የእግዚአብሔር ሰላም ማለት ምን ማለት ነው? እንዴትስ ልለማመደው እችላለው?

የሰላም ዋጋ ተመን የላትም፡፡ ከሊቅ እስከ ደቂቁ፣ ከወጣት እስከ አዛውንቱ፣ አገራት፣ ፖለቲከኞች፣ ሁሉም ሰላምን ይሻሉ፣ ገንዘባቸው ለማድረግም የማይጓዙት መንገድ የማይቧጥጡት ዳገት አይኖርም፡፡ ሰላምን በሕዝቦች እና በአገራት መካከል ለማስፈን የሚደርግ የማያቋርጥ የጠርጴዛ ዙሪያ ውይይቶች የብዙሃን መገናኛ የፊት ገጾችን ከሚያጣብቡ ጉዳዮች መካከል ግንባር ቀደም ሁነቶች ናቸው፡፡ በቤተሰብ አባላት እና በጓደኞች መካከል ያለን ጠብ አጥፍቶ ሰላም ለማስፈን የሚደረገውም እልህ አስጨራሽ ትግል የዚሁ አካል ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ከራስ ውጪ ያሉ ጠበቦችና በዙሪያችን ለማግኘት የምንጥረው ሰላም ነው፡፡ ሰው ከራሱ እና ከፈጣሪው ጋር ሲጣላስ? ይህን ጊዜ ሰላምን እንዴት ይሻት? ቀደም ብሎ መመለስ ያለበት ዋናው ጥያቄም ይኧው ነው፡፡ ይህ ጽሑፍ ከራሳችን እና ከእግዚአብሔር ጋር ስለሚኖረን ሰላም ያወሳል፡፡ 

የፊልጵስዩስ መልዕክት 4:7 “አእምሮን ሁሉ ስለሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም” ይናገራል። አብዛኛዎቹ የጳውሎስ ደብዳቤዎች የሚጀመሩት፣ “ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናነት ይሁን”፣ በሚል መግቢያ ነው፡፡ ሰላም፣ በዙሪያችን ካሉ ሰላም አደፍራሽ ሁኔታዎች በላይ ከፍ ብሎ በመንፈስ ጸጥታና እርጋታ ውስጥ መሆን ማለት ነው። ሰላም የሚለው ቃል በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ የእግዚአብሔር ስጦታ እና የባሕሪው መገለጫ እንደሆነ ተገልጿል (1ኛ ተሰሎንቄ 5፤23፤ ገላትያ 6፤16፤ 1ኛ ጴጥሮስ 1፤2፣ ዕብ 13፤20)፡፡

እግዚአብሔር ሰላም ከሆነ፣ ይህን ሰላም የምናጣጥመውም እርሱን በማወቅ ውስጥ መሆን ይኖርበታል፡፡ ወደ እርሱ ይበልጥ በቀረብን መጠን የእርሱን ሰላም የበለጠ መለማመድ እንችላለን (ያዕቆብ 4፣8)። ወደ እርሱ እንዴት መቅረብ እንደምንችል ደግሞ እግዚአብሔር ግልጽ መመሪያዎችን ሰጥቶናል። መዝሙር 24፤3-4፣ “ወደ እግዚአብሔር ተራራ ማን ይወጣል? በቅድስናውስ ስፍራ ማን ይቆማል? እጆቹ የነጹ፥ ልቡም ንጹሕ የሆነ፥ ነፍሱን ለከንቱ ያላነሣ፥ ለባልንጀራውም በሽንገላ ያልማለ።” ይላል፡፡ ይህም ሆኖ፣ ወደ ጌታ መገኘት ለመቅረብ የሚያስችለን ከራሳችን የሚመነጭ ንጽህናም ሆነ መልካምነት እንደሌለን ቅዱሳት መጻሕፍት በግልፅ ይናገራሉ (ሮሜ 3:10፣ 23)፡፡ እውነታው እንዲያ ከሆነ፣ ታዲያ የእርሱን ሰላም ለመለማመድ እንዴት ወደ እርሱ መቅረብ እንችላለን? ኢየሱስ እንዲህ አለ፣ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፥ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም። ልባችሁ አይታወክ አይፍራም”(ዮሐንስ 14፣27)፡፡ ሰላሙን ወደምንለማመድበት ወደ እግዚአብሔር መገኘት መቅረብ የምንችለው በልጁ በኢየሱስ በኩል ብቻ ነው (ዮሐንስ 14፣6)፡፡ በኢየሱስ ሞትና ትንሳኤ በማመን የሃጢአታችንን ይቅርታ እንደተቀበልን ስንገነዘብ በእግዚአብሔር ፊት እንደ ጻድቃን እንቆጠራለን (2ኛ ቆሮንቶስ 5፣21)፡፡ ኢየሱስ የሃጢአታችንን ዋጋ ስለከፈለ ይቅርታን አግኝተናል፤ ከእግዚአብሔር ቁጣም ተርፈናል። ከእግዚአብሔር ጋር ሰላም ሊኖረን የሚችለውም በዚሁ አግባብ ብቻ ነው (ሮሜ 4፣5፤ 5፣1፣ 1 ዮሐንስ 4፣10)፡፡

በሕሊናችን መንጻት የምንለማመደው የእግዚአብሔር ሰላም እግዚአብሔርን ይበልጥ ባወቅነው መጠን እየሰፋና እየጠለቀ ይሄዳል (ዕብ 10፣22)። ሁለተኛ ጴጥሮስ 1፣2  (አ.መ.ት.) እንዲህ ይላል:- “እግዚአብሔርንና ጌታችን ኢየሱስን በማወቅ ጸጋና ሰላም ይብዛላችሁ።” እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ጥልቅና ምጡቅ ፍቅር መረዳት ስንጀምር (ኤፌ. 3 ፥18-19፤ ሮሜ 8፣38-39)፣ አዕምሮአችን እና መንፈሳችን በኃይሉ እና በጥበቡ ላይ ማረፍ ይጀምራሉ። ሁሉም ነገር ለጥቅማችን አንድ ላይ እንዲሠራ የሚያደርግ መሆኑንም እንገነዘባለን (ሮሜ 8፣28)። ዓላማዎቹም ያለምንም እንቅፋት ወደግባቸው እንደሚገሰግሱ እንረዳለን (መዝሙር 33:11፤ ምሳሌ 19:21፤ ኢሳ 45:9፤ 46:9-11)።

ሆኖም ግን፣ አንዳንድ አመለካከቶቻችን የእግዚአብሔርን ሰላም ሊያጠፉ ይችላሉ፡፡ ለአብነት፣ በእግዚአብሔር ላይ ስለታመንን ብቻ እግዚአብሔር የፈለግነውን ሁሉ እንደሚሰጠን ብናስብ ራሳችንን ለተስፋ መቁረጥና ሃዘን መጋበዛችን ይሆናል፤  መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን አያረጋግጥምና (2ኛ ቆሮንቶስ 12:7 እስከ 9፤ ዕብራውያን 11:13፤ መዝሙር 10:1)፡፡ መተማመን ማለት ምንም አይነት ነገር ቢከሰት፣ ልባችንን በእግዚአብሔር ሉአላዊነት ላይ ማሳረፍ ማለት ነው፡፡ ነገሮችን በራሳችን መንገድ ለመቆጣጠር ችክ ባልን ቁጥር የእግዚአብሔርን ሰላም መለማመዳችን ጥያቄ ውስጥ ይገባል፡፡ ከእምነት ይልቅ ጭንቀትን ስንመርጥም በሰላም መኖር አዳጋች ይሆናብናል፡፡ ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ስለ ፍርሃት እና ጭንቀት በትምሕርቶቹ አስጠንቅቆናል (ማቴዎስ 6፣34፣ ሉቃስ 12፣29፣ ፊልጵስዩስ 4፣6)። ጭንቀት የሰላም ጠላት ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚያስጨንቀንን ሁሉ በእርሱ ላይ እንድንጥል ያሳስበናል (1ኛ ጴጥሮስ 5፣7)፡፡

በሰላም መኖር፣ በጠዋት የፀሐይ ብርሃ መፈንጠቅን ተከትለው ከሚፈኩ የአበባ ቅጠሎች ጋር ተማስሎ አለው፡፡ የነፍሳችን የሰላም ቅጠሎች እግዚአብሔርን ይበልጥ እያወቅን በሄድን ቁጥር እየፈኩ ይሄዳሉ። እግዚአብሔርን እያወቅነው ስንመጣ በባሕሪው ታማኝ፣ መልካምነቱም እልቆ መሳፍርት እንደሆነ እየተረዳን እንሄዳለን፡፡ ስለ ተስፋዎቹ ይበልጥ እናሰላስላለን (መዝሙር 100፣5፣ 115፣11፤ ኢሳ 26፣4)። ለእኛ ባለው ጥልቅ ፍቅር ውስጥ መሰወር እንጀምራለን (ሮሜ 8፣38-39)። ፈጽሞ በማይለዋወጠው የእግዚአብሔር ባህርይ ላይ በመመካት፣ በየጊዜው የሚለዋወጡ ሁኔታዎች የእርካታችንን ደረጃ እንዳይወስኑ እንቅፋት እንሆናለን (ያዕቆብ 1፣17፤ ሚልክያስ 3፣6)፡፡

እግዚአብሔርን መጠጊያችን የማድረግን የአኗኗር ዘይቤ ስናዳብር፣ በእግዚአብሔር ሰላም መኖር እንግዳ ነገር አይሆንም (መዝሙር 46:1፣ 62:8)፡፡ መዝሙር 91:1-2 በእግዚአብሔር ሰላም የመኖር ምስጢርን ይዟል:- “በልዑል መጠጊያ የሚኖር ሁሉን በሚችል አምላክ ጥላ ውስጥ ያድራል። እግዚአብሔርን፦ አንተ መታመኛዬ ነህ እለዋለሁ፤ አምላኬና መሸሸጊያዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ።” በልባችን ውስጥ ያለው የእግዚአብሔር መጠጊያ (ምስጢራዊ ስፍራ) በመንፈሳችን ከእግዚአብሄር ጋር የምንገናኝበት ቦታ ነው፡፡ ከእርሱ ጋር በማያቋርጥ ህብረት ውስጥ በመሆን እዚያ ስፍራ ላይ ለመኖርና በእርሱ ጥላ ስር ለማደር ስንመርጥ፣ ሁኔታዎች እንዳሰብናቸው ባይሄዱም እንኳን ሰላማችን እንደማያቋርጥ ወንዝ በልባችን ውስጥ መፍሰሱን ይቀጥላል፡፡ በችግሮቻችን ወቅቶች አይኖቻችንን ከችግሮቹ ላይ አንስተን ወደ ሰላም አምላክ መጮኽን ስንለማመድ፣ ሰላሙ በእርግጥም ከአእምሮአችን በላይ መሆኑን በተግባር በሕይወታችን ማረጋገጥ እንጀምራለን (ፊልጵስዩስ 4፣7)።

ጸሃፊ፣ አዳነው ዲሮ

Leave a Reply

%d bloggers like this: