የኤጲስ ቆጶስ፣ ሽማግሌ እና መጋቢ ልዩነት ምንድን ነው?

በአዲስ ኪዳን፣ ኤጲስ ቆጶስ (bishop) በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በአማስተማሪ መሪ  (teaching leader) ሃላፊነት የሚያገለግል ሰው መጠሪያ ነው (ፊል 1:1)፡፡ የዚህ ቃል አቻ የሆነው የግሪኩ ቃል “episkapos” – “ኤጲስ ቆጶስ”፣ “ሽማግሌ”፣ “የበላይ ተመልካች”፣ ወይም “መጋቢ” ተብሎ ተተርጉሟል። ሁሉም ስያሜዎች የሚያመለክቱት አንድን የአገልግሎት ቢሮ ስለሆነ ቃሎቹ መሠረታዊ የትርጉም ልዩነት የላቸውም፡፡

በቀደሙት አብያተ ክርስቲያናት፣ መሪዎቻቸው በቀጥታ “ሽማግሌዎች” ተብለው ተጠርተዋል፡፡ ለምሳሌ፣ በሐዋ 20:17 እንዲህ እናነባለን፣ “ከሚሊጢንም ወደ ኤፌሶን ልኮ የቤተክርስቲያንን ሽማግሌዎች አስጠራቸው”፡፡ ፊልጵስዩስ 1:1 ላይ ጳውሎስ ደብዳቤውን፣ “በፊልጵስዩስ ለሚኖሩ ከኤጲስ ቆጶሳትና ከዲያቆናት ጋር በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት ቅዱሳን ሁሉ” ሲል ይጀምራል፡፡ በግልጽ እንደሚታየው በቀደመቺቱ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩት ሁለት የአመራር ስፍራዎች ብቻ ነበሩ፤ እነሱም ሽማግሌዎች (ኤጲስ ቆጶሳት) እና ዲያቆናት ናቸው፡፡

ጳውሎስ በመልእክቶች ውስጥ፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች አድርጎ ለሚመለከታቸው ሽማግሌዎች (ኤጲስ ቆጶሳት) የብቃት መመዘኛን በተመለከተ ሁለት ጊዜ ጽፏል (በእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ፣ እነዚህ ሽማግሌዎች በአጠቃላይ እንደ አንድ ነጠላ መሪ ሳይሆን እንደ ቡድን ሆነው እንደሚያገለግሉ ልብ ይበሉ)፡፡ 

የመጀመሪያው፣ በ 1ኛ ጢሞቴዎስ 3:1-7 ላይ ይገኛል፣ “ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው። እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሰራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤ ሰው ግን የራሱን ቤት እንዲያስተዳድር ባያውቅ፥ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይጠብቃታል? በትዕቢት ተነፍቶ በዲያብሎስ ፍርድ እንዳይወድቅ፥ አዲስ ክርስቲያን አይሁን። በዲያብሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥ በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል።”

በዚህ ጥቅስ ላይ በመነሳት በርካታ ነገሮችን መረዳት እንችላለን፡፡ በመጀመሪያ፣ የኤጲስ ቆጶስ ሥራ ታላቅ ሥራ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ስራው ውስን ተግባር መሆኑንም እናያለን (በአጠቃላይ የወንዶች ተውላጠ ስም ጥቅም ላይ መዋሉን ልብ ይበሉ)፡፡ ሦስተኛ፣ የግብረገብ ልእልና ወሳኝ ሆኖ እናያለን:- (የማይነቀፍ፥ የአንዲት ሚስት ባል፥ ልከኛ፥ ራሱን የሚገዛ፥ እንደሚገባው የሚሰራ፥ እንግዳ ተቀባይ፥ ለማስተማር የሚበቃ፥ የማይሰክር፥ የማይጨቃጨቅ፣ ገር የሆነ፥ የማይከራከር፥ ገንዘብን የማይወድ፥ ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር)። አራተኛ፣ የማስተማር ችሎታ (ስጦታ) ሊኖረው ይገባል፡፡ (በቀጣዮቹ ቁጥሮች የተዘረዘሩት ዲያቆናት የማስተማር ችሎታ እንዲኖራቸው አይጠበቅባቸውም፡፡) ቲቶ 1:5-7፣ ለሽማግሌዎች ተመሳሳይ ዝርዝር ከማቅረቡ በተጨማሪ የሐሰት ትምህርትን የመገሰጽ ችሎታን በዝርዝሩ ውስጥ ያካትታል፡፡ ጴጥሮስ ለእነዚህ የቤተክርስቲያን መሪዎች ሲጽፍ ራሱን፣ “ሽማግሌ” ብሎ መጥራቱን ልብ ይበሉ (1ኛ ጴጥሮስ 5:1)፡፡

የቀድሞ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጥንታዊ ጽሑፎች፣ አስተማሪ መሪዎች (ኤጲስ ቆጶሳት) ቤተክርስቲያንን በበላይነት ለማገልገል ከዲያቆናት ጎን ሆነው ያገለግሉ እንደነበር የሚያረጋግጡ ይመስላል፡፡ የጥንት መረጃዎች የሆኑት የሮሜ ክሌመንት (Clement of Rome) እና ዲዳቼ (Didache)፣ ከመጀመሪያው ምዕተ-ዓመት መገባደጃ እስከ ሁለተኛው ምዕተ-ዓመት መጀመሪያ ድረስ፣ ኤጲስ ቆጶሳት እና ዲያቆናት የቤተክርስቲያን መሪዎች እንደነበሩ ይጠቅሳሉ፡፡

ከጊዜ በኋላ ግን፣ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጨማሪ የመሪነት ደረጃዎች (እርከኖች) ተካተዋል፡፡ በሂደትም፣ ኤጲስ ቆጶስ የሚለው ስያሜ ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን ለሚያስተዳድር ለክልል አብያተ ክርስቲያናት መሪ ጥቅም ላይ ይውል ጀመር፡፡ በ 325 ዓ.ም. በኒቂያ ጉባኤ ላይ እንደታየው፣ የእያንዳንዱ ከተማ ወይም አካባቢ የቤተ ክርስቲያን መሪ የክልሉን አብያተ ክርስቲያናት ይወክላል፡፡ እነዚህ መሪዎች “ኤጲስ ቆጶሳት” ተብለው ተጠርተዋል። ዛሬም በበርካታ አብያተ ክርስቲያኖች ዘንድ ይህ አጠቃቀም በስራ ላይ እየዋለ ይገኛል፡፡

ሆኖም፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በግልጽ የሚያሳየን፣ ሽማግሌዎች እና ዲያቆናት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትን እንደሚመሩ ነው፡፡ ሽማግሌው፣ ኤጲስ ቆጶስ ወይም መጋቢ በመባልም ይታወቃል፡፡ ይህ ገለጻ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሽማግሌዎች (ኤጲስ ቆጶሳት) እና ዲያቆናት የቀድሞዎቹ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች መሆናቸውን እንደሚገልጽ ከማሳየት አልፎ በአሁኑ ሰአት የሚታዩትን ሌሎች ተጨማሪ የቤተክርስቲያን አመራር ዘዴዎችን ስህተት አያደርግም፡፡ 

ምንጭ፦ https://www.gotquestions.org/

ትርጉም፦ አዳነው ዲሮ

3 thoughts on “የኤጲስ ቆጶስ፣ ሽማግሌ እና መጋቢ ልዩነት ምንድን ነው?”

  1. መጋቢ እና ሽማግሌ ኃላፊነታቸው እንደየቤ/ን ይለያያል፤ ለምሳሌ ሙሉወንጌል ፣ ቃለ ሕይወት ።
    ሙሉወንጌል በስነየር መጋቢ ትመራለች፡ ቃለሕይወት ደግሞ በሽማግሌዎች ትመራለች። የትኛው ነው ትክክል ?

    1. ወንድሜ ሰለሞን፣ አስቀድሜ ጥያቄህን ለዝግጅት ክፍላችን ስላደረስክ አመሰግናለው፡፡ ጥያቄህን ለመመለስ አስቀድሜ በጽሑፉ ማጠቃለያ ላይ ያለውን አንድ አንቀጽ ልዋስ፡፡ እንዲህ ይላል፣ “ይህ ገለጻ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ሽማግሌዎች (ኤጲስ ቆጶሳት) እና ዲያቆናት የቀድሞዎቹ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች መሆናቸውን እንደሚገልጽ ከማሳየት አልፎ በአሁኑ ሰአት የሚታዩትን ሌሎች ተጨማሪ የቤተክርስቲያን አመራር ዘዴዎችን ስህተት አያደርግም፡፡” ይላል፡፡ በዚህ አንቀጽ ውስጥ በግልጽ እንደሚታየው የጽሑፉ ዓላማ የቀድሞ ቤተ ክርስቲያን የአመራር ስርአት ምን እንደሚመስል ማሳየት እንጂ ከዚያ ውጪ ያሉ የአመራር ዘዴዎች ትክክል አለመሆናቸውን መናገር አይደለም፡፡ ስለዚህ የሙሉ ወንጌልም ሆነ የቃለ ሕይወት ወይም የሌላ አብያተ ክርስቲያናት የአመራር ዘይቤ በራሳቸው መልካም ወይም መጥፎ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ዋናው ቁም ነገር ያለው ያንን የአመራር ዘይቤ ለክርስቶስ ክብር በማዋሉ ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የልብ ጉዳይ ስለሆነ ፍርዱን ልብን ለሚያይ ለአምላክ እንተው፡፡

  2. ታዲያ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ እየታየ ያለው የቤ/ን አስተዳዳሪነት እንዴት ነው? ከፅሑፉ ጋር ብዙ የራቀ ጥያቄ አይደለም

Leave a Reply

%d