስ ምን መምሰል አለበት?

ቀላል ቁጥር የሌላቸው ሰዎች፣ “ክርስቲያን በፖለቲካ ውስጥ እጁን ፈጽሞ ማስገባት የለበትም” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ በሌላው ጽንፍ የሚገኙቱ ደግሞ፣ ተቀዳሚ ተጠሪነታቸው ለመንግስት ይሁን ለሚያመልኩት አምላክ መሆኑ ግራ እስኪያጋባ ድረስ የግብረገብ መለኪያቸውን አመቻምቸው፣ ለዘራቸውና ለፖለቲካ ፓርቲያቸው ደማቸው እስኪገታተር ዘብ ሲቆሙ ይታያል፡፡ በእኔ እምነት ሁለቱም ዋልታ ረገጦች ናቸው፡፡ በመጀመሪያው ጽንፍ ውስጥ ያለው ድክመት ሕዝብን የሚያጠፋው፣ ‘የአላዋቂዎች ወሬ ሳይሆን የአዋቂዎች ዝምታ’፣ የመሆኑን እውነት የመዘንጋት ነው፡፡ ዝምታ በቦታውና በጊዜው ሲሆን መልካም ቢሆንም እንደ አማኝ የክርስትናችንን የሞራል ምርሆችና መሰረቶች የሚገዳደሩ ጉዳዮች በሚኖሩበት ጊዜ አወንታዊ ተጽእኖ መፍጠር በምንችልባቸው ሁኔታዎች ሁሉ መሳተፍ ግዴታችን ነው ብዬ አምናለው፡፡ ይህ ተሳትፎ ታዲያ ከአመጽ የጸዳ እና የክርስቲያናዊ ሕይወት መርሆዎችን ጥያቄ ውስጥ የማያስገባ መሆኑን ማረጋገጥ ግድ ይላል፡፡ በሁለተኛ ጽንፍ ውስጥ የሚታየው ድክመት ደግሞ በሁለት እግር በአንድ ጊዜ ሁለት ዛፍ ላይ የመውጣት ስካር ወይም የጎራ ጉራማይሌ ችግር ነው፡፡ የአንዳንዶችን “ክርስቲያኖች” የሶሻል ሚዲያ አካውንት ለማንበብ ጊዜ ካላችሁ የምለው ምን እንደሆነ ፍንትው ሳይልላችሁ አይቀርም፡፡ “ኢየሱስ ጌታ ነው”፣ የሚል የፕሮፋይ ፒክቸር ተጠቅመው ሲያበቁ፣ ጌታቸው ኢየሱስ ሳይሆን ዘራቸው ወይም የፖለቲካ ፓርቲያቸው ሆኖ ታገኙትና ታዝናላችሁ፡፡ ከዚያም አልፈው በሃሳብ የማይመስላቸውን ሲራገሙና ሲዝቱ፣ በጸያፍ ቃሎቻቸው ሲጋረፉ ትመለከታላችሁ፡፡ ሌሎቹ ደግሞ የተሻለ ወይም መንፈሳዊ ሊያስመስላቸው የሚያስችላቸውን ጭንብል በማጥለቅ በለስላሳ ቃላት ግብዝነት የሞላው ጭንቁር ሃሳቦችን ሲረጩ ብዙ መልካም ነገር ለመስራት የሚችሉበትን ወርቃማ ጊዚያቸውን ያባክናሉ፡፡ ጌታህ ማን መሆኑን ለእኔ አትንገረኝ፤ አንተና አመልከዋለው የምትለው አምላክ ያውቃል፡፡ ስለዚህ ሽንገላውን አቁመህ ጎራህን ለይ፡፡ ሽንገላውን አቁመሽ ጎራሽን ለዪ፡፡ ምክሬ ነው፡፡

ፖለቲካ እና መግስትን በተመለከተ አማኝ፣ ማለቴ እውነተኛ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር፣ ሊያውቃቸው የሚገባቸውን ሁለት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነታዎች እንዳጋራችሁ ፍቀዱልኝ፡፡ የመጀመሪያው እውነት አማኝ በሕይወቱ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠውና ሊሻው የሚገባው ነገር የእግዚአብሔርን መንግስትና ፈቃድ መሆኑ ነው (ማቴዎስ 6፡33)። የእግዚአብሔር እቅዶች እና ዓላማዎች ቋሚዎች እንዲሁም ፈቃዱ ደግሞ የማይናወጥ ነው፡፡ ፈቃዱን ከማድረግ የትኛውም መንግስት ሆነ ሃይል ሊያግደው አይችልም (ዳንኤል 4፡34-35)። እንዳውም እውነታው የምድር መንግስታትን ወደ ስልጣን የሚያመጣውና ከስልጣናቸው የሚያስወግደው እርሱ ራሱ መሆኑ ነው (ዳንኤል 2፡21)፡፡ ልዑል በሰዎች መንግሥታት ሁሉ ላይ እንደሚገዛና እነዚህንም መንግሥታት ለወደደው እንደሚሰጥ ለማወቅ ዳንኤል 4፡17 ማንበብ በቂ ነው፡፡ ይህንን እውነት በአግባቡ ማወቁ፣ ፖለቲካ ወይም መንግስት እግዚአብሔር ፈቃዱን ለመፈፀም የሚጠቀምበት መንገድ ወይም ዘዴ እንጂ ሌላ ነገር አለመሆኑን እንድንገነዘብ ይረዳናል (ሮሜ 13፡6)። ምንም እንኳን ክፉ ሰዎች የፖለቲካ ኃይላቸውን ለክፉ ነገር ቢጠቀሙበት፣ “እግዚአብሔር፣ ለሚወዱትና እንደ ሐሳቡ ለተጠሩት፣ ነገር ሁሉ ተያይዞ ለበጎ እንዲሠራ እንደሚያደርግላቸው እናውቃለን።” (ሮሜ 8 28)። 

ሁለተኛው እውነት፣ መንግስት የሁሉ ነገር መፍትሄ እንዳልሆነ ማወቅ ነው! ለሁሉ ነገር መፍትሄ ሊሆን የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ በአዲስ ኪዳን ኢየሱስም ሆነ ሐዋሪያቱ ክርስቲያኖች የአረማዊውንን የጣኦት አምልኮ፣ ኢ-ሞራላዊ እና ብልሹ አሰራሮችን በመንግስት በኩል እንዴት ማሻሻል እንደሚችሉ ለማስተማር ጊዜያቸውን ወይም ጉልበታቸውን ሲያጠፋ በጭራሽ አናነብም። ሐዋርያት፣ ክርስቲያኖች የሮማን ምንግሥት ኢ-ፍትሃዊ የሆኑ ህጎችን ወይም የጭካኔ እቅዶችን ለመቃወም በአመጽ እንዲሳተፉም በጭራሽ አላስተማሩም፡፡ ከዚያ ይልቅ፣ ሐዋርያት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች እና እኛን የመከሩት አንድ ነገር ቢኖር ወንጌልን እንድንሰብክ እና ለወንጌል የለውጥ ኃይል ምስክር ሊሆን የሚችል የተለየ ሕይወት እንድንኖር ነው፡፡

መንግስትን በተመለከት እኛ አማኞች ያለብን ግዴታ ወይም ሃላፊነት ከወንጌል በተቃራኒ ያልቆሙ የምድሪቱን ህጎች ማክበር እና ጥሩ ዜጎች ሆኖ መገኘት ነው (ሮሜ 13፡1-2)። ስልጣን ሁሉ ከእግዚአብሔር መሆኑን እና ይህንንም ስልጣን፣ እግዚአብሔር “ክፉ የሚያደርጉትን ለመቅጣት በጎም የሚያደርጉትን ለማመስገን…” ለሰው ልጅ የሚሰጥ መሆኑን በቅዱሱ መጽሐፋችን እናነባለን (1ኛ ጴጥሮስ 2፡13-15)። ከዚህ በተጨማሪ አማኝ፣ “ማንኛውም ሰው በሥልጣን ላሉት ሹማምንት መገዛት ይገባዋል፤ ከእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ሥልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ሥልጣናት በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው። ስለዚህ፣ በባለ ሥልጣን ላይ የሚያምፅ በእግዚአብሔር ሥርዐት ላይ ማመፁ ነው፤ ይህን የሚያደርጉትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ያመጣሉ” (ሮሜ 13፡1-2) የሚለውን የእግዚአብሔር ቃል መዘንጋት የለበትም። ይህ ማለት ግን አማኝ በምርጫ መሳተፍና የክርስትና መርሆዎቼን በአንጻሩ ያራምዱልኛል ለሚላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆነ ግለሰብ ድምጽ ከመስጠት መቆጠብ አለበት ማለት አይደለም፡፡   

ከሰይጣን ታላላቅ ማታለያዎች አንዱ የፖለቲካ እና የመንግስት ባለሥልጣናት በአገር ላይ መልካም ባህላዊ ሥነ-ምግባር እና ፈርሃ እግዚአብሔራዊ አኗኗር ሊያሰፍኑ እንደሚችሉ በማሰብ ተስፋችንን በእነርሱ ላይ እንድናሳርፍ ማድረጉ ነው፡፡ የአንድ ሀገር የለውጥ ተስፋ በማንኛውም ገዥ መደብ ውስጥ አይገኝም፡፡ ቤተ ክርስቲያን፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶችን እና ክርስቲያናዊ እሴቶችን መጠበቅ፣ ማስፋፋት እና መከላከል የፖለቲከኞች ወይም የመንግሥት የሥራ ድርሻ ነው ብላ ካሰበች ትልቁን ስህተት ሰርታለች፡፡

ቤተክርስቲያን ልዩ ናት፡፡ የእግዚአብሔር ዓላማ በፖለቲካዊ አክቲቪዝም (ንቅናቄ) ግቡን አይመታም፡፡ በመንግስት ፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ በመሰንቀር ጉልበታችንን፣ ጊዜያችንን ወይም ገንዘባችንን እንድናጠፋ የሚያዝ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያ የለም፡፡ ተልእኳችን ሀገርን በፖለቲካ ተሃድሶ መለወጥ ሳይሆን ልብን በእግዚአብሔር ቃል መለወጥ ነው፡፡ አማኞች የክርስትና እድገት እና ተፅእኖ በሆነ መንገድ ከመንግስት መልካም ፖሊሲዎች ጋር ሊንሰላሰሉ (ሊተሳሰሩ) ይችላሉ ብለው ማሰብ የጀመሩ ጊዜ የቤተክርስቲያን ተልእኮ አደጋ ውስጥ ይወድቃል፡፡ ክርስቲያናዊ ግዴታችን የክርስቶስን ወንጌል ማሰራጨት እና የዘመናችንን ኃጢያቶች ወደ ብርሃን ማውጣት ነው። የግለሰቦች ልብ በወንጌል ብርሃን መለወጥ ሲጀምር፣ ባህሉ ያንን ለውጥ ማንፀባረቅ ይጀምራል፡፡

አማኞች በሁሉም አይነት ጨቋኝ አረማዊ መንግሥታ ስር ኖረዋል፤ አልፎ ተርፎም በእነዚህ መንግሥታት ዘመን አብበዋል፡፡ በተለይም በመካከለኛው ክፍለ ዘመን ጭካኔና ግፍ በሞላቸው የፖለቲካ አገዛዞች መካከል እምነታቸውን ጠብቀው ለኖሩት የመጀመሪያው ክፍለ ዘመን አማኞች ይህ እውነት ግልጽ ነው፡፡ የዓለም ብርሃን እና የምድር ጨው የሆኑት መንግስታቸው ሳይሆን እነሱ መሆናቸውን ተረድተው ነበር። የፖለቲካ ባለስልጣኖቻቸውን ማክበር ብቻ ሳይሆን ስለ እነርሱ አብዝተው መጸለይ እንዳለባቸው የሚያዘውን የጳውሎስን ትእዛዝን አጥብቀው ይከተሉ ነበር (ሮሜ 13፡1-8)። ከሁሉም በላይ ፣ እንደ አማኞች ተስፋቸውን እግዚአብሔር ብቻ በሚሰጠው ጥበቃ ላይ ማኖር እንዳለባቸው ተገንዝበዋል፡፡ በዛሬው ጊዜም ቢሆን ሁኔታው ​​ተመሳሳይ ነው። የቅዱሳት መጻሕፍትን ትምህርቶች ስንከተል፣ እግዚአብሔር እንድንሆን እንዳሰበ የዓለም ብርሃን እንሆናለን (ማቴ. 5፡16)።

አስኳሉ ሃሳብ የሚከተለው ነው፡፡ በፖለቲካው ንፋስ ተጠልፈህ መንግሥትህ በሰማይ፣ ዜግነትህ ሰማያዊ፣ ንጉሥህም ክርስቶስ መሆኑን ዘንግተህ በዘርና ጎሳ ፖለቲካ ፍልሚያ ውስጥ የሰይጣንን የጨለማና የጥላቻ ፈቃድ እያገለገልክ ከሆነ፣ ደም ስርህ እስከሚገታተር ለፍትህ ሳይሆን በአጋጣሚ ለተገኘህበት አንድ ብሔረሰብ ዘብ የምትቆም ከሆነ፣ በማታውቀውና ባላየከው ጉዳይ ሁሉ ጥልቅ እያልክ ሁሉን አዋቂ እንደሆነ አምላክ በፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጠህ ከሆነ፣ መንግሥትን በአመጽ ለመጣልና የሹማምንትን ስም በማጠልሸት የእግዚአብሔርን ሥርአት እየተቃወምክ በራስህ ላይ ፍርድ እየጠራህ ከሆነ፣ ከክርስትናህ መርሆዎች በላይ ለፖለቲካህ ፓርቲ አመለካከቶች አጎብዳጅ ከሆንክ፣ ጊዜው ሳያልፍ ቆም ብለህ የክርስትናህን ጤናማነት ወይም እውነተኛነት መጠየቅ ይኖርብሃል፡፡ ጎራህን ለይ፡፡ በሁለት ቢላ አትብላ፡፡ የምታመልከውን አሁን ምረጥ፡፡ ዘርህን ወይም አምላክህን፤ ቋንቋህን ወይም ወንጌልን፣ የፖለቲካ ፓርቲህን ወይም ክርስቲያናዊ መርህን አንዱን ምረጥ፡፡ ሁለቱንም በአንዴ ልታመልክ አትችልም፡፡ ጌታህ ማን ነው? በአንድ ጊዜ ሁለት ጌቶችን ማገልገል የሚችል ማንም ባሪያ የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል፤ ወይም አንዱን ይጠጋል፤ ሌላውን ይንቃል። የእግዚአብሔርም የጎሳህም ባሪያ መሆን አትችልም።

ልብ ይስጠን!!!

አዳነው ዲሮ           

1 thought on “ጎራህን ለይ፤ ክርስቲያን እና የፖለቲካ ተሳትፎው”

Leave a Reply

%d